የጥናት ርዕስ 44
የአምላክን ቃል ከሁሉም አቅጣጫ መርምሩ
“ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ ምን ያህል እንደሆነ [በሚገባ ተረዱ]።”—ኤፌ. 3:18
መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው
ማስተዋወቂያa
1-2. መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
አንድን ቤት ለመግዛት እያሰብክ ነው እንበል። ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ምን ነገሮችን ማየት ትፈልጋለህ? ቤቱን ከፊት ለፊት የሚያሳይ ፎቶግራፍ ብታይ ይበቃሃል? ቤቱን በአካል ለማየት እንደምትፈልግ የታወቀ ነው። ዙሪያውን መጎብኘት፣ ሁሉንም ክፍሎች መቃኘት እንዲሁም ቤቱን ከሁሉም አቅጣጫ ማየት ትፈልጋለህ። እንዲያውም ቤቱ እንዴት እንደተገነባ ለማወቅ ፕላኑን ማየት ትፈልግ ይሆናል። የምትገዛውን ቤት በደንብ ማየት እንደምትፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም።
2 መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብና ስናጠናም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን። አንድ ምሁር የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት “ጥልቅ መሠረት ካለው ትልቅ ሕንፃ” ጋር አመሳስለውታል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በጥድፊያ ካነበብከው፣ የምትማረው “የአምላክን ቅዱስ መልእክት መሠረታዊ ነገሮች” ብቻ ነው። (ዕብ. 5:12) ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ ቤቱ ሁሉ ወደ ውስጥ ገብተህ ዝርዝር መረጃዎችን ለመመርመር ጥረት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የምትችልበት አንዱ ግሩም መንገድ በውስጡ ያሉት መልእክቶች እንዴት እንደሚያያዙ ማስተዋል ነው። የምታምንባቸውን እውነቶች ምንነት ብቻ ሳይሆን በእነዚህ እውነቶች የምታምነው ለምን እንደሆነም ለመመርመር ጥረት አድርግ።
3. ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ ምን እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል? ለምንስ? (ኤፌሶን 3:14-19)
3 የአምላክን ቃል ከሁሉም አቅጣጫ በሚገባ ለመረዳት ጥልቀት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መማር ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ የእውነት ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ መረዳት እንዲችሉ’ የአምላክን ቃል በትጋት እንዲያጠኑ አበረታቷቸዋል። እንዲህ ካደረጉ በእምነታቸው ይበልጥ ‘ሥር መስደድና መታነጽ’ ይችላሉ። (ኤፌሶን 3:14-19ን አንብብ።) እኛም ይህንኑ ልናደርግ ይገባል። የአምላክ ቃል ያለውን ጥልቅ መልእክት ሙሉ በሙሉ መረዳት እንድንችል እንዴት ማጥናት እንዳለብን እስቲ እንመልከት።
ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መርምር
4. ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ምን ማድረግ እንችላለን? ምሳሌ ስጥ።
4 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን መጽሐፍ ቅዱስን ላይ ላዩን በመረዳት ብቻ ረክተን አንቀመጥም። በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” ጭምር መመርመር እንፈልጋለን። (1 ቆሮ. 2:9, 10) ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ ሊረዳህ የሚችል የግል ጥናት ፕሮጀክት ለምን አትጀምርም? ለምሳሌ ይሖዋ በጥንት ዘመን ለነበሩ አገልጋዮቹ ፍቅር ያሳያቸው እንዴት እንደሆነ ልትመረምር ትችላለህ፤ ከዚያም እነዚህ ታሪኮች ይሖዋ አንተንም እንደሚወድህ የሚያረጋግጡት እንዴት እንደሆነ ቆም ብለህ አስብ። አሊያም በጥንቷ እስራኤል የይሖዋ አምልኮ ይከናወን የነበረው እንዴት እንደሆነ ከመረመርክ በኋላ ይህን ዝግጅት በአሁኑ ጊዜ ካለው የክርስቲያን ጉባኤ ጋር ለማወዳደር ሞክር። ወይም ደግሞ ከኢየሱስ ምድራዊ ሕይወትና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ፍጻሜያቸውን ስላገኙ ትንቢቶች ጥልቀት ያለው ጥናት ልታደርግ ትችላለህ።
5. በግል ጥናትህ ላይ ምርምር ማድረግ የምትፈልገው ርዕሰ ጉዳይ አለ?
5 አንዳንድ ታታሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በግል ጥናታቸው ወቅት ከአምላክ ቃል ላይ የትኞቹን ጥልቅ ነገሮች መመርመር እንደሚፈልጉ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ከሰጧቸው መልሶች አንዳንዶቹ “ለግል ጥናት ፕሮጀክት የሚሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች” በሚለው ሣጥን ውስጥ ተዘርዝረዋል። የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮችን ተጠቅመህ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ምርምር በማድረግ ታላቅ ደስታ ማግኘት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ማጥናትህ እምነትህን ሊያጠናክረውና ‘ስለ አምላክ እውቀት እንድትቀስም’ ሊረዳህ ይችላል። (ምሳሌ 2:4, 5) ከዚህ በመቀጠል፣ ስለ የትኞቹ ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ምርምር ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን።
ስለ አምላክ ዓላማ በጥሞና አስብ
6. (ሀ) በዕቅድና በዓላማ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለሰው ልጆችና ለምድር ያለው ዓላማ “ዘላለማዊ” ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? (ኤፌሶን 3:11)
6 ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ዓላማ ምን እንደሚል እንመልከት። በዕቅድና በዓላማ መካከል ጉልህ ልዩነት አለ። ዕቅድ ማውጣት ወደ አንድ ቦታ የሚያደርስን መንገድ ከመምረጥ ጋር ይመሳሰላል። ሆኖም መንገዱ ላይ መሰናክል ካጋጠመ ዕቅዱ ይከሽፋል። ዓላማ ግን በመዳረሻው ላይ ያተኮረ ነው። የት መድረስ እንደምንፈልግ እናውቃለን፤ መንገዱን ግን አልወሰንንም። መንገዱ እንደ አስፈላጊነቱ ሊቀየር ይችላል። የይሖዋ ዓላማ በማንኛውም መንገድ መፈጸሙ አይቀርም፤ ምክንያቱም “ማንኛውንም ነገር ያዘጋጀው ለራሱ ዓላማ ነው።” (ምሳሌ 16:4) መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ዓላማ “ዘላለማዊ” እንደሆነም ይናገራል። (ኤፌ. 3:11) “ዘላለማዊ” የተባለው ይሖዋ ዓላማው ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ ረጅም ጊዜ እንዲያልፍ ስለፈቀደ ነው። በተጨማሪም የይሖዋ ዓላማ የሚያስገኘው ውጤት ዘላለማዊ ነው። ለመሆኑ የይሖዋ ዓላማ ምንድን ነው? ዓላማውን ለመፈጸምስ የትኞቹን ማስተካከያዎች አድርጓል?
7. የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ካመፁ በኋላ ይሖዋ ዓላማውን የሚፈጽምበትን መንገድ ያስተካከለው እንዴት ነው? (ማቴዎስ 25:34)
7 አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ለእነሱ ያለውን ዓላማ ነግሯቸዋል። “ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት፤ ግዟትም። እንዲሁም . . . በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረታትን በሙሉ ግዟቸው” ብሏቸዋል። (ዘፍ. 1:28) አዳምና ሔዋን በማመፃቸው የተነሳ የሰው ልጆች ኃጢአተኛ ቢሆኑም የአምላክ ዓላማ አልከሸፈም። ከዚህ ይልቅ ዓላማውን በሚፈጽምበት መንገድ ላይ ማስተካከያ አደረገ። ለሰው ልጆችና ለምድር ያለውን የመጀመሪያ ዓላማ ለመፈጸም በሰማይ መንግሥት እንደሚያቋቁም ወዲያውኑ ወሰነ። (ማቴዎስ 25:34ን አንብብ።) የሚወደን አባታችን ይሖዋ፣ የቀጠረው ጊዜ ሲደርስ ሰዎችን ስለ መንግሥቱ እንዲያስተምርና ቤዛውን በመክፈል ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንዲያወጣን አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከው። ከዚያም ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ ወደ ሰማይ በመሄድ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ። ሆኖም ስለ አምላክ ዓላማ ልንማረው የሚገባ ሌላም ነገር አለ።
8. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ ምንድን ነው? (ለ) በኤፌሶን 1:8-11 መሠረት የይሖዋ ዋነኛ ዓላማ ምንድን ነው? (የሽፋኑን ሥዕል ተመልከት።)
8 የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ፣ ይሖዋ በክርስቶስ በሚመራው መንግሥቱ አማካኝነት ለምድር ያለውን ዓላማ በመፈጸም ስሙን ከነቀፋ ነፃ እንደሚያደርገው የሚገልጽ ነው። የይሖዋ ዓላማ አይቀየርም። ዓላማውን እንደሚያሳካ ዋስትና ሰጥቶናል። (ኢሳ. 46:10, 11፤ ዕብ. 6:17, 18) ከጊዜ በኋላ ምድር ገነት ትሆናለች፤ በዚያም ፍጹምና ጻድቅ የሆኑ የአዳምና ሔዋን ዘሮች ‘ለዘላለም ተደስተው ይኖራሉ።’ (መዝ. 22:26) ይሁንና የይሖዋ ዓላማ ይህ ብቻ አይደለም። ዋነኛ ዓላማው፣ በሰማይና በምድር ያሉ ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታቱን በሙሉ አንድ ማድረግ ነው። ከዚያም ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ለእሱ ሉዓላዊነት በታማኝነት ይገዛሉ። (ኤፌሶን 1:8-11ን አንብብ።) ይሖዋ ዓላማውን የሚፈጽምበት ግሩም መንገድ አያስደንቅህም?
ስለ ወደፊቱ ጊዜ አሰላስል
9. መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ የወደፊቱን ጊዜ የት ድረስ ማየት እንችላለን?
9 ይሖዋ በኤደን ገነት የተናገረውን በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘውን ትንቢት እስቲ እንመልከት።b ትንቢቱ የይሖዋ ዓላማ እንዲፈጸም የሚያደርጉ ክንውኖችን ይጠቅሳል፤ ሆኖም እነዚህ ክንውኖች የሚፈጸሙት ትንቢቱ ከተነገረ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው። ከእነዚህ ክንውኖች መካከል፣ ክርስቶስ ከአብርሃም የዘር ሐረግ መወለዱ ይገኝበታል። (ዘፍ. 22:15-18) ከዚያም በ33 ዓ.ም. ኢየሱስ በትንቢቱ መሠረት ተረከዙ ቆሰለ። (ሥራ 3:13-15) የትንቢቱ የመጨረሻ ክፍል እስኪፈጸም ማለትም የሰይጣን ራስ እስኪጨፈለቅ ድረስ ደግሞ ከ1,000 ዓመት በላይ ይቀራል። (ራእይ 20:7-10) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሰይጣን ሥርዓትና በይሖዋ ድርጅት መካከል ያለው ጠላትነት ተፋፍሞ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ሲደርስ የሚከናወኑትን ነገሮች ይገልጽልናል።
10. (ሀ) በቅርቡ የትኞቹ ክንውኖች እንደሚፈጸሙ እንጠብቃለን? (ለ) አእምሯችንንና ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
10 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት በቅርቡ ስለሚከሰቱት ምድርን የሚያናውጡ ክንውኖች ለማሰብ ሞክር። በመጀመሪያ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ብለው ያውጃሉ። (1 ተሰ. 5:2, 3) ከዚያም ብሔራት በሁሉም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ታላቁ መከራ “ድንገት” ይጀምራል። (ራእይ 17:16) ቀጥሎም ‘የሰው ልጅ በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና መምጣቱን’ የሚያሳዩ አስደናቂ ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ። (ማቴ. 24:30) ኢየሱስ በጎቹን ከፍየሎቹ በመለየት በሰው ልጆች መካከል ይፈርዳል። (ማቴ. 25:31-33, 46) ይሁንና ሰይጣን በዚህ ወቅት እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። ሰይጣን በጥላቻ ተነሳስቶ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ በማለት የሚጠራቸውን ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ያደርጋቸዋል። (ሕዝ. 38:2, 10, 11) በዚህ መሃል ቅቡዓን ቀሪዎች ከክርስቶስና ከሰማያዊ ሠራዊቱ ጋር ሆነው በአርማጌዶን ጦርነት ለመካፈል ወደ ሰማይ ይሄዳሉ፤ ይህ ጦርነት የታላቁ መከራ መደምደሚያ ይሆናል።c (ማቴ. 24:31፤ ራእይ 16:14, 16) ከዚያም ክርስቶስ ለሺህ ዓመት ምድርን ይገዛል።—ራእይ 20:6
11. የዘላለም ሕይወት ለአንተ ምን ትርጉም አለው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
11 አሁን ደግሞ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ይበልጥ አሻግረን ለማሰብ እንሞክር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪያችን ‘ዘላለማዊነትን በልባችን ውስጥ እንዳኖረ’ ይናገራል። (መክ. 3:11) እስቲ ያኔ ከይሖዋ ጋር የሚኖርህ ዝምድና ምን እንደሚመስል አስብ። ወደ ይሖዋ ቅረብ የተባለው መጽሐፍ ገጽ 319 ላይ የሚከተለውን ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ይዟል፦ “በመቶዎች፣ በሺዎች፣ በሚሊዮኖች አልፎ ተርፎም በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት ስንኖር ስለ ይሖዋ አምላክ የምናገኘው ትምህርት አሁን ካለን እውቀት ብዙ ጊዜ እጥፍ እየጨመረ እንደሚሄድ የታወቀ ነው። እንዲያም ሆኖ ግን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሌሎች ድንቅ ነገሮች ገና መማር እንደሚቀረን እንገነዘባለን። . . . የዘላለም ሕይወት ልንገምተው ከምንችለው በላይ አርኪና አስደሳች ነው፤ ከሁሉ ይበልጥ የሚያስደስተው ደግሞ ይህ ሕይወት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ወደ ይሖዋ እየቀረብን ለመሄድ የሚያስችል አጋጣሚ የሚሰጠን መሆኑ ነው።” እስከዚያው ግን የአምላክን ቃል ስናጠና ሌላስ ምን መመርመር እንችላለን?
ዓይኖችህን አቅንተህ ወደ ሰማይ ተመልከት
12. ዓይናችንን አቅንተን ወደ ሰማይ መመልከት የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
12 የአምላክ ቃል፣ ይሖዋ የሚኖርበት ‘ከፍ ያለ ቦታ’ ምን እንደሚመስል ፍንጭ ይሰጠናል። (ኢሳ. 33:5) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋና ስለ ድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል አስደናቂ ነገሮችን ይገልጽልናል። (ኢሳ. 6:1-4፤ ዳን. 7:9, 10፤ ራእይ 4:1-6) ለምሳሌ ሕዝቅኤል ‘ሰማያት ተከፍተው አምላክ የገለጠለትን ራእዮች ማየት በጀመረበት’ ወቅት ስለተመለከታቸው አስደናቂ ነገሮች ማንበብ እንችላለን።—ሕዝ. 1:1
13. በዕብራውያን 4:14-16 መሠረት ኢየሱስ በሰማይ ሆኖ እየተጫወተ ካለው ሚና ጋር በተያያዘ የምታደንቀው ምንድን ነው?
13 ኢየሱስ በሰማይ ላይ ንጉሥና ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት ሆኖ ስለሚጫወተው ሚናም ለማሰብ ሞክር። በእሱ አማካኝነት ወደ አምላክ ‘የጸጋ ዙፋን’ በጸሎት መቅረብና “በሚያስፈልገን ጊዜ” ምሕረትና እርዳታ ለማግኘት መጠየቅ እንችላለን። (ዕብራውያን 4:14-16ን አንብብ።) ይሖዋና ኢየሱስ ከሰማይ ሆነው ስላደረጉልን እንዲሁም እያደረጉልን ስላለው ነገር ሳናሰላስል አንድም ቀን እንዲያልፍብን ልንፈቅድ አይገባም። ለእኛ ያላቸው ፍቅር ልባችንን በጥልቅ ሊነካው እንዲሁም በአገልግሎታችንና በአምልኳችን ቀናተኞች እንድንሆን ሊያነሳሳን ይገባል።—2 ቆሮ. 5:14, 15
14. ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለንን አድናቆት ማሳየት ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ የትኛው ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)
14 አምላካችንና ልጁ ላደረጉልን ነገር ያለንን አድናቆት ማሳየት ከምንችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ፣ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ነው። (ማቴ. 28:19, 20) ሐዋርያው ጳውሎስ ለአምላክና ለክርስቶስ ያለው አመስጋኝነት እንዲህ እንዲያደርግ አነሳስቶታል። የይሖዋ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” እንደሆነ ተረድቶ ነበር። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ጳውሎስ ‘በተቻለ መጠን የተወሰኑ ሰዎችን ያድን ዘንድ’ በአገልግሎቱ ብዙ ሰዎችን ለመርዳት የተቻለውን ሁሉ አድርጓል።—1 ቆሮ. 9:22, 23
የአምላክን ቃል በመመርመር ተደሰት
15. በመዝሙር 1:2 መሠረት ደስታ የሚያስገኘው ምንድን ነው?
15 መዝሙራዊው ‘በይሖዋ ሕግ ደስ የሚለው፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያሰላስል’ ሰው ደስተኛና ስኬታማ እንደሚሆን መግለጹ በእርግጥም ተገቢ ነው። (መዝ. 1:1-3 ግርጌ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆነው ጆሴፍ ሮዘርሃም ስተዲስ ኢን ዘ ሳልምስ በተባለው መጽሐፉ ላይ ስለዚህ ጥቅስ ሲናገር፣ አንድ ሰው “የአምላክን አመራር በትጋት በመፈለግ፣ በማጥናትና ለረጅም ሰዓት በማሰላሰል በቃሉ እንደሚደሰት ሊያሳይ ይገባል” ብሏል። አክሎም ‘መጽሐፍ ቅዱስን ሳናነብ ያለፈው እያንዳንዱ ቀን እንደባከነ እንደሚቆጠር’ ገልጿል። አንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ዝርዝር ሐሳቦች በማስተዋል እንዲሁም እያንዳንዱ ርዕሰ ጉዳይ የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ በመመልከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ደስታ ማግኘት ትችላለህ። የአምላክን ቃል ከሁሉም አቅጣጫ መመርመር ምንኛ የሚያስደስት ነው!
16. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
16 ይሖዋ በቃሉ ውስጥ የሚያስተምረንን ውድ እውነቶች መረዳት ከአቅማችን በላይ አይደለም። በቀጣዩ ርዕስ ላይ፣ ጥልቅ ከሆኑት እውነቶች ስለ አንዱ ይኸውም ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ስለገለጸው የይሖዋ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ እንመረምራለን። ይህን ርዕሰ ጉዳይ በመመርመር ከፍተኛ ደስታ እንደምታገኝ ተስፋ እናደርጋለን።
መዝሙር 94 ለአምላክ ቃል አመስጋኝ መሆን
a መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በመላ ሕይወታችን ደስታ የሚያስገኝልን ከመሆኑም ሌላ ወደ ሰማዩ አባታችን ይበልጥ እንድንቀርብ ይረዳናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የአምላክን ቃል ‘ስፋት፣ ርዝመት፣ ከፍታና ጥልቀት’ መመርመር የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
b በሐምሌ 2022 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚገኘውን “ሁላችንንም የሚመለከት ጥንታዊ ትንቢት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c በቅርቡ ለሚከሰቱት ምድርን የሚያናውጡ ክንውኖች ራስህን ማዘጋጀት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 230 ተመልከት።