የአምላክን መንጋ በውዴታ ጠብቁ
“ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ . . . በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ . . . ጎብኙት።” — 1 ጴጥሮስ 5:2
1. ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንደ እረኛ በመሆን ‘የአምላክን መንጋ በውዴታ ይጠብቃሉ’ ብለን መጠበቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
ይሖዋ በውዴታው እንደ እረኛ ሆኖ ሕዝቦቹን ይጠብቃል። (መዝሙር 23:1–4) “መልካም እረኛ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በግ መሰል ለሆኑት ሰዎች ሲል ፍጹም ሰብአዊ ሕይወቱን በውዴታው ሰጥቷል። (ዮሐንስ 10:11–15) ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ‘የአምላክን መንጋ በውዴታ እንደ እረኛ ሆነው እንዲጠብቁ’ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። — 1 ጴጥሮስ 5:2
2. የክርስቲያን ሽማግሌዎችን የእረኝነት እንቅስቃሴ በተመለከተ ልንመረምራቸው የሚገቡ ምን ጥያቄዎች ናቸው?
2 በውዴታ መሥራት የአምላክ አገልጋዮች ዓይነተኛ ምልክት ነው። (መዝሙር 110:3 አዓት) ነገር ግን አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ወይም የበታች እረኛ ሆኖ እንዲሾም በውዴታ መሥራቱ ብቻ በቂ አይደለም። እንደዚህ ዓይነት እረኞች ለመሆን ብቁ የሚሆኑት እነማን ናቸው? የእረኝነት ሥራቸው ምን ነገሮችንስ ይጨምራል? የእረኝነት ሥራቸውንስ የሚያከናውኑበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ምንድን ነው?
ቤትን ማስተዳደር
3. አንድ ክርስቲያን ወንድ ለቤተሰቡ ያለው አያያዝ በጉባኤ ውስጥ እረኛ ለመሆን ብቁ ለመሆኑና ላለመሆኑ ተጽዕኖ ያሳድራል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
3 አንድ ሰው “የበላይ ተመልካች” ሆኖ ከመሾሙ በፊት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ማሟላት አለበት። (1 ጢሞቴዎስ 3:1–7፤ ቲቶ 1:5–9) አንደኛ ነገር ሐዋርያው ጳውሎስ አንድ የበላይ ተመልካች “ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር” መሆን አለበት ብሏል። ይህንንም ለማለት ጥሩ ምክንያት አለ፤ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፣ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል?” (1 ጢሞቴዎስ 3:4, 5) ቲቶ በቀርጤስ ደሴት በሚገኘው ጉባኤ ሽማግሌዎችን በሚሾምበት ጊዜ “የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሆነ፣ ስድ በመሆንና ባለመታዘዝ ምክንያት የማይወቀሱ አማኞች ልጆች ያሉት ሰው” ፈልጎ እንዲሾም ተነግሮት ነበር። (ቲቶ 1:6 የ1980 ትርጉም ) አዎ፣ አንድ ክርስቲያን ወንድ ጉባኤን በእረኝነት የመጠበቅ ከባድ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ መሆኑንና አለመሆኑን ለመወሰን ቤተሰቡን እንዴት አድርጎ እንደሚይዝ መታየት አለበት።
4. ዘወትር ከሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ጸሎት በተጨማሪ ክርስቲያን ወላጆች ለቤተሰባቸው ፍቅር የሚያሳዩት እንዴት ነው?
4 ቤተሰባቸውን በመልካም የሚያስተዳድሩ ወንዶች ዘወትር ከቤተሰባቸው ጋር አብረው ከመጸለይና መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናት የበለጠ ነገር ያደርጋሉ። የሚያፈቅሯቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ሁልጊዜ ዝግጁዎች ናቸው። ወላጆች ይህን ማድረግ የሚጀምሩት ልጅ ከወለዱበት ቀን ጀምሮ ነው። ክርስቲያን ወላጆች አምላካዊ የሆኑ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ይበልጥ አጥብቀው ከተከተሉ ልጆቻቸውም በዕለታዊ ኑሮአቸው የክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች ፕሮግራም ውስጥ በመግባት ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያውቃሉ። አንድ ክርስቲያን አባት በእነዚህ ሁኔታዎች ረገድ ጥሩ አድርጎ የሚያስተዳድር መሆኑ ሽማግሌ ለመሆን ያለውን ብቃት ያንጸባርቃል። — ኤፌሶን 5:15, 16፤ ፊልጵስዩስ 3:16
5. አንድ ክርስቲያን አባት ልጆቹን “በጌታ [በይሖዋ አዓት] ምክርና በተግሣጽ” ማሳደግ የሚችለው እንዴት ነው?
5 ቤቱን በማስተዳደር ረገድ ንቁ የሆነ ክርስቲያን አባት “ልጆቻችሁን በጌታ [በይሖዋ አዓት] ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” የሚለውን የጳውሎስ ምክር አጥብቆ ይከተላል። (ኤፌሶን 6:4) ሚስትንና ልጆችን ጨምሮ ከቤተሰቡ ጋር የሚደረግ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፍቅራዊ መመሪያ ለመስጠት አጋጣሚ ይሰጣል። በዚህ መንገድ ልጆቹ ‘ተግሣጽ’ ወይም የእርማት ትምህርት ያገኛሉ። በዚህ ጊዜ የሚገኘው “ምክር” እያንዳንዱ ልጅ ይሖዋ ስለ ነገሮች ያለውን አመለካከት ወደ ማወቅ እንዲደርስ ይረዳዋል። (ዘዳግም 4:9፤ 6:6, 7፤ ምሳሌ 3:11፤ 22:6) የተዝናና ሁኔታ ባለበት በዚህ መንፈሳዊ ስብሰባ ወቅት አሳቢ የሆነ አባት ልጆቹ በሚናገሩበት ጊዜ በጥንቃቄ ያዳምጣል። በደግነት የሚቀርቡ ወደ መልሱ የሚመሩ ጥያቄዎች ስለሚያሳስቧቸው ነገሮችና ስለ ዝንባሌአቸው እውነቱን ገልጸው እንዲናገሩ ለማድረግ ያገለግላሉ። አባትዬው በልጆቻቸው ለጋ አእምሮ ውስጥ የሚመላለሰውን ሁሉ እንደሚያውቅ አድርጎ አይገምትም። በእርግጥም ምሳሌ 18:13 “ሳይሰማ ነገርን በሚመልስ ስንፍናና እፍረት ይሆንበታል” ይላል። አብዛኞቹ ወላጆች ዛሬ ልጆቻቸውን የሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች እነሱ ልጆች በነበሩበት ጊዜ ከገጠሟቸው ሁኔታዎች በጣም የተለዩ ሆነው አግኝተዋቸዋል። ስለዚህ አንድ አባት ችግሩ እንዴት መፈታት እንዳለበት ከመናገሩ በፊት የችግሩን መንስዔና ዝርዝር ሁኔታውን ለማወቅ ይጥራል። — ከያዕቆብ 1:19 ጋር አወዳድር።
6. አንድ ክርስቲያን አባት ቤተሰቡን በሚረዳበት ጊዜ የአምላክን ቃል መመልከት የሚኖርበት ለምንድን ነው?
6 አንድ ሰው የልጆቹን ችግር፣ ጭንቀትና ዝንባሌ ካወቀ በኋላ ምን ያደርጋል? በመልካም የሚያስተዳድር አባት ምን ማድረግ እንዳለበት ምክር ለማግኘት “ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር” የሚጠቅሙትን ቅዱሳን ጽሑፎች ይመረምራል። ልጆቹ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው ያስተምራቸዋል። በዚህ መንገድ እነዚህ በለጋ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች “ለማንኛውም በጎ ሥራ የተሟላ ብቃትና ሙሉ ዝግጅት” ያላቸው ይሆናሉ። — 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17 አዓት ፤ መዝሙር 78:1–4
7. ክርስቲያን አባቶች ጸሎትን በተመለከተ ምን ምሳሌ መተው ይኖርባቸዋል?
7 አምላካዊ የሆኑ ወጣቶች ከዓለማዊ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው ጋር የተያያዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል። ታዲያ ክርስቲያን አባቶች የልጆቻቸውን ፍርሃት ሊያቃልሉላቸው የሚችሉት እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ዘወትር ከእነሱ ጋር ሆነው ስለእነርሱ መጸለይ ነው። እነዚህ ወጣቶች ፈታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ ወላጆቻቸው ያላቸውን ከአምላክ ድጋፍ ለማግኘት የመፈለግ ባሕርይ ሊቀስሙ ይችላሉ። አንዲት የ13 ዓመት ልጃገረድ ራስዋን ለአምላክ መወሰንዋን በጥምቀት ከማሳየቷ በፊት ቃለ መጠይቅ ሲደረግላት የትምህርት ቤት ጓደኞቿ ይቀልዱባትና ይሰድቧት እንደነበረ ተናግራለች። ስለ ደም ቅድስና ያላትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነቷን በተመለከተ ለሚቀርብባት ተቃውሞ መልስ በምትሰጥበት ጊዜ ሌሎች ልጃገረዶች ይመቷትና ይተፉባት ነበር። (ሥራ 15:28, 29) አጸፋውን ትመልስ ነበርን? በፍጹም። “የተረጋጋሁ ሆኜ እንድቀጥል ይሖዋ እንዲረዳኝ መጸለዬን አላቋረጥኩም ነበር” በማለት አስረድታለች። “በተጨማሪም ክፉ ነገር ሲደርስብን ራሳችንን መግታት አስፈላጊ ስለመሆኑ ወላጆቼ በቤተሰብ ጥናት ያስተማሩኝን አስታወስኩ።” — 2 ጢሞቴዎስ 2:24
8. ልጆች የሌሉት አንድ ሽማግሌ ቤቱን በመልካም የሚያስተዳድር ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
8 ልጆች የሌሉት አንድ ሽማግሌም በቤቱ ውስጥ ላሉት ሰዎች በቂ መንፈሳዊና ሰብአዊ ምግብ ሊያቀርብላቸው ይችላል። ይህም የትዳር ጓደኛውንና በቤቱ ውስጥ የሚኖሩ ምናልባትም በሥሩ የሚተዳደሩ ክርስቲያን ዘመዶቹን ይጨምራል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) እንግዲያው በመልካም ማስተዳደር የጉባኤ ሽማግሌ በመሆን ኃላፊነት የሚሸከም ሰው ሊያሟላቸው ከሚገቡት ብቃቶች አንዱ ነው። ታዲያ የተሾሙ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ያላቸውን የኃላፊነት መብት እንዴት መመልከት ይኖርባቸዋል?
“በትጋት” አስተዳድሩ
9. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለተሰጣቸው ተግባር ምን ዝንባሌ መያዝ ይኖርባቸዋል?
9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ ራስነት ሥር በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መጋቢ ሆኖ አገልግሎ ነበር። (ኤፌሶን 3:2, 7፤ 4:15) እሱም በተራው በሮም የሚገኙትን የእምነት ጓደኞቹን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል:- “እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር።” — ሮሜ 12:6–8
10. የአምላክን መንጋ በእረኝነት በመጠበቅ ረገድ ጳውሎስ ዛሬ ላሉት ሽማግሌዎች ምን ምሳሌ ትቶላቸዋል?
10 ጳውሎስ በተሰሎንቄ ያሉትን ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል አሳሰባቸው:- “ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፣ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁ።” (1 ተሰሎንቄ 1:1፤ 2:11, 12) ማሳሰቢያው የተሰጠው ዓይነት በለዘበና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ስለነበረ ጳውሎስ እንዲህ ለማለት ችሏል:- “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።” (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) ከጳውሎስ አባታዊ ምሳሌ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ለወንድሞቻቸው ጥቅም ታማኝ የሆኑ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ላሉት ሁሉ በጥልቅ ያስባሉ።
11. የተሾሙ ሽማግሌዎች ለሥራ ያላቸውን ዝግጁነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
11 ታማኝ ክርስቲያን እረኞቻችን የበላይ ጥበቃቸውን በርኅራኄና ለመርዳት ዝግጁ በመሆን ያከናውናሉ። የሚያሳዩት ሁኔታ ብዙ መልእክት ያስተላልፋል። ጴጥሮስ ሽማግሌዎች የአምላክን መንጋ እንደ እረኞች ሆነው ሲጠብቁ ይህን ተግባራቸውን “በግድ” ወይም “መጥፎውን ረብ በመመኘት” እንዳያደርጉት ጴጥሮስ መክሯል። (1 ጴጥሮስ 5:2) የሃይማኖታዊ ትምህርት ተመራማሪ የሆኑት ዊልያም ባርክሌይ በዚህ ነጥብ ላይ እንዲህ በማለት አጭር ማስጠንቀቂያ ጽፈዋል:- “አንድ ሰው የእረኝነትን ኃላፊነት ተቀብሎ እንደሚያስከፋና ደስ የማይል ተግባር እንደሆነ፣ አሰልቺ እንደሆነ፣ እያጉረመረመ የሚሸከመው ነገር አድርጎ በመመልከት ሥራውን ያከናውን ይሆናል። አንድ ሰው አንድን ነገር እንዲሠራ ይጠየቅ ይሆናል። ሥራውንም ሊሠራ ይችላል። ነገር ግን እየተነጫነጨ ቢሠራው ጠቅላላ ሥራው ይበላሻል። ይሁን እንጂ [ጴጥሮስ] እያንዳንዱ ክርስቲያን ሥራውን ለመሥራት የማይበቃ እንደሆነ የሚሰማው ቢሆንም እንኳን እንዲህ የመሰለውን ሥራ ለማከናወን እየተንቀጠቀጠ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ አለበት።”
በውዴታ የሚሠሩ እረኞች
12. ክርስቲያን ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውን በውዴታ ለማገልገል ያላቸውን አቋም ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?
12 በተጨማሪም ጴጥሮስ ‘በሥራችሁ ያለውን የአምላክን መንጋ በውዴታ እንደ እረኞች ሆናችሁ ጠብቁት’ በማለት አጥብቆ ያሳስባል። ለበጎቹ የሚጨነቅ አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች እንዲህ የሚያደርገው በፈቃደኝነት፣ በራሱ ነፃ ፈቃድ፣ በመልካሙ እረኛ በኢየሱስ ክርስቶስ መመሪያ ሥር በመሆን ነው። ከዚህም በተጨማሪ “በውዴታ” ማገልገል ማለት አንድ ክርስቲያን እረኛ ‘የነፍሳችን እረኛና የበላይ ተመልካች’ ለሆነው ለይሖዋ ሥልጣን ይገዛል ማለት ነው። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን እረኛ ‘የነፍሳችን እረኛና ጠባቂ’ የሆነውን የይሖዋን ሥልጣን ይቀበላል። (1 ጴጥሮስ 2:25) አንድ ክርስቲያን የበታች እረኛ ለቲኦክራቲካዊ ዝግጅት በውዴታው አክብሮት ያሳያል። ይህንንም የሚያደርገው ምክር የሚፈልጉትን ሰዎች የአምላክ ቃል ወደሆነው ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በመምራት ነው። ምንም እንኳን የብዙ ዓመት ተሞክሮ አንድን ሽማግሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ብዙ ምክሮችን ለማካበት ቢያስችለውም ለማንኛውም ችግር ከመቅጽበት ቅዱስ ጽሑፋዊ መፍትሔ ይመጣለታል ማለት ግን አይደለም። የጥያቄውን መልስ የሚያውቀው ቢሆንም እንኳን ከጠያቂው ጋር በመሆን የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ማውጫ ወይም ተመሳሳይ ማውጫዎችን መመልከቱ ጥበብ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። እንዲህ በማድረግም በሁለት መንገዶች ትምህርት ይሠጣል፤ ይኸውም ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን እንዴት ማግኘት እንደሚቻል በማሳየትና የአምላክ ድርጅት ወዳወጣችው ጽሑፍ እንዲያተኩር በማድረግ በትህትና ለይሖዋ ያለውን አክብሮት በማሳየት ነው።
13. ሽማግሌዎች ትክክለኛ ምክር ለመስጠት ምን እርምጃዎችን ሊወስዱ ይችላሉ?
13 የቀረበለትን ጉዳይ በተመለከተ በማኅበሩ ጽሑፎች ላይ ምንም የወጣ ነገር ከሌለ አንድ ሽማግሌ ምን ማድረግ ይችላል? ጥልቅ ማስተዋል እንዲያገኝ እንደሚጸልይና ለጉዳዩ የሚሠሩ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት ፍለጋ እንደሚያደርግ ምንም አያጠራጥርም። በተጨማሪም እርዳታ የሚፈልገው ሰው የኢየሱስን ምሳሌዎች እንዲያስብበት ሐሳብ ማቅረብ ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኘው ይችላል። ሽማግሌው እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል:- “ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ አንተ ባለህበት ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ ነበር ብለህ ታስባለህ?” (1 ቆሮንቶስ 2:16) በዚህ መንገድ ጠያቂውን ማመራመሩ የጥበብ ውሳኔ እንዲያደርግ ሊረዳው ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ሽማግሌ የራሱን ሐሳብ እንደ ትክክለኛ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር አድርጎ ቢያቀርብ ምንኛ ጥበብ የጎደለው ይሆናል! ከዚህ ይልቅ ከባድ ችግሮች ሲያጋጥሙ ሽማግሌዎች እርስ በርሳቸው ሊወያዩባቸው ይችላሉ። እንዲያውም አበይት የሆኑ ጉዳዮችን በሽማግሌዎች አካል ስብሰባ ላይ እንዲወያዩባቸው ሊያቀርቡ ይችላሉ። (ምሳሌ 11:14) በስብሰባው ላይ የተደረጉት ውሳኔዎች በአንድ ቃል እንዲናገሩ ያስችሏቸዋል። — 1 ቆሮንቶስ 1:10
የዋህነት በጣም አስፈላጊ ነው
14, 15. ሽማግሌዎች ‘ሳያውቀው አንዳንድ የተሳሳቱ እርምጃዎችን የወሰደን’ አንድ ክርስቲያን በሚያስተካክሉበት ጊዜ ምን ይፈለግባቸዋል?
14 አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ሌሎችን ሲያስተምር በተለይም ምክር በሚሰጣቸው ጊዜ የዋህነትን ማሳየት ያስፈልገዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይመክረናል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፣ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት።” (ገላትያ 6:1) እዚህ ላይ “አቅኑት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል ዕድሜ ልኩን አካለ ስንኩል ሆኖ እንዳይቀር አጥንትን ወደ ቦታው መመለስን ለመግለጽ የሚያገለግለውን የቀዶ ሕክምና ቃል ያመለክታል። የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ደብልዩ ኢ ቫይን ይህንን ሁኔታ “በኃጢአት ምክንያት ቦታቸውን የሳቱትን የመንፈሳዊ አካል ክፍሎቸ መንፈሳውያን በሆኑት” አማካኝነት ወደ ቦታቸው ከመመለስ ጋር ያዛምዱታል። ሌሎች ትርጉሞች ደግ ሞ “ወደ ትክክለኛ ቦታው መመለስ፤ ወደ ትክክለኛ መሥመር ማምጣት” የሚሉት ናቸው።
15 የራስን አስተሳሰብ ማስተካከል ከባድ ነው፤ የአንድን የተሳሳተ ሰው አስተሳሰብ ወደ ትክክለኛው መሥመር መልሶ ማምጣት ደግሞ በጣም አዳጋች ሊሆን ይችላል። ሆኖም በየዋህነት መንፈስ የቀረበ እርዳታ ጥሩ ተቀባይነት ይኖረዋል። ይህም በመሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ” የሚለውን የጳውሎስን ምክር መስማትና መከተል ይኖርባቸዋል። (ቆላስይስ 3:12) ማስተካከያ እንዲደረግለት የሚያስፈልገው ግለሰብ መጥፎ አመለካከት ያለው በሚሆንበት ጊዜ ሽማግሌዎች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ‘የዋህነትን መከተል’ አለባቸው። — 1 ጢሞቴዎስ 6:11
መንጋውን በጥንቃቄ መጠበቅ
16, 17. ሽማግሌዎች ሌሎችን በሚመክሩበት ጊዜ ራሳቸውን ከምን አደጋዎች መጠበቅ ይኖርባቸዋል?
16 በገላትያ 6:1 ላይ ያለው የጳውሎስ ምክር ሌላ ነገርም ይጨምራል። ጳውሎስ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸውን እንዲህ በማለት አጥብቆ ያሳስባል:- “እናንተ እንደዚህ ያለውን [ስህተት የሠራውን] ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት፤ አንተ ደግሞ እንዳትፈተን ራስህን ጠብቅ።” እንዲህ ዓይነቱን ምክር ሰሚ ጆሮ ካጣ ውጤቱ እንዴት አስከፊ ይሆናል! አንድ የአንግሊካን ቄስ ከሚያገለግሏቸው ሁለት ምዕመናን ጋር ዝሙት ፈጽመው ተገኙ በሚለው ሪፖርት ተገፋፍቶ ዘ ታይምስ የተባለው የለንደን ጋዜጣ “አባታዊ ወይም ወንድማዊ ሁኔታ እያሳየ የመጣው ምክር ሰጪ እምነቷን በሱ ላይ ጥላ ከተጠጋችው ሴት ጋር ሲሆን ለሚያጋጥመው ፈተና መሸነፉ ለዘመናት ሲከሰት የኖረ ችግር ነው” ብሏል። ከዚያም የዚህ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ፒተር ረተር የተናገሩትን በመጥቀስ “በበሽተኞችና በወንድ አማካሪዎቻቸው መካከል ይኸውም በበሽተኞችና በሐኪሞቻቸው፣ በጠበቆቻቸው፣ በቄሶቻቸውና በአሠሪዎቻቸው መካከል ያለውን ሁኔታዎች የፈጠሩትን አጋጣሚ ለራስ ጥቅም ማርኪያ ማድረግ የጾታ ብልግና መፈጸም ይፋ ያልወጣ ጎጂና ወራዳ የሆነ ወረርሺኝ ነው” ብለዋል።
17 እንዲህ ዓይነቶቹ ፈተናዎች የይሖዋን ሕዝቦች በፍጹም አይነኳቸውም ብለን መገመት አይኖርብንም። ለብዙ ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግል የነበረ አንድ የተከበረ ሽማግሌ አንዲት ባለትዳር እኅት ብቻዋን በነበረችበት ጊዜ የእረኝነት ጉብኝት በማድረጉ በሥነ ምግባር ብልግና ውስጥ ወድቋል። ምንም እንኳን ይህ ወንድም ንስሐ ቢገባም የአገልግሎት መብቶቹን ሁሉ አጥቷል። (1 ቆሮንቶስ 10:12) ታዲያ የተሾሙ ሽማግሌዎች ፈተና ላይ በማይጥል መንገድ የእረኝነት ጉብኝታቸውን ማከናወን የሚችሉት እንዴት ነው? ለጸሎት እንዲሁም የአምላክን ቃልና ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ለመመልከት በመጠኑ ገለል ያለ ቦታ እንዴት ሊያዘጋጁ ይችላሉ?
18. (ሀ) የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋል ሽማግሌዎች አቋምን በማላላት ወራዳ ድርጊት ወደመፈጸም ከሚገፋፉ ነገሮች እንዲርቁ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ለአንዲት እኅት የእረኝነት ጉብኝት በሚያስፈልግበት ጊዜ ምን ዝግጅቶች ሊደረጉ ይችላሉ?
18 ሽማግሌዎች ሊያስቡበት የሚያስፈልጋቸው አንድ ነገር የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:3) አንድ ወጣት ምክር ከጠየቀ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ወላጆቹ በውይይቱ ውስጥ እንዲገቡ ጥረት አድርጉ። አንዲት ባለትዳር እኅት መንፈሳዊ እርዳታ በምትጠይቅበት ጊዜ በጉብኝቱ ወቅት ባሏ እንዲገኝ ዝግጅት ለማድረግ ትችላላችሁን? ይህ የማይቻል ከሆነስ? ወይም ባሏ የማያምንና በአንዳንድ መንገድ የሚያጎሳቁላት ከሆነስ? እንግዲያው ለአንዲት ላላገባች እኅት የእረኝነት ጉብኝት በሚደረግበት ጊዜ እንደምታደርጉት ተመሳሳይ የሆነ ዝግጅት አድርጉ። መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሁለት ወንድሞች አንድ ላይ ሆነው እኅትን ቢጎበኟት ጥበብ ይሆናል። ይህ አመቺ ካልሆነ ሁለቱ ወንድሞች በመንግሥት አዳራሹ ትንሽ ገለል ባለ ክፍል ውስጥ እንዲያወያዩአት ተስማሚ የሆነውን ጊዜ መምረጥ ይቻላል። በአዳራሹ ውስጥ ሌሎች ወንድሞችና እኅቶች ስለሚኖሩ ማሰናከያ የሚሆን ምንም ነገር አይኖርም። እርግጥ እነዚህ ወንድሞችና እኅቶች እየተካሄደ ያለውን ውይይት ለማየትና ለመስማት አይችሉም። — ፊልጵስዩስ 1:9, 10
19. የአምላክን በጎች በውዴታ እንደ እረኛ ሆኖ መጠበቅ ምን ጥሩ ውጤቶችን ያስገኛል? በውዴታቸው የሚያገለግሉንን እረኞች በማግኘታችን ምስጋናችንን የምንገልጸውስ ለማን ነው?
19 የአምላክን በጎች በውዴታ መጠበቅ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። መንጋው በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ትክክለኛ አቅጣጫ ይዞ የሚጓዝ መንጋ ይሆናል። እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ በዘመናችን ያሉት ክርስቲያን ሽማግሌዎችም የእምነት ጓደኞቻቸው ሁኔታ በጣም ያሳስባቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:28) በእነዚህ አስጨናቂ ቀኖች በተለይ የአምላክን ሕዝቦች እንደ እረኛ ሆኖ የመጠበቁ ኃላፊነት ከባድ ነው። ስለዚህ ሽማግሌዎች ሆነው በሚያገለግሉት ወንድሞቻችን እየተሠራ ላለው መልካም ሥራ በእርግጥ አመስጋኞች ነን። (1 ጢሞቴዎስ 5:17) እንደ እረኞች ሆነው በውዴታቸው የሚጠብቁንን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በመስጠት ስለባረከን ‘የበጎ ስጦታ ሁሉና የፍጹም በረከት’ ሰጪ ለሆነው ለአፍቃሪው ሰማያዊ እረኛችን ለይሖዋ ምስጋና ይድረሰው። — ኤፌሶን 4:8፤ ያዕቆብ 1:17
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አንድ ሰው ቤቱን በመልካም የሚያስተዳድር ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ የክርስቲያን ሽማግሌዎች የበላይ ጥበቃ የትኞቹ ጠባዮች ሊታዩበት ይገባል?
◻ ሽማግሌዎች ምክር በሚሰጡበት ጊዜ ትህትናንና የዋህነትን ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ሌላውን በመንፈሳዊ ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የሚረዳው ነገር ምንድን ነው?
◻ ሽማግሌዎች መንጋውን በእረኝነት በሚጠብቁበት ጊዜ አቋምን በማላላት ወራዳ ድርጊት ከመፈጸም ሊርቁ የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ቤቱን የሚያስተዳድር መሆን አለበት
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያናዊ እረኝነት በየዋህነትና በአስተዋይነት መደረግ ይኖርበታል