“የእውነትን ቃል በትክክል የሚጠቀም”
የአምላክ ቃል ሕይወትን የተሳካ ለማድረግ የሚጠቅሙ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚገኙበት ጎተራ ነው። አንድ የአምላክ አገልጋይ ማስተማር፣ መገሠጽና እርማት መስጠት እንዲችል ይረዳዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ቢሆንም ከዚህ መለኮታዊ ምንጭ ካለው መመሪያ ሙሉ በሙሉ ለመጠቀም ከፈለግን ሐዋርያው ጳውሎስ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር [“በትክክል የሚጠቀም” አዓት] የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” በማለት ለጢሞቴዎስ የሰጠውን ምክር መከተል አለብን።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
የአምላክ ቃል በተለያዩ ነገሮች ተመስሏል፤ ከእነዚህም መካከል አካልን በሚያዳብር ወተት፣ በጠንካራ ምግብ፣ በሚያረካና ንጹሕ በሚያደርግ ውኃ፣ በመስተዋት እንዲሁም በስለታም ሰይፍ ተመስሏል። አንድ አገልጋይ እነዚህ አገላለጾች ምን ትርጉም እንዳላቸው ከተረዳ መጽሐፍ ቅዱስን ጥሩ አድርጎ ሊጠቀምበት ይችላል።
የአምላክን ቃል ወተት ማሰራጨት
ወተት ገና ለተወለዱ ሕፃናት የሚያስፈልግ ምግብ ነው። ሕፃኑ እያደገ ሲሄድ ቀስ በቀስ ጠንካራ ምግብ መመገብ ቢጀምርም መጀመሪያ ላይ መመገብ የሚችለው ወተት ብቻ ነው። የአምላክን ቃል ብዙም የማያውቁ ሰዎች በብዙ መንገድ ከሕፃናት ጋር ይመሳሰላሉ። የአምላክን ቃል በቅርቡ ማጥናት የጀመረም ሆነ ከአምላክ ቃል ጋር ብዙም ያልተዋወቀ አንድ ሰው እውቀቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላለፈ ከሆነ መንፈሳዊ ሕፃን ከመሆኑም በላይ ለማድቀቅ የማያስቸግር ገንቢ ምግብ ማለትም መንፈሳዊ “ወተት” ያስፈልገዋል። “ጠንካራ ምግብ” ይኸውም በአምላክ ቃል ውስጥ ያሉትን ጠለቅ ያሉ ነገሮች ለመመገብ ገና አልደረሰም።—ዕብራውያን 5:12
ጳውሎስ በቆርንቶስ ለተቋቋመው አዲስ ጉባኤ “ገና ጽኑ መብል ለመብላት አትችሉም ነበረና ወተት ጋትኋችሁ” ብሎ በጻፈላቸው ጊዜ ያሉበት ሁኔታ ይህንን ይመስል ነበር። (1 ቆሮንቶስ 3:2) የቆሮንቶስ ሰዎች አስቀድሞ “ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን” ትምህርት መማር ያስፈልጋቸው ነበር። (ዕብራውያን 5:12) በዚያን ጊዜ በነበሩበት የዕድገት ደረጃ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” መመገብ አይችሉም ነበር።—1 ቆሮንቶስ 2:10
በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን አገልጋዮች መንፈሳዊ ሕፃናት ለሆኑ ሰዎች “ወተት” በመጋት ይኸውም በዋና ዋናዎቹ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው በመርዳት ልክ እንደ ጳውሎስ ለእነርሱ ያላቸውን አሳቢነት ያሳያሉ። ክርስቲያኖች እንደነዚህ ያሉት አዳዲስ ወይም ያልጎለመሱ ሰዎች ‘የቃልን ወተት እንዲመኙ’ ያበረታቷቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:2) ሐዋርያው ጳውሎስ “ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅም” ብሎ በጻፈ ጊዜ አዳዲሶች የሚያስፈልጋቸውን ልዩ ትኩረት እንዳስተዋለ አሳይቷል። (ዕብራውያን 5:13) የአምላክ አገልጋዮች በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትም ሆነ በጉባኤ ለአዳዲስ ወይም ተሞክሮ ለሌላቸው ሰዎች ንጹሑን ወተት ሲያካፍሉ ትዕግሥት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ የሰውን ችግር መረዳትና ደግነት ይፈለግባቸዋል።
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ጠንካራ ምግብ ለሌሎች ማካፈል
አንድ ክርስቲያን ለመዳን ‘ከወተት’ የበለጠ ነገር ያስፈልገዋል። ዋና ዋናዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በትክክል ከተረዳና ከተቀበለ ‘የጎለመሱ ሰዎች የሚመገቡትን ጠንካራ ምግብ’ ለመመገብ ዝግጁ ነው ማለት ነው። (ዕብራውያን 5:14 አዓት) ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ዋንኛው መንገድ የግል ጥናትን ቋሚ ልማድ በማድረግና በክርስቲያን ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ነው። እንደዚህ ያሉ ጥሩ ልማዶች አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ እንዲጠነክርና እንዲጎለምስ ከማስቻላቸውም በላይ በአገልግሎቱ ውጤታማ ያደርጉታል። (2 ጴጥሮስ 1:8) ከእውቀት በተጨማሪ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸምም የመንፈሳዊ ምግብ አንዱ ክፍል እንደሆነ መዘንጋት የለብንም።—ዮሐንስ 4:34
በዛሬው ጊዜ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለአምላክ አገልጋዮች በተገቢው ሰዓት ምግብ እንዲያቀርብና ‘ብዛት ያለውን ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ’ እንዲያስተውሉ እንዲረዳቸው ተሹሟል። ይሖዋ በጽሑፍ እያዘጋጀ በታማኝነት ‘በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ’ በሚያቀርበው ታማኝ ባሪያው አማካኝነት በመንፈሱ ጥልቅ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ይገልጣል። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ኤፌሶን 3:10, 11፤ ከራእይ 1:1, 2) እያንዳንዱ ክርስቲያን በጽሑፎች አማካኝነት በሚቀርበው በዚህ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ የመጠቀም ኃላፊነት አለበት።—ራእይ 1:3
እርግጥ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ነገሮች የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንኳ ‘ማስተዋል ያስቸግራቸዋል።’ (2 ጴጥሮስ 3:16) ከፍተኛ ጥናትና ማሰላሰል የሚጠይቁ አመራማሪ አገላለጾች፣ ትንቢቶችና ምሳሌዎች አሉ። ከዚህ የተነሳ የግል ጥናት የአምላክን ቃል በጥልቅ መቆፈርን ይጠይቃል። (ምሳሌ 1:5, 6፤ 2:1-5) በዚህ ረገድ በተለይ ሽማግሌዎች ጉባኤውን በሚያስተምሩበት ጊዜ ኃላፊነት አለባቸው። ሽማግሌዎች የጉባኤውን መጽሐፍ ጥናትም ሆነ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በመምራት ወይም የሕዝብ ንግግር በመስጠት አለዚያም በሌሎች በየትኞቹም የማስተማሪያ መስኮች ተጠቅመው ለጉባኤው ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ ሲያቀርቡ ከሚሰጡት ትምህርት ጋር በደንብ ለመተዋወቅና ‘በጥሩ የማስተማር ዘዴ’ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ አለባቸው።—2 ጢሞቴዎስ 4:2 አዓት
ጥምን የሚያረካና ቆሻሻን የሚያስወግድ ውኃ
ኢየሱስ በአንድ ምንጭ አጠገብ ላገኛት ሳምራዊት ሴት የሚጠጣ ነገር እንደሚሰጣት ነግሯት ነበር። ይህም “ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ” ይሆንላታል። (ዮሐንስ 4:13, 14፤ 17:3) ይህ ሕይወት ሰጪ ውኃ አምላክ ሕይወት ለማስገኘት በበጉ አማካኝነት ያዘጋጀውን ማንኛውንም ዝግጅት የሚያጠቃልል ሲሆን ይህ ዝግጅት ምን እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል። ይህንን “ውኃ” ተጠምተን የነበርን እንደመሆናችን መጠን በመንፈሱና በክርስቶስ ሙሽራ አማካኝነት የቀረበልንን “የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ” የሚለውን ግብዣ ተቀብለናል። (ራእይ 22:17) ይህንን ውኃ መጠጣት ለዘላለም መኖር ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ የአቋም ደረጃዎች አስቀምጧል። መለኮታዊ ምንጭ ያላቸውን እነዚህን የአቋም ደረጃዎች በተግባር ባዋልን መጠን ይሖዋ አምላክ ከሚጠላቸው ነገሮች ሁሉ ‘በመታጠብ’ በይሖዋ ቃል እንነጻለን። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) በዚህ የተነሳ በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት ‘የመታጠቢያ ውኃ’ ተብሏል። (ኤፌሶን 5:26) የአምላክ ቃል በዚህ መንገድ እንዲያጥበን ካልፈቀድንለት አምልኮታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም።
‘የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገሩ’ ሽማግሌዎች በውኃ መመሰላቸው ተስማሚ ነው። ሽማግሌዎች ‘በጥም ቦታ እንደ ወንዝ ፈሳሽ’ እንደሆኑ ኢሳይያስ ተናግሯል። (ኢሳይያስ 32:1, 2) አፍቃሪ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እረኛ ሆነው ወንድሞቻቸውን ሲጎበኙ፣ ሕይወት በሚያድሰው በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው የሚያበረታታ ትምህርት ሌሎችን ለማነጽና ለማጽናናት ሲጠቀሙ ይህንን መግለጫ ይሠሩበታል።—ከማቴዎስ 11:28, 29 ጋር አወዳድር።a
የጉባኤው አባላት የሽማግሌዎችን ጉብኝት በጉጉት ይጠባበቃሉ። “ሽማግሌዎች ምን ያህል አጽናኝ እንደሆኑ አውቃለሁ፤ ይሖዋ ይህንን ዝግጅት በማድረጉ በጣም ደስተኛ ነኝ” በማለት ቦኒ ተናግራለች። ልጆች ያለ አባት የምታሳድግ ሊንዳ የተባለች እናት “ሽማግሌዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻዎችን በመስጠት ችግሬን እንዳሸንፍ ረድተውኛል። ያዳምጡኝና ርኅራኄ ያሳዩኝ ነበር” በማለት ጽፋለች። ማይክል ደግሞ “አሳቢ በሆነ ድርጅት ውስጥ እንዳለሁ እንዲሰማኝ አድርገዋል” ብሏል። ሌላኛዋ ደግሞ “የሽማግሌዎች ጉብኝት ለረጅም ጊዜ የተጠናወተኝን የመንፈስ ጭንቀት እንዳሸንፍ ረድቶኛል” ብላለች። ሽማግሌዎች የሚያደርጉት በመንፈሳዊ የሚያነቃቃ ጉብኝት ልክ ጥምን እንደሚያረካ ቀዝቃዛ ውኃ ነው። በግ መሰል ሰዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑት መሠረታዊ ሥርዓቶች እነርሱ ለሚገኙበት ሁኔታ እንዴት እንደሚሠሩ እንዲያስተውሉ አፍቃሪ የሆኑ ሽማግሌዎች እርዳታ ሲያደርጉላቸው ይጽናናሉ።—ሮሜ 1:11, 12፤ ያዕቆብ 5:14
የአምላክን ቃል እንደ መስተዋት ተጠቀምበት
አንድ ሰው ጠንካራ ምግብ የሚመገበው ስለሚጣፍጠው ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚያስችለውን ጥንካሬ ለማግኘት ይፈልጋል። ልጅ ከሆነ ምግቡ ወደ አዋቂነት ለማደግ ይረዳኛል ብሎ ያስባል። መንፈሳዊ ምግብም እንደዚሁ ነው። የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስደሳች ሊሆን ቢችልም ዋና ዓላማው ግን ይህ አይደለም። መንፈሳዊ ምግብ ሊለውጠን ይገባል። መንፈሳዊ ምግብ የመንፈስ ፍሬዎችን ለይቶ ለማወቅና ለማፍራት እንዲሁም “የፈጠረውንም ምሳሌ እንዲመስል እውቀትን ለማግኘት የሚታደሰውን አዲሱን ሰው” ለመልበስ ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:10፤ ገላትያ 5:22-24) ከዚህም በተጨማሪ በቅዱሳን ጽሑፎች በተሻለ ሁኔታ ተጠቅመን የራሳችንንና የሰዎችን ችግር እስከመፍታት ድረስ እንድንጎለምስ ይረዳናል።
መጽሐፍ ቅዱስ በእኛ ላይ እንዲህ ያለ ውጤት ማስከተሉን እንዴት እናውቃለን? መጽሐፍ ቅዱስን ልክ እንደ መስተዋት በመጠቀም ነው። ያዕቆብ እንዲህ አለ፦ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ . . . የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ። ቃሉን የሚሰማ የማያደርገውም ቢኖር የተፈጥሮ ፊቱን በመስተዋት የሚያይን ሰው ይመስላል፤ ራሱን አይቶ ይሄዳልና፣ ወዲያውም እንደ ምን እንደ ሆነ ይረሳል። ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት፣ ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነው፣ በሥራው የተባረከ ይሆናል።”—ያዕቆብ 1:22-25
መጽሐፍ ቅዱስን ቀረብ ብለን ስንመረምረውና በአምላክ የአቋም ደረጃዎች መሠረት አሁን ያለንን ማንነት ወደፊት መሆን ካለብን ዓይነት ሰው ጋር ስናነጻጽር የአምላክን ቃል ‘እየተመለከትን’ ነው ማለት ነው። ይህንን ስናደርግ ‘ቃሉን ከመስማት አልፈን የምናደርግ’ እንሆናለን። መጽሐፍ ቅዱስ በእኛ ላይ ገንቢ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
የአምላክን ቃል እንደ ሰይፍ መጠቀም
ወደ ማጠቃለያው ስንመጣ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ቃል እንደ ሰይፍ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ አሳይቶናል። ጳውሎስ ‘ከአለቆች፣ ከሥልጣናት፣ ከዚህ ከጨለማ ዓለም ገዦችና በሰማያዊ ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት’ እንድንጠነቀቅ ሲነገረን ‘የመንፈስን ሰይፍ ማለትም የእግዚአብሔርን ቃል እንድንይዝ’ አጥብቆ አሳስቦናል። (ኤፌሶን 6:12, 17) የአምላክ ቃል ‘በእግዚአብሔር እውቀት ላይ የሚነሣ’ ማንኛውንም አስተሳሰብ ለማስወገድ ልንጠቀምበት የምንችል አስፈላጊነቱ የማያጠያይቅ የጦር ዕቃ ነው።—2 ቆሮንቶስ 10:3-5
“የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ” መሆኑ ምንም አያጠያይቅም። (ዕብራውያን 4:12) ይሖዋ በመንፈስ መሪነት ባጻፈው ቃሉ አማካኝነት ይናገራል። ሌሎችን ስታስተምርና የሐሰት ትምህርቶችን ስታጋልጥ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምበት። ሌሎችን ለማበረታታት፣ ለማነጽ፣ ለማርካት፣ ለማጽናናት፣ ለሥራ ለማነሳሳትና በመንፈሳዊ ለማጠናከር ተጠቀምበት። ይሖዋ ምንጊዜም “ደስ የሚያሰኘውን” ነገር ታደርግ ዘንድ ‘በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቅህ።’—ዕብራውያን 13:21 የ1980 ትርጉም
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመስከረም 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20-3 ላይ ያለውን “ሩኅሩኅ እረኞች ሆነው ግልገሎቹን ይጠብቃሉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች ‘የእውነትን ቃል በትክክል በመጠቀም’ ሌሎችን ያበረታታሉ