የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ዕብራውያን 4:12—“የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው”
“የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል፤ የልብንም ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።”—ዕብራውያን 4:12 አዲስ ዓለም ትርጉም
“የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን፣ ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።”—ዕብራውያን 4:12 አዲሱ መደበኛ ትርጉም
የዕብራውያን 4:12 ትርጉም
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው አምላክ ለሰው ልጆች ያስተላለፈው መልእክት እውነተኛ አስተሳሰባችንንና ውስጣዊ ግፊታችንን የማጋለጥ ኃይል አለው። ይህ መልእክት ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ጥሩ ለውጥ እንዲያደርጉም ሊረዳቸው ይችላል።
“የአምላክ ቃል ሕያው . . . ነው።” “የአምላክ ቃል” የሚለው አገላለጽ አምላክ የሰጠውን ተስፋ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ዓላማውን ያመለክታል።a የዓላማው ዋነኛ ገጽታ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች እውነተኛ ሰላምና አንድነት ኖሯቸው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው።—ዘፍጥረት 1:28፤ መዝሙር 37:29፤ ራእይ 21:3, 4
የአምላክ ቃል ወይም የገለጸው ዓላማው “ሕያው” ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ቃሉን አምነው በሚቀበሉ ሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ስለሚያሳድር ነው፤ እነዚህ ሰዎች በተስፋ የተሞላና ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት ይችላሉ። (ዘዳግም 30:14፤ 32:47) የአምላክን ቃል “ሕያው” ነው የሚያስብለው ሌላው ምክንያት ደግሞ ሕያው የሆነው አምላክ፣ የሰጠው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አሁንም እየሠራ መሆኑ ነው። (ዮሐንስ 5:17) ሰዎች ቃል ከገቡ በኋላ የገቡትን ቃል ሊረሱ ወይም ከጊዜ በኋላ፣ የገቡትን ቃል ለመፈጸም አቅሙ እንደሌላቸው ሊረዱ ይችላሉ፤ አምላክ ግን እንደ ሰዎች አይደለም። (ዘኁልቁ 23:19) ቃሉ “ያላንዳች ውጤት ወደ [እሱ] አይመለስም።”—ኢሳይያስ 55:10, 11
“የአምላክ ቃል . . . ኃይለኛ ነው።” “ኃይለኛ ነው” የሚለው አገላለጽ “የሚሠራ ነው” ወይም “ቃሉ የተነገረበትን ማንኛውንም ዓላማ ይፈጽማል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። በመሆኑም ይሖዋb አምላክ የተናገረው ማንኛውም ነገር ወይም የሰጠው ተስፋ በእርግጠኝነት ይፈጸማል። (መዝሙር 135:6፤ ኢሳይያስ 46:10) እንዲያውም አምላክ የገባውን ቃል የሚፈጽመው እኛ ልንጠብቅ ከምንችለው በላቀ ሁኔታ ነው።—ኤፌሶን 3:20c
የአምላክ ቃል “ኃይለኛ ነው” ሊባል የሚችልበት ሌላው ምክንያት ለቃሉ አድናቆት ባላቸው ሰዎች ሕይወትና ማንነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ ነው። እንዲህ ያሉት ሰዎች የአምላክ ቃል አስተሳሰባቸውን፣ አኗኗራቸውንና ግባቸውን ስለሚቀርጸው ቃሉ የሕይወታቸው ክፍል ይሆናል። (ሮም 12:2፤ ኤፌሶን 4:24) ከዚህ አንጻር ‘የአምላክ ቃል አምነው በተቀበሉት ሰዎችም ላይ በእርግጥ እየሠራ ነው’ ሊባል ይችላል።—1 ተሰሎንቄ 2:13
“የአምላክ ቃል . . . በሁለት በኩል ስለት ካለው ከየትኛውም ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው።” የአምላክ ቃል ሰንጥቆ ወይም ዘልቆ የመግባት ኃይል ያለው በመሆኑ በምሳሌያዊ ሁኔታ ከማንኛውም ሰው ሠራሽ ሰይፍ የበለጠ ስለታም ነው ሊባል ይችላል። የአምላክ ቃል ሰዎች ከሚያስተምሩት ከየትኛውም ትምህርት ይበልጥ የሰውን ልብ ማለትም ውስጣዊ ማንነት የመንካት ኃይል አለው። ዕብራውያን 4:12 ቀጥሎ የሚናገረው ሐሳብ ይህን ያሳያል።
“የአምላክ ቃል . . . ነፍስንና መንፈስን እንዲሁም መገጣጠሚያንና መቅኒን እስኪለያይ ድረስ ሰንጥቆ ይገባል።” መጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ነፍስ” የሚለው ቃል የአንድን ሰው ከላይ የሚታይ ማንነት የሚያመለክት ሲሆን “መንፈስ” የሚለው ቃል ደግሞ የግለሰቡን እውነተኛ ውስጣዊ ማንነት ሊያመለክት ይችላል። (ገላትያ 6:18) “የአምላክ ቃል” በምሳሌያዊ ሁኔታ እስከ “መቅኒ” ማለትም ድብቅ እስከሆነው ስሜታችንና ሐሳባችን ድረስ ሰንጥቆ ይገባል። ከይሖዋ የምናገኘው ትምህርት በሰዎች ሊታይ የማይችለውን እውነተኛ ውስጣዊ ማንነታችንን በማጋለጥ ጥሩ ለውጥ እንድናደርግ ያነሳሳናል። ይህ ደግሞ እኛንም ሆነ ፈጣሪያችንን ያስደስታል።
“የአምላክ ቃል [የልብን] ሐሳብና ዓላማ መረዳት ይችላል።” አንድ ሰው ለአምላክ ቃል የሚሰጠው ምላሽ የልቡን እውነተኛ ሐሳብ ማለትም በባሕርይው ወይም በምግባሩ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርገውን ውስጣዊ ግፊት የሚያሳይ ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ በማድረግ ለአምላክ ቃል አዎንታዊ ምላሽ ከሰጠ ይህ ሰው ትሑትና ቅን ነው ማለት ነው። ፈጣሪውን ማስደሰት ይፈልጋል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው በአምላክ ቃል ውስጥ ስህተት የሚፈላልግ ከሆነ እንደ ኩራትና ራስ ወዳድነት ያሉ መጥፎ ባሕርያት እንዳሉት ያሳያል። ምናልባትም አምላክ የሚያወግዛቸውን ምግባሮች ተቀባይነት እንዲያገኙ ለማድረግ እየሞከረ ሊሆን ይችላል።—ኤርምያስ 17:9፤ ሮም 1:24-27
አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው የአምላክ ቃል “ድብቅ እስከሆነው ውስጣዊ ማንነታችን ድረስ ዘልቆ የመግባት ኃይል አለው።” አምላክ ሊያየው የማይችል ወይም ቃሉ ሊያጋልጠው የማይችል ምንም ዓይነት ውስጣዊ ማንነት ሊኖር አይችልም። ዕብራውያን 4:13 “ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው” በማለት ይናገራል።
የዕብራውያን 4:12 አውድ
የዕብራውያን መጽሐፍ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ለሚገኙ የአይሁድ ክርስቲያኖች በ61 ዓ.ም. ገደማ በመንፈስ መሪነት የጻፈው ደብዳቤ ነው።
ጳውሎስ በምዕራፍ 3 እና 4 ላይ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በወቅቱ ለነበሩት ክርስቲያኖች የማስጠንቀቂያ ምሳሌ የሚሆኑት እንዴት እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዕብራውያን 3:8-12፤ 4:11) ይሖዋ እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ አውጥቶ ‘ያለስጋት ወደሚቀመጡበት’ ምድር እንደሚያስገባቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘዳግም 12:9, 10) ሆኖም ከግብፅ የወጡት እስራኤላውያን አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት እንደሌላቸው አሳይተዋል፤ ሕግጋቱን በተደጋጋሚ በመጣስም ለእሱ ታዛዥ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በዚህም የተነሳ “ወደ [አምላክ] እረፍት” መግባትና ከእሱ ጋር የመሠረቱትን ወዳጅነት ማጣጣም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዚህ ይልቅ በምድረ በዳ ሞተው አለቁ። ምንም እንኳ ዘሮቻቸው ከጊዜ በኋላ ተስፋይቱን ምድር ቢወርሱም እነሱም የወላጆቻቸውን ምሳሌ በመከተል ዓመፀኛ መሆናቸውን አሳይተዋል። ይህ ደግሞ የኋላ ኋላ ብሔሩን ትልቅ ዋጋ አስከፍሎታል።—ነህምያ 9:29, 30፤ መዝሙር 95:9-11፤ ሉቃስ 13:34, 35
ጳውሎስ ክርስቲያኖች ዓመፀኛ ከሆኑት እስራኤላውያን ትምህርት ማግኘት እንዳለባቸው አብራርቷል። እኛ እንደ እነሱ መሆን አንፈልግም። የአምላክን ቃል ከታዘዝንና በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ሙሉ እምነት እንዳለን ካሳየን ወደ አምላክ እረፍት መግባት እንችላለን።—ዕብራውያን 4:1-3, 11
የዕብራውያን መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ዕብራውያን 4:12 ላይ የሚገኘው “የአምላክ ቃል” የሚለው አገላለጽ መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ሆኖም አምላክ፣ የሰጣቸው ተስፋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩ ስላደረገ ዕብራውያን 4:12 ለመጽሐፍ ቅዱስም ሊሠራ ይችላል።
b ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c “ኤፌሶን 3:20—‘ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ [የሚቻለው]’ አምላክ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት