የእምነታችሁ ጥንካሬ —ዛሬ ይፈተናል
“ወንድሞቼ ሆይ፣ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን [“ጽናትን፣” NW] እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቊጠሩት።” —ያዕቆብ 1:2, 3
1. ክርስቲያኖች እምነታቸው እንደሚፈተን መጠበቅ ያለባቸው ለምንድን ነው?
እውነተኛ ክርስቲያኖች የመሠቃየት ፍላጎት የላቸውም። የሚደርስባቸው ሥቃይና ውርደትም አያስደስታቸውም። ቢሆንም የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ያዕቆብ የጻፋቸውን ከላይ ያሉትን ቃላት ያስታውሳሉ። ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን የአቋም ደረጃዎች በጥብቅ በመከተላቸው ምክንያት ስደትና ሌሎች ችግሮች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉ ክርስቶስ ግልጽ አድርጎላቸዋል። (ማቴዎስ 10:34፤ 24:9-13፤ ዮሐንስ 16:33) ያም ሆኖ እንዲህ ካሉት ፈተናዎች ደስታ ማግኘት ይቻላል። ግን እንዴት?
2. (ሀ) የእምነታችን መፈተን ደስታን ሊያስገኝልን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) በእኛ ሁኔታ ጽናት ሥራውን ሊፈጽም የሚችለው እንዴት ነው?
2 ስደት ወይም የእምነት ፈተና ሲደርስብን ደስተኞች የምንሆንበት ቁልፍ ምክንያት እነዚህ ፈተናዎች መልካም ፍሬ እንድናፈራ ስለሚረዱን ነው። ያዕቆብ እንዳለው ፈተናዎችን ወይም ችግሮችን መቋቋማችን ‘ጽናትን ያስገኝልናል።’ ይህንን ውድ ክርስቲያናዊ ባሕርይ በማዳበራችን ልንጠቀም እንችላለን። ያዕቆብ “ትዕግሥትም ምንም የሚጐድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:4) ጽናት አንድ የሚያከናውነው ተግባር ማለትም የሚሠራው ‘ሥራ’ አለው። ሥራው በሁሉም አቅጣጫ ምሉዓን ክርስቲያኖች እንድንሆን በማገዝ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች እኛን ሚዛናዊና ጎልማሶች ማድረግ ነው። ስለዚህ የሚደርስብን ፈተና እስከ መጨረሻው እንዲቀጥል ከፈቀድንና ቶሎ ለመገላገል ስንል ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ዘዴዎችን ተጠቅመን በአጭሩ ካልቀጨናቸው እምነታችን የተፈተነና የተጣራ ይሆናል። አንዳንድ ሁኔታዎችን በመቋቋም ወይም ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ትዕግሥት፣ ርህራሄ፣ ደግነት ወይም ፍቅር በመጠኑ ጎድሎን ከነበረ ጽናት ይበልጥ ምሉዓን እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። አዎን፣ ቅደም ተከተሉ የሚከተለው ነው:- ፈተናዎች ጽናትን ያፈራሉ፤ ጽናት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ይጨምራል፤ እነዚህ ደግሞ ለደስታ ምክንያት ይሆኑናል።—1 ጴጥሮስ 4:14፤ 2 ጴጥሮስ 1:5-8
3. ስደቶችን ወይም የእምነት ፈተናዎችን በመፍራት ወደ ኋላ ማፈግፈግ የማይኖርብን ለምንድን ነው?
3 በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ የሚደርሱብንን የእምነት ፈተናዎች ለምን መፍራት ወይም መሸሽ እንደማያስፈልገን ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፣ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፣ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።” (1 ጴጥሮስ 1:6, 7) የውዳሴ፣ የክብር፣ የምስጋናና የመዳን ጊዜ የሆነው “ታላቅ መከራ” ከምናስበውና መጀመሪያ ካመንበት ጊዜ ይልቅ ይበልጥ ቅርብ በመሆኑ እነዚህ ቃላት በተለይ ዛሬ ልዩ ማበረታቻ ይሆኑናል።—ማቴዎስ 24:21፤ ሮሜ 13:11, 12
4. አንድ ወንድም እሱና ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስላጋጠሟቸው ፈተናዎች ምን ተሰምቶት ነበር?
4 ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ከ1914 ጀምሮ ቅቡዓኑ ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች ተመልክተናል። እነዚህ ፈተናዎች የደስታ መሠረት ሆነው ነበር? ኤ ኤች ማክሚላን ያለፈውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በድርጅቱ ላይ ብዙ ከባድ ፈተናዎች ሲደርሱና በውስጡ ያሉትም እምነታቸው ሲፈተን ተመልክቼአለሁ። ድርጅቱ በአምላክ መንፈስ እርዳታ እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ሊወጣና እየጎለበተ ሊሄድ ችሏል። አዳዲስ አስተሳሰቦች ሲመጡ ቅር ከመሰኘት ይልቅ ይሖዋ ቅዱስ ጽሑፋዊ ስለሆኑ ጉዳዮች ያለንን ግንዛቤ ግልጽ እስኪያደርግልን ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ጥበብ መሆኑን ለመመልከት ችያለሁ። . . . ከጊዜ ወደ ጊዜ በአመለካከታችን ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ለማድረግ ብንገደድ ይህ ታላቅ በሆነው የቤዛ ዝግጅትና አምላክ በሰጠን የዘላለም ሕይወት ተስፋ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። ስለዚህ የጠበቅናቸው ነገሮች ሳይፈጸሙ በመቅረታቸው ወይም የአመለካከት ለውጥ በመደረጉ እምነታችን እንዲዳከም የምንፈቅድበት ምንም ምክንያት አልነበረም።”—መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ነሐሴ 15, 1966 ገጽ 504
5. (ሀ) የቅቡዓኑ መፈተን ምን ጠቃሚ ውጤት አስገኝቷል? (ለ) ይህ የመፈተን ጉዳይ ዛሬ የእኛን ትኩረት የሚስብ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ከ1914-19 የነበረውን የፈተና ጊዜ ጸንተው ያለፉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከዓለም ተጽእኖና ባቢሎናዊ ከሆኑ ብዙ ሃይማኖታዊ ልማዶች ነጻ ወጥተዋል። ቅቡዓን ቀሪዎቹ ንጹህና የጠሩ ሕዝብ ሆነው ለአምላክ በፈቃደኝነት የውዳሴ መሥዋዕት በማቅረብና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኙ እርግጠኞች በመሆን ወደፊት መገስገሳቸውን ቀጥለዋል። (ኢሳይያስ 52:11፤ 2 ቆሮንቶስ 6:14-18) ፍርዱ ከአምላክ ቤት ቢጀምርም በአንድ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚያበቃ አልነበረም። የአምላክን ሕዝቦች የማጥራቱና የማበጠሩ ሥራ አሁንም ቀጥሏል። ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ ክፍል በመሆን እየቀረበ ካለው ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት የመትረፍ ተስፋ ያላቸው ሰዎችም እምነት በመፈተን ላይ ነው። (ራእይ 7:9, 14) የእነዚህም እምነት በመፈተን ላይ ያለው ቅቡዓን ቀሪዎች ከደረሰባቸው ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ በሆኑና በሌሎችም ተጨማሪ መንገዶች ነው።
በምን ረገድ ልትፈተን ትችላለህ?
6. በብዙዎች ላይ የደረሰው የትኛው ከባድ ፈተና ነው?
6 ብዙ ክርስቲያኖች ፊት ለፊት የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ስለመቋቋም ያስባሉ። የሚከተለውን ዘገባ ያስታውሳሉ:- “[አይሁዳውያን መሪዎች] ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፉአቸው፣ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው። እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ።” (ሥራ 5:40, 41) ዘመናዊው የአምላክ ሕዝቦች ታሪክ በተለይም ደግሞ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወቅት ያሳለፉት ነገር ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች በአሳዳጆቻቸው ድብደባና ከዚያም የከፉ ነገሮች እንደተፈጸመባቸው በግልጽ ያሳያል።
7. በዚህ ዘመን ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች እምነታቸውን ያሳዩት እስከ ምን ድረስ ነው?
7 ክርስቲያኖች የስደት ዒላማ መሆናቸውን በሚመለከት ዓለም በቅቡዓን ቀሪዎችና የ“ሌሎች በጎች” ክፍል በሆኑት በእጅግ ብዙ ሰዎች መካከል ልዩነት አያደርግም። (ዮሐንስ 10:16) ባለፉት ዓመታት በሙሉ የሁለቱም ቡድን አባላት ለአምላክ ባላቸው ፍቅርና እምነት ምክንያት በከባድ እስራት ተፈትነዋል፣ በሰማዕትነት እስከመሞትም ደርሰዋል። ሁለቱም ቡድኖች ተስፋቸው ምንም ሆነ ምን የአምላክ መንፈስ አስፈልጓቸው ነበር። (ከሰኔ 15, 1996 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 31 ጋር አወዳድር።) በ1930ዎቹና በ1940ዎቹ ዓመታት በናዚዎች ግዛት ሥር በነበረችው ጀርመን ልጆችን ጨምሮ ማለፊያ የሆነ እምነት ያሳዩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮች ነበሩ። እስከሞት ድረስ የጸኑም ጥቂቶች አይደሉም። በቅርብ ዓመታት ደግሞ የይሖዋ ሕዝቦች እንደ ቡሩንዲ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ፣ ሲንጋፖርና ዛይር ባሉት አገሮች ብዙ ስደት ደርሶባቸዋል። እንዲህ ያሉ ፈተናዎች አሁንም ቢሆን አላቆሙም።
8. አንድ አፍሪካዊ ወንድም የተናገረው ሐሳብ የእምነታችን መፈተን በድብደባ መልክ ከሚመጣ ስደት ከመጽናት የበለጠ ነገር እንደሚጨምር ያሳየው እንዴት ነው?
8 ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንዳየነው እምነታችን ስውርና መሰሪ በሆኑ ሌሎች መንገዶችም በመፈተን ላይ ይገኛል። አንዳንዶቹ ፈተናዎች ፊት ለፊት የሚሰነዘሩ አይደሉም፤ እንዲሁም በቀላሉ አይለዩም። እስቲ የሚከተሉት ፈተናዎች ቢያጋጥሙህ ምን ታደርግ እንደነበረ አስብ። በአንጎላ የሚኖር አሥር ልጆች ያሉት አንድ ወንድም የነበረበት ጉባኤ ለተወሰነ ጊዜ ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር ግንኙነት ማድረግ አልቻለም ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሌሎች ወንድሞች ጉባኤውን ለመጎብኘት ችለዋል። ቤተሰቡን ይመግብ የነበረው እንዴት እንደሆነ ተጠየቀ። ለዚህ ጥያቄ መልስ መስጠት ስለከበደው ሁኔታው ቀላል እንዳልነበረ ከመግለጽ በቀር ሊናገር የቻለው ነገር አልነበረም። ልጆቹን ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ችሎ ነበርን? “አልቻልኩም። ያገኘነውን አብቃቅተን መኖር ለምደናል” ሲል መልሷል። ከዚያም እምነት በተሞላ አነጋገር “በዚህ በመጨረሻ ቀን የምንጠብቀው ይህንን አይደለምን?” ብሏል። እንዲህ ያለው እምነት ለዓለም የሚያስደንቅ ቢሆንም የመንግሥቱ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ሙሉ እምነት ላላቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ግን አዲስ ነገር አይደለም።
9. ከ1 ቆሮንቶስ 11:3 ጋር በተያያዘ ሁኔታ እየተፈተንን ያለነው እንዴት ነው?
9 እጅግ ብዙ ሰዎችም ለቲኦክራሲያዊ አሠራር በመገዛት ረገድ ይፈተናሉ። ዓለም አቀፉ የክርስቲያን ጉባኤ የሚመራው መለኮታዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችና በቲኦክራሲያዊ የአቋም ደረጃዎች ነው። ይህ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ክርስቶስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ሆኖ የተሾመ መሪ መሆኑን መቀበል ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ለእርሱና ለአባቱ በፈቃደኝነት መገዛታችን የሚታየው በቲኦክራሲያዊ ሹመት ላይና እንደ አንድ አካል ሆነን ከምንፈጽመው የይሖዋ ፈቃድ ጋር በተያያዙት ውሳኔዎች ላይ ባለን እምነት ነው። ከዚህም በላይ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ የመሪነቱን ቦታ እንዲይዙ የተሾሙ ወንዶች አሉ። አለፍጽምና ያለባቸው ሰዎች በመሆናቸው ስህተቶቻቸውን በቀላሉ ለመመልከት እንችላለን። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉትን የበላይ ተመልካቾች እንድናከብርና እንድንታዘዛቸው በጥብቅ ተመክረናል። (ዕብራውያን 13:7, 17) እንዲህ ማድረጉ አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ይሆንብሃል? በእርግጥ ይህ ለአንተ ፈተና ነውን? እንደዚያ ከሆነ በእምነትህ ላይ ከሚደርሰው ፈተና ጥቅም እያገኘህ ነው?
10. የመስክ አገልግሎታችንን በሚመለከት ምን ፈተና ያጋጥመናል?
10 በመስክ አገልግሎት አዘውትሮ በመካፈል መብትና ግዴታ ረገድም እንፈተናለን። ይህን ፈተና ለማለፍ በአገልግሎቱ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ በስብከቱ ሥራ ለይስሙላ ብቻ ከመካፈል የሚበልጥ ነገር እንደሚጨምር መገንዘብ አለብን። ኢየሱስ ያላትን ሁሉ የሰጠችውን ድሃ መበለት በማመስገን የተናገረውን አስታውሱ። (ማርቆስ 12:41-44) ‘እኔስ በተመሳሳይ ከመስክ አገልግሎቴ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በዚህ መልክ ራሴን አቅርቤያለሁን?’ ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። ሁላችንም ዘወትር ለይሖዋ ምሥክሮች ለመሆንና በማንኛውም አጋጣሚ ብርሃናችንን ለማብራት ዝግጁዎች መሆን ይገባናል።—ማቴዎስ 5:16
11. አኗኗርን በሚመለከት የሚሰጠው ምክር ፈተና ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
11 ሌላው ሊገጥመን የሚችለው ፈተና ደግሞ በየጊዜው እየጨመረ ለሚሄደው የእውነት ብርሃንና በታማኙ የባሪያ ክፍል በኩል ለሚሰጡን ምክሮች ካለን አድናቆት ጋር የተያያዘ ነው። (ማቴዎስ 24:45) ሲጋራ ያጨሱ የነበሩ ሰዎች በጉባኤ ውስጥ ለመቆየት የሚፈልጉ ከሆነ ይህን ልማዳቸውን ማቆም እንዳለባቸው ግልጽ በሆነበት ጊዜ እንደተደረገው ሁሉ አንዳንድ ጊዜ ይህ በግል ጠባያችን ላይ ማስተካከያ ማድረግን ይጠይቅ ይሆናል።a (2 ቆሮንቶስ 7:1) ወይም ፈተናው የምንሰማቸውን ሙዚቃዎች ወይም ሌሎች የመዝናኛ ዓይነቶች በተመለከተ በነበረን ምርጫ ላይ ማስተካከያ የማድረጉን አስፈላጊነትን መቀበል ሊሆን ይችላል።b የተሰጠው ምክር ጥበብ ያለበት መሆኑን እንጠራጠራለን? ወይስ የአምላክ መንፈስ አስተሳሰባችንን እንዲያስተካክልልንና አዲሱን ክርስቲያናዊ ባሕርይ እንድንለብስ እንዲረዳን እንፈቅዳለን?—ኤፌሶን 4:20-24፤ 5:3-5
12. አንድ ሰው ከተጠመቀ በኋላ እምነቱን ለማጠንከር ምን ያስፈልገዋል?
12 ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የእጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን ከተጠመቁም በኋላ ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና ማጠንከራቸውን ቀጥለዋል። ይህ በአንዳንድ ክርስቲያናዊ ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ወይም በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ አንዳንድ ስብሰባዎች ላይ ከመገኘት ወይም አልፎ አልፎ በመስክ አገልግሎት ከመካፈል የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል:- አንድ ሰው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን በአካል ሊወጣ ይችላል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ጥሏት ወጥቷልን? የአምላክን የጽድቅ ደረጃዎች የሚያቃልለው የታላቂቱ ባቢሎን መንፈስ የሚንጸባረቅባቸውን አንዳንድ ነገሮች ገና የሙጥኝ እንዳለ ነውን? የጾታ ሥነ ምግባርንና ለትዳር ጓደኛ ታማኝ መሆንን አቅልሎ ይመለከታልን? ከመንፈሳዊ ጉዳዮች ይበልጥ ለግልና ለቁሳዊ ጉዳዮች ትኩረት ይሰጣልን? አዎን፣ የዓለም እድፍ ፈጽሞ እንዳይነካው ይጠነቀቃልን?—ያዕቆብ 1:27
የተፈተነ እምነት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
13, 14. አንዳንዶች በእውነተኛው አምልኮ መንገድ ላይ መጓዝ ከጀመሩ በኋላ ምን አድርገዋል?
13 በእርግጥ ከታላቂቱ ባቢሎን ሸሽተን ወጥተን ከዓለም ተለይተን ከሆነ ትተናቸው የመጣናቸውን ነገሮች መለስ ብለን አንመልከት። ሉቃስ 9:62 ላይ ከተጠቀሰው መሠረታዊ ሥርዓት አንፃር ማናችንም ወደኋላችን መለስ ብንል የአምላክ መንግሥት ዜጎች የመሆን መብታችንን ልናጣ እንችላለን። ኢየሱስ “ማንም እርፍ በእጁ ይዞ ወደኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” ብሏል።
14 ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት ክርስቲያኖች የሆኑ አንዳንዶች ይህን ሥርዓት ለመምሰል ፈቅደዋል። የዓለምን መንፈስ አልተቋቋሙም። (2 ጴጥሮስ 2:20-22) ትኩረታቸውና ጊዜያቸው በዓለማዊ ማታለያዎች በመዋጡ መንፈሳዊ እድገታቸው ተገቷል። አእምሮአቸውና ልባቸው በአምላክ መንግሥትና በእርሱ ጽድቅ ላይ እንዲያተኩር ከማድረግና በሕይወታቸው የመጀመሪያውን ቦታ ከመስጠት ይልቅ ቁሳዊ ግቦች ወደማሳደድ ዘወር ብለዋል። እምነታቸው እንደተዳከመና ለብ ብለው እንዳሉ በመገንዘብ መለኮታዊ ምክር ተቀብለው አካሄዳቸውን ካልለወጡ ከይሖዋና ከድርጅቱ ጋር ያላቸውን ውድ ዝምድና የማጣት አደጋ ይገጥማቸዋል።— ራእይ 3:15-19
15. በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንዳገኙ ለመኖር ምን ያስፈልጋል?
15 በጣም እየቀረበ ካለው ታላቅ መከራ ለመዳን የምንበቃ መሆናችን የተመካው ልብሳችንን ‘በበጉ ደም አጥበን’ ያነጻንና ንጽህናችንን የምንጠብቅ በመሆናችን ላይ ነው። (ራእይ 7:9-14፤ 1 ቆሮንቶስ 6:11) በአምላክ ፊት ንጹሕ የሆነ የጽድቅ አቋም ከሌለን ቅዱስ አገልግሎታችን ተቀባይነት አያገኝም። በእርግጥም የተፈተነ እምነት ለመጽናት እንደሚረዳንና ከአምላክ ቁጣ እንደሚጠብቀን እያንዳንዳችን መገንዘብ ይኖርብናል።
16. የሐሰት ወሬዎች እምነታችንን ሊፈትኑ የሚችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?
16 አንዳንድ ጊዜ መገናኛ ብዙሐንና ባለሥልጣኖች ክርስቲያናዊ እምነታችንንና አኗኗራችንን በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም በሐሰት ይወነጅሉናል። ኢየሱስ ‘ከዓለም ስላልሆን ዓለም እንደሚጠላን’ በግልጽ በመናገሩ ይህ ሊያስደንቀን አይገባም። (ዮሐንስ 17:14) ሰይጣን ያሳወራቸው ሰዎች እንዲያስፈራሩንና ወኔያችንን እንዲሰልቡ በመፍቀድ በምሥራቹ እናፍራለን? ስለ እውነት በሚነገሩ የሐሰት ወሬዎች ምክንያት አዘውትረን ከመሰብሰብና በስብከት ሥራ ከመሳተፍ ወደኋላ እንላለን? ወይስ ጸንተን በመቆምና ደፋሮች በመሆን ስለ ይሖዋና ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን እውነት ለማወጅ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠን እንነሳለን?
17. እምነት በማሳየት እንድንቀጥል የሚያንቀሳቅሰን የትኛው ማረጋገጫ ነው?
17 ፍጻሜያቸውን ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ ወደ መጨረሻው ቀን በጣም ዘልቀን ገብተናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ጽድቅ የሚሰፍንበት የአዲስ ዓለም ተስፋችን በአስደሳች ሁኔታ እንደሚፈጸም ምንም አያጠራጥርም። ያ እስከሚሆን ግን ሁላችንም በአምላክ ቃል ላይ የማይናወጥ እምነት ይኑረን። የመንግሥቱን ምሥራች በመላው ዓለም መስበካችንን ለአንድ አፍታ እንኳን ባለማቆም እምነታችንን እናረጋግጥ። በየሳምንቱ ስለሚጠመቁት በሺህ የሚቆጠሩ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት አስቡ። ታዲያ ይህ ብቻውን ይሖዋ የቅጣት ፍርዱን በተመለከተ ያሳየው ትዕግሥት ለብዙ ሰዎች መዳን ምክንያት እንደሆነ አያስገነዝበንም? አምላክ ሕይወት አድን የሆነው የመንግሥቱ ስብከት እንቅስቃሴ እንዲቀጥል መፍቀዱ አያስደስተንም? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነትን መቀበላቸውና እምነታቸውን በተግባር ለማሳየት መቻላቸው ደስ አያሰኘንም?
18. ይሖዋን በማገልገል ረገድ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?
18 በአሁኑ ጊዜ በእምነታችን ላይ እየደረሰ ያለው ፈተና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቀጥል አናውቅም። ይሁን እንጂ አንድ እርግጠኛ የሆነ ነገር አለ:- ይሖዋ በዚህ በዛሬው ክፉ ሰማይና ምድር ላይ የሚፈርድበትን ቀን ቆርጧል። እስከዚያ ጊዜ ግን የእምነታችን ፈጻሚ የሆነው ኢየሱስ ያሳየውን ዓይነት፣ ፈተናን የሚቋቋም እጅግ ጠንካራ የሆነ እምነት ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በተጨማሪም በምድር ላይ ያሉ እርጅና እየተጫጫናቸው የሚገኙ ቅቡዓን ቀሪዎችና በመካከላችን ግንባር ቀደም ሆነው በድፍረት የሚያገለግሉትን ሌሎች ወንድሞች ምሳሌ እንከተል።
19. ይህን ዓለም እንደሚያሸንፍ እርግጠኛ ልትሆኑበት የምትችሉት ነገር ምንድን ነው?
19 በሰማይ መካከል ከሚበረው መልአክ ጋር በመተባበር የዘላለሙን ምሥራች ለሁሉም ብሔራት፣ ዘሮች፣ ቋንቋዎችና ሕዝቦች አላንዳች ማሰለስ ለማወጅ ቁርጥ ውሳኔ ልናደርግ ይገባል። ሁሉም “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” የሚለውን መልአኩ የሚያውጀውን መልእክት ይስሙ። (ራእይ 14:6, 7) ይህ መለኮታዊ ፍርድ በሚፈጸምበት ጊዜ የተፈተነው እምነታችን ምን ውጤት ያስገኝልናል? ከዚህ ሥርዓት ተገላግሎ ወደ አምላክ አዲስ የጽድቅ ዓለም መግባት ትልቅ ድል አይሆንምን? በእምነታችን ላይ የሚደርሱትን ፈተናዎች ጸንተን በመቋቋም እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ “ዓለምን የሚያሸንፈው እምነታችን ነው” ለማለት እንችላለን።— 1 ዮሐንስ 5:4
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
ታስታውሳለህ?
◻ በእምነታችን ላይ የሚደርሱት ፈተናዎች የደስታ ምንጭ ሊሆኑልን የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ በቀላሉ ልንለያቸው የማንችላቸው አንዳንዶቹ የእምነታችን ፈተናዎች የትኞቹ ናቸው?
◻ በእምነታችን ላይ የሚደርሱትን ፈተናዎች በማሸነፍ ዘላቂ ጥቅም ልናገኝ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኤ ኤች ማክሚላን (ፊት ለፊት በስተግራ) እርሱና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ውስጥ የሚሠሩ ወንድሞች ፍትህ በጎደለው መንገድ በታሠሩበት ጊዜ
በሚሽገን ዲትሮይት በ1928 በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኙት ልዑካን አንዱ ነበር
ወንድም ማክሚላን በሕይወቱ መጨረሻ ዓመታት እንኳ እምነቱ አልቀነሰም
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ልክ እንደዚህ ቤተሰብ በአፍሪካ የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች የተፈተነ እምነት አሳይተዋል