ምዕራፍ 17
የክርስቶስ መመለስ ሊታይ የሚችለው እንዴት ነው?
1. (ሀ) ክርስቶስ ምን ብሎ ቃል ገብቷል? (ለ) የክርስቶስ መመለስ ለምን አስፈላጊ ነው?
“እንደገና እመጣለሁ።” (ዮሐንስ 14:3 አዓት) ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱ ዋዜማ በነበረችው ምሽት ላይ ለሐዋርያቱ ይህን ቃል ገባላቸው። ክርስቶስ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ይዞ ሲመለስ የሚያመጣው ሰላም፣ ጤንነትና ሕይወት እንደ አሁኑ ጊዜ ያህል አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም ቢባል ትስማማ ይሆናል። ይሁን እንጂ ክርስቶስ የሚመለሰው እንዴት ነው? የሚያዩት እነማን ናቸው? በምንስ መንገድ?
2. (ሀ) ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ቅቡዓን ተከታዮቹን፣ ሐዋርያቱን ጭምር፣ የት እንዲኖሩ ይወስዳቸዋል? (ለ) እዚያስ ምን ዓይነት አካል ይኖራቸዋል?
2 ክርስቶስ ሲመለስ በምድር ላይ ለመኖር አይመጣም። ከዚያ ይልቅ ከእርሱ ጋር ነገሥታት ሆነው የሚገዙት አብረውት ለመሆን ወደ ሰማይ ይወሰዳሉ። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ:- “እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ [እንደገና (አዓት)] እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 14:3) ስለዚህ ክርስቶስ ሲመለስ ወደ ሰማይ የሚወሰዱት ሰዎች መንፈሳዊ አካሎች ይሆናሉ፤ ክርስቶስንም በክብራማው መንፈሳዊ አካሉ ያዩታል። (1 ቆሮንቶስ 15:44) ሆኖም ወደ ሰማይ የማይሄደው የቀረው የሰው ዘር ክርስቶስ ሲመለስ ያየዋልን?
ሰው ሆኖ ሊመለስ የማይችልበት ምክንያት
3. ሰዎች ክርስቶስን እንደገና በፍጹም እንደማያዩት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ያሳያል?
3 በዚያችው ምሽት ኢየሱስ ለሐዋርያቱ:- “ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚያም በኋላ ዓለም አያየኝም” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:19) “ዓለም” የሚለው ቃል የሰውን ዘር ያመለክታል። ስለዚህም ኢየሱስ እዚህ ላይ ከዕርገቱ በኋላ በምድር ላይ ያሉት ሰዎች እንደማያዩት በግልጽ ተናግሯል። ሐዋርያው ጳውሎስ:- “ክርስቶስንም በሥጋ እንደሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፣ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም” ብሎ ጽፎአል። — 2 ቆሮንቶስ 5:16
4. ክርስቶስ በዓይን የማይታይ ኃያል መንፈሳዊ አካል ሆኖ እንደሚመለስ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
4 ሆኖም ብዙ ሰዎች፣ ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ሲገደል የነበረውን ሰብዓዊ አካል ለብሶ ይመለሳል፤ እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖሩት ሁሉ ያዩታል ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ክብር ለብሶ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር እንደሚመለስና “በክብሩ ዙፋን” ላይ እንደሚቀመጥ ይናገራል። (ማቴዎስ 25:31) ኢየሱስ ሰው ሆኖ ቢመጣና በምድራዊ ዙፋን ላይ ቢቀመጥ በደረጃው ከመላእክት ዝቅ ይል ነበር። ነገር ግን እርሱ ከእነዚህ የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሁሉ በኃይልና በክብር የላቀ ሆኖ ስለሚመጣ ልክ እንደ እነርሱ በዓይን የማይታይ ይሆናል። — ፊልጵስዩስ 2:8-11
5. ክርስቶስ ሰብዓዊ አካል ለብሶ ሊመለስ የማይችለው ለምንድን ነው?
5 በሌላው በኩል ግን ከ1, 900 ዓመታት በፊት ኢየሱስ ራሱን ዝቅ ማድረግና ሰው መሆን አስፈልጎት ነበር። ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ለእኛ ቤዛ አድርጎ መስጠት አስፈልጎት ነበር። ኢየሱስ አንድ ጊዜ “እኔም ስለ ዓለም ሕይወት የምሰጠው እንጀራ ሥጋዬ ነው” በማለት ሁኔታውን ገልጾታል። (ዮሐንስ 6:51) ኢየሱስ ሥጋዊ አካሉን በዚህ መንገድ ለሰው ዘር መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ። ይህ መሥዋዕት ለምን ያህል ጊዜ እንደተሰጠ መቆየት ነበረበት? ሐዋርያው ጳውሎስ መልሱን ይነግረናል:- “የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ [ለሁልጊዜው (አዓት) ] በማቅረብ ተቀድሰናል።” (ዕብራውያን 10:10) ክርስቶስ ሥጋውን ለዓለም ሕይወት ከሰጠ በኋላ መልሶ ሊወስደውና እንደገና ሰው ሊሆን አይችልም። በዚህ መሠረታዊ ምክንያት የተነሣ አንድ ጊዜ ለሁልጊዜ የሠዋውን ሰብዓዊ አካሉን ይዞ ለመመለስ ፈጽሞ አይችልም።
ሥጋዊ አካሉ ወደ ሰማይ አልተወሰደም
6. ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ሥጋዊ አካሉን ይዞ ወደ ሰማይ ሄዷል ብለው የሚያምኑት ለምንድን ነው?
6 ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ሥጋዊ አካሉን ወደ ሰማይ ይዞት ሄዷል ብለው ያምናሉ። ክርስቶስ ከሞት በተነሣበት ጊዜ ሥጋዊ አካሉ በመቃብር ውስጥ አለመገኘቱን እንደ ማስረጃ አድርገው ይጠቅሳሉ። (ማርቆስ 16:5-7) በተጨማሪም ኢየሱስ ከሞቱ በኋላ ሕያው መሆኑን ለማሳየት ለደቀመዛሙርቱ በሥጋዊ አካል ታይቷቸዋል። እንዲያውም አንድ ጊዜ ሐዋርያው ቶማስ በእርግጥ ከሞት መነሣቱን እንዲያምን ሲል ኢየሱስ በጎኑ ላይ ባለው ቀዳዳ እጁን እንዲያስገባ አድርጎታል። (ዮሐንስ 20:24-27) ታዲያ ክርስቶስ ሲሞት ለብሶት የነበረውን አካል ይዞ ከሞት እንደተነሣ ይህ አያረጋግጥምን?
7. ክርስቶስ መንፈሳዊ አካል ሆኖ ወደ ሰማይ እንደሄደ የሚያረጋግጠው ምንድን ነው?
7 የለም፤ አያረጋግጥም። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንዲህ ይላል:- “ክርስቶስ . . . አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአል። በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ ።” (1 ጴጥሮስ 3:18) ሥጋና ደም ያለው አካል የለበሱ ሰዎች በሰማይ ሊኖሩ አይችሉም። ለሰማያዊ ሕይወት ትንሣኤ ስለማግኘት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፥ መንፈሳዊ አካል ይነሣል። . . . ሥጋና ደም የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርሱ አይችሉም።” (1 ቆሮንቶስ 15:44-50) በሰማይ ሊኖሩ የሚችሉት መንፈሳዊ አካል ያላቸው መንፈሳውያን ፍጡሮች ብቻ ናቸው።
8. የክርስቶስ ሰብዓዊ አካል ምን ሆነ?
8 ታዲያ የኢየሱስ ሥጋዊ አካል ምን ሆነ? ደቀመዛሙርቱ መቃብሩን ባዶ አግኝተውት የለምን? አዎን አግኝተውታል፥ ምክንያቱም አምላክ የኢየሱስን አካል ከቦታው አስወግዶት ነበር። አምላክ ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? እንደዚያ በማድረጉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ የነበረውን ትንቢት ፈጽሞታል። (መዝሙር 16:10፤ ሥራ 2:31) በዚህም ምክንያት ይሖዋ ቀደም ብሎ በሙሴ ሥጋ ላይ እንዳደረገው ሁሉ የኢየሱስንም ሥጋ ማስወገዱን ተገቢ ሆኖ አግኝቶታል። (ዘዳግም 34:5, 6) በተጨማሪም የኢየሱስ ደቀመዛሙርት በዚያን ጊዜ መንፈሳዊ ነገሮችን ገና ሙሉ በሙሉ ስላልተረዱ ሥጋው በመቃብር ውስጥ ቢቀር ኖሮ ከሞት መነሣቱ ሊገባቸው አይችልም ነበር።
9. ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ወደ ሥጋ ተለውጦ በለበሰው አካል ቀዳዳ ውስጥ ቶማስ እጁን ለማስገባት የቻለው እንዴት ነው?
9 ሆኖም ሐዋርያው ቶማስ እጁን በክርስቶስ ጎን ላይ ባለው ቀዳዳ ውስጥ ለመክተት ከቻለ ይህ ኢየሱስ በመሰቀያው እንጨት ላይ የተቸነከረውን አካል ይዞ ከሞት እንደተነሣ አያሳይምን? የለም አያሳይም፤ ኢየሱስ በድሮ ጊዜ መላእክት እንደሚያደርጉት ለጊዜው ወደ ሥጋዊ አካልነት ተለውጦ ስለነበር ነው። እርሱ ማን እንደሆነ ቶማስን ለማሳመን ቀዳዳ ያለበት አካል ለበሰ። ልክ አንድ ጊዜ አብርሃም እንዳስተናገዳቸው መላእክት እርሱም ሊበላና ሊጠጣ የሚችል ሙሉ በሙሉ ሰው የሆነ መስሎ ታያቸው። — ዘፍጥረት 18:8፤ ዕብራውያን 13:2
10. ኢየሱስ የተለያዩ ሥጋዊ አካሎችን ይለብስ እንደነበር የሚያሳየው ምንድን ነው?
10 ኢየሱስ ለቶማስ ሲሞት የነበረውን የሚመስል አካል ለብሶ ቢታየውም ለተከታዮቹ በሚታይበት ጊዜ የተለያዩ ዓይነት አካሎችን ይለብስ ነበር። በመሆኑም መግደላዊት ማርያም በመጀመሪያ ኢየሱስን አንድ አትክልተኛ ነው ብላ አስባ ነበር። በሌሎች ጊዜያትም ደቀመዛመርቱ ሲያዩት ወዲያውኑ አላወቁትም ነበር። በእነዚህ ጊዜያት እርሱን ለማወቅ ያስቻላቸው አካላዊ መልኩ ሳይሆን እነርሱ ሊገነዘቡት የሚችሉት አንድ ዓይነት ቃል ወይም ድርጊት ነበር። — ዮሐንስ 20:14-16፤ 21:6, 7፤ ሉቃስ 24:30, 31
11, 12. (ሀ) ክርስቶስ ምድርን ትቶ የሄደው በምን ሁኔታ ነበር? (ለ) ስለዚህ ክርስቶስ ይመለሳል ብለን መጠበቅ የሚኖርብን በምን ሁኔታ ነው?
11 ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለ40 ቀናት ያህል ሥጋዊ አካል በመልበስ ለደቀ መዛሙርቱ ይገለጥላቸው ነበር። (ሥራ 1:3) ከዚያም ወደ ሰማይ ሄደ። ይሁን እንጂ አንድ ሰው:- ‘በዚያን ጊዜ የታዩት ሁለቱ መላእክት “ወደ ሰማይ ሲሄድ ባያችሁበት በዚያው ሁኔታ ይመጣል” ብለው ለሐዋርያቱ ነግረዋቸው አልነበረምን?’ ብሎ ይጠይቅ ይሆናል። (ሥራ 1:11 አዓት) አዎን እንደዚያ ብለዋቸዋል። ሆኖም “ባያችሁበት በዚያው ሁኔታ ” አሏቸው እንጂ ይህንኑ አካል ይዞ ይመጣል እንዳላሏቸው ልብ በል። ታዲያ ኢየሱስ ሲሄድ የነበረው ሁኔታ ምን ነበር? በይፋ ለሕዝብ እየታየ ሳይሆን ፀጥ ባለ ሁኔታ ነበር። ስለዚህ ነገር የሚያውቁት ሐዋርያቱ ብቻ ነበሩ። ዓለም አያውቅም ነበር።
12 ኢየሱስ ሐዋርያቱን ትቶ ወደ ሰማይ ሲሄድ የነበረውን ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት አድርጎ እንደሚገልጸው እስቲ ተመልከት:- “ይህንንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” (ሥራ 1:9) ስለዚህ ኢየሱስ ወደ ሰማይ መሄድ ሲጀምር ደመና ከሐዋርያቱ ሥጋዊ ዓይኖች ሰወረው። ይህም በመሆኑ ወደ ሰማይ እየሄደ ያለው ኢየሱስ ለእነርሱ የማይታይ ሆነ። ተሰወረባቸው። ከዚያም መንፈሳዊ አካሉን ለብሶ ወደ ሰማይ ዐረገ። (1 ጴጥሮስ 3:18) እንግዲያው መመለስ ያለበት መንፈሣዊ አካል ለብሶ ለዓይን በማይታይ ሁኔታ ነው።
ዓይኖች ሁሉ የሚያዩት እንዴት ነው?
13. ክርስቶስ ከደመና ጋር ሲመጣ “ዓይኖች ሁሉ ያዩታል” የሚለውን አባባል መረዳት ያለብን እንዴት ነው?
13 ታዲያ በራዕይ 1:7 ላይ የሚገኙትን ቃላት እንዴት አድርገን መረዳት አለብን? በዚያ ላይ ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ጽፎአል:- “እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድር ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ።” እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው በሥጋዊ ዓይኖች ስለማየት ሳይሆን ስለ ማስተዋል ወይም ስለ መረዳት ነው። አንድ ሰው አንድን ነገር ሲገነዘብ ወይም ሲረዳ ‘አሁን ታየኝ’ ሊል ይችላል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የልባችሁ ዓይኖች” ወይም እንደ አዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “የማስተዋል ዓይኖች” በማለት ይናገራል። (ኤፌሶን 1:18) በዚህ ምክንያት “ዓይኖች ሁሉ . . . ያዩታል” የሚለው አነጋገር በዚያን ጊዜ ሁሉም ሰው ክርስቶስ እንደመጣ ይረዳል ወይም ያውቃል ማለት ነው።
14. (ሀ) “የወጉትም” የተባሉት እነማን ናቸው? (ለ) ሁሉም ሰው በመጨረሻ የኢየሱስን መገኘት በሚያውቅበት ጊዜ ታላቅ ወዮታ የሚሆነው ለምንድን ነው?
14 ኢየሱስን “የወጉት” ሰዎች አሁን በምድር ላይ በሕይወት የሉም። ስለዚህም እነርሱ የእነዚያን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ሰዎች አድራጎት በመከተል ዛሬ ባሉት የኢየሱስ ተከታዮች ላይ ጉዳት የሚያደርሱትን ሰዎች ያመለክታሉ። (ማቴዎስ 25:40, 45) ክርስቶስ እንደነዚህ ያሉትን ክፉዎች የሚያጠፋበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል። ስለዚህ ነገር በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ይህ ጥፋት ሲመጣባቸው ምን እየተፈጸመ እንዳለ ‘ያያሉ’ ወይም ይገነዘባሉ። ዋይታቸውም በእርግጥ ታላቅ ይሆናል!
ክርስቶስ ወደ ምድር ተመልሶ ይመጣልን?
15. “መመለስ” የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ በምን መንገድ ይሠራበታል?
15 መመለስ ሲባል ሁልጊዜ በአካል ወደ አንድ ቦታ መንቀሳቀስን አያመለክትም። ለምሳሌ የታመሙ ሰዎች ‘ጤንነታቸው ተመለሰላቸው’ ይባላል። በተጨማሪም በፊት የአንድ አገር መሪ የነበረ ሰው ወደ ሥልጣኑ ተመለሰ ተብሎ ይነገራል። በተመሳሳይም መንገድ አምላክ ለአብርሃም “የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች” ብሎ ነግሮት ነበር። (ዘፍጥረት 18:14፤ 21:1) እዚህ ላይ የይሖዋ መመለስ ቃል በቃል ይመለሳል ማለት ሳይሆን ቃል የገባውን ነገር ለመፈጸም ትኩረቱን ወደ ሣራ ያዞራል ማለት ነበር።
16. (ሀ) ክርስቶስ ወደ ምድር የሚመለሰው በምን መንገድ ነው? (ለ) ክርስቶስ መቼ ተመለሰ? በዚያን ጊዜስ ምን ሆነ?
16 በተመሳሳይም የክርስቶስ መመለስ ቃል በቃል ወደዚች ምድር ተመልሶ ይመጣል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ምድር ላይ መንግሥታዊ ሥልጣን ይቀበልና ትኩረቱን ወደ እርስዋ ያዞራል ማለት ነው። ይህንን ለማድረግ የግድ ሰማያዊ ዙፋኑን መተውና ወደ ምድር መምጣት አያስፈልገውም። ባለፈው ምዕራፍ ላይ እንዳየነው በ1914 እዘአ ላይ ክርስቶስ ተመልሶ መግዛት እንዲጀምር አምላክ የወሰነው ጊዜ እንደደረሰ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ያሳያል። በሰማይ ላይ:- “አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ” የሚል ድምፅ የተሰማው በዚያን ጊዜ ነበር። — ራዕይ 12:10
17. የክርስቶስ መመለስ በዓይን የማይታይ ስለሆነ መመለሱን ለማወቅ እንድንችል ምን ነገር ሰጥቶናል?
17 የክርስቶስ መመለስ በዓይን የማይታይ ስለሆነ ይህ በእርግጥ ስለመፈፀሙ ማረጋገጥ የሚቻልበት መንገድ ይኖራልን? አዎን አለ። ክርስቶስ ራሱ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱንና የዓለም መጨረሻ መቅረቡን ልናውቅ የምንችልበትን የሚታይ “ምልክት” ሰጥቶናል። እስቲ ይህንን “ምልክት” እንመርምረው።
[በገጽ 142 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ አካሉን መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ያንን አካል መልሶ በመውሰድ እንደገና ሰው ለመሆን አይችልም።
[በገጽ 144, 145 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢየሱስ ከሞት ከተነሣ በኋላ መግደላዊት ማርያም አትክልተኛው ይሆናል ብላ የተሳሳተችው ለምንድን ነው?
ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ቶማስን እጁን ወደ የትኛው ሥጋዊ አካል እንዲያስገባ ጠየቀው?
[በገጽ 147 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ የሚመለሰው ምድርን ለቆ በሄደበት በዚያው ሁኔታ ነው። ታዲያ ምድርን ለቆ የሄደው በምን ሁኔታ ነበር?