የጥናት ርዕስ 30
ሁላችንንም የሚመለከት ጥንታዊ ትንቢት
“በአንተና በሴቲቱ መካከል . . . ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ።”—ዘፍ. 3:15
መዝሙር 15 የይሖዋን በኩር አወድሱ!
ማስተዋወቂያa
1. አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ምን አደረገ? (ዘፍጥረት 3:15)
አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ አንድ አስደናቂ ትንቢት በመናገር ለዘሮቻቸው ተስፋ ሰጠ። ይህ ትንቢት በዘፍጥረት 3:15 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል።—ጥቅሱን አንብብ።
2. ይህን ትንቢት አስደናቂ የሚያደርገው ምንድን ነው?
2 ይህ ትንቢት የሚገኘው በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ነው። ሆኖም ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ በሆነ መልኩ ከዚህ ትንቢት ጋር ተያያዥነት አላቸው። የአንድ መጽሐፍ ስፌት ሁሉንም ገጾች ሰብስቦ እደሚያያይዝ ሁሉ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢትም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በሙሉ በአንድ የጋራ መልእክት እንዲያያዙ ያደርጋል። ይህ መልእክት ዲያብሎስንና ክፉ የሆኑ ተከታዮቹን የሚደመስስ አንድ አዳኝ እንደሚላክ የሚገልጽ ነው።b ይህ ይሖዋን ለሚወዱ ሁሉ በጣም አስደሳች ነው!
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንመልሳለን፦ በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት እነማን ናቸው? ትንቢቱ የሚፈጸመው እንዴት ነው? እንዲሁም ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት ነው?
በትንቢቱ ውስጥ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት እነማን ናቸው?
4. እባቡ ማን ነው? ይህንንስ እንዴት እናውቃለን?
4 በዘፍጥረት 3:14, 15 ላይ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት “እባቡ፣” የእባቡ “ዘር፣” “ሴቲቱ” እና የሴቲቱ ‘ዘር’ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የእያንዳንዳቸውን ማንነት ለማወቅ ይረዳናል።c በመጀመሪያ ‘የእባቡን’ ማንነት እንመልከት። እውነተኛ እባብ፣ ይሖዋ በኤደን ገነት ውስጥ የተናገረውን ነገር ሊረዳ አይችልም። በመሆኑም ይሖዋ ፍርዱን ያስተላለፈው ማሰብ በሚችል ፍጡር ላይ መሆን አለበት። ይህ ፍጡር ማን ነው? ራእይ 12:9 ማንነቱን በግልጽ ይነግረናል። ጥቅሱ “የጥንቱ እባብ” ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነ በቀጥታ ይናገራል። ይሁንና የእባቡ ዘር ማን ነው?
5. የእባቡ ዘር እነማንን ያካትታል?
5 መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ጊዜ “ዘር” የሚለውን ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምበታል። ይህም ሲባል አንዳንዶች አንድን አካል በጣም ከመምሰላቸው የተነሳ እንደ ልጆቹ ይቆጠራሉ እንደማለት ነው። ከዚህ አንጻር የእባቡ ዘር እንደ ሰይጣን ይሖዋ አምላክንና ሕዝቦቹን የሚቃወሙ መንፈሳዊ ፍጥረታትን እና ሰዎችን ያካትታል። ይህም በኖኅ ዘመን በሰማይ ላይ የነበራቸውን ቦታ የተዉትን መላእክትና እንደ አባታቸው እንደ ዲያብሎስ ዓይነት ባሕርይ ያላቸውን ክፉ ሰዎች ይጨምራል።—ዘፍ. 6:1, 2፤ ዮሐ. 8:44፤ 1 ዮሐ. 5:19፤ ይሁዳ 6
6. “ሴቲቱ” ሔዋን ልትሆን የማትችለው ለምንድን ነው?
6 ቀጥሎ ደግሞ ‘የሴቲቱን’ ማንነት እንመልከት። ሴቲቱ ሔዋን ልትሆን አትችልም። ለምን? አንድ ምክንያት ብቻ እንመልከት። ትንቢቱ የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ ‘እንደሚጨፈልቀው’ ይናገራል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው እባቡ ሰይጣን ነው። ሰይጣን ደግሞ መንፈሳዊ ፍጡር ስለሆነ የሔዋን ዘር የሆነ ማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው እሱን ሊጨፈልቀው አይችልም። ታዲያ ሰይጣን የሚጠፋው እንዴት ነው?
7. ራእይ 12:1, 2, 5, 10 እንደሚያሳየው በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰችው ሴት ማን ነች?
7 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰችው ሴት ማንነት በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል። (ራእይ 12:1, 2, 5, 10ን አንብብ።) ሴቲቱ በምድር ላይ ያለች ሴት አይደለችም። ጨረቃ ከእግሯ ሥር አለች፤ በራሷም ላይ 12 ከዋክብት ያሉት አክሊል አድርጋለች። ሴቲቱ አስደናቂ ልጅ ማለትም የአምላክን መንግሥት ወልዳለች። መንግሥቱ ያለው በሰማይ ነው፤ በመሆኑም ሴቲቱም ያለችው በሰማይ ላይ መሆን አለበት። ሴቲቱ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ታመለክታለች።—ገላ. 4:26
8. የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ማን ነው? የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነውስ መቼ ነው? (ዘፍጥረት 22:15-18)
8 የአምላክ ቃል የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ማን እንደሆነ ለማወቅም ይረዳናል። የዘሩ ዋነኛ ክፍል የሚመጣው ከአብርሃም የትውልድ መስመር እንደሆነ ተገልጿል። (ዘፍጥረት 22:15-18ን አንብብ።) ልክ ትንቢቱ እንደሚለው ኢየሱስ የመጣው ከዚህ ታማኝ ሰው የትውልድ ሐረግ ነው። (ሉቃስ 3:23, 34) ሆኖም ይህ ዘር ሰይጣን ዲያብሎስን ጨፍልቆ ከሕልውና ውጭ ማድረግ ስላለበት ተራ ሰው ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ኢየሱስ 30 ዓመት ገደማ ሲሆነው በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ የአምላክ ልጅ ሆነ። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ሆነ። (ገላ. 3:16) ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳ በኋላ ይሖዋ “የክብርና የሞገስ ዘውድ” ደፋለት፤ እንዲሁም ‘ሥልጣንን ሁሉ በሰማይና በምድር’ ሰጠው። ከተሰጠው ሥልጣን መካከል ‘የዲያብሎስን ሥራ የማፍረስ’ ሥልጣን ይገኝበታል።—ዕብ. 2:7፤ ማቴ. 28:18፤ 1 ዮሐ. 3:8
9-10. (ሀ) የሴቲቱ ዘር ሌላ ማንን ያካትታል? የሴቲቱ ዘር ክፍል የሚሆኑትስ መቼ ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ ምን እንመለከታለን?
9 ይሁንና ይህ ዘር ሁለተኛ ክፍልም አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአይሁዳውያንና ለአሕዛብ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ሐሳብ የዘሩን ሁለተኛ ክፍል ማንነት ለማወቅ ይረዳናል፤ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥም የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ በተስፋውም ቃል መሠረት ወራሾች ናችሁ።” (ገላ. 3:28, 29) ይሖዋ አንድን ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባው ያ ሰው የሴቲቱ ዘር ክፍል ይሆናል። በመሆኑም የሴቲቱ ዘር ኢየሱስን እና አብረውት የሚገዙትን 144,000 ቅቡዓን ያካትታል። (ራእይ 14:1) ሁሉም አባታቸውን ይሖዋ አምላክን ይመስላሉ።
10 በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሱትን ገጸ ባሕርያት ማንነት ተመልክተናል። አሁን ደግሞ ይሖዋ ይህ ትንቢት ደረጃ በደረጃ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ በአጭሩ እንመለከታለን።
ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
11. የሴቲቱ ዘር “ተረከዙ” የቆሰለው በምን መንገድ ነው?
11 በዘፍጥረት 3:15 ላይ በሚገኘው ትንቢት መሠረት እባቡ የሴቲቱን ዘር “ተረከዙን” ያቆስለዋል። ሰይጣን አይሁዳውያንን እና ሮማውያንን በማነሳሳት የአምላክን ልጅ እንዲገድሉት ባደረገበት ጊዜ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። (ሉቃስ 23:13, 20-24) የተረከዝ ቁስል አንድን ሰው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከእንቅስቃሴ ውጭ እንደሚያደርገው ሁሉ ኢየሱስም ሞቶ ለሦስት ቀናት ያህል መቃብር ውስጥ መቆየቱ ለጊዜው ከእንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆን አድርጎታል።—ማቴ. 16:21
12. የእባቡ ራስ የሚጨፈለቀው መቼ እና እንዴት ነው?
12 በዘፍጥረት 3:15 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም ከተፈለገ ኢየሱስ መቃብር ውስጥ መቅረት የለበትም። ለምን? ምክንያቱም በትንቢቱ መሠረት የሴቲቱ ዘር የእባቡን ዘር ይጨፈልቃል። ይህ እንዲሆን ኢየሱስ ከተረከዝ ቁስሉ ማገገም አለበት። ደግሞም አገግሟል! ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን ትንሣኤ አግኝቶ የማይሞት መንፈሳዊ ፍጡር ሆነ። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስ ሰይጣንን ጨፍልቆ ከሕልውና ውጭ ያደርገዋል። (ዕብ. 2:14) ክርስቶስና ተባባሪ ገዢዎቹ የእባቡን ዘር ማለትም የአምላክን ጠላቶች በሙሉ ከምድር ገጽ ላይ ጠራርገው ያጠፋሉ።—ራእይ 17:14፤ 20:4, 10d
ትንቢቱ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
13. የዚህ ትንቢት ፍጻሜ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
13 ራስህን የወሰንክ የአምላክ አገልጋይ ከሆንክ ከዚህ ትንቢት ፍጻሜ እየተጠቀምክ ነው። ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል። የአባቱንም ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም በእሱ አማካኝነት ይሖዋ አምላክን ማወቅና መውደድ ችለናል። በተጨማሪም ከኢየሱስ ትምህርቶች እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ጉባኤን ከሚመራበት መንገድ ጥቅም አግኝተናል። የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝ መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ አስተምሮናል። ደግሞም ሁላችንም ከኢየሱስ ሞት ማለትም ከተረከዙ መቁሰል ጥቅም ማግኘት እንችላለን። እንዴት? ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ የደሙን ዋጋ ‘ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻን’ ፍጹም መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል።—1 ዮሐ. 1:7
14. ይሖዋ በኤደን የተናገረው ትንቢት ወዲያውኑ እንዳልተፈጸመ እንዴት እናውቃለን? አብራራ።
14 ይሖዋ በኤደን ያንን ትንቢት ሲናገር የተጠቀመባቸው ቃላት ትንቢቱ የሚፈጸመው በዚያ ወቅት እንዳልሆነ ይጠቁማሉ። ሴቲቱ ተስፋ የተሰጠበትን ዘር እስክታስገኝ፣ ዲያብሎስ ተከታዮቹን እስኪያሰባስብ እንዲሁም በሁለቱ ቡድኖች መካከል ጠላትነት እስኪፈጠር ጊዜ ያስፈልጋል። ስለዚህ ትንቢት ማወቃችን ይጠቅመናል። ምክንያቱም ትንቢቱ፣ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም የይሖዋን አገልጋዮች እንደሚጠላ ያሳያል። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። (ማር. 13:13፤ ዮሐ. 17:14) በተለይ ባለፉት 100 ዓመታት ይሄኛው የትንቢቱ ክፍል ሲፈጸም በግልጽ ተመልክተናል። እንዴት?
15. ዓለም ለአምላክ ሕዝቦች ያለው ጥላቻ የጨመረው ለምንድን ነው? ሰይጣንን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም የምንለውስ ለምንድን ነው?
15 ኢየሱስ በ1914 መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ከሰማይ ተባረረ። አሁን እንቅስቃሴው በምድር አካባቢ ተገድቦ መጥፊያውን እየተጠባበቀ ነው። (ራእይ 12:9, 12) ሆኖም የሚጠብቀው እጁን አጣጥፎ አይደለም። ሰይጣን መጥፊያው መቅረቡን ስላወቀ በከፍተኛ ቁጣ ተሞልቷል፤ ቁጣውንም በአምላክ ሕዝቦች ላይ እየተወጣ ነው። (ራእይ 12:13, 17) በመሆኑም ዓለም ለአምላክ ሕዝቦች ያለው ጥላቻ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጨምሯል። ሆኖም ሰይጣንን እና ተከታዮቹን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። (ሮም 8:31) እስካሁን እንደተመለከትነው በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት አብዛኛው ክፍል ፍጻሜውን አግኝቷል። ስለዚህ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን እንችላለን።
16-18. ከርተስ፣ ኡርሱላ እና ጄሲካ ዘፍጥረት 3:15ን መረዳታቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው?
16 በዘፍጥረት 3:15 ላይ ይሖዋ የሰጠን ተስፋ፣ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና እንድንቋቋም ሊረዳን ይችላል። በጉዋም ሚስዮናዊ ሆኖ የሚያገለግለው ከርተስ እንዲህ ብሏል፦ “ለይሖዋ ያለኝን ታማኝነት የሚፈትኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሕይወቴ ውስጥ አጋጥመውኛል። ሆኖም በዘፍጥረት 3:15 ላይ በሚገኘው ትንቢት ላይ ማሰላሰሌ በሰማዩ አባቴ ላይ ያለኝን እምነት ይዤ እንድቀጥል ረድቶኛል።” ከርተስ፣ ይሖዋ ከፈተናዎቻችን ሁሉ የሚገላግለንን ቀን በጉጉት ይጠባበቃል።
17 በባቫሪያ የምትኖር ኡርሱላ የተባለች እህት ዘፍጥረት 3:15ን መረዳቷ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፉን እንድታምን እንደረዳት ገልጻለች። ሌሎቹ ትንቢቶች በሙሉ ከዚህ ትንቢት ጋር ያላቸውን ተያያዥነት ስትገነዘብ በጣም ተደነቀች። እንዲህ ብላለች፦ “የሰው ልጆች ያለተስፋ እንዳይቀሩ ሲል ይሖዋ ወዲያውኑ እርምጃ እንደወሰደ ሳውቅ ልቤ በጥልቅ ተነካ።”
18 በማይክሮኔዥያ የምትኖረው ጄሲካ እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን እንዳገኘሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ስገነዘብ የተሰማኝን ስሜት እስካሁን አስታውሳለሁ! በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት እየተፈጸመ መሆኑን ተረዳሁ። ይህም በአሁኑ ጊዜ የምንመራው አስቸጋሪ ሕይወት እውነተኛው ሕይወት እንዳልሆነ እንድገነዘብ ረዳኝ። በተጨማሪም ትንቢቱ ይሖዋን ማገልገሌ በአሁኑ ጊዜ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት ለመምራት፣ ወደፊት ደግሞ ከአሁኑም የበለጠ አስደሳች ሕይወት ለማግኘት እንደሚረዳኝ ያለኝን እምነት አጠናክሮልኛል።”
19. የትንቢቱ የመጨረሻ ክፍል እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
19 እስካሁን እንደተመለከትነው ዘፍጥረት 3:15 ፍጻሜውን እያገኘ ነው። የሴቲቱ ዘርና የእባቡ ዘር ማንነት በግልጽ ታውቋል። የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነው ኢየሱስ ከተረከዝ ቁስሉ አገግሟል። እንዲያውም አሁን ግርማ የተላበሰና የማይሞት ሕይወት ያለው ንጉሥ ነው። በሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል ውስጥ የሚካተቱትን ሰዎች የመምረጡ ሥራ እየተጠናቀቀ ነው። የትንቢቱ የመጀመሪያ ክፍል ፍጻሜውን ስላገኘ የትንቢቱ የመጨረሻ ክፍልም እንደሚፈጸም ማለትም የእባቡ ራስ እንደሚጨፈለቅ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሰይጣን ከሕልውና ውጭ ሲሆን ታማኝ የሰው ልጆች በሙሉ እፎይ ይላሉ! እስከዚያው ድረስ ግን ተስፋ አትቁረጡ። አምላካችን እምነት የሚጣልበት ነው። በሴቲቱ ዘር አማካኝነት ‘ለምድር ብሔራት ሁሉ’ የተትረፈረፈ በረከት ያፈስላቸዋል።—ዘፍ. 22:18
መዝሙር 23 ይሖዋ መግዛት ጀምሯል
a በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ካልገባን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም። ስለዚህ ትንቢት ማጥናታችን በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ያጠናክረዋል፤ እንዲሁም እሱ የገባውን ቃል በሙሉ እንደሚፈጽም ይበልጥ እንድንተማመን ያደርገናል።
b በአዲስ ዓለም ትርጉም ተጨማሪ መረጃ ለ1 ላይ የሚገኘውን “የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c “በዘፍጥረት 3:14, 15 ላይ የተጠቀሱት ገጸ ባሕርያት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
d “ከዘፍጥረት 3:15 አፈጻጸም ጋር የተያያዙ ጉልህ ክንውኖች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።