ለዕብራውያን የተጻፈ ደብዳቤ
3 ስለሆነም የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች+ የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች፣ በእሱ እንደምናምን በይፋ የምንናገርለትን፣ ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነውን ኢየሱስን አስቡ።+ 2 ሙሴ በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ እንደነበረ ሁሉ+ እሱም ለሾመው ታማኝ ነበር።+ 3 ቤቱን የሠራው፣ ከቤቱ የበለጠ ክብር ስላለው እሱ* ከሙሴ የበለጠ ክብር ይገባዋል።+ 4 እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው። 5 ሙሴም በመላው የአምላክ ቤት ላይ ታማኝ አገልጋይ ነበር። አገልግሎቱም ከጊዜ በኋላ ለሚነገሩ ነገሮች ምሥክር ነው። 6 ክርስቶስ ግን በአምላክ ቤት ላይ የተሾመ ታማኝ ልጅ ነበር።+ እኛም አፋችንን ሞልተን የመናገር ነፃነታችንንና የምንደሰትበትን ተስፋችንን እስከ መጨረሻው አጥብቀን ከያዝን የአምላክ ቤት ነን።+
7 ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦+ “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ 8 በምድረ በዳ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት በፈተና ቀን እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ፤+ 9 በዚያ፣ አባቶቻችሁ ያደረግኩትን ሁሉ ለ40 ዓመት ቢያዩም እኔን በመፈተን ተገዳደሩኝ።+ 10 በዚህም ምክንያት በዚያ ትውልድ በጣም ተንገሸገሽኩ፤ እንዲህም አልኩ፦ ‘ሁልጊዜ ልባቸው ይስታል፤ መንገዴንም ሊያውቁ አልቻሉም።’ 11 በመሆኑም ‘ወደ እረፍቴ አይገቡም’ ብዬ በቁጣዬ ማልኩ።”+
12 ወንድሞች፣ ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ ከእናንተ መካከል በማናችሁም ውስጥ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ፤+ 13 ከዚህ ይልቅ ከእናንተ መካከል አንዳችሁም ኃጢአት ባለው የማታለል ኃይል እንዳትደነድኑ “ዛሬ”+ ተብሎ የሚጠራ ጊዜ እስካለ ድረስ በየዕለቱ እርስ በርሳችሁ ተበረታቱ። 14 የክርስቶስ ተካፋዮች የምንሆነው* በመጀመሪያ የነበረንን ትምክህት እስከ መጨረሻው አጽንተን ከያዝን ብቻ ነውና።+ 15 ይህም “ዛሬ ድምፁን የምትሰሙ ከሆነ እጅግ የሚያስቆጣ ድርጊት በተፈጸመበት ጊዜ እንደሆነው ልባችሁን አታደንድኑ” እንደተባለው ነው።+
16 ድምፁን ቢሰሙም እንኳ እጅግ ያስቆጡት እነማን ነበሩ? ይህን ያደረጉት ሙሴ እየመራቸው ከግብፅ የወጡት ሁሉ አይደሉም?+ 17 ከዚህም ሌላ ለ40 ዓመት አምላክ በእነሱ እንዲንገሸገሽ ያደረጉት እነማን ናቸው?+ እነዚያ ኃጢአት የሠሩትና ሬሳቸው በምድረ በዳ ወድቆ የቀረው አይደሉም?+ 18 ደግሞስ ወደ እረፍቴ አይገቡም ብሎ የማለው ስለ እነማን ነው? እነዚያን ያልታዘዙትን በተመለከተ አይደለም? 19 ስለዚህ ሊገቡ ያልቻሉት እምነት በማጣታቸው የተነሳ እንደሆነ እንረዳለን።+