ምዕራፍ 11
‘ጋብቻ ክቡር ይሁን’
‘በልጅነት ሚስትህ ደስ ይበልህ።’—ምሳሌ 5:18
1, 2. የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን? ለምንስ?
አግብተሃል? ያገባህ ከሆንክ በትዳር ሕይወትህ ደስተኛ ነህ? ወይስ ከባድ ችግር እያጋጠመህ ነው? ከትዳር ጓደኛህ ጋር እየተራራቃችሁ እንደሆነ ይሰማሃል? በትዳር ሕይወትህ ደስታ አጥተህ እንዲሁ ችለህ ለመኖር እየታገልክ ነው? ከሆነ በአንድ ወቅት የነበራችሁ ሞቅ ያለ ፍቅር በመቀዝቀዙ እንደምታዝን የታወቀ ነው። ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ጋብቻህ የምትወደውን አምላክህን ይሖዋን የሚያስከብር እንዲሆን እንደምትፈልግ ግልጽ ነው። በመሆኑም አሁን ያለህበት ሁኔታ ሳያሳስብህና ሳያስጨንቅህ አይቀርም። ይሁን እንጂ ሁኔታህ ጨርሶ ተስፋ እንደሌለው አድርገህ አታስብ።
2 በአንድ ወቅት ትዳራቸው ደስታ ርቆት የነበረ አሁን ግን ጥሩ የትዳር ሕይወት ያላቸው ክርስቲያን ባልና ሚስቶች አሉ። እነዚህ ባልና ሚስቶች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር የሚረዳቸውን ዘዴ አግኝተዋል። አንተም ብትሆን በትዳር ሕይወትህ የበለጠ ደስታና እርካታ ማግኘት ትችላለህ። ሆኖም ይህ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
ወደ አምላክና ወደ ትዳር ጓደኛህ የበለጠ ቅረብ
3, 4. የትዳር ጓደኛሞች ወደ አምላክ ለመቅረብ መጣራቸው እርስ በርሳቸው እንዲቀራረቡ የሚያስችላቸው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
3 አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ ወደ አምላክ ለመቅረብ ጥረት ባደረጋችሁ መጠን እርስ በርሳችሁ ይበልጥ ትቀራረባላችሁ። ይህ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ ተመልከት። ከግርጌው ሰፊ የሆነና አናቱ ደግሞ ሾጣጣ የሆነ አንድ ተራራ አስብ። አንድ ወንድ በስተሰሜን በኩል ባለው የተራራው ግርጌ ቆሟል። አንዲት ሴት ደግሞ በተቃራኒው ማለትም በስተደቡብ በኩል ባለው የተራራው ግርጌ ቆማለች። ሁለቱም ተራራውን መውጣት ይጀምራሉ። በተራራው ግርጌ ሳሉ በመካከላቸው ያለው ርቀት ከፍተኛ ነው። ሁለቱም ወደ ተራራው አናት በወጡ መጠን ግን በመካከላቸው ያለው ርቀት እየቀነሰ ይሄዳል። ይህ ምሳሌ የያዘውን የሚያበረታታ ሐሳብ አስተዋልክ?
4 ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለማገልገል የምታደርገው ጥረት አንድን ተራራ መውጣት ከሚጠይቀው ጥረት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሖዋን ስለምትወደው ቀድሞውንም ቢሆን በምሳሌያዊ ሁኔታ ተራራውን ለመውጣት ጥረት እያደረግክ ነው። ይሁን እንጂ አንተና የትዳር ጓደኛህ እንደተራራቃችሁ ከተሰማህ ተራራውን እየወጣችሁ ያላችሁት በተለያየ አቅጣጫ ሆናችሁ ነው ማለት ነው። ይሁንና ተራራውን መውጣታችሁን ከቀጠላችሁ ውጤቱ ምን ይሆናል? መጀመሪያ ላይ በመካከላችሁ የሚኖረው ርቀት ከፍተኛ እንደሚሆን አይካድም። ሆኖም ተራራውን ለመውጣት ማለትም ወደ አምላክ ለመቅረብ የበለጠ ጥረት ባደረጋችሁ መጠን በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል ያለው ርቀት እየጠበበ ይመጣል። በእርግጥም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ለመቀራረብ የሚያስችልህ ቁልፍ ነገር ወደ አምላክ መቅረብ ነው። ይሁንና ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በተግባር ላይ ሲውል ጋብቻህን ለማጠናከር የሚያስችል ኃይል አለው
5. (ሀ) ወደ ይሖዋና ወደ ትዳር ጓደኛህ ይበልጥ መቅረብ የምትችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ጋብቻን እንዴት ይመለከተዋል?
5 ተራራውን ለመውጣት የሚያስችላችሁ ወሳኝ የሆነው አንዱ መንገድ፣ ሁለታችሁም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ስለ ጋብቻ የተሰጡ ምክሮች መታዘዛችሁ ነው። (መዝሙር 25:4፤ ኢሳይያስ 48:17, 18) በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን አንድ ምክር መመልከታችን ጥሩ ነው። “ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር . . . ይሁን” ብሏል። (ዕብራውያን 13:4) ይህ ምን ማለት ነው? “ክቡር” የሚለው ቃል አንድ ነገር ከፍተኛ ግምት ወይም ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ያመለክታል። ይሖዋም ጋብቻን የሚመለከተው በዚህ መንገድ ነው፤ እንደ ውድ ነገር ስለሚቆጥረው ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።
ለመታዘዝ የሚያነሳሳህ ለይሖዋ ያለህ ከልብ የመነጨ ፍቅር ነው
6. ጳውሎስ ስለ ጋብቻ በሰጠው ምክር ዙሪያ ያለው ሐሳብ ምን ያሳያል? ይህንን ማስተዋል ጠቃሚ የሆነውስ ለምንድን ነው?
6 እርግጥ ነው፣ አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ የአምላክ አገልጋዮች በመሆናችሁ ቀድሞውንም ቢሆን ጋብቻ ውድ እንዲያውም ቅዱስ እንደሆነ ታውቃላችሁ። የጋብቻን ዝግጅት ያቋቋመው ይሖዋ ራሱ ነው። (ማቴዎስ 19:4-6) ይሁን እንጂ በትዳራችሁ ውስጥ ችግሮች እያጋጠሟችሁ ከሆነ ጋብቻ ክቡር መሆኑን ማወቃችሁ ብቻውን አንዳችሁ ሌላውን በፍቅርና በአክብሮት እንድትይዙ አያነሳሳችሁ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ እንድታደርጉ ሊያነሳሳችሁ የሚችለው ምንድን ነው? ጳውሎስ ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ምክር የሰጠበትን መንገድ ልብ በል። “ጋብቻ ክቡር ነው” ከማለት ይልቅ ‘ጋብቻ ክቡር ይሁን’ ሲል ተናግሯል። ጳውሎስ ይህን ሲል ጥብቅ ምክር መስጠቱ ነበር እንጂ ስለ ጋብቻ ያለውን አመለካከት እየተናገረ አልነበረም።a ይህን ማስተዋልህ ከዚህ ቀደም ለትዳር ጓደኛህ የነበረህን አክብሮት አሁንም እንድታሳይ ሊያነሳሳህ ይችላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
7. (ሀ) የትኞቹን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙ ትእዛዛት እንፈጽማለን? ለምንስ? (ለ) ታዛዥነት ምን ጥሩ ውጤት ያስገኛል?
7 እስቲ ቆም በልና ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ የተሰጠንን ተልእኮ ወይም ለአምልኮ እንድንሰበሰብ የተሰጠንን ማሳሰቢያና እነዚህን የመሰሉትን ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዛት እንዴት እንደምትመለከታቸው አስብ። (ማቴዎስ 28:19፤ ዕብራውያን 10:24, 25) እነዚህን ትእዛዛት መፈጸም አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ጊዜያት እንደሚኖሩ አይካድም። የምትሰብክላቸው ሰዎች መልእክቱን ሊቃወሙ ወይም ሥራህ በጣም አድካሚ ከመሆኑ የተነሳ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ መገኘት ተፈታታኝ ሊሆንብህ ይችላል። እንደዚያም ሆኖ የመንግሥቱን መልእክት መስበክህንም ሆነ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህን አታቆምም። ማንም ሰው፣ ሰይጣንም እንኳ ቢሆን እንዲያስቆምህ አትፈልግም። ለምን? ለይሖዋ ያለህ ከልብ የመነጨ ፍቅር ትእዛዛቱን እንድትፈጽም ስለሚገፋፋህ ነው። (1 ዮሐንስ 5:3) ይህ ምን ጥሩ ውጤት ይኖረዋል? በስብከቱ ሥራ መካፈልህና በስብሰባዎች ላይ መገኘትህ የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ስለምታውቅ ይህን መፈጸምህ ውስጣዊ ሰላምና ጥልቅ ደስታ ያስገኝልሃል። እንዲህ ያለው ስሜት ደግሞ ኃይልህን ያድስልሃል። (ነህምያ 8:10) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?
8, 9. (ሀ) ጋብቻን ክቡር አድርገን እንድንመለከት የተሰጠውን ምክር እንድንታዘዝ ምን ሊገፋፋን ይችላል? ለምንስ? (ለ) አሁን የትኞቹን ሁለት ነጥቦች እንመረምራለን?
8 ለአምላክ ያለህ ጥልቅ ፍቅር፣ መሰናክሎች ቢኖሩም እንኳ እንድንሰብክና እንድንሰበሰብ የተሰጠንን ትእዛዝ እንድትፈጽም እንደሚገፋፋህ ሁሉ፣ ለይሖዋ ያለህ ይኸው ፍቅር፣ አስቸጋሪ መስሎ በሚታይበት ጊዜ ሳይቀር ‘ጋብቻ[ህ] ክቡር ይሁን’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንድትታዘዝ ሊገፋፋህ ይችላል። (ዕብራውያን 13:4፤ መዝሙር 18:29፤ መክብብ 5:4) በተጨማሪም ለመስበክና በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የምታደርገው ጥረት ከአምላክ ብዙ በረከት እንደሚያመጣልህ ሁሉ ጋብቻህ ክቡር እንዲሆን የምታደርገውን ጥረትም ይሖዋ የሚመለከት ከመሆኑም በላይ ይባርክሃል።—1 ተሰሎንቄ 1:3፤ ዕብራውያን 6:10
9 ታዲያ ጋብቻህን ክቡር አድርገህ እንደምትመለከተው ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ትዳርህን ሊጎዱ የሚችሉ ጠባዮችን በማስወገድ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የጋብቻ ትስስራችሁን ለማጠናከር የሚረዱ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልግሃል።
ጋብቻን የሚያቃልሉ ንግግሮችንና ጠባዮችን አስወግድ
10, 11. (ሀ) ጋብቻን የሚያቃልለው ምን ዓይነት ጠባይ ነው? (ለ) ከትዳር ጓደኛችን ጋር የትኛውን ጥያቄ አንስተን መወያየት ይኖርብናል?
10 አንዲት ክርስቲያን ሚስት “ይሖዋ ችዬ እንድኖር የሚረዳኝን ኃይል እንዲሰጠኝ እጸልያለሁ” ብላለች። ችላ የምትኖረው ምኑን ነው? “ባለቤቴ በቃላት ይመታኛል። ከውጭ የሚታይ ጠባሳ ወይም ሰንበር የለብኝም። ይሁን እንጂ ሁልጊዜ የሚሰነዝራቸው ‘ሸክም!’ እና ‘የማትረቢ!’ እንደሚሉት ያሉ ጎጂ ቃላት ልቤን አቁስለውታል” በማለት ገልጻለች። ይህች ሚስት በጣም አሳሳቢ የሆነ አንድ ጉዳይ አንስታለች። ይኸውም ባልና ሚስት አንዳቸው በሌላው ላይ የሚሰነዝሩት የስድብ ንግግር ነው።
11 ክርስቲያን የሆኑ ባልና ሚስቶች አንዳቸው በሌላው ላይ ጭካኔ የሚንጸባረቅባቸው ቃላት በመሰንዘር በቀላሉ ሊሽር የማይችል የስሜት ቁስል ማስከተላቸው ምንኛ የሚያሳዝን ነው! የትዳር ጓደኛሞች አዘውትረው ጎጂ ቃላት የሚወራወሩ ከሆነ ጋብቻቸው ክቡር እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በዚህ ረገድ የአንተ ጋብቻ እንዴት ነው? ይህን ለማወቅ የምትችልበት አንደኛው መንገድ፣ የትዳር ጓደኛህን “የምናገራቸው ቃላት ምን ስሜት ያሳድሩብሻል?” ብለህ በትሕትና መጠየቅ ነው። የትዳር ጓደኛህ ብዙ ጊዜ ስሜቷን የሚያቆስሉ ቃላት እንደምትናገር ከተሰማት ሁኔታው እንዲሻሻል የባሕርይ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ይኖርብሃል።—ገላትያ 5:15፤ ኤፌሶን 4:31
12. የአንድ ሰው አምልኮ በአምላክ ዘንድ ከንቱ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
12 ከትዳር ጓደኛህ ጋር ባለህ ግንኙነት አንደበትህን የምትጠቀምበት መንገድ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና እንደሚነካብህ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ “አንድ ሰው አምልኮቱን እያከናወነ እንዳለ የሚሰማው ቢሆንም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን እያታለለ ይኖራል፤ የዚህ ሰው አምልኮም ከንቱ ነው” ይላል። (ያዕቆብ 1:26) አንደበትህን የምትጠቀምበት መንገድ ለይሖዋ ከምታቀርበው አምልኮ ተነጥሎ ሊታይ አይችልም። አንድ ሰው የአምላክ አገልጋይ ነኝ እስካለ ድረስ በቤቱ ውስጥ የፈለገውን ነገር ቢያደርግ ምንም ችግር የለውም የሚለውን አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ አይደግፈውም። እባክህ በዚህ ረገድ ራስህን አታታልል። ይህ አቅልለን የምንመለከተው ነገር አይደለም። (1 ጴጥሮስ 3:7) ጥሩ ችሎታና ቅንዓት ሊኖርህ ይችላል፤ ይሁንና የትዳር ጓደኛህን በመጥፎ ቃላት ሆን ብለህ የምትጎዳ ከሆነ ጋብቻህን እያቃለልክ ከመሆኑም በላይ አምልኮህ በአምላክ ዘንድ ከንቱ ይሆናል።
13. አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት የትዳር ጓደኛቸውን ስሜት ሊጎዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
13 በተጨማሪም ባልና ሚስቶች በተዘዋዋሪ መንገድ አንዳቸው የሌላውን ስሜት እንዳይጎዱ መጠንቀቅ ያስፈልጋቸዋል። ሁለት ምሳሌዎች ተመልከት:- ልጆቿን ለብቻዋ የምታሳድግ አንዲት እናት ብዙ ጊዜ ወደ አንድ ባለ ትዳር ወንድም እየደወለች ምክር የምትጠይቀው ከመሆኑም በላይ ረዘም ላለ ሰዓት ያወራሉ። አንድ ያላገባ ወንድም ከአንዲት ባለ ትዳር እህት ጋር በየሳምንቱ ረዘም ላለ ሰዓት ያገለግላል። በእነዚህ ምሳሌዎች ውስጥ የተጠቀሱት ባለትዳሮች መጥፎ ሐሳብ ላይኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጂ የሚያደርጉት ነገር በትዳር ጓደኞቻቸው ላይ ምን ስሜት ይፈጥራል? እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማት አንዲት ሚስት “ባለቤቴ በጉባኤ ውስጥ ላለች እህት ይህን ያህል ጊዜና ትኩረት ሲሰጥ ማየት ይጎዳኛል። የበታችነት ስሜት እንዲሰማኝ ያደርጋል” ብላለች።
14. (ሀ) በዘፍጥረት 2:24 ላይ፣ በጋብቻ የተሳሰሩ ሰዎች ምን ግዴታ እንዳለባቸው ተገልጿል? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቅ ይኖርብናል?
14 ይህች እህትና ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሌሎች ባለትዳሮች ለምን እንደተጎዱ መረዳት አስቸጋሪ አይሆንም። የትዳር ጓደኞቻቸው “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል” የሚለውን አምላክ ጋብቻን በሚመለከት የሰጠውን መሠረታዊ መመሪያ ችላ ብለዋል። (ዘፍጥረት 2:24) እርግጥ ነው፣ ያገቡ ሰዎች ካገቡም በኋላ ወላጆቻቸውን ያከብራሉ። ይሁን እንጂ አምላክ የሚጠብቅባቸው ለትዳር ጓደኛቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ ነው። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ከልብ የሚወዱ ቢሆንም ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለባቸው ለትዳር ጓደኛቸው ነው። በመሆኑም ባለትዳር የሆኑ ክርስቲያኖች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር፣ በተለይም ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ጋር ከመጠን ያለፈ ጊዜ ማሳለፋቸው ወይም በጣም መቀራረባቸው በትዳራቸው ውስጥ ውጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል። በትዳርህ ውስጥ ውጥረት የነገሠው በዚህ ምክንያት ይሆን? ራስህን ‘የትዳር ጓደኛዬ ከእኔ ልታገኝ የሚገባትን ጊዜ፣ ትኩረትና ፍቅር እሰጣታለሁ?’ ብለህ ጠይቅ።
15. በማቴዎስ 5:28 መሠረት ባለትዳር የሆኑ ክርስቲያኖች ተቃራኒ ጾታ ላላቸው ግለሰቦች ተገቢ ያልሆነ ትኩረት ሊሰጡ የማይገባቸው ለምንድን ነው?
15 ከዚህም በላይ የትዳር ጓደኛቸው ላልሆነ ግለሰብ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት የሚሰጡ ያገቡ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለአደጋ ያጋልጣሉ። የሚያሳዝነው ባለትዳር የሆኑ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከልክ በላይ ከተቀራረቧቸው ሰዎች ጋር ፍቅር ይዟቸዋል። (ማቴዎስ 5:28) እንዲህ ያለው የስሜት ቅርርብ ጋብቻቸውን ይበልጥ የሚያቃልል ድርጊት ወደ መፈጸም መርቷቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የተናገረውን ተመልከት።
‘መኝታው ከርኩሰት የጸዳ ይሁን’
16. ጳውሎስ ጋብቻን አስመልክቶ ምን ትእዛዝ ሰጥቷል?
16 ጳውሎስ ‘ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር ይሁን’ የሚል ምክር ከሰጠ በኋላ “መኝታውም ከርኩሰት የጸዳ ይሁን፤ ምክንያቱም አምላክ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ይፈርድባቸዋል” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ዕብራውያን 13:4) ጳውሎስ የጾታ ግንኙነትን ለማመልከት “መኝታ” የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። እንዲህ ያለው ግንኙነት “ከርኩሰት የጸዳ” ነው የሚባለው ወይም ከሥነ ምግባር አኳያ ንጹሕ የሚሆነው በጋብቻ ውስጥ ከተፈጸመ ብቻ ነው። ስለሆነም ክርስቲያኖች ‘በልጅነት ሚስትህ ደስ ይበልህ’ የሚለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተሰጠ ምክር ይታዘዛሉ።—ምሳሌ 5:18
17. (ሀ) ዓለም ለምንዝር ያለው አመለካከት በክርስቲያኖች ዘንድ ቦታ የሌለው ለምንድን ነው? (ለ) ኢዮብ የተወውን ምሳሌ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው?
17 የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር የጾታ ግንኙነት የሚፈጽሙ ሁሉ ለአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ጨርሶ አክብሮት እንደሌላቸው በግልጽ ያሳያሉ። እርግጥ ነው፣ ዛሬ ብዙዎች ምንዝርን ተቀባይነት ያለው ድርጊት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ሆኖም ሰዎች ስለ ምንዝር ያላቸው አመለካከት ምንም ይሁን ምን የእነሱ አመለካከት በክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር አይገባውም። መጨረሻ ላይ ‘ሴሰኞችንና አመንዝሮችን የሚፈርድባቸው አምላክ’ እንጂ ሰዎች እንዳልሆኑ ክርስቲያኖች ይገነዘባሉ። (ዕብራውያን 10:31፤ 12:29) ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በዚህ ጉዳይ ላይ ይሖዋ ያለውን አመለካከት አጥብቀው ይይዛሉ ወይም ይታዘዛሉ። (ሮሜ 12:9) የእምነት አባት የሆነው ኢዮብ “ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ” ብሎ እንደነበረ አስታውስ። (ኢዮብ 31:1) አዎ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ወደ ምንዝር በሚመራ መንገድ ላይ አንድ እርምጃ እንኳ ላለመሄድ ሲሉ የትዳር ጓደኛቸው ያልሆነን ሰው በምኞት ዓይን ላለመመልከት ዓይናቸውን ይቆጣጠራሉ።—“መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍቺና ስለ መለያየት ምን ይላል?” የሚለውን ተጨማሪ መረጃ ተመልከት።
18. (ሀ) ምንዝር በይሖዋ ዓይን ምን ያህል ከባድ ኃጢአት ነው? (ለ) በምንዝርና በጣዖት አምልኮ መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
18 ምንዝር በይሖዋ ዓይን ምን ያህል ከባድ ኃጢአት ነው? የሙሴ ሕግ ይሖዋ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን ስሜት እንድንገነዘብ ያስችለናል። በጥንቷ እስራኤል ምንዝርና የጣዖት አምልኮ የሞት ቅጣት ከሚያስከትሉ ኃጢአቶች መካከል ይመደቡ ነበር። (ዘሌዋውያን 20:2, 10) በሁለቱ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት አስተውለሃል? ጣዖት የሚያመልክ አንድ እስራኤላዊ ከይሖዋ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አፍርሷል። በተመሳሳይም ምንዝር የሚፈጽም እስራኤላዊ ከትዳር ጓደኛው ጋር የገባውን ቃል ኪዳን ያፈርሳል። ሁለቱም የክህደት ተግባር ፈጽመዋል። (ዘፀአት 19:5, 6፤ ዘዳግም 5:9፤ ሚልክያስ 2:14) ስለሆነም ሁለቱም ታማኝ በሆነው በይሖዋ አምላክ ፊት በደለኞች ናቸው።—መዝሙር 33:4
19. አንድ ሰው ምንዝር ላለመፈጸም ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔ ምን ሊያጠናክርለት ይችላል? እንዴት?
19 እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር አይደሉም። ይሁን እንጂ ምንዝር በጥንቷ እስራኤል ከባድ ኃጢአት ተደርጎ ይታይ እንደነበር ማስተዋላቸው እንዲህ ያለውን ኃጢአት ላለመፈጸም ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ ሊያጠናክርላቸው ይችላል። እንዴት? ይህን ንጽጽር ተመልከት:- ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተህ በጉልበትህ በመንበርከክ በአንድ ሥዕል ወይም ምስል ፊት ትጸልያለህ? ‘በፍጹም አላደርገውም!’ ብለህ እንደምትመልስ ምንም ጥርጥር የለውም። ብዙ ገንዘብ ይሰጥሃል ብትባል ይህን ለማድረግ ትፈተን ይሆን? ‘በጭራሽ እንዲህ አላደርግም!’ ብለህ ትመልሳለህ። በእርግጥም፣ ጣዖት በማምለክ ይሖዋን መካድ ለአንድ እውነተኛ ክርስቲያን ዘግናኝ ነገር ነው። በተመሳሳይም ክርስቲያኖች ኃጢአት እንዲሠሩ የሚገፋፋቸው ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ምንዝር በመፈጸም በይሖዋ አምላክም ሆነ በትዳር ጓደኛቸው ላይ ክህደት መፈጸም ሲያስቡት እንኳ ሊዘገንናቸው ይገባል። (መዝሙር 51:1, 4፤ ቆላስይስ 3:5) ሰይጣንን ደስ የሚያሰኝ ሆኖም ይሖዋን በእጅጉ የሚያሳዝንና ቅዱስ የሆነውን ጋብቻን የሚያቃልል ምንም ዓይነት ድርጊት መፈጸም አንፈልግም።
የጋብቻ ትስስራችሁን ማጠናከር የምትችለው እንዴት ነው?
20. በአንዳንድ ጋብቻዎች ውስጥ ምን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟል? በምሳሌ አስረዳ።
20 ጋብቻን የሚያቃልሉ ድርጊቶችንና ጠባዮችን ከማስወገድ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ለትዳር ጓደኛህ የነበረህን አክብሮት አሁንም ማሳየት እንድትችል ምን እርምጃዎች ልትወስድ ትችላለህ? ይህን ጥያቄ ለመመለስ እንዲያስችለን የጋብቻን ዝግጅት ከአንድ ቤት ጋር እናመሳስለው። ባለትዳሮች እርስ በርስ የሚለዋወጧቸው ደግነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት፣ አሳቢነታቸውን የሚያሳዩባቸው ድርጊቶችና ሌሎች የአክብሮት መግለጫዎች ደግሞ ለቤቱ ውበት እንደሚጨምሩለት ጌጣጌጦች ተደርገው ሊታዩ ይችላሉ። ከትዳር ጓደኛህ ጋር የምትቀራረቡ ከሆነ ጋብቻህ ድምቀትና ውበት በሚጨምሩለት ጌጣጌጦች እንደተዋበ ቤት ይሆናል። አንዳችሁ ለሌላው ያላችሁ ፍቅር እየቀዘቀዘ ከመጣ ግን ጋብቻህ እነዚያ ጌጣጌጦች አንድ በአንድ ጠፍተው ምንም ዓይነት ማስጌጫ እንደሌለው ወና ቤት ሆኗል ማለት ነው። ይሁንና አምላክ ‘ጋብቻ ክቡር ይሁን’ ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ለመፈጸም ያለህ ፍላጎት ሁኔታውን ለማሻሻል እርምጃ እንድትወስድ ያነሳሳሃል። ውድ የሆነንና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠውን ነገር ለመጠገን ወይም ለማደስ ምንም ያህል ቢለፋለት የሚያስቆጭ አይሆንም። ታዲያ የጋብቻ ትስስርህን ልታድስና ልትጠግን የምትችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል “ቤት በጥበብ ይሠራል፤ በማስተዋልም ይጸናል፤ በዕውቀትም ውድና ውብ በሆነ ንብረት፣ ክፍሎቹ ይሞላሉ” ይላል። (ምሳሌ 24:3, 4) እነዚህ ቃላት ከጋብቻ ጋር በተያያዘ እንዴት ሊሠሩ እንደሚችሉ እንመልከት።
21. ጋብቻችንን ቀስ በቀስ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? (በተጨማሪም “ከትዳር ጓደኛዬ ጋር ያለኝን ግንኙነት ማሻሻል የምችለው እንዴት ነው?” በገጽ 131 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)
21 አንድን ደስታ የሰፈነበት ቤት ከሚሞሉት ‘ውድ የሆኑ ነገሮች’ መካከል እንደ እውነተኛ ፍቅር፣ አምላካዊ ፍርሃትና ጠንካራ እምነት ያሉት ባሕርያት ይገኙበታል። (ምሳሌ 15:16, 17፤ 1 ጴጥሮስ 1:7) እነዚህ ባሕርያት ጋብቻን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሰው ምሳሌ ውስጥ የተገለጸውን ቤት ውድ በሆኑ ነገሮች እንዲሞላ ያደረገው ምን እንደሆነ አስተውለሃል? “ዕውቀት” ነው። አዎ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በተግባር ላይ ሲውል የሰዎችን አስተሳሰብ የመለወጥና አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር መልሰው እንዲያቀጣጥሉ የመርዳት ኃይል አለው። (ሮም 12:2፤ ፊልጵስዩስ 1:9) በመሆኑም ከትዳር ጓደኛህ ጋር ጊዜ ወስዳችሁ ረጋ ባለ መንፈስ የዕለቱን ጥቅስ ወይም ጋብቻን የሚመለከት በመጠበቂያ ግንብ አሊያም በንቁ! መጽሔት ላይ የወጣ አንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ትምህርት በምትመረምሩበት ጊዜ፣ ቤታችሁን ሊያስጌጥ የሚችል አንድ ውብ ጌጥ የምትመረምሩ ያህል ነው። ለይሖዋ ባላችሁ ፍቅር ተነሳስታችሁ በምርምር ያገኛችሁትን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ስትጥሩ፣ በምሳሌያዊ ሁኔታ ያንን የሚያምር ጌጥ ወደ “ክፍሎቹ” እያስገባችሁ ነው። በዚህ መንገድ ጋብቻችሁ በአንድ ወቅት የነበረው ድምቀትና ውበት ቀስ በቀስ እንዲመለስ ታደርጋላችሁ።
22. ጋብቻችንን ለማጠናከር የበኩላችንን ጥረት ማድረጋችን ምን እርካታ ያስገኝልናል?
22 ጌጦቹን አንድ በአንድ ወደነበሩበት ቦታ ለመመለስ ብዙ ጊዜና ጥረት እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በአንተ በኩል የሚጠበቅብህን ለማድረግ ከጣርክ መጽሐፍ ቅዱስ “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ” በማለት የሰጠውን ምክር እየታዘዝክ እንደሆነ ስለምታውቅ ከፍተኛ እርካታ ታገኛለህ። (ሮም 12:10፤ መዝሙር 147:11) ከሁሉ በላይ ደግሞ ጋብቻህን ክቡር አድርገህ ለመያዝ ልባዊ ጥረት ማድረግህ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጣ እንድትኖር ያስችልሃል።
a በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ጳውሎስ ጋብቻን አስመልክቶ የሰጠው ምክር በወቅቱ ለክርስቲያኖች ከሰጣቸው በርካታ ምክሮች አንዱ እንደነበር ያሳያል።—ዕብራውያን 13:1-5