የጥናት ርዕስ 15
‘በንግግርህ አርዓያ’ ነህ?
“ታማኞች ለሆኑት በንግግር . . . አርዓያ ሁን።”—1 ጢሞ. 4:12
መዝሙር 90 እርስ በርስ እንበረታታ
ማስተዋወቂያa
1. የመናገር ችሎታችንን የሰጠን ማን ነው?
የመናገር ችሎታችን ከአፍቃሪው አምላካችን ያገኘነው ስጦታ ነው። የመጀመሪያው ሰው አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ፣ አንደበቱን ተጠቅሞ በሰማይ ካለው አባቱ ጋር መነጋገር ይችል ነበር። አዳዲስ ቃላት በመፍጠር የቃላት ክምችቱን ማሳደግም ይችል ነበር። አዳም ይህን ችሎታውን ተጠቅሞ ለሁሉም እንስሳት ስም አውጥቶላቸዋል። (ዘፍ. 2:19) በኋላ ላይ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ሌላ ሰው የማነጋገር አጋጣሚ አገኘ፤ ውብ የሆነችውን ሚስቱን ሔዋንን ሲያነጋግር ምንኛ ተደስቶ ይሆን!—ዘፍ. 2:22, 23
2. በጥንት ዘመንም ሆነ በዛሬው ጊዜ የመናገር ስጦታ አላግባብ ጥቅም ላይ የዋለው እንዴት ነው?
2 የሚያሳዝነው ግን ብዙም ሳይቆይ ይህ ልዩ ስጦታ አላግባብ ጥቅም ላይ ዋለ። ሰይጣን ዲያብሎስ ሔዋንን ዋሻት፤ ይህ ውሸት ደግሞ በሰው ልጆች ላይ ኃጢአትንና አለፍጽምናን አስከተለ። (ዘፍ. 3:1-4) አዳም የራሱን ጥፋት በሔዋን ይባስ ብሎም በይሖዋ ላይ በማላከክ አንደበቱን አላግባብ ተጠቀመበት። (ዘፍ. 3:12) ቃየን ወንድሙን አቤልን ከገደለው በኋላ ለይሖዋ ውሸት ተናገረ። (ዘፍ. 4:9) በኋላ ላይ ደግሞ የቃየን ዘር የሆነው ላሜህ አንድ ግጥም ገጠመ፤ ይህ ግጥም በዘመኑ ዓመፅ ምን ያህል ተስፋፍቶ እንደነበር የሚያሳይ ነው። (ዘፍ. 4:23, 24) ዛሬ ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል? የፖለቲካ መሪዎች በአደባባይ ነውረኛ ንግግር በነፃነት ሲጠቀሙ እናያለን። ስድብ ወይም የብልግና ንግግር የሌለበት ፊልም አለ ማለትም ይከብዳል። ተማሪዎች በትምህርት ቤት፣ አዋቂዎች ደግሞ በሥራ ቦታቸው ስድብና ነውረኛ ንግግር ይሰማሉ። እንዲህ ዓይነት ንግግር እየተለመደ መሄዱ በዓለም ላይ የሚታየው ሥነ ምግባር በሚያሳዝን ሁኔታ እያዘቀጠ መሄዱን ይጠቁማል።
3. ካልተጠነቀቅን ምን ሊያጋጥመን ይችላል? በዚህ ርዕስ ላይስ ምን እንመለከታለን?
3 ጠንቃቃ ካልሆንን እንዲህ ዓይነቱን አነጋገር ከመልመዳችን የተነሳ እኛ ራሳችን እንደዚያ ማውራት ልንጀምር እንችላለን። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋን ማስደሰት እንፈልጋለን፤ ስለዚህ ነውረኛ ከሆነ ንግግር እንደምንርቅ የታወቀ ነው። ሆኖም ከዚህ ባለፈ ይህን አስደናቂ ስጦታ በትክክለኛው መንገድ ይኸውም አምላካችንን ለማወደስ ልንጠቀምበት ይገባል። ይህ ርዕስ ቀጥሎ በተጠቀሱት አቅጣጫዎች እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል፦ (1) በአገልግሎት ስንካፈል፣ (2) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ እንዲሁም (3) ከሌሎች ጋር ስናወራ። እስቲ በመጀመሪያ ይሖዋ ለአነጋገራችን ትኩረት የሚሰጠው ለምን እንደሆነ እንመልከት።
ይሖዋ ለአነጋገራችን ትኩረት ይሰጣል
4. በሚልክያስ 3:16 መሠረት ይሖዋ ለንግግራችን ትኩረት የሚሰጠው ለምንድን ነው?
4 ሚልክያስ 3:16ን አንብብ። ይሖዋ እሱን እንደሚፈሩና በስሙ ላይ እንደሚያሰላስሉ በንግግራቸው የሚያሳዩ ሰዎችን ‘በመታሰቢያ መጽሐፉ’ ላይ የሚጽፈው ለምን ይመስልሃል? ንግግራችን በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴ. 12:34) ለማውራት የምንመርጠው ነገር ለይሖዋ ያለን ፍቅር ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ያሳያል። ይሖዋ ደግሞ እሱን የሚወዱ ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ይፈልጋል።
5. (ሀ) አነጋገራችን አምልኳችንን የሚነካው እንዴት ነው? (ለ) ሥዕሉ ላይ እንደሚታየው ይሖዋን በንግግራችን ማስደሰት ከፈለግን ከምን መቆጠብ ይኖርብናል?
5 አነጋገራችን አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ወይም እንዲያጣ ሊያደርግ ይችላል። (ያዕ. 1:26) አምላክን የማይወዱ አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ይቆጣሉ፣ ሌሎችን ያመናጭቃሉ እንዲሁም ጉራ ይነዛሉ። (2 ጢሞ. 3:1-5) እንደ እነሱ መሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ፍላጎታችን ይሖዋን በንግግራችን ማስደሰት ነው። ይሁንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወይም በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች በአክብሮትና በደግነት እያነጋገርን ቤት ገብተን የቤተሰባችንን አባላት የምናመናጭቅ ከሆነ ይሖዋ ሊደሰትብን ይችላል?—1 ጴጥ. 3:7
6. የኪምበርሊ አነጋገር ምን መልካም ውጤት አስገኝቷል?
6 አንደበታችንን በአግባቡ መጠቀማችን ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችንን ለይተው እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። እንዲህ ስናደርግ የሚያዩን ሰዎች “አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት” በግልጽ ማስተዋል ይችላሉ። (ሚል. 3:18) ኪምበርሊ የተባለች እህት ያጋጠማት ነገር የዚህን እውነተኝነት ያረጋግጣል።b ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለች አብራት ከምትማር አንዲት ልጅ ጋር በአንድ ፕሮጀክት ላይ እንዲሠሩ ተመደቡ። ፕሮጀክቱን አብረው ሲሠሩ ኪምበርሊ ከሌሎቹ ተማሪዎች የተለየች እንደሆነች ልጅቷ አስተዋለች። ኪምበርሊ ሌሎችን አታማም፣ ሰዎችን የምታነጋግረው በደግነት ነው እንዲሁም አትሳደብም። ልጅቷ ይህ በጣም ስላስገረማት ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። አነጋገራችን ሰዎችን ወደ እውነት የሚስብ ከሆነ ይሖዋ በጣም ይደሰታል!
7. ይሖዋ የሰጠህን የመናገር ስጦታ እንዴት ልትጠቀምበት ትፈልጋለህ?
7 ሁላችንም አነጋገራችን ይሖዋን የሚያስከብርና ከወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን የሚያደርግ እንዲሆን እንፈልጋለን። እንግዲያው ምንጊዜም ‘በንግግራችን አርዓያ ለመሆን’ ልንወስዳቸው የሚገቡንን እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።
በአገልግሎት ላይ አርዓያ ሁን
8. ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን አንደበቱን የተጠቀመበት መንገድ ምን ምሳሌ ይሆነናል?
8 የሚያስቆጣ ነገር ሲያጋጥምህ በደግነትና በአክብሮት ተናገር። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን ሰካራም፣ ሆዳም፣ የአጋንንት ወኪል፣ ሰንበትን የማያከብር፣ አምላክን የሚሳደብ ብለው በሐሰት ወንጅለውታል። (ማቴ. 11:19፤ 26:65፤ ሉቃስ 11:15፤ ዮሐ. 9:16) ሆኖም ኢየሱስ በቁጣ በመናገር ብድር አልመለሰም። እኛም እንደ ኢየሱስ ሰዎች ሲያመናጭቁን አጸፋውን ከመመለስ መቆጠብ ይኖርብናል። (1 ጴጥ. 2:21-23) እርግጥ ነው፣ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስሜትን መቆጣጠር ቀላል አይደለም። (ያዕ. 3:2) ታዲያ ምን ሊረዳን ይችላል?
9. በስብከቱ ሥራ ስንካፈል አንደበታችንን ለመቆጣጠር ምን ይረዳናል?
9 አገልግሎት ላይ አንድ ሰው በቁጣ ሲናገርህ፣ ከሰጠው ምላሽ ባሻገር ያለውን ለማስተዋል ጥረት አድርግ። ሳም የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የማነጋግረው ሰው መልእክቱን መስማት ምን ያህል እንደሚያስፈልገው እንዲሁም ነገ ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል ለማሰብ እሞክራለሁ።” አንዳንድ ጊዜ አገልግሎት ላይ ሰዎች የሚቆጡት ጥሩ ስሜት ላይ ባልነበሩበት ሰዓት ላይ ስላነጋገርናቸው ብቻ ሊሆን ይችላል። ሉሲያ የተባለች እህት የሚቆጣ ሰው ሲያጋጥማት አጭር ጸሎት ታቀርባለች፤ መረጋጋት እንድትችልና ቅር የሚያሰኝ ነገር እንዳትናገር እንዲረዳት ይሖዋን ትለምነዋለች። እኛም ሰዎች አገልግሎት ላይ ሲበሳጩ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን።
10. በ1 ጢሞቴዎስ 4:13 መሠረት ምን ግብ ሊኖረን ይገባል?
10 የማስተማር ችሎታህን አሻሽል። ጢሞቴዎስ ተሞክሮ ያለው ክርስቲያን አገልጋይ ነበር፤ ያም ቢሆን መንፈሳዊ እድገት ማድረጉን መቀጠል ነበረበት። (1 ጢሞቴዎስ 4:13ን አንብብ።) እኛስ በአገልግሎት ላይ የማስተማር ችሎታችንን ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? ጥሩ ዝግጅት ማድረግ አለብን። ደስ የሚለው፣ የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱን ብዙ መሣሪያዎች አሉን። ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ የተባለውን ብሮሹርና በክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ የሚገኘውን “በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ተጣጣር” የሚለውን ዓምድ መመልከት ትችላለህ። ታዲያ እነዚህን መሣሪያዎች በሚገባ እየተጠቀምክባቸው ነው? ጥሩ ዝግጅት ስናደርግ ፍርሃታችን ይቀንሳል፤ እንዲሁም ይበልጥ በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።
11. አንዳንድ ክርስቲያኖች የማስተማር ችሎታቸውን ለማሻሻል የረዳቸው ምንድን ነው?
11 የማስተማር ችሎታችንን ማሻሻል የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በጉባኤው ውስጥ ሌሎች የሚያስተምሩበትን መንገድ ማየትና ምሳሌያቸውን መኮረጅ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሳም ጥሩ የማስተማር ችሎታ ያላቸው ክርስቲያኖች ለዚህ የረዳቸው ምን እንደሆነ ለማሰብ ይሞክራል። የሚጠቀሙበትን ዘዴ ልብ ብሎ ይመለከታል፤ ከዚያም ምሳሌያቸውን ለመኮረጅ ጥረት ያደርጋል። ታሊያ የተባለች እህት ደግሞ የሕዝብ ንግግር በመስጠት ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች ነጥቦቻቸውን የሚያዋቅሩበትን መንገድ ለማስተዋል ጥረት ታደርጋለች። ይህም አገልግሎት ላይ ብዙ ጊዜ የሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮችን ለማብራራት ረድቷታል።
በስብሰባዎች ላይ አርዓያ ሁን
12. አንዳንዶች ምን ማድረግ ይከብዳቸዋል?
12 ድምፃችንን ከፍ አድርገን በመዘመርና በሚገባ ተዘጋጅተን መልስ በመስጠት ሁላችንም ስብሰባዎቻችን ያማሩ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን። (መዝ. 22:22) አንዳንዶች፣ ሰው በተሰበሰበበት መዘመር ወይም መልስ መስጠት ይከብዳቸዋል። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ከሆነ አንዳንዶች ፍርሃታቸውን ማሸነፍ የቻሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅህ ይጠቅምሃል።
13. በስብሰባዎች ላይ ከልብህ ለመዘመር ምን ሊረዳህ ይችላል?
13 ከልብ ዘምር። የመንግሥቱን መዝሙሮቻችንን የምንዘምርበት ዋነኛው ምክንያት ይሖዋን ማወደስ ነው። ሣራ የተባለች እህት መዝሙር ላይ ጎበዝ እንደሆነች አይሰማትም። ሆኖም ይሖዋን በመዝሙር ማወደስ ደስ ይላታል። ስለዚህ ለሌሎቹ የስብሰባው ክፍሎች እንደምትዘጋጀው ሁሉ መዝሙሮቹን አስቀድማ ቤቷ ትለማመዳለች። መዝሙሮቹን ስትለማመድ ግጥሞቹ ስብሰባው ላይ ከሚቀርቡት ክፍሎች ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ለማስተዋል ትሞክራለች። “እንዲህ ማድረጌ በመዘመር ችሎታዬ ላይ ሳይሆን በመልእክቱ ላይ ይበልጥ ማተኮር እንድችል ረድቶኛል” ብላለች።
14. ዓይናፋር ከሆንክ በስብሰባ ላይ መልስ ለመስጠት ምን ሊረዳህ ይችላል?
14 አዘውትረህ ተሳትፎ አድርግ። ይህ አንዳንዶችን በጣም ሊከብዳቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ታሊያ እንዲህ ብላለች፦ “ፍርሃቴ ድምፄ ላይ ስለማያስታውቅ ሰዎች ችግር እንዳለብኝ አያውቁም እንጂ ሰው በተሰበሰበበት መናገር በጣም ይጨንቀኛል። ስለዚህ ስብሰባ ላይ ሐሳብ መስጠት በጣም ያታግለኛል።” ይህ ግን ታሊያን ስብሰባ ላይ ተሳትፎ ከማድረግ አላገዳትም። ለስብሰባ ስትዘጋጅ የጥያቄው የመጀመሪያ መልስ አጭርና ቀጥተኛ መሆን እንዳለበት ለማስታወስ ጥረት ታደርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ስለዚህ መልሴ አጭር፣ ቀላልና ቀጥተኛ ቢሆን ምንም ስህተት የለውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም መሪው የሚፈልገውም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱን መልስ ነው።”
15. መልስ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ምን ልናስታውስ ይገባል?
15 ዓይናፋር ያልሆኑ ክርስቲያኖችም እንኳ ሐሳብ ከመስጠት ወደኋላ የሚሉበት ጊዜ አለ። ለምን? ጁልየት የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ መልስ ለመስጠት እጄን የማላወጣው መልሴ በጣም ቀላል እንደሆነና ብዙም ጥቅም እንደሌለው ስለሚሰማኝ ነው።” ይሁንና መልስ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ይሖዋ የሚጠብቅብን ምርጣችንን እንድንሰጠው ብቻ እንደሆነ አስታውስ።c ፍርሃታችንን አሸንፈን እሱን በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለማወደስ የምናደርገውን ልዩ ጥረት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።
ከሌሎች ጋር ስታወራ አርዓያ ሁን
16. ምን ዓይነት ንግግር ከአፋችን ሊወጣ አይገባም?
16 ማንኛውም ዓይነት “ስድብ” ከአፍህ አይውጣ። (ኤፌ. 4:31) ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ስድብ ከክርስቲያኖች አንደበት ጨርሶ ሊወጣ አይገባም። ሆኖም አንዳንድ የንግግር ዓይነቶች በቀጥታ ስድብ ላይመስሉ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሌሎች ባሕሎች፣ ዘሮች ወይም ብሔሮች ስናወራ አንዱን ከሌላው ዝቅ እንዳናደርግ መጠንቀቅ ይኖርብናል። በሽሙጥ በመናገር ሌሎችን እንዳንጎዳም መጠንቀቅ አለብን። አንድ ወንድም እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “አንዳንድ ጊዜ ለቀልድ ብዬ የምናገረው የሽሙጥ ንግግር ሌላውን ሰው ሊጎዳ እንደሚችል በኋላ ላይ አስተውያለሁ። ባለቤቴ እሷንም ሆነ ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ነገር ስናገር በግሌ ትነግረኛለች፤ ይህም በዓመታት ሂደት ለውጥ እንዳደርግ በጣም ረድቶኛል።”
17. ኤፌሶን 4:29 እንደሚለው ሌሎችን ማነጽ የምንችለው እንዴት ነው?
17 ንግግርህ የሚያንጽ ይሁን። ከመተቸት ወይም ከማጉረምረም ይልቅ ማመስገን የሚቀናህ ሁን። (ኤፌሶን 4:29ን አንብብ።) እስራኤላውያን አመስጋኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሷቸው ብዙ ነገሮች ነበሯቸው፤ እነሱ ግን ነጋ ጠባ ያጉረመርሙ ነበር። የአጉረምራሚነት መንፈስ ይጋባል። አሥሩ ሰላዮች ይዘው የመጡት መጥፎ ወሬ ያስከተለውን መጥፎ ውጤት ታስታውሳለህ፤ በእነሱ የተነሳ ‘እስራኤላውያን በሙሉ በሙሴ ላይ ያጉረመርሙ ጀመር።’ (ዘኁ. 13:31 እስከ 14:4) በሌላ በኩል ደግሞ ማመስገን በሌሎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። የዮፍታሔ ልጅ የጓደኞቿን ምስጋና መስማቷ በአገልግሎቷ ለመጽናት በእጅጉ እንደረዳት ምንም ጥያቄ የለውም። (መሳ. 11:40) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሣራ እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎችን ስናመሰግን ይሖዋ እንደሚወዳቸው እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥ ቦታ እንዳላቸው እንዲሰማቸው እናደርጋለን።” እንግዲያው ሌሎችን ከልብህ ለማመስገን አጋጣሚዎች ፈልግ።
18. በመዝሙር 15:1, 2 መሠረት እውነቱን መናገር ያለብን ለምንድን ነው? ይህስ ምንን ይጨምራል?
18 እውነቱን ተናገር። እውነቱን የማንናገር ከሆነ ይሖዋን ማስደሰት አንችልም። እሱ ማንኛውንም ዓይነት ውሸት ይጠላል። (ምሳሌ 6:16, 17) በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች ውሸት ምንም ችግር እንደሌለው ቢሰማቸውም እኛ ስለ ጉዳዩ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን እንፈልጋለን። (መዝሙር 15:1, 2ን አንብብ።) ዓይን ያወጣ ውሸት እንደማንናገር የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሌሎች የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ የሚያደርግ ነገርም ሆን ብለን አንናገርም።
19. ሌላው ልናስወግድ የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
19 ሐሜት አታሰራጭ። (ምሳሌ 25:23፤ 2 ተሰ. 3:11) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጁልየት ሐሜት የሚያሳድርባትን ስሜት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ሐሜት ሲወራልኝ ደስ የሚል ስሜት አይሰማኝም፤ ሐሜት በሚናገረው ሰው ላይ ያለኝ እምነት ይጠፋል። እኔንም ለሌላ ሰው እንደማያሙኝ በምን እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?” ከሌሎች ጋር ስታወራ ነገሩ ወደ ሐሜት እየተቀየረ እንደሆነ ካስተዋልክ ወሬው ወደ አዎንታዊ ነገር እንዲያመራ ለማድረግ ጥረት አድርግ።—ቆላ. 4:6
20. አንደበትህን እንዴት ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል?
20 የምንኖረው መጥፎ ንግግር በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ነው። በመሆኑም ይሖዋን የሚያስደስት አነጋገር እንዲኖረን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። የመናገር ችሎታ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ እንደሆነና አንደበታችንን ለምንጠቀምበት መንገድ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውስ። በአገልግሎትና በስብሰባዎች ላይ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ስናወራ ጥሩ አነጋገር እንዲኖረን የምናደርገውን ልባዊ ጥረት ይባርካል። ፈሪሃ አምላክ የሌለው ይህ ሥርዓት በቅርቡ ሲጠፋ ይሖዋን በአንደበታችን ማክበር በጣም ቀላል ይሆንልናል። (ይሁዳ 15) እስከዚያው ግን ‘የአፍህ ቃል’ ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።—መዝ. 19:14
መዝሙር 121 ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል
a ይሖዋ የሰጠን የመናገር ችሎታ አስደናቂ ስጦታ ነው። የሚያሳዝነው፣ ብዙ ሰዎች ይህን ስጦታ የሚጠቀሙበት ይሖዋን በሚያስደስተው መንገድ አይደለም። በሥነ ምግባር እያዘቀጠ በሄደው በዚህ ዓለም ውስጥ ንግግራችን ንጹሕና የሚያንጽ እንዲሆን ምን ይረዳናል? በአገልግሎት ስንካፈል፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ስናወራ በንግግራችን ይሖዋን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።
b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
c በስብሰባ ላይ መልስ መስጠትን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በጥር 2019 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በጉባኤ መካከል ይሖዋን አወድሱ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም አገልግሎት ላይ የተቆጣ ሰው አጋጥሞት እሱም በቁጣ እየመለሰ ነው፤ አንድ ወንድም ስብሰባ ላይ ሌሎች ሲዘምሩ እሱ ዝም ብሎ ቆሟል፤ አንዲት እህት ሐሜት እያወራች ነው።