በመንፈስ በመመላለስ ራስህን ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ ኑር
“በመንፈስ መመላለሳችሁን ቀጥሉ . . . እንዲህ ካደረጋችሁ የሥጋን ምኞት ከቶ አትፈጽሙም።”—ገላ. 5:16
1. በጴንጤቆስጤ ዕለት ምን ዓይነት ጥምቀት ተከናወነ?
በ33 ዓ.ም. በጴንጤቆስጤ ዕለት የኢየሱስ ተከታዮች በልሳን ተናግረው ነበር፤ ይህን ማድረግ የቻሉት በመንፈስ ቅዱስ ከተጠመቁ በኋላ ነው። በዚያን ወቅት ተአምራዊ የመንፈስ ስጦታ እንደተቀበሉ የሚያሳይ ነገር አከናውነዋል። (1 ቆሮ. 12:4-10) ይህ ስጦታ እንዲሁም የሐዋርያው ጴጥሮስ ንግግር ምን ውጤት አስገኘ? በርካታ ሰዎች ‘ልባቸው እጅግ ተነካ።’ እነዚህ ሰዎች ጴጥሮስ በሰጠው ማበረታቻ መሠረት ንስሐ ገብተው ተጠመቁ። የታሪክ ዘገባው “ቃሉን ከልባቸው የተቀበሉ ተጠመቁ፤ በዚያም ቀን ሦስት ሺህ ገደማ የሚሆኑ ነፍሳት ተጨመሩ” ይላል። (ሥራ 2:22, 36-41) ኢየሱስ ባዘዘው መሠረት እነዚህ ሰዎች በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ተጠምቀው መሆን አለበት።—ማቴ. 28:19
2, 3. (ሀ) በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅና በመንፈስ ቅዱስ ስም በመጠመቅ መካከል ያለውን ልዩነት ግለጽ። (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሁሉ በውኃ እንዲጠመቁ የሚጠበቅባቸው ለምንድን ነው?
2 ይሁን እንጂ በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅና በመንፈስ ቅዱስ ስም በመጠመቅ መካከል ልዩነት አለ? አዎን አለ። በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁ ሰዎች የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች በመሆን እንደገና ይወለዳሉ። (ዮሐ. 3:3) እነዚህ ሰዎች ወደፊት በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ተባባሪ ነገሥታትና የበታች ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ ስለተቀቡ የክርስቶስ መንፈሳዊ አካል ክፍል ሆነዋል። (1 ቆሮ. 12:13፤ ገላ. 3:27፤ ራእይ 20:6) በመሆኑም ይሖዋ በጴንጤቆስጤ ዕለትና ከዚያ በኋላ ይህን ጥምቀት ማለትም በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅን ያከናወነው ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን ግለሰቦች ለመምረጥ ሲል ነው። (ሮም 8:15-17) ይሁንና በዘመናችን የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች በየጊዜው በሚያደርጓቸው ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ሰዎችን በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ ያጠምቃሉ፤ ታዲያ ስለዚህ ጥምቀትስ ምን ማለት ይቻላል?
3 የውኃ ጥምቀት እውነተኛ ክርስቲያኖች ያለምንም ገደብ ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ መወሰናቸውን ለማሳየት የሚወስዱት እርምጃ ነው። ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ክርስቲያኖችም ይህን እርምጃ ወስደዋል። ሆኖም የውኃ ጥምቀት በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በዘመናችን የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶችና ሴቶችም ሊወስዱት የሚገባ አስፈላጊ እርምጃ ነው። አንድ ሰው ተስፋው ምንም ይሁን ምን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም በውኃ መጠመቅ ሊወስደው የሚገባ አስፈላጊ እርምጃ ነው። በዚህ መንገድ የተጠመቁ ክርስቲያኖች በሙሉ ‘በመንፈስ መመላለሳቸውን መቀጠል’ ይኖርባቸዋል። (ገላትያ 5:16ን አንብብ።) አንተስ በመንፈስ በመመላለስ ራስህን ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ እየኖርክ ነው?
‘በመንፈስ መመላለስ’ ሲባል ምን ማለት ነው?
4. ‘በመንፈስ መመላለስ” ሲባል ምን ማለት ነው?
4 ‘በመንፈስ መመላለስ’ ሲባል መንፈስ ቅዱስ በውስጥህ እንዲሠራ ይኸውም በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብህ መፍቀድ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር በዕለታዊ እንቅስቃሴህ በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ ትመራለህ ማለት ነው። በገላትያ ምዕራፍ 5 ላይ በመንፈስ በመመራትና በሥጋ ፍላጎት በመመራት መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ተቀምጧል።—ገላትያ 5:17, 18ን አንብብ።
5. መንፈስ ቅዱስ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር መፍቀድ ከየትኞቹ ሥራዎች መራቅን ይጨምራል?
5 መንፈስ ቅዱስ በአንተ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር የምትፈቅድ ከሆነ ከሥጋ ሥራዎች ለመራቅ ጥረት ታደርጋለህ። (ገላ. 5:19-21) ከእነዚህ የሥጋ ሥራዎች መካከል “ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ብልግና፣ ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊት፣ ጠላትነት፣ ጠብ፣ ቅናት፣ በቁጣ መገንፈል፣ የከረረ ጭቅጭቅ፣ መከፋፈል፣ መናፍቅነት፣ ምቀኝነት፣ ሰካራምነት፣ መረን የለቀቀ ፈንጠዝያ” ይገኙበታል። (ገላ. 5:19-21) በሌላ አባባል ‘ሰውነትህ ዘወትር የሚፈጽመውን ሥራ በመንፈስ ገድለሃል’ ማለት ነው። (ሮም 8:5, 13) እንዲህ ማድረግህ ለሥጋዊ ምኞት ከመሸነፍ ይልቅ አእምሮህ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ብሎም መንፈሱ የሚሰጥህን አመራር እንድትቀበል ይረዳሃል።
6. የመንፈስን ፍሬ ለማፍራት ምን እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
6 መንፈስ ቅዱስ በአንተ ውስጥ የሚሠራ ከሆነ ግሩም ባሕርያትን ይኸውም ‘የመንፈስን ፍሬ’ ታፈራለህ። (ገላ. 5:22, 23) ይሁንና የመንፈስን ፍሬ ማፍራት ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅብህ ሳትገነዘብ አትቀርም። አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ገበሬ ማሳውን ያለማል። እርግጥ ነው፣ ገበሬው የዘራው ነገር ምርት እንዲሰጥ የፀሐይ ብርሃንና ውኃ ያስፈልጋል፤ እነዚህ ነገሮች ከሌሉ ምርት አገኛለሁ ብሎ ሊጠብቅ አይችልም። መንፈስ ቅዱስን ከፀሐይ ብርሃን ጋር ማመሳሰል እንችላለን። እኛም የመንፈስን ፍሬ ለማፍራት መንፈስ ቅዱስ ያስፈልገናል። ሆኖም አንድ ገበሬ ተግቶ ካልሠራ እንዴት ምርት ሊያገኝ ይችላል? (ምሳሌ 10:4) አዎን፣ በአፈር የተመሰለውን ልብህን የምትኮተኩትበት መንገድ በውስጥህ በምታፈራው የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ጥራትና ብዛት ላይ ልዩነት ያመጣል። በመሆኑም ‘ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የሚስማማ ተግባር በመፈጸም መንፈሱ በውስጤ እንዲያፈራ እያደረግሁ ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ።
7. የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ለማፍራት ከፈለክ ማጥናትህና ማሰላሰልህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 በተጨማሪም ገበሬዎች ጥሩ ምርት ለማግኘት ሰብላቸውን ውኃ ማጠጣት ያስፈልጋቸዋል። አንተም የመንፈስን ፍሬ ለማፍራት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውንና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት የሚቀርበውን የእውነት ውኃ መጠጣት ያስፈልግሃል። (ኢሳ. 55:1) ቅዱሳን መጻሕፍት የመንፈስ ቅዱስ ውጤት እንደሆኑ ለብዙ ሰዎች ተናግረህ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞ. 3:16) በተጨማሪም ታማኝና ልባም ባሪያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውንና በንጹሕ ውኃ የተመሰለውን እውነት እንድንረዳ አስፈላጊውን ማስተዋል ይሰጠናል። (ማቴ. 24:45-47) ነጥቡ ግልጽ ነው። መንፈስ ቅዱስ በእኛ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር የአምላክን ቃል ማንበብና ማሰላሰል ይኖርብናል። አንተም እንዲህ እያደረግህ ከሆነ ስለተሰጣቸው መረጃ “ትጋት የተሞላበት ምርምርና ጥልቅ ጥናት” አድርገው የነበሩ ነቢያትን ግሩም ምሳሌ እየተከተልክ ነው። መላእክት እንኳ ተስፋ ስለተደረገበት ዘርና ስለ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ የሚናገረውን መንፈሳዊ እውነት ለመረዳት ከፍተኛ ፍላጎት አድሮባቸው የነበረ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።—1 ጴጥሮስ 1:10-12ን አንብብ።
መንፈስ ቅዱስ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
8. ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጥህ መጠየቅህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ቅዱሳን መጻሕፍትን ስላነበብክና ስላሰላሰልክ ብቻ መንፈስ ቅዱስ በአንተ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል ማለት አይደለም። የይሖዋን እርዳታና አመራር ለማግኘት ሳታሰልስ መጠየቅ ይኖርብሃል። ይሖዋ “ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ” ይችላል። (ኤፌ. 3:20፤ ሉቃስ 11:13) አንድ ሰው “አምላክ ‘ሳለምነው ምን ነገር እንደሚያስፈልገኝ አስቀድሞ የሚያውቅ’ ከሆነ ሳላሰልስ መጠየቅ የሚኖርብኝ ለምንድን ነው?” ብሎ ቢጠይቅህ ምን መልስ ትሰጠዋለህ? (ማቴ. 6:8) አንደኛ ነገር ይሖዋ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥህ መጸለይህ በእሱ እንደምትተማመን ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው ለእርዳታ ወደ አንተ ቢመጣ ግለሰቡ በአንተ እንደሚተማመን ስለሚጠቁምህ እሱን ለመርዳት አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ታደርጋለህ። (ከምሳሌ 3:27 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጥህ መጠየቅህ እሱን ስለሚያስደስተው መንፈሱን ይሰጥሃል።—ምሳሌ 15:8
9. በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህ የአምላክ መንፈስ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብህ የሚያደርገው እንዴት ነው?
9 የአምላክ መንፈስ በአንተ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዲያሳድር ማድረግ የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ከጉባኤ፣ ከልዩ፣ ከወረዳና ከአውራጃ ስብሰባዎች ጋር የተያያዘ ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህና ፕሮግራሙን በትኩረት መከታተልህ በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረግህ “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” እንድትረዳ ያስችልሃል። (1 ቆሮ. 2:10) በተጨማሪም ዘወትር ሐሳብ መስጠትህ ጥቅም ያስገኝልሃል። እስቲ ባለፉት አራት ሳምንታት ውስጥ ስለተገኘህባቸው ስብሰባዎች ቆም ብለህ አስብ። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መልስ ለመስጠትና እምነትህን ለመግለጽ ምን ያህል ጊዜ እጅህን አውጥተህ ነበር? በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆን? እንዲህ ማድረግ የሚያስፈልግህ ከሆነ በመጪዎቹ ሳምንታት ለውጥ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ያለህን ፍላጎት በማየት መንፈሱን ይሰጥሃል፤ ይህ ደግሞ ከስብሰባዎች የበለጠ ጥቅም እንድታገኝ ያስችልሃል።
10. በመንፈስ መመላለስ የትኛውን ግብዣ ለሰዎች ማቅረብን ይጨምራል?
10 በመንፈስ መመላለስ በራእይ 22:17 ላይ ለቀረበው “መንፈሱና ሙሽራይቱም ‘ና!’ እያሉ ነው። የሚሰማም ሁሉ ‘ና!’ ይበል። የተጠማም ሁሉ ይምጣ፤ የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ” ለሚለው ጥሪ ምላሽ መስጠትን ይጨምራል። መንፈሱ የሙሽራይቱ ክፍል በሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች አማካኝነት ከሕይወት ውኃ ጋር የተያያዘውን ይህን ግብዣ እያቀረበ ነው። “ና” የሚለውን ጥሪ የተቀበልክ ክርስቲያን ከሆንክ አንተም “ና” የሚለውን ጥሪ ለሌሎች ሰዎች ለማቅረብ ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ሕይወት አድን በሆነው በዚህ ሥራ ላይ መካፈል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
11, 12. መንፈስ ቅዱስ የስብከቱ ሥራ እንዲከናወን እገዛ የሚያበረክተው እንዴት ነው?
11 ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነ ሥራ በዛሬው ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ አመራር አማካኝነት እየተከናወነ ነው። መንፈስ ቅዱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለሚስዮናውያን አዳዲስ የአገልግሎት ክልሎችን በመክፈት ረገድ ምን ሚና እንደተጫወተ እንመልከት። ሐዋርያው ጳውሎስና የአገልግሎት ጓደኞቹ ‘በእስያ አውራጃ ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ከልክሏቸው ነበር’፤ መንፈሱ በቢቲኒያም እንዲሰብኩ አልፈቀደላቸውም ነበር። መንፈሱ ወደ እነዚህ ቦታዎች እንዳይሄዱ የከለከላቸው እንዴት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አንችልም፤ ሆኖም ጳውሎስን በአውሮፓ ወደሚገኘው ሰፊ መስክ መርቶት እንደነበር ግልጽ ነው። ጳውሎስ አንድ የመቄዶንያ ሰው እንዲረዳቸው ሲለምነው የሚሳይ ራእይ ተመልክቶ ነበር።—ሥራ 16:6-10
12 በዛሬው ጊዜም የይሖዋ መንፈስ በተመሳሳይ መንገድ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ እየመራ ነው። ይሖዋ ለቅቡዓኖቹ መመሪያ ለመስጠት በተአምር ራእይ አያሳያቸውም፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ይመራቸዋል። እንዲሁም መንፈሱ በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ወንድሞችና እህቶች የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ይገፋፋቸዋል። አንተም በዚህ አስፈላጊ ሥራ እየተካፈልክ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ በዚህ አስደሳች ሥራ ይበልጥ በመካፈል የምታገኘውን ደስታ መጨመር ትችላለህ?
13. ለመንፈስ ቅዱስ አመራር መገዛት የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
13 ለአምላክ ሕዝቦች የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ለመንፈስ ቅዱስ አመራር መገዛት ትችላለህ። በጃፓን የምትኖረውን ሚሆኮ የተባለች አንዲት ወጣት ሁኔታ እንመልከት። ሚሆኮ አዲስ አቅኚ ስለነበረች ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ብቃት እንደሌላት ተሰምቷት ነበር፤ የቤቱን ባለቤት ፍላጎት ሊማርክ በሚችል መንገድ መናገር እንደማትችል ይሰማት ነበር። በዚያ ሰሞን በመንግሥት አገልግሎታችን ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዴት ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ሐሳብ ወጥቶ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ እርካታ ያለው ሕይወት—እንዴት ማግኘት ይቻላል? የሚለው ብሮሹር ወጣ። ይህ ብሮሹር በተለይ በጃፓን አገር ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። ሚሆኮ ይህን ብሮሹር ማበርከት የሚቻልበትን መንገድ በተለይም እንዴት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንደሚቻል የተሰጠውን ሐሳብ ተግባራዊ አደረገች። ብዙም ሳይቆይ ከዚያ ቀደም መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ያልሆኑ ብዙ ሰዎችን ጥናት ማስጀመር ቻለች። ሚሆኮ እንዲህ ብላለች፦ “በርካታ ጥናቶችን አገኘሁ፤ ጥናቶቼ በአንድ ወቅት እስከ 12 ስለደረሱ አንዳንዶቹን ጥናት ለማስጀመር ወረፋ እንዲጠብቁ መንገር ግድ ሆኖብኝ ነበር!” በእርግጥም ለይሖዋ አገልጋዮች የሚሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ በመንፈስ የምትመላለስ ከሆነ የተትረፈረፈ በረከት ማጨድ ትችላለህ።
በአምላክ መንፈስ ተማመን
14, 15. (ሀ) ፍጽምና የሚጎድላቸው ሰዎች ራሳቸውን ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምተው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) የተሻሉ ጓደኞች ማፍራት የምትችለው እንዴት ነው?
14 የተሾምክ የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ልታከናውነው የሚገባ አገልግሎት አለህ። (ሮም 10:14) ይህን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል የተሟላ ብቃት እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንደ ቅቡዓኑ ሁሉ አንተንም ብቁ የሚያደርግህ አምላክ ነው። (2 ቆሮንቶስ 3:5ን አንብብ።) አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግና በአምላክ መንፈስ በመተማመን ራስህን ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ መኖር ትችላለህ።
15 እኛ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ፍጹም አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን መኖር ቀላል እንደማይሆንልን የታወቀ ነው። ይህን ከባድ ከሚያደርጉብህ ነገሮች መካከል አንዱ ከዚህ ቀደም ትቀርባቸው የነበሩ ሰዎች በሕይወትህ ውስጥ ባደረከው ለውጥ መደነቃቸውና ‘መሳደባቸው’ ሊሆን ይችላል። (1 ጴጥ. 4:4) ይሁንና ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ከይሖዋና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የመሠረትከውን አዲስ ዝምድና እንደ ቀላል ነገር አድርገህ አትየው። (ያዕቆብ 2:21-23ን አንብብ።) በተጨማሪም ‘የመላው የወንድማማች ማኅበር’ ክፍል በሆነው በጉባኤህ ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን ለማወቅ ጥረት ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥ. 2:17፤ ምሳሌ 17:17) ይሖዋ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ የሚችሉ ጓደኞች እንድታፈራ በመንፈሱ አማካኝነት ይረዳሃል።
16. ልክ እንደ ጳውሎስ ‘በድክመትህ ደስ ሊልህ’ የሚችለው ለምንድን ነው?
16 በጉባኤህ ውስጥ ሊረዱህ የሚችሉ ጓደኞች ቢኖሩህም እንኳ በየዕለቱ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። በየጊዜው የሚያጋጥሙህ ችግሮች ከመደራረባቸው የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ኃይልህ እንደተሟጠጠ ይሰማህ ይሆናል። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጥህ መጠየቅ የሚኖርብህ በተለይ በዚህ ወቅት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 4:7-10 እና 12:10ን አንብብ።) ጳውሎስ ሰዎች ያለባቸው ድክመት ምንም ይሁን ምን የአምላክ መንፈስ ይህን ድክመታቸውን እንደሚሸፍንላቸው ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ድካም በሚሰማህና እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ ሁሉ ብርታት ሊሰጥህ ይችላል። ጳውሎስ ‘በድክመቱ ደስ ሊሰኝ’ እንደሚችል ጽፏል። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ በውስጡ እየሠራ እንደሆነ የሚሰማው በሚደክምበት ጊዜ ነው። አንተም እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊሰማህ ይችላል!—ሮም 15:13
17. ወደ ግብህ ለመድረስ በምታደርገው ጥረት መንፈስ ቅዱስ ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
17 ራሳችንን ለይሖዋ በመወሰን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር የአምላክ መንፈስ ያስፈልገናል። በነፋስ ኃይል የሚንቀሳቀስ ጀልባ እየቀዘፍክ ነው እንበል። ግብህ ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል ነው። መንፈስ ቅዱስ ያሰብክበት ቦታ ያለምንም ጉዳት በሰላም መድረስ እንድትችል ከሚረዳህ ነፋስ ጋር ይመሳሰላል። በዚህ የሰይጣን ዓለም መንፈስ ወዲያና ወዲህ መንገዋለል አትፈልግም። (1 ቆሮ. 2:12) በመሆኑም ተስማሚ የሆነውን ነፋስ ለይተህ ማወቅና ጉዞ መጀመር አለብህ። ይህ ነፋስ መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ በአምላክ ቃልና በመንፈሱ በሚመራው ድርጅት አማካኝነት ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ይወስድሃል።
18. በአሁኑ ጊዜ ምን ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? ለምንስ?
18 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስታጠና እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ ስትገኝ የነበረ ቢሆንም እንኳ እስካሁን ድረስ ራስህን ወስነህ አልተጠመቅክ ይሆናል፤ ይህን ወሳኝ እርምጃ ካልወሰድክ ‘ለመጠመቅ የማመነታው ለምንድን ነው?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። በዛሬው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ የይሖዋን ፈቃድ ለመፈጸም የሚጫወተውን ሚና የተረዳህ እንዲሁም የሚያከናውነውን ተግባር የምታደንቅ ከሆነ ከተማርከው ትክክለኛ ነገር ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰድ። ይሖዋ አብዝቶ ይባርክሃል። መንፈስ ቅዱሱንም አትረፍርፎ ይሰጥሃል። የተጠመቅከው ከዓመታት ወይም ከአሥርተ ዓመታት በፊት ከሆነ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ በራስህ ሕይወት አይተህ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት እንዴት እንደሚያበረታህ አይተህ ይሆናል። ወደፊትም ቢሆን ለዘላለም ያበረታሃል። በመሆኑም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።
ታስታውሳለህ?
• ‘በመንፈስ መመላለስ’ ሲባል ምን ማለት ነው?
• ‘በመንፈስ መመላለስህን እንድትቀጥል’ ምን ሊረዳህ ይችላል?
• ራስህን ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአፈር የተመሰለውን ልብህን ለመኮትኮት ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንፈስ በጎ ተጽዕኖ እያሳደረብህ ነው?