የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ጋብቻ የዕድሜ ልክ ጥምረት ሊሆን ይገባዋልን?
ምን ጥያቄ አለው። ጋብቻ ሲፈጸም ተጋቢዎቹ “በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ” እና “ሞት እስኪለየን ድረስ” በማለት ቃለ መሐላ ይገቡ የለምን? አዎን፣ ብዙውን ጊዜ የጋብቻ መሐላዎች ሙሽራውና ሙሽሪት ለዕድሜ ልክ መጣመራቸውን ይገልጻሉ። ሆኖም ብዙዎች የገቡትን ቃል ኪዳን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው አይሰማቸውም። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትዳሮች አንዳንዶቹ ከጥቂት ወራት በኋላ ሌሎች ደግሞ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ እየፈረሱ ነው። ጋብቻ አክብሮት እያጣ የመጣው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መልሱን ይሰጠናል።
እስቲ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-3ን አንብብና በዚህ ዓለም ከምታየው ነገር ጋር አወዳድር። ጥቅሱ በከፊል “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ . . . የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ” ይላል። ይህ ትንቢት በሚያስደንቅ መንገድ ትክክለኛ ፍጻሜውን አግኝቷል። በአሁኑ ጊዜ እየተከሰተ ያለው ከፍተኛ የፍቺ ቁጥር እንደሚያረጋግጠው እነዚህ ባሕርያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የጋብቻን ግንኙነት አዳክመውታል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ብዙ ሰዎች ለጋብቻ አክብሮት የላቸውም። በዚህ አንጻር ራሳችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን:- ጋብቻን በቁም ነገር መመልከት ይኖርብናልን? ጋብቻ ቅዱስ ነው ሊባል ይችላልን? ክርስቲያኖች ለጋብቻ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ ለባለ ትዳሮች ምን እርዳታ ያበረክታል?
የአምላክ አመለካከት ተቀይሯልን?
አምላክ ጋብቻን በመሠረተ ጊዜ ጥምረቱ ጊዜያዊ እንደሆነ አልተናገረም። የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት እንዴት እንዳጣመረ በዘፍጥረት 2:21-24 ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሲሆን እዚያም ላይ መፋታት ወይም መለያየት እንደሚችሉ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ ቁጥር 24 “ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላል። ይህ ጥቅስ ምን ትርጉም አለው?
የሰው አካል የተለያዩ ሕብረ ሕዋሳት እርስ በርስ እንዴት እንደተያያዙና አጥንቶች እርስ በርስ እንዳይፋተጉ ተደርገው እንዴት በጥብቅ እንደተጋጠሙ ተመልከት። እንዴት ያለ አንድነት ነው! እንዴት ያለ ዘላቂ ውህደት ነው! ይሁን እንጂ ይህ ወደር የለሽ አካል ከባድ ጉዳት ቢደርስበት ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል! ስለሆነም በዘፍጥረት 2:24 ላይ የሚገኘው “አንድ ሥጋ” የሚለው አገላለጽ ጋብቻ ያለውን የተቀራረበ ዝምድናና ዘላቂ ጥምረት ይጠቁማል። እንዲሁም ጥምረቱ እንዲፈርስ ከተደረገ ከፍተኛ ሥቃይ መከተሉ እንደማይቀር በግልጽ ያስጠነቅቃል።
ባለፉት ሺህ ዓመታት የደረሱት የለውጥ ማዕበሎች የሰው ልጅ ጋብቻን በተመለከተ ባለው አመለካከት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተሉበት ቢሆንም እንኳ አምላክ አሁንም ድረስ ጋብቻን የሚመለከተው የዕድሜ ልክ ቁርኝት እንደሆነ አድርጎ ነው። ከዛሬ 2, 400 ዓመታት በፊት አንዳንድ አይሁዳውያን ወንዶች የልጅነት ሚስቶቻቸውን ትተው ወጣት ሚስቶችን አግብተው ነበር። አምላክ እንዲህ ያለውን ልማድ በማውገዝ በነቢዩ ሚልክያስ በኩል “መንፈሳችሁን ጠብቁ፣ ማንም የልጅነት ሚስቱን አያታልል። መፋታትን እጣላለሁ ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር” በማለት ተናግሯል።—ሚልክያስ 2:15, 16
ከአራት መቶ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ኢየሱስ ዘፍጥረት 2:24ን በመጥቀስና በኋላም “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” ብሎ በመናገር አምላክ ለጋብቻ የነበረው የመጀመሪያ አመለካከት እንዳልተለወጠ አረጋግጧል። (ማቴዎስ 19:5, 6) ከብዙ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሚስትም ከባልዋ አትለያይ” እንዲሁም “ባልም ሚስቱን አይተዋት” በማለት መመሪያ ሰጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) እነዚህ ጥቅሶች አምላክ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት በትክክል ይገልጻሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ጋብቻ እንዲያከትም የሚፈቅድባቸው ሁኔታዎች ይኖራሉን? አዎን፣ ከሁለቱ የትዳር ጓደኛሞች አንደኛው ከሞተ ጋብቻው ያከትማል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ዝሙት ከተፈጸመና ተበዳዩ ወገን ፍቺን ከመረጠ ጋብቻው ሊፈርስ ይችላል። (ማቴዎስ 19:9) በእነዚህ ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት አንድ ላይ መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታታል።
ጋብቻን ዘላቂ ጥምረት ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?
አምላክ፣ ትዳር የመከራ ሕይወት የሚገፋበት ሳይሆን ደስታ የሰፈነበት እንዲሆን ይፈልጋል። ባልና ሚስት ችግሮቻቸውን በጋራ እንዲፈቱና አብረው በመኖራቸው ከልብ የሚደሰቱ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ቃሉ ደስተኛና ዘላቂ ትዳር ለመምራት የሚያስችል መመሪያ ይዟል። እባክህ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት።
ኤፌሶን 4:27:- “በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ።”a በትዳሩ ደስተኛ የሆነ አንድ ሰው ይህ ጥቅስ በእርሱና በባለቤቱ መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ቶሎ ብለው እንዲፈቱ እንደሚረዳቸው ይሰማዋል። “የተፈጠረ አንድ አለመግባባት እንቅልፍ ከነሳህ ችግር አለ ማለት ነው። ችግሩ እንዲቀጥል መፍቀድ አይኖርብህም” ብሏል። እሱና ባለቤቱ አንዳንድ ጊዜ እስከ እኩለ ሌሊት ተቀምጠው ችግሮቹን አንድ በአንድ ይወያዩባቸዋል። ይህም ውጤት አስገኝቶላቸዋል። አክሎም “የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ ግሩም ውጤት ያስገኛል” ብሏል። ይህ ሰውና ባለቤቱ እንዲህ ማድረጋቸው በትዳር ዓለም 42 የደስታ ዓመታት እንዲያሳልፉ ረድቷቸዋል።
ቆላስይስ 3:13:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ . . . [“በነፃ፣” NW ] ይቅር ተባባሉ።” አንድ ባል እሱና ባለቤቱ ይህንን እንዴት ተግባራዊ እንዳደረጉ ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “እያንዳንዱ ሰው ሌላውን ቅር ሊያሰኝ የሚችል አንድ ዓይነት ጠባይ ሊኖረው ስለሚችል የትዳር ጓደኞች ምንም ዓይነት ስህተት ሳይሠሩ አንዱ ሌላውን ሊያስቆጣ ይችላል። እነዚህ ነገሮች በመካከላችን ገብተው እንዲያራርቁን ባለመፍቀድ አንዳችን ሌላውን በትዕግሥት እንይዛለን።” እነዚህ ባልና ሚስት በትዳር በቆዩባቸው 54 ዓመታት ይህ አመለካከት እንደጠቀማቸው ምንም አያጠራጥርም!
እነዚህን የመሰሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረጉ ባልና ሚስቶች የተጣመሩበትን ሰንሰለት ያጠናክረዋል። በመሆኑም ጋብቻቸው አስደሳች፣ አርኪና ዘላቂ ሊሆን ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጀመሪያው መቶ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ በነበረው የሰዓት አቆጣጠር መሠረት አንድ ቀን የሚያበቃው ፀሐይ ስትጠልቅ ነው። ስለሆነም ጳውሎስ እያንዳንዱ ቀን ከማለፉ በፊት እርቅ እንዲፈጥሩ አንባቢዎቹን ማሳሰቡ ነበር።