ምዕራፍ 13
በእሳት የነጠረ ወርቅ ግዛ
ሎዶቅያ
1, 2. ክብር ከተቀዳጀው ኢየሱስ መልእክት ከደረሳቸው ሰባት ጉባኤዎች የመጨረሻ የሆነው ጉባኤ ይገኝ የነበረው የት ነው? ከተማይቱ ተለይታ የምትታወቅባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው?
ከሙታን ከተነሳው ከኢየሱስ መልዕክት ከተቀበሉት ሰባት ጉባኤዎች የመጨረሻው ጉባኤ ሎዶቅያ ነው። ይህም መልእክት ዓይን የሚከፍትና የሚቀሰቅስ ትምህርት ይዞአል።
2 በዛሬው ጊዜ የሎዶቅያን ፍርስራሾች ከአላሴሂር ደቡብ ምሥራቅ 88 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በዴኒዝሊ ከተማ አቅራቢያ እናገኛለን። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሎዶቅያ በጣም ኃብታም ከተማ ነበረች። ከተማዋ አውራ ጎዳናዎች በሚገናኙበት ሥፍራ የተቆረቆረች ስለነበረች የባንክ ሥራና የንግድ ማዕከል ነበረች። በከተማይቱ ይሸጥ የነበረው የዓይን መድኃኒት በጣም እውቅ ሆኖ ስለነበረ ተጨማሪ ብልጽግና የሚያስገኝላት የገቢ ምንጭ ሆኖላት ነበር። በተጨማሪም ሎዶቅያ በጣም ጥሩ ጥራት ከነበረው ጥቁር ሱፍ ይሠራ በነበረው ውድ ልብስ ከፍተኛ ዝና አትርፋ ነበር። የከተማይቱ ዋና ችግር የውኃ እጥረት ሲሆን ይህም ችግር ቢሆን ከሩቅ ሥፍራ በቦይ አማካኝነት ይመጣ በነበረው ፍልውኃ ተቃልሎ ነበር። ስለዚህ ውኃው ወደ ከተማዋ ሲደርስ ለብ ያለ ይሆን ነበር።
3. ኢየሱስ ለሎዶቅያ ጉባኤ የላከውን መልእክት የከፈተው ምን በማለት ነው?
3 ሎዶቅያ በቆላስይስ አቅራቢያ የምትገኝ ከተማ ነበረች። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች ሲጽፍ ለሎዶቅያ ሰዎች ስለጻፈው ደብዳቤ ጠቅሶአል። (ቆላስይስ 4:15, 16) ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤው ምን እንደጻፈ አናውቅም። አሁን ኢየሱስ ለሎዶቅያ ክርስቲያኖች የላከው መልዕክት እንደሚያመለክተው ግን በአሳዛኝ መንፈሳዊ ሁኔታ ላይ ወድቀዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ እንደተለመደው በመጀመሪያ የተናገረው የራሱን ሥልጣንና ደረጃ የሚያመለክት ቃል ነው። እንዲህ አለ:- “በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ:- አሜን የሆነው የታመነውና እውነተኛው ምስክር፣ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል።” —ራእይ 3:14
4. ኢየሱስ “አሜን” የሆነው እንዴት ነው?
4 ኢየሱስ ራሱን “አሜን የሆነው” ሲል የጠራው ለምንድን ነው? ይህ የማዕረግ ስም ለመልእክቱ የፍርድ ክብደት ጨምሮለታል። “አሜን” የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ቃል በቃል ሲተረጎም “በእርግጥ”፣ “ይሁን”፣ “ይደረግ” የሚል ትርጉም አለው። በጸሎት መጨረሻ ላይ ሲሆን በጸሎቱ ውስጥ ከተገለጸው ነገር ጋር ሙሉ በሙሉ መስማማትን ለማረጋገጥ የሚነገር ቃል ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:16) የኢየሱስ እንከን የለሽ አቋምና መሥዋዕታዊ ሞት የይሖዋ ውድ ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ ዋስትና ሰጥቷል። በዚህም ኢየሱስ “አሜን” ሆኖአል። (2 ቆሮንቶስ 1:20) ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ማንኛውም ጸሎት ለይሖዋ አምላክ የሚቀርበው በኢየሱስ በኩል ነው።—ዮሐንስ 15:16፤ 16:23, 24
5. ኢየሱስ “የታመነውና እውነተኛው ምሥክር” የሆነው በምን መንገድ ነው?
5 በተጨማሪም ኢየሱስ “የታመነውና እውነተኛው ምስክር” ነው። የይሖዋ አምላክ ታማኝ አገልጋይ እንደመሆኑ መጠን ታማኝ፣ እውነተኛና ጻድቅ መሆኑ በትንቢቶች ሁሉ ተገልጾአል። (መዝሙር 45:4፤ ኢሳይያስ 11:4, 5፤ ራእይ 1:5፤ 19:11) ትልቁ የይሖዋ ምሥክር ኢየሱስ ነው። እንዲያውም “የእግዚአብሔር ፍጥረት መጀመሪያ” እንደመሆኑ መጠን ከመጀመሪያው አንስቶ የአምላክን ግርማ አውጆአል። (ምሳሌ 8:22-30) በምድር ላይ ሰው ሆኖ ይኖር በነበረበት ጊዜ ለእውነት መስክሮ ነበር። (ዮሐንስ 18:36, 37፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:13) ከሙታን ከተነሳ በኋላም ለደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው ቃል ከገባላቸው በኋላ እንዲህ አላቸው:- “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ቀን ጀምሮ ኢየሱስ እነዚህን ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” ምሥራቹን እንዲሰብኩ ሲመራቸው ቆይቶአል። (ሥራ 1:6-8፤ ቆላስይስ 1:23) በእውነትም ኢየሱስ የታመነውና እውነተኛው ምስክር ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነበር። የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ቃሉን ቢያዳምጡ ይጠቀማሉ።
6. (ሀ) ኢየሱስ በሎዶቅያ የነበረውን ጉባኤ መንፈሣዊ ሁኔታ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በሎዶቅያ የነበሩ ክርስቲያኖች ሳይከተሉ የቀሩት የትኛውን የኢየሱስ አርዓያ ነው?
6 ኢየሱስ ለሎዶቅያ ክርስቲያኖች ምን የሚነግራቸው መልእክት ነበረው? እነርሱን የሚያመሰግንበት ምክንያት አልነበረውም። በግልጽ የሚከተለውን ነገራቸው:- “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ፣ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።” (ራእይ 3:15, 16) እንዲህ ዓይነት መልእክት ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ቢደርስህ ምን ታደርጋለህ? ነቃ ብለህ ራስህን አትመረምርምን? የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ቸልተኞችና ምስጋና ቢሶች በመሆን በመንፈሳዊ ፈዝዘው ስለነበረ ራሳቸውን መቀስቀስ ነበረባቸው። (ከ2 ቆሮንቶስ 6:1 ጋር አወዳድር።) ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ምሳሌያቸው ሊሆን የሚገባው ኢየሱስ ለይሖዋና ለአገልገሎቱ እንደ እሳት የሚነድድ ቅንዓት ነበረው። (ዮሐንስ 2:17) ከዚህም በላይ ኢየሱስ በጣም በሚያተኩስ ሞቃት ቀን እንደሚጠጣ ቀዝቃዛ ውኃ ልዝብ፣ የማይጎዳ ሰውነት የሚያድስ እንደሆነ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ተገንዝበው ነበር። (ማቴዎስ 11:28, 29) የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ግን በራድም ሞቃትም አልነበሩም። በከተማቸው መሃል ይፈስ እንደነበረው ውኃ ለብ ያሉ ሆነዋል። ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ሊጥላቸውና ‘ከአፉ አውጥቶ ሊተፋቸው’ የሚገቡ ሆነዋል። እኛ ግን ዘወትር እንደ ኢየሱስ ሰዎችን የሚያረካ መንፈሳዊ ውኃ ለማዳረስ በቅንዓት እንጣር።—ማቴዎስ 9:35-38
“‘ሀብታም ነኝ’ . . . የምትል ስለሆንህ”
7. (ሀ) ኢየሱስ የሎዶቅያ ክርስቲያኖችን ችግር ምንጭ የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ የሎዶቅያ ክርስቲያኖች እውርና ራቁታቸውን እንደሆኑ የተናገረው ለምንድን ነው?
7 የሎዶቃውያን ችግር ምንጩ ምን ነበር? ከሚቀጥሉት የኢየሱስ ቃላት ጥሩ ሐሳብ እናገኛለን። “ሀብታም ነኝና ባለ ጠጋ ሆኜአለሁ። አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፣ ጎስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ” ብሎአል። (ራእይ 3:17፤ ከሉቃስ 12:16-21 ጋር አወዳድር።) ሀብታም በሆነ ከተማ ውስጥ ይኖሩ ስለነበር በሀብታቸው ተመክተው ነበር። አኗኗራቸው በከተማቸው ውስጥ በነበሩት ስታዲየሞች፣ ቲያትር ቤቶችና የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ተነክቶ ስለነበረ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ” ሆነው ነበር።a (2 ጢሞቴዎስ 3:4) ቁሳዊ ብልጽግና የነበራቸው ሎዶቃውያን በመንፈሳዊ ድሆችና ጎስቋሎች ነበሩ። ‘በሰማይ የሚሆን መዝገብ’ አልነበራቸውም። (ማቴዎስ 6:19-21) በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ መንግሥት የመጀመሪያውን ደረጃና ቅድሚያ በመስጠት ቀላል የዓይን ትኩረት ይዘው አልኖሩም። መንፈሳዊ ብርሃን የሌላቸው እውሮች ስለነበሩ በጨለማ ውስጥ ይኖሩ ነበር። (ማቴዎስ 6:22, 23, 33) ከዚህም በላይ ሥጋዊ ብልጽግናቸው ያማረ ልብስ ሊያስገዛቸው ቢችልም በኢየሱስ ዓይን ግን ራቁታቸውን ነበሩ። ክርስቲያን መሆናቸውን የሚያሳውቅላቸው መንፈሳዊ ልብስ አልነበራቸውም።—ከራእይ 16:15 ጋር አወዳድር።
8. (ሀ) ዛሬም በሎዶቅያ እንደነበረው ያለ ሁኔታ የሚታየው እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች በዚህ ስግብግብ ዓለም ውስጥ ራሳቸውን ያሳቱት እንዴት ነው?
8 በጣም በሚያስደነግጥ ሁኔታ ላይ ነበሩ። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ እንመለከት የለምን? ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚፈጠርበት መሠረታዊ ምክንያት ምንድን ነው? በቁሳዊ ንብረትና በሰብዓዊ ችሎታ ላይ ከመመካት የሚመጣ በራስ የመታመን ዝንባሌ ነው። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ሕዝበ ክርስትና ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች አልፎ አልፎ በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ብቻ አምላክን እንደሚያስደስቱ በማመን ራሳቸውን አታልለዋል። ለይስሙላ ብቻ ‘ቃሉን የሚያደርጉ’ በመሆን በቃኝ ብለው ይኖራሉ። (ያዕቆብ 1:22) ከዮሐንስ ክፍል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ልባቸው ያተኮረው በአዳዲስ የልብስ ፋሽኖች፣ በቆንጆ መኪናዎችና ቤቶች ላይ ነው። ሕይወታቸው የተመሠረተው በመዝናኛና በደስታ ላይ ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17) ይህ ሁሉ መንፈሳዊ ማስተዋልን ያደነዝዛል። (ዕብራውያን 5:11, 12) ለብ ያሉና ቸልተኞች ከመሆን ይልቅ ‘የመንፈሱን እሳት’ እንደገና ማቀጣጠልና ‘ቃሉን ለመስበክ’ ልባዊ ጉጉት ማሳየት ነበረባቸው። —1 ተሰሎንቄ 5:19፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2, 5
9. (ሀ) ለብ ያሉ ክርስቲያኖችን ሊያስደነግጣቸው የሚገባው የትኛው የኢየሱስ ቃል ነው? ለምንስ? (ለ) ጉባኤው የባዘኑ ‘በጎችን’ እንዴት ሊረዳቸው ይችላል?
9 ኢየሱስ ለብ ያሉ ክርስቲያኖችን የሚመለከተው እንዴት ነው? ምን እንደሚሰማው የተናገራቸው ግልጽ ቃላት ሊያስደነግጧቸው ይገባ ነበር። እርሱም “ጎስቋላና ምስኪንም ድሃም እውርም የተራቆትህም መሆንህን” አታውቅም አላቸው። ሕሊናቸው ደንዝዞ ስለነበረ የወደቁበትን አሳዛኝ ሁኔታ እንኳን ሊገነዘቡ አልቻሉም ነበር። (ከምሳሌ 16:2፤ 21:2 ጋር አወዳድር።) ይህ ዓይነቱ አሳሳቢ ሁኔታ በጉባኤው ውስጥ በቸልታ ሊታይ አይገባውም። ሽማግሌዎችና በሽማግሌዎቹ የተመደቡ ሌሎች ወንድሞች ለቅንዓት ጥሩ ምሳሌዎች በመሆንና በፍቅር የእረኝነት ጥበቃ በማድረግ እነዚህን የባዘኑ ‘በጎች’ ቀድሞ ያቀርቡ ከነበረው የሙሉ ልብ አገልግሎት ያገኙ ወደ ነበረው ደስታ ሊመልሱአቸው ይችሉ ይሆናል።—ሉቃስ 15:3-7
ሀብታም ስለመሆን የተሰጠ ምክር
10. በሎዶቅያ የነበሩ ክርስቲያኖች ከእርሱ እንዲገዙ ኢየሱስ የነገራቸው “ወርቅ” ምንድን ነው?
10 በሎዶቅያ ለነበረው አሳዛኝ ሁኔታ መድኃኒት ይገኝለት ይሆንን? እነዚህ ክርስቲያኖች የሚከተለውን የኢየሱስን ምክር ቢከተሉ ሊፈወሱ ይችሉ ነበር። “ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ . . . ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።” (ራእይ 3:18ሀ) በእሳት የተነጠረና ቆሻሻው በሙሉ የተወገደለት እውነተኛ ክርስቲያናዊ ወርቅ ‘በአምላክ ፊት ባለጠጎች’ ያደርጋቸዋል። (ሉቃስ 12:21) እንዲህ ያለውን ወርቅ ከየት ሊገዙ ይችላሉ? ከኢየሱስ ነው እንጂ በከተማቸው ይገኙ ከነበሩ ባንኮች ሊያገኙ አይችሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ባለጠጋ የሆኑ ክርስቲያኖች “ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፣ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች እንዲሆኑ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ” እንዲመክራቸው በነገረው ጊዜ ይህ ወርቅ ምን እንደሆነ ገልጾአል። “እውነተኛውን ሕይወት” ሊጨብጡ የሚችሉት በዚህ ረገድ ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ ብቻ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 6:17-19) ቁሳዊ ብልጽግና የነበራቸው ሎዶቃውያን የጳውሎስን ምክር ተከትለው በመንፈሳዊ ባለ ጠጎች መሆን ነበረባቸው።—በተጨማሪም ምሳሌ 3:13-18 ተመልከት።
11. “በእሳት የነጠረ ወርቅ” ስለገዙ ሰዎች ምን ዘመናዊ ምሳሌ አለን?
11 በዘመናችን “በእሳት የነጠረ ወርቅ” በመግዛት ረገድ አርዓያ የሚሆኑን ክርስቲያኖች ልናገኝ እንችላለንን? አዎ፣ እናገኛለን። የጌታ ቀን በቀረበበት ጊዜ እንኳን በጣም አነስተኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ስለ ሕዝበ ክርስትና ባቢሎናዊ ትምህርቶች ሐሰተኛነት መገንዘብ ጀምሮ ነበር። ከእነዚህም የሐሰት ትምህርቶች መካከል የሥላሴ፣ የነፍስ አለመሞት፣ የሲኦል ሥቃይ፣ የሕጻናት ጥምቀት፣ የሥዕሎችና ምስሎች አምልኮ (መስቀልንና የማርያምን አምልኮ ይጨምራል) ትምህርቶች ይገኛሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጠበቃ ሆነው በመቆም የሰው ልጅ ብቸኛ ተስፋ የይሖዋ መንግሥት እንደሆነችና ደህንነት የሚገኘው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ብቻ እንደሆነ ሲያውጁ ቆይተዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት የአሕዛብ ዘመን የሚፈጸመው በ1914 እንደሆነና በዚህም ዓመት በምድር ላይ አስደንጋጭ ሁኔታዎች እንደሚከሰቱ 40 ዓመት ያህል ቀደም ብለው አስታውቀው ነበር።—ራእይ 1:10
12. በመንቃት ላይ ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል ቀዳሚ በመሆን ይሠራ የነበረው ማን ነበር? በሰማይ መዝገብ በመሰብሰብ ረገድ በጣም ጥሩ ምሳሌ የተወልንስ እንዴት ነው?
12 ከነበሩበት ሁኔታ በመንቃት ላይ ከነበሩት ክርስቲያኖች መካከል በ1870ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ቻርልስ ቴዝ ራስል ቀዳሚ በመሆን በአሌጌኒ ፔንስልቫንያ (በአሁኑ ጊዜ በፒትስበርግ ክፍለ ሀገር ውስጥ ይገኛል) ዩ.ኤስ.ኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አቋቁሞ ነበር። ራስል እውነትን መፈለግ በጀመረበት ጊዜ ከአባቱ ጋር የንግድ ሽርክና ጀምሮ ስለነበር ባለ ሚልዮን ዶላር ባለጠጋ ወደመሆን ተቃርቦ ነበር። እርሱ ግን በንግድ ድርጅቱ ውስጥ የነበረውን ድርሻ በሙሉ ሸጠና ሀብቱን በመላ ምድር ላይ የአምላክን መንግሥት ለማወጁ ሥራ ተጠቀመበት። ራስል በ1884 በአሁኑ ጊዜ የፔንስልቫንያ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማህበር በመባል የሚታወቀው ማህበር የመጀመሪያ ፕሬዚደንት ሆነ። በ1916 በምዕራባዊ ዩናይትድ ስቴትስ የመጨረሻውን አድካሚ የስብከት ጉዞ በሚያደርግበት ጊዜ ወደ ኒውዮርክ ለመሄድ ባቡር እንደተሳፈረ ፓምፓ ቴክሳስ አጠገብ ሞተ። መንፈሳዊ ሀብት በሰማይ በማከማቸት ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልን አልፎአል። በዚህ ዘመንም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ራሳቸውን መሥዋዕት የሚያደርጉ አቅኚ አገልጋዮች ይህንን ምሳሌ በመከተል ላይ ናቸው።—ዕብራውያን 13:7፤ ሉቃስ 12:33, 34፤ ከ1 ቆሮንቶስ 9:16ና ከ1 ቆሮንቶስ 11:1 ጋር አወዳድር።
መንፈሳዊ የዓይን ኩል መቀባት
13. (ሀ) መንፈሣዊ ኩል የሎዶቃውያንን ሁኔታ የሚያሻሽለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ እንዴት ያለ ልብስ እንዲገዙ መክሮአል? ለምንስ?
13 በተጨማሪም ኢየሱስ ለሎዶቃውያን የሚከተለውን ጥብቅ ምክር ሰጥቶአል። “ተጎናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፣ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኩል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።” (ራእይ 3:18ለ) ከከተማው ባለ መድኃኒተኞች ሳይሆን ከኢየሱስ ብቻ ሊገኝ የሚችለውን ፈዋሽ ኩል በመግዛት ለመንፈሳዊ እውርነታቸው ፈውስ መፈለግ ነበረባቸው። ይህም መንፈሳዊ ማስተዋልን እንዲያገኙና የጠራው ዓይናቸው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ ብቻ አተኩሮ ‘በጻድቃን መንገድ’ እንዲጓዙ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 4:18, 25-27) በሎዶቅያ ይሠራ የነበረውን ውድ ጥቁር ሱፍ ሳይሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመሆን ያገኙትን ታላቅ መብት የሚያሳውቅላቸውን “ነጭ መጎናጸፊያ” መልበስ ነበረባቸው።—ከ1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10ና ከ1 ጴጥሮስ 3:3-5 ጋር አወዳድር።
14. (ሀ) ከ1879 ጀምሮ ምን ዓይነት መንፈሳዊ ኩል ለሰዎች ሲቀርብ ቆይቶአል? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የገንዘብ ድጋፍ ሲያገኙ የቆዩት ከማን ነበር? (ሐ) በእርዳታ መዋጮ አጠቃቀም ረገድ የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች የሚለዩት እንዴት ነው?
14 በዘመናችን መንፈሳዊ ኩል ሊገኝ ይችላልን? አዎ፣ ሊገኝ ይችላል። በወዳጆቹ ፓስተር ራስል ተብሎ በፍቅር ይጠራ የነበረው ሰው በ1879 ለእውነት የሚከራከር መጽሔት ማሳተም ጀመረ። ይህ መጽሔት በአሁኑ ጊዜ የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ በሚል ስያሜ በመላው ምድር ላይ ይታወቃል። በዚህ መጽሔት ሁለተኛ እትም ላይ የሚከተለውን ጽፎ ነበር። “[የዚህ መጽሔት] ደጋፊ ይሖዋ ራሱ እንደሆነ እናምናለን። ይህ በመሆኑም ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም አይለምንም ወይም አይማጠንም። ‘የተራሮች ወርቅና ብር ሁሉ የእኔ ነው’ የሚለው አምላክ የሚያስፈልገንን ገንዘብ ማስገኘት ካቃተው ያን ጊዜ መጽሔቱን ማተም ማቆም እንደሚኖርብን እናውቃለን።” አንዳንድ የቴሌቪዥን ወንጌላውያን ብዙ ሀብት ከማከማቸታቸውም በላይ አሳፋሪ በሆነ የቅንጦት (አንዳንድ ጊዜም ከሥነ ምግባር ውጭ በሆነ) አኗኗር ይኖራሉ። (ራእይ 18:3) በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው የሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግን ሳይለምኑ የሚያገኙትን መዋጮ በሙሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለውን መጪውን የይሖዋ መንግሥት የመስበክ ሥራ ለማደራጀትና ለማስፋፋት ተጠቅመውበታል። የዮሐንስ ክፍል እስከ ዛሬ ድረስ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! የሚባሉትን መጽሔቶች ያሳትማል። እነዚህ ሁለት መጽሔቶች በ2006 በጋራ ከ59 ሚልዮን በላይ በሆነ ቁጥር ተሠራጭተው ነበር። መጠበቂያ ግንብ ከ150 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይታተማል። በዚህ መንፈሳዊ ኩል ተጠቅመው ለሐሰት ሃይማኖትና የመንግሥቱን ምሥራች ለአሕዛብ ሁሉ መስበክ አጣዳፊ ለመሆኑ ዓይናቸው የተከፈተላቸው ከስድስት ሚልዮን የሚበልጡ ክርስቲያኖች ጉባኤ ይፋዊ መጽሔት መጠበቂያ ግንብ ነው።—ማርቆስ 13:10
ከተግሣጽና ከወቀሳ መጠቀም
15. ኢየሱስ በሎዶቅያ ለነበሩት ክርስቲያኖች ጠንካራ ምክር የሰጠው ለምንድን ነው? ጉባኤውስ ምክሩን እንዴት መቀበል ነበረበት?
15 አሁን ወደ ሎዶቃውያን እንመለስ። ከኢየሱስ የተሰጣቸውን ኃይለኛ ምክር እንዴት ይቀበሉት ይሆን? ተስፋ ቆርጠው ኢየሱስ ጨርሶ ተከታዮቹ እንዲሆኑ እንደማይፈልግ ይሰማቸው ይሆንን? የለም፣ ሁኔታው እንዲህ አይደለም። መልእክቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል። “እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገስጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ።” (ራእይ 3:19) የኢየሱስ ተግሣጽ ይሖዋ እንደሚሰጠው ተግሣጽ የፍቅር መግለጫ ነው። (ዕብራውያን 12:4-7) የሎዶቅያ ጉባኤ ከፍቅራዊ አሳቢነቱ መጠቀምና ምክሩን በሥራ ላይ ማዋል ይኖርበታል። ለብ ያሉ መሆናቸው ኃጢአት እንደሆነባቸው በመገንዘብ ንስሐ መግባት ይገባቸዋል። (ዕብራውያን 3:12, 13፤ ያዕቆብ 4:17) ሽማግሌዎቹ የፍቅረ ንዋይ አካሄዳቸውን አስወግደው ከአምላክ የተቀበሉትን ሥጦታ ‘መልሰው ማቀጣጠል’ ይኖርባቸዋል። የጉባኤው አባሎች በሙሉ መንፈሳዊውን ኩል እየተኳሉ ቀዝቃዛ የምንጭ ውኃ እንደመጠጣት በሚመስለው እርካታ መደሰት ይኖርባቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 1:6፤ ምሳሌ 3:5-8፤ ሉቃስ 21:34
16. (ሀ) የኢየሱስ ፍቅርና እንክብካቤ በዛሬው ጊዜ የታየው እንዴት ነው? (ለ) ጠንከር ያለ ምክር ከተሰጠን እንዴት ልንቀበለው ይገባል?
16 በዚህ ዘመን የምንኖረው እኛስ? ኢየሱስ ‘በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉትን የራሱን ሰዎች’ ይወዳቸዋል። የሚወዳቸውም “እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ” ለሁልጊዜ ነው። (ዮሐንስ 13:1፤ ማቴዎስ 28:20) ፍቅሩና መውደዱ የሚገለጸው በዘመናዊው የዮሐንስ ክፍልና በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ባሉት ኮከቦች ወይም ሽማግሌዎች በኩል ነው። (ራእይ 1:20) በዚህ ፈታኝ በሆነ ወቅት ውስጥ ሽማግሌዎች ወጣቶችም ሆንን አረጋውያን፣ ሁላችንም የዓለምን የሥነ ምግባር አተላ፣ ቁሳዊ መስገብገብና የነፃነት ወይም በራስ የመመራት መንፈስ እየተቃወምን ከቲኦክራቲካዊው በረት ውስጥ ሳንወጣ እንድንኖር ሊረዱን በጣም ይፈልጋሉ። ጠንካራ ምክር ወይም ተግሣጽ መቀበል አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ቢኖር “የተግሣጽ ምክር የሕይወት መንገድ” መሆኑን አንርሳ። (ምሳሌ 6:23) ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን እንደመሆናችን መጠን እንደገና ለመስተካከልና በአምላክ ፍቅር ውስጥ ለመኖር እንድንችል አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ ንስሐ መግባት ይኖርብናል።—2 ቆሮንቶስ 13:11
17. ሀብት መንፈሣዊ ጉዳት ሊያደርስብን የሚችለው እንዴት ነው?
17 የሀብት ፍቅር ወይም ባለጠጋነት ወይም ድህነት ለብ ያልን ክርስቲያኖች እንዲያደርገን መፍቀድ አይገባንም። ሀብት አዲስ የአገልግሎት አጋጣሚ ሊከፍትልን ቢችልም አደገኛ ሊሆንብንም ይችላል። (ማቴዎስ 19:24) አንድ ሀብታም የሆነ ሰው በየጊዜው በዛ ያለ የገንዘብ እርዳታ ካደረገ የሌሎቹን ያህል በስብከቱ ሥራ ቀናተኛ መሆን እንደማያስፈልገው ሊሰማው ይችላል። አለዚያም ሀብታም በመሆኑ ምክንያት የተለየ ሞገስ ሊሰጠው እንደሚገባ ሊያስብ ይችላል። ከዚህም በላይ ባለጠጋ ሰው ሌሎች ሊያገኙአቸው የማይችሉ ብዙ የጊዜ ማሳለፊያዎችና መደሰቻዎች ይኖሩታል። እነዚህ የጊዜ ማሳለፊያዎችና መዝናኛዎች ግን ጊዜ የሚያባክኑ ከመሆናቸውም በላይ ዝንጉ የሆኑ ሰዎችን ከክርስቲያናዊ አገልግሎት ስለሚያርቁ ልባም ያልሆኑ ሰዎችን ለብ ያሉ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ያደርጉአቸዋል። እንደነዚህ ካሉት ወጥመዶች ሁሉ እየራቅንና የዘላለምን ሕይወት ተስፋ እያደረግን በሙሉ ልባችን እንጋደል፣ ጠንክረን እንሥራ።—1 ጢሞቴዎስ 4:8-10፤ 6:9-12
‘እራት መብላት’
18. ኢየሱስ ለሎዶቅያ ክርስቲያኖች ምን ተስፋ ሰጣቸው?
18 ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ:- “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ። ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፣ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።” (ራእይ 3:20) የሎዶቅያ ክርስቲያኖች ኢየሱስን ተቀብለው ወደ ጉባኤያቸው ቢያስገቡት ኖሮ ለብ የማለት ዝንባሌያቸውን እንዲያሸንፉ ይረዳቸው ነበር።—ማቴዎስ 18:20
19. ኢየሱስ በሎዶቅያ ከነበረው ጉባኤ ጋር እራት እበላለሁ ሲል ምን እንደሚያደርግ መናገሩ ነበር?
19 ኢየሱስ ስለ እራት መናገሩ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እራት የበላበትን ጊዜ ሎዶቃውያን እንዲያስታውሱ እንዳደረጋቸው አያጠራጥርም። (ዮሐንስ 12:1-8) ከኢየሱስ ጋር አብረው የበሉ ሰዎች ሁሉ መንፈሳዊ በረከት ያገኙ ነበር። ኢየሱስ ከሙታን ከተነሳ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በአንድ ገበታ ላይ የተቀመጠባቸው ጊዜያት ነበሩ። በእነዚህም ጊዜያት ከፍተኛ ማበረታቻ አግኝተው ነበር። (ሉቃስ 24:28-32፤ ዮሐንስ 21:9-19) ስለዚህ ወደ ሎዶቅያ ጉባኤ እንደሚመጣና ከእነርሱ ጋር እራት እንደሚበላ መናገሩ ተቀብለው ቢያስገቡት ብዙ መንፈሳዊ ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው ቃል መግባቱ ነበር።
20. (ሀ) በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ ሕዝበ ክርስትና ለብ ብላ ስለነበር ምን አደረገች? (ለ) ኢየሱስ በሕዝበ ክርስትና ላይ ያስተላለፈው ፍርድ ምን አደረሰባት?
20 ኢየሱስ ለሎዶቃውያን የሰጠው የፍቅር ምክር ዛሬ ላሉት ቅቡዓን ቀሪ ክርስቲያኖች ትልቅ ትርጉም አለው። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ የጌታ ቀን በጀመረበት ጊዜ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖተኞች በአስደንጋጭ ሁኔታ ለብ ብለው እንደነበረ ያስታውሳሉ። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ጌታችን በ1914 ሲመለስ እርሱን በደስታ ከመቀበል ይልቅ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ይፈጸም በነበረው የመተራረድ ዘመቻ ተውጠው ነበር። በዚህ ጦርነት ከተካፈሉት 28 አገሮች መካከል 24ቱ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ነበሩ። የተከመረባቸው የደም ዕዳ በጣም ታላቅ ነው። በአብዛኛው በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በተደረገው የሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጊዜም የሐሰት ሃይማኖት ‘ኃጢአት እስከ ሰማይ ደርሶ’ ነበር። (ራእይ 18:5) ከዚህም በላይ ቀሳውስቱ አንዳቸውም ቢሆኑ የሰው ልጆችን ችግሮች ሊፈቱ ያልቻሉትን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማህበርን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን፣ እንዲሁም ብሔራዊ አብዮታዊ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ለመጪው የይሖዋ መንግሥት ጀርባቸውን ሰጥተዋል። ኢየሱስ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቀሳውስቱን አንድ ዓሣ አጥማጅ መረቡ ውስጥ የገቡትን የማይፈለጉ ዓሣዎች እየመነጨቀ እንደሚጥል ሁሉ አውጥቶ ጥሎአቸዋል። በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ጉስቁልናና አሳዛኝ ሁኔታ ይህ የቅጣት ፍርድ የተበየነባት መሆኑን ያረጋግጣል። በመጨረሻ የሚደርስባት ዕጣ ለሁላችንም ማስጠንቀቂያ ሊሆነን ይገባል።—ማቴዎስ 13:47-50
21. ከ1919 ወዲህ በእውነተኛው ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ለሎዶቅያ ክርስቲያኖች የተናገረውን ቃል እንዴት ተቀብለዋል?
21 በእውነተኛው ጉባኤ ውስጥም ቢሆን ሞቅ እንደሚያደርግ ትኩስ መጠጥ ወይም ጥም እንደሚያረካ ቀዝቃዛ ውኃ ያልሆኑ ለብ ያሉ ግለሰቦች አሉ። ኢየሱስ ግን አሁንም ጉባኤውን በጣም ይወደዋል። በእንግድነት ለሚቀበሉት ክርስቲያኖች ሁሉ ራሱን ያቀርባል። ብዙዎችም ለእራት እንደጋበዙት ያህል በደስታ ተቀብለውታል። ይህንን በማድረጋቸውም ከ1919 ጀምሮ ዓይኖቻቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትርጉም ተከፍተዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታላቅ በሆነ መንፈሳዊ ብርሃን ውስጥ ይገኛሉ።—መዝሙር 97:11፤ 2 ጴጥሮስ 1:19
22. ኢየሱስ የትኛውን ወደ ፊት የሚደረገውን የእራት ግብዣ በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል? ከዚህስ እራት የሚካፈሉት እነማን ናቸው?
22 ኢየሱስ ለሎዶቃውያን ሲናገር አንድ ሌላ እራት በአእምሮው ሳይዝ አልቀረም። በሌላ የራእይ መጽሐፍ ክፍል “ወደ በጉ ሠርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን [“ደስተኞች፣” NW] ናቸው” የሚል እናነባለን። ይህ እራት ይሖዋ በሐሰት ሃይማኖት ላይ ፍርዱን ካስፈጸመ በኋላ ይሖዋን ለማወደስ የሚደረግ ታላቅ ድግስ ነው። በዚህም ድግስ የሚካፈሉት ክርስቶስና በሰማይ የሚጠቃለሉት 144, 000 የሙሽራይቱ ክፍሎች ናቸው። (ራእይ 19:1-9) የጥንትዋ የሎዶቅያ ጉባኤ ታዛዥ አባሎችና የዘመናችን የእውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ንጹሕ መጎናጸፊያ የለበሱ ታማኝ የክርስቶስ ወንድሞች በዚህ የእራት ድግስ ላይ ከሙሽራው ጋር ይጋበዛሉ። (ማቴዎስ 22:2-13) ይህም ቀናተኛ ለመሆንና ንስሐ ለመግባት የሚገፋፋ ጠንካራ ምክንያት ነው።
ለድል አድራጊዎች የተዘጋጀ ዙፋን
23, 24. (ሀ) ኢየሱስ ስለ ምን ተጨማሪ ሽልማት ተናገሮአል? (ለ) ኢየሱስ በመሲሐዊ ዙፋኑ ላይ የተቀመጠው መቼ ነበር? ክርስቲያን ነን ይሉ በነበሩ ሰዎች ላይ መፍረድ የጀመረውስ መቼ ነበር? (ሐ) ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ምን አስደናቂ የሆነ ተስፋ ሰጥቶ ነበር?
23 ኢየሱስ የሚከተለውን በመናገር ስለ ሌላ ተጨማሪ ሽልማት ገልጾአል:- “እኔ ደግሞ ድል እንደነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፣ ድል ለነሳው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።” (ራእይ 3:21) በመዝሙር 110:1, 2 ላይ በሚገኙት የዳዊት ቃላት መሠረት ፍጹም አቋሙን እስከ መጨረሻው ጠብቆ የጸናው ኢየሱስ ዓለምን ድል ነስቶ በ33 እዘአ ከሙታን ከተነሳ በኋላ ከአባቱ ጋር በሰማያዊ ዙፋን ላይ እንዲቀመጥ ከፍ ተደርጎአል። (ሥራ 2:32, 33) በሌላው ወሳኝ በሆነ ዓመት በ1914 ደግሞ ኢየሱስ ንጉሥና ፈራጅ ሆኖ በራሱ መሲሐዊ ዙፋን ላይ ተቀመጠ። ፍርዱ በክርስቲያን ነን ባዮች ሁሉ ላይ በ1918 እንደጀመረ ከዚህ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ከዚያ በፊት የሞቱ ቅቡዓን ድል አድራጊዎች ከሙታን ተነስተው ከኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ ተባብረዋል። (1 ጴጥሮስ 4:17) ይህን እንደሚያደርግላቸው ቃል የገባላቸው የሞቱን መታሰቢያ ባቋቋመበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን በመናገር ነበር። “አባቴ እኔን እንደሾመኝ እኔ ደግሞ በመንግሥቴ ከማዕዴ ትበሉና ትጠጡ ዘንድ፣ በአሥራ ሁለቱም በእሥራኤል ነገድ ስትፈርዱ በዙፋኖች ትቀመጡ ዘንድ ለመንግሥት እሾማችኋለሁ።”—ሉቃስ 22:28-30
24 ‘በዳግም ፍጥረት’ ጊዜ ከነገሠው ንጉሥ ጋር ተቀምጦ ፍጹም በሆነው ቤዛ አማካኝነት ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆችን ወደ ኤደናዊ ፍጽምና በመመለሱ ሥራ መካፈል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! (ማቴዎስ 19:28፤ 20:28) ዮሐንስ እንደሚነግረን ኢየሱስ ድል ነስተው ‘ለአምላኩና ለአባቱ መንግሥትና ካህናት’ የሚሆኑትን ሁሉ ታላቅ ግርማ ባለው የይሖዋ ሰማያዊ ዙፋን ዙሪያ በዙፋን ላይ እንዲቀመጡ ያደርጋል። (ራእይ 1:6፤ 4:4) ሁላችንም ከቅቡዓን ክፍልም ሆንን ምድርን ወደ ገነትነት በመመለሱ ሥራ የሚካፈለው የአዲስ ምድር ማህበረሰብ አባሎች፣ ኢየሱስ ለሎዶቃውያን የተናገረውን ቃል ልብ እንበል።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ሥራ 3:19-21
25. (ሀ) ኢየሱስ እንደቀደሙት መልእክቶቹ ለሎዶቅያ የላከውንም መልእክት የደመደመው ምን በመናገር ነበር? (ለ) ዛሬም ግለሰብ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ለሎዶቅያ ጉባኤ የተናገረውን ቃል እንዴት መቀበል ይኖርባቸዋል?
25 ኢየሱስ በቀደሙት መልእክቶቹ እንዳደረገው ይህንንም መልእክቱን የሚደመድመው የማበረታቻና የምክር ቃል በመናገር ነው። “መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።” (ራእይ 3:22) የምንኖረው የመጨረሻው ዘመን ሊፈጸም በተቃረበበት ጊዜ ነው። ሕዝበ ክርስትና በፍቅር ረገድ ጨርሶ የቀዘቀዘች መሆንዋን የሚያሳይ ብዙ ማስረጃ በዙሪያችን አለ። እኛ ግን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደ መሆናችን መጠን ኢየሱስ በሎዶቅያ ለነበረው ጉባኤ የላከውን መልእክት፣ ጌታችን ለጉባኤዎች ሁሉ የላከውን ሰባት መልእክቶች ሞቅ ባለ ስሜት እንቀበል። ይህንንም የምናደርገው ኢየሱስ ስለዘመናችን የተናገረውን ታላቅ ትንቢት በማስፈጸሙ ሥራ በሙሉ ልባችንና ጉልበታችን ስንካፈል ነው። ትንቢቱም እንዲህ ይላል፣ “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:12-14
26. ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ዮሐንስን በቀጥታ ያነጋገረው መቼ ነው? ይሁን እንጂ በምን ነገር ተካፍሎአል?
26 ኢየሱስ ለሰባቱ ጉባኤዎች የላከው ምክር እዚህ ላይ ይፈጸማል። ከዚህ በኋላ ወደ ራእይ መጽሐፍ የመጨረሻ ምዕራፍ እስኪደርስ ድረስ ኢየሱስ ከዮሐንስ ጋር አልተነጋገረም። ቢሆንም በብዙዎቹ ራእዮች፣ ለምሳሌ ያህል የይሖዋን ፍርድ በሚያስፈጽምበት ጊዜ ታይቶአል። አሁን ከዮሐንስ ክፍል ጋር ሆነን በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጸውን ሁለተኛ አስደናቂ ራእይ እንመርምር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እነዚህ ቦታዎች ሎዶቅያ በነበረችበት ሥፍራ በተደረጉ የመሬት ቁፋሮ ጥናቶች ተገኝተዋል።
[በገጽ 73 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፍቅረ ንዋይና ጥበብ
በ1956 አንድ የጋዜጣ አዘጋጅ የሚከተለውን ጽፎ ነበር:- “ከአንድ መቶ ዓመት በፊት አንድ ተራ ሰው 72 ፍላጎቶች ሲኖሩት ከእነዚህ መካከል 16ቱ የግዴታ የሚያስፈልጉት ነገሮች እንደነበሩ ይገመት ነበር። ዛሬ ግን አንድ ተራ ሰው 474 ነገሮችን ሲፈልግ ግዴታ ያስፈልጉታል ተብለው የሚገመቱት ነገሮች ብዛት 94 ደርሶአል። ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት አንድ ተራ ሰው 200 ዓይነት ሸቀጦችን እንዲገዛ ይጠየቅ ነበር። ዛሬ ግን 32,000 የሚያክሉ የተለያዩ ሸቀጦች ለሽያጭ ይቀርባሉ። የሰው ልጅ ለመኖር የሚያስፈልጉት ነገሮች ጥቂቶች ሲሆኑ የሚፈልጋቸው ነገሮች ግን ቁጥር ሥፍር የላቸውም።” በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች በሕይወት ውስጥ ትልቁ ነገር ቁሳዊ ሀብትና ንብረት ማከማቸት እንደሆነ እንዲያምኑ በመገደድ ላይ ናቸው። በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች የመክብብ 7:12ን [NW] ጥበብ የተሞላበት ምክር ዘንግተዋል። “ጥበብ እንደ ገንዘብ ሰውን ይጠብቃል። የዕውቀት ብልጫ ግን ጥበብ ባለቤቱን በሕይወት ለማኖር መቻሉ ነው።”
[በገጽ 67 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወደ ሎዶቅያ ይመጣ የነበረው ውኃ ለብ ያለ የማይስማማ ውኃ ነበር። በሎዶቅያ የነበሩ ክርስቲያኖች የማያረካ ለብ ያለ መንፈስ ነበራቸው