የነገሥታትን ምሳሌ ተከተል
“ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ። . . . መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፣ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።”—ዘዳግም 17:18-20
1. አንድ ክርስቲያን እነማንን መምሰል ይፈልግ ይሆናል?
ራስህን እንደ ንጉሥ አድርገህ አትቆጥር ወይም ራስሽን እንደ ንግሥት አድርገሽ አትቆጥሪ ይሆናል። ታማኝ ነገሥታት የሆኑት ዳዊት፣ ኢዮስያስ፣ ሕዝቅያስ ወይም ኢዮሣፍጥ የነበራቸው ዓይነት ንጉሣዊ ሥልጣን እንደጨበጠ አድርጎ የሚቆጥር የትኛው የታመነ ክርስቲያን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ነው? ይሁንና ቢያንስ በአንድ ሁኔታ እንደ እነርሱ መሆን ትችላለህ ደግሞም መሆን ይኖርብሃል። ይህ ምንድን ነው? በዚህ ረገድ እነርሱን ለመኮረጅ መጣር ያለብህስ ለምንድን ነው?
2, 3. ይሖዋ ሰብዓዊ ንጉሥን በሚመለከት አስቀድሞ ምን ተናግሮ ነበር? ንጉሡስ ምን እንዲያደርግ ይጠበቅበታል?
2 በሙሴ ዘመን ማለትም አምላክ ለእስራኤላውያን ሰብዓዊ ንጉሥ ከማንገሡ ከረጅም ጊዜ በፊት ሕዝቡ በንጉሥ የመገዛት ፍላጎት እንደሚያድርባቸው ተናግሮ ነበር። ስለሆነም ይሖዋ ሙሴን በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ይህን የሚመለከት መመሪያ እንዲያካትት በመንፈሱ አነሳሳው። ይህ ንጉሡ እንዲከተለው የተሰጠው መመሪያ ነበር።
3 አምላክ እንዲህ አለ:- “አምላክህ እግዚአብሔር ወደሚሰጥህ ምድር በገባህ . . . ጊዜ:- በዙሪያዬ እንዳሉት አሕዛብ ሁሉ በላዬ ንጉሥ አነግሣለሁ ስትል፣ አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሣለህ። . . . በመንግሥቱም ዙፋን በተቀመጠ ጊዜ . . . ይህን ሕግ ለራሱ በመጽሐፍ ይጻፍ። አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ . . . መጽሐፉ ከእርሱ ጋር ይኑር፣ ዕድሜውንም ሁሉ ያንብበው።”—ዘዳግም 17:14-20
4. አምላክ ለነገሥታቱ የሰጠው መመሪያ ምን ማድረግን ይጨምር ነበር?
4 አዎን፣ ይሖዋ ለአምላኪዎቹ የሚመርጥላቸው ንጉሥ አሁን በመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ ተካትቶ የምታገኘውን ሕግ ለራሱ መገልበጥ ነበረበት። ከዚያም ንጉሡ የሕጉን መጽሐፍ ደጋግሞ በየዕለቱ ማንበብ አለበት። እንዲህ የሚያደርገው የማስታወስ ችሎታውን ለማሻሻል ብሎ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሕጉን ማጥናቱ ነበር። ይህም ጠቃሚ ሚና ነበረው። የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት የሚፈልግ አንድ ንጉሥ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ለማዳበርና ያንንም ላለማጣት እንዲህ ያለውን ጥናት ማድረግ ይኖርበታል። እንዲሁም ስኬታማና አስተዋይ ንጉሥ እንዲሆን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ይህን ሕግ ማጥናት ያስፈልገዋል።—2 ነገሥት 22:8-13፤ ምሳሌ 1:1-4
እንደ ንጉሥ ተማር
5. ንጉሥ ዳዊት የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መገልበጥና ማንበብ ችሏል? ይህስ ምን ስሜት አሳድሮበታል?
5 ዳዊት በእስራኤል ላይ መንገሥ በጀመረ ጊዜ በመመሪያው መሠረት ምን ማድረግ ያስፈለገው ይመስልሃል? የኦሪት መጽሐፎችን (ዘፍጥረትን፣ ዘጸአትን፣ ዘሌዋውያንን፣ ዘኁልቊንና ዘዳግምን) መገልበጥ ነበረበት። ዳዊት ሕጉን ራሱ እያነበበ መገልበጡ በአእምሮውና በልቡ ላይ ምን ዓይነት ጥልቅ ስሜት አሳድሮበት ሊሆን እንደሚችል አስብ። በተጨማሪም ሙሴ የኢዮብን መጽሐፍ እንዲሁም መዝሙር 90ን እና 91ን ሳይጽፍ አልቀረም። ዳዊት እነዚህንም ገልብጦ ይሆን? ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የኢያሱን፣ የመሳፍንትንና የሩትን መጽሐፎች ሳያገኝ አልቀረም። ስለሆነም ንጉሥ ዳዊት ሊያነብና እውቀት ሊቀስም የሚችልባቸው በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አግኝቶ እንደነበረ ከዚህ መረዳት ትችላለህ። ዳዊት በመዝሙር 19:7-11 ላይ ስለ አምላክ ሕግ ከሰጠው አስተያየት በመነሳት የሚጠበቅበትን አድርጓል ብለህ መናገር ትችላለህ።
6. ኢየሱስ እንደ ዳዊት ለቅዱሳን ጽሑፎች ከፍ ያለ ግምት እንደነበረው እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?
6 ታላቁ ዳዊት ኢየሱስም ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። ኢየሱስ በየሳምንቱ በአካባቢው ወደሚገኝ ምኩራብ የመሄድ ልማድ ነበረው። እዚያም ቅዱሳን ጽሑፎች ሲነበቡና ማብራሪያ ሲሰጥባቸው ያዳምጥ ነበር። ከዚህም በላይ በአንድ ወቅት ከአምላክ ቃል ላይ ድምፁን ከፍ አድርጎ ለሕዝብ በማንበብ ያነበበው ነገር እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ አብራርቷል። (ሉቃስ 4:16-21) ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠንቅቆ ያውቅ እንደነበረ ከዚህ በቀላሉ መረዳት ትችላለህ። የወንጌል ዘገባዎችን አንብብና ኢየሱስ ምን ያህል ጊዜ “ተብሎ ተጽፎአል” በማለት እንደተናገረ ወይም አንዳንድ ጥቅሶችን የጠቀሰባቸውን ሌሎች መንገዶች ተመልከት። አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ማቴዎስ በወንጌሉ ላይ እንደመዘገበው ኢየሱስ ባደረገው የተራራ ስብከት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች 21 ጊዜ ጠቅሶ ተናግሯል።—ማቴዎስ 4:4-10፤ 7:29፤ 11:10፤ 21:13፤ 26:24, 31፤ ዮሐንስ 6:31, 45፤ 8:17
7. ኢየሱስ በዘመኑ ከነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ምን የተለየ አቋም ወስዷል?
7 ኢየሱስ “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ . . . ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፣ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። . . . የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” የሚለውን የመዝሙር 1:1-3ን ምክር ተግባራዊ አድርጓል። ‘በሙሴ ወንበር ላይ ተቀምጠው’ የነበረ ቢሆንም ‘የአምላክን ሕግ’ ችላ ብለው ከነበሩት የዘመኑ የሃይማኖት መሪዎች ጋር ሲወዳደር ኢየሱስ ምንኛ የተለየ አቋም ወስዷል!—ማቴዎስ 23:2-4
8. የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባቸውና ማጥናታቸው ከንቱ የነበረው ለምንድን ነው?
8 ይሁን እንጂ አንዳንዶች በዮሐንስ 5:39, 40 ላይ ያሉትን ቃላት ሲያነቡ ኢየሱስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም ብሎ እንደተናገረ አድርገው ያስቡ ይሆናል። በዚህ ጥቅስ ላይ ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች እንደሚከተለው እንዳላቸው እናነባለን:- “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።” ኢየሱስ እንዲህ ሲል አይሁዳውያን አድማጮቹ ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናት እንደማያስፈልጋቸው መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ግብዞችና በቃላቸው የማይረጉ መሆናቸውን ማጋለጡ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች ወደ ዘላለም ሕይወት እንደሚያደርሷቸው ተገንዝበዋል። ሆኖም ይመረምሯቸው የነበሩት እነዚያው መጻሕፍት ወደ መሲሑ ወደ ኢየሱስ ሊመሯቸውም ይገባ ነበር። ዳሩ ግን ኢየሱስን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። ቅኖችና ለመማር ፈቃደኞች ስላልነበሩ ጥናታቸው ምንም እርባና አልነበረውም።—ዘዳግም 18:15፤ ሉቃስ 11:52፤ ዮሐንስ 7:47, 48
9. ሐዋርያትና የጥንት ነቢያት ምን ግሩም ምሳሌ ትተዋል?
9 ሐዋርያትን ጨምሮ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የነበራቸው አመለካከት ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! ‘አንድ ሰው መዳን የሚያገኝበትን ጥበብ ሊሰጡት የሚችሉትን ቅዱሳን መጻሕፍት’ አጥንተዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) በዚህ ረገድ ‘ተግተው እየፈለጉ የመረመሩትን’ የጥንት ነቢያት መስለዋል። እነዚያ ነቢያት እንዲህ ያለውን ምርምር ያደረጉት ለወረት ያህል ለጥቂት ወራት ወይም ዓመታት ብቻ አልነበረም። በተለይ ስለ ክርስቶስና እርሱ የሰውን ዘር ለማዳን የተጫወተው ሚና ስላስገኘው ክብር ‘ይመረምሩ እንደነበር’ ሐዋርያው ጴጥሮስ ተናግሯል። ጴጥሮስ በመጀመሪያ ደብዳቤው ላይ ከአሥር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች 34 ጊዜ ጠቅሶ ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 1:10, 11
10. እያንዳንዳችን መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ፍላጎት ሊያድርብን የሚገባው ለምንድን ነው?
10 በመሆኑም የአምላክን ቃል በጥንቃቄ ማጥናት የጥንቷ እስራኤል ነገሥታት እንዲያሟሉት የሚጠበቅባቸው ንጉሣዊ ሥራ እንደነበር ግልጽ ነው። ኢየሱስም ይህን ልማድ ተከትሏል። እንዲሁም በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ነገሥታት ሆነው የሚገዙ ሰዎች ቃሉን እንዲያጠኑ ይፈለግባቸዋል። (ሉቃስ 22:28-30፤ ሮሜ 8:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:12፤ ራእይ 5:10፤ 20:6) በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር በምድር ላይ የተለያዩ በረከቶች አግኝተው ለመኖር ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎችም ለነገሥታቱ የተሰጠውን ይህን ልማድ እንዲከተሉ ይጠበቅባቸዋል።—ማቴዎስ 25:34, 46
ለነገሥታቱ የተሰጠው መመሪያ ለአንተም ይሠራል
11. (ሀ) ክርስቲያኖች በጥናት ልማድ ረገድ ቸልተኞች እንዳይሆኑ መጠንቀቅ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቃችን አስፈላጊ ነው?
11 እያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን በግሉ መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር እንደሚኖርበት ምንም አያጠያይቅም። አንድ ሰው እንዲህ ማድረግ የሚኖርበት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በሚጀምርበት ጊዜ ብቻ መሆን የለበትም። ሁላችንም በሐዋርያው ጳውሎስ ዘመን የግል ጥናታቸውን ችላ ብለው እንደነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንዳንሆን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። እነዚህ ሰዎች “የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል” የመሳሰሉትን “ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት” ተምረው ነበር። ሆኖም በጥናታቸው ስላልገፉበት “ወደ ፍጻሜ [“ወደ ጉልምስና፣” NW ]” ማደግ ሳይችሉ ቀርተዋል። (ዕብራውያን 5:12–6:3) ከዚህ የተነሳ እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ‘የክርስቲያን ጉባኤ አባል የሆንኩት በቅርቡም ይሁን ከበርካታ አሥርተ ዓመታት በፊት የአምላክን ቃል በግል ስለማጥናት ምን ይሰማኛል? ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች “በእግዚአብሔር እውቀት” እያደጉ እንዲሄዱ ጸልዮአል፤ እኔስ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት አለኝ?’—ቆላስይስ 1:9-12
12. ለአምላክ ቃል ዘወትር ፍቅር ማዳበር አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ጥሩ የጥናት ልማድ እንዲኖርህ የሚረዳህ ወሳኝ የሆነው ነገር ለአምላክ ቃል ፍቅር ማዳበር ነው። መዝሙር 119:14-16 በአምላክ ቃል ደስ መሰኘት ከፈለግህ በቃሉ ላይ ዘወትር ማሰላሰል እንደሚያስፈልግህ ይናገራል። እንግዲያው አዲስ ክርስቲያንም ሆንክ ለረጅም ዓመታት የቆየህ እንዲህ ማድረግ ይኖርብሃል። ይህን ለማጉላት የጢሞቴዎስን ምሳሌ መለስ ብለህ ተመልከት። ምንም እንኳን ይህ ክርስቲያን ሽማግሌ ‘የኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር’ የነበረ ቢሆንም “የእውነትን ቃል በቅንነት” መናገር እንዲችል ትጋት ማሳየት እንደሚኖርበት ጳውሎስ አሳስቦታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:3, 15፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:15) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ‘ትጋት’ ማሳየት ጥሩ የጥናት ልማድ መከተልን የሚጨምር ነው።
13. (ሀ) ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ተጨማሪ የጥናት ጊዜ ለማግኘት ምን ማስተካከያ ማድረግ ትችላለህ?
13 ጥሩ የጥናት ልማድ ለማዳበር መውሰድ የሚኖርብህ እርምጃ መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር ለማጥናት ጊዜ መመደብ ነው። አንተስ በዚህ ረገድ ተሳክቶልሃል? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው ትክክለኛ ምላሽ ምንም ይሁን ምን ለግል ጥናት ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ መመደብህ ጥቅም እንደሚያስገኝልህ ይሰማሃል? ‘ለዚህ ጉዳይ ጊዜ መመደብ የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አንዳንዶች ማለዳ በመነሳት ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት ችለዋል። ለ15 ደቂቃ ያህል መጽሐፍ ቅዱስን ያነብባሉ ወይም የግል ጥናት ያደርጋሉ። ለአማራጭ ያህል በሳምንታዊ ፕሮግራምህ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ ትችል ይሆን? ለምሳሌ ያህል በአብዛኞቹ የሳምንቱ ቀናት ጋዜጣ የማንበብ ወይም ማታ ማታ በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና የመከታተል ልማድ ካለህ ቢያንስ አንዱን ቀን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ብትጠቀምበት ምን ይመስልሃል? ዜና በመመልከት ፋንታ አንዱን ቀን ለ30 ደቂቃ ያህል የግል ጥናት ብታደርግ በአንድ ዓመት ውስጥ የግል ጥናት የምታደርግበት 25 ሰዓት አገኘህ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ወይም ለማጥናት ተጨማሪ 25 ሰዓት በማግኘትህ ምን ያህል እንደምትጠቀም እስቲ አስበው! ሌላም አማራጭ አለ:- በሚቀጥለው ሳምንት በእያንዳንዱ ቀን የየዕለቱ ውሎህ ምን እንደሚመስል ለማጤን ሞክር። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ወይም ጥናት የምታደርግበት ተጨማሪ ጊዜ ማግኘት እንድትችል ማስቀረት ወይም በአጭር ጊዜ መፈጸም የምትችለው ሥራ ይኖር እንደሆነ ተመልከት።—ኤፌሶን 5:15, 16
14, 15. (ሀ) የግል ጥናትን በሚመለከት ግብ ማውጣት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የትኞቹን ግቦች ማውጣት ይቻላል?
14 ጥናቱን ይበልጥ ቀላልና ማራኪ ለማድረግ ምን ሊረዳህ ይችላል? ግብ ማውጣት ይረዳሃል። ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምን ዓይነት ግቦች ማውጣት ትችላለህ? ለብዙዎች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብቦ መጨረስ መጀመሪያ ላይ ሊያወጡ የሚችሉት በጣም ጥሩ ግብ ነው። ምናልባትም እስከ አሁን የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አልፎ አልፎ በማንበብ ጥቅም አግኝተህ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ትችላለህ? በመጀመሪያ አራቱን ወንጌሎች ከዚያም የተቀሩትን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በማንበብ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ለመጨረስ ባወጣኸው ግብ ላይ መድረስ ትችላለህ። ይህ የሚያስገኘውን እርካታና ጥቅም አንድ ጊዜ ካጣጣምክ በኋላ ቀጥሎ ሙሴ የጻፋቸውን እንዲሁም እስከ አስቴር መጽሐፍ ድረስ ያሉትን የታሪክ መጽሐፎች ተራ በተራ ለማንበብ ግብ አውጣ። እነዚህን ካነበብክ በኋላ የቀሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አንብበህ መጨረስ አዳጋች እንደማይሆንብህ ትገነዘባለህ። ክርስቲያን በሆነችበት ወቅት ዕድሜዋ ወደ 65 ዓመት ገደማ የሚሆናት አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የጀመረችበትንና አንብባ የጨረሰችበትን ቀን በሽፋኑ የውስጠኛ ክፍል ላይ ትጽፍ ነበር። አሁን መጽሐፍ ቅዱስን ለአምስተኛ ጊዜ ተወጥታዋለች! (ዘዳግም 32:45-47) በተጨማሪም ከኮምፒውተር ወይም በኮምፒውተር ከታተመ ወረቀት ላይ ከማንበብ ይልቅ በቀጥታ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የማንበብ ልማድ አላት።
15 መጽሐፍ ቅዱስን አንብበው ለመጨረስ ያወጡት ግብ ላይ የደረሱ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ቀጣዩ ጥናታቸውን ይበልጥ ውጤታማና መልሶ የሚክስ ለማድረግ ሌሎች ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። አንደኛው ዘዴ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በቅደም ተከተል ማንበብ ከመጀመራቸው በፊት ለማጥኛነት የመረጧቸውን ጽሑፎች ማንበብ ነው። “ ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ጠቃሚ ነው” እና ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባሉትን መጽሐፎች በማንበብ ስለ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ታሪካዊ መቼት፣ የአጻጻፍ ዘይቤና ስለያዘው ጥቅም ግሩም እውቀት ማግኘት ይቻላል።a
16. መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ የእነማንን ምሳሌ ከመኮረጅ መቆጠብ ይኖርብናል?
16 በምታጠናበት ጊዜ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ተብዬዎች የሚከተሉትን ስልት ከመኮረጅ ተቆጠብ። እነዚህ ምሁራን መጽሐፍ ቅዱስ የሰው አእምሮ ያመነጨው መጽሐፍ ይመስል ትኩረታቸው ሁሉ ያረፈው ግምገማ በማካሄድ ላይ ነው። እያንዳንዱ መጽሐፍ ለተወሰኑ አንባብያን ብቻ ታስቦ እንደተጻፈ አድርገው ይናገራሉ ወይም ጸሐፊዎቹ ይዘውት የተነሡትን ዓላማና አመለካከት በተመለከተ የራሳቸውን አስተያየት ለመስጠት ይሞክራሉ። እንዲህ ዓይነቱ ሰብዓዊ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ተራ የታሪክ መጽሐፍ ወይም በሃይማኖት ላይ ደረጃ በደረጃ ለውጥ ያስከተሉ የመጽሐፎች ስብስብ እንደሆነ ተደርጎ እንዲቆጠር ሊያደርግ ይችላል። ሌሎች ምሁራን ደግሞ በቃላት ላይ ትኩረት አድርገው ማጥናት ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ላይ የሚደረገውን ጥናት ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። የአምላክ ቃል በሚያስተላልፈው ቁም ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ በቃላቱ አመጣጥ እንዲሁም በዕብራይስጥና በግሪክኛው ትርጉማቸው ላይ ማተኮር ያስደስታቸዋል። ታዲያ እንዲህ ያለው የአጠናን ስልት ጥልቀት ያለውና ለተግባር የሚያንቀሳቅስ እምነት የሚያስገኝ ይመስልሃል?—1 ተሰሎንቄ 2:13
17. መጽሐፍ ቅዱስ ለሁሉም ሰው የሚሆን መልእክት አለው እንድንል የሚያስችለን ምንድን ነው?
17 የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን የደረሱበት መደምደሚያ ተቀባይነት አለው? እያንዳንዱ መጽሐፍ በአንድ ነጥብ ላይ ብቻ ያተኩራል ወይም የተጻፈው ለተወሰኑ አንባብያን ብቻ ነው የሚለው ሐሳብ እውነተኝነት አለው? (1 ቆሮንቶስ 1:19-21) ሐቁ እንደሚያሳየው የአምላክ ቃል የያዛቸው መጽሐፎች በሁሉም የዕድሜ ክልል ለሚገኙና የተለያየ አስተዳደግ ላላቸው ሰዎች በእኩል ደረጃ ጠቃሚ መሆናቸው ነው። ምንም እንኳን መጽሐፉ በመጀመሪያ የተጻፈው ጢሞቴዎስን ወይም ቲቶን ለመሳሰሉ ግለሰቦች አሊያም በቡድን ደረጃ ለገላትያ ወይም ለፊልጵስዩስ ሰዎች ቢሆንም ሁላችንም እነዚህን መጽሐፎች ማጥናት እንችላለን፤ ማጥናትም ይገባናል። እያንዳንዳችን እነዚህን መጽሐፎች በማንበብ የምንጠቀም ሲሆን አንዱ መጽሐፍ ብዙ ጭብጦችን የሚዳስስና ለብዙ አንባብያን የሚጠቅም ሊሆን ይችላል። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያዘለው መልእክት በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሠራል። ይህ ደግሞ በዓለም ዙሪያ ባሉ ቋንቋዎች መተርጎም ያስፈለገበትን ምክንያት እንድንረዳ ያስችለናል።—ሮሜ 15:4
አንተም ሆንክ ሌሎች የምታገኙት ጥቅም
18. የአምላክን ቃል በምታነብበት ጊዜ በየትኞቹ ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል ትችላለህ?
18 መጽሐፍ ቅዱስን በምታጠናበት ጊዜ የምታነበውን ለማስተዋል እንዲሁም ዝርዝር ጉዳዮች እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት በግልጽ ለመረዳት ጥረት ማድረግህ በጣም ይጠቅምሃል። (ምሳሌ 2:3-5፤ 4:7) ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የገለጸው ነገር ከዓላማው ጋር የቅርብ ዝምድና አለው። ስለሆነም በምታነብበት ጊዜ የምታገኘውን እውቀትና ምክር ከዓላማው ጋር አገናዝብ። የምታነበው ታሪክ፣ ሐሳብ ወይም ትንቢት ከይሖዋ ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ማሰላሰል ትችላለህ። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘እያነበብኩት ያለው ነገር ስለ ይሖዋ ምን ያሳውቀኛል? በመንግሥቱ አማካኝነት ፍጻሜውን ከሚያገኘው የአምላክ ዓላማ ጋር ምን ግንኙነት አለው?’ በተጨማሪም ‘ይህን እውቀት እንዴት ልጠቀምበት እችላለሁ? ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀስኩ ሌሎችን ለማስተማር ወይም ለመምከር ልጠቀምበት እችላለሁ?’ እያልክ ማሰላሰል ትችላለህ።—ኢያሱ 1:8
19. የተማርካቸውን ነገሮች ለሌሎች በመናገርህ እነማን ሊጠቀሙ ይችላሉ? አብራራ።
19 በምታጠናበት ጊዜ ሌሎች ሰዎችን በአእምሮህ መያዝህ ሌላም ጠቀሜታ አለው። መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበትና በምታጠናበት ጊዜ አዲስ እውቀትና አዲስ ማስተዋል ታገኛለህ። ከቤተሰቦችህ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር በምታደርገው የሚያንጽ ጭውውት ያገኘኸውን እውቀት አንስተህ ለመናገር ሞክር። ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜና ከልክ ሳያልፍ እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ጭውውቱ ጠቃሚ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከንባብህ ስላገኘኸው እውቀት ወይም ስለተደሰትህበት ነገር ከልብ ተነሳስተህ በስሜት የምታወራ ከሆነ የምትናገረው ነገር ሌሎችን የሚማርክ ሊሆን ይችላል። ከዚህም በላይ እንዲህ በማድረግህ አንተም ራስህ ትጠቀማለህ። እንዴት? በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉ ሰዎች እንደተናገሩት አንድ ሰው የተማረውን ወይም ያነበበውን ወዲያውኑ የሚሠራበት ወይም ለሌሎች ሰዎች የሚናገር ከሆነ ለረዥም ጊዜ ሊያስታውሰው ይችላል።b
20. መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግሞ ማንበብ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
20 አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ አንብበህ በጨረስህ ቁጥር አዲስ እውቀት መቅሰምህ አይቀርም። ከዚህ በፊት እምብዛም አስተውለሃቸው የማታውቃቸውን ጥቅሶች ስታገኝ በጣም ትገረማለህ። እውቀትህ እየጨመረ ይሄዳል። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች የሰው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ውጤት ሳይሆኑ ደጋግመን እንድናጠናቸውና እንድንጠቀምባቸው ተብሎ የተዘጋጁ መሆናቸውን የሚያጎላ ነው። እንደ ዳዊት ያለ ንጉሥ ‘ዕድሜውን ሁሉ ማንበብ’ ይጠበቅበት እንደነበረ አትዘንጋ።
21. የአምላክን ቃል ይበልጥ ባጠናህ ቁጥር ምን በረከቶች ልታገኝ ትችላለህ?
21 አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ለማጥናት ጊዜ የሚመድቡ ሰዎች ይህ ነው የማይባል ጥቅም ያገኛሉ። መንፈሳዊ ዕንቁዎችና ማስተዋል ያገኛሉ። ከአምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና እየተጠናከረና እየጠበቀ ይሄዳል። ለቤተሰቦቻቸው፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላሉ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ወደፊት የይሖዋ አምላኪ ለሚሆኑ ሰዎች ይበልጥ ጠቃሚ እሴቶች ይሆናሉ።—ሮሜ 10:9-14፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a እነዚህ ለጥናት የሚያገለግሉ ጽሑፎች የተዘጋጁት በይሖዋ ምሥክሮች ሲሆን በአማርኛ ባይገኙም እንኳ በሌሎች በርካታ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል።
b የነሐሴ 15, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 13-14ን ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
• የእስራኤል ነገሥታት ምን እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸው ነበር?
• ኢየሱስና ሐዋርያት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን በሚመለከት ምን ምሳሌ ትተዋል?
• የግል ጥናት የምታደርግበትን ጊዜ ለመጨመር ምን ማስተካከያ ማድረግ ትችላለህ?
• በአምላክ ቃል ላይ ምርምር የምታደርግበት ዓላማ ምን መሆን ይኖርበታል?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“መጽሐፉን ገልጦ ማንበብን የሚያክል የለም”
“አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ፈልጎ ለማግኘት . . . ከኢንተርኔት የተሻለ መሣሪያ ልናገኝ አንችልም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን አንብበን፣ አጥንተን፣ መርምረን፣ አሰላስለን በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ እንዲቀረጽ ለማድረግ ግን መጽሐፉን ገልጦ ማንበብን የሚያክል የለም።”—ኒው ዮርክ በሚገኘው የሲቲ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂ ፕሮፌሰር የነበሩት ገርትሩድ ሂመልፋርብ