ለጢሞቴዎስ የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ
2 እንግዲህ ልጄ+ ሆይ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በሚገኘው ጸጋ አማካኝነት በርታ፤* 2 ከእኔ የሰማኸውንና ብዙዎች የመሠከሩለትን ነገር፣+ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ። 3 የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር+ እንደመሆንህ መጠን አንተም በበኩልህ መከራ ተቀበል።+ 4 ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ማንኛውም ሰው ለውትድርና የመለመለውን ሰው ደስ ማሰኘት ስለሚፈልግ ራሱን በንግድ ሥራ* አያጠላልፍም። 5 በውድድር የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው የውድድሩን ደንብ ጠብቆ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አይሸለምም።+ 6 ጠንክሮ የሚሠራ ገበሬ ከፍሬው የመጀመሪያው ተቋዳሽ መሆን አለበት። 7 ለምናገረው ነገር ምንጊዜም ትኩረት ስጥ፤ ጌታም በሁሉም ነገር ማስተዋል ይሰጥሃል።
8 ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ+ እንዲሁም የዳዊት ዘር+ እንደሆነ አስታውስ፤ እኔም የምሰብከው ምሥራች ይህ ነው፤+ 9 ከዚህም የተነሳ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሬ መከራ እየተቀበልኩ ነው፤ ደግሞም ታስሬአለሁ።+ ሆኖም የአምላክ ቃል አልታሰረም።+ 10 ከዚህም የተነሳ የተመረጡትም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት የሚገኘውን መዳን ከዘላለማዊ ክብር ጋር ያገኙ ዘንድ ለእነሱ ስል ሁሉንም ነገር በጽናት ተቋቁሜ እኖራለሁ።+ 11 የሚከተለው ቃል እምነት የሚጣልበት ነው፦ አብረን ከሞትን አብረን ደግሞ በሕይወት እንደምንኖር የተረጋገጠ ነው፤+ 12 ጸንተን ከኖርን አብረን ደግሞ እንነግሣለን፤+ ብንክደው እሱም ይክደናል፤+ 13 ታማኞች ሆነን ባንገኝ እሱ ምንጊዜም ታማኝ ሆኖ ይኖራል፤ እሱ ራሱን ሊክድ አይችልምና።
14 ስለ ቃላት እንዳይነታረኩ በአምላክ ፊት እየመከርክ* እነዚህን ነገሮች ዘወትር አሳስባቸው፤ እንዲህ ያለው ነገር በሚሰሙት ሰዎች ላይ ጉዳት ከማስከተል* በስተቀር ምንም ጥቅም የለውም። 15 የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም፣ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚገባውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ ራስህን በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።+ 16 ሆኖም ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮች ራቅ፤+ እንዲህ ያሉ ንግግሮች* ሰዎች ይበልጥ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው እየሆኑ እንዲሄዱ ያደርጋሉና፤ 17 እንዲህ ያሉ ንግግሮችን የሚናገሩ ሰዎች ቃላቸው እንደተመረዘ ቁስል ይሰራጫል። ከእነሱም መካከል ሄሜኔዎስና ፊሊጦስ ይገኙበታል።+ 18 እነዚህ ሰዎች ‘ትንሣኤ ቀደም ብሎ ተከናውኗል’ ብለው በመናገር ከእውነት ርቀዋል፤+ ደግሞም የአንዳንዶችን እምነት እያፈረሱ ነው። 19 ይሁን እንጂ “ይሖዋ* የእሱ የሆኑትን ያውቃል”+ እንዲሁም “የይሖዋን* ስም የሚጠራ ሁሉ+ ከክፋት ይራቅ” የሚል ማኅተም ያለበት ጠንካራው የአምላክ መሠረት ጸንቶ ይኖራል።
20 በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ ሳይሆን የእንጨትና የሸክላ ዕቃም ይኖራል፤ አንዳንዱ ክብር ላለው ዓላማ የሚያገለግል ሲሆን ሌላው ግን ክብር ለሌለው ዓላማ ያገለግላል። 21 እንግዲህ ማንም ከእነዚህ ከኋለኞቹ ነገሮች ቢርቅ ክብር ላለው ዓላማ የሚያገለግል፣ የተቀደሰ፣ ለባለቤቱ የሚጠቅምና ለመልካም ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ መሣሪያ* ይሆናል። 22 ስለዚህ ከወጣትነት ምኞቶች ሽሽ፤ ከዚህ ይልቅ በንጹሕ ልብ ጌታን ከሚጠሩት ጋር ጽድቅን፣ እምነትን፣ ፍቅርንና ሰላምን ለማግኘት ተጣጣር።
23 በተጨማሪም ጠብ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ ሞኝነትና አላዋቂነት ከሚንጸባረቅበት ክርክር ራቅ።+ 24 የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውምና፤ ከዚህ ይልቅ ለሰው ሁሉ ገር፣*+ ለማስተማር ብቁ የሆነና በደል ሲደርስበት ራሱን የሚገዛ፣+ 25 እንዲሁም ቀና አመለካከት የሌላቸውን በገርነት* የሚያርም ሊሆን ይገባዋል።+ ምናልባትም አምላክ ትክክለኛ የእውነት እውቀት ያገኙ ዘንድ+ ለንስሐ* ያበቃቸው ይሆናል፤ 26 እነሱም ዲያብሎስ ፈቃዱን ያደርጉ ዘንድ በሕይወት እንዳሉ አጥምዶ እንደያዛቸው+ በመረዳት ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ከእሱ ወጥመድ ሊወጡ ይችላሉ።