“በጌታ ኢየሱስ እመን”—ለመዳን በኢየሱስ ማመን ብቻ በቂ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሰው ልጆችን ኃጢአት ለማስተሰረይ ሲል እንደሞተ ያምናሉ። (1 ጴጥሮስ 3:18) ይሁንና ለመዳን ኢየሱስ አዳኝ እንደሆነ ማመን ብቻውን በቂ አይደለም። አጋንንትም እንኳ ኢየሱስ “የአምላክ ልጅ” እንደሆነ ያውቃሉ፤ ሆኖም አጋንንት የሚጠብቃቸው ጥፋት እንጂ መዳን አይደለም።—ሉቃስ 4:41፤ ይሁዳ 6
ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?
ኢየሱስ ለኃጢአታችን ሲል እንደሞተ ማመን ይኖርብሃል። (የሐዋርያት ሥራ 16:30, 31፤ 1 ዮሐንስ 2:2) ይህም ኢየሱስ መኖሩንና መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ የሚናገረው ነገር በሙሉ ትክክል መሆኑን ማመንን ይጨምራል።
መጽሐፍ ቅዱስን ተማር። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ሐዋርያው ጳውሎስና ሲላስ ለአንድ የእስር ቤት ጠባቂ “በጌታ ኢየሱስ እመን፤ [ትድናለህ]” እንዳሉት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከዚያም “የይሖዋንa ቃል” አስተማሩት። (የሐዋርያት ሥራ 16:31, 32) ይህ ዘገባ የእስር ቤቱ ጠባቂ ስለ አምላክ ቃል እውቀት ሳይኖረው በኢየሱስ ማመን እንደማይችል ያሳያል። በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ያስፈልገው ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
ንስሐ ግባ። (የሐዋርያት ሥራ 3:19) ንስሐ መግባት ማለትም ቀደም ሲል በሐሳብም ሆነ በድርጊት ለፈጸምከው ኃጢአት ከልብ መጸጸት ይኖርብሃል። አምላክን የሚያሳዝን ድርጊት መፈጸምህን ትተህ “ለንስሐ የሚገባ ሥራ” ስትሠራ ሌሎች ሰዎችም ንስሐ መግባትህን ማየት ይችላሉ።—የሐዋርያት ሥራ 26:20
ተጠመቅ። (ማቴዎስ 28:19) ኢየሱስ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን የሚፈልጉ ሰዎች መጠመቅ እንዳለባቸው ተናግሯል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የእስር ቤት ጠባቂም ተጠምቋል። (የሐዋርያት ሥራ 16:33) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጴጥሮስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለ ኢየሱስ ካስተማረ በኋላ “ቃሉን በደስታ የተቀበሉ ተጠመቁ።”—የሐዋርያት ሥራ 2:40, 41
ኢየሱስን ታዘዝ። (ዕብራውያን 5:9) የኢየሱስን ‘ትእዛዛት በሙሉ የሚጠብቁ’ ሰዎች የእሱ ተከታዮች መሆናቸውን በአኗኗራቸው ያሳያሉ። (ማቴዎስ 28:20) እነዚህ ሰዎች ‘ቃሉን የሚያደርጉ ናቸው እንጂ ሰሚዎች ብቻ አይደሉም።’—ያዕቆብ 1:22
እስከ መጨረሻው ጽና። (ማርቆስ 13:13) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለመዳን ‘መጽናት ያስፈልጋቸዋል።’ (ዕብራውያን 10:36) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከሆነበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የኢየሱስን ትምህርቶች በጥብቅ የታዘዘ ከመሆኑም ሌላ ለአምላክ ታማኝ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 9:27
“የመዳን ጸሎት” ማቅረብ ለመዳን አስፈላጊ ነው?
በአንዳንድ ሃይማኖቶች ውስጥ ሰዎች “የመዳን ጸሎት” ወይም “የንስሐ ጸሎት” ተብሎ የሚጠራ ጸሎት ያቀርባሉ። በጸሎቱ ላይ፣ ኃጢአተኛ መሆናቸውን በመቀበል ኢየሱስ ለኃጢአታቸው መሞቱን እንደሚያምኑ ይገልጻሉ። በተጨማሪም ኢየሱስ ወደ ልባቸው ወይም ወደ ሕይወታቸው እንዲገባ ልመና ያቀርባሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “የመዳን ጸሎት” ማቅረብ እንዳለብን አይናገርም፤ እንዲያውም ስለዚህ ጉዳይ የሚገልጸው ምንም ነገር የለም።
አንዳንዶች አንድ ሰው “የመዳን ጸሎት” ካቀረበ በኋላ መዳኑ የተረጋገጠ እንደሚሆን ያምናሉ። ሆኖም የመዳን ዋስትና ሊሰጥ የሚችል ጸሎት የለም። ሁላችንም ፍጹማን ስላልሆንን በተደጋጋሚ እንሳሳታለን። (1 ዮሐንስ 1:8) ኢየሱስ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት አዘውትረው እንዲጸልዩ ተከታዮቹን ያስተማራቸው ለዚህ ነው። (ሉቃስ 11:2, 4) ከዚህም ሌላ የመዳን ተስፋ የነበራቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ከእምነት ጎዳና በመራቃቸው ወይም አምላክን ከማገልገል ወደኋላ በማለታቸው ምክንያት የመዳን ተስፋቸውን አጥተዋል።—ዕብራውያን 6:4-6፤ 2 ጴጥሮስ 2:20, 21
“የመዳን ጸሎት” ምንጩ ምንድን ነው?
“የመዳን ጸሎትን” አመጣጥ በተመለከተ የታሪክ ምሁራን የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ይህ ልማድ የጀመረው በፕሮቴስታንት ተሃድሶ ወቅት እንደሆነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ ሰዎች “የመዳን ጸሎት” ማቅረብ የጀመሩት በ18ኛውና በ19ኛው መቶ ዘመን በተካሄዱ ሃይማኖታዊ ንቅናቄዎች ወቅት እንደሆነ ይገልጻሉ። ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ልማድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የለውም፤ እንዲያውም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል።
a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።