የአምላክን ቃል ለማስተማር በሚገባ የታጠቁ
“[አምላክ] . . . አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አደረገን።”—2 ቆሮንቶስ 3:6 አ.መ.ት
1, 2. አንዳንድ ጊዜ ለስብከት ምን ዓይነት ጥረት ሲደረግ እንመለከታለን? ሆኖም የሚደረገው ጥረት በአብዛኛው ሳይሳካ የሚቀረው ለምንድን ነው?
ለመሥራት ብቃቱ ሳይኖርህ አንድ ሥራ ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? እስቲ አስበው:- ለሥራው የሚያስፈልጉህ ቁሳቁሶች በሙሉ ቀርበውልሃል፤ መሣሪያዎቹም ተዘጋጅተዋል። አንተ ግን ሥራው እንዴት እንደሚሠራ አታውቅም። ይባስ ብሎ ደግሞ ሥራው በጣም አጣዳፊ ነው። ሰዎች ተስፋቸውን የጣሉት በአንተ ላይ ነው። ምንኛ የሚያበሳጭ ነው!
2 እንዲህ ያለው ሁኔታ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል የፈጠራ ሐሳብ አይደለም። አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ተደራጅተው ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ለማገልገል ሙከራ አድርገዋል። እነዚህ ሙከራዎች ብዙውን ጊዜ ሳምንት ወይም ወር ሳያስቆጥሩ ወዲያው ይቆማሉ። ለምን? ሕዝበ ክርስትና ተከታዮቿ ለዚህ ሥራ ብቁ እንዲሆኑ አልረዳቻቸውም። ቀሳውስትዋ በዓለማዊ ትምህርት ቤቶችና በሃይማኖታዊ ማሠልጠኛዎች ለበርካታ ዓመታት የተማሩ ቢሆኑም ይህ የስብከት ሥራ የሚጠይቀውን ብቃት አላገኙም። እንዲህ ልንል የምንችለው ለምንድን ነው?
3. በ2 ቆሮንቶስ 3:5, 6 ላይ ሦስት ጊዜ የተጠቀሰው ቃል ምንድን ነው? ትርጉሙስ?
3 የአምላክ ቃል፣ አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የምሥራች ሰባኪ የመሆን ብቃቱን እንዴት እንደሚያገኝ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፣ በራሳችን ብቃት ከእኛ ነው የምንለው አንዳች ነገር የለንም። እርሱም . . . አገልጋዮች እንድንሆን ብቁዎች አደረገን።” (2 ቆሮንቶስ 3:5, 6 አ.መ.ት ) ሦስት ጊዜ የተጠቀሰውን ‘ብቁ’ የሚለውን ቃል ልብ በል። ምን ማለት ነው? ቫይንስ ኤክስፖዚቶሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ቢብሊካል ዎርድስ እንዲህ ይላል:- “[የግሪክኛው ቃል] ስለ ነገሮች ሲናገር ‘በቂ’. . . ስለ ሰዎች ሲናገር ደግሞ ‘ምሉዕ፣ የሚገባው’ የሚል ትርጉም ያስተላልፋል።” ስለዚህ “ብቁ” የሆነ አንድ ሰው የተሰጠውን ሥራ ለማከናወን ምሉዕ እና “የሚገባው” ይሆናል። አዎን፣ እውነተኛ የምሥራቹ አገልጋዮች ይህን ሥራ ለማከናወን ብቃት አላቸው። ለመስበክ ምሉዓን፣ የሚመጥኑ ወይም የሚገቡ ናቸው።
4. (ሀ) ለክርስቲያን አገልግሎት ብቁ የሚሆኑት የተመረጡ ጥቂት ሰዎች ብቻ እንዳልሆኑ የጳውሎስ ምሳሌ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለአገልጋይነት ብቁ እንድንሆን የሚጠቀምባቸው ሦስቱ መሣሪያዎች ምንድን ናቸው?
4 ይሁን እንጂ ይህ ብቃት የሚገኘው ከየት ነው? ከግል ተሰጥኦ? በጣም ከፍተኛ ከሆነ የማስተዋል ችሎታ? በጣም እውቅ በሆኑ ትምህርት ቤቶች ከሚሰጥ ልዩ ሥልጠና? ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ ሁሉ ነበሩት። (ሥራ 22:3፤ ፊልጵስዩስ 3:4, 5) ሆኖም ራሱን ዝቅ በማድረግ አገልጋይ የመሆን ብቃቱን ያገኘው ከከፍተኛ ትምህርት ሳይሆን ከይሖዋ አምላክ እንደሆነ አምኗል። ይህ ብቃት ለጥቂት የተመረጡ ሰዎች ብቻ የተወሰነ ነው? ጳውሎስ “ብቃታችን” በማለት ለቆሮንቶስ ጉባኤ ጽፏል። ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ በሙሉ የመደበላቸውን ሥራ እንዲያከናውኑ የሚያስፈልጋቸውን ችሎታና ብቃት እንደሚሰጣቸው ይህ ማረጋገጫ ይሰጣል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ እውነተኛ ክርስቲያኖች ብቁ እንዲሆኑ የሚያደርገው እንዴት ነው? የሚጠቀምባቸውን ሦስት መሣሪያዎች እንመልከት:- (1) ቃሉ፣ (2) ቅዱስ መንፈሱ እና (3) ምድራዊ ድርጅቱ ናቸው።
የይሖዋ ቃል ብቁ ያደርገናል
5, 6. ቅዱሳን ጽሑፎች በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራሉ?
5 በመጀመሪያ የአምላክ ቃል ለአገልጋይነት የሚያበቃን እንዴት ነው? ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 አ.መ.ት ) ስለዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች ለሰዎች የአምላክን ቃል የማስተማርን “መልካም ሥራ” እንድናከናውን የታጠቅንና “ብቁ” እንድንሆን ይረዱናል። የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባሎችስ? እነርሱም መጽሐፍ ቅዱስ አላቸው። ይኸው አንድ መጽሐፍ አንዳንድ ሰዎችን ብቁ አገልጋዮች እንዲሆኑ ሲረዳ ሌሎቹን ሊረዳ ያልቻለው ለምንድን ነው? የምናገኘው እገዛ ለመጽሐፍ ቅዱስ ባለን ዝንባሌ ላይ የተመካ ነው።
6 በዛሬው ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ በርካታ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት “በእውነት እንዳለ . . . እንደ እግዚአብሔር ቃል” አድርገው የሚቀበሉት አለመሆናቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። (1 ተሰሎንቄ 2:13) ሕዝበ ክርስትና በዚህ ረገድ ያስመዘገበችው ታሪክ በጣም የሚያሳፍር ነው። ቀሳውስቱ ለዓመታት በሃይማኖታዊ የሥልጠና ተቋማት ሲማሩ ከቆዩ በኋላ የአምላክን ቃል ለማስተማር ብቁዎች ይሆናሉን? በፍጹም አይሆኑም። ትምህርታቸውን ከመጀመራቸው በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች የነበሩ አንዳንድ ተማሪዎች ሲመረቁ ተጠራጣሪዎች ሆነዋል! ከዚያ በኋላ የማያምኑበትን የአምላክ ቃል ከመስበክ ይልቅ በፖለቲካዊ ውዝግቦች ተሰልፈው ማኅበራዊ ወንጌል በማስፋፋት ወይም በዓለማዊ ፍልስፍናዎች ላይ የተመሠረቱ ስብከቶች በማሰማት አገልግሎታቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ዘወር ያደርጋሉ። (2 ጢሞቴዎስ 4:3) በተቃራኒው ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ይከተላሉ።
7, 8. ኢየሱስ ለአምላክ ቃል የነበረው አመለካከት ከዘመኑ የሃይማኖት መሪዎች የተለየ የነበረው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች አስተሳሰቡን እንዲቀርጹበት አልፈቀደም። እንደ ሐዋርያቱ ያሉ ጥቂት ሰዎችንም ሆነ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች በሚያስተምርበት ጊዜ በቅዱሳን ጽሑፎች በሚገባ ተጠቅሟል። (ማቴዎስ 13:10-17፤ 15:1-11) ይህ አድራጎቱ በዘመኑ ከነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች የተለየ እንዲሆን አድርጎታል። ተራ ሰዎች የአምላክን ጥልቅ ነገሮች እንዳይመረምሩ አጥብቀው ያከላክሉ ነበር። እንዲያውም የዚያ ዘመን አስተማሪዎች አንዳንድ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች ጥልቅ ከመሆናቸው የተነሳ በጣም ለሚያቀርቧቸው ተማሪዎቻቸው፣ ያውም ድምፃቸውን ዝቅ አድርገውና ራሳቸውን ተሸፋፍነው ካልሆነ በቀር ለሌላ ለማንም ማወያየት እንደሌለባቸው አድርገው ያስቡ ነበር! እነዚህ ሃይማኖታዊ መሪዎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በማብራራት ረገድ የያዙት አቋም የአምላክን ስም ስለ መጥራት ከነበራቸው አጉል እምነት ያልተለየ ነበር።
8 ኢየሱስ ግን እንዲህ አልነበረም። ጥቂት የተመረጡ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሰዎች ‘ከይሖዋ አፍ የሚወጣውን ቃል ሁሉ’ ማወቅ እንደሚያስፈልጋቸው ያምን ነበር። ኢየሱስ የእውቀትን ቁልፍ ለጥቂት የተመረጡ የቅዱሳን ጽሑፎች ምሁራን ብቻ የማስጨበጥ ፍላጎት አልነበረውም። ለደቀ መዛሙርቱ “በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 4:4፤ 10:27) ኢየሱስ የአምላክን እውቀት በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማካፈል ልባዊ ፍላጎት ነበረው።
9. እውነተኛ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ይመለከቱታል?
9 የአምላክ ቃል የትምህርታችን ዋነኛ መሠረት መሆን አለበት። ለምሳሌ ያህል በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ንግግር በምናቀርብበት ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ የተመረጡ ጥቅሶችን ማንበቡ ብቻውን አይበቃም። ጥቅሶቹን ማብራራት፣ በምሳሌ ማስረዳትና የተጠቀሰበትን ዓላማ ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ከተጻፈበት ወረቀት አንስተን በአድማጮቻችን ልብ ውስጥ ጠልቆ እንዲገባ ማድረግ ነው። (ነህምያ 8:8, 12) በተጨማሪም ምክር ወይም የእርማት ተግሣጽ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀም ይገባል። የይሖዋ ሕዝቦች የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ቢሆኑም እንኳ ሁሉም የመጻሕፍት ሁሉ መጽሐፍ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ያከብራሉ።
10. በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በእኛ ላይ ምን ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል?
10 የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ይህን በመሰለ አክብሮት ስንጠቀምበት ኃይል ይኖረዋል። (ዕብራውያን 4:12) መልእክቱ እንደ ዝሙት፣ ምንዝር፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሰካራምነትና ስርቆት ከመሰሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ አድራጎቶች እንዲርቁ በማድረግ በሕይወታቸው ላይ ለውጦች እንዲያደርጉ ሰዎችን ያንቀሳቅሳቸዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አሮጌውን ሰው አውልቀው አዲሱን ሰው እንዲለብሱ ረድቷቸዋል። (ኤፌሶን 4:20-24) አዎን፣ ከማንኛውም ሰብዓዊ አስተሳሰብና ወግ በላይ አክብሮት ሰጥተን በታማኝነት ከተጠቀምንበት መጽሐፍ ቅዱስ ምሉዓንና በደንብ የታጠቅን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንድንሆን ሊረዳን ይችላል።
የይሖዋ መንፈስ ብቁ ያደርገናል
11. የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ “ረዳት” እንደሆነ መገለጹ ትክክል የሆነው ለምንድን ነው?
11 በሁለተኛ ደረጃ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል በሚገባ የታጠቅን እንድንሆን በማስቻል ረገድ የሚጫወተውን ሚና እንመልከት። የይሖዋ መንፈስ አቻ የማይገኝለት ብርቱ ኃይል እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ይሖዋ ተወዳጅ ልጁ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ ጥቅም በሚያስገኝ ሁኔታ በዚህ አስደናቂ ኃይል እንዲጠቀም ሥልጣን ሰጥቶታል። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን “ረዳት” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 16:7 NW ) ተከታዮቹም ይህን መንፈስ እንዲሰጣቸው ይሖዋን እንዲጠይቁ ከማሳሰቡም ሌላ ይሖዋም በልግስና እንደሚሰጣቸው አረጋግጦላቸዋል።—ሉቃስ 11:10-13፤ ያዕቆብ 1:17
12, 13. (ሀ) በአገልግሎታችን እንዲያግዘን መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ፈሪሳውያን መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ይሠራ እንዳልነበር ያሳዩት እንዴት ነው?
12 በየቀኑ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት በተለይም በአገልግሎታችን እንዲረዳን መጸለይ ያስፈልገናል። ይህ አንቀሳቃሽ ኃይል በእኛ ላይ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል? በአእምሯችንና በልባችን ላይ ተጽዕኖ በማሳደር እንድንለወጥ፣ እንድንጎለምስና አሮጌውን ሰው በአዲሱ ሰው እንድንተካ ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:9, 10) ውድ የሆኑ የክርስቶስን መሰል ባሕርያት እንድንለብስ ያግዘናል። ብዙዎቻችን ገላትያ 5:22, 23ን በቃላችን ማለት እንችላለን። ይህ ጥቅስ የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ይዘረዝራል። የመጀመሪያው ፍቅር ነው። ፍቅር ደግሞ ለአገልግሎታችን የግድ አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው። ለምን?
13 ፍቅር ለተግባር የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ኃይል ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ለይሖዋና ለሰው ልጆች ያላቸው ፍቅር ምሥራቹን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ይገፋፋቸዋል። (ማርቆስ 12:28-31) ይህ ዓይነቱ ፍቅር ከሌለን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች የመሆን ብቃት ሊኖረን አይችልም። በኢየሱስና በፈሪሳውያን መካከል የነበረውን ልዩነት ልብ በል። ማቴዎስ 9:36 ስለ ኢየሱስ እንዲህ ይላል:- “ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፣ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።” ፈሪሳውያን ለተራው ሕዝብ ምን ዓይነት አመለካከት ነበራቸው? “ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው” ብለዋል። (ዮሐንስ 7:49፤ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) ፈሪሳውያኑ ለሕዝቡ ምንም ዓይነት ፍቅር አልነበራቸውም። ከዚያ ይልቅ ይንቋቸው ነበር። የይሖዋ መንፈስ በውስጣቸው ይሠራ እንዳልነበረ ግልጽ ነው።
14. ኢየሱስ በአገልግሎቱ ፍቅር በማሳየት ረገድ የተወው ምሳሌ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
14 ኢየሱስ ለሕዝቡ ያዝን ነበር። ሥቃያቸውና ችግራቸው ተሰምቶታል። እረኛ እንደሌላቸው በጎች ግፍ እንደተፈጸመባቸው፣ እንደተጨነቁና እንደተጣሉ አስተውሎ ነበር። ዮሐንስ 2:25 “በሰው ያለውን ያውቅ ነበር” በማለት ይነግረናል። ኢየሱስ በፍጥረት ጊዜ የይሖዋ ዋና ሠራተኛ ስለነበር የሰው ልጆችን ተፈጥሮ በጥልቀት መገንዘብ ይችል ነበር። (ምሳሌ 8:30, 31) ይህ ግንዛቤው ፍቅሩን የጠለቀ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ፍቅር እኛንም ለስብከቱ ሥራ የሚያነሳሳን ይሁን! በዚህ ረገድ መሻሻል እንደሚያስፈልገን ከተሰማን ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጠን እንጸልይ እንዲሁም ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ ተግባር እንፈጽም። ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ይሰጠናል። ይሖዋ ምንም ነገር ሊቋቋመው የማይችለውን ይህን ኃይል በመላክ ምሥራቹን ከሁሉ በላቀ ብቃት ያከናወነውን ክርስቶስን እንድንመስል ይረዳናል።
15. ኢሳይያስ 61:1-3 ላይ የሠፈሩት ቃላት በኢየሱስ ላይ የሚሠሩትና ጻፎችንና ፈሪሳውያንን የሚያጋልጡት እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ብቃቱን ያገኘው ከየት ነው? “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው” ብሏል። (ሉቃስ 4:17-21) አዎን፣ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ኢየሱስን የሾመው ይሖዋ ራሱ ነው። ኢየሱስ ሌላ ተጨማሪ ማረጋገጫ ማግኘት አላስፈለገውም። በዘመኑ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ነበሩ? አልነበሩም። ኢየሱስ ጮክ ብሎ ያነበበውንና በእርሱ ላይ እንደሚሠራ የተናገረውን ኢሳይያስ 61:1-3ን የመፈጸም ብቃትም አልነበራቸውም። እባክህን ይህን ጥቅስ አንብብና ግብዞቹ ጻፎችና ፈሪሳውያን ይህን ብቃት የማያሟሉ እንደነበሩ ራስህ ተመልከት። ለድሆች የሚናገሩት ምንም ዓይነት ምሥራች አልነበራቸውም። ታዲያ ለታሠሩ መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን እንዴት ሊሰብኩ ይችላሉ? በመንፈሳዊ ሁኔታ እነርሱ ራሳቸው የታወሩና በሰው ሠራሽ ወጎች የተተበተቡ ነበሩ! እኛስ ከፈሪሳውያን በተለየ ሁኔታ ሰዎችን ለማስተማር ብቃቱ አለንን?
16. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ለአገልጋይነት ያላቸውን ብቃት በተመለከተ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይችላሉ?
16 እርግጥ ነው፣ ከፍተኛ ትምህርት በሚሰጥባቸው የሕዝበ ክርስትና ትምህርት ቤቶች ገብተን አልተማርንም። ከሃይማኖታዊ ማሠልጠኛ ተቋም ያገኘነው የመምህርነት ሹመት የለንም። ታዲያ ብቃት ይጎድለናል ማለት ነው? በፍጹም! የእርሱ ምሥክሮች እንድንሆን የሾመን ይሖዋ ነው። (ኢሳይያስ 43:10-12) መንፈሱን እንዲሰጠን ብንጸልይና ከጸሎታችን ጋር የሚስማማ ተግባር ብንፈጽም ከሁሉ የላቀ ብቃት እናገኛለን። ፍጹማን አለመሆናችንና ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ የተወልንን ምሳሌ በተሟላ መንገድ መከተል አለመቻላችን የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ይሖዋ መንፈሱን በመጠቀም የቃሉ አስተማሪዎች እንድንሆን ብቁ ስላደረገንና ስላስታጠቀን አመስጋኞች አይደለንም?
የይሖዋ ድርጅት ብቁ ያደርገናል
17-19. የይሖዋ ድርጅት የሚያዘጋጃቸው በየሳምንቱ የሚካሄዱት አምስቱ ስብሰባዎች ብቁ አገልጋይ እንድንሆን የሚረዱን እንዴት ነው?
17 በመጨረሻ ይሖዋ የቃሉ አስተማሪዎች የመሆን ብቃት እንድናገኝ የሚጠቀምበትን ሦስተኛ መሣሪያ ማለትም ምድራዊ ድርጅቱን እንመልከት። ምድራዊ ድርጅቱ አገልጋዮች እንድንሆን ያሠለጥነናል። እንዴት? እስቲ የሚቀርቡልንን የትምህርት ፕሮግራሞች አስብ! በአንድ ሳምንት ብቻ በአምስት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንገኛለን። (ዕብራውያን 10:24, 25) በጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት አነስ ባሉ ቡድኖች ተከፋፍለን የይሖዋ ድርጅት አዘጋጅቶ በሚያቀርብልን መጽሐፍ አማካኝነት ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እናደርጋለን። በማዳመጥና ሐሳብ በመስጠት እንማራለን እንዲሁም እርስ በርሳችን እንጽናናለን። በተጨማሪም ከመጽሐፍ ጥናቱ የበላይ ተመልካች የቅርብ ክትትልና መመሪያ እናገኛለን። በሕዝብ ስብሰባና በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ተጨማሪ የበለጸገ መንፈሳዊ ምግብ እናገኛለን።
18 ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤታችን እንዴት ማስተማር እንደምንችል ሥልጠና እንድናገኝበት ሆኖ የተዘጋጀ ነው። የተማሪ ንግግሮችን ስንዘጋጅ የአምላክን ቃል በመጠቀም በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትምህርት መስጠት የምንችልበትን መንገድ እንማራለን። (1 ጴጥሮስ 3:15) በሚገባ የምታውቁት መስሏችሁ በኋላ ግን ስትዘጋጁት አዲስ ነገር የተማራችሁበት ክፍል ተሰጥቷችሁ አያውቅም? ይህ የብዙዎች ገጠመኝ ነው። አንድን ርዕሰ ጉዳይ ለሌሎች የማስተማርን ያህል ስለዚያ ርዕሰ ጉዳይ ያለንን እውቀት የሚያሳድግ ነገር የለም። ራሳችን የምናቀርበው ክፍል ባልተሰጠን ጊዜም እንኳን የተሻልን አስተማሪዎች ለመሆን የሚያበቃን ትምህርት እናገኛለን። በእያንዳንዱ ተማሪ ላይ አንዳንድ ጥሩ ባሕርያት ለማስተዋል ስለምንችል እነዚህን ባሕርያት እንዴት ልንኮርጅ እንደምንችል እናስባለን።
19 የአገልግሎት ስብሰባም ቢሆን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንድንሆን ያስታጥቀናል። በየሳምንቱ በአገልግሎታችን ላይ ያተኮሩ ሕያው ንግግሮች፣ ውይይቶችና ሠርቶ ማሳያዎች ይቀርባሉ። እንዴት ዓይነት አቀራረብ እንጠቀም? በአገልግሎት ክልላችን የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት እንወጣ? ይበልጥ ትኩረት ልንሰጣቸው የሚገቡ ምን ዓይነት የስብከት መስኮች አሉ? ተመላልሶ መጠየቅ በምናደርግበትና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምንመራበት ጊዜ ይበልጥ ፍሬያማ አስተማሪዎች እንድንሆን የሚረዳን ምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 9:19-22) እነዚህና እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎች በአገልግሎት ስብሰባዎች ላይ በዝርዝር ውይይት ይደረግባቸዋል። ብዙዎቹ የስብሰባው ክፍሎች በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይህ ጽሑፍ አስፈላጊ ለሆነው ሥራችን እኛን ለማስታጠቅ የሚዘጋጅ ሌላ መሣሪያ ነው።
20. ከጉባኤና ከትላልቅ ስብሰባዎች የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
20 በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ ተዘጋጅተን በመገኘትና ያገኘናቸውን ትምህርቶች በማስተማር ሥራችን ላይ በመጠቀም ተጨማሪ ሰፊ ሥልጠና እናገኛለን። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አያበቃም። እንደ ወረዳና የልዩ ስብሰባ እንዲሁም እንደ አውራጃ ስብሰባ ያሉ ትላልቅ ስብሰባዎችም አሉ። እነዚህም የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንድንሆን ያስታጥቁናል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ በጥሞና ለማዳመጥና ያዳመጥናቸውንም በሥራ ላይ ለማዋል እንጓጓለን!—ሉቃስ 8:18
21. ያገኘነው ሥልጠና ውጤት እንዳስገኘ የሚያሳየው ማረጋገጫ ምንድን ነው? ለዚህ ሁሉ የሚመሰገነው ማን ነው?
21 ታዲያ ይሖዋ ያዘጋጀው ሥልጠና ውጤት አስገኝቷል? የተገኘው ውጤት ራሱ ይመስክር። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረተ ትምህርቶችን እንዲማሩና አምላክ ከሚፈልግባቸው ብቃቶች ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ እርዳታ ያገኛሉ። ቁጥራችን እያደገ ነው። ለዚህ ግን የሚመሰገነው ማንም ግለሰብ አይደለም። በዚህ ረገድ የኢየሱስን የመሰለ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” ብሏል። አብዛኞቻችን እንደ ጥንቶቹ ሐዋርያት ያልተማርንና ተራ ሰዎች ነን። (ዮሐንስ 6:44፤ ሥራ 4:13) የተሳካ ውጤት ማግኘታችን የተመካው ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ እውነት በሚስበው በይሖዋ ላይ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር” በማለት በጥሩ ሁኔታ አስቀምጦታል።—1 ቆሮንቶስ 3:6
22. በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ረገድ ከመጠን በላይ ተስፋ ልንቆርጥ የማይገባን ለምንድን ነው?
22 አዎን፣ ይሖዋ አምላክ የቃሉ አስተማሪዎች በመሆን ለምናከናውነው ሥራ ሙሉ ድጋፍ ይሰጣል። ለማስተማር እንደምንበቃ ሆኖ የማይሰማን ጊዜ ይኖር ይሆናል። ሰዎችን ወደ ራሱና ወደ ልጁ የሚስበው ይሖዋ መሆኑን አስታውስ። በቃሉ፣ በቅዱስ መንፈሱና በምድራዊ ድርጅቱ አማካኝነት አዲሶችን እንድናገለግል ብቃት የሚሰጠን ይሖዋ ነው። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ የታጠቅን የአምላክ ቃል አስተማሪዎች እንድንሆን ያዘጋጀልንን መልካም ነገሮች በመጠቀም የይሖዋን ማሠልጠኛ የምንቀበል እንሁን!
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• መጽሐፍ ቅዱስ ለስብከቱ ሥራ የሚያስታጥቀን እንዴት ነው?
• ለአገልጋይነት ብቁ እንድንሆን በመርዳት ረገድ መንፈስ ቅዱስ ምን ሚና ይጫወታል?
• ብቃት ያለህ የምሥራቹ ሰባኪ እንድትሆን የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት በምን መንገዶች ረድቶሃል?
• በአገልግሎት በምንሳተፍበት ጊዜ ትምክህት ሊኖረን የሚችለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ ቃል አስተማሪ የነበረው ኢየሱስ ለሰዎች ፍቅር አሳይቷል