የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
ኤርምያስ 33:3—“ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ”
“ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተ የማታውቀውን ታላቅና ለመረዳት አዳጋች የሆነ ነገር ወዲያውኑ እነግርሃለሁ።”—ኤርምያስ 33:3 አዲስ ዓለም ትርጉም
“ወደ እኔ ጩኽ፣ እኔም እመልስልሃለሁ፤ አንተም የማታውቀውን ታላቅና ኃይለኛ ነገርን አሳይሃለሁ።”—ኤርምያስ 33:3 የ1954 ትርጉም
የኤርምያስ 33:3 ትርጉም
አምላክ በእነዚህ ቃላት አማካኝነት ሰዎች ወደ እሱ በመጸለይ እንዲጠሩት ግብዣ አቅርቧል። ሰዎች ግብዣውን ተቀብለው ወደ አምላክ ከጸለዩ ወደፊት የሚከናወኑትን ነገሮች ይገልጥላቸዋል።
“ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ።” “ጥራኝ” የሚለው ቃል እንዲሁ የአምላክን ስም መጥራትን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘አምላክን መጥራት’ የሚለው አገላለጽ በዚህ አገባቡ የሚያመለክተው በጸሎት አማካኝነት የአምላክን እርዳታና አመራር መፈለግን ነው።—መዝሙር 4:1፤ ኤርምያስ 29:12
ይህ ግብዣ የቀረበው ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር ሳይሆን አይቀርም። ብሔሩ ለአምላክ ጀርባውን በመስጠቱ ከባቢሎን ሠራዊት ጥቃት እየተሰነዘረበት ነበር። (ኤርምያስ 32:1, 2) ይሖዋa እስራኤላውያን እሱን በጸሎት በመጥራት ወደ እሱ እንዲመለሱ ግብዣ አቅርቦላቸዋል።
“አንተ የማታውቀውን ታላቅና ለመረዳት አዳጋች የሆነ ነገር . . . እነግርሃለሁ።” አምላክ እንደሚገልጣቸው ቃል የገባቸው ነገሮች “ለመረዳት አዳጋች” (ወይም፣ ሊደረስባቸው የማይችል) ናቸው፤ ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች ሰዎች በራሳቸው ፈጽሞ ሊያውቋቸው አይችሉም። “ለመረዳት አዳጋች የሆነ ነገር” የሚለው አገላለጽ “የተሰወረ ነገር” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል።
አምላክ የሚገልጣቸው “የተሰወሩ ነገሮች” ምንድን ናቸው? ወደፊት የሚፈጸሙ ክንውኖች፣ ማለትም የጥንቷ ኢየሩሳሌም ከተማ መጥፋትና ባድማ መሆን፣ በኋላም መልሶ መገንባት ናቸው። (ኤርምያስ 30:1-3፤ 33:4, 7, 8) ሆኖም አምላክ፣ አገልጋዮቹ በብሔር ደረጃ እንደማይጠፉም ቃል ገብቷል።—ኤርምያስ 32:36-38
የኤርምያስ 33:3 አውድ
ነቢዩ ኤርምያስ ይህን መልእክት ከይሖዋ የተቀበለው በ608 ዓ.ዓ. ማለትም በንጉሥ ሴዴቅያስ የግዛት ዘመን አሥረኛ ዓመት ነው። ኤርምያስ ኢየሩሳሌም እንደምትወድቅና ሴዴቅያስ በግዞት እንደሚወሰድ ተንብዮአል። ንጉሡ በዚህ መልእክት ደስተኛ ስላልሆነ ኤርምያስን አሰረው።—ኤርምያስ 32:1-5፤ 33:1፤ 37:21
አምላክ በኤርምያስ 33:3 ላይ የሚገኘውን ግብዣ ያቀረበው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነበር። የሚያሳዝነው፣ ንጉሥ ሴዴቅያስና በብሔሩ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች በዓመፅ ጎዳናቸው ቀጠሉ። (ኤርምያስ 7:26፤ 25:4) ወደ አምላክ በመጣራት የእሱን አመራር ለማግኘት አልሞከሩም። ከአንድ ዓመት በኋላ ሴዴቅያስ ከሥልጣኑ ተሻረ፤ ኢየሩሳሌም ጠፋች፤ እንዲሁም በሕይወት የተረፉት አብዛኞቹ ሰዎች በግዞት ወደ ባቢሎን ተወሰዱ።—ኤርምያስ 39:1-7
ኤርምያስ 33:3 ላይ ያለው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንባቢዎች፣ አምላክ ወደ እሱ ለሚጸልዩና ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያጠኑ ሰዎች ‘የፈቃዱን ትክክለኛ እውቀት’ እንደሚሰጣቸውና ‘ጥልቅ ነገሮችን’ እንደሚገልጥላቸው እንዲገነዘቡ ያደርጋል። (ቆላስይስ 1:9፤ 1 ቆሮንቶስ 2:10) እነዚህ ጥልቅ ነገሮች አምላክ በቅርቡ እንደሚያከናውን ቃል የገባቸውን ነገሮች ይጨምራሉ።—ራእይ 21:3, 4
የኤርምያስ መጽሐፍን አጠቃላይ ይዘት ለማየት ይህን አጭር ቪዲዮ ተመልከት።
a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።