ቲቶ “ስለ እናንተ አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ”
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ አልፎ አልፎ ችግሮች ይከሰቱ ነበር። እነዚህ ችግሮች መፍትሄ ማግኘት ነበረባቸው። ይህ ደግሞ ድፍረትና ታዛዥነት ይጠይቅ ነበር። ቲቶ ይህ ዓይነቱን ፈታኝ ሁኔታ ከአንድ ጊዜ በላይ ስኬታማ በሆነ መንገድ የተጋፈጠ ሰው ነው። ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር አብሮ የሠራ እንደመሆኑ መጠን ሌሎች የሚሠሯቸውን ነገሮች በይሖዋ መንገድ እንዲያከናውኑ ለመርዳት ልባዊ ጥረት አድርጓል። ከዚህም የተነሳ ጳውሎስ በቆሮንቶስ ላሉ ክርስቲያኖች ቲቶ ‘ስለ እነሱ አብሮት የሚሠራ ባልንጀራው’ መሆኑን ገልጾላቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 8:23
ቲቶ ማን ነበር? ችግሮችን በመፍታት ረገድ ምን ድርሻ አበርክቷል? እንዲሁም ስለእሱ ባሕርይ በመመርመር ምን ጥቅም ማግኘት እንችላለን?
አከራካሪው የግርዘት ጉዳይ
ቲቶ ያልተገረዘ ግሪካዊ ነበር። (ገላትያ 2:3)a ጳውሎስ “በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ልጄ” ብሎ ስለጠራው ቲቶ ከሐዋርያው መንፈሳዊ ልጆች መካከል አንዱ ሳይሆን አይቀርም። (ቲቶ 1:4፤ ከ1 ጢሞቴዎስ 1:2 ጋር አወዳድር።) በ49 እዘአ አካባቢ ግርዘትን በተመለከተ ስለተነሳው ጥያቄ ለመወያየት ጳውሎስ፣ በርናባስና ሌሎችም ከሶርያ አንጾኪያ ወደ ኢየሩሳሌም በተጓዙ ጊዜ ቲቶ አብሯቸው ነበር።—ሥራ 15:1, 2፤ ገላትያ 2:1
ኢየሩሳሌም ውስጥ ያልተገረዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና በመለወጣቸው ጉዳይ ላይ ውይይት እየተካሄደ ስለነበር ቲቶን ይዘው የሄዱት አይሁዳውያንም ሆኑ አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ተገረዙም አልተገረዙ የአምላክን ሞገስ እንደሚያገኙ ለማሳየት ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል። ክርስትናን ከመቀበላቸው በፊት ፈሪሳዊ የነበሩ አንዳንድ የኢየሩሳሌም ጉባኤ አባላት፣ ወደ ክርስትና የተቀየሩ አሕዛብ የመገረዝና ሕጉን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው ተከራክረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። ቲቶን ጨምሮ ሌሎች አሕዛብ እንዲገረዙ ማስገደድ፣ መዳን የተመካው ሕጉን በሥራ በማዋል ሳይሆን ይገባናል በማንለው በይሖዋ ደግነትና በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን መሆኑን መካድ ማለት ይሆን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አሕዛብ ወይም የሌሎች ብሔራት ሕዝቦች የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንደተቀበሉ የሚያሳየውን ማስረጃ ገሸሽ ማድረግ ይሆን ነበር።—ሥራ 15:5-12
ወደ ቆሮንቶስ ተላከ
ስለ ግርዘት የተነሳው አከራካሪ ጉዳይ እልባት ካገኘ በኋላ ጳውሎስና በርናባስ ለአሕዛብ እንዲሰብኩ ሙሉ ስልጣን ተሰጥቷቸው ነበር። ከዚህ ጋር በተያያዘ ድሆች ለሆኑት ትኩረት ለመስጠትም ጥረት አድርገዋል። (ገላትያ 2:9, 10) በእርግጥም ቲቶ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት መጻሕፍት ውስጥ ከስድስት ዓመታት ገደማ በኋላ በድጋሚ ሲጠቀስ የጳውሎስ መልእክተኛ በመሆን ቅዱሳን ለሆኑት የሚሰጠውን እርዳታ ለማደራጀት በቆሮንቶስ ይገኝ ነበር። ይሁን እንጂ ቲቶ ይህን ተልዕኮ እየተወጣ ሳለ ሌላ አሳሳቢ ሁኔታ ገጠመው።
ጳውሎስ በመጀመሪያ ደረጃ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ‘ከሴሰኞች ጋር እንዳይተባበሩ’ መሆኑን መልእክቱ ያሳያል። ንስሐ ያልገባን ዘማዊ ከመካከላቸው እንዲያስወጡ መንገር የግድ አስፈልጎታል። አዎን፣ ጳውሎስ ከበድ ያለ መልእክት ያዘለ ደብዳቤ ጽፎላቸዋል፤ ይህንም ያደረገው ‘በብዙ እንባ’ ነበር። (1 ቆሮንቶስ 5:9-13፤ 2 ቆሮንቶስ 2:4) ይህ በእንዲህ እንዳለ ቲቶ ችግር ለደረሰባቸው የይሁዳ ክርስቲያኖች እየተካሄደ በነበረው እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ ድጋፍ እንዲሰጥ ወደ ቆሮንቶስ ተልኳል። በተጨማሪም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ደብዳቤ የሰጡትን ምላሽ እንዲያይ ሳይላክ አይቀርም።—2 ቆሮንቶስ 8:1-6
የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ምክር ምን ምላሽ ሰጥተው ይሆን? ጳውሎስ መልሱን ለማወቅ ስለጓጓ በተቻለው ፍጥነት ተመልሶ እንዲመጣ መመሪያ በመስጠት ቲቶን ከኤፌሶን በኤጂያን ባሕር በኩል ወደ ቆሮንቶስ ልኮት ሊሆን ይችላል። ይህ ተልዕኮ የተጠናቀቀው ክረምት በመግባቱ (በኅዳር አጋማሽ አካባቢ) ምክንያት በመርከብ የሚደረግ ጉዞ ከመቋረጡ በፊት ከሆነ ቲቶ በመርከብ ወደ ጢሮአዳ መሄድ ይችላል፤ አሊያም በሔለስፖንት በኩል በሚወስደው ረጅሙ የየብስ መንገድ ይጠቀማል። ጳውሎስ አንጥረኞቹ ያስነሱት ረብሻ ከታቀደው ጊዜ በፊት ኤፌሶንን ለቅቆ እንዲወጣ ስላስገደደው በጢሮአዳ ለመገናኘት በተቀጣጠሩበት ቦታ አስቀድሞ ሳይደርስ አይቀርም። ጳውሎስ ጢሮአዳ ውስጥ በጭንቀት ተውጦ ከቆየ በኋላ ቲቶ በመርከብ ሊመጣ እንደማይችል ተገነዘበ። ከዚህ የተነሳ ጳውሎስ መንገድ ላይ አገኘው ይሆናል በሚል ተስፋ የእግር ጉዞ ጀመረ። ጳውሎስ የአውሮፓን ምድር ከረገጠ በኋላ ቪያ ኢግናቲያ የሚባለውን መንገድ በመጠቀም መጨረሻ ከቲቶ ጋር መቄዶንያ ተገናኘ። ከቆሮንቶስ የመጣው የምስራች ለጳውሎስ ትልቅ እፎይታና ደስታ አስገኝቶለት ነበር። ጉባኤው ለሐዋርያው ምክር ጥሩ ምላሽ ሰጥቶ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 2:12, 13፤ 7:5-7
ጳውሎስ የላከው መልእክተኛ ምን ዓይነት አቀባበል ይጠብቀው ይሆን የሚለው ጉዳይ አሳስቦት የነበረ ቢሆንም እንኳ ቲቶ ተልዕኮውን እንዲወጣ አምላክ ረድቶታል። ቲቶን የተቀበሉት “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ” ነበር። (2 ቆሮንቶስ 7:8-15) የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሆኑት ደብልዩ ዲ ቶማስ የተናገሩትን ቃላት ከተጠቀምን “[ቲቶ] የጳውሎስን ኃይለኛ ወቀሳ ምንም ሳያለሳልስ የቆሮንቶስ ሰዎችን በጥበብና በዘዴ እንዳግባባቸው መገመት እንችላለን፤ ጳውሎስ ያን የመሰለ መልእክት ቢጽፍላቸውም ይህን ያደረገው ለእነሱ መንፈሳዊ ደህንነት በማሰብ ብቻ እንደሆነ አረጋግጦላቸዋል።” በዚህ መሃል ቲቶ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ባሳዩት የታዛዥነት መንፈስና ባደረጉት ገንቢ ለውጥ የተነሳ ለእነሱ ያለው ፍቅር አድጓል። ያሳዩት የሚያስመሰግን ጠባይ ለእሱ የማበረታቻ ምንጭ ሆኖለታል።
ቲቶ በይሁዳ ለሚገኙ ቅዱሳን እርዳታ የማሰባሰቡን እንቅስቃሴ ለማደራጀት ወደ ቆሮንቶስ የተላከበት ሌላው ተልዕኮስ ምን ላይ ደርሶ ይሆን? በ2 ቆሮንቶስ ላይ ከሚገኘው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ቲቶ ይህንንም ጉዳይ ሲከታተል ቆይቷል። ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ቲቶና ጳውሎስ ከተገናኙ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ55 እዘአ መጨረሻ ላይ በመቄዶንያ ሳይሆን አይቀርም። ቲቶ የጀመረውን እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ እንዲያጠናቅቅ በስም ካልተጠቀሱ ሁለት ረዳቶቹ ጋር ተመልሶ እንደተላከ ጳውሎስ ጽፏል። ቲቶ ለቆሮንቶስ ሰዎች ልባዊ ፍቅር ስላለው ተመልሶ ለመሄድ በጣም ፈቃደኛ ነበር። ቲቶ ወደ ቆሮንቶስ ተመልሶ በሄደበት ወቅት ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በመንፈስ አነሳሽነት የጻፈላቸውን ሁለተኛውን ደብዳቤ ሳይዝ አይቀርም።—2 ቆሮንቶስ 8:6, 17, 18, 22
ቲቶ ጥሩ የማደራጀት ችሎታ ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቁ ተልእኮዎችን በኃላፊነት መቀበል የሚችል ሰው ነበር። ቲቶ ደፋር፣ በሳልና ጽኑ ሰው ነበር። ጳውሎስ በቆሮንቶስ ያሉ ‘ዋነኞቹ ሐዋርያት’ ላስነሱት ተፈታታኝ ሁኔታ ቲቶ መፍትሔ ማግኘት ይችላል የሚል እምነት እንደነበረው ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (2 ቆሮንቶስ 11:5) በቲቶ ላይ የተጣለው ይህ አመኔታ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደገና ሲጠቀስ ሌላ ተፈታታኝ ሥራ በመወጣቱ ሊረጋገጥ ችሏል።
በቀርጤስ ደሴት በነበረበት ጊዜ
ጳውሎስ የሜድትራንያን ደሴት በሆነችው በቀርጤስ ያገለግል ለነበረው ለቲቶ ደብዳቤ የጻፈለት በ61 እና በ64 እዘአ መካከል ባለው ጊዜ በሆነ ወቅት ሳይሆን አይቀርም። በዚህ ጊዜ ቲቶ የሜዲትራንያን ደሴት በሆነችው በቀርጤስ በማገልገል ላይ ነበር። ጳውሎስ በዚያ የተወው ‘የጎደለውን በማሟላት እንዲያደራጅና’ ‘በየከተማው ሽማግሌዎችን እንዲሾም’ ነበር። አብዛኞቹ የቀርጤስ ሰዎች “ውሸታሞች፣ ጨካኞች፣ አውሬዎች፣ ሥራ ፈቶችና ሆዳሞች” እንደሆኑ ይነገርላቸው ነበር። ይህም በመሆኑ ቲቶ በቀርጤስም ድፍረትና ቆራጥነት የሚጠይቅ እርምጃ እንዲወስድ ይጠበቅበታል። (ቲቶ 1:5, 10-12) በደሴቲቱ ላይ የሚገኘው የክርስትና እምነት ወደፊት ምን መልክ እንደሚኖረው የሚወስን እርምጃ ስለሆነ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ ነበር። ቲቶ የበላይ ተመልካቾች ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ የሚያስባቸው ክርስቲያኖች ምን ብቃቶችን ማሟላት እንደሚፈለግባቸው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት በዝርዝር በማስቀመጥ ረድቶታል። እነዚህ ብቃቶች ዛሬም ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሚሾሙበት ጊዜ መመዘኛ ሆነው ያገለግላሉ።
ቅዱሳን ጽሑፎች ቲቶ ቀርጤስን የለቀቀው መቼ እንደሆነ አይነግሩንም። ጳውሎስ ጊዜው በውል ባልተጠቀሰበት ወቅት ዜማስና አጵሎስ በሚያደርጉት ጉዞ በዚያ ትንሽ ቆይታ እንደሚያደርጉ በመጥቀስ የሚያስፈልጋቸውን እንዲያሟላላቸው ስለጠየቀው እዚያ ረዘም ላለ ጊዜ ቆይቶ ነበር። ይሁን እንጂ ቲቶ በደሴቲቱ ላይ ለረጅም ጊዜ አይቀመጥም። ጳውሎስ አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደዚያ ለመላክ አቅዶ ነበር። ከዚያም ቲቶ ከሐዋርያው ጋር በኒቆጵልዩን ይገናኛል። ኒቆጵልዩን በሰሜን ምዕራብ ግሪክ የሚገኘው አንጋፋ ከተማ ሳይሆን አይቀርም።—ቲቶ 3:12, 13
ጳውሎስ በ65 እዘአ አካባቢ ሌላ ተልዕኮ እንዲያከናውን ቲቶን ሳይልከው እንዳልቀረ መጽሐፍ ቅዱስ ለመጨረሻ ጊዜ ስለ ቲቶ በመጠኑ ከሚጠቅሰው ሐሳብ እንረዳለን። ይህ ተልዕኮ ወደ አሁኗ ክሮኤሽያ ማለትም ከአድሪአቲክ ባሕር በስተምሥራቅ ወደምትገኘው ወደ ድልማጥያ እንዲጓዝ አድርጎታል። (2 ጢሞቴዎስ 4:10) ቲቶ በዚያ ምን እንደሚያከናውን የተነገረ ነገር የለም፤ ሆኖም ወደዚያ የተላከው የጉባኤ ጉዳዮችን እንዲቆጣጠርና በሚስዮናዊነት ሥራ እንዲካፈል እንደሆነ ይገመታል። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ቲቶ በቀርጤስ ሲያገለግል ከነበረው ኃላፊነት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ደረጃ ሠርቷል ማለት ነው።
ቲቶን የመሰሉ ጎልማሳ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በቅዱሳን ጽሑፎች መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ያላቸው የጠራ እውቀትና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በድፍረት ሥራ ላይ ማዋላቸው የጉባኤውን መንፈሳዊነት ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳል። የበላይ ተመልካቾችን በእምነታቸው እንምሰላቸው፤ እንዲሁም የእምነት ጓደኞቻችንን መንፈሳዊ ፍላጎቶች በማስቀደም ቲቶን እንደምንመስል እናሳይ።—ዕብራውያን 13:7
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ገላትያ 2:3 ቲቶ ግሪካዊ (ሔለን) እንደሆነ ይገልጻል። ይህ አባባል ቲቶ የግሪክ ተወላጅ መሆኑን ሊያመለክት ይችላል። ሆኖም አንዳንድ የግሪክ ጸሐፊዎች በውልደት ሳይሆን በቋንቋና በባሕል ግሪካዊ የሆኑ ሰዎችን ለማመልከት በብዙ ቁጥር (ሔለኒስ) ይጠቀሙ እንደነበር ይነገራል። ቲቶ ግሪካዊ የሆነው ከዚህ አንጻር ሊሆንም ይችላል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቲቶ በቆሮንቶስም ሆነ በሌሎች ቦታዎች የሚኖሩ ክርስቲያኖችን ለመጥቀም የሚጥር ደፋር የሥራ ጓደኛ ነበር