ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
እውነትን የራሴ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?
“ከልጅነቴ ጀምሮ የይሖዋ ምሥክር ነበርኩ፤ በዚህ መንገድ ያደገ ሰው ሁሉ ይሖዋን በሚገባ ያውቀዋል የሚል እምነት ነበረኝ። ሆኖም በጣም ተሳስቼ ነበር!”—አንተኔት
“እውነት ምንድ[ን] ነው?” ይህን የታወቀ ጥያቄ ያነሳው ኢየሱስን ለሞት አሳልፎ የሰጠው ጴንጤናዊው ጲላጦስ ነው። (ዮሐንስ 18:38) ይሁን እንጂ ጲላጦስ ይህን ጥርጣሬ የተሞላበት ጥያቄ ያነሳው ግልጽ የሆነ ውይይት ለማድረግ ብሎ ሳይሆን ውይይቱን ለመቋጨት እንደነበረ ግልጽ ነው። ስለ “እውነት” የማወቅ ፍላጎት አልነበረውም። አንተስ? ስለ እውነት የማወቅ ፍላጎት አለህ?
ፈላስፋዎች እውነት ምን እንደሆነ ለማወቅ ለብዙ መቶ ዘመናት ሲጥሩ የቆዩ ቢሆንም ምንም አልተሳካላቸውም። ይሁን እንጂ፣ ጲላጦስ ላነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ትችላለህ። ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ቃል እውነት መሆኑን ተናግሯል። እሱ ራሱም “እውነት” እንደሆነ ተናግሯል። ሐዋርያው ዮሐንስም “እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” ሲል ጽፏል። (ዮሐንስ 1:17፤ 14:6፤ 17:17) ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው መላው የክርስቲያን ትምህርትም “እውነት” ወይም ደግሞ የ“ወንጌል እውነት” ተብሎ ተጠርቷል። (ቲቶ 1:13, 14፤ ገላትያ 2:14፤ 2 ዮሐንስ 1, 2) ይህ የክርስቲያን ትምህርት እንደ አምላክ ስም፣ የአምላክ መንግሥት መቋቋም፣ ትንሣኤና የኢየሱስ ቤዛ ያሉትን ነገሮች በውስጡ አካትቶ የያዘ ነው።—መዝሙር 83:18 NW፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ 20:28፤ ዮሐንስ 5:28, 29
በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በክርስቲያን ወላጆቻቸው ተምረዋል። ይሁን እንጂ ይህ ማለት እነዚህ ወጣቶች ‘በእውነት እየሄዱ’ ነው ማለት ነውን? (3 ዮሐንስ 3, 4) ሙሉ በሙሉ እንደዚያ ማለት አይቻልም። ለምሳሌ ያህል የሀያ ዓመቷ ጄኒፈር ከልጅነቷ ጀምራ የይሖዋ ምሥክር ነበረች። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “እናቴ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ይዛኝ ትሄድ የነበረ ከመሆኑም በላይ ስለ ጥምቀት ማሰብ እንዳለብኝ ጠቁማኛለች። ሆኖም ‘እንዲሁ ደስ ስለሚለኝ ነው እንጂ እኔ የይሖዋ ምሥክር መሆን አልፈልግም!’ ብዬ አስብ ነበር።”
አንዳንድ ወጣቶች የተማሩትን ነገር ያምኑበታል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ነገር የጠለቀ እውቀት ሳያዳብሩ ይቀራሉ። ይህ ምን አደጋ ያስከትላል? ኢየሱስ አንዳንድ ግለሰቦች “በእነርሱ ሥር የላቸውም” ሲል አስጠንቅቋል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች ‘ለጊዜው’ ይቀጥሉ ይሆናል፤ “ኋላም በቃሉ ምክንያት መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላሉ።” (ማርቆስ 4:17) ሌሎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነታቸውን በተወሰነ ደረጃ ማስረዳት ይችላሉ፤ ሆኖም አምላክን በግለሰብ ደረጃ አያውቁትም። አኒሰ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ልጅ በነበርኩበት ጊዜ ከይሖዋ ጋር ልባዊ የሆነ ዝምድና ነበረኝ ብዬ ለመናገር ያስቸግረኛል . . . በአብዛኛው ወላጆቼ ከይሖዋ ጋር በነበራቸው ዝምድና ላይ የተመካ ነበር ማለት እችላለሁ።”
በዚህ ረገድ የአንተስ ሁኔታ ምን ይመስላል? ይሖዋ እንዲሁ የወላጆችህ አምላክ ብቻ ነው? ወይስ እንደ መጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ አንተም “አቤቱ፣ እኔ ግን በአንተ ታመንሁ፤ አንተ አምላኬ ነህ አልሁ” ለማለት ትችላለህ? (መዝሙር 31:14) እውነታውን ለመጋፈጥ ድፍረት ሊጠይቅ ይችላል። አሊግዛንደር የተባለ አንድ ወጣት “ልወስደው የሚገባኝ የመጀመሪያ እርምጃ በሐቀኝነት ራሴን በራሴ መመርመር ነበር” ሲል ተናግሯል። ራስህን በሚገባ ከመረመርክ በኋላ እውነትን (መላውን የክርስቲያን ትምህርት) ራስህ ፈትነህ እንዳልያዝከው ትገነዘብ ይሆናል። ጽኑ የሆነ እምነት ይጎድልህ ይሆናል፤ በዚህም ሳቢያ ሕይወትህ ዓላማ የሌለውና ትክክለኛ አቅጣጫ ያልተከተለ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል።
የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ “እውነትን ምርጫህ አድርግ” የሚል ርዕስ ያለውን መዝሙር ይዘምራሉ።a ይህ ምክር ለአንተ ተስማሚ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህን ልታደርግ የምትችለው እንዴት ነው? ምን በማድረግ ልትጀምር ትችላለህ?
እውነት መሆኑን ራስህ ፈትን
ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 12:2 ላይ ‘በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ ፈትናችሁ እወቁ’ የሚል ምክር ሰጥቷል። ታዲያ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” በማግኘት ነው። (ቲቶ 1:1 NW) የጥንቶቹ የቤርያ ከተማ ነዋሪዎች የሰሙትን ነገር እንዲሁ አልተቀበሉም። ከዚህ ይልቅ “ነገሩ [የተማሩት ነገር] እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን [መረመሩ]።”—ሥራ 17:11
ኤሪን የተባለች አንዲት ወጣት ክርስቲያን ይህን ማድረግ እንዳለባት ተገንዝባ ነበር። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች:- “ጥልቅ ምርምር አደረግኩ። ‘ይህ ትክክለኛው ሃይማኖት መሆኑን ማወቅ የምችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሚባል ስም ያለው አምላክ መኖሩን ማወቅ የምችለው እንዴት ነው?’ እያልኩ ራሴን ጠየቅኩ።” የራስህ የሆነ የግል ጥናት ለማድረግ የሚያስችልህ ፕሮግራም ለምን አታወጣም? ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ልትጀምር ትችላለህ።b በጥሞና አንብበው። የተጠቀሱትን ጥቅሶች በሙሉ እያወጣህ በማንበብ ከተሰጠው ሐሳብ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ልብ በል። “የእውነትን ቃል በትክክል የሚጠቀም የማያሳፍር ሠራተኛ” በምትሆንበት ጊዜ ስለ እውነት ያለህ አመለካከት እንዴት እንደሚለወጥ በመመልከት ልትገረም ትችላለህ።—2 ጢሞቴዎስ 2:15 NW
ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ለማስተዋል የሚያስቸግር” ነገር እንዳለ ተናግሯል፤ ይህ እውነት ሆኖ ታገኘዋለህ። (2 ጴጥሮስ 3:16) ሆኖም የአምላክ መንፈስ ከባድ የሆኑትን ርዕሰ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር እንድትገነዘብ ሊረዳህ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:11, 12) አንድ ነገር ለመረዳት በምትቸገርበት ጊዜ አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ። (መዝሙር 119:10, 11, 27) በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ ሞክር። ይህን እንዴት ማድረግ እንደምትችል የማታውቅ ከሆነ ሌሎች እንዲረዱህ ጠይቅ። ወላጆችህ ምናልባትም ሌሎች የጎለመሱ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ሊረዱህ ይችላሉ።
የምታጠናው ሌሎች በእውቀትህ እንዲያደንቁህ ለማድረግ እንዳልሆነ መዘንጋት የለብህም። ኮለን የተባለ አንድ ወጣት “የይሖዋን ባሕርያት እያወቃችሁ ትሄዳላችሁ” ሲል ገልጿል። ያነበብከው ነገር ወደ ልብህ ጠልቆ እንዲገባ ጊዜ ወስደህ አሰላስልበት።—መዝሙር 1:2, 3
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከጉባኤው ጋር መሰብሰብም ሊረዳህ ይችላል። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደጻፈው ጉባኤ “የእውነት ዓምድና መሠረት” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) አንዳንድ ወጣቶች ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አሰልቺ ናቸው ብለው ሲናገሩ ይሰማል። “ሆኖም ለስብሰባዎች የማትዘጋጁ ከሆነ ከስብሰባዎቹ እምብዛም ጥቅም አታገኙም” ሲል ኮለን አሳስቧል። ስለዚህ ትምህርቶቹን አስቀድመህ ተዘጋጅ። ስብሰባዎች ይበልጥ አስደሳች የሚሆኑልህ ተሳታፊ ስትሆን እንጂ ተመልካች ስትሆን አይደለም።
ለጥናት የሚሆን ጊዜ ታጣለህ?
በትምህርት ቤት ከሚሰጡህ የቤት ሥራዎችና ቤት ውስጥ ከምታከናውናቸው ተግባሮች አንጻር ሲታይ ለጥናት የሚሆን ጊዜ ማግኘቱ ከባድ ሊሆንብህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ሱዛን የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ለስብሰባዎች መዘጋጀትና የግል ጥናት ማድረግ እንዳለብኝ ስለማውቅ ለብዙ ዓመታት ስታገል ቆይቻለሁ፤ ሆኖም አልተሳካልኝም ነበር።”
ሱዛን በጣም አስፈላጊ ካልሆኑ ነገሮች ላይ ‘ጊዜ መዋጀት’ ተምራለች። (ኤፌሶን 5:15, 16) በመጀመሪያ ልታጠናቸው የሚገቡ ነገሮችን አንድ በአንድ በዝርዝር ጻፈች። ከዚያም የምታጠናበትን ጊዜ መደበች። ሆኖም በፕሮግራሟ ውስጥ ለመዝናኛ የሚሆን ጊዜም አስገብታ ነበር። የሚከተለውን ምክር ሰጥታለች:- “ክፍት የሆነውን ሰዓት ሁሉ ፕሮግራም ውስጥ አትክተቱት። ዘና የምንልበት ጊዜም ሊኖረን ይገባል።” አንተም ፕሮግራም ማውጣትህ ሊረዳህ ይችላል።
የተማርከውን ለሌሎች አካፍል
የተማርከውን ነገር ለሌሎች ማካፈልህ ትምህርቱን የራስህ ለማድረግ በጣም ይረዳሃል። ሌላ ሰው ለማስተማር ሞክር። መዝሙራዊው “አፌ ጥበብን ይናገራል፣ የልቤም አሳብ ማስተዋልን” ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 49:3
በምሥራቹ የማታፍር ከሆነ ለትምህርት ቤት ጓደኞችህና ለምታገኛቸው ሌሎች ሰዎች ለማካፈል አታመነታም። (ሮሜ 1:16) እንዲህ ዓይነቶቹን አጋጣሚዎች ተጠቅመህ እውነትን ለሌሎች በመንገር የተማርከውን ልትጠቀምበት ትችላለህ፤ በዚህ መንገድ እውነት በአእምሮህና በልብህ ውስጥ እንዲተከል ታደርጋለህ።
ከመጥፎ ባልንጀርነት ተጠበቁ
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርገው ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ?” ብሎ ለመጻፍ ተገድዷል። (ገላትያ 5:7) አሌክስ የተባለ አንድ ወጣት ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሞታል። “ከመጥፎ ባልንጀሮች ጋር በመዋል” ጊዜውን ባልባሌ ሁኔታ ያሳልፍ ስለነበረ የአምላክን ቃል ለማጥናት ያደርግ የነበረው ጥረት እንዳልሰመረለት ተናግሯል። አንተም ለመንፈሳዊ እድገትህ ስትል በዚህ ረገድ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል።
በአንጻሩ ደግሞ ጥሩ ባልንጀርነት እድገት እንድታደርግ ሊረዳህ ይችላል። ምሳሌ 27:17 “ብረት ብረትን ይስለዋል፣ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል” ይላል። እውነትን በራሳቸው ሕይወት ውስጥ በሥራ በማዋል ጥሩ ምሳሌ ከሆኑ ሰዎች ጋር ተወዳጅ። በቤተሰብህ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሰው ልታገኝ ትችል ይሆናል። ወጣቷ ጄኒፈር ወደ ኋላ መለስ ብላ በማስታወስ እንዲህ ብላለች:- “አያቴ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ሆኖልኝ ነበር። እሁድ እሁድ ለምናደርገው የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሁልጊዜ ለሦስት ሰዓት ያህል ይዘጋጅ ነበር። በትምህርቱ ውስጥ የተጠቀሰውን እያንዳንዱን ጥቅስ በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እያወጣ ያነብ የነበረ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ቃላትን መዝገበ ቃላት እያወጣ ይመለከት ነበር። እምብዛም በማይታወቁ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎች ላይ ጥልቅ ማብራሪያ ይሰጥ ነበር። ስለማንኛውም ነገር ብትጠይቁት መልስ ይሰጣችኋል።”
እውነትን የራስህ ስታደርግ በየትኛውም ዋጋ የማትለውጠውን ውድ ንብረት አገኘህ ማለት ነው። ስለዚህ እውነትን “የወላጆችህ ሃይማኖት” እንደሆነ አድርገህ ብቻ አትመልከተው። እንደሚከተለው ሲል የተናገረው መዝሙራዊ ዓይነት የጸና እምነት ሊኖርህ ይገባል:- “አባቴና እናቴ ትተውኛልና፣ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ።” (መዝሙር 27:10) መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ነገር ጠንቅቀህ በማወቅ፣ በማመን፣ እምነትህን ለሌሎች በማካፈልና ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእምነትህ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር እውነትን የራስህ እንዳደረግከው ታሳያለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከታተመው ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ ከተባለው የመዝሙር ቡክሌት የተወሰደ።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የራስህ የሆነ ምርምርና የግል ጥናት በማድረግ እውነትን ራስህ ፈትን