“ለእምነት በብርቱ ተጋደሉ”!
‘በማያዳግም ሁኔታ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠው እምነት በብርቱ ተጋደሉ።’—ይሁዳ 3 የ1980 ትርጉም
1. በዛሬው ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች በውጊያ ላይ የሚገኙት በምን መልኩ ነው?
በጦር ሜዳ የሚገኙ ወታደሮች ሕይወታቸው ሁልጊዜ አስቸጋሪና ውጣ ውረድ የሞላበት ነው። ሙሉ የውጊያ ትጥቅ ታጥቀው ሐሩርና ቁር ሳይሉ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ፣ የመሣሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ በጣም አድካሚ የሆነ ልምምድ ማድረግ፣ መቁሰልን አሊያም ሞትን ከሚያስከትል ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ራስን መከላከል ምን እንደሚመስል እስቲ አስበው። ያም ሆነ ይህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በብሔራት መካከል በሚካሄዱ ጦርነቶች አይካፈሉም። (ኢሳይያስ 2:2-4፤ ዮሐንስ 17:14) ሆኖም ግን በመንፈሳዊ አነጋገር ሁላችንም በጦርነት ውስጥ ያለን መሆናችንን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ሰይጣን ለኢየሱስ ክርስቶስና በምድር ላይ ለሚገኙ ተከታዮቹ ከፍተኛ ጥላቻ አለው። (ራእይ 12:17) ይሖዋ አምላክን ለማገልገል የሚወስኑ ሁሉ መንፈሳዊ ውጊያ ለማድረግ እንደሚመዘገቡ ወታደሮች ናቸው ለማለት ይቻላል።—2 ቆሮንቶስ 10:4
2. ይሁዳ ክርስቲያናዊ ውጊያን የገለጸው እንዴት ነው? ደብዳቤውስ በውጊያው እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው?
2 የኢየሱስ ግማሽ ወንድም የሆነው ይሁዳ እንደሚከተለው ሲል መጻፉ ተገቢ ነበር:- “ወዳጆች ሆይ! ስለ ጋራ ደኅንነታችን ልጽፍላችሁ በብርቱ ፈልጌ ነበር፤ አሁንም በማያዳግም ሁኔታ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠው እምነት በብርቱ እንድትጋደሉ ለመምከር ልጽፍላችሁ ግድ ሆነብኝ።” (ይሁዳ 3 የ1980 ትርጉም) ይሁዳ ክርስቲያኖች ‘በብርቱ እንዲጋደሉ ሲመክር’ “ሥቃይ” ከሚለው ቃል ጋር ተዛማጅ የሆነ ቃል ተጠቅሟል። አዎን፣ ይህ ውጊያ ከባድ አልፎ ተርፎም ሥቃይ የሞላበት ሊሆን ይችላል! በዚህ ውጊያ ጸንቶ መቀጠሉ አንዳንድ ጊዜ አዳጋች ይሆንባችኋልን? አጭር፣ ነገር ግን ኃይለኛ መልእክት የያዘው የይሁዳ ደብዳቤ ሊረዳን ይችላል። የሥነ ምግባር ብልግናን እንድንቋቋም፣ መለኮታዊ ሥልጣንን እንድናከብርና ራሳችንን በአምላክ ፍቅር እንድንጠብቅ ያሳስበናል። ይህንን ምክር በሥራ ላይ እንዴት ልናውል እንደምንችል እንመልከት።
የሥነ ምግባር ብልግናን ተቋቋሙ
3. በይሁዳ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ በምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር?
3 ይሁዳ ከሰይጣን ጋር በሚደረገው ውጊያ አንዳንድ ክርስቲያን ባልንጀሮቹ እየተሸነፉ እንዳሉ መገንዘብ ችሎ ነበር። መንጋው በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኝ ነበር። ይሁዳ ምግባረ ብልሹ ሰዎች “ሾልከው ገብተዋል” ሲል ጽፏል። እነዚህ ሰዎች የሥነ ምግባር ብልግናን በረቀቀ ዘዴ በማስፋፋት ላይ ነበሩ። እንዲሁም ተግባራቸውን ትክክል አስመስለው በማቅረብ “ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ [“ይገባናል የማንለው ደግነት፣” NW] በሴሰኝነት ይለውጣሉ።” (ይሁዳ 4) ምናልባትም በጥንት ዘመን እንደነበሩት አንዳንድ ግኖስቲኮች አንድ ሰው ይበልጥ ኃጢአት በሠራ ቁጥር የአምላክን ጸጋ በዚያው ልክ ይበልጥ ስለሚቀበል ብዙ ኃጢአት መሥራት የተሻለ ነው የሚል ምክንያት ያቀርቡ ይሆናል! ምናልባትም ደግ የሆነው አምላክ ፈጽሞ አይቀጣንም ብለው አስበው ይሆናል። በዚያም ሆነ በዚህ ተሳስተዋል።—1 ቆሮንቶስ 3:19
4. ይሁዳ እንደ ምሳሌ አድርጎ የጠቀሳቸው ይሖዋ ከዚህ ቀደም የወሰዳቸውን የትኞቹን ሦስት ቅዱስ ጽሑፋዊ የቅጣት እርምጃዎች ነው?
4 ይሁዳ እነዚህ ሰዎች ያቀረቧቸው በክፋት የተሞሉ ምክንያቶች ሐሰት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይሖዋ ቀደም ባሉት ጊዜያት ማለትም ‘እምነት ሳያሳዩ በቀሩት’ እስራኤላውያን፣ ከሴቶች ጋር ኃጢአት ለመሥራት ሲሉ ‘መኖሪያቸውን ትተው በመጡት መላእክት’ እንዲሁም ‘ዝሙትን ባደረጉትና ሌላን ሥጋ በተከተሉት’ በሰዶምና ገሞራ ሰዎች ላይ ስለወሰደው የፍርድ እርምጃ የሚገልጹ ሦስት ምሳሌዎችን ጠቅሷል። (ይሁዳ 5-7፤ ዘፍጥረት 6:2-4፤ 19:4-25፤ ዘኁልቁ 14:35) ይሖዋ በሦስቱም ጊዜያት በኃጢአተኞቹ ላይ ኃይለኛ የቅጣት እርምጃ ወስዷል።
5. ይሁዳ ጠቅሶ የጻፈው ከየትኛው የጥንት ነቢይ ነው? ትንቢቱስ ያለ ምንም ጥርጥር የሚፈጸም መሆኑን የሚያመለክተው እንዴት ነው?
5 ቀጥሎም ይሁዳ ከዚህ የበለጠ ታላቅ ፍርድ እንደሚኖር አመልክቷል። በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሌላ በየትኛውም ቦታ ላይ የማይገኘውን የሄኖክን ትንቢት ጠቅሷል።a (ይሁዳ 14, 15) ሄኖክ አምላካዊ ባሕርይ የሌላቸው ሰዎች ሁሉ አምላካዊ ካልሆነው ተግባራቸው ጋር ይሖዋ እንደሚፈርድባቸው ተንብዮአል። ሄኖክ የአምላክ ፍርዶች ያላንዳች ጥርጥር እንደሚፈጸሙ እርግጠኛ ስለነበር ገና ከመፈጸማቸው በፊት እንደተፈጸሙ አድርጎ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው። ሰዎች መጀመሪያ በሄኖክ በኋላም በኖኅ ላይ አሹፈው ይሆናል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ዘባቾች በሙሉ ምድርን ባጥለቀለቀው ጎርፍ ሰጥመው ጠፍተዋል።
6. (ሀ) በይሁዳ ዘመን ይገኙ የነበሩ ክርስቲያኖች ስለ ምን ነገር ማሳሰቢያ አስፈልጓቸው ነበር? (ለ) የይሁዳን ማሳሰቢያዎች ልብ ልንላቸው የሚገባን ለምንድን ነው?
6 ይሁዳ ስለ እነዚህ መለኮታዊ የፍርድ እርምጃዎች የጻፈው ለምን ነበር? ምክንያቱም በእሱ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች እነዚያ የፍርድ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ካደረጉት መጥፎና አስነዋሪ ድርጊቶች ጋር የሚመሳሰሉ ኃጢአቶች በመሥራት ላይ ነበሩ። ይሁዳ የጻፈው ስለ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶች ጉባኤውን ማሳሰብ ስላስፈለገው ነበር። (ይሀዳ 5) ይሖዋ አምላክ የሚያደርጉትን ነገር እንደሚመለከተው ዘንግተው ነበር። አዎን፣ አገልጋዮቹ ሆን ብለው ሕጎቹን ሲጥሱና ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ሲያረክሱ ይመለከታል። (ምሳሌ 15:3) እንዲህ ያሉ ድርጊቶች በጣም ያሳዝኑታል። (ዘፍጥረት 6:6፤ መዝሙር 78:40) እዚህ ግቡ የማንባል የሰው ልጆች የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ ልብ ልናሳዝን ወይም ልናስደስት እንደምንችል ማወቃችን የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን ለእሱ አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብንም የሚያደርግ ነው። በየዕለቱ ስለሚመለከተን የልጁን የኢየሱስ ክርስቶስን ፈለግ ለመከተል የተቻለንን ሁሉ ስናደርግ ልቡን ደስ ያሰኘዋል። ስለዚህ ይሁዳ የሰጠው ዓይነት ማሳሰቢያዎችን ፈጽሞ ልንጠላቸው አይገባንም፤ ከዚህ ይልቅ ልብ ልንላቸው ይገባል።—ምሳሌ 27:11፤ 1 ጴጥሮስ 2:21
7. (ሀ) ከባድ በሆኑ መጥፎ ድርጊቶች የሚካፈሉ ሰዎች ሳይውሉ ሳያድሩ እርዳታ መፈለግ የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ሁላችንም ከሥነ ምግባር ብልግና ልንርቅ የምንችለው እንዴት ነው?
7 ይሖዋ መመልከት ብቻ ሳይሆን እርምጃም ይወስዳል። ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የፍትህ አምላክ ክፉዎችን ይቀጣል። (1 ጢሞቴዎስ 5:24) ፍርዶቹ የጥንት ታሪኮች ናቸው፣ እሱ ዛሬ እኛ የምንሠራውን መጥፎ ነገር ከቁብ አይቆጥረውም የሚሉ ሰዎች ራሳቸውን እያታለሉ ናቸው። በዛሬው ጊዜ የሥነ ምግባር ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች ከክርስቲያን ሽማግሌዎች አፋጣኝ እርዳታ መሻታቸው ምንኛ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው! (ያዕቆብ 5:14, 15) መንፈሳዊ ውጊያችን በሥነ ምግባር ብልግና ላለመውደቅ መታገልንም እንደሚጨምር ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። በየዓመቱ ከመካከላችን ተወግደው የሚወጡ አሉ። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የሥነ ምግባር ብልግና ከፈጸሙ በኋላ ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች ያልሆኑ ናቸው። ሌላው ቀርቶ ወደዚህ አቅጣጫ ሊመራን የሚችለውን ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ ልናደርግ ይገባል።—ከማቴዎስ 26:41 ጋር አወዳድር።
መለኮታዊ ምንጭ ያለውን ሥልጣን አክብሩ
8. በይሁዳ 8 ላይ የተጠቀሱት “ሥልጣን ያላቸው” ሰዎች እነማን ናቸው?
8 ይሁዳ የጠቀሰው ሌላው ችግር ደግሞ ለመለኮታዊ ሥልጣን አክብሮት ማጣት ነው። ለምሳሌ ያህል በቁጥር 8 ላይ እነዚያኑ ክፉ ሰዎች “ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ” በማለት ከሷቸዋል። “ሥልጣን ያላቸው” የተባሉት እነማን ናቸው? በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት ኃላፊነት የተሰጣቸው ሆኖም ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል በጉባኤዎች ውስጥ የአምላክን መንጋ በእረኝነት እንዲጠብቁ የተሾሙ ሽማግሌዎች አሉ። (1 ጴጥሮስ 5:2) እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ የመሳሰሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችም አሉ። እንዲሁም በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረው የሽማግሌዎች አካል አጠቃላዩን የክርስቲያን ጉባኤ የሚመለከቱ ውሳኔዎችን የሚያሳልፍ የአስተዳደር አካል በመሆን ያገለግል ነበር። (ሥራ 15:6) ይሁዳ በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ አንዳንዶች እነዚህን ወንድሞች መሳደባቸው ወይም ስማቸውን ማጥፋታቸው በጥልቅ አሳስቦት ነበር።
9. ይሁዳ ለሥልጣን ተገቢውን አክብሮት አለማሳየትን አስመልክቶ የትኞቹን ምሳሌዎች ጠቅሷል?
9 ይሁዳ እንዲህ ያለውን አክብሮት የጎደለው አነጋገር ለማውገዝ በቁጥር 11 ላይ የሚከተሉትን ሦስት ተጨማሪ ምሳሌዎችን ጠቅሷል:- ቃየን፣ በለዓምና ቆሬ። ቃየን የይሖዋን ፍቅራዊ ምክር ወደ ጎን ገሸሽ በማድረግ ሆነ ብሎ ሕይወት ወደ ማጥፋት የመራውን የጥላቻ መንገድ መርጧል። (ዘፍጥረት 4:4-8) በለዓም የተሰጠው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ከሰብዓዊ ባሕርይ ውጭ ከሆነ ኃይል መሆኑ ምንም አያጠራጥርም፤ አህያው እንኳን ሳትቀር አፍ አውጥታ ተናግራው ነበር! ይሁን እንጂ በለዓም በራስ ወዳድነት በአምላክ ሕዝቦች ላይ በጀመረው ደባ ቀጠለ። (ዘኁልቁ 22:28, 32-34፤ ዘዳግም 23:5) ቆሬ የተሰጠው የኃላፊነት ቦታ ነበረው፤ ሆኖም በዚያ አልረካም። በምድር ላይ እጅግ ትሑት በነበረው ሰው በሙሴ ላይ ዓመፅ አነሳስቷል።—ዘኁልቁ 12:3፤ 16:1-3, 32
10. ዛሬ አንዳንዶች ‘ሥልጣን ያላቸውን በመሳደብ’ ወጥመድ ውስጥ ሊወድቁ የሚችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ያለው አነጋገር ሊወገድ የሚገባውስ ለምንድን ነው?
10 እነዚህ ምሳሌዎች ምክር የመስማትንና ይሖዋ በኃላፊነት ቦታ የሚጠቀምባቸውን ወንድሞች የማክበርን አስፈላጊነት በግልጽ ያስተምሩናል! (ዕብራውያን 13:17) የተሾሙ ሽማግሌዎች ልክ እንደኛው ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች በመሆናቸው በእነሱ ላይ ስህተቶችን ማግኘት በጣም ቀላል ነው። ይሁን እንጂ በስህተቶቻቸው ላይ ብናተኩርና ለእነሱ ያለንን አክብሮት ብንቀንስ ‘ሥልጣን ያላቸውን መሳደባችን አይሆንም?’ ይሁዳ በቁጥር 10 ላይ ‘የማያውቁትን ሁሉ ስለሚሳደቡ’ ሰዎች ተናግሯል። አልፎ አልፎ አንዳንዶች የሽማግሌዎች አካል ወይም የፍርድ ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ ይተቻሉ። ሆኖም ሽማግሌዎቹ እዚያ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ምን ዝርዝር ጉዳዮችን መመልከት ጠይቆባቸው እንደነበር የሚያውቁት ነገር የለም። ስለዚህ በትክክል ስለማያውቁት ነገር ለምን የስድብ ቃላት ይናገራሉ? (ምሳሌ 18:13) እንዲህ ያሉ አፍራሽ ነገሮችን በመናገር የሚቀጥሉ ሰዎች በጉባኤ ውስጥ መከፋፈልን ከመፍጠራቸውም በላይ የእምነት አጋሮች አንድ ላይ በሚሰባሰቡባቸው ቦታዎች ‘በውኃ ሥር እንደተደበቁ ዓለቶች ይሆናሉ።’ (ይሁዳ 12, 16, 19 NW) በሌሎች መንፈሳዊነት ላይ አደጋ መፍጠር በፍጹም አንፈልግም። እንዲያውም እያንዳንዳችን ለአምላክ መንጋ በሙሉ ኃይላቸው ለሚደክሙት በኃላፊነት ላይ ለሚገኙት ወንድሞች አድናቆታችንን ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—1 ጢሞቴዎስ 5:17
11. ሚካኤል በሰይጣን ላይ የስድብ ቃል ከመናገር የተቆጠበው ለምንድን ነው?
11 ይሁዳ አግባብ ላለው ሥልጣን አክብሮት ማሳየትን በተመለከተ አንድ ምሳሌ ጠቅሷል። “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር:- ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም” ሲል ጽፏል። (ይሁዳ 9) በመንፈስ አነሣሽነት ከተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በይሁዳ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ የሚገኘው ይህ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አስደናቂ ታሪክ ሁለት ጉልህ ትምህርቶችን ያስተምረናል። በአንድ በኩል ፍርድን ለይሖዋ እንድንተው ያስተምረናል። ሰይጣን የታማኙን የሙሴን አካል የሐሰት አምልኮን ለማስፋፋት ያለ አግባብ ሊጠቀምበት ፈልጎ እንደነበረ ግልጽ ነው። እንዴት ያለ ክፋት ነው! ቢሆንም ሚካኤል የፍርድ ቃል ከመናገር ይልቅ በትሕትና ዝም ማለትን መርጧል፤ ምክንያቱም የመፍረድ ሥልጣን ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። ታዲያ እኛማ ይሖዋን ለማገልገል በሚሞክሩ የታመኑ ወንዶች ላይ ከመፍረድ መቆጠብ እንዳለብን ምንም ጥርጥር የለውም።
12. በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ ወንድሞች ከሚካኤል ምሳሌ ምን መማር ይችላሉ?
12 በሌላ በኩል ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ከሚካኤል የሚማሩት ትምህርት አለ። ሚካኤል “የመላእክት አለቃ” ማለትም የመላእክት ሁሉ የበላይ ቢሆንም የሚያስቆጣ ሁኔታ ሲያጋጥመው ሥልጣኑን አለ አግባብ አልተጠቀመም። ሥልጣናቸውን አለ አግባብ መጠቀማቸው ለይሖዋ ሉዓላዊነት አክብሮት አለማሳየት መሆኑን ስለሚገነዘቡ የታመኑ ሽማግሌዎች ይህን ምሳሌ በሚገባ ይከተላሉ። የይሁዳ ደብዳቤ በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ስለነበራቸው፣ ነገር ግን ሥልጣናቸውን አለ አግባብ ስለተጠቀሙ ሰዎች ብዙ የሚናገረው ነገር አለው። ለምሳሌ ያህል ከቁጥር 12 እስከ 14 (NW) ላይ ‘ያለ ፍርሃት ራሳቸውን የሚመግቡ እረኞችን’ በጥብቅ አውግዟል። (ከሕዝቅኤል 34:7-10 ጋር አወዳድር።) በሌላ አነጋገር ለይሖዋ መንጋ ሳይሆን ለራሳቸው ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጡ ነበር። በዛሬ ጊዜ የሚገኙ ሽማግሌዎች እንዲህ ካሉት መጥፎ ምሳሌዎች ብዙ ሊማሩ ይችላሉ። እዚህ ላይ ያሉት የይሁዳ ቃላት ምን ዓይነት ሰዎች ለመሆን እንደማንፈልግ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ። ለራስ ወዳድነት እጃችንን ከሰጠን የክርስቶስ ወታደሮች ልንሆን አንችልም፤ የግል ጥቅማችንን በማሳደድ ተጠምደናል። ከዚህ ይልቅ ሁላችንም “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” የሚሉትን ቃላት ተግባራዊ እናድርግ።—ሥራ 20:35
“በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ”
13. ሁላችንም በአምላክ ፍቅር ተጠብቀን ለመኖር ከልብ መፈለግ ያለብን ለምንድን ነው?
13 በደብዳቤው ማገባደጃ ላይ ይሁዳ “በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” የሚል ልብ የሚነካ ምክር ይሰጣል። (ይሁዳ 21) በዚህ ክርስቲያናዊ ውጊያ ለመቀጠል በይሖዋ አምላክ ፍቅር ውስጥ ከመታቀፍ የበለጠ ሊረዳን የሚችል ነገር የለም። ደግሞም ጎልቶ የሚታየው የይሖዋ ባሕርይ ፍቅር ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ጳውሎስ በሮም ይገኙ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8:38, 39) ይሁንና በዚህ ፍቅር ውስጥ ለመቆየት የምንችለው እንዴት ነው? ይሁዳ በተናገረው መሠረት ልንወስዳቸው የምንችላቸውን ሦስት እርምጃዎች እንመልከት።
14, 15. (ሀ) ‘በተቀደሰ እምነት’ ራሳችንን ማነጽ ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) መንፈሳዊ ትጥቃችን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መመርመር የምንችለው እንዴት ነው?
14 በመጀመሪያ ይሁዳ ራሳችንን ‘ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ እምነት’ ላይ መገንባታችንን እንድንቀጥል ይነግረናል። (ይሁዳ 20) በቀደመው ርዕስ ውስጥ እንደተመለከትነው ይህ ቀጣይ የሆነ ሂደት ነው። የአየር ጠባይ መለዋወጥ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዲቋቋም በየጊዜው እድሳት እንደሚያስፈልገው ሕንፃ ነን። (ከማቴዎስ 7:24, 25 ጋር አወዳድር።) ስለዚህ በፍጹም ከሚገባው በላይ በራሳችን አንመካ። ከዚህ ይልቅ ይበልጥ ጠንካሮችና የታመንን የክርስቶስ ወታደሮች እንድንሆን በእምነታችን መሠረት ላይ ራሳችንን የምንገነባባቸውን አቅጣጫዎች እንፈልግ። ለምሳሌ ያህል በኤፌሶን 6:11-18 ላይ የተጠቀሱትን የመንፈሳዊ ውጊያ ትጥቆች ልንመለከት እንችላለን።
15 መንፈሳዊው የውጊያ ትጥቃችን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ትልቁ ‘የእምነት ጋሻችን’ ተፈላጊውን ጥንካሬ እንደያዘ ነውን? ያለፉትን ጥቂት ዓመታት ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት አልፎ አልፎ ከስብሰባዎች እንደ መቅረት፣ ለአገልግሎቱ ቅንዓት እንደ ማጣት ወይም ለግል ጥናት የነበረን ፍላጎት እንደ መቀነስ የመሳሰሉ አንዳንድ የቸልተኝነት ምልክቶች ይታዩብናልን? እነዚህ ምልክቶች ከታዩ ሁኔታው አደገኛ ነው! ራሳችንን በእውነት ለመገንባትና ለማጠንከር ጊዜ ሳናጠፋ እርምጃ መውሰድ አለብን።—1 ጢሞቴዎስ 4:15፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2፤ ዕብራውያን 10:24, 25
16. በመንፈስ ቅዱስ መጸለይ ማለት ምን ማለት ነው? ይሖዋን ዘወትር ልንጠይቀው የሚገባንስ ስለ የትኛው ነገር ነው?
16 በአምላክ ፍቅር ራሳችንን ለመጠበቅ የሚያስችለን ሁለተኛው መንገድ ‘በመንፈስ ቅዱስ መጸለይ’ ነው። (ይሁዳ 20) ይህ ማለት የይሖዋ መንፈስ አድሮብንና በመንፈስ ከተጻፈው ቃሉ ጋር ተስማምተን መጸለይ ማለት ነው። ጸሎት ወደ ይሖዋ በግል የምንቀርብበትና ለእሱ ያደርን መሆናችንን የምንገልጽበት ዋነኛው መንገድ ነው። ይህን ድንቅ መብት በፍጹም ችላ ልንለው አይገባም! እንዲሁም በምንጸልይበት ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን ዘወትር ልንጠይቀው እንችላለን። (ሉቃስ 11:13) ጸሎት ከሁሉ የሚበልጠው ጠንካራ ኃይላችን ነው። በዚህ እርዳታ አማካኝነት በአምላክ ፍቅር ውስጥ ተጠብቀን ለመቆየትና የክርስቶስ ወታደሮች በመሆን ለመጽናት እንችላለን።
17. (ሀ) ይሁዳ ምሕረትን አስመልክቶ የተወው ምሳሌ የሚደነቅ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) እያንዳንዳችን ምሕረት ማሳየታችንን ልንቀጥል የምንችለው እንዴት ነው?
17 በሦስተኛ ደረጃ ይሁዳ ምሕረት ማሳየታችንን እንድንቀጥል አጥብቆ መክሮናል። (ይሁዳ 22) በዚህ ረገድ እሱ ራሱ የተወው ምሳሌ የሚደነቅ ነው። ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሾልኮ በገባው ብክለት፣ የሥነ ምግባር ብልግናና ክህደት መረበሹ ትክክል ነበር። ያም ሆኖ ግን በእነዚህ ጊዜያት እንደ ምሕረት ያለውን “የለዘበ” ባሕርይ ማሳየት በጣም አደገኛ ነው ብሎ ቸኩሎ አልደመደመም። እንዲያውም ጥርጣሬ ያለባቸውን በደግነት በማስረዳትና ከባድ ኃጢአት ወደ መፈጸም ያዘነበሉትን እንኳን ሳይቀር ‘ከእሳት ነጥቆ በማውጣት’ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምሕረት ማሳየታቸውን እንዲቀጥሉ ወንድሞቹን አሳስቧል። (ይሁዳ 23፤ ገላትያ 6:1) ዛሬ ባለንበት በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለሽማግሌዎች የሚሆን እንዴት ያለ ጥሩ ምክር ነው! ሽማግሌዎች አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅ ቢሆኑም ምሕረት ለማሳየት የሚቻልበት መሠረት ካለ ግን ምሕረት ለማሳየት ይጥራሉ። በተመሳሳይ ሁላችንም አንዳችን ለሌላው ምሕረት ለማሳየት እንፈልጋለን። ለምሳሌ ያህል በጥቃቅን ነገሮች ሳይቀር ቂም ከመያዝ ይልቅ ይቅር ባይነታችንን ልናበዛ እንችላለን።—ቆላስይስ 3:13
18. በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ድል እንደምንቀዳጅ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው?
18 ውጊያችን ቀላል አይደለም። ይሁዳ እንዳለው ‘በብርቱ መጋደልን’ የሚጠይቅ ነው። (ይሁዳ 3) ጠላቶቻችን ኃይለኞች ናቸው። ሰይጣን ብቻ ሳይሆን በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ክፉ ዓለምና አለፍጽምናችን በእኛ ላይ ዘምተውብናል። ሆኖም ድል እንደምንቀዳጅ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን! ለምን? ምክንያቱም የተሰለፍነው ከይሖዋ ጎን ነው። ይሁዳ ደብዳቤውን የሚደመድመው ይሖዋ “ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ . . . ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም” የሚገባው መሆኑን በማሳሰብ ነው። (ይሁዳ 25) ይህ አስገራሚ ሐሳብ አይደለምን? ታዲያ ይኸው አምላክ ‘ከመሰናከል ሊጠብቀን’ እንደሚችል ጥያቄ ሊነሣ ይችላልን? (ይሁዳ 24) በፍጹም አይነሣም! እያንዳንዳችን የሥነ ምግባር ብልግና እንድንፈጽም የሚደርስብንን ተጽእኖ በመቋቋም፣ መለኮታዊ ሥልጣንን በማክበርና በአምላክ ፍቅር ተጠብቀን በመኖር ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በዚህ መንገድ አንድ ላይ ሆነን ክብራማ ድል እንቀዳጃለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ ተመራማሪዎች ይሁዳ ጠቅሶ የጻፈው መጽሐፈ ሄኖክ ከተባለው የአዋልድ መጽሐፍ ነው በማለት ይከራከራሉ። ይሁን እንጂ አር ሲ ኤች ሌንስኪ እንዲህ ብለዋል:- “‘መጽሐፈ ሄኖክ የተባለው መጽሐፍ ምንጩ ከየት ነው?’ ብለን እንጠይቅ ይሆናል። መጽሐፉ ባዕድ ጭማሪ ሲሆን የተለያዩ ክፍሎች መቼ እንደተጻፉ በእርግጠኝነት የሚያውቅ ማንም የለም። . . . ምናልባት አንዳንዶቹ መግለጫዎች ከራሱ ከይሁዳ አልተወሰዱ ይሆናል፤ ሆኖም ማንም ሰው እንዲህ ብሎ በእርግጠኝነት ሊናገር አይችልም።”
ለክለሳ የሚሆኑ ጥያቄዎች
◻ የይሁዳ ደብዳቤ የሥነ ምግባር ብልግናን እንድንቋቋም ትምህርት የሚሰጠን እንዴት ነው?
◻ መለኮታዊ ሥልጣንን ማክበር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ በጉባኤ ሥልጣን አለ አግባብ መጠቀምን ከበድ አድርገን መመልከት የሚገባን ለምንድን ነው?
◻ በአምላክ ፍቅር ተጠብቀን ለመኖር ምን ልናደርግ እንችላለን?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሮማውያን ወታደሮች በተለየ ሁኔታ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ውጊያ ያካሂዳሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያን እረኞች በራስ ወዳድነት ሳይሆን ከፍቅር በመነጨ ስሜት ያገለግላሉ