3 ልጄ ሆይ፣ ትምህርቴን አትርሳ፤
ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ፤
2 ረጅም ዕድሜና የሕይወት ዘመን
እንዲሁም ሰላም ያስገኙልሃልና።+
3 ታማኝ ፍቅርና ታማኝነት አይለዩህ።+
በአንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤
በልብህ ጽላት ላይ ጻፋቸው፤+
4 ያን ጊዜ በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ ታገኛለህ፤+
እንዲሁም ጥሩ ማስተዋል እንዳለህ ታስመሠክራለህ።
5 በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤+
ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ።+
6 በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤+
እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።+
7 በራስህ አመለካከት ጥበበኛ አትሁን።+
ይሖዋን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ።
8 ለሰውነትህ ፈውስ፣
ለአጥንትህም ብርታት ይሆንልሃል።
9 ባሉህ ውድ ነገሮች፣+
ከምርትህ ሁሉ በኩራት ይሖዋን አክብር፤+
10 ይህን ካደረግክ ጎተራዎችህ ጢም ብለው ይሞላሉ፤+
በወይን መጭመቂያዎችህም አዲስ የወይን ጠጅ ሞልቶ ይፈስሳል።
11 ልጄ ሆይ፣ የይሖዋን ተግሣጽ ለመቀበል እንቢተኛ አትሁን፤+
ወቀሳውም አያስመርርህ፤+
12 አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚወቅስ ሁሉ
ይሖዋም የሚወዳቸውን ይወቅሳልና።+
13 ጥበብን የሚያገኝ፣+
ጥልቅ ግንዛቤንም የራሱ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው፤
14 ጥበብን ማግኘት ብርን ከማግኘት የተሻለ ነው፤
እሷንም ማትረፍ ወርቅ ከማግኘት የተሻለ ነው።+
15 ከዛጎል ይበልጥ ውድ ናት፤
አንተ የምትመኘው ማንኛውም ነገር ሊተካከላት አይችልም።
16 በቀኟ ረጅም ዕድሜ አለ፤
በግራዋም ሀብትና ክብር ይገኛል።
17 መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤
ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም የሰፈነበት ነው።+
18 ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፤
አጥብቀው የሚይዟትም ደስተኞች ይባላሉ።+
19 ይሖዋ በጥበብ ምድርን መሠረተ።+
በማስተዋል ሰማያትን አጸና።+
20 በእውቀቱ ጥልቅ ውኃዎች ተከፈሉ፤
ደመና ያዘሉ ሰማያትም ጠል አንጠባጠቡ።+
21 ልጄ ሆይ፣ እነዚህ ባሕርያት ከእይታህ አይራቁ።
ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን ጠብቅ፤
22 ሕይወት ያስገኙልሃል፤
ለአንገትህም ጌጥ ይሆናሉ፤
23 በዚያን ጊዜ በመንገድህ ላይ ተማምነህ ትሄዳለህ፤
እግርህም ፈጽሞ አይሰናከልም።+
24 በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤+
ትተኛለህ፤ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል።+
25 ድንገት የሚከሰት የሚያሸብር ነገርም+ ሆነ
በክፉ ሰዎች ላይ የሚመጣ መዓት አያስፈራህም።+
26 ይሖዋ መታመኛህ ይሆናልና፤+
እግርህን በወጥመድ እንዳይያዝ ይጠብቃል።+
27 ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ+
ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።+
28 ለባልንጀራህ አሁኑኑ መስጠት እየቻልክ
“ሂድና በኋላ ተመልሰህ ና! ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው።
29 ከአንተ ጋር ተማምኖ እየኖረ ሳለ
ባልንጀራህን ለመጉዳት አታሲር።+
30 መጥፎ ነገር ካላደረገብህ
ከሰው ጋር ያለምክንያት አትጣላ።+
31 በዓመፀኛ ሰው አትቅና፤+
የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፤
32 ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋልና፤+
ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።+
33 ይሖዋ የክፉውን ቤት ይረግማል፤+
የጻድቁን መኖሪያ ግን ይባርካል።+
34 በፌዘኞች ላይ ይሳለቃል፤+
ለየዋሆች ግን ሞገስ ያሳያል።+
35 ጥበበኞች ክብርን ይወርሳሉ፤
ሞኞች ግን ለውርደት የሚዳርግን ነገር ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።+