አምላክ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተህ እርምጃ ትወስዳለህን?
ብዙ ጊዜ ሰዎች የሚሰጣቸውን ሕይወት አድን ማስጠንቀቂያ ችላ ይላሉ። አብዛኞቹ የፖምፔ ከተማ ነዋሪዎች ከቬሱቪየስ ተራራ ይሰማ የነበረውን ኃይለኛ የጉርምርምታ ድምፅ ችላ ለማለት መርጠው ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ አብዛኞቹ ሰዎች ስለመጪው ምድር አቀፍ እልቂት የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ችላ ይላሉ። ይሁን እንጂ ከሐቁ ለመሸሽ ለማይፈልጉ ሁሉ ማስጠንቀቂያው በመጀመሪያው መቶ ዘመን በቬሱቪየስ ተራራ ታይቶ የነበረውን መብረቅና የእሳት ወላፈን ያህል እርግጠኛ ነገር ነው። ሁለት የዓለም ጦርነቶች፣ በመቶ የሚቆጠሩ ወታደራዊ ግጭቶች፣ ረሐብ፣ ታላላቅ የምድር መናወጦች፣ ቸነፈሮች፣ የወንጀልና የዓመፅ መስፋፋት፣ በመላው ዓለም የሚከናወነው የስብከት ዘመቻ፣ እነዚህ ሁሉ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ታላቅ ወደሆነ እልቂት በአፋጣኝ በመገስገስ ላይ እንደሚገኝ የሚያሳዩ ማስጠንቀቂያዎች ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን አሳሳቢ ትንቢት ይናገራል:- “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:21) በፖምፔ ደርሶ ከነበረው ዕልቂት የተረፉ ሰዎች እንደነበሩ ሁሉ “ከሕዝብ፣ ከነገድና ከቋንቋ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎችም” ከታላቁ መከራ ይተርፋሉ ወይም ይወጣሉ። — ራእይ 7:9, 14
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ‘ይህ ጥፋት የሚመጣው መቼ ነው?’ የሚለው ነው። መከራው በጣም የቀረበ መሆኑን እንድናምን የሚያስገድደን በቂ ምክንያት አለ። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጥፋቱ የሚመጣበትን ጊዜ ለማወቅ ፈልገው ኢየሱስን “የመገኘትህና የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ምልክት ምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀውታል። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ኢየሱስ የሰጠውን መልስ ልብ በሉ።
ከዋነኞቹ የጥምሩ ምልክት ክፍሎች አንዱ የሆነው ጦርነት
ኢየሱስ አንድ ልዩ ሁኔታ ብቻ ይመጣል ብሎ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ሁሉም በአንድነት ሆነው ይህ የነገሮች ሥርዓት ሊፈጸም የተቃረበ መሆኑን የሚያስጠነቅቁ በአንድ ጥምር ምልክት ውስጥ የተካተቱ ሁኔታዎች በተከታታይ እንደሚፈጸሙ ተናገረ። ይመጣል ተብሎ የተነገረለት የመጀመሪያው ሁኔታ በማቴዎስ 24:7 ላይ ተገልጾአል:- “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል።” ከዚህ ጋር ተመሳሳይነት ባለው በራእይ 6:4 ላይ በሚገኝ ትንቢት ላይ ‘ሰላም ከምድር ላይ እንደሚወሰድ’ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮአል። በታላቅነቱ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዓይነት ጦርነት ይመጣል ማለት ነው።
ይህ ስለምድር አቀፍ ጦርነት የተነገረው ትንቢት ከማይረሳው ዓመት ማለትም ከ1914 ጀምሮ በመፈጸም ላይ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል። አሜሪካን አድቬንቸርስ የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ከ1914 በፊት ስለነበሩት ዓመታት እንዲህ ይላል:- “ብዙ አሜሪካውያን ወደ አዲሱ ዓመት የገቡት ከሙሉ ተስፋ ጋር ነበር። የሃያኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አሥር ዓመታት እስኪያልቁ ድረስ የነበረው ዘመን ‘በጣም ጥሩ ዘመን’ እየተባለ ይጠራ ነበር። . . . ሐምሌ 28, 1914 ላይ ግን ይህ ሁሉ ተስፋ በአንድ ቃል ማለትም ጦርነት የሚለው ቃል ተናጋ።” አንደኛው የዓለም ጦርነት በዚህ ሁኔታ ጀምሮ ከ1914 እስከ 1918 ቆየ። ይህ ጦርነት በአንዳንዶች “ጦርነቶችን ሁሉ የሚያቆም ጦርነት” ተብሎ ተጠርቶ ነበር። ሃያ ስምንት አገሮች በዚህ ጦርነት በቀጥታ ተካፍለዋል። በእነዚህ አገሮች ሥር ይተዳደሩ የነበሩትን አገሮች ከቆጠርን ደግሞ በዚያን ጊዜ በመላው ምድር ይኖሩ ከነበሩት ሕዝቦች መካከል 90 በመቶ የሚያክሉት በጦርነቱ ተካፍለዋል።
በተጨማሪም አንደኛው የዓለም ጦርነት እንደ አውቶማቲክ ጠመንጃ፣ የመርዝ ጋዝ፣ የእሳት ነበልባል ወርዋሪዎች፣ ታንኮች፣ አውሮፕላኖች፣ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ያሉትንና የመሳሰሉትን አዳዲስና ይበልጥ አውዳሚ የሆኑ የጦር መሣሪያዎች ሥራ ላይ የዋለባቸው ጦርነት ነበር። አሥር ሚልዮን የሚያክሉ ወታደሮች ተገድለዋል። ይህም ከዚያ በፊት በነበሩት 100 ዓመታት በተደረጉ ዋና ዋና ጦርነቶች ከተገደሉት ወታደሮች ድምር ይበልጣል። 21 ሚልዮን የሚያክሉ ወታደሮች ቆስለዋል። በእርግጥም 1914 “የመጨረሻው ቀን” መጀመሪያ መሆኑን የሚያረጋግጥ ምድር አቀፍ ጦርነት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ይሁን እንጂ ጦርነት ኢየሱስ ከተናገረው ምልክት አንዱ ክፍል ብቻ ነው።
ሌሎች የምልክቱ ክፍሎች
ኢየሱስ በመቀጠል “በልዩ ልዩ ስፍራ ረሀብና የምድር መናወጥ ይሆናል። ይህም ሁሉ እንደ ምጥ ጣር ያለ የጭንቀት መጀመሪያ ይሆናል” ብሎአል። (ማቴዎስ 24 7, 8 የ1980 ትርጉም) ሉቃስ 21:11 በዚህ ዝርዝር ላይ ‘ቸነፈርን’ ይጨምራል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ከማብቃቱ በፊት ስፓኒሽ ኢንፍሉዌንዛ (በኢትዮጵያ የኅዳር በሽታ) የተባለው ወረርሽኝ ምድርን መጥረግ ጀመረ። በመጨረሻም በበሽታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ20 ሚልዮን በላይ ሆነ። ይህም በጦርነቱ ከሞቱት የሚበልጥ ቁጥር ነው።
ጦርነት ይደረግባቸው በነበሩት ዓመታትና ከጦርነቱ በኋላ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች በረሐብ ምክንያት ሞቱ። በተጨማሪም በተለያየ ቦታ የተከሰቱት የመሬት መናወጦች ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። በ1915 በኢጣልያ አገር ከ30,000 የሚበልጡ ሰዎች ተገደሉ፤ በ1920 በቻይና 200,000 የሚያክሉ ሰዎች አለቁ፣ በ1923 በጃፓን 143,000 የሚያክሉ ሰዎች ረገፉ። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ኢየሱስ እንደተናገረው ገና የምጥ ጣር መጀመሪያ ነበር። አንድ መዝገበ ቃላት “ምጥ” የሚለውን ቃል ሲፈታ “አጭር የሆነ የውጋት ስሜት ያለው ሕመም” ብሎአል። ይህ ዓለም ከ1914 ጀምሮ መጠኑና ተደጋጋሚነቱ እየጨመረ በመጣ ውጋት ሲሠቃይ ቆይቶአል። ለምሳሌ ያህል አንደኛው የዓለም ጦርነት ከተፈጸመ ከ21 ዓመት ጊዜ በኋላ ብቻ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተከፍቶ 50 ሚልዮን ለሚያክሉ ሰዎች መጥፋት ምክንያት ሆነ። የሰውን ልጅ ወደ ኑክሌር ዘመን የከተተውም ይህ ጦርነት ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለጭንቀት ምክንያት ስለሆነ ሌላ ነገር ብዙ መነገር ተጀምሮአል። እርሱም የሰው ልጅ በአካባቢው ላይ እየፈጸመ ያለው ጥፋት ነው። ኢየሱስ ይህንን ሁኔታ በትንቢቱ ውስጥ በቀጥታ ባይጠቅሰውም መጪው ጥፋት ከመጀመሩ በፊት የሰው ልጅ ‘ምድርን ማጥፋት’ እንደሚጀምር ራእይ 11:18 ያመለክታል። የሰው ልጅ ምድርን በማበላሸት ላይ እንደሚገኝ የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እጅግ ብዙ ናቸው። ኖርማን ማየርስ የተባሉት የአካባቢ ሁኔታ አማካሪ የዓለም ሁኔታ በ1988 በተባለው መጽሐፍ ላይ እንደጠቀሱት የሚከተለውን አስፈሪ መልእክት አስተላልፈዋል:- “በራሱ የሕይወት ዘመን የጅምላ እልቂት የመድረስ አደጋ የተደቀነበት ትውልድ ከዚህ በፊት ኖሮ አያውቅም። ወደፊትም ቢሆን ይህን የመሰለ ተፈታታኝ ሁኔታ የሚያጋጥመው ትውልድ አይኖርም። የአሁኑ ትውልድ ይህን ችግር ተገንዝቦ አንድ ነገር ማድረግ ካልቻለ ሊስተካከል የማይችል ጉዳት ስለሚደርስ ‘ሌላ ሙከራ’ ለማድረግ የሚያስችል ዕድል አይኖርም።”
በየካቲት 17, 1992 ኒውስዊክ መጽሔት ላይ በከባቢ አየር ውስጥ ስለሚገኘው የኦዞን ግርዶሽ መሳሳት የቀረበውን ረፖርት ተመልከት። ግሪንፒስ በተባለው የአካባቢ ሁኔታ የሚከታተል ድርጅት ውስጥ የሚሠሩት የኦዞን ስፔሺያሊስት አሌክዛንድራ አለን በአሁኑ ጊዜ የኦዞን መሳሳት “በምድር ላይ የሚኖረውን ሕይወት በሙሉ አደጋ ላይ በሚጥል ደረጃ ላይ ደርሶአል” እንዳሉ ተጠቅሶአል። — የምድር አካባቢ እየተበላሸ ስለመሄዱ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በዚህ ገጽ ላይ የሚገኘውን ሳጥን ተመልከት።
የኢየሱስን ትንቢት ክፍሎች በሙሉ ለመዘርዘርና ለማብራራት እዚህ ቦታ አይበቃንም። (ሌሎቹን የትንቢት ገጽታዎች ባጭሩ ለመመልከት በገጽ 5 ላይ የሚገኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።) ይሁን እንጂ ሊታለፍ የማይቻል አንዱ የትንቢቱ ክፍል በማቴዎስ 24:14 ላይ ተገልጾአል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” ይህን ምድር አቀፍ የስብከት ሥራ በማከናወን ላይ ያሉት እነማን ስለመሆናቸው አያጠያይቅም። የይሖዋ ምሥክሮች በ1992 ብቻ በ229 አገሮች ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት ለዚህ ሥራ አውለዋል። ስለዚህ ይህ ሥራቸው በመጨረሻው ቀን እንደምንኖር ከሚያረጋግጡት እጅግ በጣም ግልጽ ምልክቶች አንዱ ነው።
አትሞኝ!
ያም ሆኖ ግን አንዳንዶች ይህ ዓይነቱ ስለመጨረሻው ቀን የሚሰጠው መግለጫ ነገሮችን አጨልሞ ከመመልከት የሚመነጭ ነው ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ‘በምሥራቅ አውሮፓ ኮምኒዝም መውደቁ፣ ልዕለ ኃያላን ሰላም ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ሁኔታዎች እየተሻሻሉ መሄዳቸውን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች አይደሉምን?’ ብለው ይጠይቃሉ። አይደሉም። ኢየሱስ በዚህ የመጨረሻ ጊዜ መላው ዓለም በማያቋርጥ ጦርነት፣ ረሐብ ወይም የምድር መናወጥ ይዋጣል ብሎ እንዳልተናገረ ልብ በል። ምሥራቹ በምድር በሙሉ እንዲሰበክ ከተፈለገ እጅግ ቢያንስ መጠነኛ ጸጥታ የሚገኝባቸው ዓመታት መኖር አለባቸው።
በተጨማሪም ኢየሱስ የመጨረሻውን ቀን ከኖህ የጥፋት ውኃ በፊት ከነበረው ዘመን ጋር እንዳመሳሰለ አስተውል። በዚያ ዘመን ሰዎች በተለመዱት የሕይወት ተግባሮች ማለትም በመብላት፣ በመጠጣትና በማግባት ተጠምደው ነበር። (ማቴዎስ 24:37–39) ይህም በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ሁኔታ ቢኖርም የዕለት ተዕለት ኑሮ መምራት እስከማይችልበት ደረጃ እንደማይባባስ ያመለክታል። ዛሬም ልክ በኖህ ዘመን እንደነበረው አብዛኞቹ የሰው ልጆች የጊዜውን አሳሳቢነት እስከማያስተውሉ ድረስ በዕለት ተዕለት ጉዳዮች የተዋጡ ናቸው።
ስለዚህ የፖለቲካ ሁኔታዎች የተሻሻሉ ይመስላል በማለት የቸልተኝነት አቋም መውሰድ በጣም አደገኛ ይሆናል። (ከ1 ተሰሎንቄ 5:3 ጋር አወዳድር።) የኢየሱስ ትንቢት በአሁኑ ጊዜ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች በጣም ብዙ ናቸው። ይህም ጥፋት መቅረቡን ያስጠነቅቃል።
ከጥፋቱ በኋላ የሚመጣው አስደሳች ጊዜ
በፖምፔ ላይ የደረሰው ጥፋት ሞትና ሐዘን አስከትሎ ነበር። በዚህ ሥርዓት ላይ የሚደርሰው ጥፋት ግን ውበት በተላበሰች ገነት ምድር ለሚገኘው የዘላለም ሕይወት መንገድ ይጠርጋል። (ራእይ 21:3, 4) ከዚያ በኋላ የሰው ልጆችን የሚከፋፍሉ ሰብዓዊ መንግሥታት ምድርን በጦርነት ማፈራረሳቸው ይቀራል። ከዚያ በኋላ ሰዎች የኑክሌር እልቂት ይመጣብናል ብለው አይሰጉም። ከዚያ በኋላ መርዛማ ኬሚካል ወደ ከባቢው አየር የሚተፉ ፋብሪካዎች አይኖሩም። — ዳንኤል 2:44
በዚያ ጊዜ በሕይወት የሚኖር እያንዳንዱ ሰው የመንግሥቲቱን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ የሚታዘዝ፣ ጽድቅ ወዳድና እውነተኛ ወዳጅ ይሆናል። (መዝሙር 37:10, 11) ሆስፒታሎች፣ መቃብር ቤቶችና የቀብር ቦታዎች ዘመን ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ። መፋታት፣ መለያየት፣ ሐዘንና ትካዜ፣ ሕጻናት ላይ ግፍ መሥራት የቀሩ ነገሮች ይሆናሉ። — ኢሳይያስ 25:8፤ 65:17
ከመጨረሻው ቀን ተርፋችሁ የአምላክን ክብራማ አዲስ ዓለም ለማየት ትፈልጋላችሁን? እንግዲያው “ጊዜው መቼ እንዲሆን አታወቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።” (ማርቆስ 13:33) ሆኖም የተቀጠረው ጊዜ በጣም ቅርብ መሆኑን ከዓለም ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ለብዙ ሰዎች በአደገኛ ሁኔታ ቀርቦባቸዋል። ጊዜ ማጥፋት የለብህም። ስለዚህ ሕይወት አድን የሆነ እርምጃ ወስደህ ምድር አቀፉን የመጨረሻ ቀን ምልክት ልብ ከሚሉት ሰዎች ጎን ተሰለፍ። ኢየሱስ በዓለም በሙሉ ምሥራቹ እንዲሰበክ የሰጠውን ትዕዛዝ የሚፈጽሙት እነርሱ ብቻ ስለሆኑ እነዚህን ሰዎች ለይቶ ለማወቅ አያስቸግርም። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ሆነህ “አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ” ከተባለለት ንጉሥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ተሰለፍ። — ማቴዎስ 12:18, 21
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሃያ አራት የምልክቱ ክፍሎች
1. ወደር የለሽ ጦርነት — ማቴዎስ 24:6, 7፤ ራእይ 6:4
2. የምድር መናወጥ — ማቴዎስ 24:7፤ ማርቆስ 13:8
3. ረሐብ — ማቴዎስ 24:7፤ ማርቆስ 13:8
4. ቸነፈር — ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:8 (የ1980 ትርጉም )
5. የዓመፅ መብዛት — ማቴዎስ 24:12
6. ምድርን ማበላሸት — ራእይ 11:18
7. የፍቅር መቀዝቀዝ — ማቴዎስ 24:12
8. የአስፈሪ ነገሮች መታየት — ሉቃስ 21:11
9. ቅጥ የሌለው የገንዘብ ፍቅር — 2 ጢሞቴዎስ 3:2
10. ለወላጆች አለመታዘዝ — 2 ጢሞቴዎስ 3:2
11. ከአምላክ ይበልጥ ደስታን መውደድ — 2 ጢሞቴዎስ 3:4
12. ራስ ወዳድነት ጎልቶ መታየቱ — 2 ጢሞቴዎስ 3:2
13. በአጠቃላይ የተፈጥሮ ፍቅር መጥፋት — 2 ጢሞቴዎስ 3:3
14. ሰዎች ዕርቅ ፈላጊ አለመሆናቸው — 2 ጢሞቴዎስ 3:3
15. በሁሉም የኅብረተሰብ ደረጃ ዘንድ ራስን የመግዛት ጠባይ መጥፋት — 2 ጢሞቴዎስ 3:3
16. ጥሩ የሆነውን ነገር አለመውደድ መስፋፋቱ — 2 ጢሞቴዎስ 3:3
17. ብዙዎች በግብዝነት ክርስቲያን ነን ማለታቸው — 2 ጢሞቴዎስ 3:5
18. አንዳንዶች ከመጠን በላይ የሚበሉና የሚጠጡ መሆናቸው — ሉቃስ 21:34
19. ዘባቾች ምልክቱን አናምንም ማለታቸው — 2 ጴጥሮስ 3:3, 4
20. ብዙ የሐሰት ነቢያት መኖራቸው — ማቴዎስ 24:5, 11፤ ማርቆስ 13:6
21. የተቋቋመችው የአምላክ መንግሥት ምሥራች መሰበክ — ማቴዎስ 24:14፤ ማርቆስ 13:10
22. የእውነተኛ ክርስቲያኖች መሰደድ — ማቴዎስ 24:9፤ ሉቃስ 21:12
23. በመጨረሻው ቀን መደምደሚያ ላይ የሚሰማው ሰላምና ደኅንነት ሆኗል የሚል ጩኸት — 1 ተሰሎንቄ 5:3
24. ሰዎች አደጋ እንደተደቀነባቸው የማያስተውሉ መሆናቸው — ማቴዎስ 24:39
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አምላክ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ሰምተህ እርምጃ የጊዜው ምልክት የሆኑት የመኖሪያ አካባቢ ችግሮች
◻ ሕዝብ ጥቅጥቅ ብሎ በሚኖርባቸው የሰሜን ንፍቀ ክበብ አገሮች ያለው የኦዞን ግርዶሽ የሳይንስ ሊቃውንት ከጥቂት ዓመታት በፊት ያስቡት ከነበረው በእጥፍ በሚበልጥ መጠን እየሳሳ ሄዶአል።
◻ በየቀኑ በትንሹ 140 የሚያክሉ የእፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎች ከምድር ገጽ በመጥፋት ላይ ናቸው።
◻ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘው ሙቀት ወደ ጠፈር እንዳይሄድ አፍኖ የሚይዘው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን ከኢንዱስትሪ ዘመን በፊት ከነበረው መጠን በ26 በመቶ ጨምሮአል። ጭማሪው አሁንም አልተገታም።
◻ የምድርን ሙቀት መመዝገብ ከተጀመረበት ከ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እንደ 1990 በጣም ሞቃት የሆነችበት ዘመን የለም። የምድር ሙቀት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰባቸው ሰባት ዓመታት መካከል ስድስቱ ከ1980 ወዲህ ያሉ ናቸው።
◻ የምድር ደኖች በየዓመቱ 17 ሚልዮን ሄክታር በሚያክል መጠን ይወድማሉ። ይህም የፊንላንድን ግማሽ የሚያክል ስፋት ያለው ቦታ ነው።
◻ የዓለም ሕዝብ ብዛት በየዓመቱ 92 ሚልዮን በሚያክል ብዛት ይጨምራል። ይህም በየዓመቱ የሜክሲኮን ሕዝቦች የሚያክሉ ሰዎች ይጨመራሉ ማለት ነው። ከእነዚህ መካከል 88 ሚልዮን የሚያክሉት የሚጨመሩት በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች ነው።
◻ 1.2 ቢልዮን የሚያክሉ ሰዎች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አያገኙም።
ዎርልድ ዎች የተባለ ድርጅት ባወጣው የዓለም ሁኔታ በ1992 በተባለው መጽሐፍ ገጽ 3, 4 መሠረት። ደብልዩ ደብልዩ ኖርተን እና ኩባንያው ኒውዮርክ፣ ለንደን
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጥፋቱ በኋላ ክብራማው የአምላክ አዲስ ዓለም ይመጣል