ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብሃልን?
‘በፍጹም ይቅርታ አልጠይቅም’ በማለት ጆርጅ በርናንድ ሾው ጽፎ ነበር። ሌሎች ደግሞ ‘አንዴ የሆነው ሆኗል’ በማለት ይናገሩ ይሆናል።
እኛም ክብራችን እንዳይነካ በመፍራት ጥፋታችንን ለማመን እናመነታ ይሆናል። እንዲያውም ችግሩን በዚያኛው ሰው ላይ እናላክክ ይሆናል። ወይም ደግሞ ይቅርታ ለመጠየቅ ብናስብም ጉዳዩ እስኪረሳሳ በማለት ዛሬ ነገ እያልን እንቆይ ይሆናል።
ታዲያ ይቅርታ መጠየቅ የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይቅርታ መጠየቅ የሚያስገኘው ጥቅም ይኖር ይሆን?
ፍቅር ይቅርታ እንድንጠይቅ ያስገድደናል
የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ተለይተው የሚታወቁበት ምልክት ወንድማማቻዊ ፍቅር ነው። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:35) ቅዱሳን ጽሑፎች ክርስቲያኖችን “እርስ በርሳችሁ ከልባችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” በማለት ያሳስባሉ። (1 ጴጥሮስ 1:22) በውስጣችን ያለው የጋለ ፍቅር ይቅርታ እንድንጠይቅ ያስገድደናል። ለምን? ምክንያቱም ሰብዓዊ አለፍጽምና ቅያሜዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉ የማይቀር ነው፤ እነዚህ ቅያሜዎች መፍትሄ ካላገኙ ደግሞ ፍቅር እንዳናሳይ እንቅፋት ይሆናሉ።
ለምሳሌ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ካለ አንድ ሰው ጋር የግል አለመግባባት ቢፈጠር እርሱን ላለማነጋገር እንመርጥ ይሆናል። ግለሰቡን ያስቀየምነው እኛ ብንሆን በፍቅር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደገና ማደስ የሚቻለው እንዴት ነው? አብዛኛውን ጊዜ አለመግባባቶች የሚፈቱት ይቅርታ በመጠየቅና ከዚያም ከግለሰቡ ጋር ሞቅ ያለ ወዳጃዊ ጭውውት ለማድረግ በመጣር ነው። ለእምነት ባልደረቦቻችን ፍቅር የማሳየት ዕዳ አለብን። ስለዚህ ያስቀየምነውን ሰው ይቅርታ ስንጠይቅ ከዚህ ዕዳችን ውስጥ ከፊሉን እናቃልላለን።—ሮሜ 13:8
በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ ማሪ ካርሜንና ፓኪ የረዥም ጊዜ ወዳጅነት የነበራቸው ሁለት ክርስቲያን ሴቶች ናቸው። ይሁን እንጂ ማሪ ካርሜን አንድ ጎጂ ሐሜት በመስማቷ ከፓኪ ጋር የነበራት ወዳጅነት ቀስ በቀስ እየቀዘቀዘ ይሄዳል። ምንም ነገር ሳትገልጽላት ፓኪን ጨርሶ ትርቃታለች። አንድ ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላ ማሪ ካርሜን የሰማችው ሐሜት እውነት እንዳልነበረ ተረዳች። ታዲያ የወሰደችው እርምጃ ምን ነበር? ወደ ፓኪ ሄዳ በአድራጎቷ ከልብ እንደተጸጸተች በትህትና እንድትገልጽ ፍቅር አነሳሳት። ሁለቱም ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፤ ከዚያን ጊዜ ወዲህ ወዳጅነታቸው ጽኑ ሆኖ ቀጥሏል።
ምንም ዓይነት ስህተት እንዳልሠራን ቢሰማንም እንኳ ይቅርታ መጠየቃችን አለመግባባትን ሊያስወግድ ይችላል። ማንዌል ያጋጠመውን ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ከብዙ ዓመታት በፊት አንዲት መንፈሳዊ እህታችን ታማ ሆስፒታል ስለገባች እኔና ባለቤቴ ቤቷን እንጠብቅላት ነበር። ታማ በነበረችበት ጊዜ እርሷንም ሆነ ልጆቿን ለመንከባከብ የተቻለንን ሁሉ አድርገናል። ይሁን እንጂ ወደ ቤት ከተመለሰች በኋላ የቤት ወጪዋን አለአግባብ እንዳባከንባት ለአንድ ወንድም አማራ ትነግረዋለች።
“እኛም ይህን ስንሰማ ወደ እርሷ ሄደን ምናልባት ወጣት በመሆናችንና ያለን ተሞክሮም አነስተኛ በመሆኑ እርሷ ታደርገው እንደነበረው ጥንቃቄ ሳናደርግ ቀርተን ሊሆን እንደሚችል ገለጽንላት። በዚህ ጊዜ እንዲያውም እሷ የእኛ ውለታ እንዳለባትና ከልብ እንደምታመሰግነን ገለጸችልን። ችግሩ መፍትሄ አገኘ። አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ራስን ዝቅ አድርጎ ይቅርታ መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ከዚህ ተሞክሮ ተማርኩኝ።”
እነዚህ ባልና ሚስት ፍቅር በማሳየታቸውና ‘ሰላም የሚቆምበትን ነገር በመከታተላቸው’ ይሖዋ ባርኳቸዋል። (ሮሜ 14:19) ፍቅር ለሌሎች ስሜት አሳቢ መሆንንም ይጨምራል። ጴጥሮስ ‘ለሌሎች አስቡ’ ሲል ይመክራል። (1 ጴጥሮስ 3:8) ለሌሎች የምናስብ ከሆነ አሳቢነት በጎደለው ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን ያደረስነውን ጉዳት እንድንረዳና እኛም ይቅርታ እንድንጠይቅ ያስገድደናል።
“ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ”
ታማኝ ክርስቲያን ሽማግሌዎችም እንኳ ሳይቀሩ አልፎ አልፎ በቁጣ ሊናገሩ ይችላሉ። (ከሥራ 15:37-39 ጋር አወዳድር።) በእነዚህ ወቅቶች ይቅርታ መጠየቅ በጣም ጠቃሚ ነው። አንድ ሽማግሌ ወይም ሌላ ክርስቲያን ይቅርታ መጠየቅ ቢያስቸግረው ምን ሊረዳው ይችላል?
ቁልፉ ትሕትና ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ሁላችሁም እርስ በርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ” በማለት ምክር ሰጥቷል። (1 ጴጥሮስ 5:5) አለመግባባቶች ሲነሱ አብዛኛውን ጊዜ ሁለቱም ወገኖች ጥፋተኞች መሆናቸው እውነት ቢሆንም ትሑት የሆነው ክርስቲያን ግን የሠራቸውን ስህተቶች ይመረምርና ስህተቶቹን ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናል።—ምሳሌ 6:1-5
ይቅርታ የተጠየቀው ሰውም ቢሆን ይቅር ለማለት ጥያቄውን በትሕትና መቀበል ይኖርበታል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል እርስ በርስ መነጋገር የሚፈልጉ ሁለት ሰዎች በሁለት የተለያዩ ተራሮች አናት ላይ ቆመዋል እንበል። በመካከላቸው ያለውን ገደል አሻግሮ ለመነጋገር መሞከር ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ከሁለቱ አንዱ ከተራራው ቢወርድና ሌላኛውም እንዲሁ ቢያደርግ በቀላሉ ሊነጋገሩ ይችላሉ። በተመሳሳይም ሁለት ክርስቲያኖች በመካከላቸው ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ከፈለጉ ሁለቱም ትሑት ሆነው በምሳሌያዊ አነጋገር ከተራራው ወርደው በመገናኘትና በመነጋገር በተገቢ ሁኔታ ይቅር መባባል ይኖርባቸዋል።—1 ጴጥሮስ 5:6
ይቅርታ መጠየቅ በትዳር ውስጥ በጣም አስፈላጊ ነው
በጋብቻ የተቆራኙ ፍጹም ያልሆኑ ሁለት ሰዎች አንዳቸው ሌላውን ይቅርታ መጠየቃቸው የግድ ነው። ባልም ሆነ ሚስት አንዳቸው ለሌላው ስሜት ከልብ የሚያስቡ ከሆነ አሳቢነት በጎደለው መንገድ ለተናገሩት ወይም ላደረጉት ነገር ይቅርታ እንዲጠይቁ ያነሳሳቸዋል። ምሳሌ 12:18 (የ1980 ትርጉም) “ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቆስላል፤ በጥበብ የተነገረ ቃል ግን ይፈውሳል” በማለት ይገልጻል። ‘በጥንቃቄ ጉድለት የደረሱትን ቁስሎች’ ወደ ኋላ ተመልሰን እንዳይደርሱ ማድረግ አንችልም፤ ይሁን እንጂ ከልብ ይቅርታ በመጠየቅ ሊፈወሱ ይችላሉ። እርግጥ ነው ይህ ቀጣይ የሆነ ጥንቃቄና ጥረት ይጠይቃል።
ሱዛንa የራሷን ጋብቻ አስመልክታ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ጃክb ከተጋባን 24 ዓመት አልፎናል። ይሁን እንጂ አሁንም እንኳ አንዳችን ስለሌላው አዳዲስ ነገሮችን እንማራለን። የሚያሳዝነው ከጥቂት ዓመታት በፊት ለተወሰኑ ሳምንታት ተለያይተን ኖረናል። ይሁን እንጂ ሽማግሌዎች የሰጡንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተቀብለን እንደገና አብረን መኖር ጀመርን። ሁለታችንም የተለያየ ዓይነት ተፈጥሯዊ ባሕርይ ስላለን ግጭቶች መፈጠራቸው እንደማይቀር አሁን ተረድተናል። ግጭቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ በፍጥነት ይቅርታ እንጠይቅና የሌላውን የግል አመለካከት ለመረዳት እንጥራለን። ትዳራችን ተሻሽሏል ብዬ ለመናገር ያስደፍረኛል።” ጃክም “በተጨማሪም በቀላሉ የምንበሳጭባቸው ጊዜያት መቼ እንደሆኑ ለይተን ማወቅ ችለናል። እንደነዚህ ባሉ ጊዜያት ላይ አንዳችን ሌላውን በርህራሄ ስሜት እናያለን” በማለት አክሎ ተናግሯል።—ምሳሌ 16:23
ጥፋተኛ እንዳልሆንክ ቢሰማህ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብሃል? ከፍተኛ የብስጭት ስሜት በሚነሳበት ጊዜ ጥፋቱ የማን እንደሆነ አስረግጦ ለመናገር ያስቸግራል። ይሁን እንጂ የሚፈለገው ዋነኛ ነገር በጋብቻው ውስጥ ሰላም መስፈኑ ነው። ባሏ ዳዊትን የናቀ አቢጋኤል የተባለች አንዲት እስራኤላዊ ሴትን ምሳሌ እንውሰድ። ባሏ በስንፍና ለፈጸመው ድርጊት ተጠያቂ ባትሆንም እንኳ ይቅርታ ጠይቃለች። “ጌታዬ ሆይ፣ ይህ ኃጢአት በእኔ ላይ ይሁን” በማለት ተማጸነች። ዳዊት እርሷ ባትመልሰው ኖሮ ንጹሕ ደም ያፈስ እንደነበር በአክብሮትና በትሕትና በመግለጽ ልመናዋን በጥሩ ስሜት ተቀብሏል።—1 ሳሙኤል 25:24-28, 32-35
በተመሳሳይም ለ45 ዓመታት በትዳር ላይ የቆየችው ጁን የተባለች ክርስቲያን ሴት ጋብቻ የተሳካ እንዲሆን ቀዳሚ ሆኖ ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ገልጻለች። እንዲህ አለች፦ “እኔ በግሌ ካሉኝ ስሜቶች የበለጠ አንገብጋቢ የሆነው ነገር ትዳራችን እንደሆነ ለራሴ ደጋግሜ እነግራለሁ። ስለዚህም ይቅርታ በምጠይቅበት ጊዜ ለጋብቻው አስተዋጽኦ እያበረከትኩ እንዳለሁ ይሰማኛል።” ጂም የተባለ በዕድሜ የገፋ አንድ ሰው እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ጥቃቅን ለሆኑ ነገሮች እንኳ ባለቤቴን ይቅርታ እጠይቃታለሁ። ከበድ ያለ ቀዶ ሕክምና ከዚህ በፊት አድርጋ ስለነበር በቀላሉ ትበሳጫለች። ስለዚህም ብዙዉን ጊዜ እቅፍ አደርጋትና ‘አዝናለሁ የእኔ ፍቅር። ይህን ያደረኩት አንቺን ለማበሳጨት ብዬ አይደለም’ እላታለሁ። ልክ ውኃ እንዳገኘ ተክል ወዲያው ትፈካለች።”
በጣም የምንወደውን ሰው ከጎዳን ሳይውል ሳያድር ይቅርታ መጠየቃችን ጥሩ ውጤት አለው። ሚላግሮስ ይህን አባባል በጣም ነው የምትደግፈው። እንዲህ ትላለች፦ “በራስ የመተማመን መንፈስ በማጣቴ ችግር ላይ ወድቄአለሁ። ባለቤቴ የሚሰነዝራቸው ሻካራ ቃላት በጣም ያበሳጩኛል። ይሁን እንጂ ይቅርታ ሲጠይቀኝ ወዲያው መለስ እላለሁ።” ቅዱሳን ጽሑፎችም ከዚህ ጋር በመስማማት “ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው” በማለት ይናገራሉ።—ምሳሌ 16:24
ይቅርታ መጠየቅን ልማድ አድርጉ
አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ይቅርታ የምንጠይቅ ከሆነ ሌሎች ሰዎችም ተመሳሳይ የሆነ አጸፌታ ይመልሳሉ። እንዲያውም ራሳቸው ይቅርታ ይጠይቁ ይሆናል። አንድን ሰው እንዳበሳጨነው ከጠረጠርን ጥፋተኞች አለመሆናችንን ለማስረዳት ዙሪያ ጥምጥም ከምንሄድ ይልቅ ይቅርታ መጠየቅን ለምን ልማድ አናደርግም? ዓለም ይቅርታ መጠየቅ የድክመት ምልክት እንደሆነ አድርጎ ቢመለከተውም ይቅርታ መጠየቅ የክርስቲያናዊ ጉልምስና ምልክት ነው። እርግጥ ነው የሠሩትን አንዳንድ ስህተቶች ቢያምኑም ጥፋታቸውን ለማቃለል የሚሞክሩትን ሰዎች መምሰል አንፈልግም። ለምሳሌ እንዲያው ከአንገት በላይ እንዲህ በማድረጌ አዝናለሁ ብለን ተናግረን እናውቃለን? ሰዓት አሳልፈን ብንደርስና ግን ይቅርታ ብዙ ጊዜ ብንጠይቅ ሰዓት አክባሪ ሆነን ለመገኘት ማሻሻያ አድርገናልን?
ታዲያ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብናል? አዎን። እኛም ሆንን ሌሎች ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባ ገዴታ ነው። ይቅርታ መጠየቅ ባለፍጽምና ምክንያት የሚፈጠር መቆሳሰል የሚያስከትለው ሥቃይ እንዲቀንስ ያደርጋል፤ መቃቃርንም ለማስወገድ ይረዳል። ይቅርታ በጠየቅን ቁጥር ትሕትናን እንማራለን፤ እንዲሁም ወደፊት ለሌሎች ሰዎች ስሜት ይበልጥ እንድንጠነቀቅ ያደርገናል። ይህም የእምነት ባልንጀሮቻችንና የትዳር ጓደኞቻችን እንዲሁም ሌሎች ሰዎች እንዲወዱንና እምነት እንዲጥሉብን ያደርጋቸዋል። የአእምሮ ሰላም ይኖረናል፤ ይሖዋ አምላክም ይባርከናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እውነተኛ ስማቸው አይደለም።
b እውነተኛ ስማቸው አይደለም።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ክርስቲያናዊ ፍቅር እንዲሰፍን ያደርጋል