የጴጥሮስ የመጀመሪያው ደብዳቤ
2 እንግዲህ ክፋትን ሁሉ፣ ማታለልን፣ ግብዝነትን፣ ቅናትንና ሐሜትን ሁሉ አስወግዱ።+ 2 ገና እንደተወለዱ ሕፃናት+ በአምላክ ቃል ውስጥ ለሚገኘው ያልተበረዘ* ወተት ጉጉት አዳብሩ፤ ይህም በእሱ አማካኝነት ወደ መዳን ማደግ እንድትችሉ ነው፤+ 3 ጌታ ደግ መሆኑን ቀምሳችኋልና።*
4 በሰዎች ወደተናቀው+ በአምላክ ግን ወደተመረጠውና በፊቱ ክቡር ወደሆነው ወደ እሱ ይኸውም ሕያው ወደሆነው ድንጋይ+ በመምጣት 5 እናንተ ራሳችሁ ቅዱሳን ካህናት ለመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን እየተገነባችሁ ነው፤+ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንፈሳዊ መሥዋዕት ማቅረብ ትችሉ ዘንድ ነው።+ 6 ምክንያቱም ቅዱስ መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በጽዮን የተመረጠ ድንጋይ ይኸውም ክቡር የሆነ የማዕዘን የመሠረት ድንጋይ አኖራለሁ፤ ደግሞም በእሱ የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አያፍርም።”+
7 በመሆኑም እናንተ አማኞች ስለሆናችሁ እሱ ለእናንተ ክቡር ነው፤ የማያምኑትን በተመለከተ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦ “ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣+ እሱ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ”፤+ 8 እንዲሁም “የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት ሆነ።”+ እነሱ የሚሰናከሉት ለቃሉ ስለማይታዘዙ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጠብቃቸው ነገር ይኸው ነው። 9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን+ የእሱን “ድንቅ ባሕርያት* በየቦታው እንድታውጁ+ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣+ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ”+ ናችሁ። 10 እናንተ በአንድ ወቅት የአምላክ ሕዝብ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ፤+ ቀደም ሲል ምሕረት አልተደረገላችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረት አግኝታችኋል።+
11 የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ የባዕድ አገር ሰዎችና ጊዜያዊ ነዋሪዎች+ እንደመሆናችሁ መጠን እናንተን ከሚዋጉት* ሥጋዊ ፍላጎቶች+ ምንጊዜም እንድትርቁ አሳስባችኋለሁ።+ 12 ክፉ አድራጊዎች እንደሆናችሁ አድርገው ሲከሷችሁ መልካም ሥራችሁን በዓይናቸው ማየት እንዲችሉ+ ብሎም አምላክ ለመመርመር በሚመጣበት ቀን እሱን እንዲያከብሩ በዓለም ባሉ ሰዎች መካከል መልካም ምግባር ይኑራችሁ።+
13 ለጌታ ብላችሁ ለሰብዓዊ ሥልጣን* ሁሉ ተገዙ፦+ የበላይ ስለሆነ ለንጉሥ ተገዙ፤+ 14 ደግሞም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣ መልካም የሚያደርጉትን ግን ለማመስገን በእሱ የተላኩ ስለሆኑ ለገዢዎች ተገዙ።+ 15 የአምላክ ፈቃድ፣ መልካም ነገር በማድረግ ከንቱ ንግግር የሚናገሩትን ምክንያታዊ ያልሆኑ ሰዎች አፍ ዝም እንድታሰኙ* ነውና።+ 16 እንደ ነፃ ሰዎች ኑሩ፤+ ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች+ ሆናችሁ ተጠቀሙበት እንጂ ለክፋት መሸፈኛ* አታድርጉት።+ 17 ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ፤+ ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር ይኑራችሁ፤+ አምላክን ፍሩ፤+ ንጉሥን አክብሩ።+
18 አገልጋዮች ጥሩና ምክንያታዊ ለሆኑት ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ለማይደሰቱ ጌቶቻቸውም እንኳ ተገቢ ፍርሃት በማሳየት ይገዙ።+ 19 አንድ ሰው በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረው ሲል መከራን* ችሎ ቢያሳልፍና ግፍ ቢደርስበት ይህ ደስ የሚያሰኝ ነውና።+ 20 ኃጢአት በመሥራታችሁ የሚደርስባችሁን ዱላ ብትቋቋሙ ምን ጥቅም አለው?+ መልካም ነገር በማድረጋችሁ መከራ ሲደርስባችሁ ችላችሁ ብታሳልፉ ግን ይህ አምላክ ደስ የሚሰኝበት ነገር ነው።+
21 ደግሞም የተጠራችሁት በዚህ ጎዳና እንድትሄዱ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስም እንኳ የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ+ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።+ 22 እሱ ምንም ኃጢአት አልሠራም፤+ በአንደበቱም የማታለያ ቃል አልተገኘም።+ 23 ሲሰድቡት+ መልሶ አልተሳደበም።+ መከራ ሲደርስበት+ አልዛተም፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ ሰጠ።+ 24 ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር እሱ ራሱ በገዛ አካሉ ኃጢአታችንን በእንጨት* ላይ+ ተሸከመ።+ ደግሞም “በእሱ ቁስል እናንተ ተፈወሳችሁ።”+ 25 እናንተ እንደባዘኑ በጎች ነበራችሁና፤+ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ* እረኛና+ ጠባቂ* ተመልሳችኋል።