ምሉዓን ሆናችሁና ጽኑ እምነት ኖሯችሁ ቁሙ
‘እነሆ፣ እጅግ ብዙ ሰዎች!’
የይሖዋ አገልጋዮችን ለአሥርተ ዓመታት ግራ ሲያጋባ የኖረ ጥያቄ ነው። ጥያቄውን ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ከረዥም ጊዜ በፊት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይኸው ርዕሰ ጉዳይ ብዙ ውይይቶች እንዲደረጉ ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ በመጨረሻ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ የተገኘ ሲሆን በ1935 በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የተገኙትን ተሰብሳቢዎች አስፈንጥዟል።
ከዚህ ሁሉ ውይይት በስተጀርባ የሚነሳው መሠረታዊ ጥያቄ በራእይ 7:9 ላይ የተገለጸው “ታላቅ ሕዝብ” (ኪንግ ጄምስ ቨርሽን) ወይም “እጅግ ብዙ ሰዎች” ማንነት ነበር። ይህ የአማኞች ቡድን ወደ ሰማይ ይሄድ ይሆን?
ለረዥም ዘመን መልስ ያላገኘ ጥያቄ
ከሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዘመናችን ድረስ ክርስቲያኖች ስለ “ታላቅ ሕዝብ” ማንነት ግራ ተጋብተው ኖረዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እጅግ ብዙ ሰዎች የእውነት እውቀት ቢኖራቸውም ይህንን እውነት ለመስበክ ምንም ጥረት ያላደረጉ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው የሰማያዊ ክፍል አባላት እንደሆኑ ያምኑ ነበር።
ይሁን እንጂ በስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ቅንዓት ያሳዩ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ተባባሪ የሆኑ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ወደ ሰማይ የመሄድ ምኞት አልነበራቸውም። ተስፋቸው የይሖዋ ሕዝቦች ከ1918 እስከ 1922 ባሉት ዓመታት ውስጥ “በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” በሚል ርዕስ በተከታታይ ያሰሙት ከነበረው የሕዝብ ንግግር ጋር የተስማማ ነበር። እንዲህ ያሉት ሰዎች በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ይባረካሉ።
የጥቅምት 15, 1923 መጠበቂያ ግንብ ኢየሱስ ስለ በጎችና ፍየሎች የተናገረውን ምሳሌ ትርጉም ሲያብራራ እንዲህ ብሎአል:- “በጎቹ በመንፈስ የተወለዱ ሰዎች ሳይሆኑ የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸውንና የኢየሱስ ክርስቶስን ጌትነት በአእምሮአቸው የሚቀበሉትን እንዲሁም በኢየሱስ ግዛት ሥር የሚገኘውን የተሻለ ጊዜ የሚናፍቁትንና ተስፋ የሚያደርጉትን ከአሕዛብ ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ያመለክታሉ።”—ማቴዎስ 25:31-46
ተጨማሪ ብርሃን
በ1931 የወጣው መቀደስ አንደኛ መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ስለ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 9 ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ የዓለም ፍጻሜ በሚሆንበት ጊዜ ከጥፋት እንዲተርፉ በግምባራቸው ላይ ምልክት የሚደረግባቸው ሰዎች በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የተገለጹት በጎች እንደሆኑ ገልጾአል። በ1932 የወጣው መቀደስ ሦስተኛ መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ደግሞ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ኢዩ የሐሰት ሃይማኖትን ሲያጠፋ የሚያሳየውን ቅንዓት ለማየት ተከትሎት ስለሄደው ስለ ኢዮናዳብ ገልጾ ነበር። ኢዮናዳብ እስራኤላዊ ባይሆንም ቅን ልብ የነበረው ሰው ነው። (2 ነገሥት 10:15-28) መጽሐፉ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር:- “ኢዮናዳብ ዛሬ በምድር ላይ ያሉትን ከሰይጣን ድርጅት ፈጽሞ የተለዩትንና ከጽድቅ ጎን የተሰለፉትን የሰዎች ቡድን ያመለክታል ወይም ይወክላል። ጌታ በአርማጌዶን ጊዜ ከጥፋቱና ከመከራው ጠብቆ በማውጣት በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የሚሰጠው ለእነዚህ ሰዎች ነው። ‘የበጎቹ’ ክፍል የሚሆኑት እነዚህ ሰዎች ናቸው።”
በ1934 መጠበቂያ ግንብ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው መጠመቅ እንደሚኖርባቸው ገለጸ። ይህንን ምድራዊ ክፍል በሚመለከት የፈነጠቀው ብርሃን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በድምቀት እየበራ ነበር!—ምሳሌ 4:18
ደማቅ የእውቀት ብርሃን
በራእይ 7:9-17 ላይ የፈነጠቀው የእውቀት ብርሃን በሙሉ ድምቀቱና ውበቱ ግልጽ ሆኖ የሚታይበት ጊዜ ደረሰ። (መዝሙር 97:11) የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ከግንቦት 30 እስከ ሰኔ 3, 1935 በዋሽንግተን ዲ ሲ፣ ዩ ኤስ ኤ ሊደረግ የታቀደው ስብሰባ በኢዮናዳብ ክፍል ለተመሰሉት ሁሉ “ከፍተኛ ጥቅምና ማጽናኛ” እንደሚያስገኝ ገልጾ ነበር። በእርግጥም ከፍተኛ ጥቅምና ማጽናኛ አስገኝቶአል!
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ 20, 000 ለሚያክሉ ተሰብሳቢዎች “ታላቁ ሕዝብ” በሚል ርዕስ ባደረገው ቀስቃሽ ንግግር የዘመናችን “ሌሎች በጎች” በራእይ 7:9 ላይ ከተጠቀሱት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ጋር አንድ እንደሆኑ የሚገልጽ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አቅርቦአል። (ዮሐንስ 10:16) ተናጋሪው በንግግሩ መጨረሻ ላይ “በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ የምታደርጉ ሁሉ አንድ ጊዜ ብድግ በሉ” አለ። ከአድማጮቹ መካከል በጣም ብዙ የሆኑት ብድግ ሲሉ ራዘርፎርድ “እነሆ፣ ታላቁ ሕዝብ!” አለ። ለጥቂት ጊዜ ፍጹም ጸጥታ ከሰፈነ በኋላ እንደ ነጎድጓድ የሚያስተጋባ የደስታ ጭብጨባ ተሰማ። በሚቀጥለው ቀን 840 የሚያክሉ አዳዲስ ምሥክሮች ተጠመቁ። ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል እንደሆኑ የሚናገሩ ነበሩ።
አስገራሚ ክስተት
ከ1935 ቀደም ባሉት ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ከተቀበሉትና በምሥክርነቱ ሥራ ቅንዓት ካሳዩት ሰዎች መካከል ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ብዙዎች በገነቲቱ ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ፍላጎት እንዳላቸው ይናገሩ ነበር። አምላክ የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ስላልሰጣቸው ወደ ሰማይ የመሄድ ፍላጎት ጨርሶ አልነበራቸውም። እነዚህ ሰዎች የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ እጅግ ብዙ ሰዎች መሆናቸውን ማሳወቃቸው በ1935 የ144, 000ዎቹ ቁጥር ሊሞላ መቃረቡን የሚያመለክት ነበር።—ራእይ 7:4
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀመረበት ወቅት ሰይጣን ዲያብሎስ የእጅግ ብዙ ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ነበር። በብዙ አገሮች የመንግሥቱ የስብከት ሥራ ታግዶ ነበር። በእነዚያ የጨለማ ዓመታት፣ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በጥር ወር 1942 ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “እጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥራቸው በጣም ብዙ የሚሆን አይመስልም” ብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ የተገኘው መለኮታዊ በረከት ከዚህ የተለየ ውጤት አስገኝቶአል። ቅቡዓንና ተባባሪዎቻቸው የሆኑት ሌሎች በጎች ‘ምሉዓን ሆነውና ጽኑ እምነት ይዘው በመቆም’ ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ሲፈጽሙ ቆይተዋል። (ቆላስይስ 4:12፤ ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) በ1946 በዓለም ዙሪያ ይሰብኩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 176, 456 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ነበሩ። በ2000 ደግሞ በ235 አገሮች ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉ ከ6, 000, 000 የሚበልጡ ምሥክሮች ነበሩ። በእውነትም እጅግ ብዙ ሰዎች ናቸው! አሁንም ቢሆን ቁጥራቸው እያደገ በመሄድ ላይ ነው።