ማንኛውንም መንፈሳዊ ድካም ማወቅና ማሸነፍ የሚቻልበት መንገድ
በግሪካውያን አፈ ታሪክ መሠረት በትሮጃን ጦርነት ማለትም የትሮይን ከተማ ለመቆጣጠር በተካሄደው ዘመቻ ከተሰለፉት የግሪክ ጦረኞች መካከል የላቀ ጀግንነት ያሳየ አኪሊዝ የሚባል ሰው ነበር። አኪሊዝ ሕፃን ሳለ እናቱ በስቲክስ ወንዝ ውስጥ እንደነከረችውና ከዚህም የተነሳ ከመላ ሰውነቱ ለአደጋ የተጋለጠው የእናቱ እጅ ያረፈበት ቦታ ብቻ እንደሆነ አፈ ታሪኩ ይገልጻል። ይህ ለአደጋ የተጋለጠው የሰውነቱ ክፍል በእንግሊዝኛ አኪሊዝ ሂል በሚል ምሳሌያዊ አነጋገር ይታወቃል። የትሮይ ንጉሥ የፕሪያም ልጅ የሆነው ፓሪስ የወረወረው አደገኛ ፍላጻ አኪሊዝን ወግቶ የገደለው ልክ እዚህ ቦታ ላይ ነበር።
ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ውጊያ ላይ የተሰለፉ የክርስቶስ ወታደሮች ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 2:3) ሐዋርያው ጳውሎስ “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” ሲል ገልጿል። አዎን፣ ጠላቶቻችን ከሰይጣን ዲያብሎስና ከአጋንንቱ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም።—ኤፌሶን 6:12
‘ብርቱ ተዋጊ’ ተብሎ ከተገለጸው ከይሖዋ አምላክ እርዳታ ባናገኝ ኖሮ ውጊያው የማይመጣጠን ይሆን እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘጸአት 15:3) ጨካኝ ከሆኑት ጠላቶቻችን ራሳችንን የምንከላከልበት መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ተሰጥቶናል። ሐዋርያው “የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ” ሲል ያሳሰበን በዚህ ምክንያት ነው።—ኤፌሶን 6:11
ይሖዋ አምላክ ያዘጋጀልን የጦር ትጥቅ ማንኛውንም ዓይነት መንፈሳዊ ጥቃት መቋቋም የሚችል ከፍተኛ ጥራት ያለው ትጥቅ እንደሆነ አያጠራጥርም። ጳውሎስ የሰጠውን ዝርዝር ተመልከቱ:- የእውነት መታጠቂያ፣ የጽድቅ ጥሩር፣ የሰላም ወንጌል መጫሚያ፣ የእምነት ጋሻ፣ የመዳን ራስ ቁር፣ እንዲሁም የመንፈስ ሰይፍ። አንድ ሰው ከዚህ የተሻለ ምን ዓይነት ትጥቅ ሊመኝ ይችላል? እንዲህ ዓይነቱን የጦር ትጥቅ የታጠቀ አንድ ክርስቲያን ወታደር አደገኛ ባላንጣ ቢያጋጥመውም እንኳ በድል አድራጊነት ሊወጣ ይችላል።—ኤፌሶን 6:13-17
ምንም እንኳ ይሖዋ ያዘጋጀው መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ የላቀ ጥራት ያለውና ከለላ ሊሆንልን የሚችል ቢሆንም ነገሮችን አቅልለን መመልከት አይገባንም። ሊሸነፍ አይችልም ተብሎ የተወራለትን አኪሊዝ ወደ አእምሯችን እናምጣና እኛም መንፈሳዊ አኪሊዝ ሂል ማለትም ደካማ ጎን ሊኖረን ይችል ይሆን? ተዘናግተን ከተገኘን ለሕይወታችን እንኳ አደገኛ ሊሆን ይችላል።
መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችሁን ፈትሹ
በበረዶ ላይ ሸርተቴ ሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነ ከፍተኛ የአካል ብቃት የነበረው አንድ ሰው በልምምድ ላይ ሳለ ምን ነካው ሳይባል ተዝለፍልፎ ወደቀና ሞተ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ አንድ አስደንጋጭ ዜና ይዞ ወጣ:- “ሃርት አታክ በተባለ የልብ ሕመም በየዓመቱ ከሚጠቁት 600,000 አሜሪካውያን ውስጥ ግማሾቹ አስቀድሞ ምንም የበሽታው ምልክት አይታይባቸውም።” በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው የጤንነታችን ሁኔታ እንዲሁ በሚሰማን ነገር ብቻ ሊታወቅ አይችልም።
መንፈሳዊ ጤንነታችንን በተመለከተም ነገሩ ተመሳሳይ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ሲል ይመክራል። (1 ቆሮንቶስ 10:12) ምንም እንኳ መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን ምርጥ ቢሆንም ለአደጋ የተጋለጠ የሆነ ቦታ ሊኖረው ይችላል። ይህ የሆነበት ምክንያት ኃጢአተኛ ሆነን ስለምንወለድና ኃጢአተኛ የሆነውና አለፍጽምና የወረሰው ተፈጥሯችን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ በቀላሉ ስለሚያሸንፈው ነው። (መዝሙር 51:5) ምንም እንኳ ምኞታችን ጥሩ ነገር ማድረግ ቢሆንም ተንኮለኛ የሆነው ልባችን ድክመታችንን በቸልታ እንድናልፍና በጥሩ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ በማሰብ ራሳችንን እንድናታልል ከእውነታው የራቀ ምክንያትና ሰበብ በመፍጠር ሊያዘናጋን ይችላል።—ኤርምያስ 17:9፤ ሮሜ 7:21-23
በተጨማሪም የምንኖረው ትክክልና ስህተት ለሆነው ነገር በአብዛኛው ግራ የሚያጋባና የተዛባ ትርጉም በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ነው። አንድ ነገር ትክክል ወይም ስህተት መሆኑ የሚወሰነው በሰውየው ስሜት ሊሆን ይችላል። የንግድ ማስታወቂያዎች፣ ተወዳጅ መዝናኛዎችና መገናኛ ብዙሐን እንዲህ ዓይነቱን አስተሳሰብ ያስፋፋሉ። በእርግጥም፣ ጠንቃቆች ካልሆንን እንዲህ ያለ ዝንባሌ ልናዳብርና መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችንን ማላላት ልንጀምር እንችላለን።
በእንዲህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳንወድቅ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መከተል አለብን። (2 ቆሮንቶስ 13:5) እንዲህ ስናደርግ ማንኛውንም ዓይነት ሥር የሰደደ ድክመት ማግኘትና ጠላቶቻችን ድክመቶቻችንን አውቀው ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች በመውሰድ ድክመቶቻችንን ማስወገድ እንችላለን። ሆኖም ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው? ራሳችንን በምንመረምርበት ጊዜ ማየት የምንፈልጋቸው አንዳንድ የበሽታ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የበሽታ ምልክቶቹን ለይቶ ማወቅ
መንፈሳዊ ድክመትን የሚጠቁም አንድ የተለመደ የበሽታ ምልክት በግል ጥናት ልማድ ረገድ ቸልተኛ መሆን ነው። አንዳንዶች የግል ጥናታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ቢሰማቸውም አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ግን ያቅታቸዋል። ዛሬ ያለው በሩጫ የተሞላ ሕይወት እንዲህ ባለው መጥፎ ሁኔታ ውስጥ በቀላሉ ሊጥል ይችላል። ከሁሉ የከፋው ደግሞ አንዳንዴ ሲያመቻቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስለሚያነቡና በአንዳንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ስለሚገኙ አብዛኛውን ጊዜ እንዲያው ያን ያህል እንዳልተሳነፉ ይሰማቸዋል።
እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ራስን መደለያ ነው። ጉዳዩ በሥርዓት ቁጭ ብሎ ለመመገብ ጊዜ እንደሌለው ከሚሰማው ሰው ሁኔታ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይህ ሰው ከአንድ ጉዳይ ወደ ሌላው ሲሮጥ፣ እግረ መንገዱን የሚቀመስ ነገር አፉ ላይ ያደርጋል። ረሃብ ባያጠቃውም እንኳ ይዋል ይደር እንጂ የጤና እክል ሊያጋጥመው ይችላል። በተመሳሳይም ዘወትር ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ የማንመገብ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን የሳሳና ለአደጋ የሚያጋልጥ ቦታ ሊኖረው ይችላል። ዘወትር ዓለማዊ የሆነ ፕሮፓጋንዳና ዝንባሌ ጥቃት ስለሚደርስብን ገዳይ በሆኑ የሰይጣን ጥቃቶች በቀላሉ ልንሸነፍ እንችላለን።
ሌላው የመንፈሳዊ ድካም ምልክት በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ የጥድፊያ ስሜት ማጣት ነው። ሰላም በሚሆንበት ጊዜ አንድ ወታደር ጦር ሜዳ በፍልሚያ ላይ ሲሆን የሚሰማው ዓይነት የውጥረትና የስጋት ስሜት አይኖረውም። በመሆኑም ዝግጁ ሆኖ መጠባበቅ ይህን ያህል አጣዳፊ እንዳልሆነ ሊሰማው ይችላል። ድንገት ለውጊያ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ ቢቀርብለት ዝግጁ ላይሆን ይችላል። በመንፈሳዊ ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። የጥድፊያ ስሜታችን እንዲቀዘቅዝ ከፈቀድን የሚሰነዘሩብንን ጥቃቶች ለመመከት ዝግጁ ላንሆን እንችላለን።
ይሁን እንጂ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ መውደቅ አለመውደቃችንን እንዴት ማወቅ እንችላለን? በትክክል አቋማችንን ሊያሳውቁን የሚችሉ አንዳንድ ጥያቄዎች ለራሳችን ማቅረብ እንችላለን:- ሽርሽር ለመውጣት የምጓጓውን ያህል በአገልግሎት ለመካፈል እጓጓለሁ? ለመገብየት ወይም ቴሌቪዥን ለመመልከት ጊዜ የሚኖረኝን ያህል ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት ጊዜ እንዲኖረኝ ፈቃደኛ ነኝ? ክርስቲያን በሆንኩበት ጊዜ የተውኳቸው አንዳንድ ግቦች ወይም አጋጣሚዎች ይቆጩኛል? የተደላደለ ኑሮ የሚባለው የሌሎች አኗኗር ያስቀናኛል? እነዚህ እውነታውን ለማወቅ የሚረዱ ጥያቄዎች በመሆናቸው መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን የት ጋ መጠገን እንደሚያስፈልገው ለመጠቆም ይረዳሉ።
መከላከያ የጦር ትጥቃችን መንፈሳዊ ስለሆነ የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ እንደልብ መፍሰስ መቻሉ አስፈላጊ ነው። ይህ በምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የአምላክ መንፈስ ፍሬዎችን በምናሳይበት መጠን ይንጸባረቃል። የማትወድደውን ነገር ሌሎች ሲያደርጉ ወይም ሲናገሩ በቀላሉ ትጎዳለህ፤ ይባስ ብሎም ትናደዳለህ? ምክር መቀበል ይከብድሃል፤ ወይም ሌሎች ሁልጊዜ በአንተ ላይ ስህተት የሚለቃቅሙ ሆኖ ይሰማሃል? ሌሎች ሰዎች ባገኟቸው በረከቶች ወይም የሥራ ውጤቶች ትመቀኛለህ? ከሌሎች ጋር በተለይ ደግሞ ከእኩዮችህ ጋር ተስማምቶ መኖር ይከብድሃል? በሐቀኝነት ራሳችንን መመርመራችን ሕይወታችን በአምላክ መንፈስ ፍሬዎች የተሞላ መሆኑን ወይም ደግሞ የሥጋ ሥራዎች በስውር ማቆጥቆጥ መጀመራቸውን ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል።—ገላትያ 5:22-26፤ ኤፌሶን 4:22-27
መንፈሳዊ ድካምን ለማሸነፍ የሚረዱ አዎንታዊ እርምጃዎች
የመንፈሳዊ ድካም ምልክቶችን ማስተዋል አንድ ነገር ሲሆን፣ ድክመቶቹን መጋፈጥና ነገሮችን ለማቅናት እርምጃ መውሰድ ደግሞ ፈጽሞ የተለየ ነገር ነው። የሚያሳዝነው ብዙዎች ድክመቶቻቸውን ለማስተካከል ከመጣር ይልቅ ሰበብ ማቅረብ፣ ማመካኘት፣ ችግሩን ማቃለል ወይም ችግሩን ፈጽሞ መካድ ይቀናቸዋል። ይህ ዝንባሌ ያልተሟላ የጦር ትጥቅ ለብሶ ወደ ጦር ሜዳ የመሄድ ያህል አደገኛ ነው! እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ለሰይጣን ጥቃት አጋልጦ ይሰጠናል። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም ዓይነት ጉድለት ስናይ በቶሎ ለማስተካከል አዎንታዊ እርምጃዎች መውሰድ አለብን። ምን ማድረግ እንችላለን?—ሮሜ 8:13፤ ያዕቆብ 1:22-25
የምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ የአንድን ክርስቲያን አእምሮና ልብ ለመማረክ የሚደረግ ጥረት የሚያካትት ፍልሚያ እንደመሆኑ መጠን አእምሯችንንም ሆነ ልባችንን ለመጠበቅ የሚቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። ከመንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን መካከል ልባችንን ለመጠበቅ የሚያገለግለው ‘የጽድቅ ጥሩር’ እና አእምሯችንን የሚጠብቅልን ‘የመዳን ራስ ቁር’ እንደሚገኙ አስታውሱ። ድል ማድረጋችን ወይም አለማድረጋችን የተመካው እነዚህን መንፈሳዊ የጦር ትጥቆች ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም በመቻላችን ወይም ባለመቻላችን ላይ ነው።—ኤፌሶን 6:14-17፤ ምሳሌ 4:23፤ ሮሜ 12:2
‘የጽድቅን ጥሩር’ በአግባቡ መልበስ ለጽድቅ ያለንን ፍቅርና ለክፋት ያለንን ጥላቻ በተመለከተ ዘወትር ራስን መመርመር ይጠይቃል። (መዝሙር 45:7፤ 97:10፤ አሞጽ 5:15) አቋማችን ከዚህ ዓለም የአቋም ደረጃ ጋር አብሮ አሽቆልቁሏል? በፊት በእውን ወይም በቴሌቪዥንና በፊልም እንዲሁም በመጻሕፍትና በመጽሔቶች ላይ ሲቀርቡ ያሳፍሩን ወይም ያስጸይፉን የነበሩ ነገሮች አሁን አስደሳች ሆነው አግኝተናቸዋል? ለጽድቅ ያለን ፍቅር ይህ ዓለም እንደ ነጻነትና ስልጣኔ አድርጎ የሚያወድሰው ነገር በስውር ልክስክስነትና እብሪት መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል።—ሮሜ 13:13, 14፤ ቲቶ 2:12
‘የመዳንን ራስ ቁር’ መልበስ የዚህ ዓለም ብልጭልጭ መስህቦች እንዲያዘናጉን ላለመፍቀድ ከፊታችን ያሉትን ግሩም በረከቶች በአእምሯችን ብሩህ አድርጎ መያዝን ያጠቃልላል። (ዕብራውያን 12:2, 3፤ 1 ዮሐንስ 2:16) ይህ ዓይነቱን አመለካከት መያዛችን ከቁሳዊ ንብረት ወይም ከግል ጥቅም ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳዮችን እንድናስቀድም ይረዳናል። (ማቴዎስ 6:33) በመሆኑም ይህን የጦር ትጥቅ በአግባቡ መታጠቃችንን ለማረጋገጥ በሐቀኝነት ለራሳችን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማቅረብ አለብን:- ግብ አድርጌ የያዝኩት ነገር ምንድን ነው? የተወሰኑ መንፈሳዊ ግቦች አሉኝ? እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ምን እያደረግሁ ነው? ቅቡዓን ክርስቲያን ቀሪዎችም ሆንን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ ክፍል ጳውሎስ “እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፣ . . . ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ” ሲል የተናገረውን ልንኮርጅ ይገባል።—ራእይ 7:9፤ ፊልጵስዩስ 3:13, 14
ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ የጦር ትጥቃችን የሰጠውን መግለጫ የቋጨው በሚከተለው ምክር ነው:- “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ።” (ኤፌሶን 6:18) ይህ ሐሳብ ማንኛውንም ዓይነት መንፈሳዊ ድካም ማሸነፍ ወይም መከላከል የምንችልባቸውን ሁለት ጠቃሚ እርምጃዎች ይገልጻል:- ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ማጎልበትና ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ነው።
‘በጸሎት ሁሉ’ (ኃጢአታችንን ስንናዘዝ፣ ይቅርታ እንዲደረግልን ስንለምን፣ አመራር ለማግኘት ስንጠይቅ፣ ላገኘናቸው በረከቶች ስናመሰግን፣ ልባዊ ውዳሴ ስናቀርብ) እና “ዘወትር” (በሕዝብ ፊት፣ ለብቻችን፣ በግላችን፣ ልባችን ሲያነሳሳን) ወደ ይሖዋ የመቅረብ ልማድ ሲኖረን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንመሠርታለን። ይህ ከሁሉ የላቀ ጥበቃ ሊሆንልን ይችላል።—ሮሜ 8:31፤ ያዕቆብ 4:7, 8
በሌላ በኩል “ስለ ቅዱሳን ሁሉ” ይህም ማለት ለመሰል ክርስቲያኖች እንድንጸልይ ተመክረናል። ስደትና ልዩ ልዩ መከራ የሚደርስባቸውን በሌሎች አገሮች የሚኖሩ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንን በጸሎት ልናስታውስ እንችላለን። ሆኖም በሥራም ሆነ በየቀኑ ለምናገኛቸው ክርስቲያኖችስ ምን ማድረግ እንችላለን? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደጸለየ ሁሉ እነርሱን ጠቅሰን መጸለያችን ተገቢ ነው። (ዮሐንስ 17:9፤ ያዕቆብ 5:16) እንዲህ ዓይነቶቹ ጸሎቶች እርስ በርስ እንድንቀራረብ ከማስቻላቸውም በላይ ‘የክፉውን’ ጥቃት መቋቋም እንድንችል ያጠናክሩናል።—2 ተሰሎንቄ 3:1-3
በመጨረሻም የሐዋርያው ጴጥሮስን ፍቅራዊ ምክር ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም:- “የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፣ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።” (1 ጴጥሮስ 4:7, 8) የሌሎች ሰዎችም ሆነ የራሳችን ሰብዓዊ አለፍጽምና ልባችንና አእምሯችን ውስጥ ሰርጎ በመግባት እንቅፋት ወይም የመሰናከያ ድንጋይ እንዲሆንብን መፍቀዱ በጣም ቀላል ነው። ሰይጣን ይህን ሰብዓዊ ድካም አሳምሮ ያውቃል። ከፋፍለህ ግዛ የሚለው መርኅ ከሚጠቀምባቸው መሰሪ ዘዴዎች አንዱ ነው። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ኃጢአቶችን አንዳችን ለሌላው ባለን የጠበቀ ፍቅር ለመሸፈን ፈጣን መሆንና ‘ለዲያብሎስ ፈንታ ከመስጠት’ መራቅ አለብን።—ኤፌሶን 4:25-27
ከአሁኑ በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሁኑ
ፀጉርህ አለመበጠሩን ወይም ክራቫትህ መንጋደዱን ብትመለከት ምን ታደርጋለህ? በተቻለ ፍጥነት ነገሮችን እንደምታስተካክል የታወቀ ነው። ይህ ዓይነቱ ከላይ የሚታይ እንከን ምንም ለውጥ አያመጣም በሚል ስሜት መስተካከል ያለበትን ነገር እንዳለ የሚተዉ ጥቂት ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። መንፈሳዊ ድክመቶቻችንን በሚመለከትም ከዚህ በማይተናነስ አፋጣኝ ምላሽ እንስጥ። ውጫዊ እንከኖች ሰዎች በንቀት እንዲያዩን ሊያደርጉ ይችሉ ይሆናል፤ ማስተካከያ ያልተደረገላቸው መንፈሳዊ ጉድለቶች ግን የይሖዋን ሞገስ ሊያሳጡን ይችላሉ።—1 ሳሙኤል 16:7
ይሖዋ ማንኛውንም መንፈሳዊ ድካም እንድናስወግድና በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንድንሆን የሚረዳንን ነገር ሁሉ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ሰጥቶናል። ይሖዋ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች እንዲሁም በጎለመሱና አሳቢ በሆኑ መሰል ክርስቲያኖች አማካኝነት ማድረግ ያለብንን ነገር ለማሳወቅ ዘወትር ማሳሰቢያዎችና ጥቆማዎች ይሰጠናል። እነዚህን ተቀብሎ በሥራ ማዋል የእኛ ፋንታ ነው። ይህ ጥረትና ራስን መገሰጽ ይጠይቃል። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ ሳይሸሽግ የተናገረውን አስታውስ:- “እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፣ ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ።”—1 ቆሮንቶስ 9:26, 27
መንፈሳዊ የአኪሊዝ ሂል እንዲያቆጠቁጥ ላለመፍቀድ ንቁ ሁኑ። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም መንፈሳዊ ድካም ለማወቅና ለማሸነፍ አሁኑኑ በትሕትናና በቆራጥነት አስፈላጊ የሆነውን ነገር እናድርግ።
[ከገጽ 19 የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ።”—2 ቆሮንቶስ 13:5
[ከገጽ 21 የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።”—1 ጴጥሮስ 4:7, 8
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ራስህን ጠይቅ . . .
◆ ገበያ ለመውጣት ወይም ቴሌቪዥን ለመመልከት የምጓጓውን ያህል ለስብሰባዎች ለመዘጋጀት እጓጓለሁ?
◆ የተደላደለ ኑሮ በሚባለው የሌሎች አኗኗር እቀናለሁ?
◆ ሰዎች የማልወደውን ነገር ሲያደርጉ ወይም ሲናገሩ በቀላሉ እበሳጫለሁ?
◆ ምክር መቀበል ይከብደኛል? ወይም ሌሎች ሁልጊዜ በእኔ ላይ ስህተት እንደሚለቃቅሙ ይሰማኛል?
◆ ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መኖር ይከብደኛል?
◆ የአቋም ደረጃዬ ከዓለም የአቋም ደረጃ ጋር አብሮ በማሽቆልቆል ላይ ነው?
◆ ልደርስባቸው የምፈልጋቸው መንፈሳዊ ግቦች አሉኝ?
◆ መንፈሳዊ ግቦቼ ላይ ለመድረስ ምን እያደረግሁ ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
አኪሊዝ:- ግሬት ሜን ኤንድ ፌመስ ዉመን ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ፤ የሮማ ወታደሮችና ገጽ 21:- Historic Costume in Pictures/Dover Publications, Inc., New York