ጥናት 22
ጥቅሶችን ከነጥቡ ጋር ማገናዘብ
በምታስተምርበት ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ጥቅስ ማንበብህ ብቻ በቂ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ የአገልግሎት አጋሩ ለነበረው ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- ‘የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።’—2 ጢሞ. 2:15
ለጥቅሶች የምንሰጠው ማብራሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ መሆን አለበት ማለት ነው። ከጥቅሱ ውስጥ እኛ ደስ ያለንን ሐሳብ መርጠን በመሰለን መንገድ ከማብራራት ይልቅ በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ማጤን ይጠይቅብናል። ይሖዋ ከእርሱ አፍ የሰሙትን እንደሚናገሩ አስመስለው “ከገዛ ልባቸው የወጣውን ራእይ” የሚናገሩትን ነቢያት በነቢዩ ኤርምያስ አማካኝነት አስጠንቅቋቸዋል። (ኤር. 23:16) ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን ቃል በሰብዓዊ ፍልስፍናዎች እንዳይበርዙ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸዋል:- “የሚያሳፍረውን ስውር ነገር ጥለናልና በተንኰል አንመላለስም የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅልም።” በዘመኑ የነበሩ አጭበርባሪ የወይን ጠጅ ነጋዴዎች ወይን ጠጁ እንዲበዛላቸውና ብዙ ትርፍ እንዲያገኙ ሲሉ ይበርዙት ነበር። እኛ ግን የአምላክን ቃል በሰብዓዊ ፍልስፍና አንበርዝም። ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን” ብሏል።—2 ቆሮ. 2:17፤ 4:2
ለአንድ መሠረታዊ ሥርዓት እንደ ማስረጃ አድርገህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ትጠቅስ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ ለተለያዩ ሁኔታዎች መመሪያ ሆነው የሚያገለግሉ ብዙ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ይዟል። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ይሁን እንጂ ጥቅሱን አላግባብ በመጠቀም አንተ የምትፈልገውን ሐሳብ የሚደግፍ አስመስለህ በተሳሳተ መንገድ እንዳታቀርብ መጠንቀቅ ይኖርብሃል። (መዝ. 91:11, 12፤ ማቴ. 4:5, 6) ጥቅሱን የተጠቀምህበት መንገድ ከይሖዋ ዓላማና ከጠቅላላው የአምላክ ቃል ጋር የሚስማማ መሆን ይኖርበታል።
በተጨማሪም ‘የአምላክን ቃል በትክክል መጠቀም’ የጥቅሱን መንፈስ መረዳት ይጠይቃል። ሌሎችን በቃላት ለመደብደብ የሚያገለግል “በትር” አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን ይቃወሙ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ላሉት አምላክ ለሚፈልጋቸው ዋነኛ ባሕርያት ግዴለሽ የነበሩ ቢሆንም ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ይናገሩ ነበር። (ማቴ. 22:23, 24፤ 23:23, 24) ኢየሱስ የአምላክን ቃል ሲያስተምር የአባቱን ባሕርያት አንጸባርቋል። ለእውነት ካሳየው ቅንዓት በተጨማሪ ለሚያስተምራቸውም ሰዎች ልባዊ ፍቅር ነበረው። እኛም የእርሱን ምሳሌ ለመኮረጅ መጣር ይኖርብናል።—ማቴ. 11:28
ጥቅሱን ከነጥቡ ጋር በትክክል ማገናዘባችንን እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበባችን በዚህ ረገድ ትልቅ ጥቅም አለው። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ ለእምነት ቤተሰቦች መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ በሚጠቀምበት ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ያደረገልንን ዝግጅት ከፍ አድርገን መመልከት ይኖርብናል። (ማቴ. 24:45) ታማኝና ልባም ባሪያ ከሚሰጠው ትምህርት ለመጠቀም የግል ጥናት ማድረግ እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘትና መሳተፍ ያስፈልገናል።
ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለው መጽሐፍ በቋንቋህ የሚገኝ ከሆነና በሚገባ ከተጠቀምህበት በአገልግሎት ላይ ብዙ ጊዜ የምንጠቅሳቸውን በመቶ የሚቆጠሩ ጥቅሶች እንዴት ከነጥቡ ጋር ማገናዘብ እንደምትችል ለማወቅ ይረዳሃል። ልትጠቀምበት ያሰብኸውን ጥቅስ በደንብ የማታውቀው ከሆነ ምርምር ማድረግህ ትሑት መሆንህን ያሳያል። እንዲህ ካደረግህ የእውነትን ቃል በትክክል መጠቀም ትችላለህ።—ምሳሌ 11:2
ጥቅሱ ከነጥቡ ጋር ያለውን ዝምድና ግልጽ ማድረግ። በምታስተምርበት ጊዜ አድማጮችህ እያብራራህ ባለኸው ነጥብና በጠቀስኸው ጥቅስ መካከል ያለው ዝምድና ግልጽ ሆኖ እንዲታያቸው ልታደርግ ይገባል። ጥቅሱን ከማንበብህ በፊት አንድ ጥያቄ አንስተህ ከነበረ የምትጠቅሰው ጥቅስ ላነሳኸው ጥያቄ መልስ የሚሰጠው እንዴት እንደሆነ አድማጮችህ በግልጽ መረዳት መቻል አለባቸው። ጥቅሱን የጠቀስኸው አንድ ሐሳብ ለመደገፍ ብለህ ከሆነ ደግሞ ጥቅሱ ለነጥቡ እንዴት ማስረጃ እንደሚሆን ለተማሪው ግልጽ ማድረግ ይኖርብሃል።
ብዙውን ጊዜ ጥቅሱን ማንበባችን ብቻውን በቂ አይሆንም። ምናልባትም ስናነብ ተፈላጊውን ነጥብ አጉልተን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አብዛኛው ሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ብዙም ትውውቅ እንደሌለውና ጥቅሱን አንዴ ስላነበብክለት ብቻ ነጥቡን ይረዳዋል ማለት እንደማይቻል አትዘንጋ። እየተወያያችሁበት ካለው ሐሳብ ጋር በቀጥታ የሚያያዘውን ነጥብ እንዲያስተውለው አድርግ።
ይህም ብዙውን ጊዜ እየተወያያችሁበት ካለው ነጥብ ጋር በቀጥታ የሚዛመዱትን ቁልፍ ቃላት መለየት ይጠይቅብሃል። ቀላሉ ዘዴ መልእክት አዘል የሆኑትን እነዚህን ቃላት መድገም ነው። ከአንድ ሰው ጋር እየተወያየህ ከሆነ ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ለመለየት የሚረዳ ጥያቄ ልትጠይቀው ትችል ይሆናል። ንግግር በምትሰጥበት ጊዜ ደግሞ አንዳንድ ተናጋሪዎች እንደሚያደርጉት ቁልፍ የሆኑት ቃላት ለየት ብለው እንዲታዩ ለማድረግ ስትል ሌላ ተመሳሳይ ቃል ትጠቀም ወይም ሐሳቡን ደግመህ ትጠቅስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህንን ለማድረግ ከመረጥህ አድማጮች በምትወያዩበት ነጥብና በጥቅሱ አቀማመጥ መካከል ያለው ዝምድና እንዳይድበሰበስባቸው መጠንቀቅ ይኖርብሃል።
ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ለይተህ ካወጣህ መሠረት ጥለሃል ማለት ነው። ከዚህ በኋላ ወደ ቀጣዩ እርምጃ ማለፍ ትችላለህ። ጥቅሱን ያስተዋወቅህበት መንገድ የጠቀስህበትን ዓላማ የሚጠቁም ነውን? ከሆነ አድማጮችህ ከጥቅሱ በሚጠብቁት ሐሳብና ጎላ አድርገህ በገለጽኻቸው ቃላት መካከል ያለውን ዝምድና እንዲገነዘቡ መርዳት ይኖርብሃል። ጥቅሱን ለማስተዋወቅ የተጠቀምህበት ዘዴ የምታነብበትን ምክንያት በግልጽ የሚጠቁም ባይሆንም እንኳ ሌላ ልታደርገው የሚገባ ነገር አለ።
ፈሪሳውያን ከባድ ነው ብለው ያሰቡትን አንድ ጥያቄ ይዘው ወደ ኢየሱስ በመምጣት “ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስ መልስ የሰጠው ዘፍጥረት 2:24ን መሠረት በማድረግ ነበር። በጥቅሱ የተወሰነ ነጥብ ላይ ብቻ እንዳተኮረና ሊያስተላልፍ የፈለገውን መልእክት ግልጽ እንዳደረገላቸው ልብ በል። ኢየሱስ ሁለቱም “አንድ ሥጋ” እንደሆኑ ከተናገረ በኋላ “እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው” በማለት ደምድሟል።—ማቴ. 19:3-6
አንድ ጥቅስ የተጠቀሰበትን ዓላማ ግልጽ ለማድረግ ምን ያህል ማብራሪያ መስጠት ይኖርብሃል? ይህን የሚወስነው አድማጮችህ እነማን ናቸው? ደግሞስ ውይይት እየተደረገበት ያለው ነጥብ ምን ያህል ክብደት የሚሰጠው ነው? የሚለው ጉዳይ ነው። ግብህ ቀላልና ቀጥተኛ ማብራሪያ መስጠት ሊሆን ይገባል።
ጥቅሶችን ተጠቅሞ ማስረዳት። ሥራ 17:2, 3 ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ስላከናወነው አገልግሎት ሲገልጽ ‘ከመጻሕፍት እየጠቀሰ ያስረዳቸው’ እንደነበር ይናገራል። እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ይህን ችሎታ ለማዳበር ሊጥር ይገባል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ከገለጸና እነዚህ ነገሮች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በትንቢት እንደተነገሩ ካስረዳ በኋላ “እኔ የምሰብክላችሁ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ነው” በማለት ሐሳቡን ደምድሟል።
ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ ውስጥ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ጠቅሷል። የሚፈልገውን ነጥብ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ወይም ለማብራራት አንድ ቃል ወይም አጭር ሐረግ በመምረጥ ትርጉሙን ያስረዳ ነበር። (ዕብ. 12:26, 27) ጳውሎስ ዕብራውያን ምዕራፍ 3 ላይ መዝሙር 95:7-11ን ጠቅሶ ጽፏል። ከጥቅሱ ሦስት ነጥቦችን ነጥሎ በማውጣት ሰፋ ያለ ማብራሪያ እንደሰጠ ልብ በል:- (1) ስለ ልብ የተጠቀሰውን ሐሳብ (ዕብ. 3:8-12)፣ (2) “ዛሬ” የሚለውን ቃል (ዕብ. 3:7, 13-15፤ 4:6-11) እንዲሁም (3) “ወደ እረፍቴ አይገቡም” የሚለውን ዓረፍተ ነገር ትርጉም (ዕብ. 3:11, 18, 19፤ 4:1-11) አብራርቷል። የምትጠቅሰውን እያንዳንዱን ጥቅስ ከነጥቡ ጋር ስታዛምድ ይህንን የጳውሎስን ምሳሌ ለመኮረጅ ሞክር።
በሉቃስ 10:25-37 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ታሪክ ኢየሱስ ጥቅሶችን በመጠቀም እንዴት ጥሩ አድርጎ እንዳስረዳ ለማስተዋል ሞክር። ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድ ሰው “መምህር ሆይ፣ የዘላለምን ሕይወት እንድወርስ ምን ላድርግ?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም በመጀመሪያ ሰውዬው ራሱ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት እንዲገልጽ በመጋበዝ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት። ቀጥሎም የአምላክ ቃል የሚያዝዘውን መፈጸም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ ገለጸ። ከዚያ በኋላ ግን ኢየሱስ ሰውዬው ዋናውን ቁም ነገር እንዳልተገነዘበ ሲያስተውል ከጥቅሱ መካከል “ባልንጀራ” የሚለውን ቃል በመውሰድ ሰፊ ማብራሪያ ሰጠው። እንዲሁ የቃሉን ፍቺ ከመንገር ይልቅ ሰውዬው ራሱ ወደ ትክክለኛ መደምደሚያ እንዲደርስ የሚረዳ ምሳሌ ተጠቅሟል።
ኢየሱስ ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ዝምድና ያላቸውን ጥቅሶች ብቻ ይጠቀም እንዳልነበር ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ጥቅሶቹን በማስተዋል ከተነሳው ጥያቄ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ያብራራ ነበር።
ሰዱቃውያን የትንሣኤን ተስፋ ውድቅ ለማድረግ በማሰብ ጥያቄ ባነሱ ጊዜ ኢየሱስ በዘጸአት 3:6 ላይ በሚገኝ አንድ ነጥብ ላይ ብቻ በማተኮር መልስ ሰጥቷል። ይሁንና ጥቅሱን ጠቅሶ ብቻ ዝም አላለም። ከጥቅሱ በመነሳት ትንሣኤ የአምላክ ዓላማ እንደሆነ በግልጽ አስረድቷል።—ማር. 12:24-27
ጥቅሶችን ተጠቅመህ በትክክልና በጥሩ ሁኔታ የማስረዳት ችሎታ ማዳበርህ የተዋጣልህ አስተማሪ እንድትሆን ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል።