“ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ”
“እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”—1 ጴጥሮስ 5:5
1, 2. የሰው ልጆችን ጠባይ በጥልቅ የሚነኩ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሁለት ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
የአምላክ ቃል ከሚገልጻቸው ባሕርያት መካከል እርስ በርስ የሚቃረኑ ሁለት ባሕርያት አሉ። ሁለቱም የሰውን ልጅ ጠባይ በእጅጉ ይነካሉ። አንደኛው ‘ትሕትና’ እንደሆነ ተገልጿል። (1 ጴጥሮስ 5:5) አንድ መዝገበ ቃላት ይህንን ባሕርይ “ራስን ዝቅ የማድረግ ጠባይ ወይም መንፈስ፤ ከትዕቢት ፈጽሞ የራቀ” በማለት ተርጉሞታል። ትሕትና በአምላክ አመለካከት ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ባሕርይ ነው።
2 የትሕትና ተቃራኒ ኩራት ነው። ኩራት “ለራስ ከልክ ያለፈ ግምት መስጠት፣ ሌላውን ዝቅ አድርጎ መመልከት” የሚል ፍች ተሰጥቶታል። ኩራት ራስ ወዳድ ሲሆን ሌሎች ላይ ምንም ያክል ጉዳት ያስከትል ቁሳዊ ጥቅምን፣ ዝናንና ሌሎች ጥቅሞችን ለማግኘት ከመጣጣር ወደኋላ አይልም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ባሕርይ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል አንዱን ሲገልጽ ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው’ በማለት ይናገራል። በተጨማሪም ‘አንዱ በሌላው ላይ መቅናቱ’ “ነፋስን እንደ መከተል” እንደሆነና በሞት ጊዜ ‘ምንም ሊወስድ እንደማይችል’ ይናገራል። እንዲህ ያለው የኩራት ባሕርይ በአምላክ ዘንድ ፈጽሞ የተጠላ ነው።—መክብብ 4:4፤ 5:15፤ 8:9
በመላው ዓለም እየተስፋፋ ያለ መንፈስ
3. በመላው ዓለም በመስፋፋት ላይ የሚገኘው መንፈስ ምንድን ነው?
3 ዛሬ ያለው ዓለም ተለይቶ የሚታወቀው ከሁለቱ ባሕርያት በየትኛው ነው? በመላው ዓለም ላይ ሰፍኖ ያለው መንፈስ የትኛው ነው? ዎርልድ ሚሊታሪ ኤንድ ሶሻል ኤክስፔንዲቸርስ 1996 “የ20ኛውን መቶ ዘመን ያክል አሰቃቂ . . . የዓመፅ ድርጊት የተፈጸመበት ዘመን የለም” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። በዚህ መቶ ዘመን ለፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት የሚደረገውን ፉክክር ጨምሮ ብሔራዊ፣ ሃይማኖታዊና ጎሳዊ ግጭቶች ከ100 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ለሕልፈተ ሕይወት ዳርገዋል። በግለሰቦች ላይ የሚታየው የራስ ወዳድነት ጠባይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ቺካጎ ትሪቡን “ማኅበራዊው ቀውስ በጭፍን የሚፈጸም ዓመፅን፣ ልጆች ማስነወርን፣ ፍቺን፣ ስካርን፣ ኤድስን፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች የሚወስዱትን የራስን ሕይወት የማጥፋት እርምጃን፣ አደንዛዥ ዕፅን፣ ዱርዬነትን፣ አስገድዶ መድፈርን፣ ዲቃላ መውለድን፣ ጽንስ ማስወረድን፣ የወሲብ ሥዕሎችንና ጽሑፎችን፣ . . . ውሸትን፣ ማጭበርበርን፣ የፖለቲካ ሙስናን የሚጨምር ነው። . . . በአሁኑ ጊዜ ከሥነ ምግባር አንፃር ትክክል ወይም ስህተት የሚባል ነገር የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።” በዚህም የተነሳ ዩ ኤን ክሮኒክል “ኅብረተሰቡ በመፈረካከስ ላይ ነው” ብሏል።
4, 5. የዓለም መንፈስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጊዜያችን በሚናገረው ትንቢት ላይ በትክክል የተገለጸው እንዴት ነው?
4 እነዚህ ሁኔታዎች ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ያለንበትን ዘመን አስመልክቶ ከተናገራቸው ትንቢቶች ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማሉ። “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ . . . ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4
5 ይህ ጥቅስ በዓለማችን ላይ ሰፍኖ የሚገኘውን መንፈስ በትክክል የሚገልጽ ነው። ይህ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ እኔ ልቅደም የሚል ዝንባሌ ነው። በብሔራት መካከል ያለው ፉክክር በግለሰቦች መካከል ያለው ፉክክር ነጸብራቅ ነው። ለምሳሌ ያህል ከፍተኛ የፉክክር መንፈስ በሚታይበት ስፖርት የሚካፈሉ በርካታ ስፖርተኞች በሌሎች ላይ ምንም ዓይነት ስሜታዊ ወይም አካላዊ ጉዳት ቢያስከትል ዋነኛ ምኞታቸው አንደኛ መውጣት ነው። እንዲህ ያለው የራስ ወዳድነት መንፈስ በልጆችም ዘንድ በመስፋፋት ላይ ሲሆን በትልልቅ ሰዎች በአብዛኛው የኑሮ ዘርፍ በመንጸባረቅ ላይ ይገኛል። ይህም “ጥል፣ ክርክር፣ ቅንዓት፣ ቊጣ፣ አድመኛነት፣ መለያየት” አስከትሏል።—ገላትያ 5:19-21
6. የራስ ወዳድነትን መንፈስ የሚያራምደው ማን ነው? ይሖዋ ስለዚህ ዓይነቱ ጠባይ ምን አመለካከት አለው?
6 የዚህ ዓለም የራስ ወዳድነት መንፈስ “ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው” ፍጡር የሚያስፋፋው እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን በዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ዘመን በሚኖሩ ሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ በማስመልከት ሲናገር “ለምድር . . . ወዮላ[ት]፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እ[ርስዋ] ወርዶአልና” በማለት ይተነብያል። (ራእይ 12:9-12) ስለዚህ እርሱም ሆነ የእርሱ አጫፋሪ የሆኑት አጋንንቱ በሰው ልጅ ቤተሰብ ውስጥ የራስ ወዳድነት መንፈስ ለማራመድ ያለ የሌለ ኃይላቸውን አስተባብረዋል። ይሁን እንጂ ይሖዋ እንዲህ ስላለው ዝንባሌ እንዴት ይሰማዋል? “በልቡ የታበየ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነው” በማለት ቃሉ ይናገራል።—ምሳሌ 16:5
ይሖዋ ከትሑታን ጋር ነው
7. ይሖዋ ትሑታንን የሚመለከታቸው እንዴት ነው? ምንስ ያስተምራቸዋል?
7 በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ትሑት የሆኑ ሰዎችን ይባርካል። ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ ባቀረበው መዝሙር ላይ “አንተ የተጠቃውን [“ትሑቱን፣” NW] ሕዝብ ታድናለህና፤ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ” በማለት ተናግሯል። (2 ሳሙኤል 22:1, 28) በመሆኑም የአምላክ ቃል “እናንተ . . . የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” በማለት ይመክራል። (ሶፎንያስ 2:3) ይሖዋ እርሱን በትሕትና ለሚፈልጉ ሁሉ ይህ ዓለም ከሚያንጸባርቀው ፈጽሞ የተለየ መንፈስ እንዲያዳብሩ ያስተምራቸዋል። “ለገሮችም መንገ[ዱ]ን ያስተምራቸዋል።” (መዝሙር 25:9፤ ኢሳይያስ 54:13) ይህ መንገድ የፍቅር መንገድ ነው። አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር በመስማማት ትክክል የሆነውን ነገር በማድረግ ላይ የተመሠረተ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ይህ በመሠረታዊ ሥርዓቶች የሚመራ ፍቅር “አይመካም፣ አይታበይም . . . የራሱንም አይፈልግም።” (1 ቆሮንቶስ 13:1-8) ከዚህም በተጨማሪ የሚገለጸው በትሕትና ነው።
8, 9. (ሀ) በመሠረታዊ ሥርዓት የሚመራው ፍቅር ምንጭ ማን ነው? (ለ) ኢየሱስ ያንጸባረቀውን ዓይነት ፍቅርና ትሕትና ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
8 ጳውሎስና ሌሎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ይህን ዓይነቱን ፍቅር ከኢየሱስ ትምህርቶች ተምረውታል። ኢየሱስም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብሎ ከሚናገርለት ከአባቱ ከይሖዋ ይህን ፍቅር ተምሯል። (1 ዮሐንስ 4:8) ኢየሱስ በፍቅር ሕግ እንዲኖር የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ እንደዚያም አድርጓል። (ዮሐንስ 6:38) ኢየሱስ ለተጨቆኑ፣ ለድሆችና ለኃጢአተኞች ይራራ የነበረው በዚህ ምክንያት ነበር። (ማቴዎስ 9:36) “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፣ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” በማለት ነግሯቸዋል።—ማቴዎስ 11:28, 29፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
9 ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ በመናገር እርሱ ያሳየውን ዓይነት ፍቅርና ትሕትና የማሳየትን አስፈላጊነት አመልክቷቸዋል። (ዮሐንስ 13:35) ከዚህ ራስ ወዳድ ከሆነው ዓለም የተለዩ ይሆናሉ። ኢየሱስ ተከታዮቹን በሚመለከት “ከዓለም አይደሉምና” ብሎ ለመናገር የቻለው ከዚህ የተነሳ ነው። (ዮሐንስ 17:14) የሰይጣን ዓለም የሚያንጸባርቀውን የኩራትና የራስ ወዳድነት መንፈስ ፈጽሞ አያንጸባርቁም። ከዚያ ይልቅ ኢየሱስ ያሳየውን የፍቅርና የትሕትና መንፈስ ያንጸባርቃሉ።
10. ይሖዋ በጊዜያችን ያሉትን ትሑታን በተመለከተ ምን በማከናወን ላይ ነው?
10 በዚህ የመጨረሻ ዘመን ትሑት ሰዎች አንድ ላይ እንደሚሰባሰቡና በፍቅርና በትሕትና ላይ የተመሠረተ አንድ ዓለም አቀፋዊ ማኅበረሰብ እንደሚመሠርቱ የአምላክ ቃል አስቀድሞ ተንብዮአል። የይሖዋ ሕዝቦች የኩራት መንፈስ ይበልጥ እያየለ በሚሄድበት ዓለም ውስጥ እየኖሩ ከዚያ ተቃራኒ የሆነ ባሕርይ ማለትም የትሕትና ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። እነርሱም “ወደ እግዚአብሔር ተራራ [ከፍ ወዳለው እውነተኛ አምልኮ] . . . እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።” (ኢሳይያስ 2:2, 3) በአምላክ መንገድ የሚጓዘው ይህ ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ በይሖዋ ምሥክሮች የተገነባ ነው። እነሱም ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄደውን ‘አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ የተውጣጡትን እጅግ ብዙ ሰዎች’ ይጨምራሉ። (ራእይ 7:9) ይህ እጅግ ብዙ ሕዝብ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያቀፈ ነው። ታዲያ ይሖዋ ትሑት እንዲሆኑ የሚያሠለጥናቸው እንዴት ነው?
ትሕትናን መማር
11, 12. የአምላክ አገልጋዮች ትሕትናን የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
11 ፈቃደኛ በሆኑት ሕዝቦቹ ላይ የሚሠራው የአምላክ መንፈስ የዓለምን መጥፎ መንፈስ እንዲያሸንፉና የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች እንዲያፈሩ ያስችላቸዋል። የአምላክ መንፈስ ‘ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ የውሃትን፣ ራስ መግዛትን’ ያፈራል። (ገላትያ 5:22, 23) የአምላክ አገልጋዮች እነዚህን ባሕርያት እንዲያዳብሩ ለመርዳት ‘እርስ በርሳቸው ለጥል የሚነሳሱ፣ የሚቀናኑና በከንቱ የሚመኩ’ እንዳይሆኑ ይመከራሉ። (ገላትያ 5:26) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ . . . እናገራለሁ” በማለት ገልጿል።—ሮሜ 12:3
12 የአምላክ ቃል “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቊጠር፤ እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” በማለት ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ይናገራል። (ፊልጵስዩስ 2:3, 4) “እያንዳንዱ የባልንጀራውን ጥቅም እንጂ አንድ ስንኳ የራሱን ጥቅም አይፈልግ።” (1 ቆሮንቶስ 10:24) አዎን፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆኑ ቃላትና ተግባራት የሚገለጽ “ፍቅር” ሌሎችን “ያንጻል።” (1 ቆሮንቶስ 8:1) የፉክክር ሳይሆን የትብብር መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል። እኔ ልቅደም የሚለው አስተሳሰብ በይሖዋ አገልጋዮች መካከል ቦታ የለውም።
13. ትሕትናን መማር ያለብን ለምንድን ነው? አንድ ሰው ይህን ባሕርይ ሊማር የሚችለው እንዴት ነው?
13 ይሁን እንጂ በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት የትሕትናን ባሕርይ ይዘን አልተወለድንም። (መዝሙር 51:5) ይህን ባሕርይ የግድ መማር ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ከልጅነታቸው ሳይሆን ትልቅ ከሆኑ በኋላ የይሖዋን መንገዶች ለተማሩ ሰዎች አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ይህ አሮጌ ዓለም በሚያንጸባርቀው ዝንባሌ ላይ የተመሠረተ ባሕርይ አዳብረዋል። ስለዚህ ‘አስቀድሞ ይኖሩበት የነበረውን አሮጌውን ሰውነት ማስወገድንና በእውነተኛ ጽድቅና ቅድስና እግዚአብሔርን ለመምሰል የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት መልበስን’ መማር አለባቸው። (ኤፌሶን 4:22, 24 የ1980 ትርጉም) ቅን ሰዎች አምላክ በሚሰጣቸው እርዳታ እርሱ የሚፈልግባቸውን ነገሮች ማድረግ ይችላሉ። “ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ።”—ቆላስይስ 3:12፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
14. ኢየሱስ ከሌሎች ልቆ የመታየትን ፍላጎት ምን በማለት አውግዟል?
14 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን መማር ነበረባቸው። ደቀ መዛሙርት የሆኑት ትልልቅ ሰዎች ከሆኑ በኋላ ስለነበር ዓለማዊ የፉክክር መንፈስ በመጠኑም ቢሆን በውስጣቸው ነበር። ከእነርሱ መካከል የሁለቱ እናት ልጆቿ ትልቅ ቦታ እንዲያገኙ በለመነች ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “የአሕዛብ አለቆች [ሕዝቡን] እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ። በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፣ ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤ እንዲሁም የሰው ልጅ [ኢየሱስ] ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።” (ማቴዎስ 20:20-28) ኢየሱስ ራሳቸውን ከሌሎች የሚያስበልጥ የማዕረግ ስሞችን እንዳይጠቀሙ ለደቀ መዛሙርቱ ከነገራቸው በኋላ “ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ” በማለት ጨምሮ ነግሯቸዋል።—ማቴዎስ 23:8
15. በበላይ ተመልካችነት ለማገልገል የሚጣጣሩ ሁሉ ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖራቸው ይገባል?
15 እውነተኛ የኢየሱስ ተከታይ ለክርስቲያን ባልደረቦቹ አገልጋይ አዎን፣ ባሪያ ነው። (ገላትያ 5:13) በተለይ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ የበላይ ተመልካች ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ እንደዚያ መሆን አለባቸው። ክብር ወይም ሥልጣን ለማግኘት ፈጽሞ መሽቀዳደም የለባቸውም። ‘ለመንጋው ምሳሌ መሆን እንጂ ማኅበሮቻቸውን በኃይል መግዛት አይገባቸውም።’ (1 ጴጥሮስ 5:3) በእርግጥም የራስን ጥቅም ብቻ የመፈለግ መንፈስ አንድ ሰው ለበላይ ተመልካችነት የማይበቃ መሆኑን የሚጠቁም ነው። እንዲህ ያለው ግለሰብ ጉባኤውን ይጎዳል። እርግጥ ነው፣ ‘ለበላይ ተመልካችነት መጣጣር’ ተገቢ ቢሆንም ይህ ሌሎች ክርስቲያኖችን ለማገልገል ካለ ውስጣዊ ምኞት የሚመነጭ መሆን ይኖርበታል። የበላይ ተመልካች ሆነው የሚያገለግሉ ሁሉ በጉባኤ ውስጥ ካሉ በጣም ትሑት ሰዎች መካከል መሆን ስላለባቸው የበላይ ተመልካችነት ክብር ወይም ሥልጣን ማግኛ ተደርጎ መታየት የለበትም።—1 ጢሞቴዎስ 3:1, 6 NW
16. ዲዮጥራጢስ በአምላክ ቃል ውስጥ የተወገዘው ለምንድን ነው?
16 ሐዋርያው ዮሐንስ “ወደ ቤተ ክርስቲያን ጻፍሁ፤ ዳሩ ግን ዋናቸው ሊሆን የሚወድ ዲዮጥራጢስ አይቀበለንም” በማለት የተሳሳተ አመለካከት ስለነበረው አንድ ሰው ይነግረናል። ይህ ሰው የራሱን ሥልጣን ለማስጠበቅ ሲል ሌሎችን ያንጓጥጥ ነበር። ስለዚህም ዮሐንስ እኔ ልቅደም የሚል ዝንባሌ የነበረውን ዲዮጥራጢስን የሚያወግዙ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲያሰፍር የአምላክ መንፈስ ገፋፍቶታል።—3 ዮሐንስ 9, 10
ትክክለኛው ባሕርይ
17. ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና በርናባስ ትሕትናን ያሳዩት እንዴት ነበር?
17 ትክክለኛ የትሕትና ባሕርይ የነበራቸው በርካታ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛሉ። ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ “ከእግሩ [ከጴጥሮስ] በታች ወደቀና ሰገደለት።” “ጴጥሮስ ግን” ከመጠን ያለፈ አክብሮት ከመቀበል ይልቅ “ተነሣ፤ እኔ ራሴ ደግሞ ሰው ነኝ ብሎ አስነሣው።” (ሥራ 10:25, 26) ጳውሎስና በርናባስ ልስጥራ በነበሩበት ጊዜ ጳውሎስ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረን አንድ ሰው ፈወሰ። በዚህም የተነሳ ሕዝቡ እነዚህ ሐዋርያት አማልክት ናቸው ብለው ተናገሩ። ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ “ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቡ መካከል እየጮኹ ሮጡ፣ እንዲህም አሉ:- እናንተ ሰዎች፣ ይህን ስለ ምን ታደርጋላችሁ? እኛ ደግሞ እንደ እናንተ የምንሰማ ሰዎች ነን” አሏቸው። (ሥራ 14:8-15) እነዚህ ትሑታን ክርስቲያኖች ከሰዎች ክብር ለመቀበል አልፈለጉም ነበር።
18. አንድ ትሑት ኃያል መልአክ ለዮሐንስ ምን ብሎ ነገረው?
18 ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠውን’ ራእይ የተቀበለው በአንድ መልአክ በኩል ነበር። (ራእይ 1:1) አንድ መልአክ በአንድ ሌሊት 185,000 የአሦራውያን ሠራዊትን ገድሎ ስለነበር ዮሐንስ አንድ መልአክ ባለው ኃይል ለምን እንደተደነቀ ሊገባን ይችላል። (2 ነገሥት 19:35) ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይተርካል:- “በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ። እርሱም:- እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር . . . አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ።” (ራእይ 22:8, 9) ይህ ኃያል መልአክ ምንኛ ትሑት ነበር!
19, 20. የሮማ ድል አድራጊ ጄኔራሎችን እብሪት ኢየሱስ ካሳየው የትሕትና ባሕርይ ጋር አነጻጽር።
19 ትሑት በመሆን ረገድ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። የአምላክ አንድያ ልጅና የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የወደፊት ንጉሥ ነበር። ራሱን ንጉሥ አድርጎ ለሕዝቡ ባቀረበ ጊዜ በሮም ዘመን በድል አድራጊነት ወደ አገራቸው ይመለሱ የነበሩ ጄኔራሎች ያደርጉ እንደነበረው አላደረገም። ጄኔራሎቹ ከድል ሲመለሱ በነጭ ፈረስ ወይም ሌላው ቀርቶ በዝሆን፣ በአንበሳ ወይም በነብር በሚጎተት በወርቅና በዝሆን ጥርስ ባጌጠ ሰረገላ ላይ ተቀምጠው ሲያልፉ ሕዝቡ በከፍተኛ ሰልፍ ይቀበላቸው ነበር። ከሰልፈኞቹ ጋር የድል መዝሙር የሚዘምሩ ሙዚቀኞችና በትላልቅ ጋሪዎች ላይ የተጫኑ የጦርነቱን ገጽታ የሚያሳዩ ምርኮኞች ይታያሉ። ከእነዚህ ምርኮኞች መካከል ከቤተሰቦቻቸው ጋር የተማረኩ ነገሥታት፣ ገዥዎችና ጄኔራሎች ይገኙበታል። ብዙውን ጊዜም እነርሱን ለማዋረድ ልብሳቸው ተገፎ ራቁታቸውን እንዲሄዱ ይደረግ ነበር። ድርጊቱ ኩራትንና እብሪተኝነትን በግልጽ የሚያሳይ ነው።
20 ይህን ሁኔታ ኢየሱስ ራሱን ካቀረበበት ሁኔታ ጋር አነጻጽር። “እነሆ፣ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ . . . ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል” የሚለውን ስለ እርሱ የተነገረውን ትንቢት በትሕትና ለመፈጸም ፈቃደኛ ነበር። ልዩ በሆነ ሰረገላ ሳይሆን ለጭነት በሚያገለግል እንስሳ ተቀምጦ ለመሄድ ፈቃደኛ በመሆን ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዘካርያስ 9:9፤ ማቴዎስ 21:4, 5) ትሑታን ሰዎች እውነተኛ የትሕትና ባሕርይ ያለውን፣ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ፣ አፍቃሪ፣ ሩኅሩኅና መሐሪ የሆነውን ኢየሱስን በአዲሱ ዓለም በመላው ምድር ላይ እንዲገዛ ይሖዋ ስለ ሾመላቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው!—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ፊልጵስዩስ 2:5-8
21. ትሕትና ምንን አያመለክትም?
21 ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ፣ ጳውሎስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎች የታመኑ ወንዶችና ሴቶች ትሑት እንደነበሩ መገለጹ የትሕትና ባሕርይ የድክመት ምልክት ነው የሚለውን አስተሳሰብ ውድቅ የሚያደርግ ነው። እነዚህ ሰዎች ደፋሮችና ቀናተኞች ስለነበሩ ትሕትና መንፈሰ ጠንካራነትን የሚያሳይ ነው። ከፍተኛ አእምሮአዊና ሥነ ምግባራዊ ጥንካሬ ስለነበራቸው ከባድ ፈተናዎችን ተቋቁመዋል። (ዕብራውያን ምዕራፍ 11) በዛሬው ጊዜ ያሉት ትሑት የይሖዋ አገልጋዮችም ኃያሉ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ስለሚደግፋቸው ተመሳሳይ የሆነ ጥንካሬ አላቸው። በዚህም የተነሳ “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ” ተብለን በጥብቅ ተመክረናል።—1 ጴጥሮስ 5:5, 6፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7
22. በሚቀጥለው ጥናት ምን ነገር ይብራራል?
22 የአምላክ አገልጋዮች ሊያሳዩት የሚገባ ሌላ የትሕትና ዘርፍ አለ። ይህም የፍቅርን መንፈስ ለመገንባትና በጉባኤዎች ውስጥ የትብብር መንፈስ እንዲሰፍን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንዲያውም የትሕትና ዋነኛ ክፍል ነው። ይህም በሚቀጥለው ጥናት ላይ ይብራራል።
ለክለሳ ያህል
◻ በዚህ ዓለም ላይ ተስፋፍቶ የሚገኘው መንፈስ ምን እንደሆነ አብራራ።
◻ ይሖዋ ትሑታንን እንዴት ይመለከታቸዋል?
◻ ትሕትናን መማር ያለብን ለምንድን ነው?
◻ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ የትሕትናን ባሕርይ በማንጸባረቅ ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ግለሰቦች እነማን ናቸው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መልአኩ ለዮሐንስ ‘እንዳታደርገው ተጠንቀቅ! እኔም እንዳንተው ባሪያ ነኝ’ ብሎታል