‘ይሖዋ ሆይ፣ ፈትነኝ’
ይሖዋ “ልብን ይመረምራል።” (ምሳሌ 17:3) ይህ ሁላችንንም በእጅጉ የሚያጽናና መሆን ይኖርበታል። ለምን? ምክንያቱም ውጫዊ ገጽታን ብቻ አይተው መፍረድ ከሚቀናቸው የሰው ልጆች በተለየ መልኩ በሰማይ የሚኖረው አባታችን “ልብን ያያል።”—1 ሳሙኤል 16:7
እኛም ራሳችን ብንሆን ውስጣዊ ግፊታችንን እና ዝንባሌያችንን በትክክል መመዘን እንደማንችል ግልጽ ነው። ለምን? ምክንያቱም ልባችን “ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ” ስለሆነ ነው። ታዲያ ልባችንን ‘ማን ሊያውቀው ይችላል?’ አምላክ “እኔ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] . . . ልብን እመረምራለሁ ኩላሊትንም እፈትናለሁ” በማለት ስለተናገረ እሱ ልባችንን ያውቀዋል። (ኤርምያስ 17:9, 10 የ1954 ትርጉም) አዎን፣ ይሖዋ ውስጣዊ ግፊታችንን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን የያዘውን ‘ልባችንን’ ያውቃል፤ እንዲሁም ‘ኩላሊታችንን’ ማለትም የውስጥ ሐሳባችንን እና ስሜታችንን በሚገባ ይረዳል።
ክርስቲያኖች ፈተና የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?
በመሆኑም በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት “ይሖዋ ሆይ፤ ፈትነኝ፤ መርምረኝም፤ ኩላሊቴንና ልቤን አጥራልኝ” ማለቱ አያስገርምም። (መዝሙር 26:2 NW) ይህ ሲባል ዳዊት በድርጊቱም ሆነ በንግግሩ እንከን የማይገኝበትና ይሖዋ ቢፈትነው ምንም የሚፈራበት ምክንያት የሌለው ሰው ነበር ማለት ነው? በጭራሽ! ዳዊት ልክ እንደ እኛ ፍጽምና የጎደለው ሰው ከመሆኑም ባሻገር የአምላክን መሥፈርቶች ሙሉ በመሉ ያሟላ አልነበረም። ዳዊት ከነበረበት ድክመት የተነሳ በርካታ ከባድ ስህተቶችን የፈጸመ ቢሆንም ‘በልበ ቅንነት’ ወይም በጽኑ አቋም ተመላልሷል። (1 ነገሥት 9:4) ይህን ያደረገው እንዴት ነው? የተሰጠውን ተግሣጽ በመቀበልና አካሄዱን በማስተካከል ነው። በዚህ መንገድ ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር እንዳለው አሳይቷል። ዳዊት ሙሉ በሙሉ ለአምላክ ያደረ ሰው ነበር።
ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ ፍጽምና የጎደለን ሰዎች መሆናችንን እና በንግግርም ሆነ በድርጊት ልንበድል እንደምንችል ያውቃል። ይሁንና አምላክ የወደፊት ሁኔታዎችን በማወቅ ችሎታው ተጠቅሞ የምንከተለውን የሕይወት ጎዳና አስቀድሞ አልወሰነልንም። ይሖዋ የፈጠረን የመምረጥ ነፃነት እንዲኖረን አድርጎ ሲሆን ምርጫችንንም ያከብርልናል። የመምረጥ ነፃነት አምላክ በደግነቱ የሰጠን ስጦታ ነው።
ሆኖም ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ውስጣዊ ግፊታችንን ጨምሮ ማንነታችንን በተወሰነ መጠን ሊፈትን ይችላል። ይህንንም የሚያደርገው የልባችንን ሁኔታ በግልጽ የምናሳይበት አጋጣሚ በመስጠት ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ውስጣዊ ዝንባሌያችን በግልጽ እንዲታይ ለማድረግ ሲል የተለያዩ ሁኔታዎች ወይም ፈተናዎች እንዲደርሱብን ሊፈቅድ ይችላል። ይህም ይሖዋን የቱን ያህል እንደምንወደውና ለእሱ ምን ያህል ታማኞች እንደሆንን ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጠናል። ይሖዋ በእኛ ላይ እንዲደርሱ የሚፈቅዳቸው እነዚህ ፈተናዎች በሁሉም ረገድ ‘ምንም የማይጎድለን ፍጹማንና ምሉአን’ መሆን አለመሆናችንን በማሳየት የእምነታችንን ጥራት ሊጠቁሙ ይችላሉ።—ያዕቆብ 1:2-4
በጥንት ዘመን የደረሰ የእምነት ፈተና
የአንድ ሰው እምነትና ውስጣዊ ግፊቶች እንዲታዩ የሚያደርጉ ፈተናዎች በይሖዋ አገልጋዮች ላይ መድረሳቸው እንግዳ ነገር አይደለም። የእምነት አባት የሆነው አብርሃም የገጠመውን ሁኔታ ተመልከት። እውነተኛው አምላክ “አብርሃምን ፈተነው።” (ዘፍጥረት 22:1) እነዚህ ቃላት በተነገሩበት ወቅት አብርሃም በአምላክ ላይ የነበረው እምነት ተፈትኖ ነበር። ከዓመታት በፊት ይሖዋ፣ አብርሃም ቤተሰቡን ይዞ የበለጸገች ከተማ ከሆነችው ዑር ወደማያውቀው ምድር እንዲሄድ ጠይቆት ነበር። (ዘፍጥረት 11:31፤ የሐዋርያት ሥራ 7:2-4) አብርሃም ዑር በነበረበት ወቅት የራሱ ቤት ሳይኖረው አይቀርም፤ ይሁንና ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በከነዓን ሲኖር ቋሚ መኖሪያ ቤት አልገዛም። (ዕብራውያን 11:9) አብርሃም በዘላንነት በኖረባቸው ጊዜያት ድርቅ፣ የጦር መሣርያ የታጠቁ ሽፍቶች እንዲሁም በአካባቢው የነበሩ አረማዊ ገዢዎች የእሱንም ሆነ የቤተሰቡን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው ነበር። በእነዚያ ጊዜያት ሁሉ አብርሃም እጅግ ጠንካራ እምነት እንዳለው ተረጋግጧል።
ከዚህ በኋላ ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት ለአብርሃም ከባድ ፈተና አቀረበለት:- “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን . . . የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው።” (ዘፍጥረት 22:2) ለአብርሃም ይስሐቅ እንደማንኛውም ዓይነት ልጅ አልነበረም። ሚስቱ ሣራ የወለደችለት ብቸኛ ልጅ ነበር። አምላክ ለአብርሃም በገባው ቃል መሠረት ‘ዘሩ’ የከነዓንን ምድር የሚወርሰውና ለብዙዎች በረከት መሆን የሚችለው በልጁ በይስሐቅ በኩል ብቻ ነበር። ደግሞም አብርሃም የጓጓው ተስፋውን እውን የሚያደርግለት ልጅ ለመውለድ ነበር፤ ይህንንም ልጅ ማለትም ይስሐቅን በተአምር አግኝቷል!—ዘፍጥረት 15:2-4, 7
በመሆኑም ለአብርሃም ይህን ትእዛዝ መረዳት ምን ያህል ከባድ እንደሚሆንበት ልትገምት ትችላለህ። ይሖዋ የሰው መሥዋዕት እንዲቀርብለት ይሻል? ይሖዋ፣ አብርሃም የኋላ ኋላ ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብለት የሚጠይቀው ከሆነ ልጅ በመውለድ የሚገኘውን ታላቅ ደስታ በስተ እርጅናው እንዲያጣጥም ለምን ፈቀደ?a
አብርሃም ለእነዚህ ጥያቄዎች ግልጽ መልስ ባያገኝም ወዲያውኑ ታዘዘ። መሥዋዕቱን እንዲያቀርብበት ወደተመረጠው ተራራ ለመድረስ ሦስት ቀን ፈጀበት። ከዚያም ተራራው ላይ መሠዊያ ከሠራ በኋላ በላዩ ላይ እንጨት ረበረበ። ፈተናው በጣም አስጨናቂ የሆነው በዚህ ጊዜ ነበር። አብርሃም ቢላውን አንስቶ ልጁን ሊያርደው ሲል፣ ይሖዋ በአንድ መልአክ አማካኝነት አስቆመውና “እግዚአብሔርን እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና” አለው። (ዘፍጥረት 22:3, 11, 12) አብርሃም ከይሖዋ ይህንን መስማቱ ምን ያህል እንደሚያስደስተው አስብ! ይሖዋ ቀደም ሲል ስለ አብርሃም እምነት የነበረው ግምት ትክክል ነበር። (ዘፍጥረት 15:5, 6) ከዚያም አብርሃም በይስሐቅ ምትክ አንድ በግ መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ይሖዋም ለአብርሃም ዘሩን አስመልክቶ የገባለትን ቃል ኪዳን እንደሚያጸናለት ዳግመኛ አረጋገጠለት። አብርሃም የይሖዋ ወዳጅ ተብሎ የተጠራው ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው።—ዘፍጥረት 22:13-18፤ ያዕቆብ 2:21-23
እኛም የእምነት ፈተና ይገጥመናል
በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮችም ከፈተና እንደማያመልጡ ሁላችንም እንገነዘባለን። ይሁንና የሚያጋጥሙን አብዛኞቹ ፈተናዎች ይሖዋ ከሚያዘን ነገሮች ጋር የተያያዙ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ በእኛ ላይ እንዲደርሱብን የሚፈቅዳቸው ናቸው።
ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” ሲል ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12) እንዲህ ዓይነቱ ስደት ከትምህርት ቤት ጓደኛ፣ ከወዳጅ፣ ከዘመድ አዝማድ፣ ከጎረቤት አሊያም ስለ እኛ የተሳሳተ ግንዛቤ ካላቸው የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሊመጣ ይችላል። ፈተናው ትችትና አካላዊ ጥቃት ብሎም አንድ ክርስቲያን ለመተዳደሪያ የሚሆን ገቢ እንዳያገኝ መሰናክል መሆንን የሚጨምር ሊሆን ይችላል። ከዚህም ባሻገር እውነተኛ ክርስቲያኖች በሁሉም የሰው ዘር ላይ የሚደርሱት ችግሮች ማለትም ሕመም፣ አሳዛኝ ሁኔታዎችና የፍትሕ መጓደል ያጋጥማቸዋል። እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች የአንድን ሰው እምነት ይፈትናሉ።
ሐዋርያው ጴጥሮስ አንድ ሰው እምነቱ መፈተኑ የሚያስገኝለትን ጥቅም ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በብዙ ዐይነት ፈተና ውስጥ [ናችሁ] . . . እነዚህ ነገሮች በእናንተ ላይ የደረሱት፣ በእሳት ተፈትኖ ቢጠራም፣ ጠፊ ከሆነው ወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረው እምነታችሁ እውነተኛ መሆኑ እንደተረጋገጠና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን እንዲያስገኝላችሁ ነው።” (1 ጴጥሮስ 1:6, 7) አዎን፣ ፈተናዎች የሚያስገኙት ውጤት ወርቅን በእሳት ከማንጠር ጋር ተነጻጽሯል። የማጥራቱ ሂደት ንጹሕ የሆነውን በመለየት ቆሻሻውን ያስወግዳል። ፈተናዎች ሲደርሱብን የእኛም እምነት ከዚህ ጋር በሚመሳሰል የማጥራት ሂደት ውስጥ ያልፋል።
ለምሳሌ ያህል፣ አንድ መጥፎ አጋጣሚ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ደርሶብን ከባድ ችግር ውስጥ እንወድቅ ይሆናል። በዚህ ወቅትም ቢሆን እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ከልክ በላይ አይጨነቁም። ይሖዋ “ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም” ሲል በሰጠው ዋስትና ይጽናናሉ። (ዕብራውያን 13:5) ይሖዋ አምላክ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚባርክላቸው በመተማመን ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ መስጠታቸውን ይቀጥላሉ። እምነታቸው በአስቸጋሪ ጊዜያት ደግፎ ያቆማቸዋል፤ እንዲሁም አላስፈላጊ በሆኑ ጭንቀቶች በመዋጥ ያሉበትን ሁኔታ ይበልጥ ከማወሳሰብ ይጠብቃቸዋል።
ፈተና የእምነታችንን ድክመት በግልጽ በማሳየት ማስተካከያ የማድረግን አስፈላጊነት ስለሚያስገነዝበን ጠቃሚ ነው። አንድ ሰው ራሱን እንዲህ እያለ መጠየቅ ይኖርበታል:- ‘እምነቴን ማጠንከር የምችለው እንዴት ነው? በአምላክ ቃል ላይ ጸሎት የታከለበት ጥናት በማድረግና በማሰላሰል ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ያስፈልገኝ ይሆን? ከእምነት አጋሮቼ ጋር አንድ ላይ እንድሰበሰብ ከተደረገልኝ ዝግጅት ሙሉ ጥቅም እያገኘሁ ነው? ስለሚያስጨንቁኝ ነገሮች ለይሖዋ አምላክ በጸሎት ከመንገር ይልቅ በራሴ እየታመንኩ ይሆን?’ ይሁንና እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን በመጠየቅ ራሳችንን መመርመራችን እምነታችንን ለማጠንከር የምንወስደው የመጀመሪያው እርምጃ ብቻ ነው።
አንድ ሰው እምነቱን ለማጠናከር ‘ተንኰል የሌለበትን የቃሉን ወተት በመመኘት’ የመንፈሳዊ ምግብ ፍላጎቱን ለማሻሻል መጣር ይኖርበታል። (1 ጴጥሮስ 2:2 የ1954 ትርጉም፤ ዕብራውያን 5:12-14) መዝሙራዊው “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስለዋል” በማለት የገለጸው ዓይነት ሰው ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—መዝሙር 1:2
ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። የአምላክ ቃል እየነገረን ያለውን ነገር በቁም ነገር ማሰብና የተሰጠንን ማሳሰቢያ በሥራ ላይ ማዋል ያስፈልገናል። (ያዕቆብ 1:22-25) ይህን ስናደርግ ለአምላክ ፈቃድ ያለን ፍቅር ይጨምራል፤ እንዲሁም ጸሎቶቻችን ይበልጥ ግልጽና በግል ሁኔታችን ላይ ያተኮሩ ይሆናሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአምላክ ላይ ያለን እምነት ይበልጥ ይጠነክራል።
የተፈተነ እምነት ያለው ዋጋ
እምነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የሚያስችለን በጣም ወሳኝ ባሕርይ መሆኑን መገንዘባችን እምነታችንን እንድናጠናክር ሊገፋፋን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል:- “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሁሉ እግዚአብሔር መኖሩንና ከልብ ለሚሹትም ዋጋ እንደሚሰጥ ማመን አለበት።” (ዕብራውያን 11:6) በመሆኑም “እምነቴ እንዲጠነክር ደግሞ አንተ እርዳኝ!” በማለት ኢየሱስን እንደለመነው ሰው ሊሰማን ይገባል።—ማርቆስ 9:24 NW
የእምነታችን መፈተን ሌሎችንም ሊጠቅም ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን የሚወደውን ሰው በሞት ሲያጣ አምላክ በሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ያለው እምነት ያጽናናዋል። ይህ ክርስቲያን ቢያዝንም ‘ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች አያዝንም።’ (1 ተሰሎንቄ 4:13, 14) አንድ ክርስቲያን ያለው እምነት ምን ያህል እንዳጽናናው የሚመለከቱ ሌሎች ሰዎች በእርግጥም የያዘው ነገር ውድ መሆኑን እንዲገነዘቡ ይረዳቸው ይሆናል። ይህ ደግሞ ‘ምናለ እኔም እንዲህ ዓይነት እምነት ቢኖረኝ’ የሚል ስሜት እንዲያድርባቸው ስለሚያደርግ የአምላክን ቃል እንዲማሩና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆኑ ሊገፋፋቸው ይችላል።
ይሖዋ የተፈተነ እምነት ትልቅ ዋጋ እንዳለው ያውቃል። በተጨማሪም በእምነት ላይ የሚደርሱ ፈተናዎች የእምነታችንን ጥንካሬ እንድናስተውል ይረዱናል። በእምነታችን ላይ ያለውን ድክመት እንድናውቅና ያሉብንን ጉድለቶች እንድናስተካክል ጥሩ አጋጣሚ ይሰጡናል። በመጨረሻም፣ የሚደርሱብንን ፈተናዎች በተሳካ ሁኔታ መወጣታችን ሌሎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ሊረዳቸው ይችላል። በመሆኑም ጠንካራ እምነት ማለትም ተደራራቢ ፈተናዎች ቢደርሱበትም እንኳ “ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ምስጋናን ክብርንና፣ ውዳሴን” የሚያስገኝ እምነት ለማዳበር የምንችለውን ሁሉ እናድርግ።—1 ጴጥሮስ 1:7
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የይስሐቅን “መሥዋዕት” ምሳሌያዊ ትርጉም ለመረዳት የሐምሌ 1, 1989 [እንግሊዝኛ] መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22ን ወይም 13-110 ገጽ 14ን ተመልከት።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
From the Illustrated Edition of the Holy Scriptures by Cassell, Petter, & Galpin
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብርሃም ያከናወናቸው የእምነት ሥራዎች የይሖዋ ወዳጅ እንዲሆን አስችለውታል
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፈተናዎች፣ እምነታችን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዳለው ያሳያሉ