ሕሊናህ የሚነግርህን ተግባራዊ አድርግ
“ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም።”—ቲቶ 1:15
1. ጳውሎስ በቀርጤስ ከነበሩት ጉባኤዎች ጋር ምን ግንኙነት ነበረው?
ሐዋርያው ጳውሎስ ሦስተኛ ሚስዮናዊ ጉዞውን ካጠናቀቀ በኋላ ታሰረ፤ ጥቂት ቆይቶም ለሁለት ዓመታት ያህል በእስር ወደቆየባት ወደ ሮም ተወሰደ። ጳውሎስ ከእስር ሲፈታ ምን አደረገ? ከእስር ከተፈታ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከቲቶ ጋር ወደ ቀርጤስ ደሴት ሄደ። ከቲቶ ከተለየ በኋላም እንዲህ ሲል ጽፎለታል:- “አንተን በቀርጤስ የተውሁህ ገና ያልተስተካከለውን ነገር እንድታስተካክልና ባዘዝሁህ መሠረት በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው።” (ቲቶ 1:5) ቲቶ የተጣለበት ኃላፊነት ሕሊናን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ማየትን ይጨምር ነበር።
2. ቲቶ በቀርጤስ ደሴት ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ለምን ዓይነት ችግሮች መፍትሔ መስጠት ነበረበት?
2 ጳውሎስ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ብቃቶችን በሚመለከት ለቲቶ ከነገረው በኋላ፣ በዚያ “ዐመፀኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች” እንዳሉ ጠቁሞታል። እነዚህ ሰዎች “ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር ቤተ ሰብን ሁሉ በመበከል ላይ” ነበሩ። በመሆኑም ቲቶ ‘አጥብቆ ሊገሥጻቸው’ ይገባ ነበር። (ቲቶ 1:10-14፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:7) ጳውሎስ ቀለም ነክቶት ያደፈን ጥሩ ጨርቅ የሚያመለክት ቃል በመጠቀም የእነዚህ ሰዎች አእምሮና ሕሊና ‘እንደረከሰ’ ተናግሯል። (ቲቶ 1:15) ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ የግዝረትን ሥርዓት ይጠብቁ ስለነበር አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይቀሩም። እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች በዛሬው ጊዜ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ ተጽዕኖ አያሳድሩ ይሆናል። እንደዚያም ሆኖ ጳውሎስ ሕሊናን አስመልክቶ ለቲቶ ከሰጠው ምክር ብዙ የምንማረው ቁም ነገር አለ።
ሕሊናቸው የረከሰ ሰዎች
3. ጳውሎስ ለቲቶ ሕሊናን በተመለከተ ምን ጽፎለታል?
3 ጳውሎስ ስለ ሕሊና እንዲናገር ያነሳሳው ምን እንደሆነ ልብ በል። “ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ እንዲያውም አእምሮአቸውና ኅሊናቸው የረከሰ ነው። እግዚአብሔርን እናውቃለን ይላሉ፤ ዳሩ ግን በተግባራቸው ይክዱታል።” በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው በጊዜው የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ጤናማ ወይም “ትክክለኛ እምነት እንዲኖራቸው” ማስተካከያዎች ማድረግ ነበረባቸው። (ቲቶ 1:13, 15, 16) እነዚህ ሰዎች ንጹሕ የሆነውንና ያልሆነውን የመለየት ችግር ነበረባቸው፤ ይህ ደግሞ ከሕሊና ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው።
4, 5. በቀርጤስ ጉባኤ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምን ችግር ነበረባቸው? ይህስ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው እንዴት ነው?
4 ይህ ከመሆኑ ከአሥር ዓመት በፊት የክርስቲያኖች የበላይ አካል፣ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪ ለመሆን የግድ መገረዝ እንደማያስፈልግ የወሰነ ሲሆን ይህንንም ጉባኤዎች እንዲያውቁት አድርጓል። (የሐዋርያት ሥራ 15:1, 2, 19-29) ያም ሆኖ በቀርጤስ የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ‘የግዝረትን ሥርዓት ይከተሉ ነበር።’ እነዚህ ሰዎች “ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር” የበላይ አካሉን በግልጽ ተቃውመዋል። (ቲቶ 1:10 [የታረመው የ1980 ትርጉም], 11) አስተሳሰባቸው ስለተዛባ በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን ስለ መብልና ስለ መንጻት ሥርዓት የሚናገሩ ደንቦች ይከተሉና ሌሎችም እንደዚያ እንዲያደርጉ ያበረታቱ ነበር። ከዚህም በላይ በኢየሱስ ዘመን እንደነበሩት ፈሪሳውያን በሕጉ ላይ የራሳቸውን አስተሳሰብ ይጨምሩ ብሎም የአይሁድን ተረትና የሰውን ትእዛዝ ይጠብቁ ነበር።—ማርቆስ 7:2, 3, 5, 15፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:3
5 እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በማመዛዘን ችሎታቸው እንዲሁም ትክክልና ስህተት የሆነውን በመለየት ችሎታቸው ማለትም በሕሊናቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። ጳውሎስ “ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም” ሲል ጽፏል። የእነዚህ ሰዎች ሕሊና በመዛባቱ ምክንያት ለድርጊቶቻቸውም ሆነ ለውሳኔዎቻቸው አስተማማኝ መመሪያ ሊሆናቸው አልቻለም። ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን የተለያየ ውሳኔ ሊያደርግ በሚችልባቸው የግል ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የእምነት አጋሮቻቸውን ይነቅፉ ነበር። በዚህ መንገድ የቀርጤስ ክርስቲያኖች ርኩስ ያልሆነውን ነገር ርኩስ አድርገው ይመለከቱት ነበር። (ሮሜ 14:17፤ ቈላስይስ 2:16) እነዚህ ሰዎች አምላክን እናውቀዋለን ቢሉም በተግባራቸው ግን ክደውታል።—ቲቶ 1:16
“ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው”
6. ጳውሎስ እንዴት ስላሉ ሁለት ዓይነት ሰዎች ተናግሯል?
6 ጳውሎስ ለቲቶ ከጻፈለት መልእክት ምን ትምህርት እናገኛለን? እስቲ በሚከተለው ሐሳብ ውስጥ የቀረበውን ንጽጽር ልብ በል:- “ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው፤ ለርኩሳንና ለማያምኑ ግን ንጹሕ የሆነ ምንም ነገር የለም፤ እንዲያውም አእምሮአቸውና ኅሊናቸው የረከሰ ነው።” (ቲቶ 1:15) ጳውሎስ በሥነ ምግባር ንጹሕ ለሆነ ክርስቲያን ሁሉ ነገር ንጹሕና የተፈቀደ ነው ማለቱ እንዳልነበር ግልጽ ነው። ምክንያቱም ጳውሎስ በሌላ ደብዳቤው ላይ ዝሙት፣ ጣዖት አምልኮ፣ መናፍስታዊ ድርጊትና የመሳሰሉትን የሚፈጽሙ ሰዎች ‘የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ’ ተናግሯል። (ገላትያ 5:19-21) ስለሆነም ጳውሎስ ስለ ሁለት ዓይነት ሰዎች ይኸውም በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ንጹሕ ስለሆኑና ስላልሆኑ ሰዎች እየተናገረ ነበር ብለን መደምደም እንችላለን።
7. ዕብራውያን 13:4 ምንን ያወግዛል? ይሁንና ምን ጥያቄ ሊነሳ ይችላል?
7 ቅን የሆኑ ክርስቲያኖች ማስወገድ የሚገባቸው መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ የሚከለክላቸውን ነገሮች ብቻ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ የሚከተለውን በግልጽ የተቀመጠ መሠረታዊ ሥርዓት ተመልከት:- “ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች [“ዝሙት በሚፈጽሙ፣” NW] ሁሉ ላይ ይፈርዳል።” (ዕብራውያን 13:4) ክርስቲያኖች ያልሆኑና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እውቀት የሌላቸው ሰዎች እንኳ ይህ ጥቅስ ምንዝርን እንደሚያወግዝ መገንዘብ አይሳናቸውም። ከዚህም ሆነ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መረዳት እንደሚቻለው ያገቡ ሰዎች ከሕጋዊ የትዳር ጓደኛቸው ውጭ የሚፈጽሙትን የጾታ ግንኙነት አምላክ ያወግዛል። ይሁንና ሁለት ያላገቡ ሰዎች በአፍ የሚደረግ የጾታ ግንኙነት ቢፈጽሙስ? በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች ይህ ድርጊት የጾታ ግንኙነት ስላልሆነ ምንም ክፋት የለውም ሲሉ ይደመጣል። አንድ ክርስቲያን በአፍ የሚደርግን የጾታ ግንኙነት ንጹሕ እንደሆነ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል?
8. በአፍ የሚፈጸምን የጾታ ግንኙነት በሚመለከት የክርስቲያኖች አቋም በዓለም ከሚገኙ በርካታ ሰዎች የሚለየው እንዴት ነው?
8 ዕብራውያን 13:4 እና 1 ቆሮንቶስ 6:9 [NW] አምላክ ምንዝርንም ሆነ ዝሙትን (በግሪክኛው ፖርኒያ) እንደሚያወግዝ ያረጋግጣሉ። ይሁንና ዝሙት ምንን ይጨምራል? ፖርኒያ የሚለው ግሪክኛ ቃል የጾታ ብልትን ተፈጥሯዊም ሆነ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ ለብልግና ድርጊት መጠቀምን ያካትታል። በተጨማሪም ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆነው ጋብቻ ውጭ የሚደረግን ማንኛውንም ዓይነት ልቅ የጾታ ግንኙነት ያመለክታል። በመሆኑም፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች በአፍ የሚደረግ የጾታ ግንኙነት ተቀባይነት እንዳለው ቢነገራቸውም ወይም ደግሞ እነሱ ራሳቸው የሚያምኑበት ቢሆንም እንኳ ይህ ድርጊት ከዝሙት የሚፈረጅ ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች “ለፍላፊዎችና አታላዮች” በአስተሳሰባቸውና በድርጊታቸው ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩባቸው አይፈቅዱም። (ቲቶ 1:10) ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን የላቀ የአቋም ደረጃ አጥብቀው ይከተላሉ። በአፍ የሚፈጸም የጾታ ግንኙነት ትክክል እንደሆነ ለማሳመን ምክንያት ከመደርደር ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ይህ ድርጊት ዝሙት ወይም ፖርኒያ መሆኑን ይገነዘባሉ። በመሆኑም ሕሊናቸውን ይህን ነገር እንዲጠላ ያሠለጥኑታል።a—የሐዋርያት ሥራ 21:25፤ 1 ቆሮንቶስ 6:18፤ ኤፌሶን 5:3
የተለያየ ሕሊና፣ የተለያየ ውሳኔ
9. ‘ሁሉም ነገር ንጹሕ ከሆነ’ ሕሊና የሚኖረው ሚና ምንድን ነው?
9 ታዲያ ጳውሎስ “ለንጹሓን ሁሉም ነገር ንጹሕ ነው” ሲል ምን ማለቱ ነው? ጳውሎስ እየተናገረ ያለው አስተሳሰባቸውን እንዲሁም ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን የመለየት ችሎታቸውን በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃል ውስጥ ከምናገኛቸው የአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ስላስማሙ ክርስቲያኖች ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች በቀጥታ ያልተከለከሉ በርካታ ጉዳዮችን በተመለከተ አንዳቸው ከሌላው የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚችል ይገነዘባሉ። በመሆኑም ሌሎችን ከመንቀፍ ይልቅ አምላክ ያላወገዛቸውን ነገሮች “ንጹሕ” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ቀጥተኛ መመሪያ በማይሰጥባቸው የኑሮ ዘርፎች ላይ ሌሎች እነሱ ያላቸው ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው አይጠብቁም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዴት ሊከሰት እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ እስቲ እንመልከት።
10. የሠርግ (ወይም የቀብር) ሥነ ሥርዓት ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል?
10 አንዱ የትዳር ጓደኛ ብቻ የይሖዋ ምሥክር የሆነባቸው በርካታ ቤተሰቦች አሉ። (1 ጴጥሮስ 3:1፤ 4:3) ይህ ሁኔታ የዘመድ ሠርግ ወይም ቀብር በሚኖርበት ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉትን ጨምሮ ሌሎች ተፈታታኝ ችግሮች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ እምነቷን የማይጋራ ባል ያላት አንዲት ክርስቲያን ሊያጋጥማት የሚችለውን ሁኔታ ተመልከት። የባለቤቷ ዘመድ የሚያገባበት ጊዜ ደርሷል፤ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወነው ደግሞ በሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው። (ወይም ደግሞ የባለቤቷ ወላጅ አሊያም ዘመድ ሞቷል፤ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የሚከናወነውም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው።) ባልና ሚስቱ በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ የተጋበዙ ሲሆን ባልየው ሚስቱ አብራው እንድትሄድ ፈልጓል። የዚህች ክርስቲያን ሕሊና በሥነ ሥርዓቱ ላይ ስለ መገኘቷ ምን ይላል? ምን ታደርግ ይሆን? የሚከተሉትን ሁለት አማራጮች ተመልከት።
11. አንዲት ክርስቲያን ሚስት በቤተ ክርስቲያን በሚደረግ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ይኖርባት እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን ምን ብላ ልታስብ ትችላለች? ይህስ ወደ ምን መደምደሚያ ያደርሳታል?
11 ሊዲያ፣ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ‘ከታላቂቱ ባቢሎን ውጡ’ የሚለውን ጥብቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ በደንብ አሰላሰለችበት። (ራእይ 18:2, 4) የይሖዋ ምሥክር ከመሆኗ በፊት የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ የሚካሄድበት ቤተ ክርስቲያን አባል ስለነበረች በቦታው የሚገኙ ሰዎች በሙሉ እንደ ጸሎትና መዝሙር ባሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዲካፈሉ እንደሚጠበቅባቸው ታውቃለች። እንዲህ ባለው ሥነ ሥርዓት ላይ ምንም ዓይነት ተካፋይነት እንዲኖራትም ሆነ አቋሟን እንድታላላ ግፊት እንዲደረግባት ስላልፈለገች በዚህ ቦታ ላይ ጨርሶ ላለመገኘት ወሰነች። ሊዲያ በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ራሷ የሆነውን ባሏን የምታከብር ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር ለመተባበር ትፈልጋለች። ሆኖም የምትከተላቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች መጣስ አትፈልግም። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) በመሆኑም ባለቤቷ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ቢወስንም እሷ ግን አብራው ልትሄድ እንደማትችል በዘዴ ታስረዳዋለች። በቦታው ተገኝታ በአንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ ለመካፈል ፈቃደኛ ባትሆን እሱን ሊያሳፍረው እንደሚችል በመግለጽ በዚያ አለመገኘቷ የተሻለ እንደሚሆን ልትነግረው ትችላለች። ይህ ውሳኔዋ ሕሊናዋን ከማቆሸሽ ይጠብቃታል።
12. አንድ ሰው በቤተ ክርስቲያን በሚፈጸም የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኝ ሲጋበዝ ምን ብሎ ሊያስብ ይችላል? ምን ውሳኔስ ሊያደርግ ይችላል?
12 ሩትም የሊዲያ ዓይነት ሁኔታ ገጥሟታል። እሷም ለባሏ አክብሮት ያላት ሲሆን ለአምላክ ታማኝ ለመሆንም ቁርጥ ውሳኔ አድርጋለች። እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናዋ የሚነግራትን ትሰማለች። ሩት፣ ሊዲያ ባሰበችባቸው ጉዳዮች ላይ ካሰላሰለች በኋላ በግንቦት 15, 2002 መጠበቂያ ግንብ ላይ “የአንባቢያን ጥያቄዎች” በሚለው ዓምድ ሥር የወጣውን ሐሳብ በጸሎት አሰበችበት። ሦስቱ ዕብራውያን የጣዖት አምልኮ በሚካሄድበት ቦታ ላይ እንዲገኙ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ያከበሩ ቢሆንም በጣዖት አምልኮው ባለመካፈል ጽኑ አቋማቸውን እንደጠበቁ አስታወሰች። (ዳንኤል 3:15-18) በመሆኑም ሩት ከባለቤቷ ጋር ለመሄድ፣ ሆኖም በማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላለመካፈል ወሰነች። በዚህ መንገድ ከሕሊናዋ ጋር የሚስማማ እርምጃ ወስዳለች። ሩት ሕሊናዋ እንድታደርግ የሚፈቅድላት ነገር ምን እንደሆነና እንዳልሆነ በግልጽ ሆኖም በዘዴ ለባለቤቷ አስረዳችው። ባለቤቷም በእውነተኛውና በሐሰተኛው አምልኮ መካከል ያለውን ልዩነት መገንዘብ እንደሚችል እምነት አላት።—የሐዋርያት ሥራ 24:16
13. ሁለት ክርስቲያኖች በአንድ ዓይነት ጉዳይ ላይ የተለያየ ውሳኔ ማድረጋቸው ሊረብሸን የማይገባው ለምንድን ነው?
13 ሁለት ክርስቲያኖች በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ ውሳኔ ማድረጋቸው፣ አንድ ሰው የሚወስደው እርምጃ ምንም ለውጥ አያመጣም ወይም ከሁለት አንዳቸው ደካማ ሕሊና አላቸው ማለት ነው? በፍጹም። ሊዲያ ቀደም ሲል ከቤተ ክርስቲያን መዝሙርና ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ከነበራት ተሞክሮ በመነሳት በዚያ ቦታ ላይ መገኘቷ በተለይ ለእሷ አደገኛ እንደሚሆን ተስምቷታል። ከዚህም ባሻገር ቀደም ሲል ከባለቤቷ ጋር በሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ውይይት በሕሊናዋ ላይ ተጽዕኖ አድርጎ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ለእሷ የተሻለ ነው ብላ ያሰበችውን ውሳኔ አድርጋለች።
14. ክርስቲያኖች የግል ውሳኔን በሚጠይቁ ጉዳዮች ረገድ ሊዘነጉት የማይገባው ነገር ምንድን ነው?
14 የሩት ውሳኔስ የተሳሳተ ነበር? ሌሎች ሩት ያደረገችው ውሳኔ የተሳሳተ ነው ወይም አይደለም ብለው መፍረድ አይችሉም። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመገኘት ሆኖም በማንኛውም ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ላለመካፈል በመወሰኗ ሊነቅፏት አይገባም። ጳውሎስ የተወሰኑ የምግብ ዓይነቶችን ስለመብላት ወይም ስላለመብላት የሚደረጉ የግል ውሳኔዎችን በተመለከተ የሰጠውን ምክር ልብ በል:- “የሚበላ የማይበላውን አይናቅ፤ የማይበላውም፣ የሚበላውን አይኰንን፤ . . . እርሱ ቢወድቅ ወይም ቢቆም ለጌታው ነው፤ ጌታ ሊያቆመው ስለሚችልም ይቆማል።” (ሮሜ 14:3, 4) የትኛውም እውነተኛ ክርስቲያን አንድ ሰው የሠለጠነ ሕሊናው የሚሰጠውን መመሪያ ችላ እንዲል አያበረታታም። ምክንያቱም እንዲህ ማድረግ ሕይወቱን ሊያድንለት የሚችለውን መልእክት እንዳያዳምጥ የማበረታታት ያህል ነው።
15. አንድ ክርስቲያን ውሳኔ ሲያደርግ ስለ ሌሎች ሕሊናና ስሜት በቁም ነገር ማሰብ ያለበት ለምንድን ነው?
15 ቀደም ሲል በተመለከትነው ሁኔታ ውስጥ የተጠቀሱት ሁለት እህቶች ከግምት ውስጥ ሊያስገቧቸው የሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ ውሳኔያቸው በሌሎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ሲል መክሮናል:- “በወንድምህ መንገድ ላይ የማሰናከያ ድንጋይ ወይም ወጥመድ እንዳታስቀምጥ ቁርጥ ሐሳብ አድርግ።” (ሮሜ 14:13) ሊዲያ፣ ከዚያ በፊት የተከሰተ ተመሳሳይ ሁኔታ በጉባኤዋ ወይም በቤተሰቧ ውስጥ ችግር ፈጥሮ እንደነበር ታውቅ ይሆናል። በመሆኑም እሷ የምታደርገው ውሳኔ በልጆቿ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ከዚህ በተቃራኒ ሩት ከዚህ ቀደም ሌላ ሰው ያደረገው ተመሳሳይ ውሳኔ በጉባኤዋም ሆነ በአካባቢዋ ያሉ ሰዎችን ስሜት እንዳልጎዳ ታውቃለች። ሁለቱ እህቶችም ሆኑ እኛ ሁላችን፣ በአግባቡ የሠለጠነ ሕሊና አንድ ውሳኔ በሌሎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አቅልሎ እንደማይመለከት መገንዘብ ይኖርብናል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “በእኔ ከሚያምኑት ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሰው፣ ከባድ የወፍጮ ድንጋይ በዐንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር ተጥሎ ቢሰጥም ይሻለዋል።” (ማቴዎስ 18:6) አንድ ሰው ድርጊቱ ሌሎችን ሊያሰናክል እንደሚችል ማስተዋል ከተሳነው፣ በቀርጤስ እንደነበሩት አንዳንድ ክርስቲያኖች ሕሊናው ረክሶ ወይም ቆሽሾ ሊሆን ይችላል።
16. አንድ ክርስቲያን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ምን ዓይነት ለውጥ እንዲያሳይ ይጠበቅበታል?
16 አንድ ክርስቲያን ሕሊናውን በመስማትና ሕሊናው ከሚያስተላልፍለት መልእክት ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ማሻሻያ እያደረገ መሄድ እንዳለበት ሁሉ በመንፈሳዊ ማደጉን መቀጠልም ይኖርበታል። በቅርቡ የተጠመቀውን የማርቆስን ሁኔታ እንመልከት። ማርቆስ ሕሊናው ቀደም ሲል ይካፈልባቸው ከነበሩ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ልማዶች እንዲርቅ ይነግረዋል። እነዚህ ልማዶች ከጣዖት አምልኮ ወይም ከደም ጋር የተያያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 21:25) ሌላው ቀርቶ አምላክ ከሚያወግዛቸው ነገሮች ጋር ይመሳሰላሉ ብሎ ከሚያስባቸው ነገሮች ሁሉ ይርቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች፣ አንዳንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ጨምሮ እሱ ምንም ችግር የለባቸውም ብሎ ከሚያስባቸው ነገሮች ሲርቁ መመልከቱ ግራ አጋብቶታል።
17. ጊዜና መንፈሳዊ እድገት በአንድ ክርስቲያን ሕሊናና በሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት እንደሆነ ግለጽ።
17 በጊዜ ሂደት ማርቆስ በእውቀት እያደገና ይበልጥ ወደ አምላክ እየቀረበ መጥቷል። (ቈላስይስ 1:9, 10) ታዲያ ይህ ምን ለውጥ አመጣ? ሕሊናው ብዙ ሥልጠና አግኝቷል። አሁን ማርቆስ ሕሊናውን በበለጠ የመስማት ዝንባሌ ማዳበርና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሚገባ ማመዛዘን ችሏል። እንዲያውም አምላክ ከሚያወግዛቸው ነገሮች ጋር “ይመሳሰላሉ” ብሎ በማሰብ የሚርቃቸው ነገሮች በእርግጥ የአምላክን አስተሳሰብ እንደማይቃረኑ ተረድቷል። ከዚህም በተጨማሪ ማርቆስ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ መከተልንና በሚገባ የሠለጠነው ሕሊናው የሚነግረውን መስማትን ስለተማረ ቀደም ሲል ጥሩ ናቸው ብሎ ያስባቸው የነበሩትን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላለማየት እንዲወስን ሕሊናው ረድቶታል። አዎን፣ ሕሊናው ይበልጥ እየሠለጠነ ሄዷል።—መዝሙር 37:31
18. ለደስታችን ምክንያት የሚሆን ምን ነገር አለ?
18 በአብዛኞቹ ጉባኤዎች ውስጥ በሁሉም ክርስቲያናዊ የእድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች አሉ። አንዳንዶች በቅርቡ አማኝ የሆኑ ናቸው። የእነዚህ ክርስቲያኖች ሕሊና አንዳንድ ጉዳዮችን በተመለከተ ምንም ድምፅ አያሰማ ይሆናል፤ በሌሎች ጉዳዮች ረገድ ደግሞ ሕሊናቸው ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። እነዚህ ሰዎች የይሖዋን መመሪያ መከተልንና የሠለጠነውን ሕሊናቸውን መስማትን እንዲማሩ ጊዜና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (ኤፌሶን 4:14, 15) በሌላ በኩል ደግሞ በዚያው ጉባኤ ውስጥ ጥልቅ እውቀት ያላቸው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ላይ በማዋል ተሞክሮ ያካበቱና ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ ሕሊና ያላቸው በርካታ ክርስቲያኖች መኖራቸው ያስደስታል። ከሥነ ምግባርና ከመንፈሳዊ ነገሮች አኳያ በጌታ ዘንድ “ንጹሕ” የሆነውን ማስተዋል በሚችሉ “ንጹሓን” መካከል መሆን ምንኛ ደስ ያሰኛል! (ኤፌሶን 5:10) ሁላችንም ወደዚህ ደረጃ መድረስና ከትክክለኛው የእውነት እውቀት ጋር የሚስማማና ለአምላክ ታማኝ የሆነ ሕሊና ማዳበር ግባችን ይሁን።—ቲቶ 1:1
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የመጋቢት 15, 1983 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) በገጽ 30 እና 31 ላይ በባልና ሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ሐሳብ ይሰጣል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በቀርጤስ የሚገኙ አንዳንድ ክርስቲያኖች የረከሰ ሕሊና ሊኖራቸው የቻለው እንዴት ነው?
• በሚገባ የሠለጠነ ሕሊና ያላቸው ሁለት ክርስቲያኖች የተለያየ ውሳኔ ሊያደርጉ የሚችሉት ለምንድን ነው?
• ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ሕሊናችን ምን መሆን አለበት?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሲሲሊ
ግሪክ
ቀርጤስ
ትንሿ እስያ
ቆጵሮስ
የሜድትራንያን ባሕር
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሁለት ክርስቲያኖች የተለያዩ ውሳኔዎች ሊያደርጉ ይችላሉ