አረጋውያንን መንከባከብ ፈታኝም የሚክስም ነው
ሺኔጹ የሚባል አንድ ክርስቲያን አገልጋይ በተሰጠው የሥራ ምድብ በጥልቅ ተደስቶ ነበር። ሦስት አባላት ያለው ቤተሰቡ የሚስቱን እናት የሚጨምር ነበር። ከሚስቱ ጋር እየተጓዘ ሌሎች ጉባኤዎችን ለመጎብኘት ይችል እንደሆነ እንዲያስብበት እስከተጠየቀበት ቀን ድረስ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስተማር በአንድ አነስተኛ የይሖዋ ምስክሮች ጉባኤ ውስጥ በደስታ ይሠራ ነበር። ይህ ሥራ በየሣምንቱ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ነበር። በተሰጠው ዕድል ከፍተኛ ደስታ ተሰማው፤ ነገር ግን እናትየዋን ማን ይንከባከባል?
ብዙ ቤተሰቦች በዕድሜ የገፉ ወላጆችን እንዴት በተሻለ ሁኔታ መንከባከብ ይቻላል? የሚለው ተመሳሳይ ፈታኝ ሁኔታ ውሎ አድሮ ያጋጥማቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች ገና በደህና ጤንነትና በሥራ ላይ ሳሉ ጉዳዩ እምብዛም አያሳስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ትንንሽ ነገሮች ማርጀት መጀመራቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። ለምሳሌ በመርፌ ቀዳዳ ውስጥ ክር ሲያስገቡ መንቀጥቀጣቸው፣ ወይም አንድን የተበላሸ ነገር ለመጨረሻ ጊዜ ያዩት መቼ እንደሆነ አለማታስወሳቸው አንዳንዱ ምልክት ነው። ብዙውን ጊዜ ግን አረጋውያን ስለሚያስፈልጋቸው ነገሮች የሚያስገነዝብ አንድ ድንገተኛ አደጋ ወይም ሕመም ሊፈጠር ይችላል። በዚህ ጊዜ አንድ ነገር መደረግ አለበት።
በአንዳንድ አገሮች ወላጆች በመጠኑም ቢሆን ጥሩ ጤንነት ካላቸው የኋለኞቹን ወርቃማ ዓመታት ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ከማሳለፍ ይልቅ ብቻቸውን ሆነው ማሳለፍን ይመርጣሉ። በምሥራቅና በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ባሉ ብዙ አገሮች ውስጥ ግን በዕድሜ የገፉ ሰዎች ከልጆቻቸው ጋር በተለይም ከትልቁ ወንድ ልጃቸው ጋር መኖራቸው የተለመደ ነገር ነው። በተለይ ከወላጆች አንዱ የአልጋ ቁራኛ ከሆነ ይህ ሁኔታ የማይቀር ነገር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በጃፓን 65 ዓመትና ከዚያም በላይ የሆናቸው በጥቂቱም ቢሆን የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ወደ 24,000 የሚጠጉ አረጋውያን የሚኖሩት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነው።
ሥነ ምግባራዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች
ምንም እንኳን ብዙዎች “የተፈጥሮ ፍቅር” የጎደላቸውና “ራሳቸውን የሚወድዱ” በሆኑበት ትውልድ ውስጥ የምንኖር ብንሆንም አረጋውያንን በተመለከተ ግልጽ የሆኑ ሥነ ምግባራዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች አሉን። (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ፓርኪሰንዝ የተባለ የነርቭ በሽታ ያለባቸውን በዕድሜ የገፉ እናቷን የምትንከባከብ ቶሜኮ የተባለች ሴት ለእናቷ የሚሰማትን ሥነ ምግባራዊ ግዴታ ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ለ20 ዓመታት ተንከባክባኛለች። እኔ ደግሞ አሁን ይህኑ ነገር ለእርሷ ላደርግላት እፈልጋለሁ።” ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “የወለደህን አባትህን ስማ፣ እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” በማለት አጥብቆ መክሯል። — ምሳሌ 23:22
በማያምነው ወላጅ በኩል የሚኖር ቀለል ያለ ወይም ኃይለኛ ሃይማኖታዊ ጥላቻ ይህንን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ አይሽረውም። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “ነገር ግን ለእርሱ ስለሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” ሲል በመንፈስ መሪነትና አነሳሽነት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ካከናወናቸው የመጨረሻ ተግባሮች አንዱ እናቱ እንክብካቤ የምታገኝበትን መንገድ ማዘጋጀቱ ስለ ነበር በዚህ በኩል ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። — ዮሐንስ 19:26, 27
የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቋቋም
ቤተሰቦች ለብዙ ዓመታት ተለያይተው ከኖሩ በኋላ እንደገና አንድ ላይ መኖር ሲጀምሩ ሁሉም ብዙ ማስተካከያዎችን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ለውጦች ለማድረግ ከፍተኛ ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና የሌላውን ችግር መረዳትን የሚጠይቅ ነው። ታላቁ ልጅ ወይም ሌላ ወንድ ወይም ሴት ልጅ ቤተሰቡን ይዞ ወደ ወላጆቹ ቤት ቢገባ አዳዲስ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ። አዲስ ሥራ መያዝ፣ ልጆችን አዲስ ትምህርት ቤት ማስገባትና ከአዲስ አካባቢ ጋር መለማመድ ያስፈልግ ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ሚስቲቱ ሥራ ይጨምርባታል።
ማስተካከያ ማድረጉ ለወላጆችም ቢሆን ከባድ ነው። የተወሰነ የግል ኑሮ፣ ጸጥታና ነጻነት ለምደው ይሆናል። አሁን ግን ትኩስ ኃይል ያላቸው የልጅ ልጆቻቸውና የጓደኞቻቸው ጩኸትና ረብሻ ይኖራል። የራሳቸውን ውሳኔ ሲያደርጉ ቆይተው ነበር። ስለዚህ እነሱን ለመምራት የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ ላያስደስታቸው ይችላል። ብዙ ወላጆች የወንዶች ልጆቻቸው ቤተሰቦች አንድ ቀን ከእነርሱ ጋር ለመኖር እንደሚመጡ አስቀድመው በማየት በቤታቸው ጎን ሌላ ቤት ይሠራሉ፤ ወይም ተጨማሪ ክፍሎችን በመቀጠል በኮሪደሮች አገናኝተው ለሁሉም የተወሰነ ነፃነትን የሚሰጥ ሁኔታ ያዘጋጃሉ።
ቤቱ አነስተኛ ከሆነ ደግሞ አዲስ ለሚመጡት ሰዎች የሚኖሩበት ክፍል እንዲያገኙ ሲባል ከዚህ የበለጠ ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል። አንዲት እናት አራት ሴቶች ልጆቿ ለ80 ዓመት ሴት አያታቸው ክፍል ለማዘጋጀት ሲባል መኝታ ቤታቸው ውስጥ ተጨማሪ ዕቃዎችና ሌሎች ነገሮች መቀመጥ ሲጀምሩ ምን ያህል ተበሳጭተው እንደነበረ ስታስታውስ ትስቃለች። አሁንም ቢሆን ማስተካከያዎች የማድረጉን አስፈላጊነት ሁሉም እየተቀበሉት ሲሄዱና ፍቅር “የራሱ የሆነውን አይፈልግም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥብቅ ምክር ሲያስታውሱ ከእነዚህ ችግሮች አብዛኞቹ ሊቃለሉ ይችላሉ። — 1 ቆሮንቶስ 13:5
ነጻነት ማጣት
ባሏ የእምነቷ ተካፋይ ካልሆነና ቤተሰቡን ይዞ ወደ ወላጆቹ ቤት ለመግባት ቢወስን አንዲት ክርስቲያን ሴት ከባድ ችግር ይፈጠርባት ይሆናል። ያን ሁሉ ቤተሰብ መያዙ የሚጠይቀው ብዙ ሥራ ክርስቲያናዊ ግዴታዎቿን ከሌሎቹ ሥራዎች ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን የማይቻል ሊመስላት ይችላል። ሴጹኮ እንዲህ አለች:- “ባለቤቴ የጃጁ እናቱን እቤት ውስጥ ብቻቸውን መተው አደገኛ እንደሆነ ተሰማው። ስለዚህ ሁልጊዜ እቤት እንድሆን ፈለገ። ስብሰባ ለመሄድ ከሞከርኩ ይበሳጭና ቅሬታ ያሰማል። በጃፓን ኅብረተሰብ ውስጥ ስላደግሁ እኔም በመጀመሪያ ላይ እሳቸውን ብቻቸውን ትቶ መሄድ ስህተት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ችግሮቹ ሊፈቱ የሚችሉ እንደሆኑ ተገነዘብኩ።”
ሂሳኮም ተመሳሳይ ችግር ነበረባት። “ከባለቤቴ ቤተሰቦች ጋር ለመኖር ወደ ቤታቸው ስንገባ ባለቤቴ ዘመዶቹ የሚያስቡትን ነገር በመፍራት ሃይማኖቴን እንድለውጥና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎቼን እንዳቆም ፈለገ። ይባስ ብሎ ደግሞ እሁድ እሁድ በአቅራቢያው የሚኖሩ ዘመዶች እኛን ለመጠየቅ ይመጡ ስለነበር ወደ ስብሰባዎች ለመሄድ አስቸጋሪ ሆነብኝ። ከዚህም በተጨማሪ ልጆቹ ወደ ስብሰባዎች ከመሄድ ይልቅ ከአጎታቸውና ከአክስታቸው ልጆች ጋር ለመጫወት ይፈልጉ ነበር። መንፈሳዊነታችን እየተጐዳ እንዳለ ለማየት ችዬ ነበር። ቁርጥ ያለ አቋም በመውሰድ ሃይማኖቴ እንደ ልብስ ሊቀየር የሚችል ነገር እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ ለእኔ በጣም ትልቅ ቁምነገር መሆኑን ማስረዳት ነበረብኝ። ከጊዜ በኋላ የቤተሰቡ ሁኔታ ተስተካከለ።”
አንዳንዶች በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ቀን እየመጣች የምትረዳቸውን የትርፍ ሰዓት የቤት ሠራተኛ በመቅጠር ተጨማሪ ነፃ ጊዜ በማግኘት በኩል ያለውን ችግር ሊያቃልሉ ችለዋል። ሌሎች ደግሞ አንዳንድ ቦታ ለመሄድና ለክርስቲያናዊ ሥራዎቻቸው የሚሆን የተወሰነ ነፃነት ያገኙት የልጆቻቸውን፣ በአቅራቢያ ያሉ ዘመዶቻቸውንና እንዲያውም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ጓደኞቻቸውን እርዳታ በመጠየቅ ነው። ባሎችም ቢሆኑ በምሽቶችና በሳምንቱ መጨረሻ ቀኖች ላይ እቤት በሚሆኑበት ጊዜ እርዳታ ሊሰጡ ችለዋል። — መክብብ 4:9
በሥራ እንዲያዙ ማድረግ
በዕድሜ የገፉትን በሥራ እንዲያዙ ማድረግም ሌላው ሊቀበሉት የሚገባ ሁኔታ ነው። አንዳንድ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ወጥ መሥራትና በሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎች መካፈል ደስ ይላቸዋል። ልጆቹን እንዲጠብቁ ቢጠየቁ ተፈላጊነት እንዳላቸው ይሰማቸዋል፤ እንዲሁም አንድን አነስተኛ የጓሮ አትክልት ወይም አበቦችን ቢንከባከቡ አለበለዚያም በአንድ ዓይነት የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያ ቢካፈሉ እርካታ ያገኛሉ።
ሌሎች ግን አብዛኛውን ጊዜ ተኝተው እንዲውሉና ሰው እንዲጠብቃቸው ይፈልጋሉ። ነገር ግን በተቻለ መጠን በሥራ እንዲሳተፉ ማድረግ ለራሳቸው ደህንነት፣ ዕድሜ ለመጨመርና ለአእምሮ ንቃት በጣም አስፈላጊ ነው። ሂዴኮ ምንም እንኳን እናቷ በተሽከርካሪ ወንበር የሚሄዱ ቢሆኑም እናቷ ተፈላጊ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ለማድረግ ያስፈልግ የነበረው ነገር እሳቸውን ወደ ስብሰባዎች መውሰድ ነበር። ሁሉም ሞቅ ባለ ሁኔታ ይቀበሏቸውና በውይይቶችም ውስጥ ተካፋይ እንዲሆኑ ያደርጓቸው ነበር። ለሳቸው የተሰጣቸው ትኩረት የኋላ ኋላ ከአንዲት አሮጊት እህት ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ወደ መስማማት መራቸው። አልዝሄመርዝ በሚባል ቶሎ መጃጀትን የሚያስከትል በማዕከላዊ ሥርዓተ–ነርቭ በሽታ የሚሰቃዩ አንድን እናት የሚንከባከቡ ባልና ሚስት ሴትየዋን ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወሰዷቸው። “በጠቅላላው ምንም ነገር ማድረግ አይፈልጉም ነበር” ሲሉ የተገነዘቡትን ተናገሩ። “በስብሰባዎች ጊዜ ግን ደስተኛ ይሆናሉ። ሞቅ ያለ አቀባበል ስለሚደረግላቸው በፈቃደኝነት ይሄዳሉ። እዚያ መሄዳቸው በጣም እንደጠቀማቸው ይሰማናል።”
በዚህ ርዕሰ ትምህርት መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሺኔጹ ተጓዥ አገልጋይ ሆኖ በሚሠራበት አካባቢ አማካይ ቦታ ላይ ለሚስቱ እናት የሚሆን አንድ አፓርታማ በማግኘቱ ለችግሩ መፍትሄ አግኝቷል። በዚህ መንገድ በየሳምንቱ የተለያዩ ጉባኤዎችን በሚጎበኝበት ጊዜ በመካከል ባለው እረፍት ከእሳቸው ጋር ለመቆየት ቻሉ። ሚስቱ ክዮኮ እንዲህ አለች:- “እናቴ በጣም አስፈላጊ የሆነው ሥራችን ክፍል እንደሆነችና ተፈላጊ እንደሆነች ይሰማታል። ባለቤቴ አንድ ልዩ ምግብ እንድትሠራልን ሲጠይቃት ደስ ይላታል።”
ከመጃጀት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን መቋቋም
ወላጆች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ በየደረጃው የሚለያይ የመጃጀት ጠባይ ያሳያሉ። ስለዚህ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። ቀናትን፣ ሰዓታትን፣ ወቅቶችንና የገቡትን ቃል ይረሳሉ። ጸጉራቸውን መቆረጥና ልብሳቸውን ማጠብ ይዘነጉ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ እንዴት መልበስና ገላቸውን መታጠብ እንዳለባቸው እንኳን ይረሱ ይሆናል። ብዙዎች ግራ የሚጋቡ ይሆናሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሌሊት እንቅልፍ አይወስዳቸውም። አንዴ የተናገሩትን ነገር ደጋግመው የማውራት ዝንባሌ አላቸው። ይህ ሲነገራቸው ደግሞ ደስ አይላቸውም። አእምሮአቸው ያታልላቸዋል። አንድ ነገር እንደተሰረቁ ወይም ዘራፊዎች ቤቱን ሰብረው ሊገቡ እንደሆነ የምራቸውን ይናገሩ ይሆናል። አራት ሴቶች ልጆች ያሉበት አንድ ቤተሰብ ሴት አያታቸው ልጆቹ የጾታ ብልግና ፈጽመዋል እያሉ የሚያሰሙትን መሠረተ ቢስ የሆነ የማያቋርጥ ስሞታ መቻል ነበረባቸው። እንዲህ አሉ:- “ነገሩ ደስ የማይል ነበር፤ ነገር ግን ክሱን መቻልና የውይይታችንን ርዕስ ለመቀየር መሞከርን ተምረናል። ከአያታችን ጋር ልክ አይደለሽም ብሎ መጨቃጨቅ ከንቱ ነበር።” — ምሳሌ 17:27
መሟላት የሚኖርባቸው ስሜታዊ ፍላጎቶች
ዕድሜ በአረጋውያን ላይ ፈታኝ ሁኔታዎችን ያመጣባቸዋል። ጽናትን የሚጠይቁ የሚየሰቃዩ በሽታዎች፣ መንቀሳቀስ አለመቻልና የአእምሮ ጭንቀት አሉባቸው። ብዙዎች ሕይወታቸው አቅጣጫ ወይም ዓላማ እንደሌለው ይሰማቸዋል። ሸክም እንደሆኑ ይሰማቸውና መሞት እንደሚሻላቸው ይናገሩ ይሆናል። እንዲወደዱ፣ እንዲከበሩና ሌሎች በኅብረት በሚያደርጓቸው ነገሮች እንዲካፈሉ ይፈልጋሉ። (ዘሌዋውያን 19:32) ሂሳኮ እንዲህ አለች:- “እማማ በሚኖሩበት ጊዜ ሁሉ በውይይታችን ውስጥ እንዲገቡ ለማድረግ እንሞክራለን። ከተቻለም ውይይቱ በእርሳቸው ላይ እንዲያተኩር እናደርጋለን።” ሌላው ቤተሰብ ደግሞ ወንድ አያታቸው የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውይይት እንዲመሩ በመጠየቅ አዛውንቱ ለራሳቸው አክብሮት እንዲሰማቸው ለማድረግ ይጥራል።
ለአረጋውያን ዘወትር ተገቢ አመለካከት ለመያዝ ያለማቋረጥ ጥረት ማድረግ አለብን። የአልጋ ቁራኛ የሆኑ በሽተኞች ዝቅ በሚያደርግ ሁኔታ እንደተናገሯቸው ወይም አክብሮት በጎደለው ሁኔታ እንደያዟቸው ሲሰማቸው በጣም ቅር ይሰኛሉ። አካለ ስንኩል ከሆኑት አማቷ ጋር የምትኖረው ኪሚኮ “እማማ ንቁ ነበሩ፤ ሳስታምማቸው ልቤ ከእሳቸው ጋር እንዳልሆነ ወይም ዝቅ አድርጌ እየተመለከትኋቸው እንደሆነ ያውቁ ነበር” በማለት ስለሁኔታው ተናግራለች። ሂዴኮም አመለካከቷን ማስተካከል ቀላል ሆኖ አላገኘችውም። “አማቴን መንከባከብ ሲኖርብኝ በመጀመሪያ ላይ ተበሳጭቼ ነበር። አቅኚ [የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የሆንኩ የይሖዋ ምስክር] ነበርኩ፤ አሁን ያንን አገልግሎት አጣሁ። ከዚያ ግን አስተሳሰቤን ማስተካከል እንደሚያስፈልገኝ ተመለከትኩ። ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት በጣም አስፈላጊ ቢሆንም ቅሉ ይህም የአምላክን ትዕዛዛት የምንከተልበት በጣም አስፈላጊው ክፍል ነበር። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ደስታ ለማግኘት ከፈለግሁ የበለጠ ፍቅርና በሳቸው ቦታ ሆኜ ማሰብን ማዳበር እንደሚያስፈልገኝ ተገነዘብኩ። የሥራዬ ክፍል ስለሆነ ብቻ እንደ ልምድ አድርጌ አንዳንድ ነገሮችን ሳላስብባቸው በምሠራበት ጊዜ ሕሊናዬን ያስጨንቀኛል። አደጋ ደርሶብኝ ከታመምኩ በኋላ ግን ስለ አማቴና ስለነበረባቸው ሕመም አሰብኩ። ከዚያ በኋላ ለሳቸው ልባዊ ስሜት ማሳየትንና በእርሳቸው ቦታ ሆኜ ማሰብን ቀላል ሆኖ አገኘሁት።”
እንክብካቤ አድራጊዎችም በጥንቃቄ መያዝ ያስፈልጋቸዋል
በዕድሜ የገፉትን የመንከባከቡ ሸክም በተለይ ለወደቀባቸው ሰዎች አድናቆትን የመግለጽ አስፈላጊነት ቸል ተብሎ ሊታለፍ የማይገባው ነው። (ከምሳሌ 31:28 ጋር አወዳድር።) አብዛኞቹ ሴቶች የአድናቆት ቃላትን እያገኙ ወይም ሳያገኙ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ ሥራቸው የሚያጠቃልላቸውን ነገሮች ካሰብንበት እንዲህ ዓይነት የምስጋና ቃላት በእርግጥ ተገቢ መሆናቸውን እንገነዘባለን። የጽዳት፣ ልብስ የማጠብና ምግብ የማብሰል ተጨማሪ ሥራ መኖሩ የማይቀር ነው። በዕድሜ የገፋውን በሽተኛ ወደ ሆስፒታል ወይም ወደ ሐኪም ማመላለሱን፤ እንዲሁም በዕድሜ የገፋውን በሽተኛ ማብላትና ማጠብንም አስቡ። አማቷን ለረጅም ጊዜ ስትንከባከብ የቆየች አንዲት ሴት እንዲህ አለች:- “ባለቤቴ አድናቆቱን በቃላት መግለጽ እንደሚከብደው አውቃለሁ። ነገር ግን እያደረግሁት ያለውን ነገር እንደሚያደንቀው በሌሎች መንገዶች ያሳየኛል።” ትንሽ የምስጋና ቃላት የሚደረገውን ድካም ዋጋማ ሊያደርጉት ይችላሉ። — ምሳሌ 25:11
በብዙ ትካሳላችሁ
ያረጁ ወላጆችን ለአያሌ ዓመታት ሲንከባከቡ የቆዩ ብዙ ቤተሰቦች ይህን ማድረጋቸው እንደ ጽናት፣ ራስን መሥዋዕት ማድረግ፣ ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር፣ ትጋት፣ ራስን ዝቅ ማድረግና ርኅራኄ ያሉ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን እንዲያዳብሩ እንደረዳቸው ተናግረዋል። ብዙ ቤተሰቦች በስሜትም እርስ በርስ የተቀራረቡ ሆነዋል። ሌላው ጥቅም ደግሞ ከወላጆች ጋር ይበልጥ የመነጋገርና እነርሱን የበለጠ ለማወቅ የሚያስችል አጋጣሚ ማግኘቱ ነው። ሂሳኮ ስለ አማቷ እንዲህ አለች:- “ደስ የሚል ሕይወት አሳልፈዋል። ብዙ ችግሮችም አጋጥሟቸዋል። እሳቸውን የበለጠ ለማወቅና ካሁን በፊት ያልተገነዘብኳቸውን ባሕርዮቻቸውን ማድነቅን ተምሬአለሁ።”
የባሏን ወላጆችና የአልጋ ቁራኛ የሆኑትን አያቱን የምትንከባከበው ኪሚኮ “መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናቴ በፊት ከባሌ ተፋትቼ ከሁኔታው ለመሸሽ የፈለግሁበት ጊዜ ነበር” በማለት ተናግራለች። “ከዚያም ‘ባልቴቶችን በመከራቸው መጠየቅ’ እንዳለብን አነበብኩ። (ያዕቆብ 1:27) የቻልኩትን ያህል አድርጌአለሁ። ስለዚህ አሁን ከቤተሰቡ ውስጥ ማንም ቢሆን ስለ እምነቴ ትክክለኛ የሆነ ቅሬታ ሊያሰማ አይችልም። ሕሊናዬ ንጹሕ ነው።” ሌላው ደግሞ እንዲህ አለ:- “የአዳም ኃጢአት ያመጣውን አሠቃቂ ውጤት በዓይኖቼ ስለተመለከትኩ የቤዛውን አስፈላጊነት ይበልጥ ተገንዝቤአለሁ።”
በቅርቡ ሌላ ተጨማሪ የቤተሰባቸሁ አባል ወደ ቤታችሁ ይመጣልን? ወይም ምናልባት ካረጁ ወላጆቻችሁ ጋር አብራችሁ ለመኖር ወደ ቤታቸው ትሄዳላችሁን? የማወላወል ስሜት አላችሁን? ለምን እንደዚያ እንደሚሰማችሁ መረዳት አያቅትም። መደረግ ያለባቸው ለውጦችና ማስተካከያዎች ይኖራሉ። ሆኖም ፈታኙን ሁኔታ ከተወጣችሁት በጣም እንደምትካሱ ምንም አትጠራጠሩ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አረጋውያን እንደተወደዱና እንደተከበሩ እንዲሰማቸው ያስፈልጋቸዋል