‘ደፋሮችና ጠንካሮች ሁኑ!’
“አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33
1. እስራኤላውያን በከነዓን ምድር ይጠብቋቸው ከነበሩት ጠላቶች አንጻር ምን ማበረታቻ ተሰጣቸው?
እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረው ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርበው ሳለ ሙሴ “ጽኑ፣ አይዞአችሁ፣ አትፍሩ፣ ከፊታቸውም አትደንግጡ፤ አምላክህ እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል” በማለት ተናገራቸው። በኋላም ሙሴ እስራኤላውያንን እየመራ ወደ ከነዓን ምድር የሚያስገባውን ኢያሱን ለብቻው ጠርቶ ደፋር መሆን እንዳለበት በድጋሚ መከረው። (ዘዳግም 31:6, 7) በኋላም ይሖዋ ራሱ ኢያሱን “ጽና፣ አይዞህ። . . . ጽና፣ እጅግ በርታ” በማለት አበረታታው። (ኢያሱ 1:6, 7, 9) እነዚህ ቃላት ወቅታዊ ነበሩ። እስራኤላውያኑ ከዮርዳኖስ ማዶ የሚጠብቋቸውን ኃያላን ጠላቶች ለመግጠም ድፍረት ያስፈልጋቸው ነበር።
2. ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ እንገኛለን? ምን መሆንስ ያስፈልገናል?
2 ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች በቅርቡ ተስፋ ወደተገባው አዲስ ዓለም ስለሚገቡ እነሱም እንደ ኢያሱ ደፋሮች መሆን ያስፈልጋቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 7:14) ይሁንና የእኛ ሁኔታ ከኢያሱ የተለየ ነው። ኢያሱ የተዋጋው በሰይፍና በጦር ነበር። እኛ የምንዋጋው መንፈሳዊ ውጊያ ስለሆነ በሥጋዊ የጦር መሣሪያዎች ፈጽሞ አንጠቀምም። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ ኤፌሶን 6:11-17) ከዚህም በላይ ኢያሱ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገባ በኋላም ብዙ አስፈሪ ጦርነቶችን ማድረግ ነበረበት። እኛ ግን አስፈሪ ውጊያ የሚገጥመን ወደ አዲሱ ዓለም ከመግባታችን በፊት ማለትም አሁን ነው። ደፋር እንድንሆን የሚጠይቁብንን አንዳንድ ሁኔታዎች እስቲ እንመልከት።
መጋደል ያለብን ለምንድን ነው?
3. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቀንደኛው ጠላታችን ምን ይገልጻል?
3 ሐዋርያው ዮሐንስ “ከእግዚአብሔር እንደሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:19) እነዚህ ቃላት ክርስቲያኖች እምነታቸውን ጠብቀው ለመኖር መጋደል ያለባቸው ለምን እንደሆነ ያሳያሉ። አንድ ክርስቲያን ታማኝነቱን መጠበቁ በመጠኑም ቢሆን ለሰይጣን ሽንፈት ነው። በመሆኑም ሰይጣን ልክ “እንደሚያገሣ አንበሳ” ታማኝ ክርስቲያኖችን ለማስፈራራትና ከዚያም አልፎ ለመዋጥ ይጥራል። (1 ጴጥሮስ 5:8) በእርግጥም በቅቡዓን ክርስቲያኖችና በባልንጀሮቻቸው ላይ ጦርነት ከፍቷል። (ራእይ 12:17) በዚህ ውጊያ አውቀውም ይሁን ሳያውቁት የእርሱን ፈቃድ በሚያሟሉ ሰዎች ይጠቀማል። ሰይጣንንና ወኪሎቹን በሙሉ በጽናት ለመቋቋም ድፍረት ይጠይቃል።
4. ኢየሱስ ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል? ሆኖም እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ባሕርይ አሳይተዋል?
4 ኢየሱስ፣ ሰይጣንና ወኪሎቹ ምሥራቹን በብርቱ እንደሚቃወሙ ስለሚያውቅ ተከታዮቹን “በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፣ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” በማለት አስጠንቅቋል። (ማቴዎስ 24:9) እነዚህ ቃላት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ተፈጽመዋል፤ ዛሬም ይፈጸማሉ። እንዲያውም በአንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰው ስደት በታሪክ ዘመናት ከደረሰው ሁሉ የከፋ ነው። ያም ሆኖ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ግፍ በድፍረት ተቋቁመዋል። ‘ሰውን መፍራት ወጥመድ እንደሚያመጣ’ ስለሚያውቁ በወጥመድ መያዝ አይፈልጉም።—ምሳሌ 29:25
5, 6. (ሀ) ደፋር መሆንን የሚጠይቁብን አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ታማኝ ክርስቲያኖች ድፍረት የሚጠይቅ ፈተና ሲደርስባቸው ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው?
5 ከስደት በተጨማሪ ድፍረት እንድናሳይ የሚጠይቁብን ሌሎች ችግሮችም አሉብን። ለማያውቁት ሰው ምሥራቹን መናገር ለአንዳንድ አስፋፊዎች ትግል የሚጠይቅ ነው። አንዳንድ ተማሪዎች ለአገር ወይም ለባንዲራ ታማኝ መሆናቸውን የሚገልጹ ቃላት በሕዝብ ፊት እንዲደግሙ በሚጠየቁበት ጊዜ ድፍረታቸው ተፈትኗል። እንዲህ ያለው የታማኝነት መግለጫ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ክርስቲያን የሆኑ ልጆች በድፍረት አምላክን የሚያስከብር እርምጃ ወስደዋል። እንዲህ ያለው መልካም ምሳሌነታቸው የሚያኮራ ነው።
6 በተጨማሪም ተቃዋሚዎች መገናኛ ብዙኃንን ተጠቅመው ስለ አምላክ አገልጋዮች የሐሰት ወሬ ሲያናፍሱ ወይም ‘ሕግን ተንተርሰው’ የእውነተኛውን አምልኮ እንቅስቃሴ ለመገደብ ሲሞክሩ ድፍረት ያስፈልገናል። (መዝሙር 94:20 NW ) ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክሮች አሳቾች ወይም ሐሰተኞች ናቸው የሚል ዜና በጋዜጣ፣ በራዲዮ ወይም በቴሌቪዥን ሲሰራጭ ብንሰማ ምን ይሰማናል? መረበሽ ይገባናል? በፍጹም። እንዲህ ያሉ ነገሮች እንደሚከሰቱ እንጠብቃለን። (መዝሙር 109:2) መጽሐፍ ቅዱስ “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል” ብሎ ስለሚናገር አንዳንድ ሰዎች እንደዚህ ያሉትን የተናፈሱ የሐሰትና የተዛቡ ወሬዎች ቢያምኑም መገረም የለብንም። (ምሳሌ 14:15) ታማኝ ክርስቲያኖችም በወንድሞቻቸው ላይ የሚነዙ ወሬዎችን የማይቀበሉ ከመሆናቸውም በላይ በሐሰት ዜናዎች የተነሳ ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አይቀሩም፣ በመስክ አገልግሎት ያላቸውን ተሳትፎ አይቀንሱም ወይም እምነታቸውን አያላሉም። በተቃራኒው “በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን . . . በክብርና በውርደት፣ በክፉ ወሬና በመልካም ወሬ ራሳችንን እናማጥናለን አሳቾች ስንባል እውነተኞች ነን።”—2 ቆሮንቶስ 6:4, 8
7. የውስጥ ስሜታችንን ለማወቅ ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ እንችላለን?
7 ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት “እግዚአብሔር የኃይል . . . መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና። እንግዲህ በጌታችን ምስክርነት . . . አትፈር” ብሎታል። (2 ጢሞቴዎስ 1:7, 8፤ ማርቆስ 8:38) እነዚህን ቃላት በምናነብበት ጊዜ ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ እንችላለን:- ‘ስለ እምነቴ አፍራለሁ? ወይስ ደፋር ነኝ? በሥራ ቦታዬ ወይም ትምህርት ቤት ለማገኛቸው ሰዎች የይሖዋ ምሥክር መሆኔን እነግራቸዋለሁ? ወይስ ለመደበቅ እሞክራለሁ? ከሌሎች የተለየሁ ሆኜ መታየት ያሳፍረኛል? ወይስ ከይሖዋ ጋር ባለኝ ዝምድና ተለይቼ ብታወቅ ያኮራኛል?’ ምሥራቹን መስበክን ወይም በሰዎች ዘንድ የማይወደድ እምነት መያዝን በተመለከተ አፍራሽ ስሜት ያለው ማንም ቢኖር ይሖዋ ለኢያሱ “ጽና፣ እጅግ በርታ” በማለት የሰጠውን ምክር ያስታውስ። ትልቁን ቦታ የሚይዘው የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም የትምህርት ቤት ጓደኞቻችን የሚሰጡት አስተያየት ሳይሆን የይሖዋና የኢየሱስ ክርስቶስ አመለካከት መሆኑን ፈጽሞ አንዘንጋ።—ገላትያ 1:10
ደፋሮች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
8, 9. (ሀ) በአንድ ወቅት የጥንት ክርስቲያኖች ድፍረት የተፈተነው እንዴት ነበር? (ለ) ጴጥሮስና ዮሐንስ ሲዛትባቸው ምን መልስ ሰጡ? እነሱና ወንድሞቻቸውስ ምን አጋጠማቸው?
8 በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ታማኝነታችንን ጠብቀን ለመኖር ይበልጥ ደፋሮች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? የጥንት ክርስቲያኖች ድፍረት ያዳበሩት እንዴት ነበር? በኢየሩሳሌም የነበሩት ሊቀ ካህናትና ሽማግሌዎች ጴጥሮስና ዮሐንስ በኢየሱስ ስም መስበካቸውን እንዲያቆሙ በነገሯቸው ጊዜ የሆነውን ነገር ተመልከት። ደቀ መዛሙርቱ መስበካቸውን እንደማያቆሙ ሲናገሩ ዛቱባቸውና ለቀቋቸው። ከዚህ በኋላ ወደ ወንድሞች ሄደው ሁሉም በአንድነት “ጌታ [ይሖዋ] ሆይ ወደዛቻቸው ተመልከት . . . ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት [“በፍጹም ድፍረት፣” አ.መ.ት ] ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው” በማለት ጸለዩ። (ሥራ 4:13-29) በምላሹም ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አጠነከራቸውና ከጊዜ በኋላ የአይሁድ መሪዎች እንደመሰከሩት ‘ኢየሩሳሌምን በትምህርታቸው ሞሏት።’—ሥራ 5:28
9 በዚያ ወቅት የሆነውን ነገር አንድ በአንድ እንመርምር። ደቀ መዛሙርቱ በአይሁድ መሪዎች ሲዛትባቸው እጃቸውን መስጠት አልፈለጉም። ከዚህ ይልቅ መስበካቸውን ለመቀጠል ድፍረት እንዲሰጣቸው ጸለዩ። ከዚያም ከጸሎታቸው ጋር የሚስማማ እርምጃ ወሰዱ፤ ይሖዋም በመንፈስ ቅዱሱ አጠነከራቸው። ጳውሎስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከሌላ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የጻፈው ነገር ስደት በገጠማቸው እውነተኛ ክርስቲያኖችም ላይ እንደሚሠራ የእነርሱ ሁኔታ ያሳያል። ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” በማለት ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 4:13 አ.መ.ት
10. በተፈጥሯቸው ዓይን አፋር የሆኑ የኤርምያስ ተሞክሮ የሚረዳቸው እንዴት ነው?
10 አንድ ሰው በተፈጥሮው ዓይን አፋር ቢሆንስ? ተቃውሞ ቢያጋጥመው ይሖዋን በድፍረት ማገልገል ይችላል? እንዴታ! ይሖዋ ኤርምያስን ነቢይ አድርጎ ሲሾመው ምን እንደተሰማው አስታውስ። ለጋው ወጣት “ብላቴና ነኝ” ብሎ መለሰ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ብቃት እንደሌለው ሆኖ ተሰምቶት ነበር። ያም ሆኖ ይሖዋ በሚከተሉት ቃላት አበረታታው:- “ወደምሰድድህ ሁሉ ትሄዳለህና፣ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና:- ብላቴና ነኝ አትበል። እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና ከፊታቸው አትፍራ።” (ኤርምያስ 1:6-10) ኤርምያስ በይሖዋ ላይ ትምክህት ስለነበረው ከይሖዋ ባገኘው ብርታት የነበረውን የፍርሃት ስሜት አስወግዶ በእስራኤል ምድር የሚደነቅ ድፍረት ያሳየ ምሥክር ለመሆን በቅቷል።
11. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች እንደ ኤርምያስ ደፋሮች እንዲሆኑ የሚረዳቸው ምንድን ነው?
11 በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከኤርምያስ ጋር የሚመሳሰል ተልእኮ አላቸው። በአገልግሎት ክልላቸው ግዴለሽ የሆኑ ሰዎች፣ ፌዝና ስደት ቢያጋጥማቸውም “እጅግ ብዙ ሰዎች” በሚያደርጉላቸው ድጋፍ እየታገዙ የይሖዋን ዓላማዎች ማስታወቃቸውን ገፍተውበታል። (ራእይ 7:9፤ ዮሐንስ 10:16) ይሖዋ ለኤርምያስ “አትፍራ” በማለት በተናገራቸው ቃላት ይበረታታሉ። በአምላክ የተላኩ ተወካዮች እንደሆኑና የእርሱን መልእክት እንደሚሰብኩ ፈጽሞ አይዘነጉም።—2 ቆሮንቶስ 2:17
ልንመስላቸው የሚገቡን የድፍረት ምሳሌዎች
12. ኢየሱስ ደፋር በመሆን ረገድ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል? ተከታዮቹን ያበረታታውስ እንዴት ነው?
12 እንደ ኤርምያስ ደፋሮች በሆኑ ሌሎች ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰል ድፍረትን ለማዳበር በምናደርገው ጥረት ሊረዳን ይችላል። (መዝሙር 77:12) ለምሳሌ ያህል፣ የኢየሱስን አገልግሎት ስንመረምር በሰይጣን ሲፈተን እንዲሁም በአይሁድ መሪዎች የተጠናከረ ተቃውሞ ሲያጋጥመው ባሳየው ድፍረት መገረማችን አይቀርም። (ሉቃስ 4:1–13፤ 20:19-47) ኢየሱስ ይሖዋ በሰጠው ብርታት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 16:33፤ 17:16) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የእርሱን ምሳሌ ከተከተሉ እነሱም አሸናፊዎች ይሆናሉ። (1 ዮሐንስ 2:6፤ ራእይ 2:7, 11, 17, 26) ይሁን እንጂ ‘ደፋሮች መሆን’ ያስፈልጋቸው ነበር።
13. ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ምን ማበረታቻ ሰጣቸው?
13 ኢየሱስ ከሞተ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጳውሎስና ሲላስ በፊልጵስዩስ በወህኒ ተጣሉ። ቆየት ብሎም ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ጉባኤ ሲያበረታታ “በአንድ ልብ ስለ ወንጌል ሃይማኖት አብራችሁ እየተጋደላችሁ፣ በአንድ መንፈስ እንድትቆሙ ስለ ኑሮአችሁ እሰማ ዘንድ፣ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ። በአንድም ነገር እንኳ በተቃዋሚዎች አትደንግጡ” ብሏቸዋል። ጳውሎስ ይህን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሲያጠናክራቸው “ይህም [የክርስቲያኖች መሰደድ] [ለአሳዳጆቹ] የጥፋት፣ ለእናንተ ግን የመዳን ምልክት ነው፣ ይህም ከእግዚአብሔር ነው፤ ይህ [“መብት፣” NW ] ስለ ክርስቶስ ተሰጥቶአችኋልና፤ ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም” ብሏል።—ፊልጵስዩስ 1:27-29
14. ጳውሎስ በሮም ያሳየው ድፍረት ምን ውጤት አስገኝቷል?
14 ጳውሎስ ፊልጵስዩስ ለሚገኘው ጉባኤ ደብዳቤውን የጻፈው ሮም በሚገኘው እስር ቤት በድጋሚ ታስሮ በነበረበት ወቅት ነበር። እስረኛ ቢሆንም ለሌሎች በድፍረት መስበኩን ቀጥሎ ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? “እስራቴ ስለ ክርስቶስ እንደሆነ፣ በቤተ መንግሥት ዘበኞችና በሌሎችም ሁሉ ዘንድ ታውቆአል። በእኔ መታሰር ምክንያት በጌታ ካሉት ወንድሞች ብዙዎቹ የእግዚአብሔርን ቃል ያለ ፍርሃት፣ በድፍረት ለመናገር ብርታት አግኝተዋል” በማለት ጽፏል።—ፊልጵስዩስ 1:13, 14 አ.መ.ት
15. ደፋሮች ለመሆን ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠናክሩልን መልካም የእምነት ምሳሌዎችን የት ልናገኝ እንችላለን?
15 የጳውሎስ ምሳሌነት እኛንም ያበረታታናል። በዘመናችንም በአምባገነን መሪዎች ወይም በቀሳውስት በሚተዳደሩ አገሮች የደረሰባቸውን ስደት በጽናት የተቋቋሙ ክርስቲያኖች ያሳዩት ምሳሌነት ያበረታታናል። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል የአብዛኞቹ ታሪክ በመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፎች ላይ ተዘግቧል። እነዚህን ታሪኮች ስታነብ ባለ ታሪኮቹ እንደኛው ተራ ሰዎች መሆናቸውን አስታውስ። ይሁን እንጂ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟቸው ከይሖዋ ባገኙት ከወትሮው የበለጠ ኃይል ሊጸኑ ችለዋል። እኛም ተመሳሳይ ችግር ቢደርስብን ይሖዋ ይህንኑ እንደሚያደርግልን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።
የድፍረት አቋማችን ይሖዋን ያስደስተዋል እንዲሁም ያስከብረዋል
16, 17. በዛሬው ጊዜ የድፍረት አቋም ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
16 አንድ ክርስቲያን ለእውነትና ለጽድቅ ጽኑ አቋም ከያዘ ደፋር ነው። ይህ ክርስቲያን ይህን ጽኑ አቋም የያዘው በውስጡ ፍርሃት እየተሰማው በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የበለጠ ደፋር ነው። በእርግጥም ማንኛውም ክርስቲያን ከልቡ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም የሚፈልግ ከሆነ፣ ታማኝ ሆኖ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ካደረገ፣ ያለማቋረጥ በአምላክ ላይ ከታመነና ይሖዋ ቀደም ሲል እንደሱ ያሉ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ግለሰቦችን እንዳጠነከራቸው ሁልጊዜ የሚያስታውስ ከሆነ ደፋር መሆን ይችላል። ከዚህም በላይ የድፍረት አቋማችን ይሖዋን እንደሚያስደስተውና እንደሚያስከብረው ከተገነዘብን ይበልጡን ላለመላላት ቁርጥ ውሳኔ እናደርጋለን። ለይሖዋ የጠለቀ ፍቅር ስላለን ፌዝም ሆነ ከዚህ የከፋ ነገር ቢደርስብን ጸንተን ለመቆም የቆረጥን እንሆናለን።—1 ዮሐንስ 2:5፤ 4:18
17 በእምነታችን ምክንያት መከራ ሲደርስብን ይህ የሆነው አንድ ዓይነት ኃጢአት በመሥራታችን እንደሆነ አድርገን ፈጽሞ ማሰብ አይኖርብንም። (1 ጴጥሮስ 3:17) መከራ የሚደርስብን የይሖዋን ሉዓላዊነት ስለምንደግፍ፣ መልካም ስለምናደርግና የዓለም ክፍል ባለመሆናችን ምክንያት ነው። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጴጥሮስ “መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሡ፣ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል” ብሏል። በተጨማሪም ጴጥሮስ “ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፣ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ” ብሏል። (1 ጴጥሮስ 2:20፤ 4:19) አዎን፣ እምነታችን አፍቃሪውን አምላካችንን ይሖዋን ያስደስተዋል፣ ክብርም ያመጣለታል። ይህ ደግሞ ደፋር ለመሆን የሚያስችል እንዴት ያለ ጠንካራ ምክንያት ነው!
በባለ ሥልጣናት ፊት ቀርቦ መናገር
18, 19. በአንድ ዳኛ ፊት ቀርበን ድፍረት የተሞላበት አቋም ስንይዝ እግረ መንገዳችንን ምን መልእክት እያስተላለፍን ነው?
18 ኢየሱስ እንደሚሰደዱ ለተከታዮቹ ሲነግራቸው “ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፣ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤ ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፣ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ” በማለት ጨምሮም ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 10:17, 18) በሐሰት ተወንጅሎ በዳኛ ወይም በአንድ ገዢ ፊት መቅረብ ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱን አጋጣሚ ለእነዚህ ግለሰቦች በድፍረት ለመመስከር ብንጠቀምበት የደረሰብንን አስቸጋሪ ሁኔታ አንድ ጠቃሚ ዓላማ ለማከናወን ወደሚያስችል አጋጣሚ ልንቀይረው እንችላለን። እግረ መንገዳችንንም ለሚዳኙን ግለሰቦች ይሖዋ በ2ኛው መዝሙር ላይ የተናገራቸውን “አሁንም እናንት ነገሥታት፣ ልብ አድርጉ፤ እናንተ የምድር ፈራጆችም፣ ተገሠጹ። ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ” የሚሉትን ቃላት እናስተላልፋለን። (መዝሙር 2:10, 11) ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በሐሰት ተወንጅለው ወደ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ዳኞች የአምልኮ ነፃነትን ስለሚያስከብሩ ለዚህ አመስጋኞች ነን። አንዳንድ ዳኞች ግን ለተቃዋሚዎች ተጽዕኖ ይንበረከካሉ። እንደዚህ ላሉት ዳኞች ቅዱስ ጽሑፉ “ተገሠጹ” ይላቸዋል።
19 ዳኞች ከፍተኛው ሕግ የይሖዋ አምላክ ሕግ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ዳኞችን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች በይሖዋ አምላክና በኢየሱስ ክርስቶስ ተጠያቂዎች መሆናቸውን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ሮሜ 14:10) እኛ ግን በአንድ ሰብዓዊ ዳኛ ፊት ፍትሕ አገኘንም አላገኘን ይሖዋ እንደሚደግፈን ስለምናውቅ ደፋሮች የምንሆንበት በቂ ምክንያት አለን። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በእርሱ የታመኑ ሁሉ ደስተኞች ናቸው’ ይላል።—መዝሙር 2:12
20. ስደት ሲደርስብንም ሆነ ስማችንን የሚያጠፉ ዘገባዎች ሲሰራጩ ደስተኞች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?
20 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ እንዲህ ብሏል: “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሐሤትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” (ማቴዎስ 5:11, 12) ስደት በራሱ የሚያስደስት ነገር ባይሆንም በመገናኛ ብዙኃን የሚሠራጩትን ስማችንን የሚያጠፉ ዘገባዎችን ጨምሮ የሚደርሱብንን ስደቶች በጽናት ስንቋቋም ይህ ለደስታ ምክንያት የሚሆን ነገር ነው። ጸንተን ስንቆም ይሖዋን እናስደስታለን፤ ይህም ለሽልማት ያበቃናል። ድፍረት የተሞላበት አቋም መያዛችን እውነተኛ እምነት እንዳለን የሚያሳይ በመሆኑ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘን ያረጋግጥልናል። በእርግጥም እንዲህ ያለው አቋም በይሖዋ ላይ ፍጹም ትምክህት እንዳለን ያሳያል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ እንደምንመለከተውም እንዲህ ያለው እምነት ለአንድ ክርስቲያን ወሳኝ ነው።
ምን ትምህርት አግኝተናል?
• በዛሬው ጊዜ ደፋር መሆንን የሚጠይቁ ምን ሁኔታዎች አሉ?
• ደፋር መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
• አንዳንድ የድፍረት ምሳሌዎች እነማን ናቸው?
• በድፍረት እርምጃ መውሰድ የምንፈልገው ለምንድን ነው?
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጀርመን የምትኖረው ሲሞን አርኖልድ (አሁን ሊብስተር ትባላለች)፣ በማላዊ የሚኖረው ዊዳስ ማዶና እንዲሁም በዩክሬይን የሚኖሩት ሊዲያ እና ኦሌክሲ ኩርዳስ በድፍረት ክፉውን አሸንፈዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በወንጌል አናፍርም
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በእስር ቤት ያሳየው ድፍረት ምሥራቹን ለማስፋፋት አገልግሏል
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋማችንን ለአንድ ዳኛ ስንገልጽ አስፈላጊ መልእክት እያስተላለፍን ነው