የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የዮሐንስና የይሁዳ ደብዳቤዎች ጎላ ያሉ ነጥቦች
ሐዋርያው ዮሐንስ በ98 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በኤፌሶን ሆኖ እንደጻፋቸው የሚገመቱት ሦስት ደብዳቤዎች በመንፈስ መሪነት ከተጻፉት የመጨረሻ መጻሕፍት መካከል ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ደብዳቤዎች፣ ክርስቲያኖች በብርሃን መመላለሳቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም የክህደት ትምህርትን እንዲቃወሙ ያበረታታሉ። ዮሐንስ በሦስተኛው ደብዳቤው ላይ ክርስቲያኖችን በእውነት እንዲመላለሱ ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው አንድነት እንዲኖራቸውም አበረታቷቸዋል።
የኢየሱስ ወንድም የሆነው ይሁዳ በፍልስጤም ሆኖ መልእክቱን የጻፈው በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደሆነ ይገመታል። ይሁዳ በዚህ ደብዳቤው ላይ ወደ ጉባኤው ሾልከው የገቡ መጥፎ ሰዎችን አስመልክቶ ለእምነት ባልንጀሮቹ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ ጎጂ ተጽዕኖዎችን እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ የሚገልጽ ምክር ለግሷቸዋል። ዮሐንስ ለጻፋቸው ሦስት ደብዳቤዎች እንዲሁም ለይሁዳ መልእክት ትኩረት መስጠታችን፣ እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች እያሉም በእምነት ጠንካሮች ሆነን እንድንቀጥል ሊረዳን ይችላል።—ዕብ. 4:12
በብርሃንና በእምነት መመላለሳችሁን እንዲሁም መዋደዳችሁን ቀጥሉ
ዮሐንስ የመጀመሪያ ደብዳቤውን የጻፈው ከክርስቶስ ጋር አንድነት ላላቸው በሙሉ ሲሆን በመልእክቱ ላይ ክርስቲያኖች ክህደትን እንዲቃወሙ እንዲሁም ለእውነትና ለጽድቅ ጽኑ አቋም ይዘው እንዲቀጥሉ የሚረዳቸው ጠቃሚ ምክር ሰጥቷል። ሐዋርያው፣ በብርሃንና በእምነት የመመላለስን እንዲሁም እርስ በርስ የመዋደድን አስፈላጊነት አበክሮ ገልጿል።
ዮሐንስ “[አምላክ] በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኀብረት አለን” በማለት ጽፏል። ሐዋርያው አክሎም አምላክ የፍቅር ምንጭ በመሆኑ “እርስ በርሳችን እንዋደድ” ብሏል። “እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን መፈጸም ነው።” ዓለምን የምናሸንፈው በይሖዋ አምላክ፣ በቃሉና በልጁ ላይ ባለን ‘እምነት’ ነው።—1 ዮሐ. 1:7፤ 4:7፤ 5:3, 4
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
2:2፤ 4:10—ኢየሱስ ‘የማስተሰረያ’ መሥዋዕት የሆነው እንዴት ነው? ማስተሰረይ የሚለው ቃል ‘ምሕረት’ ወይም ‘ይቅርታ’ ማስገኘት የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ፣ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ በመስጠት ፍጹም ፍትሕ የሚጠይቀውን ነገር አሟልቷል፤ እንዲህ ማድረጉ ለሰው ልጆች ምሕረት ስላስገኘ የማስተሰረያ መሥዋዕት ሆኗል ሊባል ይችላል። በዚህ መሥዋዕት አማካኝነት አምላክ በኢየሱስ ላይ እምነት ላላቸው ሰዎች ምሕረት ማድረግ እንዲሁም ኃጢአታቸውን ይቅር ማለት ይችላል።—ዮሐ. 3:16፤ ሮሜ 6:23
2:7, 8—ዮሐንስ “የቈየ” እና “አዲስ” ትእዛዝ በማለት የተናገረው ስለ የትኛው ትእዛዝ ነው? ዮሐንስ የተናገረው የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቀውን የወንድማማች ፍቅር አስመልክቶ ስለተሰጠው ትእዛዝ ነበር። (ዮሐ. 13:34) ኢየሱስ ይህንን ትእዛዝ የሰጠው ዮሐንስ በመንፈስ መሪነት የመጀመሪያ ደብዳቤውን ከመጻፉ ከ60 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ነበር፤ በመሆኑም ሐዋርያው ይህንን ትእዛዝ “የቈየው” ብሎ ጠርቶታል። አማኞች ከክርስትና ሕይወታቸው ‘መጀመሪያ’ አንስቶ ይህን ትእዛዝ ያውቁት ነበር። ሆኖም ይህ ትእዛዝ ‘ባልንጀራን እንደ ራስ በመውደድ’ ብቻ ሳይወሰን የራስን ጥቅም በመሠዋት ፍቅር ማሳየትን ስለሚጨምር “አዲስ ትእዛዝ” ተብሏል።—ዘሌ. 19:18፤ ዮሐ. 15:12, 13
3:2 NW—ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “ገና አልተገለጠም” የተባለው ነገር ምንድን ነው? “ልክ ባለበት ሁኔታ” የሚያዩትስ ማንን ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ከሞት ከተነሱ በኋላ መንፈሳዊ አካል አግኝተው ወደ ሰማይ ሲሄዱ ምን እንደሚመስሉ ገና አልተገለጠላቸውም። (ፊልጵ. 3:20, 21) ሆኖም ‘[አምላክ] በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደሚሆኑ ያውቃሉ፤ ምክንያቱም እሱን ልክ ባለበት ሁኔታ’ ማለትም “መንፈስ” እንደሆነ ‘ያዩታል።’—2 ቆሮ. 3:17, 18
5:5-8—ውኃ፣ ደምና መንፈስ “ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ” የሚመሠክሩት እንዴት ነው? ኢየሱስ በውኃ ሲጠመቅ ይሖዋ በእሱ እንደሚደሰት ስለገለጸ ውኃ መስክሯል ሊባል ይቻላል። (ማቴ. 3:17) “ለሰዎች ሁሉ ቤዛ” ሆኖ የተሰጠው የኢየሱስ ደም ወይም ሕይወቱ ደግሞ ኢየሱስ የአምላክ ልጅ መሆኑን ይመሰክራል። (1 ጢሞ. 2:5, 6) ኢየሱስ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በእሱ ላይ መውረዱ የአምላክ ልጅ መሆኑን ያሳያል፤ መንፈስ ቅዱስ፣ ኢየሱስ “በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ [እንዲፈውስ]” አስችሎታል።—ዮሐ. 1:29-34፤ ሥራ 10:38
ምን ትምህርት እናገኛለን?
2:9-11፤ 3:15፦ አንድ ክርስቲያን፣ ማንኛውም ነገር ወይም ግለሰብ ለወንድሞቹ ያለውን ፍቅር እንዲያጠፋበት የሚፈቅድ ከሆነ የት እንደሚሄድ ሳያውቅ በመንፈሳዊ ጨለማ ይመላለሳል።
‘በእውነት ጸንታችሁ መሄዳችሁን’ ቀጥሉ
ዮሐንስ፣ ሁለተኛ ደብዳቤውን የጀመረው “ሽማግሌው፤ . . . ለተመረጠችው እመቤትና ለልጆቿ” በማለት ነው። ሐዋርያው “[ከልጆቿ] አንዳንዶቹ . . . በእውነት ጸንተው እየሄዱ” በማግኘቱ መደሰቱን ገልጿል።—2 ዮሐ. 1, 4
ዮሐንስ ፍቅርን እንዲያዳብሩ ማበረታቻ ከሰጣቸው በኋላ “ይህም ፍቅር፤ በትእዛዛቱ መሠረት እንመላለስ ዘንድ ነው” በማለት ጽፏል። ከዚህም በላይ “አታላይና የክርስቶስ ተቃዋሚ” ስለሆነ ሰው ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—2 ዮሐ. 5-7
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
1, 13—‘የተመረጠችው እመቤት’ የተባለችው ማን ናት? ዮሐንስ ይህን ያለው አንዲት ሴትን ለማመልከት ሊሆን ይችላል፤ እዚህ ላይ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል ኪርያ ሲሆን ትርጉሙም “እመቤት” ማለት ነው። አሊያም ደግሞ ይህን ቃል የተጠቀመው አሳዳጆችን ለማደናገር አንድን ጉባኤ በምሳሌያዊ አነጋገር ለመጥራት ፈልጎ ሊሆን ይችላል። ዮሐንስ እዚህ ላይ ስለ አንድ ጉባኤ እየተናገረ ከሆነ ልጆቿ የተባሉት የጉባኤው አባላት ሲሆኑ ‘የእኅቷ ልጆች’ የተባሉት ደግሞ የሌላ ጉባኤ አባላት ናቸው ማለት ነው።
7—ዮሐንስ እዚህ ላይ የተናገረው ስለ የትኛው የኢየሱስ ‘መምጣት’ ነው? አሳቾች በዚህ ‘እንደማያምኑ’ የሚያሳዩት እንዴት ነው? እዚህ ላይ የተጠቀሰው ‘መምጣት’ ኢየሱስ ወደ ፊት በማይታይ መንገድ የሚመጣበትን ሁኔታ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሥጋ መምጣቱንና ክርስቶስ ሆኖ መቀባቱን ያመለክታል። (1 ዮሐ. 4:2) አሳቾች፣ ኢየሱስ በሥጋ መምጣቱን አምነው አይቀበሉም። ኢየሱስ በምድር ላይ መኖሩን ወይም በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን ይክዱ ይሆናል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
2, 4፦ ‘እውነትን’ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ክርስቲያናዊ ትምህርቶች በሙሉ ማወቃችንና ከተማርነው ነገር ጋር በሚስማማ መንገድ መኖራችን ለመዳናችን በጣም አስፈላጊ ነው።—3 ዮሐ. 3, 4
8-11፦ ‘የአምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ጸጋ፣ ምሕረትና ሰላም’ እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ያለንን በፍቅር ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት ላለማጣት ከፈለግን መንፈሳዊነታችን እንዳይዳከም ‘መጠንቀቅ’ አለብን፤ እንዲሁም ‘በክርስቶስ ትምህርት የማይኖሩ’ ሰዎችን መቀበል የለብንም።—2 ዮሐ. 3
‘አብረን ለእውነት መሥራት’
ዮሐንስ፣ ሦስተኛ ደብዳቤውን የጻፈው ጋይዮስ ለተባለ ወዳጁ ነው። ሐዋርያው “ልጆቼ በእውነት የሚመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የሚበልጥ ደስታ የለኝም” በማለት ጽፏል።—3 ዮሐ. 4
ጋይዮስ፣ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚያገለግሉ ወንድሞችን በመርዳት ረገድ ‘ታማኝ በመሆኑ’ ዮሐንስ አመስግኖታል። ሐዋርያው “አብረን ለእውነት እንድንሠራ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ልናስተናግድ ይገባናል” ብሏል።—3 ዮሐ. 5-8
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
11—አንዳንዶች ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙት ለምንድን ነው? ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም የሌላቸው አንዳንድ ሰዎች አምላክን በማስተዋል ዓይናቸው መመልከት ይሳናቸዋል። እነዚህ ሰዎች አምላክን በዓይናቸው ማየት ስለማይችሉ እሱ እንደማያያቸው ያስባሉ፤ ድርጊታቸውም እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው።—ሕዝ. 9:9
14—“ወዳጆች” የተባሉት እነማን ናቸው? ዮሐንስ እዚህ ላይ “ወዳጆች” ሲል እርስ በርስ የሚቀራረቡ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን የእምነት ባልንጀሮቹን በአጠቃላይ ማመልከቱ ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
4፦ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ግለሰቦች፣ ከእነሱ በዕድሜ የሚያንሱ የጉባኤው አባላት ‘በእውነት ሲመላለሱ’ መመልከት በጣም ያስደስታቸዋል። ወላጆችም ልጆቻቸው የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ በመርዳት ረገድ ሲሳካላቸው ከምንም ነገር ጋር የማይወዳደር ደስታ ያገኛሉ!
5-8፦ ለወንድሞቻቸውና ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ወንድሞቻቸውን በትጋት ከሚያገለግሉት ክርስቲያኖች መካከል ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ሚስዮናውያን፣ በቤቴል ቤቶች ወይም በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም አቅኚዎች ይገኙበታል። የእነዚህን ክርስቲያኖች እምነት መኮረጅ የሚኖርብን ከመሆኑም በላይ በፍቅር ልንደግፋቸው ይገባል።
9-12፦ ታማኝ የነበረውን የድሜጥሮስን እንጂ ስም አጥፊ የሆነውን የዲዮጥራጢስን ምሳሌ መኮረጅ አይኖርብንም።
‘በአምላክ ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ’
(ይሁዳ 1-25)
ይሁዳ ወደ ጉባኤው ሾልከው የገቡ ግለሰቦችን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “የሚያጉረመርሙና ሌሎችን ሰዎች የሚከሱ ናቸው፤ ርኩስ ምኞታቸውን ይከተላሉ፤ በራሳቸው ይታበያሉ፤ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሌሎችን ይክባሉ።”—ይሁዳ 4, 16
ክርስቲያኖች መጥፎ ተጽዕኖዎችን መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው? ይሁዳ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወዳጆች ሆይ፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የተናገሩትን አስታውሱ።” አክሎም “በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” ብሏል።—ይሁዳ 17-21
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
3, 4—ይሁዳ፣ ክርስቲያኖችን ‘ለእምነት እንዲጋደሉ’ የመከራቸው ለምን ነበር? ይህን ያደረገው ‘ፈሪሀ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ወደ ጉባኤው ሾልከው ገብተው’ ስለነበር ነው። እነዚህ ሰዎች “የአምላካችንን ጸጋ በርኩሰት የሚለውጡ” ነበሩ።
20, 21—‘በአምላክ ፍቅር ራሳችንን መጠበቅ’ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችለው በሦስት መንገዶች ነው፦ (1) የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናትና በስብከቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈል “እጅግ ቅዱስ በሆነው [እምነታችን]” ራሳችንን በመገንባት፣ (2) ‘በመንፈስ ቅዱስ’ ማለትም ከአምላክ መንፈስ ጋር በሚስማማ መንገድ በመጸለይ እንዲሁም (3) የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ባስቻለን የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት በማሳደር በአምላክ ፍቅር ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን።—ዮሐ. 3:16, 36
ምን ትምህርት እናገኛለን?
5-7፦ ክፉዎች ከይሖዋ ፍርድ ሊያመልጡ ይችላሉ? ይሁዳ የዘረዘራቸው ሦስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች እንደሚያሳዩት ይህ ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው።
8-10፦ የመላእክት አለቃ የሆነው ሚካኤል የተወውን ምሳሌ በመኮረጅ እኛም ይሖዋ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች አክብሮት ማሳየት ይገባናል።
12 NW፦ በውኃ ውስጥ የተደበቀ ዐለት ለመርከቦች ወይም ለዋናተኞች አደገኛ እንደሆነ ሁሉ ፍቅር ያላቸው መስለው የሚቀርቡን ከሃዲዎችም ለእምነታችን አደገኛ ናቸው። የሐሰት አስተማሪዎች ለጋስ ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም በመንፈሳዊ ባዶ ስለሆኑ ዝናብ እንደሌላቸው ዳመናዎች ናቸው። እንዲህ ያሉት ሰዎች በመከር ጊዜ ፍሬ እንደማይገኝባቸው የሞቱ ዛፎች ናቸው። ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች እንደሚሞቱ ሁሉ እነሱም ጥፋት ይጠብቃቸዋል። በእርግጥም ከከሃዲዎች መራቅ የጥበብ አካሄድ ነው።
22, 23፦ እውነተኛ ክርስቲያኖች መጥፎ የሆነውን ነገር ይጠላሉ። በጉባኤ የሚገኙ የጎለመሱ ክርስቲያኖች በተለይም የተሾሙ የበላይ ተመልካቾች ‘ተጠራጣሪ የሆኑትን’ ከእሳት ማለትም ከዘላለማዊ ጥፋት ለማዳን ሲሉ መንፈሳዊ እርዳታ ይሰጧቸዋል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ውኃ፣ መንፈስና ደም ‘ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደ ሆነ’ ይመሠክራሉ