ከምታያቸው ነገሮች ባሻገር ተመልከት!
ጥሩ የማየት ችሎታ በረከት ነው። እንዲያውም አብዛኞቹ ሰዎች የማየት ችሎታ ከምንም ነገር ይበልጥ ውድ እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከአካላዊ የማየት ችሎታ የበለጠ ከፍ አድርገው የሚመለከቱት አንድ ሌላ ዓይነት የማየት ችሎታ እንዳለ ተናግሯል። ጳውሎስ “እኛ የምንመለከተው የማይታየውን ነገር እንጂ የሚታየውን አይደለም” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 4:18 የ1980 ትርጉም) በእርግጥም አንድን ሰው የማይታዩትን ነገሮች ለማየት የሚያስችለው በጣም ልዩ የሆነ የማየት ችሎታ ነው! ይህን የማየት ችሎታ ግሩም የሆነ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ ብለን ልንጠራው እንችላለን።
ለምን አስፈለገ?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች እንደዚህ ዓይነቱ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ በጣም ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቲያናዊ አገልግሎታቸውን ያከናውኑ የነበሩት በከባድ መከራና ችግር ሥር ሆነው ነበር። ጳውሎስ ሁኔታውን በዚህ መንገድ ገልጾታል፦ “በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤ እንሰደዳለን እንጂ አንጣልም፤ እንወድቃለን እንጂ አንጠፋም።”—2 ቆሮንቶስ 4:8, 9
እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ቢኖሩም ታማኞቹ ደቀ መዛሙርት የጸና አቋም ይዘው ነበር። በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት በማሳደር፣ “ተስፋ አንቆርጥም፣ ምንም እንኳ ውጫዊ ሰውነታችን ቢጠፋ፣ ውስጣዊ ሰውነታችን በየቀኑ ይታደሳል” በማለት እንደ ጳውሎስ ለመናገር ችለው ነበር። ሆኖም በየቀኑ እንዲታደሱ ያስቻላቸው ምንድን ነው? ቀጥሎ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ቀላልና ጊዜያዊ የሆነ መከራችን፣ ወደር የሌለውን እጅግ ታላቅ የሆነ ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። እኛ የምንመለከተው የማይታየውን ነው እንጂ የሚታየውን አይደለም፤ ምክንያቱም የሚታየው ነገር ጊዜያዊ ነው፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው።”—2 ቆሮንቶስ 4:16-18 የ1980 ትርጉም
ጳውሎስ ፈተናዎች፣ ችግሮች፣ ስደቶችም ሆኑ ማናቸውም ዓይነት መከራዎች ከፊት ለፊታቸው የሚጠብቃቸውን ክብራማ ሽልማት እንዳይጋርዱባቸው መንፈሳዊ ወንድሞቹን እያበረታታቸው ነበር። ዓይናቸውን ክርስቲያናዊ ሕይወት በሚያስገኛቸው አስደሳች ውጤቶች ላይ በመትከል ካጋጠሟቸው ጊዜያዊ ሁኔታዎች ባሻገር መመልከት ነበረባቸው። በትግሉ ወደፊት ለመግፋት ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ በየዕለቱ እንዲያጠናክሩ የረዳቸው ይህ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም በዚያ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ያህል እንደዚህ ዓይነቱ ጥሩ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ ያስፈልጋቸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ያሉትን መከራዎች ጊዜያዊ እንደሆኑ አድርገህ ተመልከታቸው!
በየቀኑ ለማየት የማንፈልጋቸውን ነገሮች መመልከታችን አይቀርም። መስተዋት ስንመለከት የአካላችንን አለፍጽምና የሚጠቁሙ የማንፈልጋቸውን ጉድለቶች በአካላችን ላይ እናያለን። የአምላክን ቃል እንደ መስተዋት አድርገን በመጠቀም አተኩረን ስንመለከት በራሳችንም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ መንፈሳዊ ጉድለቶችን እንመለከታለን። (ያዕቆብ 1:22-25) በተጨማሪም በየቀኑ በጋዜጣዎች ወይም በቴሌቪዥን ላይ ስለ ፍትሕ መጓደል፣ ጭካኔና አሠቃቂ ድርጊት የሚገልጹ ዘገባዎችን ስንመለከት እናዝናለን።
ሰይጣን በምናያቸው ነገሮች ምክንያት ተስፋ እንድንቆርጥ ወይም እንድንዘናጋና በእምነታችን መወላወል እንድንጀምር ይፈልጋል። ይህ እንዳይደርስብን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጴጥሮስ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና፤ ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏል” በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እንድንከተል የሰጠውን ምክር መቀበል ይኖርብናል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ኢየሱስ በማናቸውም የክርስቲያናዊ ሕይወት ዘርፍ ፍጹም ምሳሌ ይሆነናል።
ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ምሳሌያችን መሆኑን ሲያመለክት ኢየሱስ መከራ መቀበሉን ለየት አድርጎ ጠቅሷል። በእርግጥም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከባድ መከራ ደርሶበታል። ኢየሱስ የሰው ልጆች ሲፈጠሩ የይሖዋ “ዋና ሠራተኛ” የነበረ እንደ መሆኑ መጠን አምላክ ለሰው ልጆች ምን ዓላማ እንደ ነበረው በትክክል ያውቅ ነበር። (ምሳሌ 8:30, 31) ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ግን ኃጢአትና አለፍጽምና በሰው ልጆች ላይ ያስከተሉባቸውን ነገሮች በቀጥታ ተመልክቷል። በየቀኑ የሰዎችን አለፍጽምናና ድክመት ይመለከት ነበር። በተጨማሪም እነዚህ ነገሮች የሚያስከትሉትን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቋቋም ነበረበት። ይህ በጣም ፈታኝ ሆኖበት እንደ ነበር አያጠራጥርም።—ማቴዎስ 9:36፤ ማርቆስ 6:34
ኢየሱስ ሌሎች ሰዎች ሲሠቃዩ ከማየቱም በላይ በራሱም ላይ መከራ ደርሶበታል። (ዕብራውያን 5:7, 8) ይሁን እንጂ ፍጹም የሆነ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ ስለ ነበረው የጸና አቋም በመያዝ የሚያገኘውን የላቀ የማይጠፋ ሕይወት ሽልማት አሻግሮ ተመልክቷል። በዚያን ጊዜ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ የተጨነቁት የሰው ልጆች ካሉበት ጎስቋላ ሁኔታ የይሖዋ የመጀመሪያ ዓላማ ወደ ነበረው ፍጽምና የመመለስ መብት ይኖረዋል። እነዚህን የማይታዩ የወደፊት ተስፋዎች በዓይነ ሕሊናው አተኩሮ በመመልከቱ የማያቋርጡ መከራዎች ቢያጋጥሙትም ከአምላክ አገልግሎት ደስታ እንዲያገኝ አስችሎታል። ጳውሎስ ከዚህ ቆየት ብሎ “እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል [“በመከራ እንጨት” አዓት] ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጧል” በማለት ጽፏል።—ዕብራውያን 12:2
ኢየሱስ ችግሮችና ፈታኝ ሁኔታዎች ተስፋ እንዲያስቆርጡት፣ እንዲያዘናጉት ወይም እምነቱን እንዲያናጉበት አልፈቀደም። የእርሱ ደቀ መዛሙርት እንደ መሆናችን መጠን የእርሱን የላቀ ምሳሌ በቅርብ መከተል ይኖርብናል።—ማቴዎስ 16:24
ዘላለማዊ በሆኑት የማይታዩ ነገሮች ላይ አተኩር!
ኢየሱስ እንዲጸና ስላስቻለው ነገር ጳውሎስ በሚጽፍበት ወቅት “የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ [“አትኩረን በመመልከት፣” አዓት] በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ” በማለት ልንከተለው የሚገባንን አካሄድ ጠቁሞናል። (ዕብራውያን 12:1, 2) አዎን፣ ክርስቲያናዊ ሩጫችንን በተሳካ ሁኔታና በደስታ ለመሮጥ ከፊታችን ካሉት ነገሮች ባሻገር መመልከት ይኖርብናል። ይሁን እንጂ ኢየሱስን ‘አትኩረን መመልከት’ የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
አንደኛ ኢየሱስ በ1914 የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሰማይ በመግዛት ላይ ነው። እርግጥ ይህ በሥጋዊ ዓይናችን የሚታይ ነገር አይደለም። ሆኖም ኢየሱስን ‘አትኩረን ከተመለከትን’ መንፈሳዊ የማየት ችሎታችን እርሱ በአሁኑ ወቅት ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋትና ሰይጣንንና አጋንንታዊ ጭፍሮቹን ከማንኛውም እንቅስቃሴ ለማገድ እንደ ተዘጋጀ እንድንመለከት ያስችለናል። አሁንም ይበልጥ አሻግረን ስንመለከት መንፈሳዊ የማየት ችሎታችን ‘ሞት፣ ኀዘን፣ ጨኸት ወይም ሥቃይ የማይኖርበትንና የቀደመው ሥርዓት የሚያልፍበትን’ አስደሳች አዲስ ዓለም ያሳየናል።—ራእይ 19:11-16፤ 20:1-3፤ 21:4
ስለዚህ በየቀኑ ሊያጋጥሙን በሚችሉት ጊዜ ያዊ ችግሮች በጣም ከመጨነቅ ይልቅ ዓይናችንን ዘላለማዊ በሆኑት ነገሮች ላይ ለምን አንተክልም? በእምነት ዓይናችን በዚች በተበከለችዋ ምድር ላይ ካለው በሽታና ስግብግብነት ባሻገር በማየት ጤናሞች፣ ደስተኞችና አሳቢ በሆኑ ሰዎች የምትሞላውን ገነት ለምን አንመለከትም? ከአካላዊና መንፈሳዊ ጉድለቶቻችን ባሻገር በመመልከት በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከእነዚህ ነገሮች ለዘላለም ነፃ የምንሆንበትን ጊዜ ለምን አናይም? በጦርነት፣ በወንጀልና በዓመፅ ከሚከሰተው ታላቅ እልቂት ባሻገር በማየት ከሞት የተነሡ ሰዎች የይሖዋን ጽድቅና ሰላም ሲማሩ ለምን አትመለከትም?
ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስን ‘አትኩሮ መመልከት’ መንፈሳዊ የማየት ችሎታችንን ተጠቅመን የአምላክ መንግሥት በዓይን የማይታይ ቢሆንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ በሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች መካከል የፈጠረውን አንድነት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ የወንድማማች መዋደድና መንፈሳዊ ብልጽግና በትኩረት መመልከትን ይጨምራል። በጀርመን የምትገኝ አንዲት ክርስቲያን ዩናይትድ ባይ ዲቫይን ቲቺንግ የተባለውን የቪዲዮ ካሴት ከተመለከተች በኋላ እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “የቪዲዮ ካሴቱ በመላው ዓለም የሚገኙ ብዙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ከሕዝብ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ይበልጥ እንዳሰላስል ረድቶኛል። ዓመፅና ጥላቻ በሞላበት ዓለም ውስጥ ይህን የመሰለ የወንድማማች አንድነት ማግኘት ምንኛ ውድ ነው!”
ይሖዋ፣ ኢየሱስ፣ ታማኞች መላእክትና በሚልዮን የሚቆጠሩ መሰል ክርስቲያኖች ከጎንህ እንዳሉ ‘ይታይሃልን’? ይህ የሚታይህ ከሆነ ተስፋ ቆርጠህ እድገት እንዳታደርግና በክርስቲያናዊ አገልግሎት ‘የማታፈራ’ እንድትሆን ሊያደርግህ በሚችለው ‘በዚህ ዓለም አሳብ’ ከመጠን በላይ አትጨነቅም። (ማቴዎስ 13:22) ስለዚህ መንፈሳዊ ዓይንህን በተቋቋመው የአምላክ መንግሥትና ይህ መንግሥት አሁንም ሆነ ወደፊት በሚያመጣቸው በረከቶች ላይ በመትከል ኢየሱስን ‘አትኩረህ ተመልከት።’
በአሁኑ ጊዜ የማይታዩትን ነገሮች ለማየት እንድትበቃ ተጣጣር!
በአምላክ ዘላለማዊ አዲስ ዓለምና እየተፈረካከሰ ባለው በዚህ አሮጌ ዓለም መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት በመመልከት በአሁኑ ጊዜ በእምነት ዓይናችን ብቻ ማየት የምንችላቸውን ነገሮች ቃል በቃል ለማየት የምንበቃ ዓይነት ሰዎች ለመሆን የሚያስችለንን ተገቢ ጠባይ ለማሳየት መገፋፋት ይኖርብናል። ከሞት የሚነሡ እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎች ትንሣኤ በሚያገኙበት ወቅት ከመሞታቸው በፊት ካዩት ዓለም በጣም በተለየ ሁኔታ ምድር ጽድቅ የሰፈነባት ገነት ሆና ሲመለከቱ ያዩትን ማመን ያቅታቸዋል። በዚያን ጊዜ በሕይወት ተገኝተን እነዚህን ሰዎች ስንቀበላቸውና አምላክ ምን እንዳደረገ ስናስረዳቸው የምናገኘውን ደስታ በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱት!—ከኢዩኤል 2:21-27 ጋር አወዳድር።
አዎን፣ ጥሩ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ በጣም ውድ የሆነ ነገር ነው! በተጨማሪም ጥሩ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ እንደያዝን መቀጠላችን በጣም አስፈላጊ ነው። ዘወትር የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋችንን ለሌሎች ሰዎች በመናገር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ መለኮታዊ መመሪያ ለማግኘት በመጸለይ ጥሩ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ እንደያዝን ለመቀጠል እንችላለን። ይህም ከምናያቸው ነገሮች ባሻገር ለመመልከት የሚያስችለን ጥሩና አጥርቶ የሚያሳይ መንፈሳዊ የማየት ችሎታ እንዲኖረን ይረዳናል!