በእውቀት ማደጋችሁን ቀጥሉ
“በእምነታችሁ . . . እውቀትን ጨምሩ። ” — 2 ጴጥሮስ 1:5
1, 2. (ሀ) ሰማያትን በመመልከት ምን ልትማር ትችላለህ? (ሮሜ 1:20) (ለ) የሰው ልጅ እውቀት የሚጨምረው እስከ ምን ድረስ ነው?
በጠራና ጨለማ በሆነ ሌሊት ከቤትህ ወጣ ብለህ ብሩኅ የሆነችውን ጨረቃንና ለቁጥር የሚታክቱትን ከዋክብት በማየት ምን ልትማር ትችላለህ? እነዚህን ሁሉ ስለ ሠራ ፈጣሪ አንድ ነገር ልትማር ትችላለህ። — መዝሙር 19:1–6፤ 69:34
2 እንደዚህ ያለውን እውቀትህን ለመጨመር እቤትህ ጣራ ላይ ወጥተህ ትመለከታለህን? እንደዚያ ላታደርግ ትችላለህ። የሳይንስ ሊቃውንት ስለ ጽንፈ ዓለምና ስለ ፈጣሪው ያላቸውን እውቀት ምንም ያህል እንዳልጨመሩ ነገሩን ለማስረዳት አልበርት አንስታይን እንደዚህ ባለ ምሳሌ ተጠቅሟል።a ዶክተር ሌዊስ ቶማስ “ከዘመናት ሁሉ ይበልጥ በጣም ፍሬያማ በሆነው በዚህ ዘመን ከፍተኛው ሳይንሳዊ ግኝት ምንም አለማወቃችንን መረዳታችን ነው። ስለ ተፈጥሮ የምናውቀውና የተረዳነው በጣም ትንሹን ብቻ ነው” በማለት ጽፈዋል።
3. የእውቀት መጨመር ኀዘንን የሚጨምረው በምን መንገድ ነው?
3 ይህንን እውቀት ለማግኘት በመፈለግ የአንድ ሰው ዕድሜ ነው ተብሎ ከሚታሰበው ጊዜ ቀሪውን እንኳ ብታሳልፍ ሕይወት ምን ያህል አጭር እንደሆነና ሰው ባለፍጽምናና በዚህ ዓለም ‘ጠማማነት’ የተነሣ እውቀቱን የሚጠቀምበት በጣም በተመጠነ መንገድ መሆኑን ይበልጥ ትገነዘባለህ። ሰሎሞን ይህንን ነጥብ ጠቅሶ “በጥበብ መብዛት ትካዜ ይበዛልና፤ እውቀትንም የሚጨምር ኀዘንን ይጨምራልና” በማለት ጽፏል። (መክብብ 1:15, 18) ከአምላክ ዓላማ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው እውቀትና ጥበብ ትርፉ ኀዘንና ብስጭት ነው። — መክብብ 1:13, 14፤ 12:12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:20
4. እንዲኖረን መፈለግ የሚገባን ምን ዓይነት እውቀት ነው?
4 ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እውቀታችንን የመጨመር ፍላጎት እንዳያድርብን መምከሩ ነውን? ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:18) ይህንን ምክር በእውቀት እንድናድግ ለእኛ የተሰጠ ማሳሰቢያ አድርገን ልንወስደው እንችላለን እንዲሁም ይገባናል። ይሁን እንጂ እውቀቱ ምን ዓይነት ነው? ይህንን እውቀት እንዴት ልንጨምር እንችላለን? እንደዚያስ እያደረግን ነውን?
5, 6. እውቀት ማግኘት እንደሚያስፈልገን ጴጥሮስ ጎላ አድርጎ የጠቀሰው እንዴት ነው?
5 የጴጥሮስ ሁለተኛ ደብዳቤ ዋና መልእክት ያተኮረው ስለ ጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪና ስለ ኢየሱስ ያለንን ትክክለኛ እውቀት በማሳደጉ ጉዳይ ላይ ነው። በደብዳቤው መክፈቻ ላይ “የመለኮቱ ኃይል፣ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ [በትክክለኛ እውቀት አዓት]፣ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል [ለአምላክ ያደሩ ለመሆን አዓት] የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፣ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት [ትክክለኛ እውቀት አዓት] ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 1:2, 3) ጸጋና ሰላም ማግኘቱን ስለ አምላክና ስለ ልጁ እውቀት ከመቅሰም ጋር አያይዞታል። የእውነተኛ እውቀት መሠረቱ ፈጣሪያችን ይሖዋ ስለሆነ እንደዚያ መባሉ ምክንያታዊ ነው። አምላክን የሚፈራ ሰው ነገሮችን በትክክለኛ ብርሃን ሊመለከታቸውና ወደ ተገቢ መደምደሚያዎችም ሊደርስ ይችላል። — ምሳሌ 1:7
6 ቀጥሎም ጴጥሮስ “በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነትም እውቀትን፣ በእውቀትም ራስን መግዛት፣ ራስንም በመግዛት መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት]፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል [ለአምላክ ያደሩ በመሆንም አዓት] የወንድማማችን መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ። እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፣ በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጉአችኋልና” በማለት አሳስቧል። (2 ጴጥሮስ 1:5–8)b በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እውቀት የማግኘቱ ጉዳይ ሰዎችን በዚህ ዓለም ከመቆሸሽ እንዲያመልጡ የሚረዳቸው መሆኑን እናነባለን። (2 ጴጥሮስ 2:20) ስለዚህ ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ለመሆን በመዘጋጀት ላይ ያሉ ሁሉ ይሖዋን በማገልገል ላይ እንዳሉት ሰዎች እውቀት የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ግልጽ አድርጎታል። አንተስ ከእነዚህ ከሁለቱ ቡድኖች በአንደኛው ውስጥ አለህበትን?
ተማር፣ ደጋግመው፣ ሥራበት
7. ብዙ ሰዎች መሠረታዊ ስለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ትክክለኛ እውቀት ያገኙት በምን መንገድ ነው?
7 መልእክታቸው እውነትነት እንዳለው ስለተገነዘብህ ከይሖዋ ምስክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ ይሆናል። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ እንደሚባለው መጽሐፍ ባለ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዳ ጽሑፍ አማካኝነት በሳምንት አንድ ጊዜ ለአንድ ሰዓት ያህል እየተወያየህ ይሆናል። እጅግ በጣም ጥሩ ነው! ከይሖዋ ምስክሮች ጋር እንደዚህ ያለ ጥናት ያደረጉ ብዙ ሰዎች ትክክለኛ እውቀት አግኝተዋል። ታዲያ የእውቀትህን መጠን ለመጨመር በግልህ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበውልሃል።c
8. ለጥናቱ ሲዘጋጅ ብዙ ለመማር አንድ ተማሪ ምን ሊያደርግ ይችላል?
8 ከሁሉም በፊት ለጥናትህ ስትዘጋጅ የሚጠናው ጽሑፍ ምን እንደያዘ አገላብጠህ ተመልከተው። ይህም ማለት የምዕራፉን ርዕስ፣ ንዑሳን ርዕሶቹንና ትምህርቱን በምሳሌ ለማስረዳት የቀረቡ ሥዕሎች ካሉ እነሱን ሁሉ መመልከትን ይጨምራል። ከዚያም አንቀጹን ወይም የጽሑፉን አንድ ክፍል ስታነብ ቁልፍ ሐሳቦቹንና እርሱን ለማብራራት የተጠቀሱትን ጥቅሶች ፈልገህ ለማግኘት ሞክርና አስምርባቸው ወይም ደመቅ አድርገህ ቀባቸው። የተጠቀሱትን እውነቶች አውቀሃቸው እንደሆነ ለማረጋገጥ እንድትችል ለየአንቀጾቹ የቀረቡትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር። ይህን ስታደርግ መልሶቹን በራስህ አገላለጽ ለመናገር ሞክር። በመጨረሻም ዋና ዋና ሐሳቦቹንና የቀረቡትን ማስረጃዎች ለማስታወስ እየሞከርክ ትምህርቱን ከልሰው።
9. አንድ ሰው ስለ ጥናት የተሰጡትን ሐሳቦች ቢሠራባቸው እውቀት በማግኘት ረገድ እንዴት ሊጠቀም ይችላል?
9 እነዚህን ሐሳቦች ከሠራህባቸው እውቀትህ እንደሚጨምር ልትጠባበቅ ትችላለህ። ለምን እንደዚህ እንላለን? አንዱ ምክንያት እንደዚህ ስታደርግ ለማወቅ ባለህ ጉጉት ተነሣስተህ፣ ማለትም አፈሩን አለስልሰህ፣ ትምህርቱን ታጠናለህ። አጠቃላይ መልኩን ስታይና ዋና ዋና ነጥቦቹ የቀረቡበትን አሳማኝ ማብራሪያዎች ስትመለከት ዝርዝር ሐሳቦቹ ከትምህርቱ መልእክት ወይም ከመደምደሚያው ጋር እንዴት እንደተዛመዱ ትገነዘባለህ። መጨረሻ ላይ የምታደርገው ክለሳ ያጠናኸውን እንድታስታውስ ይረዳሃል። ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ወቅት ምን ታደርጋለህ?
10. (ሀ) አንዳንድ ቁም ነገሮችን ወይም አዳዲስ ሐሳቦችን ደጋግሞ መናገሩ ብቻ ጥቅም የሌለው ለምንድን ነው? (ለ) “እየቆዩ የተማሩትን ማስታወስ” ምን ማድረግን ይጨምራል? (ሐ) እስራኤላውያን ልጆች ትምህርትን ከመደጋገም እንዴት ተጠቅመው ሊሆን ይችላል?
10 በማስተማሩ መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎች ወቅቱን የጠበቀና በዓላማ የተደረገ ድግምግሞሽ ጠቃሚ መሆኑን ተረድተዋል። ይህ ገና ተማሪ ሳለህ አንዳንድ ስሞችን፣ አስረጂዎችን ወይም ሐሳቦችን ስትማር ትደጋግም እንደነበረው እንዲሁ ቃላትን የማስተጋባት ጉዳይ ብቻ አይደለም። የተማርከውን እንደገና ለመጥቀስ ስትፈልግ ከአእምሮህ በቶሎ ጠፍቶ የረሳህበትን ጊዜ ታስታውሳለህን? ለምን ረሳኸው? አንድን አዲስ ቃል ወይም ማስረጃ ማስተጋባት አሰልቺ ሊሆንና ውጤቱም ዘላቂነት ላይኖረው ይችላል። ይህንን ሁኔታ ምን ነገር ሊለውጠው ይችላል? ለማወቅ ያለህ እውነተኛ ፍላጎት በዚህ በኩል ሊረዳህ ይችላል። ሌላው ጠቃሚ ነገር ደግሞ አልፎ አልፎ ነገሮቹን በዓላማ መደጋገም ነው። አንድን ነጥብ አንብበህ ከተማርክ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎች ቆይተህ በአእምሮህ ውስጥ ከመደብዘዙ በፊት ምን እንደተማርክ ራስህን በውስጥህ ጠይቀህ ለማስታወስ መሞከር ነው። ይህ ዘዴ “እየቆዩ የተማሩትን ማስታወስ” ተብሎ ይጠራል። በአእምሮህ የማስታወሻ መዝገብ ውስጥ የገባው ነገር ከመደብዘዙ በፊት አእምሮህን በማነቃቃት የተማርከውን ነገር በአእምሮህ ይዘህ ለረጅም ጊዜ ማቆየት ትችላለህ። በእስራኤል አገር አባቶች ለልጆቻቸው የአምላክን ትእዛዞች ማስተማር ነበረባቸው። (ዘዳግም 6:6, 7) “አስተምረው” ተብሎ የተተረጎመው “ኢንከልኬት” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል በመደጋገም ዘዴ ተጠቅመህ ትምህርቱን አስተላልፍ ማለት ነው። ስለዚህም እነዚያ አባቶች በመጀመሪያ ለልጆቻቸው ሕጉ ምን እንደሚል ይነግሯቸዋል። ቆይተው ደግሞ ያንኑ ትምህርት ይደግሙላቸዋል። ከዚያም ስለተማሩት ነገር ልጆቻቸውን ጥያቄ ይጠይቋቸዋል።
11. በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት የመማሩን ሂደት ከፍ ለማድረግ ምን ሊደረግ ይቻላል?
11 አንድ የይሖዋ ምስክር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየመራልህ ወይም እየመራችልሽ ከሆነ ጥናቱን በምታጠኑበት ጊዜ አልፎ አልፎ እድገት ለማድረግ የሚረዳ ክለሳ በማዘጋጀት ሊረዳህ ይችላል ወይም ልትረዳሽ ትችላለች። ይህ ለልጆች እንደተዘጋጀ ጥናት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። ይህ ዘዴ በደንብ ለመማር የሚረዳ ስለሆነ በየወቅቱ በሚዘጋጁት የክለሳ ጥያቄዎች ደስ ብሎህ ተሳተፍ። ከዚያም ጥናቱ ሲያበቃ በሚደረገው የማጠቃለያ ጥያቄ የምታስታውሰውን በመመለስ ተካፋይ ሁን። ነጥቦቹን ስታብራራ ለሌላ ሰው እንደምታስተምር አድርገህ በራስህ አነጋገር ለመጠቀም ሞክር። (1 ጴጥሮስ 3:15) ይህንን ማድረግህ የተማርከው ነገር ለረጅም ጊዜ በአእምሮህ ውስጥ እንዲቆይ ይረዳሃል። — ከመዝሙር 119:1, 2,125 እና ከ2 ጴጥሮስ 3:1 ጋር አወዳድር።
12. የማስታወስ ችሎታውን ለማሻሻል ተማሪው በበኩሉ ምን ሊያደርግ ይችላል?
12 ሌላው ሊረዳህ የሚችለው እርምጃ በአንድና በሁለት ቀን ውስጥ ለአንድ ሌላ ሰው ማለትም ለትምህርት ቤት ጓደኛህ፣ አብሮህ ለሚሠራ ወይም ለጎረቤትህ ስለተማርከው ነገር መናገር ነው። ርዕሱን በመጥቀስ ልትጀምርና ከዚያም የቀረቡትን ቁልፍ የማሳመኛ ነጥቦች ወይም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ድጋፍ ሰጪ ጥቅሶችን ታስታውስ እንደሆነ ራስህን ለመፈተሽ እንደምትፈልግ ልትጠቅስለት ትችላለህ። ምናልባት ይህ ሁኔታ የሌላውን ሰው ፍላጎት ይቀሰቅስ ይሆናል። ፍላጎት እንኳ ባይቀሰቅስ ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ያገኘኸውን አዲስ እውቀት መድገምህ የተማርከውን ለማስታወስ እንድትችል ያግዝሃል። እንዲህ ከሆነ በ2 ጴጥሮስ 3:18 ላይ ባለው ማሳሰቢያ መሠረት እውቀት አግኝተሃል ማለት ነው።
ንቁ ሆኖ መማር
13, 14. እንዲሁ እውቀት በማግኘትና በማስታወስ ብቻ መርካት የማይገባን ለምንድን ነው?
13 መማር ሲባል እውቀት ወደ አእምሮ ማስገባት ወይም አንዳንድ ሐሳቦችን ለማስታወስ መቻል ማለት ብቻ አይደለም። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሃይማኖታዊ ሰዎች በድግምት ጸሎቶቻቸው አማካኝነት ይህንን ያደርጉ ነበር። (ማቴዎስ 6:5–7) ይሁን እንጂ እየደጋገሙ በሚናገሩት ሐሳብ እንዴት ተነኩ? የጽድቅ ፍሬዎችን አፍርተው ነበርን? ፈጽሞ አላፈሩም! (ማቴዎስ 7:15–17፤ ሉቃስ 3:7, 8) አንዱ ችግራቸው ውጤት ያለው ሥራ እንዲሠሩ የሚያደርጋቸው እውቀት ወደ ልባቸው ጠልቆ አለመግባቱ ነበር።
14 በጴጥሮስ አነጋገር መሠረት በጥንትም ጊዜ ይሁን አሁን የክርስቲያኖች ሁኔታ ከዚያ የተለየ መሆን ይኖርበታል። በእምነታችን ላይ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች ከመሆን የሚጠብቀንን እውቀት እንድንጨምር አሳስቦናል። (2 ጴጥሮስ 1:5, 8) ይህ ምክር በእኛ ላይ እንዲሠራ ከተፈለገ በዚህ እውቀት የማደግና እውቀቱም ውስጣችንን ጠልቆ እንዲነካ መፈለግ ይገባናል። ይህ ሁልጊዜ እንደዚያ ላይሆን ይችላል።
15. በአንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ዘንድ ምን ችግር ተፈጥሮ ነበር?
15 በጳውሎስ ዘመን የነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ ችግር ነበረባቸው። አይሁድ እንደመሆናቸው ስለ ቅዱሳን ጽሑፎች መጠነኛ የሆነ እውቀት ነበራቸው። ስለ ይሖዋና እሱ ስለሚፈልግባቸው አንዳንድ ነገሮች ያውቁ ነበር። በኋላም ስለ መሲሑ የሚናገር ተጨማሪ እውቀት አገኙ፣ በእሱም አመኑበት፣ ከዚያም ክርስቲያን በመሆን ተጠመቁ። (ሥራ 2:22, 37–41፤ 8:26–36) ለብዙ ወራትና ዓመታት በክርስቲያን ስብሰባዎች ተገኝተው ጥቅሶችን በማንበብና ሐሳብ በመስጠት ተሳትፈው መሆን አለበት። እንዲህም ሆኖ አንዳንዶቹ በእውቀት አላደጉም ነበር። ጳውሎስ “እስከ አሁን በነበረው ጊዜ እናንተ አስተማሪዎች መሆን በተገባችሁ ነበር፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት ሌላ ሰው እንደገና እንዲያስተምራችሁ ያስፈልጋል፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም” በማለት ጽፎ ነበር። (ዕብራውያን 5:12 የ1980 ትርጉም) ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በእኛስ ላይ ሊደርስ ይችል ይሆንን?
16. ፐርማፍሮስት እየተባለ የሚጠራው ቋሚ የሆነ ቅዝቃዜ ምንድን ነው? ተክሎችንስ እንዴት ይነካቸዋል?
16 እንደ ምሳሌ አድርገን አማካይ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች በሆነባቸው በአርክቲክና በሌሎች ስፍራዎች የሚገኘውን ፐርማፍሮስት እየተባለ የሚጠራውን ሁልጊዜ ቀዝቃዛ የሆነውን መሬት እንውሰድ። እስከ 900 ሜትር በሚደርስ ጥልቀት ላይ የሚገኘው አፈር፣ ድንጋይና ከመሬት በታች ያለው ውኃ ወደ ጠጣርነት እስኪለወጥ ድረስ በጣም ቀዝቃዛዎች ናቸው። በበጋ በረዶው ከቀለጠ ከላይ ያለው የአፈሩ ክፍል ተገልጦ (ሊያበቅል የሚችል መሬት) ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ጥልቀት የሌለው የተገለጠ አፈር ከሥር ወዳለው ፐርማፍሮስት ወደሆነው መሬት እርጥበቱ ሰርጎ ስለማይገባና ስለማይጠፍ አብዛኛውን ጊዜ ጭቃማ ይሆናል። በዚህ ጥልቀት በሌለው አፈር ላይ የሚበቅሉት ተክሎች ብዙ ጊዜ መጠናቸው አነስተኛ የሆነና የቀጨጩ ናቸው። ሥሮቻቸው ፐርማፍሮስቱን ጥሰው ሊገቡ አይችሉም። ‘ታዲያ ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ የእውነት እውቀት ከማደጌ ጋር ምን ያገናኘዋል?’ ብለህ ትገረም ይሆናል።
17, 18. በአንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ላይ የተፈጠረውን ችግር በምሳሌ ለማስረዳት ፐርማፍሮስትና ተክሎችን ማብቀል የሚችለው ጥልቀት የሌለው አፈር እንዴት ሊያገለግሉ ይችላሉ?
17 ፐርማፍሮስት ትክክለኛ እውቀትን ለማግኘት በሚደረገው እንቅስቃሴም ሆነ የተማረውን ለማስታወስ ምንም ጥረት የማያደርግ አእምሮ ያለውን ሰው ሁኔታ ሊገልጽ የሚችል ተስማሚ ምሳሌ ነው። (ከማቴዎስ 13:5, 20, 21 ጋር አወዳድር።) ግለሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ጨምሮ ስለ ሌሎች ጉዳዮች መማር የሚያስችል በቂ የአእምሮ ችሎታ አለው። “የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያ ትምህርት” ተምሯል እንዲሁም እነዚያ ዕብራውያን ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ብቃቱን አሟልቶ ተጠምቆ ይሆናል። ነገር ግን “ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት” ትቶ ‘ወደ ጉልምስና አልገፋ’ ይሆናል። — ዕብራውያን 5:12፤ 6:1 የ1980 ትርጉም
18 በዚያን ጊዜ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በስብሰባ ሲገኙ ምን ያደርጉ እንደነበረ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል እንቅልፍም አልወሰዳቸውም። ዳሩ ግን አእምሮአቸው በመማሩ ሂደት ይሳተፍ ነበርን? ነቅተውና ተግተው በእውቀት እያደጉ ነበርን? ምናልባት እንደዚያ ላይሆን ይችላል። ላልጎለመሱት በስብሰባው ላይ የሚደረገው ነገር ሁሉ ከሥሩ ጥልቀት ያለው ቅዝቃዜ ኖሮ ከላዩ ግን ጥልቀት እንደሌለው መሬት ሆኖባቸው ነበር። ጠንካራ ወይም አመራማሪ የሆኑት የእውነት ሥሮች ፐርማፍሮስት በሆነው አእምሮ ውስጥ ጠልቀው መግባት አልቻሉም። — ከኢሳይያስ 40:24 ጋር አወዳድር።
19. የብዙ ዓመት ልምድ ያለው ክርስቲያን እንደ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሊሆን የሚችለው በምን መንገድ ነው?
19 ዛሬ በሚኖር አንድ ክርስቲያን ላይም ተመሳሳይ ነገር ሊደርስበት ይችላል። በስብሰባዎች ላይ ቢገኝም እነዚህን አጋጣሚዎች በእውቀት እንዲያሳድጉት አድርጎ አይጠቀምባቸውም። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ነቅቶ የመሳተፉስ ጉዳይ? ለአዲስ ሰው ወይም ለአንድ ወጣት ልጅ ጥቅስ ለማንበብ ፈቃደኛ መሆኑ ወይም አንቀጹ ውስጥ ባሉት ቃላት ተጠቅሞ ሐሳብ መስጠቱ ጥረት ማድረግ ጠይቆበት ይሆናል። ይህም ጥሩ የሆነ የሚያስመሰግነው ሙከራ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ ሌሎቹ ክርስቲያን ከሆኑበት ጊዜ አንጻር ሲታይ በእውቀት ማደጋቸውን እንዲቀጥሉበት ከፈለጉ የተሳትፎ ልምምድ ካደረጉበት ከዚህ የመጀመሪያ ሙከራ አልፈው መራመድ እንደሚኖርባቸው አመልክቷል። — ዕብራውያን 5:14
20. እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ምን ምርመራ ማድረግ ይገባናል?
20 አንድ ለረጅም ጊዜ የቆየ ክርስቲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከማንበብ ወይም ከአንቀጹ እያነበበ ሐሳብ ከመስጠት ምንም እልፍ የማይል ከሆነ የሱ ተሳትፎ “ጥልቀት በሌለው” የአእምሮው ክፍል ብቻ የተደረገ ተሳትፎ ነው ማለት ነው። ስለ ፐርማፍሮስት የሰጠነውን ምሳሌ ብንቀጥልበት፣ ስብሰባ አልፎ ስብሰባ ሲተካ ጥልቀት ያለው የአእምሮው የመማር ችሎታ እንደዛው እንደ ቀዘቀዘ ይቀጥላል ማለት ነው። ራሳችንን እንደዚህ እያልን ልንጠይቅ ይገባናል:- ‘የእኔ ሁኔታ እንደዚህ ነውን? ፐርማፍሮስት እንዲኖርብኝ ፈቅጄ ይሆንን? እውቀት ለማግኘት በአእምሮዬ ንቁ የሆንኩና ጉጉት ያለኝ ነኝን?’ ምንም እንኳ ለጥያቄዎቹ የምንሰጠው ሐቀኛ መልስ ደስ የሚል ላይሆን ቢችልም በእውቀት ለማደግ ከአሁን ጀምረን እርምጃ መውሰድ እንችላለን።
21. ለስብሰባ በመዘጋጀት ወይም በስብሰባ ላይ በመገኘት በኩል ከዚህ በፊት የተወያየንባቸውን የትኞቹን እርምጃዎች ልትሠራባቸው ትችላለህ?
21 በግላችን በአንቀጽ 8 ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ በሥራ ላይ ልናውል እንችላለን። ከጉባኤው ጋር መቀራረብ የጀመርንበት ጊዜ ምንም ያህል ረጅም ይሁን በጉልምስና ለማደግና ብዙ ለማወቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። ይህም ለአንዳንዶች ለስብሰባ ሲዘጋጁ ይበልጥ ትጋት መጨመርን ምናልባትም ለብዙ ዓመታት ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ነገር ግን ቀስ በቀስ የተዉአቸውን ልማዶቻቸውን መመለስ ማለት ሊሆን ይችላል። በምትዘጋጅበት ጊዜ ቁልፍ ነጥቦቹ የትኞቹ እንደሆኑና ነጥቦቹን በሚያሳምን መንገድ ለማቅረብ የተጠቀሱትን ለአንተ እንግዳ የሆኑብህን ጥቅሶች ለመረዳት ሞክር። እየተጠና ባለው ትምህርት ውስጥ የሚገኙትን አዲስ አቀራረቦች ወይም የአገላለጽ አቅጣጫዎች ተመልከት። በተመሳሳይም በስብሰባው ወቅት በአንቀጽ 10 እና 11 ላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች ልትሠራባቸው ሞክር። በአእምሮህ ውስጥ ያለውን የሙቀት መጠን ከፍ እንዳደረግህ ያህል በአእምሮህ ንቁ ለመሆን ጣር። እንደዚህ ማድረግ ማንኛውንም ዓይነት “ፐርማፍሮስት” ወደ አእምሮህ የማስገባት ዝንባሌ እንዳይኖር ይከላከላል። ሆን ተብሎ የሚደረገው እንደዚህ ዓይነቱ ጥረት ቀደም ሲል ተፈጥሮ የነበረን ማንኛውንም “የቀዘቀዘ” ሁኔታ ያቀልጠዋል። — ምሳሌ 8:12, 32–34
እውቀት ፍሬያማ ለመሆን ይረዳል
22. እውቀታችንን ለመጨመር ጥረት ብናደርግ እንዴት እንጠቀማለን?
22 በጌታችንና በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት በማደጉ ጉዳይ ላይ ብንሠራበት በግለሰብ ደረጃ እንዴት እንጠቀማለን? ሆነ ብለን ጥረት በማድረግ የአእምሮአችንን የማሰብ ኃይል እውቀት እንዲወስድ ብናዘጋጀው፣ አዲስና ይበልጥ አመራማሪ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሥር ሊሰዱና ማስተዋላችንም ጨምሮ እነዚህ ነገሮች በቋሚነት አእምሮአችን ውስጥ እንዲቀረጹ ለማድረግ እንችላለን። ስለ ልብ ዓይነቶች በተለያዩ ምሳሌዎች ላይ ኢየሱስ ከተናገረው ነገር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። (ሉቃስ 8:5–12) በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር ጠንካራ ሥር ሊያበቅልና ተክሉን ደግፎ በማቆም ፍሬ እንዲያፈራ ሊያደርገው ይችላል። — ማቴዎስ 13:8, 23
23. 2 ጴጥሮስ 3:18 የሚናገረውን ልብ ካልን ምን ውጤቶች ሊገኙ ይችላሉ? (ቆላስይስ 1:9–12)
23 የኢየሱስ ምሳሌ ለየት ያለ ቢሆንም የተገኙት ጥሩ ውጤቶች ግን ጴጥሮስ እንዲህ ብሎ ከጠቀሰው ተስፋ ጋር ይመሳሰላል:- “ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነትም እውቀትን . . . እነዚህ ነገሮች ለእናንተ ሆነው ቢበዙ፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ያደርጓችኋልና።” (2 ጴጥሮስ 1:5–8) አዎን፣ በእውቀት ማደጋችን ፍሬያማዎች እንድንሆን ይረዳናል። ተጨማሪ እውቀት መውሰዳችንን ይበልጥ ደስ የሚያሰኝ ሆኖ እናገኘዋለን። (ምሳሌ 2:2–5) የምትማረው ነገር በውስጥህ ይቆይልሃል ሌሎችንም ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ስታስተምራቸው ይጠቅምሃል። ስለዚህ በዚህም መንገድ ቢሆን ብዙ ፍሬ ልታፈራና ለአምላክና ለልጁ ክብር ልታመጣ ትችላለህ። ጴጥሮስ ሁለተኛውን ደብዳቤ የደመደመው እንደዚህ በማለት ነው:- “ነገር ግን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና እውቀት እደጉ። ለእርሱ አሁንም እስከ ዘላለምም ቀን ድረስ ክብር ይሁን።” — 2 ጴጥሮስ 3:18
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “በእውቀት የመጨመራችን ጉዳይ ስለ ጨረቃ ብዙ ለማወቅ ፈልጎ ይህችን የብርሃን ምንጭ ጠጋ ብሎ ለማየት ሲል እቤቱ ጣራ ላይ ከወጣ ሰው ጋር ይመሳሰላል።”
b በዚህ አንቀጽ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሱት እምነትና በጎነት የተባሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሕርዮች በሐምሌ 15, 1993 እትማችን ላይ ተብራርተዋል።
c እነዚህ ሐሳቦች ብዙ የቆዩትን ክርስቲያኖችም የግል ጥናት ሲያደርጉና ለጉባኤ ስብሰባዎች ሲዘጋጁ ይበልጥ መጠቀም እንዲችሉ ሊረዷቸው ይችላሉ።
ታስታውሳለህን?
◻ እውቀትህን የመጨመር ፍላጎት ሊኖርህ የሚገባው ለምንድን ነው?
◻ አንድ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከጥናቱ በይበልጥ መጠቀም የሚችለው እንዴት ነው?
◻ በፐርማፍሮስት ምሳሌ መሠረት ከየትኛው አደጋ ለመራቅ ትፈልጋለህ?
◻ እውቀት ለመጨመር ባለህ ችሎታ ረገድ ለማሻሻል ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአእምሮ ፐርማፍሮስት ችግር አለብኝን?