በእምነታችን ላይ በጎነትን መጨመር የምንችለው እንዴት ነው?
“በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ። ” — 2 ጴጥሮስ 1:5 አዓት
1, 2. የይሖዋ ሕዝቦች በጎ የሆነውን ነገር ያደርጋሉ ብለን መጠበቅ የሚገባን ለምንድን ነው?
ይሖዋ ማንኛውንም ነገር በጎ በሆነ መንገድ ያከናውናል። ጽድቅና መልካም የሆነ ነገር ያደርጋል። ስለዚህ ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘በገዛ ክብሩና በበጎነቱ’ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ጠርቷቸዋል በማለት ስለ አምላክ ለመናገር ችሏል። ስለ በጎው ሰማያዊ አባታቸው ያገኙት ትክክለኛ እውቀት ከልብ ለአምላክ ያደሩ ሆኖ ለመኖር የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ አሳይቷቸዋል። — 2 ጴጥሮስ 1:2, 3
2 ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ተወደዱ ልጆች አምላክን የምትመስሉ ሁኑ” በማለት ክርስቲያኖችን አሳስቧል። (ኤፌሶን 5:1 አዓት) ልክ እንደ ሰማያዊ አባታቸው የይሖዋ አምላኪዎችም በማንኛውም ሁኔታ ነገሮችን በበጎ መንገድ ማከናወን ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ በጎነት ምንድን ነው?
በጎነት ምንድን ነው?
3. “በጎነት” እንዴት ተብሎ ተተርጉሟል?
3 አንድ መዝገበ ቃላት “በጎነት” የሚለውን ቃል “በጎ አድራጊነትና ግብረ መልካምነት” ብሎ ይተረጉመዋል። በጎነት “ትክክለኛ ድርጊትና አስተሳሰብ፤ በባሕርዩ ጥሩ ነገሮችን የተሞላ” ነው። በጎ የሆነ ሰው ጻድቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በጎነት “ትክክለኛ የአቋም ደረጃን ማሟላት” ተብሎም ተተርጉሟል። ለክርስቲያኖች የሚሆኑት “ትክክለኛ የአቋም ደረጃዎች” የሚወሰኑት ግን በአምላክ ሲሆን እርሱም በቅዱስ ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ አስፍሮላቸዋል።
4. ክርስቲያኖች በ2 ጴጥሮስ 1:5–7 ላይ የተጠቀሱትን የትኞቹን ጠባዮች ለማዳበር ብርቱ ጥረት ማድረግ አለባቸው?
4 እውነተኛ ክርስቲያኖች ከይሖዋ አምላክ የጽድቅ ደረጃዎች ጋር በመስማማት እጅግ ታላቅ በሆነው ተስፋው ላይ እምነት በማሳደር አዎንታዊ ምላሽ ይሰጣሉ። ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ የሚለውን የጴጥሮስን ምክር ይከተላሉ:- “ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነትም እውቀትን፣ በእውቀትም ራስን መግዛት፣ ራስንም በመግዛት መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል [ለአምላክ ያደሩ መሆንን አዓት]፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል [ለአምላክ ያደሩ በመሆንም አዓት] የወንድማማችን መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።” (2 ጴጥሮስ 1:5–7) አንድ ክርስቲያን እነዚህን ጠባዮች ለማዳበር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለበት። ይህንን በጥቂት ቀኖች ወይም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሊያጠናቅቀው አይችልም። ከዚህ ይልቅ በሕይወቱ ሁሉ ጥረት ማድረግን ይጠይቅበታል። በእምነታችን ላይ በጎነትን መጨመሩ ትግል ይጠይቃል።
5. ከቅዱስ ጽሑፉ አኳያ በጎነት ምንድን ነው?
5 የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ኤም አር ቫንሳን “በጎነት” የሚለው ጥንታዊው የግሪክኛ ቃል ትርጉም “የየትኛውንም ነገር ከፍተኛ ደረጃ” የሚያመለክት አገባብ እንደነበረው ተናግረዋል። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች የአምላክን “በጎነት” እንዲነግሩ ሲያበረታታ የተጠቀመበት ቃል የብዙ ቁጥር ነው። (1 ጴጥሮስ 2:9) ከቅዱሳን ጽሑፎች አኳያ ስንመለከተው በጎነት የተገለጸው “የስነ ምግባር ኃይል፣ የስነ ምግባር ጉልበት፣ የነፍስ ብርታት” ሆኖ እንጂ እንቅስቃሴ አልባ ጠባይ ሆኖ አይደለም። ጴጥሮስ በጎነትን ሲጠቅስ የአምላክ አገልጋዮች ሊያሳዩትና ጠብቀው ሊያቆዩት የሚገባውን ከፍተኛ የስነ ምግባር ጥንካሬ በአእምሮው ይዞ ነው። ይሁን እንጂ ፍጹማን ስላልሆንን በአምላክ ዓይን በጎ የሆነውን ነገር ልናደርግ እንችላለንን?
ፍጹማን ባይሆኑም በጎ ናቸው
6. ፍጹማን ባንሆንም በአምላክ ዓይን በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ እንችላለን ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
6 አለፍጽምናንና ኃጢአትን ስለወረስን በአምላክ ዓይን በጎ የሆነውን እንዴት ልናደርግ እንደምንችል ግራ ይገባን ይሆናል። (ሮሜ 5:12) በጎ የሆኑ ሐሳቦች፣ ቃሎችና ድርጊቶች ሊፈልቁበት የሚችሉ ንጹሕ ልብ ለማግኘት የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ምንም ጥርጥር የለውም። (ከሉቃስ 6:45 ጋር አወዳድር።) ከቤርሳቤህ ጋር በተያያዘ መንገድ ኃጢአት ከሠራ በኋላ ንስሐ የገባው መዝሙራዊ ዳዊት “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት ለምኗል። (መዝሙር 51:10) ዳዊት የአምላክን ይቅርታና በበጎ መንገድ መመላለስ እንዲችል የሚያስፈልገውን እርዳታ አገኘ። እኛም ከባድ ኃጢአት ብንሠራና የአምላክንና የጉባኤ ሽማግሌዎችን እርዳታ ብንቀበል ወደ በጎው መንገዳችን ልንመለስና በእርሱም መመላለሳችንን ልንቀጥል እንችላለን። — መዝሙር 103:1–3, 10–14፤ ያዕቆብ 5:13–15
7, 8. (ሀ) በጎዎች ሆነን ለመቀጠል ከፈለግን ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (ለ) ክርስቲያኖች በጎዎች እንዲሆኑ ምን እርዳታ አለላቸው?
7 በወረስነው ኃጢአተኛነት ምክንያት የበጎነትን መንገድ መከተል የሚፈልግብንን ነገር ሁሉ ለማድረግ የማያቋርጥ ውስጣዊ ውጊያ ማድረግ ይኖርብናል። በበጎነታችን ለመቀጠል ከፈለግን ራሳችንን የኃጢአት ባሪያዎች ማድረግ የለብንም። ከዚህ ይልቅ በማንኛውም ጊዜ በጎውን በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ “ለጽድቅ ባሪያዎች” እንሁን። (ሮሜ 6:16–23) እርግጥ ነው የሥጋ ምኞታችንና የኃጢአተኝነት ዝንባሌዎቻችን በጣም ኃይለኞች ናቸው። ከዚህም የተነሣ በእነዚህና አምላክ ከእኛ በሚፈልግብን በጎ ነገሮች መካከል ግጭት አለ። እንዲህ ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል?
8 በአንድ በኩል የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይሉ በሚመራን መንገድ መሄድ ያስፈልገናል። ስለዚህ የሚቀጥለውን የጳውሎስን ምክር መከተል ይገባናል:- “በመንፈስ ተመላለሱ፣ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፣ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።” (ገላትያ 5:16, 17) አዎን፣ ለጽድቅ የሚሆነውን ኃይል ከአምላክ መንፈስ ስናገኝ ለትክክለኛ አኗኗር መምሪያ የሚሆነንን ደግሞ ከቃሉ እናገኛለን። በተጨማሪም ፍቅር የተሞላበት የይሖዋ ድርጅት እርዳታና የ“ታማኝና ልባም ባሪያ” ምክርም አለልን። (ማቴዎስ 24:45–47) ስለሆነም ከኃጢአተኛ ዝንባሌዎቻችን ጋር በምናደርገው ውጊያ ልናሸንፍ እንችላለን። (ሮሜ 7:15–25) እርግጥ ነው ንጹሕ ያልሆነ ሐሳብ ወደ አእምሮአችን ብቅ ቢል ወዲያውኑ ልናስወግደውና በጎነት የጎደለውን ነገር ለማድረግ የሚመጣብንን ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ እንዲሰጠን ወደ አምላክ ልንጸልይ እንችላለን። — ማቴዎስ 6:13
በጎነትና በአእምሮአችን ውስጥ የሚመጡ ሐሳቦች
9. ለበጎ አኗኗር ምን ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ ያስፈልጋል?
9 በጎነት አንድ ሰው በአእምሮው ከሚያመነጨው ሐሳብ ይጀምራል። መለኮታዊ ተቀባይነትን ለማግኘት ከፈለግን ጽድቅ፣ ጥሩና በጎ ስለሆኑ ነገሮች ማሰብ ይኖርብናል። ጳውሎስ እንዲህ አለ:- “በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፣ እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፣ እነዚህን አስቡ።” (ፊልጵስዩስ 4:8) አስተሳሰባችንን ጽድቅና ንጹሕ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ልናደርግ ይገባናል። በጎነት የጎደላቸውን ነገሮች ደግሞ ልንጠላቸው ይገባናል። ጳውሎስ “ከእኔ የተማራችሁትንና የተቀበላችሁትን የሰማችሁትንም ያያችሁትንም እነዚህን አድርጉ” ለማለት ችሏል። እኛም በአስተሳሰባችን፣ በአነጋገራችንና በአድራጎታችን እንደ ጳውሎስ በጎ ጠባይ የምናሳይ ከሆንን በክርስቲያናዊ ኑሮ ጥሩ ባልንጀሮችና ግሩም ምሳሌዎች በመሆናችን ‘የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል።’ — ፊልጵስዩስ 4:9
10. 1 ቆሮንቶስ 14:20ን በሥራ ላይ ማዋሉ በጎ በሆነው ጠባያችን ለመቀጠል እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?
10 በአስተሳሰባችን በጎዎች ሆነን ለመቀጠልና ሰማያዊ አባታችንን ለማስደሰት የምንፈልግ ከሆነ “በአእምሮ ሕፃናት አትሁኑ፤ ለክፋት ነገር ሕፃናት ሁኑ እንጂ በአእምሮ የበሰሉ ሁኑ” በማለት ጳውሎስ የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ማዋሉን አስፈላጊ ሆኖ እናገኘዋለን። (1 ቆሮንቶስ 14:20) ይህም ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ክፋት ምን እንደሆነ ለማወቅ ወይም ሞክረን ለማየት አንጓጓም ማለት ነው። አእምሮአችንን በዚህ መንገድ እንዲመረዝ ከመፍቀድ ይልቅ በዚህ ረገድ ልምድ የሌለው ወይም እንደ ሕፃን ንጹሕ ሆነን መቅረትን እንመርጣለን። እንዲሁም ብልግናና መጥፎ ድርጊት በይሖዋ ዓይን ኃጢአት መሆናቸውን ሙሉ በሙሉ እንገነዘባለን። በጎ ሆነን ከልባችን በመነሳሳት እርሱን ለማስደሰት መፈለጋችን ይጠቅመናል ምክንያቱም በሰይጣን ኃይል ከተያዘው ከዚህ ዓለም የሚመጡትን ንጹሕ ያልሆኑ የመዝናኛ ዓይነቶችንና ሌሎች አእምሮን የሚያቆሽሹ ተጽእኖዎችን እንድናስወግድ ይገፋፋናል። — 1 ዮሐንስ 5:19
በጎነትና ንግግራችን
11. በጎ መሆን ምን ዓይነት አነጋገርን መጠቀም ይጠይቃል? በዚህስ ረገድ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ የተዉልንን ምን ምሳሌ እናገኛለን?
11 ሐሳባችን ሁሉ በጎ ከሆነ በምንናገረው ነገር ላይ ትልቅ ለውጥ ያስከትላል። በጎ መሆን ንጹሕ፣ ለዛ ያለው፣ እውነተኛና የሚገነባ ንግግር መናገርን ይጠይቃል። (2 ቆሮንቶስ 6:3, 4, 7) ይሖዋ “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝሙር 31:5) በሚያደርጋቸው ነገሮች ሁሉ የታመነ ነው፤ ሊዋሽ ስለማይችልም ተስፋዎቹ ሁሉ አስተማማኝ ናቸው። (ዘኁልቁ 23:19፤ 1 ሳሙኤል 15:29፤ ቲቶ 1:2) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ይገባናል የማንለው ደግነትንና እውነትን የተሞላ’ ነው። በምድር ሳለ ከአባቱ የሰማውን እውነት ሁልጊዜ ይናገር ነበር። (ዮሐንስ 1:14፤ 8:40) ከዚህም በላይ ኢየሱስ “ኃጢአት አላደረገም፣ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም።” (1 ጴጥሮስ 2:22) የአምላክና የክርስቶስ አገልጋዮች ከሆንን ልክ ‘ወገባችንን በእውነት እንደታጠቅን’ ያህል በንግግራችን እውነተኞች በአኗኗራችንም ንጹሖች እንሆናለን። — ኤፌሶን 5:9፤ 6:14
12. በጎዎች ለመሆን ከፈለግን ልንሸሻቸው የሚገቡ የንግግር ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው?
12 በጎዎች ከሆንን ልንሸሻቸው የሚገቡ የአነጋገር ዓይነቶች አሉ። ራሳችንን በሚቀጥሉት የጳውሎስ ምክሮች እንመራለን:- “መራርነትና ንዴት ቁጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ።” “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፣ ይልቁን ምስጋና እንጂ።” (ኤፌሶን 4:31፤ 5:3, 4) በጽድቅ የተሞላው ልባችን ክርስቲያናዊ ያልሆኑትን ንግግሮች እንድንሸሽ ስለሚያነሳሳን ሌሎች ከእኛ ጋር አብሮ መቆየቱን በጣም የሚያረካ ሆኖ ያገኙታል።
13. ክርስቲያኖች አንደበታቸውን መቆጣጠር የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
13 አምላክን ለማስደሰትና በጎ የሆኑ ነገሮችን ለመናገር ያለን ምኞት አንደበታችንን ለመቆጣጠር ይረዳናል። በኃጢአተኝነት ዝንባሌያችን የተነሣ ሁላችንም አልፎ አልፎ በቃል እንሰናከላለን። ሆኖም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ‘በፈረሶች አፍ ውስጥ ልጓም ብናስገባ’ ወደምንመራቸው ሁሉ በታዛዥነት ይሄዱልናል ብሏል። እንግዲያው ለአንደበታችን ልጓም ለማስገባት በጣም ጥረት ማድረግና በበጎ መንገድ ብቻ ልንጠቀምበት መሞከር ይገባናል። ቁጥጥር የማይደረግበት አንደበት “ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል።” (ያዕቆብ 3:1–7) ከአምላክ የራቀው የዚህ ዓለም ክፉ ጠባዮች በጠቅላላ ካልተገራ አንደበት ጋር የተያያዙ ናቸው። በሐሰት ምስክርነት፣ በተሳዳቢነትና በሐሜተኝነት ለሚደርሱት ጉዳቶች ሁሉ ተጠያቂው እርሱው ነው። (ኢሳይያስ 5:20፤ ማቴዎስ 15:18–20) ስድ የተለቀቀ አንደበት የስድብ፣ የቁስልና የስም አጥፊነት ጠባሳ ትቶ ሲያልፍ በሚገድል መርዝ የተሞላ ይሆናል። — መዝሙር 140:3፤ ሮሜ 3:13፤ ያዕቆብ 3:8
14. ክርስቲያኖች ሊያስወግዱት የሚገባ ሁለት ዓይነት አንደበት እንዴት ያለ ነው?
14 ያዕቆብ እንዳመለከተው ስለ አምላክ ጥሩ ነገር ተናግረን ‘ይሖዋን በባረክንበት’ አንደበታችን አላግባብ ተጠቅመን ክፉ ነገር እንዲደርስባቸው ‘ሰዎችን ብንረግምበት’ ተገቢ አይሆንም። በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ለአምላክ ውዳሴ ዘምረን ወጣ ስንል ደግሞ ስለ እምነት ጓደኞቻችን ክፉ ነገር ማውራት እንዴት ያለ ኃጢአት ነው! ከአንድ ምንጭ ጣፋጭና መራራ ውኃ ሊፈልቅ አይችልም። ይሖዋን እናገለግላለን የምንል ከሆነ ሌሎች ሰዎች አስቀያሚ ቃላት ከመናገር ይልቅ በጎ የሆኑ ነገሮችን መናገር አለባቸው ብለው የመጠበቅ መብት አላቸው። እንግዲያው ክፉ አነጋገሮችን አስወግደን ባልንጀሮቻችንን የሚጠቅሙና በመንፈሳዊ የሚገነቧቸውን ነገሮች እንናገር። — ያዕቆብ 3:9–12
በጎነትና ድርጊቶቻችን
15. ከጠማማ መንገድ መራቅ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
15 የክርስቲያን አስተሳሰብና አነጋገር በጎ መሆን ካለበት፣ ድርጊቶቻችንስ? በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝልን ብቸኛው መንገድ በጎ አኗኗር ነው። ማንም የይሖዋ አገልጋይ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸዋል ብሎ በማሰብ አታላይነትንና ሸፋጭነትን መርጦ በጎነትን ሊተው አይችልም። ምሳሌ 3:32 “ጠማማ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ርኩስ ነውና፤ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው” ይላል። ከይሖዋ ጋር ያለንን የተቀራረበ ዝምድና የምንወደው ከሆነ እነዚህ የሚከነክኑ ቃላት ተንኰል ከማውጠንጠንና ማንኛውንም ዓይነት የሸፍጥ ሥራ ከመሥራት ሊያግዱን ይገባል። እንዲያውም የይሖዋ ነፍስ ከምትጠላቸው ሰባት ነገሮች አንዱ “ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ” ነው። (ምሳሌ 6:16–19) ነገሩ እንዲህ ከሆነ ሰዎችን ለመጥቀምና ለሰማያዊ አባታችን መከበር ስንል ከእንደዚህ ያለ ነገር በመሸሽ በዚያ ፋንታ በጎ የሆነ ነገር እናድርግ።
16. ክርስቲያኖች በማንኛውም ዓይነት የግብዝነት ድርጊት መካፈል የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
16 የበጎነትን ባሕርይ ለማሳየት ሐቀኞች እንድንሆን ይፈለግብናል። (ዕብራውያን 13:18) ድርጊቶቹ ከቃሎቹ ጋር የማይጣጣሙ ግብዝ ሰው በጎ ሰው አይደለም። እዚህ ላይ የተሠራበት “ግብዝ” የሚለው የግሪክኛ ቃል “መልስ የሚሰጥ” እና በመድረክ ላይ የወጣ ተዋናይ የሚል ትርጉም አለው። የግሪክና የሮማ ተዋናዮች ጭንብል ወይም የፊት መሸፈኛ ያደርጉ ስለነበር ይህ ቃል በምሳሌያዊ አባባል ለአስመሳይ ሰው ይሠራበት ጀመር። ግብዞች “የማይታመኑ” ናቸው። (ከሉቃስ 12:46 እና ከማቴዎስ 24:50, 51 ጋር አወዳድር።) ግብዝነት ክፋትን ወይም ሸርን ሊያመለክት ይችላል። (ማቴዎስ 22:18፤ ማርቆስ 12:15፤ ሉቃስ 20:23) አምኖ የተጠጋ ሰው የፈገግታ፣ የሽንገላና የአስመሳይ ድርጊቶች ሰለባ ቢሆን እንዴት ያሳዝናል! በሌላው በኩል ደግሞ እምነት ከሚጣልባቸው ክርስቲያኖች ጋር ጉዳዮቻችንን እንደምናከናውን ስናውቅ የልባችን ደስታ በጣም ከፍ ያለ ይሆናል። በጎዎች በመሆናችንና ግብዞች ባለመሆናችንም አምላክ ይባርከናል። የእርሱ ሞገስም ‘ግብዝነት የሌለበት የወንድማማች መዋደድን’ ለሚያሳዩና ‘ግብዝነት የሌለበት እምነት’ በያዙት ላይ ያርፋል። — 1 ጴጥሮስ 1:22፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:5
በጎነት በሥራ የሚገለጽ ጥሩነት ነው
17, 18. የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ጥሩነትን ስናሳይ ከሌሎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ምን እናደርጋለን?
17 በእምነታችን ላይ በጎነትን ከጨመርን አምላክ ሊቀበላቸው የማይችላቸውን ነገሮች ከማሰብ፣ ከመናገርና ከማድረግ እንቆጠባለን። ሆኖም ክርስቲያናዊ በጎነትን ማሳየቱ ጥሩ ነገር የማድረግንም ልማድ እንድንጨምርበት ይጠይቅብናል። እንዲያውም በጎነት ጥሩነት ተብሎም ተተርጉሟል። ጥሩነት ደግሞ የይሖዋ መንፈስ ፍሬ እንጂ በሰው ጥረት ብቻ ሊገኝ የሚችል ባሕርይ አይደለም። (ገላትያ 5:22, 23) የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ጥሩነትን እያሳየን ስለሌሎች ደኅንነት የምናስብ እንድንሆንና ፍጽምና ባይኖራቸውም ለሚያሳዩአቸው ጥሩ ጠባዮች እንድናመሰግናቸው ይገፋፋናል። ለብዙ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉት ቆይተዋልን? እንግዲያው ልናከብራቸውና ስለ እነርሱና ለአምላክ ስላቀረቡት አገልግሎታቸው ጥሩ ነገር ልንናገር ይገባናል። ሰማያዊው አባታችን ለስሙ ያሳዩትን ፍቅርና በእምነት ያደረጓቸውን በጎ የሆኑ ነገሮች ስለማይረሳ እኛም እንደርሱ እንሁን። — ነህምያ 13:31፤ ዕብራውያን 6:10
18 የበጎነት ባሕርይ ታጋሾች፣ የሰው ችግር የሚገባንና ርኅሩኆች እንድንሆን ያደርገናል። አንድ ይሖዋን የሚያመልክ ጓደኛችን መከራ ቢደርስበት ወይም የመንፈስ ጭንቀት ቢያድርበት አፍቃሪው አባታችን እኛን እንደሚያጽናናን እኛም በሚያጽናና ቃል እናነጋግረውና አንድ ዓይነት ማጽናኛ እንዲያገኝ እናደርጋለን። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) ምናልባት የሚያፈቅሩት ሰው ስለሞተባቸው ያዘኑ ካሉ አብረናቸው እናዝናለን። የበጎነት መንፈስ ፍቅራዊ የሆነ መልካም ነገር እንድናደርግ ስለሚገፋፋን የደረሰባቸውን ችግር ማቃለል የምንችልበት መንገድ ካለ እናቃልልላቸዋለን።
19. በአስተሳሰባችን፣ በቃላችንና በድርጊታችን በጎዎች ከሆንን ሌሎች እኛን እንዴት አድርገው ይይዙናል?
19 ስለ ይሖዋ ጥሩ ነገሮችን በመናገር እርሱን እንደምንባርክ ሁሉ ሌሎችም እኛ በአስተሳሰባችን፣ በንግግራችንና በድርጊታችን በጎዎች በመሆናችን ሊባርኩን ይችላሉ። (መዝሙር 145:10) ጥበብ ያለበት አንድ ምሳሌ “በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤ የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል” ይላል። (ምሳሌ 10:6) ክፉና ረብሸኛ ሰው በሌሎች ተወዳጅ እንዲሆን የሚያደርገው በጎነት ይጎድለዋል። የዘራውን ያጭዳል፤ ምክንያቱም ሰዎች ስለ እርሱ መልካም ነገር በመናገር ከልባቸው ሊባርኩት አይችሉም። (ገላትያ 6:7) እንግዲያው የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናቸው የሚያስቡትን፣ የሚናገሩትንና የሚያደርጉትን ሁሉ በጎ በሆነ መንገድ ማከናወናቸው ምንኛ የተሻለ ነው! እነርሱን ለመባረክና ስለ እነርሱ ጥሩ ነገር ለመናገር የሚገፋፉትን ሰዎች ፍቅር፣ እምነትና አክብሮት ያተርፍላቸዋል። ከዚህም በላይ አምላካዊው የበጎነት ጠባያቸው በዋጋ ሊተመን የማይችለውን የይሖዋን በረከት ያስገኝላቸዋል። — ምሳሌ 10:22
20. በጎ የሆኑ አስተሳሰቦች፣ ንግግሮችና ድርጊቶች በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ ምን ዓይነት ውጤት ሊኖራቸው ይችላል?
20 በጎ የሆኑ አስተሳሰቦች፣ ንግግሮችና ድርጊቶች የይሖዋን ሕዝቦች ጉባኤ እንደሚጠቅሙ ምንም ጥርጥር የለውም። አማኞች እርስ በርሳቸው ሲዋደዱና አክብሮት በተሞላው መንገድ ሲከባበሩ በመካከላቸው የወንድማማች መዋደድ ያብባል። (ዮሐንስ 13:34, 35) በቅን ልቦና የቀረበ ምስጋናና ማበረታቻን ጨምሮ በጎ ንግግር መናገር ሞቅ ያለ የሕብረትና የአንድነት ስሜት እንዲኖር ይረዳል። (መዝሙር 133:1–3) ልብን በደስታ ሞቅ የሚያደርግ በጎ ድርጊት ሌሎችን በተመሳሳይ መንገድ ምላሽ እንዲሰጡ ያነሳሳቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ክርስቲያናዊውን በጎ ጠባይ ልማድ ማድረጉ በበጎነቱ የታወቀውን የሰማዩን አባታችንን የይሖዋን በረከትና ሞገስ ያስገኝልናል። እንግዲያው አምላክ በሰጠን የተከበረና እጅግ ታላቅ ተስፋ ላይ እምነታችንን በመጣል አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱን ዓላማችን እናድርግ። እንዲሁም በእምነታችን ላይ በጎነትን ለመጨመር ልባዊ ጥረት ለማድረግ የቆረጥን እንሁን።
መልሶችህ ምንድን ናቸው?
◻ “በጎነት” የሚለውን ቃል እንዴት ብለህ ትገልጸዋለህ? ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች በጎ ሊሆኑ የሚችሉትስ ለምንድን ነው?
◻ ለበጎነት ምን ዓይነት ሐሳቦች አስፈላጊ ናቸው?
◻ በጎነት ንግግራችንን ሊነካ የሚገባው እንዴት ነው?
◻ በጎነት በድርጊታችን ላይ ምን ዓይነት ውጤት ሊያስከትል ይገባዋል?
◻ በጎ በመሆን ከሚገኙት ጥቅሞች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጣፋጭና መራራ ውኃ ከአንድ ምንጭ ሊፈልቅ ስለማይችል፣ ሌሎች ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች በጎ ነገር ብቻ ይናገራሉ ብለው መጠበቃቸው ተገቢ ነው