በዚህ የመጨረሻ ቀን “የልብ ንጽሕናን” ጠብቆ መኖር
ቪቶርዮ ሜሶሪ የተባለ አንድ የካቶሊክ ጋዜጠኛ በቅርቡ በጣሊያን ውስጥ በቤተ ክርስቲያን የተፈጸመውን አሳፋሪ የፆታ ድርጊት አስመልክቶ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ጊዜ ድንግልና በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ማንም ሊክደው የማይችል ሐቅ ሆኗል። . . . ሆኖም ቀሳውስት ድንግል ሆነው መቆየት አለባቸው የሚለውን ሕግ መሰረዙ ብቻ መፍትሔ አያመጣም፤ ምክንያቱም 80 በመቶ የሚሆነው ክስ የተያያዘው ግብረ ሰዶም ከመፈጸም ጋር ሲሆን ቄሶቹ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የፆታ ድርጊት በመፈጸም ይኸውም አዋቂም ሆነ ትንንሽ ወንዶችን በፆታ በማስነወር ይከሰሳሉ።”—ላ ስታምፓ
ክፋት መስፋፋቱ በዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ውስጥ እንደምንገኝ ያለምንም ጥርጥር ያመለክታል። (2 ጢሞ. 3:1-5) የዜና ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በዘመናችን የሚታየው የሥነ ምግባር ውድቀት በተራው ሕዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን የአምላክ አገልጋይ ነን በሚሉ ሰዎች ላይም መጥፎ ተጽዕኖ አሳድሯል። የእነዚህ ሰዎች የተበላሸና ንጹሕ ያልሆነ ልብ ነውረኛ የሆኑ ተግባራትን ወደ መፈጸም መርቷቸዋል። (ኤፌ. 2:2) ኢየሱስ “ከልብ ክፉ ሐሳብ፣ ግድያ፣ ምንዝር፣ ዝሙት፣ ሌብነት፣ በሐሰት መመስከርና ስድብ ይወጣሉ” በማለት ማስጠንቀቁ የተገባ ነው። (ማቴ. 15:19) ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹ “የልብ ንጽሕናን” እንዲወዱ ይፈልጋል። (ምሳሌ 22:11) ታዲያ በዚህ አስቸጋሪ ዘመን አንድ ክርስቲያን ‘የልቡን ንጽሕና’ መጠበቅ የሚችለው እንዴት ነው?
“የልብ ንጽሕናን” መጠበቅ ሲባል ምን ማለት ነው?
ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ልብ” ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ልብ የሚለው ቃል “የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት” እንዲሁም “የአንድን ሰው ሥነ ምግባራዊ አቋም የሚወስነው ሃይማኖታዊ ዝንባሌ የተተከለበትን ይኸውም አምላክ ልዩ ትኩረት የሚያደርግበትን ክፍል” ያመለክታል። ልብ ውስጣዊ ማንነታችንን ያመለክታል። ከላይ የተገለጸው ማመሳከሪያ ጽሑፍ ጎላ አድርጎ እንደተናገረው ይሖዋ የሚመረምረውና አገልጋዮቹ ካሏቸው ነገሮች ውስጥ የሚያደንቀው ይህን ነገር ነው።—1 ጴጥ. 3:4
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ንጹሕ” የሚለው ቃል በአካላዊ ሁኔታ ንጹሕ መሆንን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይሁንና ቃሉ በሥነ ምግባርም ሆነ በሃይማኖት ረገድ ያልተበከለን ይኸውም ያልተበረዘን፣ ያልቆሸሸን ወይም ያልጎደፈን ነገር ለማመልከትም ያገለግላል። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ልባቸው ንጹሕ የሆነ ደስተኞች ናቸው” በማለት ተናግሯል። ኢየሱስ እዚህ ላይ በምሳሌያዊ አነጋገር ውስጣቸው ንጹሕ ስለሆኑ ሰዎች እየተናገረ ነበር። (ማቴ. 5:8) እነዚህ ሰዎች ፍቅራቸው፣ ምኞታቸውና አመለካከታቸው ንጹሕ ነው። እንዲሁም ይሖዋን ለእሱ ባላቸው ፍቅርና አድናቆት ተነሳስተው ያላንዳች ግብዝነት በሙሉ ልብ ይወዱታል። (ሉቃስ 10:27) አንተም በዚህ ረገድ ንጹሕ መሆን እንደምትፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም።
“የልብ ንጽሕናን” ጠብቆ መኖር ቀላል አይደለም
አንድ የይሖዋ አገልጋይ “እጆቹ” ብቻ ሳይሆኑ “ልቡም ንጹሕ” ሊሆን ይገባል። (መዝ. 24:3, 4 የ1954 ትርጉም) ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ለአምላክ አገልጋዮች “የልብ ንጽሕናን” ጠብቆ መኖር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተፈታታኝ ሆኗል። ሰይጣን፣ እሱ የሚገዛው ዓለምና ፍጹም ያልሆነው ሥጋችን እኛን ከይሖዋ ለማራቅ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጉብናል። በመሆኑም ይህን ተጽዕኖ ለመቋቋም “የልብ ንጽሕናን” መውደዳችን እንዲሁም የልባችንን ንጽሕና ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረጋችን ከአደጋ የሚጠብቀን ከመሆኑም ሌላ የአምላክ ወዳጅ ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። ታዲያ የልባችንን ንጽሕና ጠብቀን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
በዕብራውያን 3:12 ላይ እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ እናገኛለን፦ “ወንድሞች፣ ሕያው ከሆነው አምላክ በመራቅ እምነት የለሽ የሆነ ክፉ ልብ ከእናንተ መካከል በማናችሁም ውስጥ እንዳያቆጠቁጥ ተጠንቀቁ።” ‘እምነት የለሽ ልብ’ ካዳበርን ‘የልባችንን ንጽሕና’ ጠብቀን መኖር አንችልም። ታዲያ ሰይጣን ዲያብሎስ በአምላክ ላይ ያለን እምነት እንዲዳከም ለማድረግ የትኞቹን አስተሳሰቦች ያስፋፋል? ከእነዚህ አስተሳሰቦች መካከል የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ፣ የሥነ ምግባር ደንብና ሃይማኖታዊ እውነት እንደየሰዉ ይለያያል የሚለው አመለካከት እንዲሁም ቅዱሳን መጻሕፍት በመለኮታዊ መሪነት መጻፋቸውን መጠራጠር ይገኙበታል። እንዲህ ያሉ አደገኛ አስተሳሰቦች ተጽዕኖ እንዲያሳድሩብን መፍቀድ የለብንም። (ቆላ. 2:8) ከእነዚህ ጥቃቶች ራሳችንን ለመጠበቅ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ በጥልቀት ማሰላሰላችን አስፈላጊ ነው። የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት መቅሰማችን ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና ይሖዋ ሰዎችን ለሚይዝበት መንገድ ያለንን አድናቆት ያቀጣጥልልናል። ከተሳሳቱ አመለካከቶች መራቅ የምንፈልግ እንዲሁም በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ምንጊዜም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል የምንሻ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅርና አድናቆት ማዳበራችን የግድ አስፈላጊ ነው፤ ይህ ደግሞ ምንጊዜም የልባችንን ንጽሕና ለመጠበቅ ያስችለናል።—1 ጢሞ. 1:3-5
የሥጋ ምኞት ሲታገለን
‘የልባችንን ንጽሕና’ ጠብቀን ለመኖር የምናደርገውን ጥረት አስቸጋሪ ሊያደርግብን የሚችለው ሌላው ነገር ከሥጋ ምኞትና ቁሳዊ ሀብት ከማካበት ፍላጎት ጋር የተያያዘ ነው። (1 ዮሐ. 2:15, 16) የገንዘብ ፍቅር ወይም ቁሳዊ ሀብትና ንብረት የማካበት አባዜ የአንድ ክርስቲያን ልብ እንዲበላሽና ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚቃረኑ ነገሮችን እንዲያደርግ ሊገፋፋው ይችላል። አንዳንዶች በሥራ ቦታ ታማኝነታቸውን አጉድለዋል፣ አጭበርብረዋል ሌላው ቀርቶ የሌሎችን ገንዘብ ወይም ንብረት ሰርቀዋል።—1 ጢሞ. 6:9, 10
በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋን ላለማሳዘን ጤናማ ፍርሃት በማዳበር፣ ፍትሕን በመውደድና ጥሩ ሕሊና ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ “የልብ ንጽሕናን” እንደምንወድ ማሳየት እንችላለን። እንዲህ ያለው ፍቅር ምንጊዜም “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር” ይገፋፋናል። (ዕብ. 13:18) ሐቀኞች በመሆን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጋችን ደግሞ ግሩም ምሥክርነት ይሰጣል። በአንድ የሕዝብ ማመላለሻ ድርጅት ውስጥ በሹፌርነት የሚሠራ ኤሚልዮ የተባለ አንድ ጣሊያናዊ የይሖዋ ምሥክር 680 የአሜሪካ ዶላር የያዘ አንድ የገንዘብ ቦርሳ ወድቆ ያገኛል። ኤሚልዮ ቦርሳውን ለአለቃው በመስጠቱ የሥራ ባልደረቦቹ በጣም ተገረሙ፤ አለቃውም ቦርሳውን ለባለቤቱ መለሰ። አንዳንድ የኤሚልዮ የሥራ ባልደረቦች በባሕርይው በመደነቃቸው ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት ያደረባቸው ከመሆኑም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ከሁለት ቤተሰቦች ውስጥ ሰባት ሰዎች እውነትን ተቀበሉ። በእርግጥም በንጹሕ ልብ ተገፋፍተን ሐቀኛ መሆናችን ሰዎች አምላክን እንዲያወድሱ ሊያነሳሳቸው ይችላል።—ቲቶ 2:10
የአንድ ክርስቲያን ልብ ንጹሕ እንዳይሆን መጥፎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ነገሮች መካከል ስለ ፆታ የተዛባ አመለካከት መያዝ ይገኝበታል። ብዙ ሰዎች ከጋብቻ በፊት፣ ከትዳር ጓደኛ ውጪ እንዲሁም ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማቸዋል፤ እንዲህ ያለው አመለካከት የአንድን ክርስቲያን ልብ ሊበክል ይችላል። አንድ ሰው ለስሜቱ ተሸንፎ የፆታ ብልግና ቢፈጽም ሌሎች ኃጢአቱን እንዳያውቁበት ለማድረግ ሲል ሁለት ዓይነት ኑሮ ሊኖር ይችላል። እንዲህ የሚያደርግ ሰው ‘የልብ ንጽሕና’ እንደሌለው ግልጽ ነው።
ጋብሪኤሌ የተጠመቀው የ15 ዓመት ልጅ እያለ ሲሆን ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው አቅኚ ሆነ። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር ገጥሞ በምሽት ጭፈራ ቤቶች ጊዜውን ማሳለፍ ጀመረ። (መዝ. 26:4) ጋብሪኤሌ በዚህ መንገድ ሥነ ምግባር የጎደለውና ግብዝነት የሚንጸባረቅበት አኗኗር መከተል ጀመረ፤ በመሆኑም ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ። ይህ የይሖዋ የተግሣጽ ዝግጅት ስለ ሁኔታው ቆም ብሎ እንዲያስብ አደረገው። ጋብሪኤሌ እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ ቀደም በቁም ነገር የማላያቸውን ነገሮች በሙሉ ማድረግ ጀመርኩ። ይሖዋ የሚለውን ነገር ለመስማት ጥረት እያደረግሁ መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ቲኦክራሲያዊ ጽሑፎችን በጥንቃቄ ማጥናት ጀመርኩ። የግል ጥናት ምን ያህል እንደሚክስና እንደሚያስደስት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና ከልብ የመነጨ ጸሎት ምን ያህል ብርታት እንደሚሰጥ መመልከት ችያለሁ።” እነዚህ ነገሮች ጋብሪኤሌ ይከተል የነበረውን መጥፎ ሥነ ምግባር እንዲተውና ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንደገና እንዲያጠናክር ረድተውታል።
በአሁኑ ጊዜ ጋብሪኤሌ ከሚስቱ ጋር እንደገና አቅኚ ሆኖ እያገለገለ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸውን ጽሑፎች ማጥናት አንድ ሰው ልቡ ንጹሕ እንዲሆንና ከመጥፎ ሥነ ምግባር እንዲርቅ እንደሚረዳው የጋብሪኤሌ ሁኔታ ያሳያል።—ማቴ. 24:45፤ መዝ. 143:10
በመከራ ወቅት “የልብ ንጽሕናን” ጠብቆ መኖር
አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ተቃዋሚዎች፣ የኢኮኖሚ ችግርና ከባድ ሕመም በሚያሳድሩት ጫና የተነሳ ተስፋ ቆርጠዋል። እንዲህ ያሉ ነገሮች በልባቸው ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳደሩበት ጊዜም አለ። ንጉሥ ዳዊትም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ስለነበር “መንፈሴ በውስጤ ዝላለች፤ ልቤም በውስጤ ደንግጦአል” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 143:4) ዳዊት እንዲህ ያለውን ችግር እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስላደረገላቸው ነገሮችና እሱንም ቢሆን እንዴት እንዳዳነው መለስ ብሎ ማሰቡ ነበር። ይሖዋ ለታላቅ ስሙ ሲል ባደረጋቸው ነገሮች ላይ አሰላስሏል። ዳዊት ስለ አምላክ ሥራዎችም ዘወትር ያሰላስል ነበር። (መዝ. 143:5) በተመሳሳይም እኛ ስለ ፈጣሪያችንና ስላደረጋቸው ነገሮች በሙሉ እንዲሁም ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር ማሰላሰላችን መከራ በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ የልባችንን ንጽሕና እንድንጠብቅ ይረዳናል።
ሰዎች ሲበድሉን ወይም እንደበደሉን ሲሰማን ልንመረር እንችላለን። ዘወትር ነገሩን የምናወጣና የምናወርድ ከሆነ ለወንድሞቻችን አሉታዊ ስሜት ሊያድርብን ይችላል። ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ልናቆም፣ ራሳችንን ልናገልና ሌሎችን ችላ ልንል እንችላለን። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ‘የልባችንን ንጽሕና’ ለመጠበቅ ካለን ፍላጎት ጋር ይስማማል? የልብ ንጽሕናን መጠበቅ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት እንዲሁም አለመግባባት ሲፈጠር የምንወስደውን እርምጃ እንደሚጨምር ግልጽ ነው።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸና በሥነ ምግባር እያዘቀጠ በመጣው በዚህ ዓለም ውስጥ እኛ እውነተኛ ክርስቲያኖች “የልብ ንጽሕናን” ስለምንወድ በቀላሉ ተለይተን እንታወቃለን። የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን ውስጣዊ ሰላም ያስገኝልናል፤ ይህ ደግሞ በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከሁሉም በላይ ደግሞ “ልባቸው ንጹሕ” የሆኑትን ሰዎች ከሚወደው ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንመሠርታለን። (መዝ. 73:1) አዎን፣ ኢየሱስ “የልብ ንጽሕናን” የሚወዱ ሰዎች አምላክ ለእነሱ እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ ‘አምላክን እንደሚያዩ’ ቃል ስለገባ እኛም ደስተኛ ይሆናሉ ከተባሉት ሰዎች መካከል ልንቆጠር እንችላለን።—ማቴ. 5:8