ንቁ ሆነው የሚኖሩ ደስተኞች ናቸው!
“እነሆ፣ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።”— ራእይ 16:15
1. የይሖዋ ቀን ቅርብ በመሆኑ ምን ነገር ልንጠብቅ እንችላለን?
ታላቁ የይሖዋ ቀን ቀርቧል፤ ይህ ደግሞ የጦርነት ቀን ነው! ሐዋርያው ዮሐንስ ጓጉንቸር የሚመስሉ ‘የአጋንንንት መናፍስት’ ወደ ምድር “ነገሥታት” ወይም ገዥዎች ሁሉ ሲወጡ በራእይ ተመልክቷል። የወጡት ምን ለማድረግ ነው? ‘በታላቁ ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደሚሆነው ጦር ሊያስከትቷቸው ነው!’ ዮሐንስ በመቀጠል “በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ አስከተቱአቸው” ብሏል።— ራእይ 16:13-16
2. የማጎጉ ጎግ ማን ነው? በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝር ምን ይከሰታል?
2 በቅርቡ ይሖዋ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችውን ታላቂቱ ባቢሎንን እንዲያጠፏት የዚህ ሥርዓት ፖለቲካዊ ኃይሎችን ያነሳሳቸዋል። (ራእይ 17:1-5, 15-17) ከዚያም የማጎጉ ጎግ ማለትም ወደ ምድር አካባቢ የተጣለው ሰይጣን ዲያብሎስ ጭፍሮቹን ለዘመቻ አሰልፎ ሰላማዊ በሆኑትና ምንም መከላከያ የሌላቸው መስለው በሚታዩት የይሖዋ ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ይከፍታል። (ሕዝቅኤል 38:1-12) ይሁን እንጂ አምላክ ሕዝቦቹን ለማዳን እርምጃ ይወስዳል። ይህ ‘የታላቁና አስፈሪው የይሖዋ ቀን’ መጀመሪያ ይሆናል።— ኢዩኤል 2:31፤ ሕዝቅኤል 38:18-20
3. በሕዝቅኤል 38:21-23 ላይ ያለውን ዘገባ እንዴት ትገልጸዋለህ?
3 አዎን፣ ሐር— ማጌዶን ወይም አርማጌዶን ተብሎ ወደሚጠራው የዓለም ሁኔታ ስንደርስ ይሖዋ ሕዝቦቹን በማዳን የቀረውን የሰይጣን ሥርዓት ርዝራዥ ሙሉ በሙሉ ጠራርጎ ያጠፋል። በሕዝቅኤል 38:21-23 ላይ የሚገኙትን ትንቢታዊ ቃላት አንብብና ትዕይንቱን በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይሖዋ ኃይሉን በመጠቀም ዶፍ፣ አውዳሚ የበረዶ ድንጋይ፣ የሚንቀለቀል እሳትና ገዳይ ቸነፈር ያወርዳል። የጎግ ጭፍሮች ውዥንብር ውስጥ ገብተው እርስ በርሳቸው ሲተላለቁ በምድር ዙሪያ ሽብር ይነግሣል። ይሖዋ አገልጋዮቹን ለማዳን መለኮታዊ ጥበቃ የሚያደርግላቸው ሲሆን ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጠላቶች መካከል ግን በሕይወት የሚተርፍ አይኖርም። በትንቢት የተነገረው ‘ታላቅ መከራ’ ሲጠናቀቅ አምላካዊ አክብሮት ከሌለው የሰይጣን ሥርዓት የሚተርፍ አንድም ነገር አይኖርም። (ማቴዎስ 24:21) የሞት ጣር ይዟቸውም ቢሆን ክፉዎች ጥፋቱን ማን እንዳመጣባቸው ይገነዘባሉ። ድል አድራጊው አምላካችን ራሱ “እኔም ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ” ሲል ተናግሯል። እነዚህ እንግዳ ክስተቶች የሚፈጸሙት በክርስቶስ መገኘት ወቅት በእኛው ዘመን ነው።
እንደ ሌባ ይመጣል
4. ኢየሱስ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት የሚመጣው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው?
4 ክብር የተጎናጸፈው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “እነሆ፣ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ” በማለት ተናግሯል። እንደ ሌባ ሆኖ መምጣት ማለት ድንገተኛ፣ ያልተጠበቀና አብዛኞቹ ሰዎች አንቀላፍተው እያለ መምጣት ማለት ነው። ኢየሱስ ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት እንደ ሌባ ሆኖ በሚመጣበት ጊዜ በእርግጥ ንቁ ሆነው የቆዩትን ያድናቸዋል። ለዮሐንስ እንዲህ ብሎታል:- “ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” (ራእይ 16:15) እነዚህ ቃላት የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? በመንፈሳዊስ ንቁ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
5. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የቤተ መቅደሱን አገልግሎት ለማከናወን የሚያስችል ምን ዝግጅት ነበር?
5 በአጠቃላይ ሲታይ አንድ ዘብ ጠባቂ በሥራው ላይ እያለ ቢያንቀላፋ መጥቶ ልብሱን የሚገፈው ሰው አይኖርም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበትና የካህናትና ሌዋውያን ምድቦች ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ያገለግሉ በነበረበት ወቅት ይህ ነገር በቤተ መቅደሱ ውስጥ ይፈጸም ነበር። ንጉሥ ዳዊት በመቶዎች የሚቆጠሩት የእስራኤል ካህናትና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩት ሌዋውያን ረዳቶቻቸው በ24 ምድቦች ተደራጅተው እንዲያገለግሉ ያደረገው በ11ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 24:1-18) ከአንድ ሺህ በላይ የሰለጠኑ ሠራተኞች ያሉት እያንዳንዱ ምድብ የቤተ መቅደሱን የተለያዩ አገልግሎቶች ለማከናወን ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ተራ የሚደርሰው ሲሆን በእያንዳንዱ ተራው ወቅት ለአንድ ሙሉ ሳምንት ያገለግላል። ይሁንና በዳስ በዓል ወቅት 24ቱም ምድቦች በሙሉ ሥራቸው ላይ ይገኛሉ። በማለፍ በዓላትም ወቅት ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልግ ነበር።
6. ኢየሱስ “ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብጹዕ ነው” ሲል በተዘዋዋሪ መንገድ ስለምን ነገር መጥቀሱ ሊሆን ይችላል?
6 ኢየሱስ “ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው” ሲል የቤተ መቅደሱን ጥበቃ በተመለከተ ያን ጊዜ የነበረውን አሠራር በተዘዋዋሪ መጥቀሱ ሊሆን ይችላል። የአይሁዳውያን ሚሽና እንዲህ ይላል:- “ካህናቱ በቤተ መቅደሱ በሦስት ቦታዎች ማለትም በአብቲናስ ቤት፣ በእሳቱ ቤትና በምድጃው ቤት እንዲጠብቁ ሲደረግ ሌዋውያን ደግሞ በሃያ አንድ ቦታዎች ማለትም አምስት ሰዎች ቤተ መቅደሱ በሚገኝበት ጉብታ ላይ ባሉት አምስት በሮች ላይ፣ አራት ሰዎች በውስጠኛው አራት ማዕዘኖች ላይ፣ አምስት ሰዎች በቤተ መቅደሱ አደባባይ አምስት በሮች ላይ፣ አራት ሰዎች በአራቱ የአደባባዩ ውጨኛ ማዕዘኖች ላይ፣ አንድ ሰው በመሥዋዕት ቤት እንዲሁም አንድ ሌላ ሰው በመጋረጃው ቤት፣ አንዱ ደግሞ ከምሕረት መቀመጫው ጀርባ ባለው ቦታ [ከቅድስተ ቅዱሳኑ ኋላ ካለው ግድግዳ ውጪ] እንዲቆሙ ይደረጋል። የቤተ መቅደሱ ጉብታ ኃላፊ መቅረዝ ይዞ እያንዳንዱ ጠባቂ ዘንድ ይሄዳል፤ በዚህ ጊዜ ከጠባቂዎቹ መካከል ቆሞ ‘የቤተ መቅደሱ ጉብታ ኃላፊ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን!’ ያላለ ወይም ተኝቶ እንደነበር የታወቀበት ጠባቂ ካለ ኃላፊው በያዘው በትር ይመታዋል፤ እንዲሁም ልብሱን ሳይቀር የማቃጠል መብት ነበረው።”— ሚሽና ሚዶስ (“መለኪያዎች”)፣ 1 አንቀጽ 1-2 ትርጉም በኸርበርት ዳንቢይ።
7. በቤተ መቅደሱ ውስጥ በጥበቃ ሥራ የተሠማሩት ካህናትና ሌዋውያን ነቅተው መጠበቅ የነበረባቸው ለምንድን ነው?
7 በተረኛው ምድብ ውስጥ ያሉት ብዙ ሌዋውያንና ካህናት ንቁ ሆነው የቤተ መቅደሱን አደባባይ ይጠብቁና ርኩስ የሆነ ሰው ወደ አደባባዩ እንዳይገባ ይከላከሉ ነበር። “የቤተ መቅደሱ ጉብታ ኃላፊም” ሆነ “የቤተ መቅደሱ አለቃ” በምሽቱ ጥበቃ ጊዜ 24ቱንም ጣቢያዎች ስለሚዞሩ እያንዳንዱ ጠባቂ ሥራውን ችላ ብሎ እንዳይገኝ ንቁ ሆኖ መጠበቅ ነበረበት።— ሥራ 4:1
8. ምሳሌያዊዎቹ የክርስቲያን መጎናጸፊያዎች ምንድን ናቸው?
8 ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ አብረዋቸው የሚያገለግሉት አጋሮቻቸው በመንፈሳዊ ንቁ መሆንና ምሳሌያዊ መጎናጸፊያዎቻቸውን መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ በይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለሚከናወነው አገልግሎት እንደተሾምን የሚያሳዩ ውጫዊ መግለጫዎች ናቸው። የተጣለብንን የሥራ ኃላፊነት እንድንወጣና የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ የመሆን መብታችንን እንድንፈጽም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ተሰጥቶናል። የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ምድብ ቦታችን ላይ ሆነን የምናንቀላፋ ከሆነ የታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አለቃ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የመያዝ አደጋ ያጋጥመናል። በዚያን ወቅት በመንፈሳዊ አንቀላፍተን ከተገኘን በምሳሌያዊ አነጋገር ልብሳችን ተገፎ በእሳት ይቃጠላል። ታዲያ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?
ንቁ ሆነን መኖር የምንችልበት መንገድ
9. በክርስቲያናዊ ጽሑፎች እየታገዙ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
9 በክርስቲያናዊ ጽሑፎች እየታገዙ ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ማጥናት በመንፈሳዊ ንቁ ለመሆን ያስችለናል። እንዲህ ያለው ጥናት ለአገልግሎት ያስታጥቀናል፣ ችግሮችን ለመቋቋም ከማስቻሉም በላይ ዘላለማዊ ደስታ የሚገኝበትን መንገድ ይጠቁመናል። (ምሳሌ 8:34, 35፤ ያዕቆብ 1:5-8) ጥናታችን ጥልቀት ያለውና እየሰፋ የሚሄድ መሆን ይኖርበታል። (ዕብራውያን 5:14 እስከ 6:3) ዘወትር ጥሩ ምግብ መመገብ ንቁና ጠንቃቃ እንድንሆን ሊረዳን ይችላል። የተመጣጠነ ምግብ እጦት ምልክት የሆነው መልፈስፈስ እንዳይታይብን ሊከላከልልን ይችላል። አምላክ በተቀባው “ታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል በቂ መንፈሳዊ ምግብ ስለሚያቀርብልን ሳንመገብ ቀርተን ደካማ የምንሆንበት ወይም የምናሸልብበት ምንም ምክንያት የለም። (ማቴዎስ 24:45-47) በግልና በቤተሰብ ጥናት አማካኝነት ዘወትር መንፈሳዊ ምግብ መመገባችን በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖርና ‘በእምነት ጤናሞች’ ሆነን ለመገኘት የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው።— ቲቶ 1:13 NW
10. ክርስቲያናዊ የጉባኤ፣ የልዩና የወረዳ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር የሚረዱን እንዴት ነው?
10 ክርስቲያናዊ የጉባኤ፣ የልዩና የወረዳ እንዲሁም የአውራጃ ስብሰባዎች በመንፈሳዊ ንቁ እንድንሆን ይረዱናል። እነዚህ ስብሰባዎች ማበረታቻ ይሰጡናል፤ እንዲሁም ‘እርስ በርስ ለመልካም ሥራ መነቃቃት’ የምንችልበትን አጋጣሚ ይፈጥሩልናል። በተለይ ደግሞ ‘ቀኑ ሲቀርብ እያየን’ አዘውትረን መሰብሰብ ይኖርብናል። ያ ቀን ዛሬ በእርግጥም ቀርቧል። ‘ይሖዋ’ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበት ‘ቀን’ ነው። በእርግጥ ለዚያ ቀን ከፍተኛ ግምት የምንሰጠው ከሆነ (ደግሞም ልንሰጠው ይገባል) ‘አንድ ላይ መሰብሰባችንን አንተውም።’— ዕብራውያን 10:24, 25፤ 2 ጴጥሮስ 3:10
11. ክርስቲያናዊ አገልግሎት በመንፈሳዊ ንቁ ለመሆን የግድ አስፈላጊ ነው ማለት የምንችለው ለምንድን ነው?
11 በመንፈሳዊ ንቁ ለመሆን በክርስቲያናዊ አገልግሎት በሙሉ ልብ መካፈል የግድ አስፈላጊ ነው። በምሥራቹ የስብከት ሥራ ዘወትር በቅንዓት መሳተፍ ጠንቃቆች እንድንሆን ያደርገናል። አገልግሎታችን ለሰዎች ስለ አምላክ ቃል፣ ስለ መንግሥቱና ስለ ዓላማው ለመናገር ብዙ አጋጣሚዎችን ይፈጥርልናል። ከቤት ወደ ቤት መመስከር፣ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንዲሁም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተሰኘውን በመሳሰሉ ጽሑፎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ትልቅ እርካታ ያስገኛል። በጥንቷ ኤፌሶን የነበሩት ሽማግሌዎች ጳውሎስ “ሕዝብ ባለበትና ከቤት ወደ ቤት” እንዳስተማራቸው መስክረዋል። (ሥራ 20:20, 21 NW) እርግጥ ነው አንዳንድ የታመኑ የይሖዋ ምሥክሮች በተወሰነ መጠን አገልግሎታቸውን የሚገታ ከባድ የጤና እክል ይገጥማቸዋል። ይሁን እንጂ ስለ ይሖዋና ስለ ንግሥናው ለሌሎች ሰዎች የሚናገሩበትን መንገድ ይፈልጋሉ፤ ይህን በማድረጋቸው በጣም ይደሰታሉ።— መዝሙር 145:10-14
12, 13. ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት መጠመድ የማይገባን ለምንድን ነው?
12 ከልክ በላይ በሌሎች ነገሮች ከመጠመድ መቆጠብ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንኖር ይረዳናል። ኢየሱስ ስለ መገኘቱ በተናገረ ጊዜ ሐዋርያቱን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል:- “ነገር ግን ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና።” (ሉቃስ 21:7, 34, 35) ሆዳምነትና ሰካራምነት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ይጋጫሉ። (ዘዳግም 21:18-21) ምሳሌ 23:20, 21 (የ1980 ትርጉም) እንዲህ ይላል:- “ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡና ብዙ ምግብ ከሚበሉ ጋር ጓደኛ አትሁን፤ ምክንያቱም ሰካራሞችና ሆዳሞች ይደኸያሉ፤ ሙያው ማንቀላፋት ብቻ የሆነ ሰውም ደኽይቶ ቡትቶ ይለብሳል።”— ምሳሌ 28:7
13 ያለ ልክ መብላትና መጠጣት እዚህ ደረጃ ላይ ባይደርሱም እንኳ ግለሰቡ ድብታ እንዲይዘው አልፎ ተርፎም የአምላክን ፈቃድ በመፈጸም በኩል ሰነፍና ግድ የለሽ እንዲሆን ሊያደርጉት ይችላሉ። ስለ ቤተሰብ ኑሮ፣ ስለ ጤና እና ስለመሳሰሉት ነገሮች መጨነቃችን አይቀርም። ይሁንና በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት የምናስቀድም ከሆነና ሰማያዊ አባታችን የሚያስፈልገንን እንደሚያሟላልን ትምክህት ካለን ደስታ እናገኛለን። (ማቴዎስ 6:25-34) አለዚያ ግን “ያ ቀን” “እንደ ወጥመድ” ምናልባትም ተሠውሮ እንደተቀመጠ ወይም ያልጠረጠሩ እንስሳትን አባብሎ እንደሚይዝ ወጥመድ ሊደርስብን ይችላል። ‘በመጨረሻው ቀን’ እንደምንኖር ሙሉ በሙሉ ተገንዝበን ንቁ ሆነን ከኖርን እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብንም።— ዳንኤል 12:4
14. ልባዊ ጸሎት ማቅረብ የሚገባን ለምንድን ነው?
14 በመንፈሳዊ ንቁ ለመሆን የሚረዳን ሌላው ነገር ከልብ የሚቀርብ ጸሎት ነው። ኢየሱስ በታላቁ ትንቢቱ ውስጥ “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ” በማለት ጨምሮ አሳስቧል። (ሉቃስ 21:36) አዎን፣ ዘወትር በይሖዋ ጎን ለመሰለፍና የሰው ልጅ የተባለው ኢየሱስ ይህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ለማጥፋት በሚመጣበት ጊዜ ሞገስ አግኝተን በፊቱ ለመቆም እንድንችል እንጸልይ። ለራሳችንና በጸሎታችን ለምናስባቸው መሰል አማኞች ጥቅም ስንል ‘በጸሎት ንቁ ሆነን መኖር ያስፈልገናል።’— ቆላስይስ 4:2፤ ኤፌሶን 6:18-20
ጊዜው እያለቀ ነው
15. የጽድቅ ሰባኪዎች በመሆን የምንፈጽመው አገልግሎት ምን ነገር ያከናውናል?
15 ታላቁን የይሖዋን ቀን መምጣት ስንጠባበቅ በአገልግሎቱ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ እንደምንፈልግ ምንም አያጠራጥርም። ስለዚህ ጉዳይ ከልባችን ወደ እርሱ የምንጸልይ ከሆነ “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” ሊከፈትልን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 16:8, 9) አምላክ በቀጠረው ጊዜ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት የሚገባቸውን ጻድቅ “በጎች” ዘላለማዊ ጥፋት ከሚገባቸው አምላካዊ አክብሮት ከሌላቸው “ፍየሎች” በመለየት ፍርድ ይሰጣል። (ዮሐንስ 5:22) በጎቹን ከፍየሎቹ የምንለየው እኛ አይደለንም። ይሁን እንጂ የጽድቅ ሰባኪዎች በመሆን የምናከናውነው አገልግሎት ሰዎች ዛሬ አምላክን እያገለገሉ መኖርን መርጠው ኢየሱስ ‘በክብሩ በሚመጣበት’ ጊዜ ለሕይወት ከሚለዩት ሰዎች ወገን የመሆን ተስፋ እንዲያገኙ በር ይከፍትላቸዋል። ይህ የነገሮች ሥርዓት የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑ “ለዘላለም ሕይወት ትክክለኛ ዝንባሌ” ያላቸውን ሰዎች ለመፈለግ የምናደርገውን እንቅስቃሴ በሙሉ ልብ የማከናወኑን አስፈላጊነት ያጎላዋል።— ማቴዎስ 25:31-46፤ ሥራ 13:48 NW
16. ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
16 በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለም ጊዜው አልቆበት ነበር፤ ይህ የነገሮች ሥርዓት የቀረውም ጊዜ በቅርቡ ያበቃል። እንግዲያውስ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንሁን። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በማሳየት መጠመቃቸው የስብከት ሥራችን እየጎለበተ እንደሄደ ያሳያል። እነዚህ ሰዎች የተባረከው የይሖዋ ድርጅት ክፍል በሌላ አባባል “ሕዝቡ የማሰማሪያውም በጎች” እየሆኑ ነው። (መዝሙር 100:3) ‘ታላቁና የሚያስፈራው የይሖዋ ቀን’ ከመምጣቱ በፊት ብዙ ሰዎች ተስፋ እንዲጨብጡ በሚያስችለው የመንግሥቱ የስብከት ሥራ መካፈል እንዴት ያስደስታል!
17, 18. (ሀ) በምንሰብክበት ጊዜ አንዳንዶች ምን ዓይነት ምላሽ ይሰጡናል ብለን መጠበቅ ይኖርብናል? (ለ) ፌዘኞች ምን እንደሚደርስባቸው የተረጋገጠ ነው?
17 ልክ እንደ ኖኅ እኛም የአምላክ ድጋፍና ጥበቃ አለን። አዎን፣ ሕዝቡ ሥጋ የለበሱት መላእክትና ኔፍሊሞች በኖኅ መልእክት ተዘባብተውበት መሆን አለበት፤ ይሁን እንጂ ወደ ኋላ እንዲል አላደረገውም። ዛሬም ‘በመጨረሻው ቀን’ እንደምንኖር የሚያሳዩትን በርካታ ማስረጃዎች ስንጠቅስ አንዳንዶች ይዘብቱ ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) እንዲህ ዓይነቱ ፌዝ የክርስቶስን መገኘት በተመለከተ የተነገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ ነው። ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም:- የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።”— 2 ጴጥሮስ 1:16፤ 3:3, 4፤ ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን።
18 ዛሬ ያሉት ፌዘኛ ሰዎች ‘ከፍጥረት ጀምሮ የተለወጠ ነገር የለም። ሰዎች ይበላሉ፣ ይጠጣሉ፣ ያገባሉ፣ ልጆች ወልደው ያሳድጋሉ፤ ሕይወት በዚህ መልኩ ይቀጥላል። ኢየሱስ በሥልጣኑ ቢገኝም እንኳ በእኛ ዘመን እርምጃ አይወስድም። ብለው ያስባሉ። ምንኛ ተሳስተዋል! በኖኅ ዘመን የነበረው ክፉ ትውልድ በደረሰበት እንደ መቅሰፍት ያለ ጥፋት ጨርሶ እንደተደመሰሰ ሁሉ ዛሬ ያሉትም በመሀሉ በሌላ ምክንያት ካልሞቱ በቀር የዚህ ክፉ ትውልድ ክፍል በመሆናቸው ከታላቁ የይሖዋ ቀን ጥፋት አያመልጡም።— ማቴዎስ 24:34
ንቁ ሆነን መኖር ይገባናል!
19. ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራችንን እንዴት ልናየው ይገባል?
19 ራሳችንን ለይሖዋ የወሰንን ሰዎች ከሆንን በተሳሳቱ አስተሳሰቦች ፈጽሞ የምናሸልብ መሆን የለብንም። ይህ ንቁ ሆነን የምንኖርበት፣ በመለኮታዊ ትንቢት ላይ እምነት እንዳለን የምናሳይበት እንዲሁም ‘አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት’ የማድረግ ተልእኮአችንን የምንወጣበት ጊዜ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) ይህ ሥርዓት ወደ መጨረሻው እየተቃረበ ሲመጣ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር ሆነን ይሖዋ አምላክን ከማገልገል እንዲሁም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በመስበኩ ምድር አቀፍ ሥራ ከመካፈል የሚበልጥ ሌላ መብት ሊኖር አይችልም።— ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10
20. ካሌብና ኢያሱ ምን ምሳሌ ትተውልናል? እነርሱ ያደረጉት ነገር እኛን እንዴት ይነካናል?
20 አንዳንዶቹ የይሖዋ ሕዝቦች ለብዙ አሥርተ ዓመታት ምናልባትም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ይሖዋን ሲያገለግሉ ቆይተዋል። እውነተኛውን አምልኮ የተቀበልነው በቅርቡም እንኳ ቢሆን ‘ፈጽሞ ይሖዋን እንደተከተለው’ እስራኤላዊው ካሌብ እንሁን። (ዘዳግም 1:34-36) ካሌብና ኢያሱ እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ነጻ ከወጡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት በሚገባ ተዘጋጅተው ነበር። ይሁን እንጂ ጎልማሳ የነበሩት እስራኤላውያን በአጠቃላይ እምነት በማጣታቸው 40 ዓመታት በበረሃ ተንከራተው ሞተዋል። ካሌብና ኢያሱ ያን ሁሉ ጊዜ ከእነርሱ ጋር በመከራ መጽናት አስፈልጓቸዋል፤ ይሁን እንጂ በመጨረሻ እነዚህ ሁለት ሰዎች ወደ ተስፋይቱ ምድር ገብተዋል። (ዘኁልቁ 14:30-34፤ ኢያሱ 14:6-15) ‘ፈጽሞ ይሖዋን የምንከተልና’ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን የምንኖር ከሆነ ወደ አምላክ አዲስ ዓለም በመግባት እንደሰታለን።
21. በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ብንኖር ምን እናገኛለን?
21 በፍጻሜው ዘመን ላይ እንደምንኖርና ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ እንደሆነ ማስረጃዎቹ በግልጽ ያሳያሉ። ይህ የምናንቀላፋበትና መለኮታዊውን ፈቃድ ከመፈጸም የምንዘናጋበት ጊዜ አይደለም። የምንባረከው በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ክርስቲያን አገልጋዮችና የይሖዋ አምላኪዎች አድርጎ የሚያሳውቀንን ልብሳችንን ከጠበቅን ብቻ ነው። ‘ነቅተን ለመኖር፣ በእምነት ጸንተን ለመቆም፣ በብርታት ወደፊት ለመግፋት እንዲሁም እየጎለበትን ለመሄድ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። (1 ቆሮንቶስ 16:13) የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን እያንዳንዳችን ጽኑዎችና ደፋሮች እንሁን። እንዲህ ካደረግን ነቅተው በመኖራቸው ደስተኛ ከሆኑትና በታማኝነት እያገለገሉ ታላቁ የይሖዋ ቀን በሚጀምርበት ጊዜ ራሳቸውን አዘጋጅተው ከሚቆዩት ሰዎች መካከል እንሆናለን።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ምሳሌያዊ መጎናጸፊያዎቻችን ምንድን ናቸው? ልንጠብቃቸውስ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ መኖር የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ ፌዘኞች ያጋጥሙናል ብለን ልንጠብቅ የሚገባው ለምንድን ነው? እንዴትስ ልናያቸው ይገባል?
◻ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ክርስቲያኖች ንቁ ሆነው እንዲኖሩና የተጣለባቸውን የሥራ ኃላፊነት እንዲወጡ የሚረዳቸውን የአምላክ መንፈስ ያገኛሉ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመንፈሳዊ ንቁ ሆነህና ምሳሌያዊ መጎናጸፊያህን ጠብቀህ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃልን?