እምነት በማሳየት አምላክ ለሰጠን ተስፋዎች አዎንታዊ ምላሽ ስጥ
“የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋን [ይሖዋ አምላክ ] ሰጠን። ” — 2 ጴጥሮስ 1:4
1. እውነተኛ እምነትን እንድናሳይ ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?
ይሖዋ በገባልን ተስፋዎች ላይ እምነት እንድንጥል ይፈልጋል። ሆኖም ‘እምነት ለሁሉ አይሆንም።’ (2 ተሰሎንቄ 3:2) ይህ ባሕርይ የአምላክ መንፈስ ወይም የአንቀሳቃሽ ኃይሉ ፍሬ ነው። (ገላትያ 5:22, 23) ስለሆነም ይህንን እምነት ሊያሳዩ የሚችሉት በይሖዋ መንፈስ የሚመሩት ብቻ ናቸው።
2. ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእምነት” የሰጠው ፍቺ ምንድን ነው?
2 ይሁን እንጂ እምነት ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “የማናያቸውን ነገሮች ስለመኖራቸው የሚያስረዳ ነው” በማለት ጠርቶታል። የእነዚህ የማይታዩ ነገሮች ማረጋገጫ በጣም ጠንካራ በመሆኑ እምነት ከእርሱ ጋር እኩል እንደሆነ ተደርጎ ተቆጥሯል። በተጨማሪም እምነት ያላቸው ሰዎች በይሖዋ አምላክ ስለተሰጡት ተስፋዎች በሙሉ የተፈጸሙ ያህል እርግጠኞች እንዲሆኑ የሚያደርጋቸውን ዋስትና ስለሚሰጣቸው፣ እምነት “በተስፋ የምንጠባበቃቸውን ነገሮች እንደምናገኝ የሚያረጋግጥ” ተብሎ ተገልጿል። — ዕብራውያን 11:1 የ1980 ትርጉም
እምነትና የይሖዋ ተስፋዎች
3. ቅቡዓን ክርስቲያኖች እምነት ካሳዩ ምን ያገኛሉ?
3 ይሖዋን ደስ ለማሰኘት ከፈለግን በተስፋዎቹ ላይ እምነት መጣል ይኖርብናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ በ64 እዘአ ገደማ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው በሁለተኛ መልእክቱ ላይ ይህንኑ ቁምነገር አስገንዝቧል። ቅቡዓን የእምነት ጓደኞቹ እምነት ካሳዩ ከአምላክ የተሰጣቸውን “የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ” ሲፈጸም ለማየት እንደሚችሉ ጠቅሶላቸዋል። ከዚህም የተነሣ “ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች” በመሆን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሰማያዊ መንግሥት ተባባሪ ወራሾች ይሆናሉ። በእምነታቸውና በይሖዋ አምላክ እርዳታ በዚህ ዓለም ካሉት ብልሹ ልማዶችና ድርጊቶች መዳፍ አምልጠዋል። (2 ጴጥሮስ 1:2–4) እስቲ አስበው! እውነተኛ እምነት የሚያሳዩ ሰዎች አሁንም እንኳ ተመሳሳይ የሆነ ወደር የሌለው ነፃነት ባለቤት ሆነዋል።
4. በእምነታችን ላይ የትኞቹን ባሕርያት መጨመር አለብን?
4 ይሖዋ በገባልን ተስፋዎች ላይ ያለን እምነትና ከአምላክ ለተሰጠን ነፃነት አመስጋኞች መሆናችን የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ጥሩ ምሳሌ የምናሳይ ክርስቲያኖች እንድንሆን ሊገፋፋን ይገባል። ጴጥሮስ እንዲህ አለ:- “ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነትም እውቀትን፣ በእውቀትም ራስን መግዛት፣ ራስንም በመግዛት መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት]፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል [ለአምላክ ያደሩ በመሆንም አዓት] የወንድማማችን መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።” (2 ጴጥሮስ 1:5–7) እንደዚህ በማለት ጴጥሮስ በአእምሮአችን ውስጥ ብንቀርጻቸው የሚጠቅሙንን ነገሮች ዘርዝሮልናል። እነዚህን ባሕርያት ቀረብ ብለን በመመልከት እንመርምራቸው።
እምነት የተገነባባቸው ዋና ዋና ነገሮች
5, 6. በጎነት ምንድን ነው? በእምነታችን ላይስ ልንጨምረው የምንችለው እንዴት ነው?
5 ጴጥሮስ በጎነት፣ እውቀት፣ ራስን መግዛት፣ ጽናት፣ ለአምላክ ያደሩ መሆን፣ የወንድማማች መዋደድና ፍቅር አንዳቸው በሌላው ላይና በእምነታችን ላይ የሚጨመሩ ነገሮች ናቸው ብሏል። እነዚህ ባሕርያት እምነታችን የተገነባባቸው ዋና ዋና ነገሮች እንዲሆኑ ለማድረግ ጠንክረን መሥራት አለብን። ለምሳሌ ያህል በጎነት ከእምነት ነጥለን ልናሳየው የምንችለው ባሕርይ አይደለም። ደብሊው ኢ ቫይን የተባሉት የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ በ2 ጴጥሮስ 1:5 ላይ “እምነትን በማሳየት ረገድ በጎነት በጣም አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል” በማለት ጠቅሰዋል። ጴጥሮስ የጠቀሳቸው እያንዳንዳቸው ባሕርያት እምነታችንን ሊገነቡ የሚችሉ ነገሮች ናቸው።
6 በመጀመሪያ ደረጃ በእምነታችን ላይ በጎነትን መጨመር ይኖርብናል። በጎ መሆን ማለት በአምላክ ዓይን ጥሩ የሆነውን ማድረግ ማለት ነው። እዚህ ላይ “በጎነት” ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል አንዳንድ ትርጉሞች “ጥሩነት” በማለት ተርጉመውታል። (ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን፣ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል፣ ቱደይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን ) በጎነት መጥፎ ማድረግን እንድናስወግድ ወይም ሰዎችን የሚጎዳ ነገር እንዳናደርግ ይገፋፋናል። (መዝሙር 97:10) በተጨማሪም ሌሎች ሰዎችን በመንፈሳዊ፣ በአካላዊና ስሜታዊ በሆነው ፍላጎታቸው ለመጥቀም ሲባል የሚደረግን መልካም ሥራን ለመሥራት ያደፋፍራል።
7. በእምነታችንና በበጎነታችን ላይ እውቀትን መጨመር ያለብን ለምንድን ነው?
7 ጴጥሮስ በእምነታችንና በበጎነታችን ላይ እውቀትን እንድንጨምር ያሳሰበን ለምንድን ነው? እምነታችንን የሚፈታተኑ አዳዲስ ነገሮች ሲያጋጥሙን ትክክለኛውን ከስሕተቱ ለመለየት እንድንችል እውቀት እንዲኖረን ያስፈልጋል። (ዕብራውያን 5:14) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና የአምላክን ቃል በሥራ ላይ በማዋል በሚገኘው ተሞክሮ እንዲሁም በዕለታዊ ኑሮአችን ላይ ተግባራዊ ጥበብን በመጠቀም እውቀታችንን ማሳደግ እንችላለን። ይህም በበኩሉ በመከራ ጊዜ እምነታችንን ጠብቀን ለመቆምና በጎ ነገር ማድረጋችንን እንድንቀጥል በማድረግ ሊረዳን ይችላል። — ምሳሌ 2:6–8፤ ያዕቆብ 1:5–8
8. ራስን መግዛት ምንድን ነው? ከጽናት ጋርስ የተያያዘው እንዴት ነው?
8 መከራዎችን በእምነት ለመቋቋም እንድንችል በእውቀታችን ላይ ራስን መግዛት መጨመር ያስፈልገናል። “ራስን መግዛት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ራሳችንን የመቆጣጠር ችሎታን ያመለክታል። ይሄኛው የመንፈስ ፍሬ በአስተሳሰባችን፣ በቃላችንና በጠባያችን ረገድ ራሳችንን እንድንገታ ይረዳናል። ራስ የመግዛትን ባሕርይ በማሳየት ስንቀጥል በሱ ላይ ጽናትን እንጨምራለን። በግሪክኛ “ጽናት” የሚለው ቃል በድፍረት መቋቋምን እንጂ የማያመልጡት መከራ ሲመጣ እያዘኑ መሸነፍን አያመለክትም። ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ በደረሰበት ሥቃይ የጸናው በፊት ለፊቱ ይጠብቀው በነበረው ደስታ ምክንያት ነው። (ዕብራውያን 12:2) ከጽናት ጋር ተያይዞ ከአምላክ የሚሰጥ ብርታት እምነታችንን ያጠናክርልናል፤ እንዲሁም በመከራ ጊዜ ደስተኞች በመሆን ፈተናዎችን እንድንቋቋምና በስደት ጊዜም እንዳንወላውል ይረዳናል። — ፊልጵስዩስ 4:13
9. (ሀ) ለአምላክ ያደሩ መሆን ምንድን ነው? (ለ) ለአምላክ ያደሩ በመሆናችን ላይ የወንድማማች መዋደድን መጨመር ያለብን ለምንድን ነው? (ሐ) በወንድማማች መዋደዳችን ላይ ፍቅርን መጨመር የምንችለው እንዴት ነው?
9 በጽናታችን ላይ ለአምላክ ያደሩ መሆንን መጨመር ይኖርብናል። ይህም አክብሮታዊ ፍርሃትን፣ አምልኮንና ይሖዋን ማገልገልን ያመለክታል። ለአምላክ ያደሩ መሆንን ስንሠራበትና ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት አድርጎ እንደሚይዝ ስንመለከት እምነታችን ያድጋል። ሆኖም አምላካዊ ባሕርያትን ለማሳየት እንድንችል የወንድማማች መዋደድ እንዲኖረን ያስፈልጋል። እንዲያውም “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?” (1 ዮሐንስ 4:20) ልባችን ለሌሎቹ የይሖዋ አገልጋዮች እውነተኛ የሆነ የመውደድ ስሜት እንድናሳድርና በማንኛውም ጊዜ የሚበጃቸውን እንድናስብላቸው ሊገፋፋን ይገባል። (ያዕቆብ 2:14–17) ታዲያ በወንድማማች መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ የተባልነው ለምንድን ነው? ጴጥሮስ እዚህ ላይ ለወንድሞቻችን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የሰው ልጆች ፍቅርን ማሳየት እንደሚኖርብን መናገሩ ግልጽ ነው። ይህ ፍቅር በተለይ ምሥራቹን በመስበክና ሰዎችን በመንፈሳዊ በመርዳት ይገለጻል። — ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
ውጤቶቹን ማነጻጸር
10. (ሀ) በጎነት፣ እውቀት፣ ራስን መግዛት፣ ጽናት፣ ለአምላክ ያደሩ መሆን፣ የወንድማማች መዋደድና ፍቅር በእምነታችን ላይ ሲጨመሩ ምን ዓይነት ሁኔታ እናሳያለን? (ለ) ክርስቲያን ነኝ የሚል አንድ ግለሰብ እነዚህ ባሕርያት ቢጎድሉት ምን ይሆናል?
10 በጎነትን፣ እውቀትን፣ ራስን መግዛት፣ ጽናትን፣ ለአምላክ ያደሩ መሆንን፣ የወንድማማች መዋደድንና ፍቅርን በእምነታችን ላይ ብንጨምር አምላክ በሚቀበለው መንገድ ማሰብ፣ መናገርና ማድረግ እንችላለን። በተቃራኒው ግን ክርስቲያን ነኝ የሚለው ግለሰብ እነዚህን ጠባዮች ሳያሳይ ቢቀር በመንፈሳዊ ዕውር ይሆናል። ከአምላክ ለተገኘው ‘ብርሃን ዓይኑን ይጨፍናል’ ከቀደመው ኃጢአቱ መንጻቱንም ረስቷል ማለት ነው። (2 ጴጥሮስ 1:8–10፤ 2:20–22) በዚህ ነገር ጉድለት ተገኝቶብን አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለንን እምነት እንዳናጣ እንጠንቀቅ።
11. ከታማኝ ቅቡዓን ምን ነገሮችን ልንጠብቅ እንችላለን?
11 ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት አላቸው፤ እነርሱን የጠራበትንና የመረጠበትንም ዓላማ ለማስፈጸም የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። በመንገዳቸው ላይ ምንም ዓይነት የማሰናከያ እንቅፋት ቢጋረጥባቸውም አምላካዊ የሆኑትን ባሕርያት ያሳያሉ ብለን ልንጠብቅባቸው እንችላለን። የታመኑ ሆነው የተገኙ ቅቡዓን ‘ወደ ዘላለሙ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት’ እንዲገቡ በሰማይ ላይ መንፈሳዊ ሕይወትን በትንሣኤ አማካኝነት ያገኛሉ። — 2 ጴጥሮስ 1:11
12. የ2 ጴጥሮስ 1:12–15ን ቃላት የምንረዳቸው እንዴት ነው?
12 ጴጥሮስ በቅርቡ እንደሚሞት ተገንዝቦ ነበር። ከጊዜ በኋላም ሰማያዊ ሕይወትን በትንሣኤ እንደሚቀበል ይጠባበቅ ነበር። ነገር ግን “በዚህ ማደሪያ” ማለትም በሰብአዊ አካሉ በሕይወት እስካለ ድረስ በእምነት ጓደኞቹ ውስጥ እምነት ለመገንባትና መለኮታዊ ተቀባይነትን ለማግኘት በሚያስፈልጉት ነገሮች ላይ ማሳሰቢያ በመስጠት ለማነቃቃት ሞክሯል። በሞት ከተለያቸው በኋላ የጴጥሮስ መንፈሳዊ ወንድሞችና እኅቶች ቃሎቹን በማስታወስ እምነታቸውን ሊያጠናክሩ ይችላሉ። — 2 ጴጥሮስ 1:12–15
ትንቢታዊውን ቃል ማመን
13. ስለ ክርስቶስ መምጣት እምነት የሚያጠነክር ማስረጃ አምላክ ያቀረበው እንዴት ነው?
13 አምላክ ራሱ ኢየሱስ “በኃይልና በብዙ ክብር” መምጣቱ እርግጠኛ መሆኑን በተመለከተ እምነትን የሚያጠነክር ማረጋገጫ ሰጥቷል። (ማቴዎስ 24:30፤ 2 ጴጥሮስ 1:16–18) አረማውያን ቀሳውስት ስለ አማልክቶቻቸው በማስረጃ ያልተደገፈ የሐሰት ተረት ሲናገሩ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ግን በተአምር በተለወጠ ጊዜ ለታየው የክርስቶስ ክብር የዓይን ምስክሮች ነበሩ። (ማቴዎስ 17:1–5) ከፍተኛ ክብር ሲጎናጸፍ አይተዋል፤ እንዲሁም ኢየሱስ የሚወደው ልጁ እንደሆነ የገለጸበትን የአምላክን የራሱን ድምፅ ሰምተዋል። እንዲህ ያለው ማስታወቂያና ለክርስቶስ የተሰጠው አንጸባራቂ ሁኔታ የክብሩና የግርማው ማረጋገጫዎች ነበሩ። ጴጥሮስ በዚህ መለኮታዊ ራእይ ምክንያት ያንን ቦታ የአርሞንኤም የተራራ ሰንሰለት ሳይሆን አይቀርም፣ “ቅዱሱ ተራራ” በማለት ጠርቶታል። — ከዘጸአት 3:4, 5 ጋር አወዳድር።
14. በኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ እምነታችን ሊነካ የሚገባው እንዴት ነው?
14 የኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ እምነታችንን እንዴት ሊነካው ይገባል? ጴጥሮስ “ከእርሱም ይልቅ እጅግ የጸና የትንቢት ቃል አለን፤ ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ በልባችሁ እስኪወጣ ድረስ ይህን ቃል እየጠነቀቃችሁ መልካም ታደርጋላችሁ” ብሏል። (2 ጴጥሮስ 1:19) ‘የትንቢቱ ቃል’ ስለመሲሑ የሚናገሩትን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የሚገኙትን ትንቢቶች ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ “በኃይልና በብዙ ክብር” እንደሚመጣ የተናገረውንም ቃል እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ቃሉ በኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ አማካኝነት “እጅግ የጸና” የሆነው እንዴት ነው? በዚያን ጊዜ የታየው ሁኔታ ክርስቶስ በመንግሥት ሥልጣኑ በታላቅ ክብር እንደሚመጣ የተነገሩትን የትንቢት ቃሎች እውነተኛነት አረጋግጧል።
15. የትንቢቱን ቃል በጥንቃቄ መከታተሉ ምን ነገሮችን ማድረግ ይጨምራል?
15 እምነታችንን ለማጠንከር የትንቢቱን ቃል በጥንቃቄ መከታተል ይኖርብናል። ይህም ያንን ቃል ማጥናት፣ በክርስቲያን ስብሰባዎች ወቅት መወያየትና ምክሮቹን በሥራ ላይ ማዋልን ይጨምራል። (ያዕቆብ 1:22–27) ልባችንን የሚያበራ ‘በጨለማ ስፍራ የሚበራ መብራት’ እንዲሆንልን ማድረግ ይኖርብናል። (ኤፌሶን 1:18) “ምድርም እስኪጠባ ድረስ” ወይም “የንጋት ኮከብ” የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በክብሩ ራሱን እስከሚገልጥበት ጊዜ ድረስ ሊመራን የሚችለው እንደዚህ ካደረግን ብቻ ነው። (ራእይ 22:16) ያ መገለጥ ለእምነት የለሾች ጥፋትን እምነት ለሚያሳዩት ደግሞ በረከቶችን ያመጣላቸዋል። — 2 ተሰሎንቄ 1:6–10
16. በአምላክ ቃል ውስጥ ሚገኙት ትንቢታዊ ተስፋዎች በሙሉ ይፈጸማሉ ብለን ልናምን የምንችለው ለምንድን ነው?
16 ጴጥሮስ “በመጽሐፍ ያለውን ትንቢት ማንም ለገዛ ራሱ ሊተረጉም አልተፈቀደም፤ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ” በማለት ስለተናገረ የአምላክ ነቢያቶች ትንቢት የተናገሩት ብልህና አስተዋይ ሰዎች ስለነበሩ አይደለም። (2 ጴጥሮስ 1:20, 21) ለምሳሌ ያህል ዳዊት “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ” ብሏል። (2 ሳሙኤል 23:1, 2) ጳውሎስም “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 አዓት) የአምላክ ነቢያቶች በመንፈሱ አነሳሽነት ስለጻፉ በቃሉ ውስጥ የሚገኙት ተስፋዎች ሁሉ ይፈጸማሉ ብለን ለማመን እንችላለን።
በአምላክ ተስፋዎች ላይ እምነት ነበራቸው
17. ለአቤል እምነት መሠረት የሆነው ተስፋ ምንድን ነው?
17 ከክርስትና ዘመን በፊት ለነበሩት እንደ ‘ታላቅ ደመና’ ለሆኑት ምሥክሮች የእምነታቸው መሠረት የይሖዋ ተስፋዎች ነበሩ። (ዕብራውያን 11:1 እስከ 12:1) ለምሳሌ አቤል “የእባቡን” ራስ የሚቀጠቅጠው “ዘር” እንደሚመጣ አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ እምነት ነበረው። በአቤል ወላጆች ላይ የተላለፈው የአምላክ ቅጣት ለመፈጸሙ በቂ ማረጋገጫ ነበር። ከኤደን ውጭ የነበረችው የተረገመችው ምድር እሾህንና አሜከላን በማብቀሏ ምክንያት አዳምና ቤተሰቡ በፊታቸው ወዝ እንጀራን በልተዋል። አቤል ሔዋን ለባልዋ ስትገዛና አዳምም ሲሠለጥንባት ሳይመለከት አልቀረም። በእርግዝናዋ ወቅት ይሰማት ስለነበረው ሥቃይም ሳታወራ አልቀረችም። ወደ ኤደን ገነት የሚያስገባው በርም በኪሩቤሎችና በምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍ ይጠበቅ ነበር። (ዘፍጥረት 3:14–19, 24) እነዚህ ሁሉ በተስፋው ዘር አማካኝነት መዳን እንደሚመጣ ለአቤል ‘የሚያረጋግጡ’ መተማመኛ ሆነውለት ነበር። አቤል በእምነት ተገፋፍቶ ከቃየል ይልቅ የሚበልጥን መሥዋዕት ለአምላክ አቀረበ። — ዕብራውያን 11:1, 4
18, 19. አብርሃምና ሣራ እምነት ያሳዩት በምን መንገዶች ነበር?
18 የዕብራውያን አባቶች የነበሩት አብርሃም፣ ይስሐቅና ያዕቆብ ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት ነበራቸው። አብርሃም አምላክ የምድር ወገኖች ሁሉ ራሳቸውን በዘርህ ይባርካሉ በማለት የሰጠውን ተስፋና ለዘሮቹ መኖሪያ የሚሆን አገር እንደሚሰጣቸው አምላክ የነገረውን ቃል አመነ። (ዘፍጥረት 12:1–9፤ 15:18–21) ልጁ ይሥሐቅና የልጅ ልጁ ያዕቆብም ‘ያንኑ ተመሳሳይ ተስፋ ከእርሱ ጋር አብረው ወርሰዋል።’ አብርሃም በተስፋይቱ ምድር ላይ “እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ” እንዲሁም “መሠረት ያላትን ከተማ” ማለትም ለምድራዊ ሕይወት ከሞት የምታስነሣውን የአምላክን ሰማያዊ መንግሥት ይጠብቅ ነበር። (ዕብራውያን 11:8–10) አንተስ ተመሳሳይ እምነት አለህን?
19 የአብርሃም ሚስት ሣራ በአምላክ ተስፋ ላይ እምነት አሳድራ ዕድሜዋ 90 ዓመት በሆነበትና ልጅ የመውለጃዋ ዕድሜ ካለፈ በኋላ “ዘርን ለመፅነስ” ኃይል በማግኘት ይስሐቅን ወለደች። በዚህም የ100 ዓመት ዕድሜ የነበረው አብርሃም ልጅ ከመውለድ አንጻር ሲታይ “የሞተን ሰው እንኳን ከመሰለው” ከዚህ ሰው ከጊዜ በኋላ “በብዛታቸው እንደ ሰማይ ኮከብ” የሆኑ ልጆች ተወለዱ። — ዕብራውያን 11:11, 12፤ ዘፍጥረት 17:15–17፤ 18:11፤ 21:1–7
20. የዕብራውያን አባቶች ቃል የተገባላቸውን ተስፋ ፍጻሜ ሙሉ በሙሉ ባያዩም ምን አደረጉ?
20 ታማኞቹ የዕብራውያን አባቶች የተገባላቸው ተስፋ ሙሉ በሙሉ መፈጸሙን ሳይመለከቱ ሞተዋል። ዳሩ ግን “[ተስፋ የተገባላቸውን ነገሮች] ከሩቅ አይተው ልክ እንዳገኙት አድርገው ተደሰቱ፤ በምድር ላይ እንግዶችና መጻተኞች መሆናቸውንም ተገነዘቡ።” ተስፋይቱ ምድር የአብርሃም ዝርያዎች ውርሻ ሳትሆን ብዙ ትውልዶች አለፉ። በሕይወት በኖሩባቸው ጊዜያት ሁሉ ግን እነዚህ ፈሪሐ አምላክ ያላቸው የዕብራውያን አባቶች በይሖዋ ተስፋዎች ላይ እምነት ያላቸው መሆኑን አሳይተዋል። እምነታቸውን ስላላጠፉ አምላክ ለእነርሱ ባዘጋጀላቸው “ከተማ” ማለትም በመሲሐዊቷ መንግሥት ምድራዊ ግዛት ውስጥ እንዲኖሩ በቅርቡ ትንሣኤ ያገኛሉ። (ዕብራውያን 11:13–16 የ1980 ትርጉም። ) በተመሳሳይም አስደሳች ተስፋዎቹ ሲፈጸሙ አሁኑኑ ባናይም እንዲህ ያለው እምነት ለይሖዋ ታማኞች ሆነን በመቆም እንድንቀጥል ሊያደርገን ይችላል። እምነታችን አብርሃም እንዳደረገው አምላክን እንድንታዘዘው ይገፋፋናል። እሱ መንፈሳዊ ውርሻን ለዘሮቹ እንዳስተላለፈ ሁሉ እኛም ልጆቻችንን ይሖዋ በሰጠን የተከበረና እጅግ ታላቅ ተስፋ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ልንረዳቸው እንችላለን። — ዕብራውያን 11:17–21
እምነት ለክርስቲያኖች የግድ አስፈላጊ ነው
21. በዛሬው ጊዜ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት እምነታችን ምንን መጨመር አለበት?
21 እምነት የይሖዋ ተስፋዎች ይፈጸማሉ ብሎ በልበ ሙሉነት ከመጠበቅ የበለጠ ነገርንም ይጨምራል። የሰውን ልጆች ታሪክ ሁሉ ስናየው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አቋም ለማግኘት በተለያዩ መንገዶች እምነትን መግለጽ ያስፈልግ እንደነበረ እንመለከታለን። ጳውሎስ “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር የሚቀርብ ሰው፣ እግዚአብሔር መኖሩንና እርሱን ለሚፈልጉት ሰዎችም ሽልማት የሚሰጥ መሆኑን ማመን አለበት” በማለት ጠቅሷል። (ዕብራውያን 11:6 የ1980 ትርጉም። ) በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የሚፈልግ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስና አምላክ በእርሱ በኩል ባዘጋጀው ቤዛዊ መሥዋዕቱ ላይ እምነት ማሳየት አለበት። (ሮሜ 5:8፤ ገላትያ 2:15, 16) ይህም ኢየሱስ ራሱ እንደሚከተለው በማለት እንደተናገረው ነው:- “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ ማንም እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን [የሰው ዘር ዓለም] እንዲሁ ወዷልና። በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” — ዮሐንስ 3:16, 36
22. መሲሐዊቷ መንግሥት የትኛውን ተስፋ ትፈጽማለች?
22 ክርስቲያኖች በሚጸልዩላት መንግሥት አማካኝነት በሚፈጸሙት የአምላክ ተስፋዎች አፈጻጸም ረገድ ኢየሱስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ዳንኤል 7:13, 14፤ ማቴዎስ 6:9, 10) ጴጥሮስ እንዳሳየው የኢየሱስ ተአምራዊ መለወጥ ኢየሱስ በመንግሥት ክብርና በኃይል እንደሚመጣ የሚናገረውን የትንቢት ቃል እውነተኛነት አረጋግጧል። መሲሐዊቷ መንግሥት ሌላውን አምላክ የገባውን ተስፋ ወደ ፍጻሜው እንደምታመጣ በማሳየት ጴጥሮስ “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” በማለት ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ትንቢትም የአይሁድ ግዞተኞች በ537 ከዘአበ በገዢው በዘሩባቤልና በሊቀ ካህኑ በኢያሱ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት ወደ ምድራቸው በተመለሱ ጊዜ ተፈጽሟል። (ኢሳይያስ 65:17) ይሁን እንጂ ጴጥሮስ “አዲስ ሰማይ” ማለትም ሰማያዊቷ መሲሐዊ መንግሥት፣ “አዲስ ምድር” ማለትም በዚህች ምድር ላይ የሚኖሩ ጽድቅ ወዳድ ሰብአዊ ማኅበረሰብን ታስተዳድራለች በማለት ስለመጪው ጊዜ መናገሩ ነው። — ከመዝሙር 96:1 ጋር አወዳድር።
23. ቀጥለን በጎነትን የሚመለከት የትኛውን ጥያቄ እንመረምራለን?
23 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችና የተወዳጅ ልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን አምላክ ቃል የገባልንን አዲስ ዓለም ለማየት እንናፍቃለን። በቅርቡ እንደሚፈጸም እናውቃለን፤ ይሖዋ የሰጠን የተከበረና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋውም እንደሚፈጸም እናምናለን። በአምላካችን ፊት ተቀባይነት ባለው መንገድ ለመመላለስ እንድንችል እምነታችንን ለማጠናከር በእርሱ ላይ በጎነትን፣ እውቀትን፣ ራስ መግዛትን፣ ጽናትን፣ ለአምላክ ያደሩ መሆንን፣ የወንድማማች መዋደድንና ፍቅርን እንጨምር።a እዚህ ነጥብ ላይ ስንደርስ በጎነትን እንዴት ልናሳይ እንችላለን? የሚለው ጥያቄ ሊነሣ ይችላል። የእኛ በጎነት ራሳችንንና ሌሎችን በተለይም አምላክ ለሰጣቸው ተስፋዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን በእምነታቸው ላረጋገጡት ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ሊጠቅም የሚችለው እንዴት ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እምነትና በጎነት በዚህ መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ ተብራርተዋል። እውቀት፣ ራስን መግዛት፣ ጽናት፣ ለአምላክ ያደሩ መሆን፣ የወንድማማች መዋደድና ፍቅር ወደፊት በሚወጡት እትሞች ላይ በስፋት ይተነተናሉ።
መልሶችህ ምንድን ናቸው?
◻ “እምነት” እንዴት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል?
◻ በ2 ጴጥሮስ 1:5–7 መሠረት በእምነታችን ላይ የምንጨምራቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?
◻ የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ በእምነታችን ላይ ምን ውጤት ሊያስከትል ይገባል?
◻ በጥንት ዘመን በነበሩት በአቤል፣ በአብርሃም፣ በሣራና በሌሎቹም ምን ጥሩ የእምነት ምሳሌ እናይባቸዋለን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስ ተአምራዊ ለውጥ የአንድን ሰው እምነት እንዴት ሊነካው እንደሚችል ታውቃለንህን?