በምድር ላይ ለዘላለም መኖር—አምላክ የሰጠው ተስፋ
“ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቷል፤ የተገዛው ግን . . . በተስፋ [ነው]።”—ሮም 8:20
1, 2. (ሀ) በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረው ተስፋ ለእኛ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በርካታ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረው ሐሳብ የማይዋጥላቸው ለምንድን ነው?
በቅርብ ጊዜ ውስጥ እርጅናና ሞት እንደሚወገዱ እንዲሁም ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትማር የተሰማህን ደስታ ታስታውስ ይሆናል። (ዮሐ. 17:3፤ ራእይ 21:3, 4) ምናልባትም ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለሌሎች ስታካፍል ቆይተህ ይሆናል። በእርግጥም የምንሰብከው ምሥራች ካሉት በጣም አስፈላጊ ገጽታዎች አንዱ ስለ ዘላለም ሕይወት የሚናገረው ተስፋ ነው። ይህ ተስፋ ስለ ሕይወት ባለን አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከመሆኑም በላይ ሕይወታችንን በምንጠቀምበትና ችግሮችን በምንፈታበት መንገድ ላይ ለውጥ ያመጣል።
2 ብዙውን ጊዜ እንደሚታየው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር ለሚናገረው ተስፋ ትኩረት አይሰጡም። መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ እንደምትሞት የሚያስተምር ቢሆንም አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ ከእነሱ ተለይታ ወደ መንፈሳዊው ዓለም የምትሄድ የማትሞት ነፍስ እንዳለቻቸው የሚገልጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የሌለው ትምህርት ያስተምራሉ። (ሕዝ. 18:20) በመሆኑም በርካታ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ይቻላል የሚለው ሐሳብ አይዋጥላቸውም። እንግዲያው እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው፦ በእርግጥ ይህ ተስፋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ አለው? ከሆነ አምላክ ይህን ተስፋ አስመልክቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰዎች የተናገረው መቼ ነው?
‘ፍጥረት ለከንቱነት የተገዛው በተስፋ ነው’
3. አምላክ ለሰው ልጆች ያለው ዓላማ ከሰው ዘር ታሪክ መጀመሪያ አንስቶ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?
3 ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ የገለጸው የሰው ዘር ታሪክ በጀመረበት ወቅት ላይ ነው። አምላክ፣ አዳም ታዛዥ ከሆነ ለዘላለም መኖር እንደሚችል በግልጽ ነግሮት ነበር። (ዘፍ. 2:9, 17፤ 3:22) የመጀመሪያዎቹ የአዳም ትውልዶች፣ በወቅቱ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የሰው ዘር ፍጽምናውን እንዳጣ ሳያስተውሉ እንዳልቀሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ወደ ኤደን ገነት የሚያስገባው በር የተዘጋ ከመሆኑም ሌላ ሰዎች ያረጁና ይሞቱ ነበር። (ዘፍ. 3:23, 24) የሰዎች ዕድሜም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄድ ጀምሮ ነበር። አዳም የኖረው 930 ዓመት ነው። ከጥፋት ውኃው የተረፈው ሴም 600 ዓመት ብቻ የኖረ ሲሆን ልጁ አርፋክስድ ደግሞ 438 ዓመት ኖሯል። የአብርሃም አባት ታራ የኖረው 205 ዓመት ነበር። አብርሃም ለ175 ዓመት፣ ይስሐቅ ለ180 እንዲሁም ያዕቆብ ለ147 ዓመት ያህል ኖረዋል። (ዘፍ. 5:5፤ 11:10-13, 32፤ 25:7፤ 35:28፤ 47:28) የሰዎች ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄዱ ብዙዎች ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን እንዳጡ እንዲገነዘቡ አድርጓቸው መሆን አለበት። ታዲያ ይህን ተስፋቸውን መልሰው እንደሚያገኙ ለማመን የሚያስችላቸው በቂ ምክንያት ይኖራቸው ይሆን?
4. በጥንት ዘመን የነበሩት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች አዳም ያጣቸውን በረከቶች አምላክ መልሶ እንደሚያመጣ ለማመን የሚያስችል ምን ምክንያት ነበራቸው?
4 የአምላክ ቃል ‘[ሰብዓዊው] ፍጥረት ለከንቱነት የተገዛው በተስፋ ነው’ ይላል። (ሮም 8:20) ይህ ተስፋ ምንድን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው የመጀመሪያው ትንቢት ‘የእባቡን ራስ ስለሚቀጠቅጥ’ አንድ ‘ዘር’ ይናገራል። (ዘፍጥረት 3:1-5, 15ን አንብብ።) ዘሩን በሚመለከት የተነገረው ይህ ቃል፣ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ‘አምላክ ለሰው ልጆች ያለውን ዓላማ አይለውጥም’ የሚል ተስፋ እንዲያድርባቸው አድርጓል። ይህ ትንቢት፣ እንደ አቤልና ኖኅ ያሉ ሰዎች አዳም ያጣቸውን በረከቶች አምላክ መልሶ እንደሚያመጣ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዲኖራቸው አድርጓል። እነዚህ ሰዎች ‘የዘሩ ተረከዝ መቀጥቀጥ’ ደም ማፍሰስን እንደሚጨምር ሳይገነዘቡ አልቀሩም።—ዘፍ. 4:4፤ 8:20፤ ዕብ. 11:4
5. አብርሃም በትንሣኤ ላይ እምነት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?
5 እስቲ የአብርሃምን ሁኔታ እንመልከት። አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ‘አንድያ ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ደርሶ’ ነበር። (ዕብ. 11:17) እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነው ለምንድን ነው? (ዕብራውያን 11:19ን አንብብ።) በትንሣኤ ላይ እምነት ስለነበረው ነው! አብርሃም በትንሣኤ ለማመን የሚያስችል መሠረት ነበረው። ደግሞም ይሖዋ፣ አብርሃም የመውለድ ችሎታውን መልሶ እንዲያገኝ በማድረግ እሱም ሆነ ሚስቱ ሣራ በስተ እርጅናቸው ልጅ እንዲወልዱ አድርጓል። (ዘፍ. 18:10-14፤ 21:1-3፤ ሮም 4:19-21) በተጨማሪም ይሖዋ ‘ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ነው’ በማለት ለአብርሃም ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍ. 21:12) በመሆኑም አብርሃም፣ አምላክ ይስሐቅን ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኛ እንዲሆን የሚያስችሉት አጥጋቢ ምክንያቶች ነበሩት።
6, 7. (ሀ) ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ለአብርሃም የገባለት ቃል ኪዳን ለሰው ዘሮች ተስፋ የሚፈነጥቀው እንዴት ነው?
6 አብርሃም ታላቅ እምነት እንዳለው በማሳየቱ ይሖዋ የአብርሃምን ልጅ ወይም “ዘር” አስመልክቶ ከእሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። (ዘፍጥረት 22:18ን አንብብ።) ከጊዜ በኋላ ‘የዘሩ’ ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ታውቋል። (ገላ. 3:16) ይሖዋ ለአብርሃም ‘ዘሩን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም’ እንደሚያበዛው ነግሮታል፤ ይህ ደግሞ አብርሃም ‘የዘሩን’ ብዛት እንደማያውቅ ያሳያል። (ዘፍ. 22:17) ይሁንና ከጊዜ በኋላ ‘የዘሩ’ ቁጥር ታወቀ። ኢየሱስ ክርስቶስና በመንግሥቱ አብረውት የሚገዙት 144,000 ሰዎች የዚህ “ዘር” ክፍል መሆናቸው ግልጽ ሆነ። (ገላ. 3:29፤ ራእይ 7:4፤ 14:1) ‘የምድር ሕዝቦች ሁሉ የሚባረኩት’ በዚህ መሲሐዊ መንግሥት አማካኝነት ነው።
7 አብርሃም፣ ይሖዋ ከእሱ ጋር የገባው ቃል ኪዳን ምን ትርጉም እንዳለውና ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በተሟላ መልኩ መረዳት እንደማይችል ግልጽ ነው። ያም ሆኖ አብርሃም “እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዕብ. 11:10) ይህች ከተማ የአምላክን መንግሥት ታመለክታለች። አብርሃም ይህ መንግሥት የሚያስገኘውን በረከት ለመውረስ እንደገና በሕይወት መኖር አለበት። በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚችለው ደግሞ በትንሣኤ አማካኝነት ነው። ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉትም ሆኑ ከሞት የሚነሱት ሰዎችም የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።—ራእይ 7:9, 14፤ 20:12-14
“መንፈስ ገፋፍቶኛል”
8, 9. የኢዮብ መጽሐፍ በአንድ ሰው ላይ ስለ ደረሰ መከራ በመተረክ ብቻ የተወሰነ አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?
8 የአብርሃም የልጅ ልጅ የሆነው ዮሴፍና ነቢዩ ሙሴ በኖሩባቸው ዘመናት መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ኢዮብ የተባለ ሰው በምድር ላይ ይኖር ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የኢዮብን መጽሐፍ የጻፈው ሙሴ ሳይሆን አይቀርም፤ ይህ መጽሐፍ ይሖዋ በኢዮብ ላይ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ለምን እንደሆነና ኢዮብ በመጨረሻ ምን በረከት እንዳገኘ ይተርክልናል። ይሁንና የኢዮብ መጽሐፍ በአንድ ሰው ላይ ስለ ደረሰ መከራ በመተረክ ብቻ ሳይወሰን ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታትን ሁሉ ስለሚመለከቱ ጥያቄዎችም ተናግሯል። መጽሐፉ፣ የይሖዋ አገዛዝ ጽድቅ የሰፈነበት መሆኑን እንድናስተውል የሚረዳን ሲሆን በምድር ላይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ንጹሕ አቋማቸውን የመጠበቃቸውና ሕይወት የማግኘታቸው ጉዳይ በኤደን ከተነሳው ጥያቄ ጋር የተያያዘ መሆኑን እንድንረዳ ያስችለናል። ኢዮብ፣ የተነሳው ጥያቄ ምን እንደሆነ ባይገነዘብም ሦስቱ ጓደኞቹ ንጹሕ አቋሙን እንዳልጠበቀ ሊያሳምኑት በሞከሩ ጊዜ አልተቀበላቸውም። (ኢዮብ 27:5) ይህ ሁኔታ እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከመሆኑም በላይ ንጹሕ አቋማችንን መጠበቅና የይሖዋን ሉዓላዊነት መደገፍ የምንችል መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል።
9 ወደ ኢዮብ የመጡት ሦስቱ አጽናኝ ተብዬዎች ተናግረው ከጨረሱ በኋላ “የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ” መናገር ጀመረ። ኤሊሁ፣ እንዲናገር ያነሳሳው ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጽ “የምናገረው ሞልቶኛልና፤ በውስጤ ያለውም መንፈስ ገፋፍቶኛል” ብሏል። (ኢዮብ 32:5, 6, 18) ኤሊሁ በመንፈስ ተመርቶ የተናገረው ሐሳብ የኢዮብ መከራ ባበቃ ጊዜ ፍጻሜውን ያገኘ ቢሆንም በውስጡ የያዘው ቁም ነገር ለሌሎች ሰዎችም ትልቅ ትርጉም አለው። የኤሊሁ ንግግር ንጹሕ አቋማቸውን ለሚጠብቁ ሁሉ ትልቅ ተስፋ ይዟል።
10. ይሖዋ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የበለጠ ተፈጻሚነት ሊኖረው የሚችል መልእክት እንዲናገሩ ግለሰቦችን ያነሳሳበት ጊዜ እንዳለ የሚያሳይ ምን ምሳሌ አለ?
10 ይሖዋ፣ በሰው ልጆች ሁሉ ላይ የበለጠ ተፈጻሚነት ሊኖረው የሚችል መልእክት እንዲናገሩ ግለሰቦችን ያነሳሳበት ጊዜ አለ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልም ካየው የረጅሙ ዛፍ መቆረጥ ጋር በተያያዘ ነቢዩ ዳንኤል የተናገረው ትንቢት ይህ እውነት መሆኑን ያሳያል። (ዳን. 4:10-27) ይህ ሕልም ከናቡከደነፆር ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ቢያገኝም ከዚያ የበለጠ ተፈጻሚነት እንዳለው የሚጠቁም ነገር አለ። የአምላክ ሉዓላዊ ገዥነት መገለጫ የሆነውና በዳዊት ሥርወ መንግሥት ይወከል የነበረው የአምላክ መንግሥት ከ2,520 ዓመታት በኋላ (ከ607 ዓ.ዓ. አንስቶ ሲቆጠር ማለት ነው) እንደገና እንደሚገለጥ ያመለክታል።a ኢየሱስ ክርስቶስ በ1914 በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመ ጊዜ አምላክ በምድር ላይ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑ እንደገና ተረጋግጧል። የአምላክ መንግሥት ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች የተዘረጋውን ተስፋ በቅርቡ እውን የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ እስቲ ለማሰብ ሞክር!
“ወደ ጉድጓድ ከመውረድ አድነው!”
11. ኤሊሁ የተናገረው ሐሳብ ስለ አምላክ ምን ይጠቁመናል?
11 ኤሊሁ፣ ለኢዮብ መልስ በሰጠበት ጊዜ ‘ለሰው ቅን የሆነውን ነገር ሊነግረው ስለሚችል ከሺዎች መካከል ስለተገኘ አንድ መልእክተኛ ይኸውም አንድ ቃል አቀባይ’ ተናግሮ ነበር። ይህ መልእክተኛ ‘አምላክ በዚያ ሰው ደስ ይሰኝ ዘንድ ልመና ቢያቀርብ’ ምን መልስ ያገኝ ይሆን? ኤሊሁ እንዲህ ብሏል፦ “ከዚያም እሱ [አምላክ] ሞገስን ያሳየዋል፤ እንዲህም ይላል፦ ‘ቤዛ ስላገኘሁ ወደ ጉድጓድ ከመውረድ አድነው! ሥጋው ከልጅ ሥጋ የበለጠ ይለምልም፤ ብርቱ ወደነበረበት የወጣትነት ዘመኑም ይመለስ።’” (ኢዮብ 33:23-26 NW) ይህ አባባል፣ አምላክ ንስሐ በሚገቡ የሰው ልጆች ምትክ የሚቀርብ “ቤዛ” ወይም የኃጢአት መሸፈኛ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑን ያሳያል።—ኢዮብ 33:24
12. ኤሊሁ የተናገረው ሐሳብ ለሰው ዘር በሙሉ ምን ተስፋ ይዟል?
12 ነቢያት የጻፉትን እያንዳንዱን ነገር በተሟላ ሁኔታ እንዳልተረዱት ሁሉ ኤሊሁም የቤዛውን ትርጉምና አስፈላጊነት ሙሉ በሙሉ አልተረዳው ይሆናል። (ዳን. 12:8፤ 1 ጴጥ. 1:10-12) ያም ሆኖ ኤሊሁ የተናገረው ሐሳብ፣ አንድ ቀን አምላክ ቤዛ ተቀብሎ እርጅና ከሚያስከትለው መከራ ብሎም ከሞት የሰው ልጆችን እንደሚገላግላቸው ተስፋ ይሰጣል። የኤሊሁ ንግግር አስደናቂ ስለሆነው የዘላለም ሕይወት ተስፋ ይገልጻል። የኢዮብ መጽሐፍ ወደፊት ትንሣኤ እንደሚኖር ጭምር ይናገራል።—ኢዮብ 14:14, 15
13. ኤሊሁ የተናገረው ሐሳብ ለክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው?
13 ኤሊሁ የተናገረው ሐሳብ፣ ይህ ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት እንደሚተርፉ ተስፋ ለሚያደርጉ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችም ትልቅ ትርጉም አለው። ከጥፋቱ ከሚተርፉት መካከል የሚገኙት አረጋውያን ወደ ወጣትነታቸው ዘመን ይመለሳሉ። (ራእይ 7:9, 10, 14-17) ከዚህም በላይ ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮች፣ ወደፊት ከሞት የሚነሱ ሰዎች ወደ ወጣትነት ዘመናቸው ሲመለሱ የመመልከት አጋጣሚ እንዳላቸው ማወቃቸው ያስደስታቸዋል። እርግጥ ነው፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሰማይ የማይሞት ሕይወት ማግኘታቸውም ሆነ የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” በምድር ላይ ለዘላለም መኖራቸው የተመካው በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳላቸው በተግባር በማሳየታቸው ላይ ነው።—ዮሐ. 10:16፤ ሮም 6:23
ሞት ከምድር ይወገዳል
14. እስራኤላውያን የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ ከተፈለገ የሙሴ ሕግ ካመጣባቸው ኩነኔ ነፃ የሚያወጣቸው ነገር ያስፈልጋቸው እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
14 የአብርሃም ዘሮች ከአምላክ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ቃል ኪዳን በገቡበት ወቅት ራሳቸውን የቻሉ አንድ ብሔር ሆነዋል። ይሖዋ ሕጉን በሰጣቸው ጊዜ “ሥርዐቴንና ሕጌን ጠብቁ፤ እነዚህን የሚጠብቅ በሕይወት ይኖርባቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ዘሌ. 18:5) ይሁን እንጂ እስራኤላውያን ፍጹም ከሆኑት የሕጉ መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር ስላልቻሉ ሕጉ ይኮንናቸው የነበረ ሲሆን ከዚህ ኩነኔ ነፃ የሚያወጣቸው ነገር ያስፈልጋቸው ነበር።—ገላ. 3:13
15. ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ የጻፈው ሐሳብ ወደፊት ምን በረከት እንደሚመጣ ያሳያል?
15 ከሙሴ በኋላም ቢሆን ይሖዋ፣ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ ዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲጽፉ በመንፈሱ መርቷቸዋል። (መዝ. 21:4፤ 37:29) ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙራዊው ዳዊት በጽዮን ያሉ የይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎች ያላቸውን አንድነት አስመልክቶ የጻፈውን መዝሙር የደመደመው እንዲህ በማለት ነበር፦ “በዚያ እግዚአብሔር በረከቱን፣ ሕይወትንም እስከ ዘላለም አዞአል።”—መዝ. 133:3
16. ይሖዋ ወደፊት ‘በመላው ምድር’ ላይ የሚያደርገውን ነገር በተመለከተ በኢሳይያስ በኩል ምን በማለት ቃል ገብቷል?
16 ይሖዋ፣ ኢሳይያስ በምድር ላይ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገር ትንቢት እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል። (ኢሳይያስ 25:7, 8ን በNW አንብብ።b) ኃጢአትና ሞት አየር እንደሚያሳጣ “መሸፈኛ” ወይም ብርድ ልብስ የሰውን ልጅ ጀቡነውታል። ይሖዋ ኃጢአትና ሞት እንደሚዋጡ ወይም “ከመላው ምድር” እንደሚወገዱ ለሕዝቦቹ አረጋግጦላቸዋል።
17. ትንቢት የተነገረለት መሲሕ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ለመክፈት ምን ሚና ይጫወታል?
17 ከዚህም በተጨማሪ ወደ ምድረ በዳ ከሚለቀቀው ፍየል ጋር በተያያዘ በሙሴ ሕግ ውስጥ በግልጽ የሰፈረውን መመሪያ እስቲ እንመልከት። በዓመት አንዴ በስርየት ቀን ላይ ሊቀ ካህናቱ ‘ሁለት እጆቹን በሕይወት ባለው ፍየል ራስ ላይ ይጭናል፤ ከዚያም በላዩ ላይ የእስራኤላውያንን ክፋት በሙሉ ይናዘዝበታል፤ እነዚህንም በፍየሉ ራስ ላይ ይጭናል፤ ፍየሉም ኀጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል።’ (ዘሌ. 16:7-10, 21, 22) ኢሳይያስ፣ የብዙዎችን “ደዌ፣” ‘ሕመም’ እና “ኀጢአት” በመሸከም ከፍየሉ ጋር የሚመሳሰል ሚና የሚጫወት መሲሕ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሯል፤ መሲሑ ይህን በማድረግ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ይከፍታል።—ኢሳይያስ 53:4-6, 12ን አንብብ።
18, 19. በኢሳይያስ 26:19 እና በዳንኤል 12:13 ላይ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው ተስፋ የትኛው ነው?
18 ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ለእስራኤል ብሔር እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ በድናቸውም ይነሣል። እናንት በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣ ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ። ጠልህ እንደ ንጋት ጠል ነው፤ ምድር ሙታንን ትወልዳለች።” (ኢሳ. 26:19) የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት፣ የሞቱ ሰዎች ወደፊት ትንሣኤ እንደሚያገኙና በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ በግልጽ ይናገራሉ። ለምሳሌ ዳንኤል ወደ 100 ዓመት በተጠጋበት ጊዜ ይሖዋ “ታርፋለህ፤ በቀኖቹ መጨረሻም ተነሥተህ የተመደበልህን ርስት ትቀበላለህ” በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶታል።—ዳን. 12:13
19 ማርታ የሞተውን ወንድሟን አስመልክታ “በመጨረሻው ቀን፣ በትንሣኤ እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” በማለት ለኢየሱስ ልትመልስለት የቻለችው በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት ስለነበራት ነው። (ዮሐ. 11:24) ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶችና ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ተመርተው የጻፏቸው መጻሕፍት በትንሣኤ ተስፋ ላይ ለውጥ መደረጉን የሚያሳዩ ናቸው? ይሖዋ ለሰዎች የሰጠው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እስከ አሁን ድረስ አልተቀየረም? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
b ኢሳይያስ 25:7, 8 (NW)፦ “በዚህም ተራራ ላይ ሕዝቦችን ሁሉ የሸፈነውን መሸፈኛ እንዲሁም በብሔራት ሁሉ ላይ የተዘረጋውን ጨርቅ በእርግጥ ያስወግዳል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፤ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ ከፊት ሁሉ እንባን ይጠርጋል። በሕዝቡ ላይ የደረሰውንም ነቀፋ ከመላው ምድር ያስወግዳል፤ ምክንያቱም ይህን የተናገረው ይሖዋ ራሱ ነው።”
ልታብራራ ትችላለህ?
• ሰብዓዊው ፍጥረት ‘ለከንቱነት የተገዛው’ በየትኛው ተስፋ ነው?
• አብርሃም በትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው?
• ኤሊሁ ለኢዮብ የተናገረው ሐሳብ ለሰው ልጆች ምን ተስፋ ይዟል?
• የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትንሣኤ እንዲሁም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዳለ በአጽንኦት የገለጹት እንዴት ነው?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤሊሁ ለኢዮብ የተናገረው ሐሳብ፣ የሰው ልጆች እርጅና ከሚያስከትለው መከራ ብሎም ከሞት የሚገላገሉበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዳንኤል ‘በቀኖቹ መጨረሻ ላይ ተነስቶ የተመደበለትን ርስት እንደሚቀበል’ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል