አምላክ ባስተማረህ መንገድ ሂድ
“ወደ እግዚአብሔር ተራራ . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በፍለጋውም እንሄዳለን።”—ሚክያስ 4:2
1. ሚክያስ በተናገረው መሠረት በመጨረሻው ቀን አምላክ ለሕዝቦቹ ምን ያደርግላቸዋል?
የአምላክ ነቢይ የነበረው ሚክያስ “በመጨረሻው ዘመን” ማለትም በዘመናችን ብዙ ሰዎች አምላክን ለማምለክ በትጋት እንደሚፈልጉ አስቀድሞ ተናግሯል። እነርሱም እርስ በርሳቸው “ወደ እግዚአብሔር ተራራ . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በፍለጋውም እንሄዳለን” እየተባባሉ ይበረታታሉ።—ሚክያስ 4:1, 2
2, 3. ሰዎች ገንዘብን የሚወድዱ ይሆናሉ ሲል ጳውሎስ የተነበየው ትንቢት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?
2 ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:1–5ን ማጥናታችን በነዚህ ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ከአምላክ የተማሩ መሆን የሚያመጣውን ውጤት እንድንገነዘብ ይረዳናል። ባለፈው ርዕስ ጳውሎስ “ራሳቸውን የሚወዱ” እንዳይሆኑ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ የሚሉ ሰዎች የሚያገኟቸውን ጥቅሞች በመመልከት ጥናታችንን ጀምረን ነበር። ጳውሎስ በመጨመር በዘመናችን ሰዎች “ገንዘብን የሚወዱ” ይሆናሉ ብሏል።
3 ይህ አባባል ጊዜያችንን በሚገባ የሚገልጸው መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ዘመናዊውን ታሪክ አጥንቶ የኮሌጅ ዲግሪ መጫን አያስፈልግም። በየዓመቱ በሚልዮን የሚቆጠር ትርፍ እያካበቱ ስለማይረኩ የባንክና የንግድ ድርጅት ኃላፊዎች አላነበብክም? እነዚህ ገንዘብ ወዳዶች ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ስለሚፈልጉ ሕጋዊ ያልሆኑ ዘዴዎችን እንኳን ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም። የጳውሎስ አነጋገር ሀብታሞች ባይሆኑም ለገንዘብ የሚስገበገቡትንና ፈጽሞ የማይረኩትንም ሰዎች ይጨምራል። በአካባቢህ እንዲህ ያሉ ብዙ ሰዎችን ታውቅ ይሆናል።
4-6. ክርስቲያኖች ገንዘብ ወዳዶች እንዳይሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የረዳቸው እንዴት ነው?
4 ጳውሎስ የጠቀሰው ነገር ሊወገድ የማይችል የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርይ ነውን? ከብዙ ዘመናት በፊት የሚከተለውን ሐቅ የተናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዳለው ከሆነ ይህ ሊወገድ የማይችል ነገር አይደለም። እንዲህ በማለት እውነቱን ገልጧል፦ “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” አምላክ ‘ገንዘብ የክፋት ሁሉ ሥር ነው’ እንዳላለ ልብ በል። የክፋት ሁሉ ሥር የሆነው “ገንዘብን መውደድ” ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:10
5 እንዲያውም ጳውሎስ በተናገራቸው ቃላት ዙሪያ ያለው ሐሳብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በውርስ አግኝተውም ይሁን በሐቅ ሠርተው በወቅቱ በነበረው የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ባለጠጎች የነበሩ አንዳንድ ጥሩ ክርስቲያኖች እንደነበሩ ያመለክታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ስለዚህ የኑሮ ደረጃችን ምንም ዓይነት ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ ወዳዶች ከመሆን አደጋ እንድንርቅ ያስጠነቅቀናል። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ አሳዛኝና በጣም የተስፋፋ መጥፎ ጠባይ እንድንርቅ የሚረዳ ተጨማሪ ትምህርት ይሰጣልን? እንዴታ! ለምሳሌ በኢየሱስ የተራራ ስብከት ላይ ይህ ተነግሮናል። በዚህ ስብከት የተገለጸው ጥበብ በመላው ዓለም ከፍተኛ ዝና ያተረፈ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:26–33 ላይ የተናገረውን ተመልከት።
6 በሉቃስ 12:15–21 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው ኢየሱስ ሀብት ለማካበት ሲደክም ኖሮ በድንገት ስለ ሞተ ባለጠጋ ተናግሯል። ኢየሱስ ሊያስገነዝብ የፈለገው ቁም ነገር ምን ነበር? “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፣ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ምክር በተጨማሪ ስንፍናን ያወግዛል፤ ጠንክሮ በሐቅ መሥራትም አስፈላጊ መሆኑን ይናገራል። (1 ተሰሎንቄ 4:11, 12) እንዲህ ያለው ምክር ለዘመናችን አይሠራም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ነገር ግን ይህ ምክር ለዘመናችን ይሠራል፣ በመሥራትም ላይ ነው።
የተማሩና የተጠቀሙ
7. መጽሐፍ ቅዱስ ሀብትን አስመልክቶ የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ ልናደርገው እንደምንችል እርግጠኞች የምንሆንበት ምን ምክንያት አለን?
7 በብዙ አገሮች በሁሉም የኢኮኖሚና የማኅበረሰብ ደረጃዎች ላይ ያሉ እነዚህን ገንዘብን በሚመለከት የተሰጡትን መለኮታዊ መመሪያዎች ሥራ ላይ ያዋሉ ሕያው ምሳሌ የሚሆኑ ወንዶችና ሴቶች ማግኘት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ይህን በማድረጋቸው የይሖዋ ምስክር ያልሆኑ ሰዎች እንኳን ለመመልከት እስኪችሉ ድረስ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጠቅመዋል። ለምሳሌ ያህል ሪልጅየስ ሙቭመንትስ ኢን ኮንተምፕረሪ አሜሪካ በተባለው በፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ የኅትመት ክፍል በተዘጋጀው መጽሐፍ ላይ የሰብዓዊ ባሕርይ ተመራማሪ የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “[ምስክሮቹ] በሰዎች ዘንድ ከበሬታን ለማግኘት በአዲስ መኪና፣ ውድ በሆኑ ልብሶች ወይም በተቀናጣ ኑሮ ላይ እንደማይመኩ በጽሑፎቻቸውና በጉባኤ ስብሰባዎቻቸው ላይ ይነገራቸዋል። በዚሁ ላይ ደግሞ ማንኛውም የይሖዋ ምስክር አሠሪው የሚፈልግበትን የሙሉ ቀን ሥራ በሐቀኝነትና በትጋት መሥራት ይኖርበታል። . . . እንዲህ ያለው ባሕርይ ብዙም ችሎታ የሌለውን ሠራተኛ እንኳን በጣም ተፈላጊ ሠራተኛ ሊያደርገው ይችላል። [በአሜሪካ ውስጥ] በሰሜን ፊላደልፊያ የሚኖሩ ምስክሮች በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የደረጃ እድገት አግኝተዋል።” አምላክ በቃሉ አማካኝነት የሚሰጠውን መመሪያ የተቀበሉ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ መቋቋም አዳጋች እንዲሆንብን የሚያደርጉት ዝንባሌዎች ንቁዎች እንደሆኑ ግልጽ ነው። የእነሱ የሕይወት ተሞክሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወደተሻለና አስደሳች ወደሆነ ሕይወት እንደሚመራን ያረጋግጣል።
8. “ትምክህተኞች፣” “ትዕቢተኞች” እና “ተሳዳቢዎች” የሚሉት ቃላት ሊያያዙ የሚችሉት ለምንድን ነው? የእነዚህ ሦስት ቃላት ትርጉምስ ምንድን ነው?
8 ጳውሎስ ቀጥሎ የጠቀሳቸውን ሦስት ነገሮች ልናያይዛቸው እንችላለን። በመጨረሻው ቀን ሰዎች “ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች” ይሆናሉ። እነዚህ ሦስት ባሕርያት አንድ ባይሆኑም ሁሉም ከኩራት ጋር ይዛመዳሉ። የመጀመሪያው ባሕርይ ‘ትምክህተኝነት’ ነው። አንድ መዝገበ ቃላት እንደሚናገረው እዚህ ላይ የገባው የግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉሙ ‘ከሚገባ በላይ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ’ ወይም ‘ማድረግ የማይችለውን አደርጋለሁ ብሎ ተስፋ መስጠት’ ማለት ነው። ስለዚህ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እዚህ ላይ “ጉረኞች” የሚለውን ቃል ለምን እንደሚጠቀሙ ሊገባን ይችላል። ቀጥሎ የተጠቀሰው “ትዕቢተኞች” ወይም ቃል በቃል ሲተረጎም “ከሌላው የሚበልጡ መስለው የሚታዩ” የሚለው ነው። በመጨረሻ የተጠቀሰው “ተሳዳቢዎች” ነው። ተሳዳቢዎች ሲባል አምላክን ስለሚያዋርዱ ወይም በአምላክ ላይ መጥፎ ቃል ስለሚናገሩ ሰዎች ብቻ መናገሩ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቃሉ በሰዎች ላይ ጎጂ፣ አዋራጅ ወይም የስድብ ቃል የሚናገሩትንም ይጨምራል። ስለዚህ ጳውሎስ የተናገረው አምላክንም ሆነ ሰዎችን ስለሚሳደቡ ሰዎች ነው።
9. ጎጂ ጠባዮች ተስፋፍተው የሚገኙ ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ምን ዓይነት ባሕርይ እንዲያዳብሩ ያበረታታል?
9 ጳውሎስ የተናገራቸው ዓይነት ባሕርያት ካላቸው የሥራ ባልደረቦች ወይም የትምህርት ቤት ጓደኞች ወይም ዘመዶች ጋር ስትሆኑ እንዴት ይሰማችኋል? ኑሯችሁ ቀላል ይሆንላችኋል ወይስ በጊዜያችን ያለውን ሁኔታ መቋቋም እንዳትችሉ በማድረግ ኑሯችሁን ይበልጥ ያወሳስቡባችኋል? የአምላክ ቃል ግን በ1 ቆሮንቶስ 4:7፤ በቆላስይስ 3:12, 13 እንዲሁም በኤፌሶን 4:29 ላይ እንደሚገኙት ያሉ መመሪያዎችን በመስጠት ከእነዚህ ጠባዮች እንድንርቅ ያስተምረናል።
10. የይሖዋ ሕዝቦች መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት በመቀበላቸው ጥቅም እንዳገኙ የሚያመለክተው ምንድን ነው?
10 ክርስቲያኖች ፍጹማን ባይሆኑም እነዚህን ጥሩ ትምህርቶች ሥራ ላይ ማዋላቸው በዚህ አስጨናቂ ዘመን እጅግ ጠቅሟቸዋል። ላ ቺቪልታ ካቶሊካ የተባለው የጣሊያንኛ መጽሔት የይሖዋ ምስክሮች በጣም እየበዙ ከሄዱባቸው ምክንያቶች አንዱን ሲጠቅስ “ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴው አባሎቹ ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋቸውን ጠንካራ ጠባይ ግልጽ በሆነ መንገድ ያስተምራቸዋል” ብሏል። ጸሐፊው “ጠንካራ ጠባይ” ሲሉ “ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች” ናቸው ማለታቸው ነውን? አይደለም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱሳውያን መጽሔት በመቀጠል “ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴው አባሎቹ ከሌሎች ልዩ የሚያደርጋቸውን ጠባይ ግልጽና ጠንካራ በሆነ መንገድ ያስተምራቸዋል። ሃይማኖቱ የፍቅርና የወንድማማችነት፣ እንዲሁም የመረዳዳት መንፈስ ያለበት አቀባበል የሚያገኙበት ቦታ ነው” ሲል ጽፏል። ምስክሮቹ ከሚማሩት ነገር ብዙ ጥቅም በማግኘት ላይ መሆናቸው ግልጽ አይደለምን?
የቤተሰብን አባላት የሚጠቅም ትምህርት
11, 12. ጳውሎስ በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ የሚኖረው ሁኔታ ምን መልክ እንደሚኖረው በትክክል የተነበየው እንዴት ነው?
11 የሚቀጥሉትን እርስ በርሳቸው የሚዛመዱ አራት ነገሮች ደግሞ በአንድ ምድብ ልናጠቃልላቸው እንችላለን። በመጨረሻው ቀን ብዙ ሰዎች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው [ታማኝነት የጎደላቸው፣ አዓት] [የተፈጥሮ አዓት] ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ ጳውሎስ ተንብዮአል። ከእነዚህ መጥፎ ጠባዮች ሁለቱ ማለትም ምስጋና ቢስነትና ታማኝ አለመሆን በአካባቢያችን በጣም የተስፋፉ መሆናቸውን ታውቃላችሁ። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እነዚህን ሁለት ጠባዮች ‘ለወላጆች ባለመታዘዝ’ እና ‘የተፈጥሮ ፍቅር በማጣት’ መካከል ለምን እንዳሰፈራቸው በቀላሉ መገንዘብ እንችላለን። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ አራት ጠባዮች እርስ በርሳቸው የተሳሰሩ ናቸው።
12 ወጣትም ሆነ ሽማግሌ፣ አስተዋይ የሆነ ማንኛውም ሰው፣ ለወላጆች አለመታዘዝ በጣም የተስፋፋ መሆኑንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አይክድም። ወጣቶች ለተደረገላቸው ነገር ሁሉ አያመሰግኑም በማለት ብዙ ወላጆች ያማርራሉ። በአንጻሩ ደግሞ ብዙ ወጣቶች ወላጆቻቸው በሥራ ስለተወጠሩ፣ ዓላማቸውን ለማሳካት ስለሚሯሯጡ፣ ደስታ ስለሚያሳድዱ ወይም ስለ ራሳቸው ብቻ ስለሚያስቡ ለእነርሱ (ወይም ባጠቃላይ ለቤተሰባቸው) የሚገባቸውን እንክብካቤ እንደማያደርጉላቸው በምሬት ይናገራሉ። ጥፋተኛው የትኛው ወገን እንደሆነ ለመፍረድ ከመሞከር ይልቅ ይህ ሁኔታ ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት እንመልከት። በወጣቶችና በትላልቅ ሰዎች መካከል የሐሳብ አለመጣጣም በመፈጠሩ ምክንያት ወጣቶች የራሳቸውን የምግባር፣ እንዲያውም የብልግና ለማለት ይቻላል፣ ደንብ አውጥተዋል። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች እርግዝና፣ ፅንስ ማስወረድ እንዲሁም በሩካቤ ሥጋ የሚተላለፉ በሽታዎች እንደ ሰደድ እሳት ተዛምተዋል። በየቤቱ የተፈጥሮ ፍቅር በመጥፋቱ ምክንያት ጠብና አምባጓሮ በዝቷል። በምትኖርበት አካባቢ የተፈጸመ ሌላ ምሳሌ ለመጥቀስ ትችል ይሆናል። እነዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ፍቅር በንኖ እየጠፋ እንደሆነ የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች ናቸው!
13, 14. (ሀ) ብዙ ቤተሰቦች እየፈራረሱ እንዳሉ ስንመለከት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማተኮር ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) አምላክ የቤተሰብን ኑሮ አስመልክቶ ምን ጥበብ ያለበት ምክር ይሰጣል?
13 ይህም ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጎሣቸው ወይም ከዘራቸው ወይም ከብሔራቸው አባሎች ጋር የሚጋጩና የሚጣሉ ሰዎች ቁጥር እየበዛ የመጣበትን ምክንያት ሊያስረዳን ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ እነዚህን ችግሮች የምንጠቅሰው የጊዜያችንን መጥፎ ገጽታ ብቻ ለማጉላት እንዳልሆነ አስታውስ። የትኩረት አቅጣጫችን ያነጣጠረባቸው ሁለት ነጥቦች፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጳውሎስ የዘረዘራቸው መጥፎ ጠባዮች ከሚያደርሱት ጉዳት ሊጠብቀን ይችላልን? የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በሕይወታችን ውስጥ ሥራ ላይ ብናውል እንጠቀማለንን? የሚሉ ናቸው። ጳውሎስ የዘረዘራቸውን አራት ነጥቦች በተመለከተ ለሁለቱም ጥያቄዎች መልሱ አዎን፣ የሚል እንደሚሆን ግልጽ ነው።
14 አጠቃላይ የሆነ መግለጫ እንስጥ ቢባል ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይበልጥ አስደሳችና የተሳካ የቤተሰብ ኑሮ የሚያስገኝ ትምህርት አይገኝም ለማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል የቤተሰብ አባሎች የቤተሰባቸው ኑሮ ችግር እንዳያጋጥመው ብቻ ሳይሆን የተሳካ እንዲሆንም ጭምር ሊረዳቸው እንደሚችል ለማሳየት አንድ ምሳሌ ብንጠቅስ እንኳን ሊበቃ ይችላል። ለባሎች፣ ለሚስቶችና ለልጆች የተሰጡ በሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ ሌሎች በርካታ ጥሩ ጥሩ ምክሮች ቢኖሩም ቆላስይስ 3:18–21 ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። እነዚህ ምክሮች በጊዜያችንም ይሠራሉ። በእውነተኛ ክርስቲያኖች ቤት ውስጥም ቢሆን ችግሮችና ተፈታታኝ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙ መሆኑ አይካድም። ቢሆንም የተገኘው አጠቃላይ ውጤት መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰቦች የሚጠቅም ትምህርት እንደሚሰጥ ያረጋግጣል።
15, 16. አንዲት ተመራማሪ በዛምቢያ የሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮችን ካጠኑ በኋላ ምን ዓይነት ሁኔታ እንዳላቸው ተገነዘቡ?
15 የካናዳው የሌዝብሪጅ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ የሆኑ አንዲት ሴት ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል የዛምቢያን ማኅበራዊ ኑሮ አጥንተው ነበር። በጥናታቸው ማጠቃለያ ላይ እንዲህ አሉ፦ “የይሖዋ ምስክሮች ጠንካራ ትዳር በመመሥረት ረገድ ከሌሎቹ የሃይማኖት ክፍሎች ይበልጥ የተሳካ ውጤት አግኝተዋል። . . . አንዱ ሌላውን በሚይዝበት አያያዝ ረገድ ራሳቸው በሆነው በአምላክ እንደሚጠየቁ የሚያምኑት ባልና ሚስቶች በመካከላቸው ከዛቻና ከማስፈራራት የራቀ፣ የመረዳዳትና የመተጋገዝ አዲስ ዓይነት ዝምድና እንዲኖር ስላደረጉ የተሳካ ውጤት አግኝተዋል። . . . የይሖዋ ምስክር የሆነ ባል ለልጆቹና ለሚስቱ ደኅንነት በማሰብ ኃላፊነቱን በመወጣት ረገድ የጎለመሰ እንዲሆን ትምህርት ይሰጠዋል። . . . ባልና ሚስት ታማኝ ግለሰቦች እንዲሆኑ ይበረታታሉ። . . . እርስ በርስ ታማኝ ለመሆኑ ጉዳይ የሚሰጠው ይህ ከፍተኛ ቦታ በጋብቻቸው ውስጥ የጠበቀ ትስስር እንዲኖር አድርጓል።”
16 የጥናቱ ሪፖርት በብዙ የሕይወት ተሞክሮዎች ላይ የተመሠረተ ነበር። ለምሳሌ ያህል እኚህ አጥኚ “የይሖዋ ምስክሮች የሆኑ ወንዶች ከአካባቢው ልማድ የተለየ ነገር ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፤ ሚስቶቻቸውን በአትክልት ቦታ ይረዳሉ፤ ይህንንም የሚያደርጉት የአትክልት ቦታው በሚዘጋጅበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተከላና በቁፋሮ ጊዜ ጭምር ነው” ብለዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሰዎችን ሕይወት እንደሚለውጥና የተሻሉ ቤተሰቦችን እንደሚያስገኝ የሚያሳዩ ብዙ ተሞክሮዎች እንዳሉ ግልጽ ነው።
17, 18. በውርስ የተገኘ ሃይማኖትንና ከጋብቻ በፊት የሚፈጸምን የጾታ ግንኙነት አስመልክቶ በተደረገው ጥናት ምን የሚያስገርም ውጤት ተገኘ?
17 ቀደም ሲል የነበረው ርዕሰ ትምህርት ጆርናል ፎር ዘ ሳይንቲፊክ ስተዲ ኦቭ ሪሊጅን በተባለ ጽሑፍ ላይ የሠፈረ አንድ ጥናት ጠቅሶ ነበር። ይህ መጽሔት በ1991 “ሃይማኖታዊ ቅርስና ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት፦ ብሔራዊ ናሙና ከሆኑ ወጣቶች የተገኘ መረጃ” በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አውጥቶ ነበር። ከጋብቻ በፊት የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ምን ያህል እንደተስፋፋ ሳትገነዘብ አትቀርም። ብዙዎች ገና በትንሽነታቸው ለጾታ ስሜታቸው ይሸነፋሉ፤ እንዲሁም ወጣቶች ከተለያዩ ብዙ ሰዎች ጋር የጾታ ግንኙነት ይፈጽማሉ። ታዲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይህን በመሰለው ሁኔታ ላይ ለውጥ ያመጣ ይሆን?
18 ሦስት ተባባሪ ፕሮፌሰሮች በዚህ ጥያቄ ላይ ጥናት አድርገው ነበር። ፕሮፌሰሮቹ ‘ሃይማኖታዊ ወጎችን በሚያጠብቁ ክርስቲያን ቤተሰቦች ውስጥ ካደጉ ወጣቶችና ጎልማሶች መካከል ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት የፈጸሙት አነስተኛ እንደሆኑ የሚያመለክት መረጃ’ እናገኛለን ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። ታዲያ ከጥናታቸው ያገኙት መረጃ ምን ነበር? በአጠቃላይ ከ70 እስከ 82 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ከማግባታቸው በፊት የጾታ ግንኙነት ፈጽመው ተገኙ። አንዳንዶቹ “ሃይማኖትን የሚያከረው ባሕላቸው ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም የነበራቸውን ዕድል የቀነሰው ቢሆንም ‘በአሥራዎቹ ዓመታት ውስጥ ባሉት ወጣቶች’ ላይ ግን ይህን የመሰለ ውጤት አላስገኘም።” እነኚሁ አጥኚዎች እንዲያውም “ከዋነኞቹ የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች ጋር ሲወዳደሩ ይበልጥ ሃይማኖተኛ በሚመስሉ ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ ወጣቶች ከጋብቻ በፊት የጾታ ግንኙነት የፈጸሙበት አጋጣሚ ከፍ ብሎ ተገኝቷል” ብለዋል። (ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።)
19, 20. አምላክ የሚሰጠው ትምህርት የይሖዋ ምስክሮች የሆኑ ብዙ ወጣቶችን የረዳቸውና ከጉዳት የጠበቃቸው እንዴት ነው?
19 “ከሌሎች ወጣቶች ተቃራኒ ሆነው” የተገኙት የይሖዋ ምስክሮች ወጣቶች ግን ከእነዚህ ፈጽመው የተለዩ እንደሆኑ ፕሮፌሰሮቹ ተገንዝበዋል። እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ? “በጋራ በሚካፈሏቸው ተሞክሮዎች፣ ተስፋዎችና ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት . . . ከፍተኛ ማኅበራዊ ውኅደትና የዓላማ ጽናት ስለሚያገኙ ለሃይማኖታቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚገዙበት መጠን ከፍተኛ ሆኗል።” ቀጥለውም ፕሮፌሰሮቹ “ምስክሮቹ በወጣትነታቸውም ሆነ በጉርምስና ዕድሜያቸው የወንጌላዊነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።
20 ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የይሖዋ ምስክሮች የሥነ ምግባር ርኩሰት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ በመርዳት ጠቅሟቸዋል። ይህም አቋማቸው ፈውስ ከማይገኝላቸውና ቀሳፊ ከሆኑ በሩካቤ ሥጋ ከሚተላለፉ በሽታዎች ጠብቋቸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ሕይወት ከማጥፋት ጋር የሚተካከለውን ፅንስ የማስወረድ ወንጀል ከመፈጸምም አድኗቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ ወጣቶች ንጹሕ ሕሊና ይዘው ጋብቻ ለመመሥረት አስችሏቸዋል። ይህ ደግሞ ጋብቻቸው ጠንካራ መሠረት እንዲኖረው ያስችላል። እንዲህ ያለው ትምህርት አስጨናቂ የሆነውን ይህን ዘመን እንድንቋቋምና ይበልጥ ደስተኞችና ጤነኞች እንድንሆን ይረዳናል።
ገንቢ ትምህርት
21. ጳውሎስ ስለ ዘመናችን በትክክል የተነበያቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
21 አሁን ወደ 2 ጢሞቴዎስ 3:3, 4 መለስ እንበልና ጳውሎስ በዘመናችን እንደሚኖሩና ዘመናችን ለሁሉም ባይሆንም ለአብዛኞቹ ሰዎች አስጨናቂ እንዲሆንባቸው እንደሚያደርጉ የተናገራቸውን ሌሎቹን ነገሮች እንመልከት። “[ሰዎች] ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ [እንዲሁም] ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።” እንዴት ያለ ትክክለኛ መግለጫ ነው! ደስ የሚለው ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደነዚህ ካሉት ነገሮች እንድንጠበቅና እነርሱንም ለመቋቋም እንድንችል ማድረግ ብቻ ሳይሆን የተሳካ ውጤት እንድናገኝም የሚያስችለን መሆኑ ነው።
22, 23. ጳውሎስ ዝርዝሩን የደመደመው ምን ጥሩ ማሳሰቢያ በመስጠት ነው? ይህስ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
22 ሐዋርያው ጳውሎስ ዝርዝር መግለጫውን የደመደመው ገንቢ በሆነ መንፈስ ነው። ይህ ነው የማይባል ጥቅም ለማግኘት የሚያስችለንን አምላካዊ ትዕዛዝ ጭምር ሰጥቶናል። ጳውሎስ ‘የአምልኮት መልክ ስላላቸው፣ ኃይሉን ግን የካዱ’ ሰዎች ጠቀሰና “ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” አለ። የአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አባላት ሆነው ሳሉ ከጋብቻ በፊት ሩካቤ ሥጋ የፈጽሙት ወጣቶች ቁጥር ሃይማኖትን ያን ያህል አጥብቀው ከማይከተሉት ሌሎች ወጣቶች በልጦ እንደተገኘ አስታውስ። በእነዚህ የቤተ ክርስቲያን አባላት የሚፈጸመው የጾታ ብልግና ከሌሎች የማይብስ እንኳን ቢሆን የጾታ ብልግና መፈጸማቸው ብቻውን አምልኮታቸው ምንም ዓይነት ኃይል የሌለው መሆኑን አያረጋግጥምን? በውነቱ ሃይማኖታዊ ትምህርት ሰዎች በንግድ ጉዳዮች በሚያሳዩት ጠባይ፣ የበታቾቻቸውን በሚይዙበት መንገድ፣ ከዘመዶቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነትና በሥነ ምግባራቸው ላይ ለውጥ አስከትሏልን?
23 የጳውሎስ አነጋገር ከአምላክ ቃል የተማርነውን ሁሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባን ያመለክታል። የክርስትናን እውነተኛ ኃይል በግልጽ የሚያሳይ አምልኮ ሊኖረን ይገባል። ጳውሎስ ምንም ዓይነት ኃይል የሌለው አምልኮ ስላላቸው ሰዎች ሲናገር “ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” ብሎናል። ይህ ብዙ ጥቅሞች ሊያስገኝልን የሚችል ግልጽ ትዕዛዝ ነው።
24. በራእይ ምዕራፍ 18 ላይ ያለው ጥብቅ ማሳሰቢያ ከጳውሎስ ምክር ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
24 ግን ጥቅም የሚያስገኝልን በምን በምን መንገዶች ነው? የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ታላቂቱ ባቢሎን ስለምትባል ምሳሌያዊት አመንዝራ ሴት ሥዕላዊ መግለጫ ይሰጠናል። ታላቂቱ ባቢሎን ይሖዋ አምላክ መርምሮ የማይረባ ነው ብሎ ለጣለው ዓለም አቀፍ የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ምሳሌ እንደሆነች ማስረጃዎች ያመለክታሉ። እኛ ግን ከእርስዋ ጋር መቆጠር አይኖርብንም። ራእይ 18:4 “ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። ይህ ጳውሎስ “ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” ሲል ከሰጠው ትዕዛዝ ጋር አንድ አይደለምን? በዚህ አስጨናቂ በሆነው ዘመናችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከምናገኛቸው ጥቅሞች አንዱ ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዕዛዝ ለመፈጸም መቻላችን ነው።
25, 26. ከይሖዋ የሚመጣውን ትምህርት የሚቀበሉና በሥራ ላይ የሚያውሉ ሰዎች ወደፊት ምን ያገኛሉ?
25 አምላክ በቅርቡ በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ ይወስዳል። ሁሉንም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት፣ ከቀሩት የዚህ ክፉ ሥርዓት ክፍሎች ጋር ይደመስሳቸዋል። ራእይ 19:1, 2 እንደሚያመለክተው ይህ እርምጃ ታላቅ ደስታ ያመጣል። በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ትምህርት የተቀበሉና የተከተሉ ሁሉ በሕይወት ተርፈው የዚህ አስጨናቂ ዘመን እንቅፋቶች በሙሉ ከተወገዱ በኋላ በዚህ ትምህርት እየተመሩ ለሁልጊዜው በምድር ላይ እንዲኖሩ ይፈቀድላቸዋል።—ራእይ 21:3, 4
26 በእርግጥም ተመልሳ በምትመጣው በዚያች ምድራዊት ገነት ውስጥ መኖር ልንገምተው እንኳን ከምንችለው በላይ አስደሳች ይሆናል። አምላክ እንዲህ ያለ ሕይወት ማግኘት እንደምንችል ቃል ገብቶልናል። ያለምንም መጠራጠር እርሱን ልናምነው ይገባናል። ስለዚህ የአምላክን ጠቃሚ ትምህርት የምንቀበልበትና የምንከተልበት ብዙ ምክንያቶች አሉን። ይህን ትምህርት መቀበልና መከተል ያለብን መቼ ነው? አስጨናቂ በሆነው በአሁኑ ዘመንና እንደምትመጣ ቃል በገባልን ገነት ውስጥ የአምላክን ትምህርት እንከተል!—ሚክያስ 4:3, 4
ልናሰላስልባቸው የሚገቡ ነጥቦች
◻ የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋ ስለ ሀብት ከሰጠው ምክር ጥቅም ያገኙት እንዴት ነው?
◻ አንድ የኢየሱሳውያን መጽሔት የአምላክ አገልጋዮች ቃሉን ተግባራዊ በማድረጋቸው ምን ጥቅም እያገኙ እንዳሉ መሰከረ?
◻ በዛምቢያ የተደረገ አንድ ጥናት መለኮታዊውን ትምህርት ተግባራዊ የሚያደርጉ ቤተሰቦች ምን ጥቅም እንዳገኙ ገለጸ?
◻ መለኮታዊ ትምህርት ለወጣቶች ምን ዓይነት ጥበቃ ያደርግላቸዋል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መዘዙ ምንኛ የከፋ ነው!
ኤድስንና በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን አስመልክቶ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ የቀረበ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች የጾታ ግንኙነትንና አደንዛዥ ዕፆችን ሞክረው ማየት ስለሚወዱና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በመጣል ጊዜያዊ ደስታ ማግኘት ስለሚፈልጉ፤ እንዲሁም የማይሞቱ መስሎ ስለሚሰማቸውና በሥልጣን ላይ ስለሚያምፁ በኤድስ የመያዝ ሰፊ አደጋ ከፊታቸው ተደቅኗል።—ኒው ዮርክ ዴይሊ ኒውስ፣ እሁድ፣ መጋቢት 7, 1993
“በአውሮፓ፣ በአፍሪካና በደቡብ ምሥራቅ እስያ የተካሄደ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ጥናት የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣት ሴቶች በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ላለው የኤድስ በሽታ በሁለተኛነት ደረጃ ‘ፊት ለፊት’ እየተሰለፉ ነው ብሏል።—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዓርብ፣ ሐምሌ 30, 1993
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጉባኤም ሆነ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የይሖዋ ምስክሮችን ጠቅሟቸዋል