የጥናት ርዕስ 42
ይሖዋ ምን እንድትሆን ያደርግሃል?
“ፍላጎት እንዲያድርባችሁም ሆነ ለተግባር እንድትነሳሱ በማድረግ ኃይል የሚሰጣችሁ አምላክ ነው።”—ፊልጵ. 2:13
መዝሙር 104 የአምላክ ስጦታ የሆነው መንፈስ ቅዱስ
ማስተዋወቂያa
1. ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል ምን ማድረግ ይችላል?
ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን ይችላል። ለምሳሌ ይሖዋ አስተማሪ፣ አጽናኝ እና ወንጌላዊ ሆኗል፤ እነዚህ ይሖዋ ከሆናቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። (ኢሳ. 48:17፤ 2 ቆሮ. 7:6፤ ገላ. 3:8) በሌላ በኩል ደግሞ ዓላማውን ለመፈጸም ብዙ ጊዜ ሰዎችን ይጠቀማል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20፤ 2 ቆሮ. 1:3, 4) ይሖዋ፣ ለማንኛችንም ቢሆን ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስፈልገንን መሆን እንድንችል ጥበብና ኃይል ሊሰጠን ይችላል። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት የይሖዋ ስም ትርጉም፣ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ያጠቃልላል።
2. (ሀ) ይሖዋ እየተጠቀመብን መሆኑን አንዳንድ ጊዜ የምንጠራጠረው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 ሁላችንም ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም ቢጠቀምብን ደስ ይለናል፤ ሆኖም አንዳንዶች ይሖዋ እየተጠቀመባቸው መሆኑን ይጠራጠራሉ። ለምን? ዕድሜያቸውና ያሉበት ሁኔታ፣ ማከናወን የሚችሉትን ነገር እንደሚገድቡባቸው አሊያም ችሎታ እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው ነው። በተቃራኒው ደግሞ አንዳንዶች፣ እያደረጉ ያሉት ነገር በቂ እንደሆነና ተጨማሪ ጥረት ማድረግ እንደማያስፈልጋቸው ያስባሉ። በዚህ ርዕስ ላይ ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም እያንዳንዳችንን ብቁ የሚያደርገን እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። ይሖዋ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች አገልጋዮቹ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደረገውና ኃይል የሰጣቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችንም እንመረምራለን። በመጨረሻም ይሖዋ እንዲጠቀምብን መፍቀድ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።
ይሖዋ ብቁ የሚያደርገን እንዴት ነው?
3. በፊልጵስዩስ 2:13 መሠረት ይሖዋ የእሱን ፈቃድ የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርብን የሚያደርገው እንዴት ነው?
3 ፊልጵስዩስ 2:13ን አንብብ።b ይሖዋ የእሱን ፈቃድ የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርብን ሊያደርገን ይችላል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? በጉባኤያችን ውስጥ እርዳታ ማበርከት የምንችልበት አንድ ሁኔታ እንዳለ እናስተውል ይሆናል። አሊያም ከጉባኤያችን ክልል ውጭ እርዳታ የሚያስፈልግበት ቦታ እንዳለ የሚጠቁም ከቅርንጫፍ ቢሮው የተላከ ደብዳቤ ሽማግሌዎች ጉባኤ ላይ ያነቡ ይሆናል። በመሆኑም ‘እርዳታ ማበርከት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ ይሆናል። ወይም ደግሞ አንድ ከባድ ኃላፊነት እንድንቀበል ተጠይቀን ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ሥራውን በተገቢው መንገድ ማከናወን መቻላችንን እንጠራጠር ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ሐሳብ ካነበብን በኋላ ‘ይህን ጥቅስ ሌሎችን ለመርዳት ልጠቀምበት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይሖዋ ምንም ነገር እንድናደርግ አያስገድደንም። ይሁን እንጂ ያለንበትን ሁኔታ ለመመርመር ፈቃደኞች እንደሆንን ሲመለከት ያሰብነውን ነገር በተግባር የማዋል ፍላጎት እንዲያድርብን ይረዳናል።
4. ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል የሚሰጠን እንዴት ነው?
4 ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለማድረግ የሚያስችል ኃይልም ሊሰጠን ይችላል። (ኢሳ. 40:29) ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት ችሎታዎቻችንን እንድናሻሽል ሊረዳን ይችላል። (ዘፀ. 35:30-35) ይሖዋ አንዳንድ ኃላፊነቶችን እንዴት መወጣት እንደምንችል በድርጅቱ አማካኝነት ሊያሠለጥነን ይችላል። አንድን ሥራ እንዴት ማከናወን እንደምትችል ግራ ከገባህ እርዳታ ጠይቅ። በተጨማሪም በሰማይ ያለው ለጋሱ አባታችን ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ እንዲሰጥህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ሉቃስ 11:13) ይሖዋ የተለያዩ ወንዶችና ሴቶች ፈቃዱን ለማድረግ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደረገውና ኃይል የሰጣቸው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ብዙ ታሪኮችን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ከእነዚህ ዘገባዎች የተወሰኑትን ስንመረምር ይሖዋ አንተንም በተመሳሳይ መንገድ ሊጠቀምብህ የሚችለው በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ለማሰብ ሞክር።
አንዳንድ ወንዶች ምን መሆን ችለዋል?
5. ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት በሙሴ ለመጠቀም ከመረጠበት ጊዜ እንዲሁም እሱን ከተጠቀመበት መንገድ ምን እንማራለን?
5 ይሖዋ፣ ሙሴን የእስራኤላውያን ነፃ አውጪ እንዲሆን አድርጎታል። ሆኖም ይሖዋ ሙሴን የተጠቀመበት መቼ ነው? ሙሴ “የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ” በመማሩ ሕዝቡን ለመምራት ብቃት እንዳለው በተሰማው ጊዜ ነበር? (ሥራ 7:22-25) አይደለም፤ ይሖዋ ሙሴን የተጠቀመበት ትሑትና ገር ሰው እንዲሆን ሥልጠና ከሰጠው በኋላ ነው። (ሥራ 7:30, 34-36) ይሖዋ፣ በግብፁ ኃያል ገዢ ፊት ለመቆም የሚያስችል ድፍረት ለሙሴ ሰጥቶታል። (ዘፀ. 9:13-19) ይሖዋ በሙሴ ለመጠቀም ከመረጠበት ጊዜ እንዲሁም እሱን ከተጠቀመበት መንገድ ምን እንማራለን? ይሖዋ የሚጠቀመው አምላካዊ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ በሚጥሩ እንዲሁም ብርታት ለማግኘት በእሱ በሚታመኑ ሰዎች ነው።—ፊልጵ. 4:13
6. ይሖዋ ንጉሥ ዳዊትን ለመርዳት በቤርዜሊ መጠቀሙ ምን ያስተምረናል?
6 ከተወሰኑ መቶ ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሖዋ፣ ንጉሥ ዳዊት የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት በቤርዜሊ ተጠቅሟል። ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከዳዊት ልጅ ከአቢሴሎም እየሸሹ በነበሩበት ወቅት ‘ተርበው፣ ደክሟቸውና ተጠምተው’ ነበር። በዚህ ወቅት አረጋዊ ሰው የነበረው ቤርዜሊና አብረውት የነበሩት ሰዎች፣ ለዳዊትና ለተከተለው ሕዝብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማቅረብ ሲሉ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። ቤርዜሊ ዕድሜው ስለገፋ ይሖዋ ሊጠቀምበት እንደማይችል አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን የአምላክ አገልጋዮች ለመርዳት ሲል ያለውን ነገር በልግስና ሰጥቷል። (2 ሳሙ. 17:27-29) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? በየትኛውም ዕድሜ ላይ ብንገኝ ይሖዋ፣ በአካባቢያችንም ሆነ በሌሎች አገሮች ያሉ መሠረታዊ ነገሮችን ለማግኘት የሚቸገሩ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመርዳት ሊጠቀምብን ይችላል። (ምሳሌ 3:27, 28፤ 19:17) እነዚህን ወንድሞቻችንን በቀጥታ መርዳት ባንችልም እንኳ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ እንችላለን፤ በመዋጮ የተገኘው ገንዘብ እርዳታ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ሲፈጠር ጥቅም ላይ ይውላል።—2 ቆሮ. 8:14, 15፤ 9:11
7. ይሖዋ ስምዖንን የተጠቀመበት እንዴት ነው? ይህን ማወቃችን የሚያበረታታን እንዴት ነው?
7 ይሖዋ፣ ስምዖን ለተባለ በኢየሩሳሌም የሚኖር ታማኝ አገልጋዩ መሲሑን ሳያይ እንደማይሞት ቃል ገብቶለት ነበር። አረጋዊው ስምዖን መሲሑን ለበርካታ ዓመታት ሲጠባበቅ ስለነበር እንዲህ ያለ ተስፋ ሲሰጠው በጣም ተበረታትቶ መሆን አለበት። ደግሞም እምነት በማሳየቱና በመጽናቱ ተክሷል። አንድ ቀን ስምዖን “በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መጣ።” በዚያም ሕፃኑን ኢየሱስን አገኘ፤ ይሖዋም ክርስቶስ የሚሆነውን ይህን ልጅ በተመለከተ ትንቢት እንዲናገር ስምዖንን ተጠቀመበት። (ሉቃስ 2:25-35) ስምዖን፣ ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን የማየት አጋጣሚ ባይኖረውም እንኳ ላገኘው መብት አመስጋኝ ነበር፤ ወደፊት ደግሞ ከዚህም የላቀ በረከት ያገኛል! ይህ ታማኝ ሰው፣ በአዲሱ ዓለም ውስጥ የኢየሱስ አገዛዝ ለምድር ሕዝቦች ሁሉ የሚያመጣውን በረከት ይመለከታል። (ዘፍ. 22:18) እኛም ብንሆን ይሖዋ በየትኛውም መንገድ ቢጠቀምብን እሱ ለሚሰጠን መብት አመስጋኞች ልንሆን ይገባል።
8. ይሖዋ ልክ እንደ በርናባስ እኛንም ሊጠቀምብን የሚችለው እንዴት ነው?
8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ዮሴፍ የተባለ ለጋስ ሰው፣ ይሖዋ እንዲጠቀምበት ራሱን አቅርቦ ነበር። (ሥራ 4:36, 37) ዮሴፍ ሌሎችን በማጽናናት ረገድ የተዋጣለት ስለነበር ሳይሆን አይቀርም ሐዋርያት “የመጽናናት ልጅ” የሚል ትርጉም ያለው በርናባስ የሚል ስም ሰጥተውት ነበር። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ሳኦል ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ብዙዎቹ ወንድሞች እሱን ለመቅረብ ፈርተው ነበር፤ ምክንያቱም ሳኦል ጉባኤዎችን በማሳደድ ይታወቅ ነበር። ይሁን እንጂ አፍቃሪ የሆነው በርናባስ ሳኦልን ረዳው፤ ሳኦል፣ በርናባስ ላሳየው ደግነት በጣም አመስጋኝ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። (ሥራ 9:21, 26-28) ከጊዜ በኋላ፣ በኢየሩሳሌም ያሉት ሽማግሌዎች ርቃ በምትገኘው በሶርያ አንጾኪያ ያሉትን ወንድሞች ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ተሰማቸው። ታዲያ ይህን ኃላፊነት እንዲወጣ ማንን ላኩ? የላኩት በርናባስን ነው! ደግሞም ጥሩ ምርጫ አድርገዋል። በርናባስ “ሁሉም በጽኑ ልብ ለጌታ ታማኞች ሆነው እንዲቀጥሉ” እንዳበረታታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሥራ 11:22-24) ዛሬም በተመሳሳይ ይሖዋ ለእምነት ባልንጀሮቻችን “የመጽናናት ልጅ” እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ወንድሞቻችንን እንድናጽናና ሊጠቀምብን ይችላል። አሊያም የታመመን ወይም የመንፈስ ጭንቀት ያለበትን ሰው በአካል ሄደን ወይም ስልክ ደውለን የሚያበረታታ ሐሳብ እንድናካፍለው ያነሳሳን ይሆናል። ይሖዋ ልክ እንደ በርናባስ አንተንም እንዲጠቀምብህ ራስህን ታቀርባለህ?—1 ተሰ. 5:14
9. ይሖዋ፣ ቫሲሊ የተባለን አንድ ወንድም ብቃት ያለው መንፈሳዊ እረኛ እንዲሆን ከረዳበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?
9 ይሖዋ፣ ቫሲሊ የተባለን አንድ ወንድም ብቃት ያለው መንፈሳዊ እረኛ እንዲሆን ረድቶታል። ቫሲሊ በ26 ዓመቱ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እንዲያገለግል ሲሾም፣ ጉባኤውን በተለይም አስቸጋሪ ሁኔታ የገጠማቸውን የጉባኤውን አባላት በመንፈሳዊ ለመርዳት ብቃት እንደሌለው ስለተሰማው ፍርሃት አድሮበት ነበር። ይሁን እንጂ ተሞክሮ ካላቸው ሽማግሌዎች ጋር በማገልገሉ እንዲሁም በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት በመካፈሉ ግሩም ሥልጠና ማግኘት ችሏል። ቫሲሊ እድገት ለማድረግ በትጋት ሠርቷል። ለምሳሌ፣ ሊደርስባቸው የሚችል ትናንሽ ግቦች አወጣ። እያንዳንዱ ግብ ላይ መድረስ ሲችል ቀስ በቀስ ፍርሃቱን ማሸነፍ ቻለ። በአሁኑ ወቅት ቫሲሊ እንዲህ ይላል፦ “ያን ጊዜ ያስፈራኝ የነበረው ነገር አሁን ከፍተኛ ደስታ ያስገኝልኛል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን የሚያጽናና ተስማሚ ጥቅስ እንዳገኝ ይሖዋ ሲረዳኝ በጣም እደሰታለሁ።” ወንድሞች፣ እናንተም እንደ ቫሲሊ ይሖዋ እንዲጠቀምባችሁ ራሳችሁን ካቀረባችሁ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል የሚያስፈልገውን ችሎታ ይሰጣችኋል።
አንዳንድ ሴቶች ምን መሆን ችለዋል?
10. አቢጋኤል ምን አድርጋለች? እሷ ከተወችው ምሳሌስ ምን ትምህርት አግኝታችኋል?
10 ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ከንጉሥ ሳኦል እየሸሹ ስለነበር እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። የዳዊት ሰዎች፣ ናባል የተባለውን ሀብታም እስራኤላዊ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ምግብ እንዲሰጣቸው ጠየቁት። እነዚህ ሰዎች ናባልን ለመጠየቅ ያልፈሩት፣ በምድረ በዳ ለነበሩ በጎቹ ጥበቃ አድርገውላቸው ስለነበር ነው። ስግብግብ የሆነው ናባል ግን ምንም ነገር መስጠት አልፈለገም። ዳዊት በዚህ በጣም ስለተናደደ ናባልንም ሆነ በቤቱ ውስጥ ያለውን ወንድ ሁሉ ለመግደል ቆርጦ ተነሳ። (1 ሳሙ. 25:3-13, 22) የናባል ሚስት የሆነችው አቢጋኤል ግን አስተዋይና ውብ ሴት ነበረች። የበቀል እርምጃ በመውሰድ በራሱ ላይ የደም ዕዳ እንዳያመጣ ዳዊትን እግሩ ላይ ወድቃ ለመነችው፤ ይህ ትልቅ ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃ ነበር። ጉዳዩን በይሖዋ እጅ እንዲተወው በመጠየቅ በዘዴ ምክር ሰጠችው። አቢጋኤል በትሕትና የተናገረችው ሐሳብ እና ማስተዋል የተንጸባረቀበት ድርጊቷ የዳዊትን ልብ ነካው። አቢጋኤልን ወደ እሱ የላካት ይሖዋ እንደሆነ ዳዊት ተገነዘበ። (1 ሳሙ. 25:23-28, 32-34) አቢጋኤል፣ ይሖዋ እንዲጠቀምባት የሚያደርጉ ባሕርያት አዳብራ ነበር። ይሖዋ በዛሬው ጊዜም ዘዴኛና አስተዋይ የሆኑ ክርስቲያን እህቶችን የቤተሰባቸውንና የጉባኤያቸውን አባላት እንዲያበረታቱ ሊጠቀምባቸው ይችላል።—ምሳሌ 24:3፤ ቲቶ 2:3-5
11. የሻሉም ሴቶች ልጆች ምን አድርገዋል? በዘመናችንስ የእነሱን ምሳሌ እየተከተሉ ያሉት እነማን ናቸው?
11 ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ፣ የኢየሩሳሌም ቅጥር በተጠገነበት ወቅት ይሖዋ ለሥራው ከተጠቀመባቸው ሰዎች መካከል የሻሉም ሴቶች ልጆች ይገኙበታል። (ነህ. 2:20፤ 3:12) የሻሉም ልጆች አባታቸው ገዢ ቢሆንም ከባድና አደገኛ የሆነውን ሥራ ለማከናወን ፈቃደኞች ሆነዋል። (ነህ. 4:15-18) እነዚህ ሴቶች፣ “ራሳቸውን ዝቅ በማድረግ” በሥራው መካፈል ካልፈለጉት ታዋቂ የሆኑ የተቆአ ሰዎች የተለየ መንፈስ አሳይተዋል! (ነህ. 3:5) የሻሉም ሴቶች ልጆች ሥራው በ52 ቀናት ውስጥ ብቻ ሲጠናቀቅ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን አስቡት! (ነህ. 6:15) በዘመናችንም ፈቃደኛ የሆኑ እህቶች ለየት ባለ የቅዱስ አገልግሎት ዘርፍ ይኸውም ለይሖዋ አምልኮ የሚውሉ ሕንፃዎችን በመገንባቱና በመጠገኑ ሥራ መካፈላቸው ያስደስታቸዋል። የእነዚህ እህቶች ችሎታ፣ ቅንዓትና ታማኝነት ለሥራው መሳካት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
12. ይሖዋ ልክ እንደ ጣቢታ እኛንም ሊጠቀምብን የሚችለው እንዴት ነው?
12 ጣቢታ ለሌሎች በተለይም ለመበለቶች “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት” ልግስና እንድታሳይ ይሖዋ አነሳስቷታል። (ሥራ 9:36) ጣቢታ በጣም ለጋስና ደግ ስለነበረች፣ ስትሞት ብዙዎች እጅግ አዝነዋል። ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ ከሞት ሲያስነሳት በጣም ተደሰቱ። (ሥራ 9:39-41) ከጣቢታ ምን ትምህርት እናገኛለን? ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን፣ ወንዶችም ሆንን ሴቶች ሁላችንም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን የሚጠቅሙ ነገሮች ማከናወን እንችላለን።—ዕብ. 13:16
13. ይሖዋ፣ ሩት የተባለችን ዓይናፋር እህት የተጠቀመባት እንዴት ነው? ከዚህ ጋር በተያያዘስ ሩት ምን ብላለች?
13 ሩት የተባለች አንዲት ዓይናፋር እህት፣ ሚስዮናዊ ለመሆን ትመኝ ነበር። ሩት ትንሽ ልጅ ሳለች ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው በፍጥነት እየሄደች ትራክቶችን ታሰራጭ ነበር። “ይህ ሥራ በጣም ያስደስተኝ ነበር” ብላለች። በሌላ በኩል ግን ከቤት ወደ ቤት ስትሄድ ሰዎቹን ማነጋገርና ስለ አምላክ መንግሥት መስበክ ይከብዳት ነበር። ሩት ዓይናፋር ብትሆንም እንኳ በ18 ዓመቷ የዘወትር አቅኚ ሆነች። በ1946 በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብታ የሠለጠነች ሲሆን በኋላ ላይ በሃዋይና በጃፓን አገልግላለች። ይሖዋ በእነዚህ አገሮች ምሥራቹን በማስፋፋት ረገድ ብዙ ሥራ እንድታከናውን ይህችን እህት ተጠቅሞባታል። ሩት ወደ 80 ለሚጠጉ ዓመታት በአገልግሎት ስትካፈል ከቆየች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። ዓይናፋርነቴን እንዳሸንፍ ረድቶኛል። ይሖዋ በእሱ የሚታመንን ማንኛውንም ሰው ሊጠቀምበት እንደሚችል ሙሉ እምነት አለኝ።”
ይሖዋ እንዲጠቀምባችሁ ፍቀዱ
14. በቆላስይስ 1:29 መሠረት ይሖዋ እንዲጠቀምብን ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
14 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ፣ የተለያዩ ሚናዎችን እንዲጫወቱ አገልጋዮቹን ተጠቅሞባቸዋል። አንተንስ ምን እንድትሆን ያደርግህ ይሆን? ይህ በአብዛኛው የተመካው ጥረት ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆንህ ላይ ነው። (ቆላስይስ 1:29ን አንብብ።) ራስህን በፈቃደኝነት ካቀረብክ ይሖዋ ቀናተኛ ወንጌላዊ፣ ውጤታማ አስተማሪ፣ ጥሩ አጽናኝ፣ የተዋጣለት ሠራተኛ፣ አሳቢ ወዳጅ ወይም ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል።
15. በ1 ጢሞቴዎስ 4:12, 15 ላይ በተገለጸው መሠረት በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣት ወንድሞች ይሖዋ ምን ለማድረግ እንዲረዳቸው መጸለያቸው አስፈላጊ ነው?
15 ዕድሜያችሁ ለአካለ መጠን እየደረሰ ያለ ወጣት ወንዶችስ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? የጉባኤ አገልጋይ በመሆን ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል የሚያስችል አቅም ያላቸው ወንዶች በጣም ያስፈልጋሉ። በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ከጉባኤ አገልጋዮች ይልቅ የሽማግሌዎች ቁጥር ይበልጣል። እናንት ወጣት ወንድሞች፣ በጉባኤ ውስጥ ተጨማሪ ኃላፊነት የመቀበል ፍላጎት ማዳበር ትችሉ ይሆን? አንዳንድ ወንድሞች “አስፋፊ ሆኜ ካገለገልኩ ይበቃኛል” ይላሉ። አንተም እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚያስፈልገውን ብቃት የማሟላት ፍላጎት ለማዳበር እንዲረዳህ እና እሱን በሙሉ ልብህ ለማገልገል የሚያስችል ኃይል እንዲሰጥህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው። (መክ. 12:1) እርዳታህ በጣም ያስፈልገናል!—1 ጢሞቴዎስ 4:12, 15ን አንብብ።
16. ይሖዋን ምን ልንጠይቀው ይገባል? ለምንስ?
16 ይሖዋ፣ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር እንድትሆን ሊያደርግህ ይችላል። እንግዲያው የእሱን ሥራ የማከናወን ፍላጎት እንዲያድርብህ ለምነው፤ ከዚያም የሚያስፈልግህን ኃይል እንዲሰጥህ ጠይቀው። በየትኛውም ዕድሜ ላይ የምትገኝ ቢሆን በአሁኑ ወቅት ይሖዋን ለማክበር ጊዜህን፣ ጉልበትህንና ንብረትህን ተጠቀምበት። (መክ. 9:10) በፍርሃት ወይም ብቁ አይደለሁም በሚል ስሜት የተነሳ፣ በይሖዋ አገልግሎት ምርጥህን ለመስጠት የሚያስችሉህ ግሩም አጋጣሚዎች አያምልጡህ። አፍቃሪ የሆነው አባታችን የሚገባውን ክብር እንዲያገኝ ለማድረግ ትንሽም ቢሆን አስተዋጽኦ ማበርከት መቻላችን እንዴት ያለ ግሩም መብት ነው!
መዝሙር 127 ምን ዓይነት ሰው መሆን አለብኝ?
a በይሖዋ አገልግሎት የምታከናውነው ነገር በቂ እንዳልሆነ ይሰማሃል? ይሖዋ አሁንም ሊጠቀምብህ እንደሚችል ትጠራጠራለህ? አሊያም ደግሞ ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ እሱን የበለጠ ለማገልገል ራስህን ማቅረብህ ያን ያህል አስፈላጊ እንዳልሆነ ይሰማሃል? ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም መሆን የሚያስፈልግህን እንድትሆን ሲል ፍላጎት እንዲያድርብህ የሚያደርገውም ሆነ ኃይል የሚሰጥህ በየትኞቹ መንገዶች እንደሆነ በዚህ ርዕስ ላይ ይብራራል።
b ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች ቢሆንም የተናገረው ሐሳብ ለሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች ይሠራል።