ሲላስ የማበረታቻ ምንጭ
የክርስትና ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤዎችን ለማበረታታትም ሆነ ምሥራቹን በምድር ዙሪያ ለማዳረስ ታማኝ የሆኑ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሚያከናውኑት ሥራ አስፈላጊ ነበር። በመጀመሪያ ከተሾሙት የበላይ ተመልካቾች መካከል ነቢይና የኢየሩሳሌም ጉባኤ ቀደምት አባል የነበረው ሲላስ ይገኝበታል። የስብከቱ ሥራ ከፍተኛ እድገት ሲያሳይ ቁልፍ ሚና የነበረው ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ምድር ወንጌልን ከሰበኩት ሚስዮናውያን መካከልም አንዱ ነበር። ሲላስ ይህን ሁሉ ለማከናወን ብቁ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው? ልንኮርጃቸው የሚገቡ ምን ባሕርያትስ ነበሩት?
የግርዘት ጥያቄ
በ49 እዘአ አካባቢ አደገኛ መከፋፈል ሊያስከትል ይችል የነበረው የግርዘት ጥያቄ ሲነሳ በኢየሩሳሌም የነበረው የአስተዳደር አካል ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ለክርስቲያኖች ግልጽ መመሪያ መላክ አስፈልጎት ነበር። ስልዋኖስ በመባልም የሚታወቀው ሲላስ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ ብቅ ያለው በዚህ ጊዜ ነበር። ሲላስ ውሳኔ ካስተላለፉት ሰዎች መካከል አንዱ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ‘የሐዋርያትና የሽማግሌዎች’ መልእክተኛ በመሆን ውሳኔያቸውን ‘በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ወንድሞች’ እንዲያደርስ ተመርጧል። በአንጾኪያ ሲላስና ይሁዳ (በርስያን) ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር በመሆን ይዘው የመጡትን አስቸኳይ መልእክት ያቀረቡ ሲሆን በኢየሩሳሌም ስለተካሄደው ስብሰባ፣ ስለደረሱበት መደምደሚያና ስለ ደብዳቤው ይዘት በቃል እንደሚነግሯቸውም ግልጽ ነው። በተጨማሪም “ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጸኑአቸው።” በአንጾኪያ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ‘ደስ መሰኘታቸው’ የዚህ ተልእኮ አስደሳች ውጤት ነበር።—ሥራ 15:1-32
በመሆኑም ሲላስ ይህ መሠረታዊ ጥያቄ መፍትሄ እንዲያገኝ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል። ይሁን እንጂ የተሰጠው ሥራ ቀላል አልነበረም። የአንጾኪያ ጉባኤ ለተላለፈው ውሳኔ ምን ምላሽ እንደሚሰጥ ማወቅ የሚቻልበት መንገድ አልነበረም። ስለዚህ “ሐዋርያት በጻፉት ደብዳቤ ላይ ያለውን ሐሳብ ማብራራት የሚችል ከፍተኛ ጥበብና ብልሃት ያለው ሰው ያስፈልግ ነበር” በማለት አንድ ተንታኝ ተናግረዋል። ሲላስ ጥንቃቄ ለሚጠይቀው ለዚህ ሥራ መመረጡ ምን ዓይነት ሰው እንደነበር ፍንጭ ይሰጠናል። የአስተዳደር አካሉን መመሪያዎች በታማኝነት እንደሚያስተላልፍ ትምክህት ሊጣልበት የሚችል ሰው ነው። በተጨማሪም በጉባኤው ውስጥ አወዛጋቢ ጉዳይ በሚፈጠርበት ጊዜ የማስማማት ችሎታ ያለው አስተዋይ የበላይ ተመልካችም ሳይሆን አይቀርም።
ከጳውሎስ ጋር ተጓዘ
ሲላስ ከዚህ ተልዕኮ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ይመለስ አይመለስ በእርግጠኝነት የሚታወቅ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ ዮሐንስ ማርቆስን በተመለከተ በበርናባስና በጳውሎስ መካከል አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ ጳውሎስ በመጀመሪያ የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት የሰበከላቸውን ከተሞች እንደገና ለመጎብኘት በማቀድ አዲስ ለሚያደርገው ጉዞ በወቅቱ በአንጾኪያ የነበረውን ሲላስን መረጠ።—ሥራ 15:36-41
ሲላስ መልእክቱን ለአሕዛብ ለማዳረስ የነበረው አዎንታዊ አመለካከት እንዲሁም ነቢይና የአስተዳደር አካሉ ቃል አቀባይ እንደመሆኑ መጠን ያስተላለፉትን ውሳኔ በሶርያና በኪልቂያ ለሚገኙ አማኞች ለማድረስ ያበረከተው አስተዋጽኦ እርሱን ለመምረጥ ተጽዕኖ ሳያሳድር አይቀርም። የተገኘው ውጤት በጣም ግሩም ነበር። የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቈረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው። አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ይበረቱ ነበር፣ በቊጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።”—ሥራ 16:4, 5
ሚስዮናውያኑ ጉዟቸውን እየቀጠሉ ሲሄዱ መንፈስ ቅዱስ ከአንዴም ሁለቴ ሊሄዱ ካሰቡበት አቅጣጫቸውን አስቀየራቸው። (ሥራ 16:6, 7) ጢሞቴዎስን የሚመለከት በውል ያልተጠቀሰ “ትንቢት” ከተነገረ በኋላ ጢሞቴዎስ በልስጥራን በጉዞ ላይ ካለው ቡድን ጋር ተቀላቀለ። (1 ጢሞቴዎስ 1:18፤ 4:14) እርሱም ጭምር ትንቢት የመናገር ስጦታ ለነበረው ማለትም ለጳውሎስ በታየው ራእይ አማካኝነት እነዚህ የጉዞ ጓደኛሞች በአውሮፓ ወደምትገኘው ወደ መቄዶንያ በመርከብ እንዲሄዱ ተነገራቸው።—ሥራ 16:9, 10
ተደብድበው ታሰሩ
ሲላስ “የወረዳ ዋና ከተማ” በሆነችው በፊልጵስዩስ የማይረሳ መከራ አጋጠመው። ጳውሎስ አንዲት ገረድ ያደረባትን የምዋርተኝነት መንፈስ ካወጣ በኋላ ጌቶችዋ የገቢ ምንጫቸው መቋረጡን ሲመለከቱ ሲላስና ጳውሎስን ወደ ከተማው ሹማምት ፊት ጎትተው አመጡአቸው። በዚህ ምክንያት እነዚህ ሁለት ሰዎች ልብሳቸው ተገፍፎ በገበያ ቦታው ላይ በዱላ በመደብደብ በሕዝብ ፊት እንደ ወንጀለኞች የመቆጠር ውርደት ደረሰባቸው።—ሥራ 16:12, 16-22
ይህ ዓይነቱ ግርፋት አንድ ሰው መፈጠሩን እንዲጠላ የሚያደርግ አሰቃቂ ቅጣት ከመሆኑም በላይ በጳውሎስና በሲላስ ሁኔታ ደግሞ ሕገ ወጥ ቅጣት ነበር። ለምን? የሮማውያን ሕግ ማንኛውም የሮም ዜጋ መገረፍ እንደሌለበት ደንግጓል። ጳውሎስ ሮማዊ ዜግነት ያለው ሲሆን ሲላስም ሳይኖረው እንደማይቀር ይገመታል። ጳውሎስና ሲላስ ‘ብዙ ከተደበደቡ’ በኋላ ወደ ወኅኒ የተጣሉ ሲሆን እዚያም እግራቸው ከግንድ ጋር ተጠርቆ ታሰረ። ጉስታፍ ስታሊን ስለዚህ ግንድ ሲያብራሩ “እስረኛው እንዳይተኛ ለማድረግ ሲባል በተፈለገው መጠን እግሮቹን ለመለጠጥ የሚያስችል አሰቃቂ መሣሪያ” መሆኑን ተናግረዋል። በዚህ ጊዜ ጀርባቸው በሙሉ ቆሳስሎ ሊሆን ቢችልም እኩለ ሌሊት ላይ “ጳውሎስና ሲላስ እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር።”—ሥራ 16:23-25
ይህ ሁኔታ የሲላስን ባሕርይ በሚመለከት ሌላ ተጨማሪ ነገር ያሳውቀናል። መከራ የደረሰባቸው ለክርስቶስ ስም ሲሉ በመሆኑ ደስተኛ ነበር። (ማቴዎስ 5:11, 12፤ 24:9) ሲላስና የጉዞ ጓደኞቹ ቀድሞ በአንጾኪያ በነበራቸው ተልዕኮ ወቅት ጉባኤውን በማበረታታትና በማጠናከር መሰል ክርስቲያኖችን ማስደሰት የቻሉት ይህ ዓይነት መንፈስ ስለነበራቸው መሆኑ ግልጽ ነው። ጳውሎስና ሲላስ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ የተነሳ በተአምራዊ መንገድ ከእስር ቤት መፈታታቸውና ራሱን ሊገድል የነበረው ጠባቂ ከነቤተሰቡ በአምላክ ላይ እምነት ማሳደሩ ደስታቸውን ጨምሮላቸው መሆን አለበት።—ሥራ 16:26-34
ጳውሎስም ሆነ ሲላስ ግርፋቱና እስራቱ በፍርሃት አላርበደበዳቸውም። እንዲፈቷቸው ትእዛዝ ሲተላለፍ ሹማምቱ እንደጠበቁት ከፊልጵስዩስ በእፍረት ሹልክ ብለው ለመውጣት ፈቃደኛ አልሆኑም። በእነርሱ ሐሳብ ከመመራት ይልቅ እብሪተኛና አምባገነን የሆኑትን ባለሥልጣኖች ተጠያቂ አደረጉዋቸው። ጳውሎስ “እኛ የሮሜ ሰዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በሕዝብ ፊት ደብድበው በወኅኒ ጣሉን፤ አሁንም በስውር ይጥሉናልን?” ሲል ጠይቋል። “አይሆንም፤ ራሳቸው ግን መጥተው ያውጡን አላቸው።” ሹማምቱ ድርጊታቸው ሊያስከትልባቸው የሚችለውን ጣጣ በመፍራት ሁለቱ ሰዎች ከተማቸውን ለቅቀው እንዲወጡላቸው መለማመጥ ግድ ሆነባቸው።—ሥራ 16:35-39
ሮማውያን እንደመሆናቸው መጠን መብታቸውን ለባለሥልጣኖቹ ካስገነዘቡ በኋላ ጳውሎስና ሲላስ ሹማምቱ ያቀረቡላቸውን ጥያቄ ተቀበሉ። ይሁን እንጂ ጓደኞቻቸውን ሳይሰናበቱ አልሄዱም። በዚህ ጊዜ የአጠቃላዩ የስብከት ጉዞ ገጽታ ከሆነው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ ሲላስና ጓደኛው በድጋሚ ወንድሞችን ‘ካጽናኗቸው’ በኋላ ጉዟቸውን ቀጠሉ።—ሥራ 16:40
ከመቄዶንያ ወደ ባቢሎን
ጳውሎስ፣ ሲላስና የጉዞ ጓደኞቻቸው በደረሰባቸው ሁኔታ ተስፋ ሳይቆርጡ ወደ አዳዲስ የሚስዮናዊ መስኮች ጉዟቸውን ቀጠሉ። እንደገና በተሰሎንቄ ችግር ገጠማቸው። ጳውሎስ በሦስት ሰንበት ጊዜ ውስጥ ያከናወነው አገልግሎት ስኬታማ በመሆኑ ቅንዓት ያደረባቸው ተቃዋሚዎች ረብሻ ስላነሳሱ ሚስዮናውያኑ ከተማውን በሌሊት ጥለው መውጣታቸው የጥበብ እርምጃ ሆኖ ተገኘ። ከዚያም ወደ ቤርያ አቀኑ። ጳውሎስና ጓደኞቹ በከተማይቱ ውስጥ ስላከናወኑት ሥራ ተቃዋሚዎቹ ሲሰሙ ከተሰሎንቄ ተነስተው ገስግሰው መጡ። ጳውሎስ ለብቻው ጉዞውን የቀጠለ ሲሆን ሲላስና ጢሞቴዎስ ግን ፍላጎት ያሳዩ አዳዲስ ሰዎች ያሉበትን ቡድን ለመርዳት በቤርያ ቀሩ። (ሥራ 17:1-15) ሲላስና ጢሞቴዎስ የምሥራችና ምናልባትም በመቄዶንያ ከሚገኙ ታማኝ ወዳጆቹ የተላከለትን ስጦታ ይዘው በቆሮንቶስ ከጳውሎስ ጋር በድጋሚ ተገናኙ። ይህ ስጦታ ተቸግሮ የነበረው ሐዋርያ በመካከሉ ጀምሮት የነበረውን ዓለማዊ ሥራ አቋርጦ በሙሉ ኃይሉ ወደ ሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራው እንዲመለስ አስችሎት መሆን አለበት። (ሥራ 18:1-5፤ 2 ቆሮንቶስ 11:9) ቆሮንቶስ ውስጥ ሲላስና ጢሞቴዎስ ወንጌላውያንና የጳውሎስ የጉዞ ጓደኞች እንደሆኑ ተደርገውም ተቆጥረዋል። ስለዚህ በዚህ ከተማም ቢሆን ተሳትፏቸው እንዳልቀነሰ በግልጽ መረዳት ይቻላል።—2 ቆሮንቶስ 1:19
በዚህ ወቅት ለተሰሎንቄ ሰዎች ከቆሮንቶስ የተጻፉት እነዚህ ሁለት ደብዳቤዎች ከዳር እስከ ዳር ብዙ ቁጥር የሚያመለክት ተውላጠ ስም መያዛቸው ሲላስና ጢሞቴዎስ ለመልእክቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን እንደሚያሳይ ይገመታል። ሆኖም ሲላስ በመጻፍ ሥራ ላይ ተሳትፏል የሚለው ሐሳብ በዋነኛነት የተመሠረተው ጴጥሮስ ከራሱ ደብዳቤዎች ስለ አንዱ በተናገረው ሐሳብ ነው። ጴጥሮስ ከባቢሎን የላከው የመጀመሪያ ደብዳቤው ‘የታመነ ወንድም በሆነው በስልዋኖስ እጅ’ መጻፉን ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 5:12, 13) ይህ አባባል ስልዋኖስ ደብዳቤውን ማድረሱን ብቻ የሚያሳይ ሊሆን ቢችልም በሁለቱ የጴጥሮስ ደብዳቤዎች መካከል ያለው የአጻጻፍ ዘይቤ ልዩነት ጴጥሮስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ለመጻፍ ሲላስን በጸሐፊነት ቢጠቀምበትም ሁለተኛው ደብዳቤ ሲጻፍ ምንም ድርሻ እንዳልነበረው የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። በመሆኑም ሲላስ ከነበሩት ልዩ ልዩ ተሰጥኦዎችና ቲኦክራሲያዊ መብቶች መካከል አንዱ ጸሐፊ ሆኖ ማገልገሉ ሳይሆን አይቀርም።
ሊከተሉት የሚገባ አርአያ
ሲላስ እንዳከናወናቸው ስለምናውቃቸው ሥራዎች ቆም ብለን ስናስብ በሕይወቱ ያሳለፋቸው ነገሮች አስደናቂ ሆነው እናገኛቸዋለን። በጊዜያችን ላሉ ሚስዮናውያንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በጣም ግሩም ምሳሌ ነው። ከፍተኛ ወጪ ቢጠይቅበትም ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለዝና ሳይሆን ሌሎችን ለመርዳት ሲል ራሱን ሳይቆጥብ ብዙ ርቀት ተጉዟል። ዓላማው ጥበብና ዘዴ በተሞላበት ምክር፣ ጥሩ ዝግጅት በተደረገባቸውና ግለት ባላቸው ንግግሮች እንዲሁም በመስክ አገልግሎት በሚያሳየው ቅንዓት ሌሎችን ማበረታታት ነበር። በተደራጀው የይሖዋ ሕዝብ መካከል ማንኛውም ዓይነት የሥራ ድርሻ ቢኖርህ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታም ሥር ተመሳሳይ የሆነ ገንቢ አመለካከት ለመያዝ ከጣርክ አንተም ለእምነት ጓደኞችህ የመጽናኛ ምንጭ ልትሆን ትችላለህ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሁለተኛው የጳውሎስ ሚስዮናዊ ጉዞ
ታላቁ ባሕር
አቴና
ደርቤ
ልስጥራን
ኢቆንዮን
ጢሮአዳ
ፊልጵስዩስ
አንፊጶል
ተሰሎንቄ
ቤርያ
አንጾኪያ
ቆሮንቶስ
ኤፌሶን
ኢየሩሳሌም
ቂሣርያ
[ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.