ለእምነታችን መከላከያ ማቅረብ
“ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ።”—1 ጴጥሮስ 3:15
1, 2. የይሖዋ ምሥክሮች የሚደርስባቸው ተቃውሞ የማያስደንቃቸው ለምንድን ነው? ሆኖም ምን ፍላጎት አላቸው?
በብዙ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በአጠቃላይ ሐቀኞችና ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች መሆናቸው ይታወቃል። ብዙ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ምንም ችግር የማይፈጥሩ ጥሩ ጎረቤቶች እንደሆኑ ይናገራሉ። የሚያስገርመው ግን እነዚህ ሰላም ወዳድ ክርስቲያኖች በጦርነትም ሆነ በሰላም ጊዜያት አለአግባብ ስደትና መከራ ይደርስባቸዋል። እንዲህ ያለ ተቃውሞ ስላጋጠማቸው አይደነቁም። እንዲያውም የሚጠብቁት ነገር ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ይኖሩ የነበሩ የታመኑ ክርስቲያኖች በሌሎች ዘንድ ‘ይጠሉ’ እንደነበር ያውቃሉ፤ ታዲያ በዛሬው ጊዜ የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ለመሆን የሚጥሩ ሰዎች ከዚያ የተለየ ሁኔታ እንዴት ይጠብቃሉ? (ማቴዎስ 10:22) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” ይላል።—2 ጢሞቴዎስ 3:12
2 የይሖዋ ምሥክሮች ስደት እንዲደርስባቸው አይፈልጉም፤ ወይም ከስደቱ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ማለትም ቅጣት፣ እስራት ወይም እንግልት ሲደርስባቸው አይደሰቱም። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ያላንዳች እንቅፋት መስበክ እንዲችሉ ‘ጸጥና ዝግ ያለ ሕይወት መምራት’ ይፈልጋሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:1, 2) በአብዛኞቹ አገሮች አምልኳቸውን ለማከናወን የሚያስችል ሃይማኖታዊ ነፃነት ማግኘታቸውን ያደንቃሉ፤ እንዲሁም የሰብዓዊ መንግሥታት ገዥዎችን ጨምሮ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም” ለመኖር የሚችሉትን ሁሉ በትጋት ያደርጋሉ። (ሮሜ 12:18፤ 13:1–7) ታዲያ ‘የሚጠሉት’ ለምንድን ነው?
3. የይሖዋ ምሥክሮች አለአግባብ እንዲጠሉ የሚያደርጋቸው አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?
3 በመሠረቱ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ስደት እንዲደርስባቸው ያደረገው ምክንያትና ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሉበት ምክንያት ተመሳሳይ ነው። በመጀመሪያ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሃይማኖታዊ እምነታቸው መሠረት የሚያከናውኗቸው ነገሮች በአንዳንዶች ዘንድ እንዲጠሉ ያደርጓቸዋል። ለምሳሌ ያህል ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን ምሥራች በቅንዓት ይሰብካሉ፤ ሆኖም ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ቅንዓታቸውን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት የስብከት ሥራቸው “የሰዎችን እምነት በግድ የማስቀየር ጥረት” እንደሆነ አድርገው ይወስዱታል። (ከሥራ 4:19, 20 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ብሔራት ከሚያካሂዱት ፖለቲካና ጦርነት ገለልተኞች ናቸው፣ ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ምሥክሮቹ ታማኝ ዜጎች አይደሉም የሚል የተሳሳተ ትርጉም እንዲሰጣቸው ሲያደርግ ቆይቷል።—ሚክያስ 4:3, 4
4, 5. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች የሐሰት ክስ ዒላማዎች የሆኑት እንዴት ነው? (ለ) አብዛኛውን ጊዜ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ በዋነኝነት ስደት የሚቆሰቁሱት እነማን ናቸው?
4 በሁለተኛ ደረጃ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነሱ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ነገር በሚናገሩና እምነታቸውን አጣምመው በሚያቀርቡ ሰዎች የሐሰት ክስ ይሰነዘርባቸዋል። በዚህ ምክንያት በአንዳንድ አገሮች በደል ተፈጽሞባቸዋል። በተጨማሪም ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ለማክበር ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና በመሻታቸው ምክንያት “ፀረ ልጆች” እና “ራስን በራስ ማጥፋትን የሚያበረታታ ኑፋቄ” የሚል የተሳሳተ ስም ተሰጥቷቸዋል። (ሥራ 15:29) ሐቁ ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፤ የይሖዋ ምሥክሮች ለሕይወት ከፍተኛ ግምት የሚሰጡ ሲሆን ለራሳቸውም ሆነ ለልጆቻቸው ከሁሉ የተሻለውን የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ይፈልጋሉ። ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት በየዓመቱ ብዙ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ይሞታሉ የሚለው ክስ ምንም መሠረት የሌለው ነው። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሁሉም የቤተሰብ አባላት ላይ ተመሳሳይ የሆነ ውጤት ስለማይኖረው ምሥክሮቹ ቤተሰቦችን ይለያያሉ ተብለውም ተከሰዋል። ይሁንና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በደንብ የሚተዋወቁ ሰዎች ምሥክሮቹ የቤተሰብን ሕይወት ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱ፣ ባልና ሚስት አንዳቸው ሌላውን እንዲወድዱና እንዲያከብሩ እንዲሁም ልጆች አማኞች ለሆኑትም ሆነ ላልሆኑት ወላጆቻቸው ታዛዦች መሆን እንዳለባቸው የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛት ለመከተል እንደሚጥሩ ያውቃሉ።—ኤፌሶን 5:21—6:3
5 አብዛኛውን ጊዜ በይሖዋ አገልጋዮች ላይ በዋነኝነት ስደት የሚቆሰቁሱት በፖለቲካ ባለ ሥልጣናትና በመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም የምሥክሮቹን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚጥሩ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ናቸው። ታዲያ፣ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታችንም ሆነ በተግባራችን ወይም በሚቀርቡብን የሐሰት ክሶች ምክንያት ለሚደርስብን እንዲህ ላለው ተቃውሞ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው?
“ምክንያታዊነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ”
6. ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ስላሉ ሰዎች ሚዛናዊ አመለካከት መያዙ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 በመጀመሪያ ደረጃ ሃይማኖታዊ እምነታችንን ስለማይጋሩን ሰዎች ትክክለኛ አመለካከት ማለትም የይሖዋን አመለካከት ልንይዝ ይገባል። አለዚያ የራሳችን አመለካከት አላስፈላጊ የሆነ ጥላቻ ወይም ነቀፋ ሊጋብዝ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ገርነታችሁ [“ምክንያታዊነታችሁ፣” NW] ለሰው ሁሉ ይታወቅ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 4:5) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ያሉ ሰዎችን በተመለከተ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታናል።
7. ‘በዓለም ከሚገኝ እድፍ ራስን መጠበቅ’ ምን ማድረግን ይጨምራል?
7 በሌላ በኩል ደግሞ ቅዱሳን ጽሑፎች ‘በዓለም ከሚገኝ እድፍ ራሳችንን እንድንጠብቅ’ በግልጽ ይመክሩናል። (ያዕቆብ 1:27፤ 4:4) እዚህ ላይ የሚገኘው “ዓለም” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች ላይ እንደተሠራበት ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ውጭ ያለውን ሰብአዊ ኅብረተሰብ የሚያመለክት ነው። የምንኖረው በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፤ በሥራ፣ በትምህርት ቤትና በጉርብትና እንገናኛለን። (ዮሐንስ 17:11, 15፤ 1 ቆሮንቶስ 5:9, 10) ይሁንና ከአምላክ የጽድቅ መንገዶች ጋር ከሚቃረኑ አመለካከቶች፣ አነጋገርና ጠባይ በመራቅ በዓለም ከሚገኝ እድፍ ራሳችንን እንጠብቃለን። ከዚህ ዓለም ጋር በተለይም ለይሖዋ የአቋም መስፈርቶች ምንም አክብሮት ከሌላቸው ሰዎች ጋር በጣም መቀራረብ ያለውን አደጋ መገንዘባችንም በጣም አስፈላጊ ነው።—ምሳሌ 13:20
8. ከዓለም እድፍ ራስን ስለ መጠበቅ የተሰጠው ምክር ሌሎችን በንቀት ዓይን እንድንመለከት መሠረት የማይሆነን ለምንድን ነው?
8 ይሁን እንጂ በዓለም ከሚገኝ እድፍ ራሳችንን እንድንጠብቅ የተሰጠው ምክር የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን እንድናንቋሽሽ መሠረት አይሆነንም። (ምሳሌ 8:13) ቀደም ሲል ባጠናነው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ምሳሌ አስታውሱ። የገነቡት የአምልኮ ሥርዓት በይሖዋ ፊት ሞገስን አላገኘም፤ አይሁዳውያን ካልሆኑ ሰዎችም ጋር ጥሩ ግንኙነት ለመፍጠር አላስቻለም። (ማቴዎስ 21:43, 45) እነዚህ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ አክራሪ ሰዎች አሕዛብን ይንቁ ነበር። እኛ ግን እንዲህ ያለ ጠባብ አመለካከት በመያዝ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን አናንቋሽሽም። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ የእኛም ፍላጎት ሁሉም ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት መልእክት ሰምተው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ ነው።—ሥራ 26:29፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
9. ሚዛናዊ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት መያዝ እምነታችንን ስለማይጋሩ ሰዎች በምንናገርበት ጊዜ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
9 ሚዛናዊ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ አመለካከት የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን በተመለከተ እንዴት መናገር እንዳለብን እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል። ጳውሎስ በቀርጤስ ደሴት የሚገኙ ክርስቲያኖች “ማንንም የማይሰድቡ [“በማንም ላይ ክፉ ነገር [የማይናገሩ]፣” የ1980 ትርጉም]፣ የማይከራከሩ፣ ገሮች፣ ለሰው ሁሉ የዋህነትን ሁሉ የሚያሳዩ እንዲሆኑ” እንዲያሳስባቸው ቲቶን አዝዞታል። (ቲቶ 3:2) ክርስቲያኖች “በማንም” ላይ ክፉ ነገር እንዳይናገሩ እንደታዘዙ ልብ በሉ፤ ይህ ደግሞ በቀርጤስ የሚኖሩ ውሸታም፣ ሆዳምና ሰነፍ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎችን ሳይቀር የሚጨምር ነበር። (ቲቶ 1:12) ስለዚህ እምነቶቻችንን ስለማይጋሩን ሰዎች በምንናገርበት ጊዜ የሚያንኳስሱ ቃላት መጠቀም ቅዱስ ጽሑፋዊ አይሆንም። ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ ሌሎች ሰዎች ወደ ይሖዋ አምልኮ እንዳይመጡ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ለሌሎች ያለን አመለካከትና ከእነሱ ጋር ያለን ግንኙነት በይሖዋ ቃል ላይ ከሚገኙት ምክንያታዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ ከሆነ የአምላክን “ትምህርት በሁሉ ነገር [እናስመሰግናለን።]”—ቲቶ 2:10
ዝም የምንልበት ጊዜ፣ የምንናገርበት ጊዜ
10, 11. ኢየሱስ (ሀ) ‘ዝም ለማለት’ (ለ) ‘ለመናገር’ ጊዜ እንዳለው እንደሚያውቅ ያሳየው እንዴት ነበር?
10 መክብብ 3:7 “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። አሁን ችግሩ ተቃዋሚዎችን በዝምታ የምናልፈው ወይም ለእምነታችን መከላከያ ለማቅረብ መናገር የሚያስፈልገን መቼ ነው የሚለው ነው። ጠንቃቃ በመሆን ረገድ ሁልጊዜ ፍጹም ከነበረው ከኢየሱስ ምሳሌ ብዙ ልንማር እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 2:21) ‘ዝም ማለት’ የሚገባው መቼ እንደሆነ ያውቅ ነበር። ለምሳሌ ያህል የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በጲላጦስ ፊት በሐሰት በከሰሱት ጊዜ ኢየሱስ “ምንም አልመለሰም።” (ማቴዎስ 27:11–14) አምላክ ለእሱ ያለው ፈቃድ እንዳይፈጸም የሚያግድ ነገር እንዳይኖር ሲል ምንም ነገር ሊናገር አልወደደም። ከዚህ ይልቅ ይፋ የነበረው ተግባሩ እንዲናገር መረጠ። በትዕቢት የተሞላ አእምሯቸውንና ልባቸውን እውነት እንኳ ሊለውጠው እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ ሆን ብሎ ዝም በማለት ክሳቸውን ችላ ብሎ አልፎታል።—ኢሳይያስ 53:7
11 ይሁን እንጂ ኢየሱስ መቼ ‘መናገር’ እንዳለበትም ያውቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የሐሰት ክሶቻቸውን በማፍረስ በግልጽና በይፋ እየተቸ ይከራከር ነበር። ለምሳሌ ያህል ጻፎችና ፈሪሳውያን በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል ብለው በመክሰስ በተሰበሰበ ሕዝብ ፊት ሊያዋርዱት በሞከሩ ጊዜ እነዚህን የሐሰት ክሶች በዝምታ ማለፍ አልመረጠም። አሳማኝ የሆነ ምክንያትና ኃይለኛ ምሳሌ በመጠቀም የውሸት ክሱን አጋልጧል። (ማርቆስ 3:20–30፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 15:1–11፤ 22:17–21ና ዮሐንስ 18:37ን ተመልከት።) በተመሳሳይም ኢየሱስ አሳልፎ ከተሰጠና ከታሠረ በኋላ በሳንሄድሪን ፊት ሲቀርብ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ” ሲል በዘዴ ጠየቀው። ዝም ማለቱ ክርስቶስ መሆኑን ክዷል የሚል ትርጉም ሊሰጠው ስለሚችል በዚህ ‘ጊዜም መናገር’ ነበረበት። ስለዚህ ኢየሱስ “እኔ ነኝ” ብሎ መለሰ።—ማቴዎስ 26:63, 64፤ ማርቆስ 14:61, 62
12. ጳውሎስና በርናባስ በኢቆንዮን በድፍረት እንዲናገሩ ያነሳሷቸው ሁኔታዎች ምን ነበሩ?
12 በተጨማሪም የጳውሎስንና የበርናባስን ምሳሌ ተመልከት። ሥራ 14:1, 2 እንዲህ ይላል:- “በኢቆንዮንም እንደ ቀድሞ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገብተው ከአይሁድና ከግሪክ ሰዎች ብዙ እስኪያምኑ ድረስ ተናገሩ። ያላመኑት አይሁድ ግን የአሕዛብን ልብ በወንድሞች ላይ አነሣሡ አስከፉም።” ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል “ያላመኑት አይሁድ ግን አሕዛብን በመቀስቀስና አእምሯቸውን በመመረዝ ክርስቲያኖችን እንዲጠሉ አደረጉ” ይላል። አይሁዳውያን ተቃዋሚዎች መልእክቱን ለመቀበል እምቢ ማለታቸው ሳይበቃቸው ክርስቲያኖች በአሕዛብ ዘንድ እንዲጠሉ ለማድረግ የስም ማጥፋት ዘመቻ አፋፍመው ነበር።a ለክርስትና እንዴት ያለ ከፍተኛ ጥላቻ ነበራቸው! (ከሥራ 10:28 ጋር አወዳድር።) ጳውሎስና በርናባስ በዚህ ጊዜ ‘መናገር’ እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ነበር፤ አለበለዚያ አዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ከሕዝቡ በሚደርስባቸው ተቃውሞ ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። “ስለዚህ ጳውሎስና በርናባስ የጌታን ነገር በድፍረት እየተናገሩ እዚያ ብዙ ጊዜ ቆዩ።” ይሖዋም ተአምራታዊ ምልክቶች እንዲያደርጉ ሥልጣን በመስጠት በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታቸውን አሳይቷቸዋል። ይህ ደግሞ “እኩሌቶቹ ከአይሁድ እኩሌቶቹም ከሐዋርያት ጋር” እንዲሆኑ አድርጓል።—ሥራ 14:3, 4
13. ነቀፋን በተመለከተ በአብዛኛው ‘ዝም ማለት’ የተመረጠ የሚሆነው መቼ ነው?
13 ታዲያ ሲነቅፉን ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው? ይህ በሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። አንዳንድ ሁኔታዎች ‘ዝም ለማለት ጊዜ አለው’ የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ እንድናደርግ የሚያስገድዱን ይሆናሉ። በተለይ ይህ አስፈላጊ የሚሆነው እኛን ለመቃወም ቆርጠው የተነሡ ሰዎች ፍሬ ቢስ ወደሆነ ክርክር ሊያስገቡን በሚሞክሩበት ጊዜ ነው። አንዳንድ ሰዎች እውነትን ማወቅ እንደማይፈልጉ መዘንጋት የለብንም። (2 ተሰሎንቄ 2:9–12) ለማመን ፈቃደኛ ያልሆነ ኩሩ ልብ ያላቸውን ሰዎች ለማሳመን መጣሩ እርባና የለውም። ከዚህም በላይ በሐሰት ከሚከሰን ሰው ሁሉ ጋር የምንከራከር ከሆነ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውንና የሚክሰውን እንቅስቃሴ ማለትም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በእርግጥ ለማወቅ የሚፈልጉትን ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የመርዳቱን ሥራ እንዳናከናውን ሊያዘናጋን ይችላል። ስለዚህ እኛን የሚመለከት የሐሰት ወሬ ለመንዛት ቆርጠው የተነሡ ተከራካሪዎች ሲያጋጥሙን በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ምክር “ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ” ይላል።—ሮሜ 16:17, 18፤ ማቴዎስ 7:6
14. በሌሎች ፊት ለእምነታችን መከላከያ ማቅረብ ያለብን በምን መንገዶች ነው?
14 እርግጥ ይህ ሲባል ለእምነታችን መከላከያ አናቀርብም ማለት አይደለም። ዝም ለማለት ጊዜ እንዳለው ሁሉ “ለመናገርም ጊዜ አለው።” ስማችንን ለማጥፋት ሲባል ለሚሰነዘረው ትችት ስለተጋለጡ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እናስባለን። ከልብ ስለምናምንባቸው ነገሮች ለሌሎች ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኞች ነን፤ እንዲያውም እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ደስተኞች ነን። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፣ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።” (1 ጴጥሮስ 3:15) እውነተኛ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ከልብ ስለምናምንባቸው ነገሮች ማስረጃ ሲፈልጉና ተቃዋሚዎች ስላነሷቸው የሐሰት ክሶች ሲጠይቁ አጥጋቢ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልሶችን በመስጠት ለእምነታችን መከላከያ ማቅረቡ የእኛ ኃላፊነት ነው። በተጨማሪም መልካም ምግባራችን ብዙ ሊናገር ይችላል። የሚያመዛዝን አእምሮ ያላቸው ታዛቢዎች ከአምላክ የጽድቅ የአቋም መስፈርቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር በእርግጥ እንደምንጥር ሲመለከቱ እኛን በመቃወም የሚቀርቡ ክሶች ሐሰት መሆናቸውን በቀላሉ ሊገነዘቡ ይችላሉ።—1 ጴጥሮስ 2:12–15
ስም የሚያጠፉ ዘገባዎችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል?
15. የይሖዋ ምሥክሮች በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርብ የተዛባ መረጃ ዒላማ መሆናቸውን የሚያሳይ አንድ ምሳሌ የትኛው ነው?
15 አልፎ አልፎ መገናኛ ብዙሐን የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ የተዛቡ መረጃዎች ያቀርባሉ። ለምሳሌ ያህል በነሐሴ 1, 1997 ታትሞ የወጣ አንድ የሩሲያ ጋዜጣ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የእምነታቸው አባላት የሆኑ ሰዎች ‘ሚስቶቻቸው፣ ባሎቻቸውና ወላጆቻቸው እምነታቸውን ለመረዳትና ለመቀበል የማይፈልጉ ከሆነ ጨርሶ እንዲያገሏቸው ያበረታታሉ’ ሲል የምሥክሮቹን ስም የሚያጠፋ ጽሑፍ አውጥቷል። የይሖዋ ምሥክሮችን በደንብ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ይህ ክስ ሐሰት መሆኑን ያውቃል። ክርስቲያኖች የማያምኑ የቤተሰብ አባሎቻቸውን ማፍቀርና ማክበር እንዳለባቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገር ሲሆን ምሥክሮቹ ደግሞ ይህን መመሪያ ለመከተል ይጥራሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:12–16፤ 1 ጴጥሮስ 3:1–4) ይሁንና ዘገባው ታትሞ በመውጣቱ ብዙ አንባቢዎች የተሳሳተ መረጃ ደርሷቸዋል። በሐሰት በምንከሰስበት ጊዜ ለእምነታችን መከላከያ ማቅረብ የምንችለው እንዴት ነው?
16, 17 እና በገጽ 16 ላይ የሚገኘው ሣጥን። (ሀ) በመገናኛ ብዙሃን ለሚነዛው የሐሰት ወሬ ምላሽ መስጠትን በተመለከተ መጠበቂያ ግንብ በአንድ ወቅት ምን ብሎ ነበር? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በመገናኛ ብዙሃን ላይ ለሚቀርቡ አፍራሽ ዘገባዎች ምላሽ የሚሰጡባቸው ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
16 እዚህ ላይም ቢሆን “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው።” መጠበቂያ ግንብ በአንድ ወቅት ላይ እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡትን የሐሰት ወሬዎች ችላ ብለን ማለፋችን ወይም በተገቢ መንገድ ለእውነት መከራከራችን የተመካው በሁኔታዎቹ፣ በትችት ሰንዛሪውና ተቺው በተነሣበት ዓላማ ላይ ነው።” በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር አፍራሽ ዘገባዎችን ችላ ብሎ ማለፉ የተሻለ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ውሸቶቹ ይበልጥ እንዳይስፋፉ ያደርጋል።
17 በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ‘መናገር’ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ሐቀኛ የሆነ ጋዜጠኛ ወይም ሪፖርተር ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተሳሳተ መረጃ ደርሶት ሊሆን ስለሚችል ስለ እኛ እውነተኛውን መረጃ ቢያገኝ ደስ ይለው ይሆናል። (“በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተቃጣውን ስም የማጥፋት ሙከራ እንዲስተካከል ማድረግ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ አፍራሽ ዘገባዎች የስብከት ሥራችንን የሚያስተጓጉል መሠረተ ቢስ ጥላቻ የሚቀሰቅሱ ከሆነ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ተወካዮች ለእውነት መከላከያ ለማቅረብ ሲሉ አንዳንድ ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን ይወስዱ ይሆናል።b ለምሳሌ ያህል ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በመቅረብ እውነታውን እንዲያሳውቁ ይመደቡ ይሆናል፤ ምክንያቱም በዚህ ጊዜ ዝም ማለቱ የይሖዋ ምሥክሮች መልስ እንደሌላቸው ሊያስቆጥር ይችላል። ግለሰብ የይሖዋ ምሥክሮች ጥበበኛ በመሆን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርና ማኅበሩ የወከላቸው ሰዎች በጉዳዩ ላይ ከሚሰጡት መመሪያ ጋር ይተባበራሉ።—ዕብራውያን 13:17
ለምሥራቹ ሕጋዊ መከላከያ ማቅረብ
18. (ሀ) ለመስበክ የሰብዓዊ መንግሥታት ፈቃድ የማያስፈልገን ለምንድን ነው? (ለ) የመስበክ ፈቃድ በምንከለከልበት ጊዜ የትኛውን አካሄድ እንከተላለን?
18 የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበክ ሥልጣን የተሰጠን ከሰማይ ነው። ይህን ሥራ እንድንሠራ ያዘዘን ኢየሱስ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” ተሰጥቶታል። (ማቴዎስ 28:18–20፤ ፊልጵስዩስ 2:9–11) ከዚህም የተነሣ ምሥራቹን ለመስበክ የሰብዓዊ መንግሥታት ፈቃድ አያስፈልገንም። ይሁንና ሃይማኖታዊ ነፃነት ማግኘት የመንግሥቱን መልእክት ለማስፋፋት እንደሚረዳ እንገነዘባለን። አምልኳችንን እንድናከናውን ነፃነት ባገኘንባቸው አገሮች የስብከት ሥራችንን ለማስከበር ሕጋዊ በሆኑ መንገዶች እንጠቀማለን። እንዲህ ያለውን ነፃነት በተከለከልንባቸው አገሮች ደግሞ ሕጋዊ ከሆነው አሠራር ሳንወጣ ይህን ነፃነት ለማግኘት እንጥራለን። ዓላማችን ማኅበራዊ ለውጥ ማምጣት ሳይሆን ‘ምሥራቹን መከላከልና ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ’ ማድረግ ነው።c—ፊልጵስዩስ 1:7 NW
19. (ሀ) ‘የአምላክን ለአምላክ ማስረከባችን’ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ማድረግ ነው?
19 የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ መሆኑን አምነን ተቀብለናል። የእሱ ሕግ ከሁሉ የላቀ ነው። ሰብዓዊ መንግሥታትን በሚገባ በመታዘዝ ‘የቄሣርን ለቄሣር እናስረክባለን።’ ነገር ግን ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ማለትም ‘የአምላክን ለአምላክ በማስረከብ’ ኃላፊነታችን ረገድ ምንም ነገር ጣልቃ እንዲገባብን አንፈቅድም። (ማቴዎስ 22:21) ይህን ማድረጋችን በብሔራት ዘንድ ‘የጥላቻ ዒላማ’ እንደሚያደርገን ሙሉ በሙሉ እንገነዘባለን፤ ሆኖም ይህ ደቀ መዝሙር መሆናችን የሚጠይቀው ዋጋ ክፍል እንደሆነ እናውቃለን። የይሖዋ ምሥክሮች በ20ኛው መቶ ዘመን በሕግ ረገድ ያስመዘገቡት ታሪክ እምነታችንን ለመከላከል ቆርጠን የተነሣን መሆናችንን ይመሠክራል። በይሖዋ እርዳታና ድጋፍ ‘ምሥራቹን በትጋት ማስተማራችንንና መስበካችንን’ እንገፋበታለን።—ሥራ 5:42
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ማቲው ሄንሪስ ኮሜንተሪ ኦን ዘ ሆል ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው የአይሁድ ተቃዋሚዎች የክርስትናን እምነት የሚቃወሙ አይሁዶች “እምብዛም ወደማያውቋቸው [አሕዛብ] እንኳ ሳይቀር ሥራዬ ብለው በመሄድ ክርስትናን እንዲንቁ ብቻ ሳይሆን ጥላቻ እንዲያድርባቸው ለማድረግ ተንኮል የተሞላ አእምሯቸው ሊያፈልቅ የሚችለውን መጥፎ ነገር ሁሉ ይነግሯቸው ነበር።”
b በሩሲያ የሚታተመው ጋዜጣ (በአንቀጽ 15 ላይ የተገለጸው) ስማቸውን የሚያጠፋ ርዕስ ካወጣ በኋላ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በመገናኛ ብዙሃን በሚቀርቡ ዘገባዎች ላይ የሚነሱ ክርክሮችን የሚዳኘው የሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምክር ቤት በርዕሱ ላይ የተዘረዘሩትን የሐሰት ክሶች እንዲመረምር ጥያቄ አቀረቡ። በቅርቡ ፍርድ ቤቱ ይህንን ስም አጥፊ ርዕስ አትሞ በማውጣቱ ጋዜጣውን ክፉኛ የሚነቅፍ ውሳኔ አስተላልፏል።—ንቁ! ኅዳር 22, 1998 (እንግሊዝኛ) ገጽ 26–7 ተመልከት።
c በገጽ 19–22 ላይ የሚገኘውን “ምሥራቹ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኝ ማድረግ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[ታስታውሳለህን?]
◻ የይሖዋ ምሥክሮች ‘የሚጠሉት’ ለምንድን ነው?
◻ ሃይማኖታዊ አመለካከቶቻችንን የማይጋሩንን ሰዎች እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?
◻ ለተቃዋሚዎች ምላሽ በመስጠት በኩል ኢየሱስ ምን ሚዛናዊነት የተንጸባረቀበት ምሳሌ ትቷል?
◻ በምንነቀፍበት ጊዜ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፣ ለመናገርም ጊዜ አለው” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት ልንሠራበት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለተቃጣው ስም የማጥፋት ሙከራ ምላሽ መስጠት
“በቦሊቪያ በምትገኘው በያክዊባ መንደር የሚገኝ አንድ የወንጌላውያን ቡድን በከሃዲዎች የተዘጋጀ ፊልም ለማሳየት ከአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ዝግጅት አደረገ። ፕሮግራሙ ያሳደረውን መጥፎ ተጽእኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሽማግሌዎች የይሖዋ ምሥክሮች—ከስሙ በስተጀርባ ያለው ድርጅት እና መጽሐፍ ቅዱስ—የእውነትና የትንቢት መጽሐፍ የሚሉትን የቪዲዮ ካሴቶች ለሕዝብ እንዲያሳዩላቸው ገንዘብ ለመክፈል ከሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ጋር ተነጋገሩ። አንድ የሬዲዮ ጣቢያ ባለቤት የማኅበሩን ቪዲዮ ካሴቶች ከተመለከተ በኋላ በከሃዲዎቹ ፕሮግራም አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮችን ስም ለማጥፋት የተቃጣው ሙከራ ስላናደደው መጪውን የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ በሚመለከት ነፃ የማስተዋወቂያ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል። በስብሰባው ላይ ከተጠበቀው በላይ ብዙ ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን ምሥክሮቹም በአገልግሎታቸው ላይ በሚያነጋግሯቸው ጊዜ ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ቀና ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀምረዋል።”—የ1997 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ፣ ገጽ 61–2
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የተቺዎቹን የሐሰት ክሶች በግልጽ ያጋለጠባቸው ወቅቶች ነበሩ