ባሎች—የራስነት ሥልጣንን በመጠቀም ረገድ ክርስቶስን ምሰሉ
“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው።”—1 ቆሮንቶስ 11:3
1, 2. (ሀ) የአንድ ባል ስኬታማነት በምን ሊለካ ይችላል? (ለ) የጋብቻ መሥራች አምላክ መሆኑን መቀበል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
የአንድን ባል ስኬታማነት የምትለካው በምንድን ነው? በአእምሮ ችሎታው፣ በአካላዊ ጥንካሬው አሊያም በገቢው መጠን ነው? ወይስ ሚስቱንና ልጆቹን በፍቅርና በደግነት በመያዙ? ብዙ ባሎች ሚስቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በሚይዙበት መንገድ ቢመዘኑ በዓለም መንፈስና በሰብዓዊ የአቋም ደረጃዎች ስለሚመሩ ተሳክቶላቸዋል ለማለት አያስደፍርም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በዋነኝነት፣ አምላክ የሰጠውን መመሪያ ተቀብለው በሥራ ላይ ባለማዋላቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ‘ከአዳም የወሰዳትን ዐጥንት ሴት አድርጎ ከሠራት በኋላ ወደ አዳም በማምጣት’ ጋብቻን እንደመሠረተ ይናገራል።—ዘፍጥረት 2:21-24
2 ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመኑ ለነበሩት ተቺዎች እንደሚከተለው ባለ ጊዜ የጋብቻ መሥራች አምላክ መሆኑን የሚገልጸው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እውነት መሆኑን አረጋግጧል:- “ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አድርጎ እንደ ፈጠራቸው አላነበባችሁምን? እንዲህም አለ፤ ‘ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣመራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ የተባለው በዚህ ምክንያት አይደለምን? ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር [በጋብቻ] ያጣመረውን ሰው አይለየው።” (ማቴዎስ 19:4-6) የጋብቻ ስኬታማነት የተመካው፣ ጋብቻን የመሠረተው አምላክ መሆኑን በመቀበልና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው።
ለአንድ ባል ስኬታማነት ቁልፉ ምንድን ነው?
3, 4. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ጥልቅ እውቀት እንዲኖረው ያስቻለው ምንድን ነው? (ለ) የኢየሱስ ምሳሌያዊ ሚስት ማን ነች? ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት መያዝ ይገባቸዋል?
3 ኢየሱስ የተናገራቸውን ነገሮች ማጥናትና ያደረጋቸውን ነገሮች መኮረጅ አንድ ባል ስኬታማ እንዲሆን ይረዳዋል። ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በተፈጠሩም ሆነ በጋብቻ በተጣመሩበት ወቅት ስለነበረ ስለ ጋብቻ ጥልቅ እውቀት አለው። ይሖዋ አምላክ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ” ብሎት ነበር። (ዘፍጥረት 1:26) አዎን፣ አምላክ ይህን የተናገረው ከማንም ወይም ከምንም በፊት ለፈጠረውና “በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ” ለነበረው ለኢየሱስ ነው። (ምሳሌ 8:22-30 የ1954 ትርጉም) እርሱ “ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው።” ግኡዙ አጽናፈ ዓለም ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊትም እንኳ በሕይወት ስለነበረ እርሱ ‘የአምላክ ፍጥረት መጀመሪያ’ ነው።—ቈላስይስ 1:15፤ ራእይ 3:14 የ1954 ትርጉም፤ ሉቃስ 1:26-31
4 ኢየሱስ ‘የአምላክ በግ’ ተብሎ የተጠራ ሲሆን በምሳሌያዊ መንገድ ባል እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። በአንድ ወቅት፣ አንድ መልአክ “ና፤ የበጉ ሚስት የሆነችውን ሙሽራ አሳይሃለሁ” ሲል ተናግሮ ነበር። (ዮሐንስ 1:29፤ ራእይ 21:9) ታዲያ የበጉ ሙሽራ ወይም ሚስት ማን ነች? “የበጉ ሚስት” የተባሉት በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙት በመንፈስ የተቀቡ ታማኝ ተከታዮቹ ናቸው። (ራእይ 14:1, 3) በመሆኑም፣ ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበት መንገድ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት ሊይዟቸው እንደሚገባ ምሳሌ ይሆናቸዋል።
5. ኢየሱስ ለእነማን ምሳሌ ይሆናል?
5 መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው” በማለት ኢየሱስ ለተከታዮቹ በሙሉ ምሳሌ እንደሚሆን ይገልጻል። (1 ጴጥሮስ 2:21) በተለይ ደግሞ ለወንዶች ምሳሌ ይሆናቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ ነው፤ የሴትም ራስ ወንድ ነው፤ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር ነው” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 11:3) ክርስቶስ የወንድ ራስ እንደመሆኑ መጠን ባሎች ምሳሌውን ሊኮርጁ ይገባል። በመሆኑም ቤተሰብ ስኬታማና ደስተኛ እንዲሆን ከተፈለገ የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት በተግባር መዋል ይኖርበታል። ደስተኛ ቤተሰብ ለመመሥረት፣ ኢየሱስ እንደ ሚስቱ የተቆጠሩትን ደቀ መዛሙርቱን በፍቅር እንደያዛቸው ሁሉ ባሎችም ሚስቶቻቸውን በፍቅር ሊይዟቸው ይገባል።
በትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት
6. ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር እንዴት ሊኖሩ ይገባል?
6 በመከራ በተሞላው በዚህ ዓለም፣ በተለይ ባሎች ትዕግሥትንና ፍቅርን በማንጸባረቅ እንዲሁም የጽድቅ መሥፈርቶችን በጥብቅ በመከተል ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) መጽሐፍ ቅዱስ “እናንተ ባሎች ሆይ፣ . . . ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 3:7 የ1954 ትርጉም) አዎን፣ ባሎች በትዳራቸው ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ችግር ልክ እንደ ኢየሱስ በማስተዋል ሊፈቱት ይገባል። ኢየሱስ ማንም ሰው ከደረሰበት የበለጠ ፈተና ደርሶበታል። ይሁንና የመከራው ምንጭ ሰይጣን፣ አጋንንቱና ይህ ክፉ ዓለም እንደሆኑ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። (ዮሐንስ 14:30፤ ኤፌሶን 6:12) ኢየሱስ ፈተና ሲያጋጥመው አልተገረመም። ስለዚህ ባለትዳሮችም “በሥጋቸው ላይ መከራ” ሲደርስባቸው ሊደነቁ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ ያገቡ ሰዎች መከራ ወይም ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል መጠበቅ እንዳለባቸው ይገልጻል።—1 ቆሮንቶስ 7:28 የ1954 ትርጉም
7, 8. (ሀ) ከሚስት ጋር በማስተዋል መኖር ምንን ይጨምራል? (ለ) ሚስቶች አክብሮት የሚገባቸው ለምንድን ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ ባሎች እንዴት ከሚስቶቻቸው ጋር መኖር እንዳለባቸው ሲገልጽ “ደካማ ፍጥረት ስለ ሆኑ ከሚስቶቻችሁ ጋር በማስተዋል አብራችሁ ኑሩ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 3:7 የ1954 ትርጉም) የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልግ ባል፣ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ወንዶች ያደርጉታል ብሎ እንደተነበየው ሚስቱን አይጨቁንም፤ ከዚህ ይልቅ በአክብሮት ይይዛታል። (ዘፍጥረት 3:16) ከእርሷ የበለጠ ጉልበት ቢኖረውም እንኳ ውድ እንደሆነች ንብረቱ አድርጎ ይመለከታታል እንጂ ጉልበቱን እርሷን ለመጉዳት አይጠቀምበትም። እንዲያውም ስሜቷን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁልጊዜ በአክብሮት ይይዛታል።
8 ባሎች ለሚስቶቻቸው ተገቢ አክብሮት ማሳየት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ . . . የሕይወትንም በረከት አብረዋችሁ ስለሚወርሱ አክብሯቸው” በማለት መልሱን ይሰጣል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ባሎች፣ ይሖዋ እርሱን የሚያመልክን ወንድ እርሱን ከምታመልክ ሴት አስበልጦ እንደማይመለከት ሊገነዘቡ ይገባል። የአምላክን ሞገስ ያገኙ ሴቶች ከወንዶች እኩል የዘላለም ሕይወት ሽልማት ያገኛሉ። እንዲያውም ብዙ ሴቶች “በወንድና በሴት መካከል ልዩነት” በሌለበት በሰማይ የመኖር መብት አግኝተዋል። (ገላትያ 3:28) ስለዚህ ባሎች፣ አንድ ሰው በአምላክ ዘንድ ውድ እንደሆነ የሚያስቆጥረው ወንድ ወይም ሴት፣ ባል ወይም ሚስት አሊያም ልጅ መሆኑ ሳይሆን ታማኝነቱ መሆኑን መዘንጋት አይኖርባቸውም።—1 ቆሮንቶስ 4:2
9. (ሀ) ባሎች ሚስቶቻቸውን ማክበር የሚገባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ለሴቶች አክብሮት ያሳየው እንዴት ነው?
9 ጴጥሮስ “ጸሎታችሁ እንዳይደናቀፍ” በማለት የተናገራቸው ቃላት፣ አንድ ባል ሚስቱን በአክብሮት መያዙ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላሉ። አንድ ሰው ጸሎቱ መደናቀፉ ወይም መከልከሉ በጣም አደገኛ ነው። በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ ቸልተኛ የአምላክ አገልጋዮች እንደደረሰባቸው ሁሉ አንድ ባል ሚስቱን የማያከብር ከሆነ ጸሎቱ እንዳያልፍ ሊታገድ ይችላል። (ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:43, 44) ያገቡም ሆኑ ትዳር የመመሥረት እቅድ ያላቸው ክርስቲያን ወንዶች ኢየሱስ ሴቶችን እንዴት በአክብሮት ይይዝ እንደነበር መመርመራቸው አስተዋይነት ነው። ኢየሱስ በአገልግሎት በሚዘዋወርበት ወቅት ሴቶች አብረውት እንዲሆኑ ፈቅዶላቸዋል፤ እንዲሁም በደግነትና በአክብሮት ይይዛቸው ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት አንድ አስደናቂ እውነት መጀመሪያ ለሴቶቹ ከነገራቸው በኋላ እነርሱ ደግሞ ለወንዶቹ እንዲነግሯቸው አድርጓል።—ማቴዎስ 28:1, 8-10፤ ሉቃስ 8:1-3
በተለይ ለባሎች የሚሆን ምሳሌ
10, 11. (ሀ) በተለይ ባሎች የኢየሱስን ምሳሌ መመርመር ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ባሎች ለሚስቶቻቸው ፍቅር ማሳየት የሚገባቸው እንዴት ነው?
10 ቀደም ሲል እንደተገለጸው መጽሐፍ ቅዱስ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ዝምድና ክርስቶስ ‘ከሙሽራው’ ማለትም ከቅቡዓን ተከታዮቹ ጉባኤ ጋር ካለው ዝምድና ጋር ያነጻጽረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ክርስቶስ . . . [ለ]ቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ባልም የሚስቱ ራስ ነው” ይላል። (ኤፌሶን 5:23) እነዚህ ቃላት ባሎች፣ ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ የነበረውን የራስነት ሥልጣን እንዴት እንደተጠቀመበት እንዲመረምሩ ሊያነሳሷቸው ይገባል። ባሎች የኢየሱስን ምሳሌ በሚገባ መኮረጅ እንዲሁም ኢየሱስ ለጉባኤው እንዳደረገው ሁሉ ለሚስቶቻቸው አመራር መስጠት ብሎም እነርሱን ማፍቀርና መንከባከብ የሚችሉት እንዲህ ዓይነት ምርምር ካደረጉ ብቻ ነው።
11 መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ” በማለት ያሳስባል። (ኤፌሶን 5:25) በኤፌሶን ምዕራፍ አራት ላይ “ቤተ ክርስቲያን” ወይም ጉባኤው “የክርስቶስ አካል” ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ምሳሌያዊ አካል ከሁለቱም ጾታዎች የተውጣጡ በርካታ አባላት ያሉት ሲሆን ሁሉም አካሉ በአግባቡ ተግባሩን እንዲያከናውን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። እርግጥ ነው፣ “አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ” ኢየሱስ ነው።—ኤፌሶን 4:12፤ ቈላስይስ 1:18፤ 1 ቆሮንቶስ 12:12, 13, 27
12. ኢየሱስ ለምሳሌያዊ አካሉ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?
12 ኢየሱስ የአካሉ ክፍሎች የሆኑትን ሰዎች በአሳቢነት በመንከባከብ ለምሳሌያዊ አካሉ ይኸውም ለጉባኤው ፍቅር አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል ደቀ መዛሙርቱ በደከማቸው ጊዜ “እስቲ . . . ከእኔ ጋር ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” ብሏቸው ነበር። (ማርቆስ 6:31) ከሐዋርያቱ አንዱ፣ ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ያደረጋቸውን ነገሮች ሲዘግብ “ወገኖቹን የወደዳቸውን [በምሳሌያዊ መንገድ የአካሉ ክፍሎች የሆኑትን] እስከ መጨረሻ ወደዳቸው” ብሏል። (ዮሐንስ 13:1 የ1954 ትርጉም) በእርግጥም ኢየሱስ ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ትቷል!
13. ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲወዱ ምን ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል?
13 ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስ ለባሎች የተወውን ምሳሌ መጥቀሱን በመቀጠል እንዲህ ሲል አሳስቧል:- “ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው።” አክሎም ጳውሎስ “ከእናንተ እያንዳንዱ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ” ብሏል።—ኤፌሶን 5:28, 29, 33
14. አንድ ባል ፍጽምና በሚጎድለው አካሉ ላይ ምን አያደርግም? ይህ ሁኔታ ሚስቱን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ ምን ይጠቁማል?
14 እስቲ አስበው፣ ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው የገዛ አካሉን ሆነ ብሎ የሚጎዳ ይመስልሃል? አንድ ሰው እንቅፋት ቢመታው፣ ስለተደናቀፈ እግሩን ይመታዋል? በጭራሽ! አንድ ባል በወዳጆቹ ፊት ራሱን ያዋርዳል? ወይም ደግሞ ድክመቶቹን እያነሳ ራሱን ያማል? በፍጹም እንደዚህ አያደርግም! ታዲያ ሚስቱ ስህተት ብትሠራ ክፉ ቃል መናገር ወይም ከዚያ የከፋ ነገር ማድረግ ይገባዋል? ባሎች የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የሚስቶቻቸውንም ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:24፤ 13:5
15. (ሀ) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ሰብዓዊ ድክመት ባሳዩበት ጊዜ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ምን ነገር አድርጓል? (ለ) ከዚህ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል?
15 ኢየሱስ በተገደለበት ምሽት ደቀ መዛሙርቱ ሰብዓዊ ድክመት ታይቶባቸው ነበር፤ ይሁንና ኢየሱስ በዚህ ጊዜ አሳቢነት ያሳያቸው እንዴት እንደሆነ ተመልከት። በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ በነበሩበት ጊዜ በተደጋጋሚ እንዲጸልዩ ቢነግራቸውም ሦስት ጊዜ ተኝተው አገኛቸው። በዚህ ወቅት በድንገት የታጠቁ ሰዎች ከበቧቸው። ኢየሱስም ሰዎቹን “የምትፈልጉት ማንን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስን” በማለት ሲመልሱለት፣ “እርሱ እኔ ነኝ” አላቸው። የሚሞትበት ‘ሰዓት መድረሱን’ ስላወቀ “እኔን የምትፈልጉ ከሆነ፣ እነዚህ፣ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ። ኢየሱስ የምሳሌያዊ ሙሽራው ክፍል ለሆኑት ለደቀ መዛሙርቱ ደህንነት ሳያስብ የቀረበት ጊዜ የለም፤ በዚህም ጊዜ ቢሆን ከመያዝ የሚያመልጡበትን መንገድ አመቻችቶላቸዋል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ በመመርመር ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የሚጠቁሙ በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማግኘት ይችላሉ።—ዮሐንስ 18:1-9፤ ማርቆስ 14:34-37, 41
የኢየሱስ ፍቅር በስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ አልነበረም
16. ኢየሱስ ለማርታ ምን ዓይነት ስሜት ነበረው? ሆኖም እርማት የሰጣት እንዴት ነው?
16 ኢየሱስ፣ ብዙ ጊዜ በእንግድነት ይቀበሉት የነበሩትን “ማርታን፣ እኅቷንና አልዓዛርን ይወዳቸው” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዮሐንስ 11:5) ያም ሆኖ ኢየሱስ፣ ማርታ ምግብ ለማዘጋጀት መባከኗ ከእርሱ መንፈሳዊ ትምህርት ለመቅሰም የሚያስችላትን ጊዜ እንደተሻማባት ሲመለከት አስፈላጊውን ምክር ከመስጠት ወደኋላ አላለም። በዚህ ጊዜ “ማርታ፣ ማርታ፤ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፤ ትዋከቢአለሽም፤ የሚያስፈልገው ግን አንድ ነገር ብቻ ነው” ብሏት ነበር። (ሉቃስ 10:41, 42) ማርታ ኢየሱስ ይወዳት እንደነበረ ማወቋ ምክሩን ሳታንገራግር እንድትቀበል እንዳደረጋት ግልጽ ነው። በተመሳሳይም ባሎች ሚስቶቻቸውን ለአነጋገራቸው እየተጠነቀቁ በደግነትና በፍቅር ሊይዟቸው ይገባል። እንደዚያም ሆኖ እርማት መስጠት በሚያስፈልግበት ጊዜ እንደ ኢየሱስ በግልጽ ከመናገር ወደኋላ ማለት የለባቸውም።
17, 18. (ሀ) ኢየሱስ ጴጥሮስን የገሠጸው እንዴት ነበር? ጴጥሮስ እርማት ያስፈለገው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ባል ምን ኃላፊነት አለበት?
17 በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድና “በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በኦሪት ሕግ መምህራን እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣ ዘንድ እንደሚገባው” ለሐዋርያቱ ገለጸላቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን ወደ ጐን ሳብ አድርጎ “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” እያለ ይገሥጸው ጀመር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጴጥሮስ ስሜታዊ ሆኖ ነበር። ስለሆነም እርማት አስፈልጎት ነበር። ኢየሱስም “አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለ ሌለ መሰናክል ሆነህብኛል!” አለው።—ማቴዎስ 16:21-23
18 ኢየሱስ መከራን መቀበሉና መገደሉ የአምላክ ፈቃድ መሆኑን እየገለጸላቸው ነበር። (መዝሙር 16:10፤ ኢሳይያስ 53:12) ስለሆነም ጴጥሮስ ኢየሱስን መገሠጹ ስህተት ነበር። አዎን፣ እኛም አልፎ አልፎ እንደሚያስፈልገን ሁሉ ጴጥሮስ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሊሰጠው ይገባ ነበር። ባል የቤተሰቡ ራስ እንደመሆኑ መጠን ሚስቱን ጨምሮ የቤተሰቡን አባላት የማረም ሥልጣንም ሆነ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። ጥብቅ መሆን የሚያስፈልግበት ጊዜ ቢኖርም እርማቱ መሰጠት ያለበት በደግነትና በፍቅር ነው። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ አመለካከቱን እንዲያስተካክል እንደረዳው ሁሉ ባሎችም ከሚስቶቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት አልፎ አልፎ እንዲሁ ማድረግ ያስፈልጋቸው ይሆናል። ለምሳሌ ያህል አንድ ባል የሚስቱ አለባበስ ወይም አጋጌጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው አንጻር ልከኛ እንዳልሆነ ሲሰማው አንዳንድ ማስተካከያዎችን እንድታደርግ በደግነት ሊመክራት ይችላል።—1 ጴጥሮስ 3:3-5
ባሎች ታጋሽ መሆናቸው አስፈላጊ ነው
19, 20. (ሀ) በኢየሱስ ሐዋርያት መካከል ምን ችግር ተነስቶ ነበር? ኢየሱስ ችግሩን የፈታው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ምን ያህል ተሳክቶለታል?
19 ባሎች መታረም ያለበት ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜ፣ በቀና አመለካከት ተነሳስተው ችግሩን ለማስተካከል የሚያደርጉት ጥረት ወዲያውኑ ጥሩ ውጤት ያስገኛል ብለው መጠበቅ አይኖርባቸውም። ኢየሱስ የሐዋርያቱን አመለካከት ለማስተካከል የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ ጠይቆበታል። ለምሳሌ ያህል፣ በሐዋርያቱ መካከል የነበረው የፉክክር መንፈስ በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት መገባደጃ ላይ እንደገና ታይቷል። ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ ይከራከሩ ነበር። (ማርቆስ 9:33-37፤ 10:35-45) በዚህ ጉዳይ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ከተከራከሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስ የማለፍ በዓልን ለመጨረሻ ጊዜ አብሯቸው ለማክበር ዝግጅት አደረገ። በዚህ ወቅት በአካባቢው ልማድ መሠረት አንዳቸውም እንኳ አቧራ የለበሰውን የሌሎቹን እግር በማጠብ እንደ አነስተኛ የሚቆጠረውን ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን አላቀረቡም። ኢየሱስ ግን ይህን አደረገ። ከዚያም “ምሳሌ ትቼላችኋለሁ” አላቸው።—ዮሐንስ 13:2-15
20 ልክ እንደ ኢየሱስ ትሑት የሆኑ ባሎች የሚስቶቻቸው ትብብርና ድጋፍ እንደማይለያቸው እሙን ነው። ይሁንና ታጋሽ መሆን ያስፈልጋቸዋል። ሐዋርያቱ የማለፍ በዓሉን ባከበሩበት በዚያው ምሽት ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በድጋሚ ተከራክረዋል። (ሉቃስ 22:24) በአብዛኛው አመለካከትንም ሆነ ምግባርን ማስተካከል የሚቻለው ቀስ በቀስና በጊዜ ሂደት ነው። ሆኖም በሐዋርያቱ ላይ እንደታየው ውሎ አድሮ ጥሩ ውጤት መገኘቱ ምንኛ የሚያስደስት ነው!
21. ተፈታታኝ ሁኔታዎች በበዙበት በዛሬው ጊዜ ባሎች ምን ነገር እንዳይዘነጉና ምን እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል?
21 ትዳር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይገጥሙታል። ብዙዎች የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን አክብደው አይመለከቱትም። በመሆኑም ባሎች ጋብቻ ስለተመሠረተበት መንገድ በጥልቅ ሊያስቡ ይገባል። ጋብቻን ከመሠረቱ ያቋቋመው አፍቃሪው አምላክ ይሖዋ መሆኑን አትዘንጉ። ልጁን የሰጠን ቤዛና አዳኝ እንዲሆነን ብቻ ሳይሆን ባሎች ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ እንዲሆን ጭምር ነው።—ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:29
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• የጋብቻ መሥራች ማን መሆኑን መገንዘባችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዲወዱ ማበረታቻ የተሰጣቸው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
• ባሎች የራስነት ሥልጣናቸውን በመወጣት ረገድ ክርስቶስን እንዲኮርጁ ምሳሌ የሚሆኗቸው፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘባቸው የትኞቹ መንገዶች ናቸው?
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሎች ኢየሱስ ሴቶችን እንዴት ይይዛቸው እንደነበር መመርመር ያለባቸው ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በደከማቸው ጊዜ አሳቢነት ያሳያቸው ነበር
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሎች ሚስቶቻቸውን ለአነጋገራቸው እየተጠነቀቁ በደግነት ምክር ሊሰጧቸው ይገባል