ምዕራፍ ሦስት
ትዳርን ዘላቂ ለማድረግ የሚረዱ ሁለት ቁልፍ ነገሮች
1, 2. (ሀ) ጋብቻ የተቋቋመው ለምን ያህል ጊዜ እንዲቆይ ታስቦ ነው? (ለ) ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት በጋብቻ ባስተሳሰራቸው ጊዜ ጥምረታቸው ጊዜያዊ እንደሚሆን የሚያመለክት ምንም ነገር አልነበረም። አዳምና ሔዋን በጋብቻ እንዲጣመሩ የተደረገው ዕድሜ ልካቸውን አብረው እንዲኖሩ ነው። (ዘፍጥረት 2:24) አምላክ ክብራማ ለሆነ ትዳር ያወጣው መስፈርት አንድን ወንድና አንዲትን ሴት የሚያስተሳስር ነው። በቅዱስ ጽሑፋዊው መመሪያ መሠረት ባልና ሚስት ተፋትተው ሌላ ማግባት የሚችሉት አንዳቸው ወይም ሁለቱም ከባድ የጾታ ብልግና የፈጸሙ እንደሆነ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 5:32
2 ሁለት ግለሰቦች አንድ ላይ ሆነው ገደብ ለሌለው ረጅም ዘመን በደስታ መኖር ይችላሉን? አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሁለት ወሳኝ ወይም ቁልፍ ነገሮች ይጠቅሳል። ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ እነዚህን ነገሮች ከተጠቀሙባቸው ደስታና ብዙ በረከት ማግኘት ይችላሉ። እነዚህ ቁልፍ ነገሮች ምንድን ናቸው?
የመጀመሪያው ቁልፍ
3. የትዳር ጓደኛሞች ሊያዳብሯቸው የሚገቡ ሦስት የፍቅር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
3 የመጀመሪያው ቁልፍ ነገር ፍቅር ነው። የሚገርመው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለያዩ የፍቅር ዓይነቶች ተገልጸዋል። አንዱ በቅርብ ጓደኛሞች መካከል የሚንጸባረቅ ለአንድ ሰው በግለሰብ ደረጃ የምናሳየው የጋለ የፍቅር ዓይነት ነው። (ዮሐንስ 11:3) ሌላው ደግሞ በቤተሰብ አባላት መካከል ያለ ፍቅር ነው። (ሮሜ 12:10) ሦስተኛው አንድ ሰው ለተቃራኒ ጾታ ሊያድርበት የሚችለው ፍቅር ነው። (ምሳሌ 5:15-20) እርግጥ ነው፣ ባልና ሚስት እነዚህን የፍቅር ዓይነቶች ማዳበር አለባቸው። ሆኖም ከእነዚህ ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ አራተኛ የፍቅር ዓይነት አለ።
4. አራተኛው የፍቅር ዓይነት ምንድን ነው?
4 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በተጻፉበት በመጀመሪያው ቋንቋ ለዚህ ለአራተኛው የፍቅር ዓይነት የገባው ቃል አጋፔ የተባለው ነው። ይህ ቃል “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በሚለው በአንደኛ ዮሐንስ 4:8 ላይ ተሠርቶበታል። በእርግጥም “እርሱ [አምላክ] አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።” (1 ዮሐንስ 4:19) አንድ ክርስቲያን ይህን ፍቅር በመጀመሪያ ለይሖዋ አምላክ ከዚያም ለሰዎች የማሳየትን ባሕርይ ያዳብራል። (ማርቆስ 12:29-31) አጋፔ የተባለው ቃል በኤፌሶን 5:2 ላይም በሚከተለው መንገድ ተሠርቶበታል:- “ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ . . . ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ።” ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የእውነተኛ ተከታዮቹ መለያ እንደሚሆን ተናግሯል:- “እርስ በርሳችሁ ፍቅር [አጋፔ] ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:35) አጋፔ በ1 ቆሮንቶስ 13:13 ላይም እንዴት እንደተሠራበት ልብ በሉ:- “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር [አጋፔ] ነው።”
5, 6. (ሀ) ፍቅር ከእምነትና ከተስፋ የሚበልጠው ለምንድን ነው? (ለ) ፍቅር ትዳርን ዘላቂ ለማድረግ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው በየትኞቹ ምክንያቶች የተነሳ ነው?
5 ይህን አጋፔ የተባለውን የፍቅር ዓይነት ከእምነትና ከተስፋ እንዲበልጥ ያደረገው ምንድን ነው? በመሠረታዊ ሥርዓቶች፣ ያውም በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙ ትክክለኛ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ በመሆኑ ነው። (መዝሙር 119:105) መልካም የሚደረግለት ሰው የሚገባው ሆነም አልሆነ ከአምላክ አመለካከት አንፃር ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር ለሌሎች ማድረግ የሚጠይቅ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አሳቢነት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የትዳር ጓደኛሞች የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንዲከተሉ ይረዳቸዋል:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ።” (ቆላስይስ 3:13) የሚዋደዱ የትዳር ጓደኛሞች ‘አንዳቸው ለሌላው የጠለቀ ፍቅር [አጋፔ]’ ያላቸው ከመሆኑም በላይ ይህን ፍቅር ያዳብሩታል፤ ምክንያቱም “ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥሮስ 4:8) ፍቅር ስህተቶችን እንደሚሸፍን ልብ በሉ። ፍጹም ያልሆነ ማንኛውም ሰው ስህተት መሥራቱ ስለማይቀር ፍቅር ስህተትን ጨርሶ ያስወግዳል ማለት አይደለም።—መዝሙር 130:3, 4፤ ያዕቆብ 3:2
6 ባልና ሚስት እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ለአምላክና አንዳቸው ለሌላው የማሳየትን ባሕርይ በሚያዳብሩበት ጊዜ ‘ፍቅር ለዘወትር የማይወድቅ’ በመሆኑ ትዳራቸው ዘላቂና አስደሳች ይሆናል። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ፍቅር “ፍጹም የአንድነት ማሠሪያ ነው።” (ቆላስይስ 3:14 NW) ያገባችሁ ከሆናችሁ እናንተም ሆናችሁ የትዳር ጓደኛችሁ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማዳበር የምትችሉት እንዴት ነው? የአምላክን ቃል አንድ ላይ ሆናችሁ በማንበብ ተነጋገሩበት። ኢየሱስ የተወውን የፍቅር ምሳሌ በማጥናት እርሱን ለመምሰል፣ እንደ እሱ ለማሰብና ለማድረግ ጣሩ። በተጨማሪም የአምላክን ቃል መማር በምትችሉባቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ተገኙ። ከዚህም ሌላ አምላክ የቅዱስ መንፈሱ ፍሬ የሆነውን እንዲህ ዓይነቱን የላቀ የፍቅር ዓይነት ማዳበር ትችሉ ዘንድ እንዲረዳችሁ በጸሎት ጠይቁት።—ምሳሌ 3:5, 6፤ ዮሐንስ 17:3፤ ገላትያ 5:22፤ ዕብራውያን 10:24, 25
ሁለተኛው ቁልፍ
7. አክብሮት ማሳየት ማለት ምን ማለት ነው? በትዳር ውስጥ አክብሮት ማሳየት ያለበትስ ማን ነው?
7 ሁለት የተጋቡ ሰዎች በእርግጥ እርስ በርሳቸው የሚዋደዱ ከሆነ አንዳቸው ለሌላው አክብሮት ይኖራቸዋል፤ አክብሮት ማሳየት ደግሞ አንድ ትዳር አስደሳች እንዲሆን የሚያደርግ ሁለተኛው ቁልፍ ነገር ነው። አክብሮት የሚለው ቃል “ለሌሎች ከፍ ያለ ግምትና ቦታ መስጠት” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። የአምላክ ቃል ባሎችንና ሚስቶችን ጨምሮ ሁሉም ክርስቲያኖች ‘እርስ በርስ በመከባበር ረገድ ግንባር ቀደሞች’ እንዲሆኑ ይመክራል። (ሮሜ 12:10) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንዲሁም እናንተ ባሎች ሆይ፣ . . . ልክ እንደ ተሰባሪ ዕቃ ሚስቶቻችሁን በክብር በመያዝ ከእነርሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ።” (1 ጴጥሮስ 3:7 NW) ሚስትም “ለባልዋ የጠለቀ አክብሮት” እንዲኖራት ተመክራለች። (ኤፌሶን 5:33 NW) አንድን ሰው የምታከብሩት ከሆነ ለዚያ ሰው ደግ ከመሆናችሁም በላይ ክብሩን ትጠብቃላችሁ፣ የሚሰጠውን ሐሳብ ከፍ አድርጋችሁ ትመለከታላችሁ፣ እንዲሁም የሚጠይቃችሁን ምክንያታዊ ነገር ሁሉ በፈቃደኝነት ታሟሉለታላችሁ ማለት ነው።
8-10. አክብሮት ማሳየት የጋብቻ ጥምረት እንዳለ እንዲቀጥልና አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርግባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
8 ትዳራቸው አስደሳች እንዲሆን የሚፈልጉ ሁሉ ‘ለራሳቸው የሚጠቅመውን ብቻ ሳይሆን [ለትዳር ጓደኛቸውም] የሚጠቅመውን በመመልከት’ አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ። (ፊልጵስዩስ 2:4) ለራሳቸው ብቻ ጠቃሚ የሆነውን አይመለከቱም፤ ይህ ራስ ወዳድነት ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ለትዳር ጓደኛቸውም የተሻለ የሆነውን ነገር ያስባሉ። እንዲያውም የትዳር ጓደኛቸውን ፍላጎት ያስቀድማሉ።
9 የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው አክብሮት ማሳየታቸው በአመለካከት ደረጃ በመካከላቸው ልዩነት መኖሩን አምነው እንዲቀበሉ ይረዳቸዋል። ሁለት ሰዎች በሁሉም ነገር ላይ አንድ ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው መጠበቁ ምክንያታዊ አይደለም። ለባልየው አስፈላጊ የሆነው ነገር ለሚስትየዋ ያን ያህል አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፤ ልክ እንደዚሁም ሚስትየዋ የምትወደው ነገር ባልየው የማይወደው ሊሆን ይችላል። ሆኖም አመለካከታቸውና ምርጫቸው ከይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እስካልተጋጨ ድረስ አንዳቸው የሌላውን አመለካከትና ምርጫ ማክበር ይኖርባቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:16፤ ከፊልሞና 14 ጋር አወዳድሩ።) በተጨማሪም በሰዎች ፊትም ሆነ በግል ግለሰቡን የሚያቃልሉና ዝቅ የሚያደርጉ አስተያየቶችን ወይም ቀልዶችን ከመናገር በመቆጠብ አንዳቸው የሌላውን ክብር መጠበቅ አለባቸው።
10 አዎ፣ የትዳር ጓደኛሞች ለአምላክና አንዳቸው ለሌላው የሚያሳዩት ፍቅር እንዲሁም እርስ በርስ መከባበራቸው ትዳራቸው ስኬታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሁለት ቁልፍ ነገሮች ናቸው። እነዚህን ቁልፍ ነገሮች በትዳር ሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ አንዳንድ መስኮች መጠቀም የሚቻለው እንዴት ነው?
የክርስቶስ ዓይነት የራስነት ሥልጣን
11. በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረት በትዳር ውስጥ ራስ የሚሆነው ማን ነው?
11 ወንድ የተዋጣለት የቤተሰብ ራስ እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ባሕርያትን ይዞ እንደተፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። በመሆኑም ወንድየው የሚስቱንና የልጆቹን መንፈሳዊና ሥጋዊ ደህንነት በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ነው። የይሖዋን ፈቃድ የሚያንጸባርቁ ሚዛናዊ ውሳኔዎችን ማድረግ የሚጠበቅበት ከመሆኑም ሌላ በአምላካዊ አኗኗር ጥሩ ምሳሌ መሆን አለበት። “ሚስቶች ሆይ፣ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ . . . ባል የሚስት ራስ ነውና።” (ኤፌሶን 5:22, 23) ይሁን እንጂ ባልየውም በእርሱ ላይ ሥልጣን ያለው ራስ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ጥበበኛ የሆነ ባል የእሱ ራስ የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን በመምሰል የራስነት ሥልጣኑን እንዴት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ይማራል።
12. ኢየሱስ ተገዥነትን በማሳየትና የራስነትን ሥልጣን በመጠቀም ረገድ ምን ጥሩ ምሳሌ ትቷል?
12 ኢየሱስም ራስ አለው፤ እርሱም ይሖዋ ነው። ኢየሱስ ለይሖዋ በሚገባ ይገዛል። “የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 5:30) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ኢየሱስ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው።” (ቆላስይስ 1:15) መሲሕ ሆኗል። የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ራስ እንደሚሆንና የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በመሾም ከመላእክት ሁሉ በላይ እንደሚሆን ያውቅ ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:9-11፤ ዕብራውያን 1:4) እንዲህ ያለ የላቀ ሥልጣንና ከፍ ያሉ ተስፋዎች ይጠብቁት የነበረ ቢሆንም ሰው ሆኖ የነበረው ኢየሱስ ኃይለኛ፣ ግትር ወይም ደግሞ ከሌሎች ብዙ የሚጠብቅ አልነበረም። ደቀ መዛሙርቱ ሊታዘዙት እንደሚገባ በየጊዜው በማሳሰብ ሥልጣኑን አላግባብ የሚጠቀም አምባገነን ሰው አልነበረም። ኢየሱስ በተለይ ለተጨቆኑት የሚራራና አፍቃሪ ነበር። “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴዎስ 11:28-30) ከእርሱ ጋር መሆን በጣም የሚያስደስት ነበር።
13, 14. አንድ አፍቃሪ የሆነ ባል ኢየሱስን በመምሰል የራስነት ሥልጣኑን የሚጠቀመው እንዴት ነው?
13 የቤተሰቡ ሕይወት አስደሳች እንዲሆን የሚፈልግ ባል የኢየሱስን ግሩም ባሕርያት ቢመረምር ጥሩ ይሆናል። ጥሩ ባል የራስነት ሥልጣኑን ሚስቱን ለማስፈራራት እንደ መሣሪያ አድርጎ አላግባብ በመጠቀም ኃይለኛና አምባገነን አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ሚስቱን ያፈቅራል እንዲሁም ያከብራታል። ምንም ስህተት የማይሠራው ኢየሱስ እንኳ ‘በልቡ ትሑት’ ከነበረ ስህተት ሊሠራ የሚችል አንድ ባል ደግሞ ይበልጥ ትሑት መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። ስህተት በሚሠራበት ጊዜ የሚስቱ ይቅር ባይነት ያስፈልገዋል። ስለዚህ ምንም እንኳ “ይቅርታ፣ ተሳስቻለሁ” ብሎ መናገሩ ከባድ ሊሆን ቢችልም ትሑት የሆነ ባል ስህተቱን አምኖ ይቅርታ ይጠይቃል። አንዲት ሚስት ኩሩና እልኸኛ ከሆነ ባል ይልቅ ትሑትና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ባል ያለውን የራስነት ሥልጣን ማክበር ይቀላታል። በአንጻሩም ባልዋን የምታከብር ሚስት እርሷም ስህተት በምትሠራበት ጊዜ ይቅርታ ትጠይቃለች።
14 አምላክ ሴትን ሲፈጥር ትዳርን አስደሳች ለማድረግ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸውን ጥሩ ጥሩ ባሕርያት ሰጥቷታል። ጥበበኛ የሆነ ባል ይህን የሚገነዘብ በመሆኑ እነዚህን ባሕርያት እንዳትጠቀምባቸው አፍኖ አይዛትም። ብዙዎቹ ሴቶች ከወንዶች የበለጠ የሚራሩና የሌሎች ሰዎች ስሜትና ችግር በጣም የሚሰማቸው ናቸው፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ ቤተሰብን በሚገባ ለመያዝና ሰብዓዊ ዝምድናዎችን ለማጠናከር በጣም አስፈላጊ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ሴቷ ቤቱን ለኑሮ ተስማሚና አመቺ የማድረግ ልዩ ችሎታ አላት። በምሳሌ ምዕራፍ 31 ላይ የተገለጸችው “ባለሙያ ሚስት” [የ1980 ትርጉም] ብዙ ጥሩ ባሕርያትና ግሩም ተሰጥኦዎች አሏት፤ ቤተሰቧም በእነዚህ ባሕርያትና ተሰጥኦዎች ሙሉ በሙሉ ተጠቅሟል። ለምን? ምክንያቱም የባልዋ ልብ “ይታመንባታል።”—ምሳሌ 31:10, 11
15. አንድ ባል ለሚስቱ ክርስቶስ ያሳየውን ዓይነት ፍቅርና አክብሮት ማሳየት የሚችለው እንዴት ነው?
15 በአንዳንድ ባህሎች ባል ያለው ሥልጣን ከልክ በላይ ስለሚጋነን ጥያቄ መጠየቅ እንኳ አክብሮት የጎደለው ድርጊት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። ሚስቱን ልክ እንደ ባሪያ አድርጎ ሊይዛት ይችላል። ባል የራስነት ሥልጣኑን በዚህ መንገድ አላግባብ መጠቀሙ ከሚስቱ ጋር ያለውን ብቻ ሳይሆን ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ጭምር ያሻክርበታል። (ከ1 ዮሐንስ 4:20, 21 ጋር አወዳድር።) በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ባሎች ቤተሰባቸውን የመምራት ኃላፊነታቸውን ችላ በማለት ሚስቶቻቸው በቤተሰቡ ላይ እንዲሠለጥኑ ያደርጋሉ። ለክርስቶስ በሚገባ የሚገዛ ባል ሚስቱን አይጨቁናትም ወይም ደግሞ ክብሯን አይገፍም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የራሱን ጥቅም በመሠዋት ያሳየውን ፍቅር ይኮርጃል፤ በተጨማሪም የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር ይሠራበታል:- “ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደደና ራሱን ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ።” (ኤፌሶን 5:25 የ1980 ትርጉም) ክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮቹን በጣም ይወዳቸው ስለነበረ ነፍሱን ለእነርሱ አሳልፎ ሰጥቷል። አንድ ጥሩ ባል ከሚስቱ ብዙ ነገር ከመጠበቅ ይልቅ ለእሷ ጥቅም በማሰብ የኢየሱስን ዓይነት ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ጠባይ ለማሳየት ይጥራል። አንድ ባል ለክርስቶስ ሲገዛና የክርስቶስ ዓይነት ፍቅርና አክብሮት ሲያሳይ ሚስቱ ራሷን ለእሱ ለማስገዛት ትገፋፋለች።—ኤፌሶን 5:28, 29, 33
የሚስት ተገዥነት
16. አንዲት ሚስት ከባሏ ጋር ባላት ግንኙነት የትኞቹን ባሕርያት ማሳየት ይኖርባታል?
16 አዳም ከተፈጠረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ “እግዚአብሔር አምላክም አለ:- ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፤ የሚመቸውን [“ማሟያ የምትሆነውን፣” NW] ረዳት እንፍጠርለት።” (ዘፍጥረት 2:18) አምላክ ሔዋንን የፈጠረው ተፎካካሪ እንድትሆን ሳይሆን “ማሟያ” እንድትሆን ነው። ጋብቻ የተመሠረተው እርስ በርሳቸው በሚፎካከሩ ሁለት ካፒቴኖች እንደሚነዳ መርከብ እንዲሆን ታስቦ አይደለም። ባልየው የራስነት ሥልጣኑን ፍቅራዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ያለበት ሲሆን ሚስትየዋ ደግሞ ፍቅርና አክብሮት ማሳየት እንዲሁም በፈቃደኝነት መገዛት ይኖርባታል።
17, 18. አንዲት ሚስት ለባሏ እውነተኛ ረዳት መሆን የምትችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
17 ይሁን እንጂ ጥሩ ሚስት ከመገዛትም በተጨማሪ ሌላ የምታደርገው ነገር አለ። ባልዋ የሚያደርጋቸውን ውሳኔዎች በመደገፍ ጥሩ ረዳት ሆና ለመገኘት ትጥራለች። እርግጥ የባልዋ ውሳኔ የምትስማማበት ዓይነት በሚሆንበት ጊዜ እንዲህ ማድረጉ አይከብዳትም። ሆኖም ውሳኔው የምትስማማበት ዓይነት በማይሆንበት ጊዜ እንኳ ለባልዋ ጥሩ ድጋፍ መስጠቷ ውሳኔው ይበልጥ ጥሩ ውጤት እንዲያስገኝ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።
18 አንዲት ሚስት ባልዋ ጥሩ የቤተሰብ ራስ እንዲሆን በሌሎች መንገዶችም ልትረዳው ትችላለች። ባልዋን ከመተቸት ወይም ደግሞ ፈጽሞ ሊያረካት እንደማይችል እንዲሰማው ከማድረግ ይልቅ ቤተሰቡን በግንባር ቀደምትነት በመምራት ለሚያደርገው ጥረት ያላትን አድናቆት ልትገልጽለት ትችላለች። ገንቢ የሆነ አመለካከት በመያዝ ከባልዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት በምታደርግበት ጊዜ “የዋህና ዝግተኛ መንፈስ” በባልዋ ፊት ብቻ ሳይሆን ‘በአምላክም ፊት ትልቅ ዋጋ’ ያለው መሆኑን ማስታወስ ይኖርባታል። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4፤ ቆላስይስ 3:12) ባልየው አማኝ ባይሆንስ? ሚስቶች ባሎቻቸው አማኞች ሆኑም አልሆኑ “የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፣ ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ ንጹሖች፣ በቤት የሚሠሩ፣ በጎዎች፣ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ” ቅዱሳን ጽሑፎች ማበረታቻ ይሰጣሉ። (ቲቶ 2:4, 5) ከሕሊና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ብቅ በሚሉበት ጊዜ አማኝ ያልሆነው ባል ጉዳዩ “በየዋህነትና በጥልቅ አክብሮት” [NW] እስከቀረበለት ድረስ በአብዛኛው የሚስቱን አቋም ማክበሩ አይቀርም። አንዳንድ የማያምኑ ባሎች ‘የሚስቶቻቸውን ንጹሕ አኗኗርና የጠለቀ አክብሮት በመመልከት ያለ ትምህርት በሚስቶቻቸው አኗኗር’ ተለውጠዋል።—1 ጴጥሮስ 3:1, 2, 15፤ 1 ቆሮንቶስ 7:13-16
19. አንዲት ሚስት ባሏ የአምላክን ሕግ የሚያስጥስ ድርጊት እንድትፈጽም ቢጠይቃት ምን ማድረግ ይኖርባታል?
19 አንድ ባል አምላክ የከለከለውን ነገር ሚስቱ እንድታደርግ ቢጠይቃትስ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ከተፈጠረ ታላቁ ገዥዋ አምላክ እንደሆነ ማስታወስ አለባት። ሐዋርያት የአምላክን ሕግ እንዲጥሱ ባለሥልጣኖች ባዘዟቸው ጊዜ የወሰዱትን አቋም ትከተላለች። ሥራ 5:29 ሐዋርያቱ ያደረጉትን ነገር እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ጴጥሮስና ሐዋርያትም መልሰው አሉ:- ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል።”
ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ
20. ፍቅርና አክብሮት በጣም አስፈላጊ የሆኑበት አንዱ ትልቅ መስክ የትኛው ነው?
20 ፍቅርና አክብሮት ማሳየት በሌላ የትዳር መስክ ማለትም በባልና ሚስት መካከል በሚኖረው የሐሳብ ልውውጥ ረገድም አስፈላጊ ነው። አፍቃሪ የሆነ ባል ሚስቱን ስለ ሥራዋ፣ ስላሉባት ችግሮች እንዲሁም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስላላት አመለካከት ያወያያታል። አንድ ባል ለሚስቱ እንዲህ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። ጊዜ ወስዶ ሚስቱን የሚያነጋግርና የምትለውን ከልቡ የሚያዳምጥ ባል ለእሷ ፍቅርና አክብሮት እንዳለው ያሳያል። (ያዕቆብ 1:19) አንዳንድ ሚስቶች ባሎቻችን አያጫውቱንም በማለት ያማርራሉ። ይህ በጣም ያሳዝናል። እርግጥ ነው፣ በዚህ ውጥረት ባየለበት ዘመን ባሎች ሥራ ይበዛባቸው ይሆናል፤ ከዚህም በተጨማሪ አንዳንድ ሚስቶች ባለው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የተነሳ ተቀጥረው ለመሥራት ይገደዱ ይሆናል። ቢሆንም ባልና ሚስት መነጋገርና መጫወት የሚችሉበት ጊዜ መመደብ አለባቸው። አለዚያ ግን በመካከላቸው መራራቅ ሊፈጠር ይችላል። ስሜታቸውንና ችግራቸውን የሚረዳላቸው ሰው ለማግኘት ሲሉ ከትዳር ውጪ ከሌላ ሰው ጋር ለመወዳጀት የሚገደዱበት ሁኔታ ከተፈጠረ የከፋ መዘዝ ሊደርስ ይችላል።
21. ሥርዓታማ አነጋገር ትዳርን አስደሳች ለማድረግ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?
21 ሚስቶችና ባሎች የሐሳብ ልውውጥ የሚያደርጉበት መንገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። “ያማረ ቃል . . . ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው።” (ምሳሌ 16:24) የትዳር ጓደኛችሁ አማኝ ሆነም አልሆነ የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይሠራል:- “ንግግራችሁ ሁልጊዜ፣ በጨው እንደ ተቀመመ፣ [ማራኪ በሆነ መንገድ ማለት ነው] በጸጋ ይሁን።” (ቆላስይስ 4:6) አንደኛው ወገን ችግር ገጥሞት ከነበረ ሌላኛው የትዳር ጓደኛ ደግነትና አሳቢነት የተሞላባቸው ጥቂት ቃላት መናገሩ ትልቅ ውጤት ሊኖረው ይችላል። “በወቅቱ በትክክል የተነገረ ቃል፣ በብር ላይ እንደፈሰሰ የወርቅ ጌጥ፣ ውበት ይኖረዋል።” (ምሳሌ 25:11 የ1980 ትርጉም) የድምፃችን ቃናና የቃላት ምርጫችን ወሳኝ ነው። ለምሳሌ ያህል በቁጣ መንፈስና በትእዛዝ መልክ አንዳቸው ሌላውን “በሩን ዝጊው/ጋው!” ይሉ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ግን በለዘበ አንደበትና አሳቢነት በተሞላበት ሁኔታ “እባክሽ/ህ በሩን ትዘጊው/ጋው?” ብለው ቢናገሩ ንግግራቸው ‘በጨው የተቀመመ’ ይሆናል።
22. ባልና ሚስት ዘወትር በመካከላቸው ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
22 የለዘበ አንደበት፣ ፈገግታና ፍቅራዊ ስሜት የሚንጸበረቅባቸው አካላዊ መግለጫዎች፣ ደግነት፣ አሳቢነትና ርኅራኄ በባልና ሚስት መካከል ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ባልና ሚስት በመካከላቸው ዘወትር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ እንዲኖር ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በግልጽ ለመናገር ነፃነት የሚሰማቸው ከመሆኑም ሌላ ቅር የሚያሰኙ ነገሮች ወይም ደግሞ ውጥረት ሲያጋጥማቸው አንዳቸው ሌላውን ማጽናናትና መርዳት ይችላሉ። የአምላክ ቃል “የተጨነቁትን ነፍሳት አጽናኗቸው” ሲል አጥብቆ ያሳስባል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) አንዳንድ ጊዜ ባል ሌላ ጊዜ ደግሞ ሚስት በሐዘን የሚዋጡባቸው ጊዜያት ይኖራሉ። በእነዚህ ጊዜያት አንዳቸው ሌላውን በመገንባት እርስ በርሳቸው ‘ሊጽናኑ’ ይችላሉ።—ሮሜ 15:2
23, 24. ፍቅርና አክብሮት በባልና ሚስት መካከል የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት አስተዋጽኦ የሚያደርጉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጡ።
23 የሚዋደዱና እርስ በርሳቸው የሚከባበሩ የትዳር ጓደኛሞች የማይስማሙበትን ነገር ሁሉ እንደ ትልቅ ችግር አድርገው አይመለከቱትም። አንዳቸው በሌላው ላይ “መራራ” ላለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (ቆላስይስ 3:19) ‘የለዘበች መልስ ቁጣን እንደምትመልስ’ ሁለቱም ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ምሳሌ 15:1) የልባቸውን ስሜት አውጥተው የሚነግሯችሁን የትዳር ጓደኞቻችሁን እንዳታንቋሽሹ ወይም እንዳትነቅፉ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። ከዚህ ይልቅ በዚህ መንገድ ስሜታቸውን መግለጻቸው የእነሱን አመለካከት በሚገባ ለመረዳት የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ አድርጋችሁ ቁጠሩት። አንድ ላይ ሆናችሁ በመካከላችሁ የተፈጠረውን ልዩነት ለመፍታትና የጋራ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጥረት አድርጉ።
24 በአንድ ወቅት ሣራ በጊዜው ተፈጥሮ ለነበረ አንድ ችግር መፍትሔ የሚሆን ሐሳብ ለባልዋ ለአብርሃም አቅርባ እንደነበረና ያቀረበችው ሐሳብ ከአብርሃም ስሜት ጋር የማይጣጣም እንደነበር አስታውሱ። ሆኖም አምላክ አብርሃምን “የምትነግርህን ቃል ሁሉ ስማ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 21:9-12) አብርሃም እንደተባለው በማድረጉ ተባርኳል። በተመሳሳይም አንድ ባል ሚስቱ እሱ በአእምሮው ከያዘው ነገር የተለየ ሐሳብ ብታቀርብለት ቢያንስ ቢያንስ የምትለውን ነገር መስማት ይኖርበታል። በአንጻሩ ደግሞ ሚስትየዋ እሷ ብቻ በመናገር ለመጫን ከመሞከር ይልቅ ባልዋ የሚለውንም መስማት ይኖርባታል። (ምሳሌ 25:24) ባልየውም ሆነ ሚስትየዋ ሁልጊዜ የራሳቸው ሐሳብ እንዲፈጸም ለማድረግ የሚጥሩ ከሆነ ፍቅርና አክብሮት የጎደለው ድርጊት ይሆናል።
25. ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ ከጾታ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የትዳር ሕይወት አስደሳች እንዲሆን አስተዋጽኦ የሚያበረክተው እንዴት ነው?
25 ባልና ሚስት በሚያደርጉት የጾታ ግንኙነት ረገድም ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። ራስ ወዳድነትና ራስን መግዛት አለመቻል ይህን በጣም የተቀራረበ ዝምድና ሊያሰነካክለው ይችላል። ትዕግሥት በተሞላበት ሁኔታ በግልጽ መነጋገር እጅግ አስፈላጊ ነው። ሁለቱም ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ መንገድ አንዳቸው ለሌላው ደህንነት የሚያስቡ ከሆነ የጾታ ግንኙነት ብዙውን ጊዜ ከባድ ችግር አይፈጥርም። እንደ ሌሎቹ ጉዳዮች ሁሉ በዚህም ጉዳይ ረገድ “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።”—1 ቆሮንቶስ 7:3-5፤ 10:24
26. እያንዳንዱ ትዳር የራሱ ጥሩና መጥፎ ገጠመኞች ቢኖሩትም እንኳ ባልና ሚስት የአምላክን ቃል መስማታቸው ደስታ ማግኘት እንዲችሉ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
26 የአምላክ ቃል እንዴት ያለ ግሩም ምክር ይሰጣል! እያንዳንዱ ትዳር የራሱ ጥሩና መጥፎ ገጠመኞች እንደሚኖሩት አይካድም። ይሁን እንጂ ባልና ሚስት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለተገለጸው የይሖዋ አስተሳሰብ ሲገዙና ዝምድናቸው በመሠረታዊ ሥርዓት በሚመራ ፍቅርና በአክብሮት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ሲያደርጉ ትዳራቸው ዘላቂና አስደሳች እንደሚሆን እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። በዚህ መንገድ አንዳቸው ሌላውን ብቻ ሳይሆን የጋብቻ መሥራች የሆነውን ይሖዋ አምላክንም ያከብራሉ።