ምዕራፍ 25
ሁለቱን ምሥክሮች እንደገና ሕያው ማድረግ
1. ብርቱው መልአክ ዮሐንስን ምን እንዲያደርግ ጠየቀው?
ሁለተኛው ወዮታ ከመፈጸሙ በፊት ብርቱው መልአክ ዮሐንስን በሌላ ትንቢታዊ ትርዒት እንዲካፈል ጠየቀው። ይህ ትንቢታዊ ትርዒት ቤተ መቅደሱን የሚመለከት ነበር። (ራእይ 9:12፤ 10:1) ዮሐንስ የሚከተለውን ይነግረናል:- “በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ እንዲህም ተባለልኝ:- ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ።”—ራእይ 11:1
ቤተ መቅደሱ
2. (ሀ) እስከ ዘመናችን ድረስ ጸንቶ የሚቆየው የትኛው ቤተ መቅደስ ነው? (ለ) የቤተ መቅደሱ ሊቀ ካህናት ማን ነው? ቅድስተ ቅዱሳኑስ ምንድን ነው?
2 እዚህ ላይ የተጠቀሰው ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም የነበረ እውነተኛ ቤተ መቅደስ ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ በ70 እዘአ በሮማውያን ሠራዊት ጠፍቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከዚህ ጥፋት በፊት እንኳን ሐዋርያው ጳውሎስ እስከ ዘመናችን ድረስ ጸንቶ የሚቆይ ሌላ ቤተ መቅደስ እንደሚኖር ገልጾአል። ይህ ቤተ መቅደስ የመገናኛውን ድንኳንና በኋላም በኢየሩሳሌም የታነጹትን ቤተ መቅደሶች ጥላነት የፈጸመ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነው። “በሰው ሳይሆን በጌታ [“በይሖዋ፣” NW] የተተከለ ነው።” ሊቀ ካህኑም ጳውሎስ ‘በሰማያት ባለው የግርማ ዙፋን ቀኝ’ እንደተቀመጠ የተናገረለት ኢየሱስ ነው። ቅድስተ ቅዱሳኑ ደግሞ ይሖዋ የሚገኝበት ሰማያዊ ሥፍራ ነው።—ዕብራውያን 8:1, 2፤ 9:11, 24
3. በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የነበረው (ሀ) ቅድስተ ቅዱሳኑን ከቅድስቱ ይለይ የነበረው መጋረጃ (ለ) የእንስሳቱ መሥዋዕት (ሐ) መሰዊያው የምን ምሳሌ ነው?
3 የመገናኛውን ድንኳን ቅድስተ ቅዱሳን ከቅድስቱ ይለይ የነበረው መጋረጃ የኢየሱስን ሥጋ እንደሚያመለክት ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጾአል። ኢየሱስ የገዛ ነፍሱን መሥዋዕት ባደረገበት ጊዜ ይህ መጋረጃ ለሁለት ተቀደደ። ይህም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የኢየሱስ ሥጋ ይሖዋ ወደሚገኝበት ወደ ሰማይ እንዳይገባ የሚያደርገው ማገጃ ሊሆን እንደማይችል ያመለክታል። ቅቡዓን የበታች ካህናቱ በታማኝነት ከሞቱ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ወደ ሰማያት ይገባሉ። (ማቴዎስ 27:50, 51፤ ዕብራውያን 9:3፤ 10:19, 20) በተጨማሪም ጳውሎስ በቤተ መቅደሱ በየጊዜው ይቀርቡ የነበሩት የእንስሳት መሥዋዕቶች ኢየሱስ መሥዋዕት አድርጎ ወደሚያቀርበው አንድ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት እንደሚያመለክቱ ጠቅሷል። በቤተ መቅደሱ እድሞ ይገኝ የነበረው መሠዊያ ይሖዋ እንደ ፈቃዱ ያዘጋጀውን “ለብዙዎች” ማለትም መጀመሪያ ለቅቡዓን በኋላ ደግሞ ደህንነት ለማግኘት አጥብቀው ለሚፈልጉት “ሌሎች በጎች” የቀረበውን የኢየሱስ መሥዋዕት ለመቀበል ያደራጀውን ዝግጅት ያመለክታል።—ዕብራውያን 9:28፤ 10:9, 10፤ ዮሐንስ 10:16
4. (ሀ) ቅዱሱ ሥፍራ (ለ) የውስጠኛው እድሞ የምን ምሳሌ ነው?
4 ከዚህ በመለኮታዊ ኃይል አነሳሽነት ከተጻፈው መረጃ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የነበረው ቅድስት በመጀመሪያ ኢየሱስ በኋላም 144, 000ዎቹ ነገሥታትና ካህናት “በመጋረጃው” በኩል ከማለፋቸው በፊት በዚህ ምድር ላይ ሳሉ የነበሩበትን የቅድስና ሁኔታ እንደሚያመለክት ልንገነዘብ እንችላለን። (ዕብራውያን 6:19, 20፤ 1 ጴጥሮስ 2:9) ኢየሱስ በ29 እዘአ በዮርዳኖስ ወንዝ ከተጠመቀ በኋላ አምላክ ልጁ መሆኑን እንደ መሰከረለት ሁሉ የአምላክን መንፈሳዊ ልጅነት ማግኘታቸውን ያመለክታል። (ሉቃስ 3:22፤ ሮሜ 8:15) ካህናት ያልሆኑ እስራኤላውያን ሊመለከቱ በሚችሉትና መሥዋዕቶቹ ይቀርቡበት በነበረው ውስጣዊ እድሞ የተመሰለው ነገር ምንድን ነው? የውስጠኛው እድሞ ሰው የነበረው ኢየሱስ ሕይወቱን ለሰው ልጆች ቤዛ እንዲሰጥ ያስቻለውን የፍጽምና አቋም ያመለክታል። በተጨማሪም የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች በምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት የተሰጣቸውን የጻድቅነትና የቅዱስነት አቋም ያመለክታል።a—ሮሜ 1:7፤ 5:1
ቤተ መቅደሱን መለካት
5. በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በሚገኙ ትንቢቶች ውስጥ (ሀ) የኢየሩሳሌም መለካት (ለ) ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ቤተ መቅደስ መለካት ምን ያመለክት ነበር?
5 ዮሐንስ “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን” እንዲለካ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። ታዲያ ይህ ምን ያመለክታል? በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትንቢቶች ውስጥ የቤተ መቅደስ መለካት ፍጹም በሆነው የይሖዋ ሕግ መሠረት ፍትሕ እንደሚፈጸም ዋስትና የሚሰጥ ድርጊት ነው። ክፉ በነበረው በንጉሥ ምናሴ ዘመን ኢየሩሳሌም መለካትዋ በዚያች ከተማ ላይ የተወሰነው የጥፋት ፍርድ ፈጽሞ ሊለወጥ የማይችል መሆኑን አመልክቶ ነበር። (2 ነገሥት 21:13፤ ሰቆቃወ ኤርምያስ 2:8) ኤርምያስ ኢየሩሳሌም ስትለካ ማየቱ ግን ከተማይቱ ዳግመኛ እንደምትሠራ የሚያረጋግጥ ነበር። (ኤርምያስ 31:39፤ በተጨማሪም ዘካርያስ 2:2-8ን ተመልከት።) በተመሳሳይም ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው ቤተ መቅደስ አንድ በአንድ መለካቱ እውነተኛ አምልኮ በአገራቸው ውስጥ ተመልሶ እንደሚቋቋም በባቢሎን ግዞት ለነበሩት አይሁዳውያን ዋስትና የሚሰጥ ነበር። በተጨማሪም እስራኤል በደለኛነትዋን ትታ ቅዱስ ከሆኑት የይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምታ መኖር እንደሚገባት የሚያሳስብ ነበር።—ሕዝቅኤል 40:3, 4፤ 43:10
6. ዮሐንስ ቤተ መቅደሱንና በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚያገለግሉትን ካህናት እንዲለካ መነገሩ የምን ምልክት ነው? አስረዳ።
6 ስለዚህ ዮሐንስ ቤተ መቅደሱንና በቤተ መቅደሱ የሚያመልኩትን ካህናት እንዲለካ መታዘዙ ይሖዋ ስለ ቤተ መቅደሱ ዝግጅትና በቤተ መቅደሱ ስለሚያመልኩት ሰዎች ያወጣውን ዓላማ ሊያግድ የሚችል ምንም ዓይነት ኃይል እንደማይኖርና እነዚህም ዓላማዎች ወደ ፍጻሜያቸው በመቃረብ ላይ እንደሆኑ የሚያረጋግጥ ምልክት ነው። አሁን ማንኛውም ነገር በብርቱው የይሖዋ መልአክ እግር ሥር በመሆኑ “የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ቤት ተራራ ከተራሮች ሁሉ በላይ” የሚሆንበት ጊዜ ነው። (ኢሳይያስ 2:2-4) የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ለብዙ መቶ ዘመናት ከቆየው ከሕዝበ ክርስትና ክህደት በላይ ከፍ ብሎ መታየት ይኖርበታል። በተጨማሪም ከአሁን በፊት የሞቱ ታማኝ የኢየሱስ ወንድሞች ከሙታን ተነስተው ወደ “ቅድስተ ቅዱሳን” የሚገቡበት ጊዜ ነው። (ዳንኤል 9:24፤ 1 ተሰሎንቄ 4:14-16፤ ራእይ 6:11፤ 14:4) የመጨረሻዎቹ የምድር ታታሚ “የእግዚአብሔር ባሮች” በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች በመሆን በአምላክ የቤተ መቅደስ ዝግጅት ውስጥ ለሚኖራቸው ቋሚ ቦታ ብቁዎች እንዲሆኑ በመለኮታዊው የአቋም ደረጃ መሠረት መለካት ይኖርባቸዋል። የዘመናችን የዮሐንስ ክፍል አባሎች እነዚህን ቅዱስ የአቋም ደረጃዎች በሚገባ ያውቁአቸዋል። የአቋም ደረጃዎቹንም ለማሟላት ቆርጠዋል።—ራእይ 7:1-3፤ ማቴዎስ 13:41, 42፤ ኤፌሶን 1:13, 14፤ ከሮሜ 11:20 ጋር አወዳድር።
የአደባባዩ መረገጥ
7. (ሀ) ዮሐንስ እድሞውን እንዳይለካ የተነገረው ለምን ነበር? (ለ) ቅድስቲቱ ከተማ ለ42 ወራት የተረገጠችው መቼ ነበር? (ሐ) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የይሖዋን የጽድቅ ደረጃዎች ለ42 ወራት ሳይጠብቁ የቀሩት እንዴት ነበር?
7 ዮሐንስ እድሞውን እንዳይለካ የተከለከለው ለምንድን ነው? እንደሚከተለው በማለት ይነግረናል። “በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው፣ አትለካውም እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።” (ራእይ 11:2) የውስጠኛው እድሞ በመንፈስ የተወለዱ ክርስቲያኖች በምድር ላይ በሚኖሩበት ጊዜ የሚኖራቸውን የጻድቅነት አቋም እንደሚያመለክት ቀደም ብለን ተመልክተናል። ቀጥለን እንደምንመለከተው እዚህ ላይ የተጠቀሰው 42 ወር ቃል በቃል የሚወሰድ ሲሆን ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ በከባድ ፈተና ላይ የነበሩበትን ከታኅሣሥ 1914 እስከ ሰኔ 1918 ያለውን ጊዜ ያመለክታል። በእነዚህ የጦርነት ዓመታት የይሖዋን የጽድቅ ደረጃዎች ጠብቀው ይገኙ ይሆንን? አብዛኞቹ አልጠበቁም። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በአጠቃላይ ለመለኮታዊ ሕግ ከመታዘዝ ይልቅ ብሔረተኛነትን አስቀድመዋል። በአብዛኛው በሕዝበ ክርስትና ግዛት ውስጥ በተደረገው በዚህ ጦርነት የሁለቱም ወገን ቀሳውስት ወጣቶች ወደ ጦር ምሽጎች እንዲገቡ ይሰብኩ ነበር። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል። ፍርዱ በ1918 በአምላክ ቤት በጀመረበት ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ በዚያ ብዙ ደም ባፋሰሰው ጦርነት ውስጥ ገብታ ነበር። የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በሙሉ ያፈሰሱት ደም እስከ አሁን ድረስ ለፍትሕ ይጮሃል። (1 ጴጥሮስ 4:17) ወደ ውጭ መጣላቸው የማይሻርና የማይለወጥ ሆኖአል።—ኢሳይያስ 59:1-3, 7, 8፤ ኤርምያስ 19:3, 4
8. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ተገንዝበው ነበር? ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ያልተገነዘቡት ምን ነገር ነበር?
8 ጥቂቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችስ? ወዲያውኑ በ1914 መለኮታዊ የአቋም ደረጃዎችን ስለማሟላታቸው መመዘን ነበረባቸውን? አልነበረባቸውም። ምክንያቱም እነርሱም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ እንዳሉት ክርስቲያን ነን ባዮች መፈተን ይኖርባቸዋል። ከፍተኛ ስደትና ፈተና እንዲደርስባቸው ‘መተውና ለአሕዛብ መሰጠት’ ነበረባቸው። ብዙዎቹ ሌሎች ሰዎችን ለመግደል መዝመት እንደማይገባቸው ተገንዝበው ነበር። ይሁን እንጂ ስለ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ሙሉ በሙሉ አልተረዱም ነበር። (ሚክያስ 4:3፤ ዮሐንስ 17:14, 16፤ 1 ዮሐንስ 3:15) አንዳንዶች ከአሕዛብ በደረሰባቸው ተጽእኖ ተሸንፈዋል።
9. በአሕዛብ ተረግጦ የነበረው ቅዱስ ከተማ ምንድን ነው? ይህንንስ ከተማ በምድር ላይ ይወክሉ የነበሩት እነማን ነበሩ?
9 ይሁን እንጂ የተቀደሰችው ከተማ በአሕዛብ የተረገጠችው እንዴት ነበር? ይህ ትንቢት የራእይ መጽሐፍ ከመጻፉ ከ25 ዓመታት በፊት የጠፋችውን ኢየሩሳሌም የሚያመለክት ትንቢት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ቅዱሱ ከተማ ቆየት ብሎ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸችውና በአሁኑ ጊዜ በምድር ላይ በመቅደሱ ውስጠኛ አደባባይ በሚኖሩት ቅቡዓን ክርስቲያን ቀሪዎች የተወከለችውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌም ያመለክታል። ከጊዜ በኋላ እነዚህም ቅቡዓን ቀሪዎች የቅዱሱ ከተማ ክፍል ይሆናሉ። ስለዚህ እነዚህን ክርስቲያኖች መርገጥ ከተማይቱን ራስዋን ከመርገጥ ተለይቶ አይታይም።—ራእይ 21:2, 9-21
ሁለቱ ምሥክሮች
10. የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች በሚረገጡበት ጊዜ ምን ማድረግ ይገባቸው ነበር?
10 እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች ቢረገጡም እንኳን የይሖዋ ታማኝ ምሥክሮች ከመሆን አላፈገፈጉም። በዚህም ምክንያት ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ። እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።”—ራእይ 11:3, 4
11. ታማኞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ማቅ” ለብሰው ትንቢት መናገራቸው ምን ትርጉም አለው?
11 እነዚህ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ትንቢት የሚናገሩት “ማቅ ለብሰው” ስለሆነ መጽናት ያስፈልጋቸዋል። ‘ማቅ መልበሳቸው’ ምን ማለት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ማቅ የሐዘን ምልክት ነበር። አንድ ሰው ማቅ ከለበሰ በሐዘን ቅስሙ ተሰብሮአል ማለት ነበር። (ዘፍጥረት 37:34፤ ኢዮብ 16:15, 16፤ ሕዝቅኤል 27:31) ማቅ የአምላክ ነቢያት ከሚናገሩት የሐዘንና የጥፋት መልእክት ጋር ዝምድና አለው። (ኢሳይያስ 3:8, 24-26፤ ኤርምያስ 48:37፤ 49:3) በተጨማሪም ማቅ መልበስ መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ተቀብሎ ንስሐ መግባትን ወይም ራስን ማዋረድን ሊያመለክት ይችላል። (ዮናስ 3:5) ሁለቱ ምሥክሮች የለበሱት ማቅ የይሖዋን የፍርድ መልእክት በማወጁ ሥራ በትህትና መጽናታቸውን የሚያመለክት ይመስላል። በአሕዛብ ላይ ከባድ ሐዘን የሚያመጣውን የበቀል ቀን የሚያውጁ ምሥክሮች ነበሩ።—ዘዳግም 32:41-43
12. ቅድስቲቱ ከተማ የምትረገጥበት የጊዜ ርዝመት ምሳሌያዊ ያልሆነው ለምንድን ነው?
12 የዮሐንስ ክፍል ለተወሰነ ጊዜ ማለትም ለ1,260 ቀናት ወይም ለ42 ወራት የይሖዋን መልእክት መስበክ ነበረበት። ይህም ጊዜ ቅድስቲቱ ከተማ ከምትረገጥበት ጊዜ ጋር እኩል ነው። ይህ የጊዜ ርዝመት በሁለት የተለያዩ መንገዶች ይኸውም በመጀመሪያ በወራት ቀጥሎ ደግሞ በቀናት ስለተገለጸ የጊዜው ርዝመት ቃል በቃል መሆን ያለበት ይመስላል። በተጨማሪም በጌታ ቀን መጀመሪያ ላይ የአምላክ ሕዝቦች እዚህ ላይ በትንቢት ከተነገረው ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል ከባድ ሁኔታ የደረሰባቸው የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ነበር። ይህም ከታኅሣሥ 1914 እስከ ሰኔ 1918 ድረስ ያለው ጊዜ ነው። (ራእይ 1:10) በሕዝበ ክርስትናና በመላው ዓለም ላይ ስለሚመጣው ፍርድ የሚገልጸውን ‘ማቅ መሰል’ መልእክት ሰብከዋል።
13. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሁለት ምሥክሮች መመሰላቸው ምን ያመለክታል? (ለ) ዮሐንስ ሁለቱን ምሥክሮች “ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች” ብሎ መጥራቱ የትኛውን የዘካርያስ ትንቢት ያስታውሰናል?
13 በሁለት ምሥክሮች መመሰላቸው ራሱ መልእክታቸው የተረጋገጠና ትክክለኛ መሆኑን ያረጋግጥልናል። (ከዘዳግም 17:6ና ከዮሐንስ 8:17, 18 ጋር አወዳድር።) ዮሐንስ “በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ” “ሁለቱ የወይራ ዛፎችና ሁለቱ መቅረዞች” እንደሆኑ ተናግሮላቸዋል። ይህም ባለ ሰባት ቅርንጫፍ መቅረዝና ሁለት የወይራ ዛፎች የተመለከተውን የዘካርያስን ትንቢት የሚጠቅስ ይመስላል። የወይራ ዛፎቹ “በምድር ሁሉ ጌታ አጠገብ የቆሙት” “ሁለቱ የተቀቡ” ሰዎች ማለትም ገዥውን ዘሩባቤልና ሊቀ ካህኑን ኢያሱ እንደሚያመለክቱ ተነግሮአል።—ዘካርያስ 4:1-3, 14
14. (ሀ) ዘካርያስ በራእይ የተመለከታቸው ሁለት የወይራ ዛፎች የምን ምሳሌዎች ነበሩ? መቅረዙስ? (ለ) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ ምን ደርሶባቸዋል?
14 ዘካርያስ ይኖር የነበረበት ዘመን የእድሳትና የግንባታ ዘመን ነበር። የሁለቱን የወይራ ዛፎች ራእይ መመልከቱ ደግሞ ዘሩባቤልና ኢያሱ ሕዝቦቻቸውን ለሥራ በሚያነሳሱበት ጊዜ የይሖዋ መንፈስ አብሮአቸው እንደሚሆን የሚያመልክት ነው። ዘካርያስ በራእይ የተመለከተው የመቅረዝ ራእይ “የጥቂቱን ነገር ቀን” እንዳይንቅ የሚያሳስበው ነበር። ምክንያቱም የይሖዋ ዓላማ የሚፈጸመው “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW]።” (ዘካርያስ 4:6, 10፤ 8:9) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለሰው ልጆች የእውነትን ብርሃን በትጋት ያደርሱ የነበሩት ጥቂት ክርስቲያኖችም በተመሳሳይ የግንባታ ሥራ ይፈጽማሉ። እነርሱም ለሌሎች የመጽናናት ምንጭ ይሆናሉ። ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም “የጥቂቱን ነገር ቀን” ሳይንቁ በይሖዋ ኃይል መመካትን ይማራሉ።
15. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሁለቱ ምሥክሮች ተብለው መጠራታቸው ምን ተጨማሪ ነገር ያስታውሰናል? አስረዳ። (ለ) ሁለቱ ምሥክሮች ምን ዓይነት ምልክት እንዲያሳዩ ሥልጣን ተሰጥቶአቸዋል?
15 በተጨማሪም ሁለት ምሥክሮች ተብለው መጠራታቸው ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ በተለወጠበት ጊዜ የሆነውን ነገር ያሳስበናል። በዚህ ራእይ ሦስቱ የኢየሱስ ሐዋርያት ኢየሱስ በሙሴና በኤልያስ ታጅቦ በመንግሥት ግርማ ሲገለጥ ተመልክተው ነበር። ይህም ኢየሱስ እነዚህ ሁለት ነቢያት ጥላ የሆኑለትን ሥራ ለመፈጸም በ1914 ዙፋኑ ላይ መቀመጡን የሚያመለክት ነው። (ማቴዎስ 17:1-3) አሁን ደግሞ ሁለቱ ምሥክሮች ሙሴና ኤልያስ የፈጸሙትን ዓይነት ምልክት ሲፈጽሙ መታየታቸው የተገባ ነው። ለምሳሌ ያህል ዮሐንስ ስለ እነዚህ ሁለት ምሥክሮች እንዲህ ብሎአል:- “ማንምም ሊጎዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል፣ ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጎዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል። እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው።”—ራእይ 11:5, 6ሀ
16. (ሀ) የእሳቱ ምልክት በእስራኤል መካከል በሙሴ ሥልጣን ላይ ግድድር የደረሰበትን ጊዜ የሚያስታውሰን እንዴት ነው? (ለ) በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ያቃለሉትና ችግርና መከራ እንዲደርስባቸው ያደረጉት እንዴት ነው? እነርሱስ አፀፋውን የመለሱት እንዴት ነው?
16 ይህ ደግሞ በእሥራኤል አንዳንድ ሰዎች የሙሴን ስልጣን በተገዳደሩበት ጊዜ የተፈጸመውን ነገር ያስታውሰናል። በዚህ ጊዜ ነቢዩ እሳታማ የፍርድ ቃላት ተናገረ። ይሖዋ ከሰማይ ቃል በቃል እሳት አውርዶ 250 ሰዎችን አጠፋ። (ዘኍልቁ 16:1-7, 28-35) በተመሳሳይም የሕዝበ ክርስትና መሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ከመንፈሳዊ ኮሌጅ የተመረቁ አይደሉም ብለው አንቋሸዋቸው ነበር። ይሁን እንጂ የአምላክ ምሥክሮች አገልጋይነታቸውን የሚያረጋግጥ ከፍተኛ የምሥክር ወረቀት ነበራቸው። የምሥክር ወረቀቶቻቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክታቸውን የተቀበሉት ቅን ሰዎች ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 3:2, 3) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1917 የራእይንና የሕዝቅኤልን መጻሕፍት የሚያብራራ ጠንካራ መልእክት የያዘ ያለቀለት ምሥጢር የተባለ መጽሐፍ አወጡ። መጽሐፉ ከወጣ በኋላ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወርሐዊ የተባለ ባለ አራት ገጽ ትራክት ተዘጋጅቶ በ10 ሚልዮን ቅጂዎች ተሰራጨ። በዚህ ትራክት ላይ የሰፈረው ርዕሰ ትምህርት “የታላቂቱ ባቢሎን ውድቀት—ሕዝበ ክርስትና መከራ መቀበል የሚኖርባት ለምንድን ነው?—የመጨረሻውስ ውጤት ምን ይሆናል?” የሚል ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ በነገሩ የተናደዱ ቀሳውስት ጦርነቱ በፈጠረው ሁኔታ በመጠቀም መጽሐፉ እንዲታገድ አደረጉ። በሌሎች አገሮችም መጽሐፉ የሳንሱር እገዳ ተጣለበት። ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች የመንግሥት ዜናዎች በተባሉት ባለ አራት ገጽ ትራክቶች አማካኝነት በሚወጡት እሳታማ መልእክቶች መዋጋታቸውን ቀጠሉ። የጌታ ቀን ወደፊት እየገፋ በሄደ መጠን የሕዝበ ክርስትናን መንፈሳዊ በድንነት የሚያጋልጡ ጽሑፎች ወጥተዋል።—ከኤርምያስ 5:14 ጋር አወዳድር።
17. (ሀ) በኤልያስ ዘመን ምን ድርቅንና እሳትን የሚመለከት ነገር ተፈጽሞ ነበር? (ለ) ከሁለቱ ምሥክሮች አፍ እሳት የወጣው እንዴት ነው? ስለ ምን ዓይነት ድርቅ ተናግረው ነበር?
17 ስለ ኤልያስስ ምን ሊባል ይቻላል? ይህ ነቢይ በእሥራኤል ነገሥታት ዘመን ይሖዋ የበአል አምላኪዎች በሆኑ እስራኤላውያን ላይ በመቆጣቱ ምክንያት ድርቅ እንደሚሆን ተናግሮ ነበር። ድርቁም ለሦስት ዓመት ተኩል የቆየ ነበር። (1 ነገሥት 17:1፤ 18:41-45፤ ሉቃስ 4:25፤ ያዕቆብ 5:17) ቆየት ብሎም ከሃዲው ንጉሥ አካዝያስ ኤልያስን አስገድደው እንዲያመጡለት ወታደሮች በላከ ጊዜ ነቢዩ እሳት ከሰማይ ወርዳ እንድትበላቸው አዝዞ ነበር። ኤልያስ ወደ ንጉሡ ለመሄድ የተስማማው የወታደሮቹ አዛዥ የይሖዋ ነቢይ ስለመሆኑ ተገቢ አክብሮት ካሳየ በኋላ ነበር። (2 ነገሥት 1:5-16) በተመሳሳይም ቅቡዓን ቀሪዎች ከ1914 እስከ 1918 በነበረው ጊዜ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ስላለው መንፈሣዊ ድርቅ አስታውቀዋል። ‘በሚያስፈራውና በታላቁ የይሖዋ ቀን’ እሳታማ ፍርድ እንደሚደርስባትም አስጠንቅቀዋል።—ሚልክያስ 4:1, 5፤ አሞጽ 8:11
18. (ሀ) ለሁለቱ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሥልጣን ተሰጥቶ ነበር? ይህስ ለሙሴ ተሰጥቶት ከነበረው ሥልጣን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? (ለ) ሁለቱ ምሥክሮች ሕዝበ ክርስትናን ያጋለጡት እንዴት ነው?
18 ዮሐንስ ስለ ሁለቱ ምሥክሮች የሚቀጥለውን ተናግሮአል:- “ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው።” (ራእይ 11:6ለ) ይሖዋ ፈርኦን እስራኤልን እንዲለቅ ለማስገደድ ሲል በሙሴ ተጠቅሞ በጨቋኝዋ በግብፅ ምድር ላይ መቅሰፍት አውርዶ ነበር። ከመቅሰፍቶቹ አንዱ ውኃውን ወደ ደም መለወጥ ነበር። ከብዙ ዘመናት በኋላ የእስራኤላውያን ጠላቶች የነበሩት ፍልስጥኤማውያን ይሖዋ በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ይህን ድርጊት አስታውሰው “ከዚህ ኃያል አምላክ ማን ሊያድነን ይችላል? ግብፃውያንን በምድረበዳ የመታ [“የቀሰፈ፣” ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን] ይህ አምላክ አይደለምን?” ብለው ጮኸዋል። (1 ሳሙኤል 4:8 NW፤ መዝሙር 105:29) ሙሴ በዘመናችን ሃይማኖታዊ መሪዎች ላይ የሚመጣውን የአምላክ ፍርድ ለማወጅ ሥልጣን የተሰጠውን ኢየሱስን ያመለክታል። (ማቴዎስ 23:13፤ 28:18፤ ሥራ 3:22) አንደኛው የዓለም ጦርነት በተደረገበት ጊዜም የክርስቶስ ወንድሞች ማለትም ሁለቱ ምሥክሮች ሕዝበ ክርስትና ለመንጎችዋ የምትሰጠው “ውኃ” ነፍሰ ገዳይና ቀሳፊ መሆኑን አጋልጠዋል።
ሁለቱ ምሥክሮች ተገደሉ
19. የራእይ መጽሐፍ በሚሰጠው መግለጫ መሠረት ሁለቱ ምሥክሮች የምሥክርነት ሥራቸውን ሲፈጽሙ ምን ይሆናል?
19 ይህ በሕዝበ ክርስትና ላይ የወረደው መቅሰፍት በጣም ከባድ ስለነበረ ሁለቱ ምሥክሮች ለ42 ወራት ማቅ ለብሰው ከመሰከሩ በኋላ ሕዝበ ክርስትና ባላት ዓለማዊ ተደማጭነት ተጠቅማ ‘አስገደለቻቸው።’ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፎአል:- “ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል ያሸንፋቸውማል ይገድላቸውማል። በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት። ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኩል በድናቸውን ይመለከታሉ፣ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም። እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል በደስታም ይኖራሉ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ።”— ራእይ 11:7-10
20. “ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ” ምንድን ነው?
20 ‘አውሬ’ የሚለው ቃል በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው 37 ጊዜ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው ጊዜ መሆኑ ነው። ስለዚህኛውም ሆነ ስለተቀሩት ሌሎች አውሬዎች ቆየት ብለን እንመረምራለን። ለአሁኑ ግን “ከጥልቁ የወጣው አውሬ” ሰይጣን የፈጠረው ሕያው የፖለቲካ ሥርዓት ነው ማለት ብቻ ይበቃናል።b—ከራእይ 13:1ና ከዳንኤል 7:2, 3, 17 ጋር አወዳድር።
21. (ሀ) የሁለቱ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ጠላቶች ጦርነቱ በፈጠረው ሁኔታ የተጠቀሙት እንዴት ነው? (ለ) የሁለቱ ምሥክሮች አስከሬን ሳይቀበር መቅረቱ ምን ያመለክታል? (ሐ) የሦስት ቀን ተኩሉን የጊዜ ርዝመት እንዴት መረዳት ይኖርብናል? (የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።)
21 ከ1914 እስከ 1918 ድረስ በነበረው ጊዜ ብሔራት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ተወጥረው ነበር። የብሔረተኝነት ስሜት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ ነበር። በ1918 የጸደይ ወራት የሁለቱ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ጠላቶች በተፈጠረው ሁኔታ ለመጠቀም ተነሱ። የመንግሥታትን ሕጋዊ መሣሪያዎች በመጠቀም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ መካከል በኃላፊነት የሚሰሩ አገልጋዮችን በሐገር ክህደት የሐሰት ክስ አስወንጅለው አሳሰሩ። በታማኝነት ይተባበሩአቸው የነበሩ ባልደረቦቻቸው በነገሩ ተደናገጡ። የመንግሥቱ ሥራ የቆመ ያህል መሰለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት በመታሰቢያ መቃብር ውስጥ አለመቀበርና በውጭ መጣል ትልቅ ውርደት ነበር። (መዝሙር 79:1-3፤ 1 ነገሥት 13:21, 22) ስለዚህ ሁለቱ ምሥክሮች አለመቀበራቸው ትልቅ ውርደት እንደሚደርስባቸው ያመለክታል። በጣም ሞቃት በሆነው የፓለስጢና አየር ጠባይ በመንገድ ላይ የተጣለ አስከሬን ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ መሽተት ይጀምራል።c (ከዮሐንስ 11:39 ጋር አወዳድር።) እነዚህ በትንቢቱ ውስጥ የተነገሩት ዝርዝር ጉዳዮች ሁለቱ ምሥክሮች የሚደረስባቸውን ከፍተኛ ውርደት ያመለክታሉ። ከላይ የጠቀስናቸው አገልጋዮች ጉዳያቸው በይግባኝ በሚታይበት ጊዜ እንኳን የዋስ መብት ተነፍጎአቸው ነበር። “በታላቂቱ ከተማ” ለሚኖሩት ሰዎች እስኪሸቱ ድረስ በአደባባይ ተጋልጠዋል። ይሁን እንጂ ይህች “ታላቅ ከተማ” ማን ነች?
22. (ሀ) ታላቂቱ ከተማ ምንድን ነች? (ለ) ሁለቱ ምሥክሮች ፀጥ እንዲሉ በመደረጋቸው የሕዝብ ጋዜጦች ከቀሳውስት ጋር በመተባበር ደስ መሰኘታቸውን የገለጹት እንዴት ነው? (ሣጥኑን ተመልከት።)
22 ዮሐንስ አንዳንድ ፍንጭ ሰጥቶናል። ኢየሱስ በዚህች ከተማ እንደተሰቀለ ተናግሮአል። ይህን ሲለን ወዲያውኑ ወደ አእምሮአችን የምትመጣው ከተማ ኢየሩሳሌም ነች። በተጨማሪም ታላቂቱ ከተማ ሰዶምና ግብጽ ተብላ እንደምትጠራ ተናግሮአል። የጥንትዋ ኢየሩሳሌም በመጥፎ ድርጊቶችዋ ምክንያት ሰዶም ተብላ የተጠራችበት ጊዜ ነበር። (ኢሳይያስ 1:8-10፤ ከሕዝቅኤል 16:49, 53-58 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በላይ የመጀመሪያዋ የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረችው ግብጽ የዚህ ዓለማዊ ሥርዓት ምሳሌ የሆነችባቸው ጊዜያት አሉ። (ኢሳይያስ 19:1, 19፤ ኢዩኤል 3:19) ስለዚህ ይህች ታላቅ ከተማ አምላክን አመልካለሁ እያለች እንደ ሰዶም በአምላክ ፊት እርኩስና ኃጢአተኛ ሆና የተገኘችውን “ኢየሩሳሌም” ታመለክታለች። የከሃዲዋ ኢየሩሳሌም ዘመናዊ እኩያ የሆነችው የሕዝበ ክርስትና ምሳሌ ነች። የሕዝበ ክርስትና አባሎች ሰላም ያሳጣቸውን የሁለቱን ምሥክሮች ስብከት ጸጥ ለማሰኘት በመቻላቸው በጣም ተደስተዋል።
እንደገና ተነሱ!
23. (ሀ) ከሦስት ቀን ተኩል በኋላ ሁለቱ ምሥክሮች ምን ሆኑ? ይህስ ጠላቶቻቸው ምን እንዲሰማቸው አደረገ? (ለ) ራእይ 11:11, 12 እና ይሖዋ በሸለቆ ውስጥ በነበሩት ደረቅ አጥንቶች ላይ እፍ ስለ ማለቱ የሚናገረው የሕዝቅኤል ትንቢት ዘመናዊ ፍጻሜያቸውን ያገኙት መቼ ነው?
23 ታላላቅ ጋዜጦችም የአምላክን ሕዝቦች በመንቀፍ ከቀሳውስት ጋር ተባብረዋል። አንድ ጋዜጣ “ያለቀለት ምሥጢር አለቀለት!” ብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ አባባል ነበር። ሁለቱ ምሥክሮች እንደሞቱ አልቀሩም። እንዲህ እናነባለን:- “ከሦስቱ ቀን ተኩልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ፣ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው። በሰማይም:- ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ።” (ራእይ 11:11, 12) ስለዚህ ሕዝቅኤል በራእይ ተመልክቶት በነበረው ሸለቆ ውስጥ የነበሩት አጽሞች ያጋጠማቸውን የመሰለ ሁኔታ አጋጠማቸው። በእነዚህ ደረቅ አጽሞች ላይ ይሖዋ እፍ አለባቸውና ሕያው ሆኑ። ይህም የሆነው የእስራኤል ብሔር በባቢሎን ለ70 ዓመት በግዞት ከቆየ በኋላ እንደገና የሚወለድ መሆኑን ለማመልከት ነበር። (ሕዝቅኤል 37:1-14) እነዚህ የሕዝቅኤልና የራእይ ሁለት ትንቢቶች ዘመናዊ ፍጻሜያቸውን ያገኙት ይሖዋ ‘ሞተው’ የነበሩትን ምሥክሮቹን አዲስ ሕይወትና ኃይል ሰጥቶ ባስነሳበት በ1919 ነበር።
24. ሁለቱ ምሥክሮች ሕያዋን በሆኑ ጊዜ ሃይማኖታዊ አሳዳጆቻቸው ምን ተሰማቸው?
24 አሳዳጆቹን ምን ያህል የሚያስደነግጥ ነገር ነበር! የሁለቱ ምሥክሮች አጥንቶች በድንገት ሕያው ሆነው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ለቀሳውስቱ ሊዋጥ የማይችል መራራ ኪኒን ሆኖባቸው ነበር። በእነርሱ ሴራ ምክንያት ታስረው የነበሩት አገልጋዮች ከእስር መውጣታቸውና ከቀረበባቸው ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ መደረጋቸው ይበልጡኑ መራራ ሆነባቸው። በተጨማሪም በ1919 የመስከረም ወር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩ ኤስ ኤ ከፍተኛ ስብሰባ ባደረጉ ጊዜ ትልቅ ድንጋጤ ወደቀባቸው። ትንሽ ቀደም ብሎ ከእሥራት የተፈታው ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ በዚህ ስብሰባ ላይ “መንግሥቱን ማስታወቅ” በተባለው ንግግሩ ተሰብሳቢዎቹን ለሥራ አነሳስቶአቸዋል። ይህ ንግግር በራእይ 15:2 እና በኢሳይያስ 52:7 ላይ የተመሠረተ ነበር። የዮሐንስ ክፍል አባሎች እንደገና ትንቢት መናገር ወይም በይፋ ለሕዝብ መስበክ ጀመሩ። በድፍረት የሕዝበ ክርስትናን ግብዝነት እያጋለጡ በብርታት ላይ ብርታት ጨመሩ።
25. (ሀ) ሁለቱ ምሥክሮች “ወደዚህ ውጡ” የተባሉት መቼ ነበር? ይህስ የተፈጸመው እንዴት ነው? (ለ) የሁለቱ ምሥክሮች ወደ ሕይወት መመለስ በታላቂቱ ከተማ ላይ እንዴት ያለ ድንጋጤ አመጣ?
25 ሕዝበ ክርስትና በ1918 አግኝታ የነበረውን ድል ለማግኘት በተደጋጋሚ ሞክራ ነበር። ረብሻ በማነሳሳት፣ ሕጎችን በማጣመም፣ በማሳሰርና በማስገደልም ጭምር የተቻላትን ሁሉ አደረገች። ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ አልተሳካላትም። ከ1919 በኋላ የሁለቱ ምሥክሮች መንፈሳዊ ግዛት በሕዝበ ክርስትና ሊደፈር በማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። ይሖዋ በዚህ ዓመት ለሕዝቦቹ “ወደዚህ ውጡ” አላቸው። እነርሱም ትዕዛዙን ተቀብለው ጠላቶቻቸው ሊመለከቱት እንጂ መንካት ወደማይችሉበት ከፍተኛ መንፈሳዊ ደረጃ ላይ ወጡ። በዚህ ዓይነት እንደገና መቋቋማቸው በታላቂቱ ከተማ ላይ ስላስከተለው ድንጋጤ ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል:- “በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፣ ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ ወደቀ፣ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፣ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፣ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ።” (ራእይ 11:13) በሃይማኖት ዓለም ውስጥ ታላቅ መናወጥ ሆኖ ነበር። እነዚህ ሕያው የተደረጉ ክርስቲያኖች ሥራቸውን ማከናወን በጀመሩ ጊዜ ተቋቁመው የኖሩት ሃይማኖቶች መሪዎች የቆሙበት መሬት ከሥራቸው የከዳቸው መስሎ ነበር። የከተማቸው አንድ አሥረኛና ምሳሌያዊ 7,000 ሰዎች በነገሩ በጣም ስለተነኩ እንደተገደሉ ተነግሮአል።
26. በከተማው አሥረኛና በራእይ 11:13 ላይ በተጠቀሱት “ሰባት ሺህ” ሰዎች የተመሰሉት እነማን ናቸው? አስረዳ።
26 “ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ” የሚለው ሐረግ ኢሳይያስ ስለ ጥንትዋ ኢየሩሳሌም ትንቢት በተናገረ ጊዜ የከተማው አሥረኛ እጅ ቅዱስ ዘር ሆኖ ከጥፋቱ እንደሚተርፍ የተናገረውን ያስታውሰናል። (ኢሳይያስ 6:13) በተመሳሳይም 7,000 የሚለው ቁጥር ኤልያስ በእስራኤል ምድር በታማኝነት የጸና እርሱ ብቻ እንደሆነ በተሰማው ጊዜ ገና ለበአል ያልሰገዱ 7,000 ታማኝ ሰዎች እንዳሉት ይሖዋ እንደተናገረ ያስታውሰናል። (1 ነገሥት 19:14, 18) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህ 7,000 ሰዎች የክርስቶስን ምሥራች ለተቀበሉት አይሁዳውያን ቀሪዎች ምሳሌ እንደሚሆኑ ተናግሮ ነበር። (ሮሜ 11:1-5) እነዚህ ጥቅሶች በራእይ 11:13 ላይ የተጠቀሱት “ሰባት ሺህ ሰዎች” እና የከተማው “አሥረኛ እጅ” የሁለቱን ምሥክሮች መልእክት ተቀብለው ከኃጢአተኛዋ ታላቅ ከተማ የወጡትን ሰዎች እንደሚያመለክት ያስረዳናል። እነዚህ ሰዎች ለሕዝበ ክርስትና እንደሞቱ ያህል ነው። ስማቸው ከአባሎችዋ መዝገብ ተፍቆአል። ለሕዝበ ክርስትና ሙታን ሆነዋል።d
27, 28. (ሀ) ‘የቀሩት የሰማይን አምላክ ያከበሩት’ እንዴት ነው? (ለ) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ምንን አምነው ለመቀበል ተገድደው ነበር?
27 ይሁን እንጂ የቀሩት የሕዝበ ክርስትና ክፍሎች ‘ለሰማይ አምላክ ክብር የሰጡት’ እንዴት ነው? ከክህደት ሃይማኖታቸው ወጥተው የአምላክ አገልጋዮች በመሆን እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ አምላክን ያከበሩት የቫንሳንት የአዲስ ኪዳን የቃላት ጥናት “ለሰማዩ አምላክ ክብር ሰጡ” የሚለውን ሐረግ ሲያብራራ በገለጸው መንገድ ነው። በዚህ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተብሎአል:- “ሐረጉ የሚያመለክተው መለወጥን ወይም ንስሐ መግባትን ወይም ምስጋና ማቅረብን አይደለም። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በብዙ ቦታዎች እንደተገለጸው አምኖ መቀበልን ያመለክታል። ከኢያሱ 7:19፤ ከዮሐንስ 9:24፤ ከሥራ 12:23ና ከሮሜ 4:20 ጋር አወዳድር።” ሕዝበ ክርስትና በንዴት ብትቃጠልም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የሚያመልኩት አምላክ እነርሱን ወደ ክርስቲያናዊ ሥራቸው በመመለስ ታላቅ ነገር እንዳደረገ ለመቀበል ተገድዳለች።
28 ቀሳውስቱ ይህን የተቀበሉት ወይም ያመኑት በራሳቸው አእምሮ ብቻ ሊሆን ይችላል። አንዳቸውም ቢሆኑ የሁለቱን ምሥክሮች አምላክ በይፋ እንደተቀበሉ የሚያረጋግጥ ማስረጃ አናገኝም። ቢሆንም ይሖዋ በዮሐንስ በኩል የተናገረው ትንቢት በ1919 በልባቸው ውስጥ ምን ተሰምቶአቸው እንደነበረና ምን ያህል እፍረትና ድንጋጤ ወድቆባቸው እንደነበረ እንድናስተውል ይረዳናል። ከዚያ ዓመት ጀምሮ ሕዝበ ክርስትና በጎችዋን እንደያዘች ለመቆየት ምንም ያህል ጥረት ብታደርግ ‘ሰባት ሺህዎቹ’ ሰዎች ጥለዋት መውጣት ሲጀምሩ የዮሐንስ ክፍል አባሎች የሚያመልኩት አምላክ ከራሳቸው አምላክ እንደሚበልጥ ቀሳውስቱ ለመቀበል ተገድደዋል። በሚቀጥሉትም ዓመታት ከመንጎቻቸው ብዙዎቹ ጥለዋቸው ስለ ወጡ ይህን ቁምነገር በበለጠ ግልጽነት ለመረዳት ችለዋል። ይህም ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ በበአል አምላኪዎች ላይ ድል ሲጎናጸፍ ሕዝቡ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ አምላክ ነው! እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] እርሱ አምላክ ነው!” እያሉ ያሰሙትን ጨኸት የሚያስተጋባ ይሆናል።—1 ነገሥት 18:39
29. ዮሐንስ ምን ነገር ፈጥኖ እንደሚመጣ ገለጸ? ሕዝበ ክርስትናስ ምን ተጨማሪ ነውጥ ይጠብቃታል?
29 አሁን ግን ሌላ ነገር እናዳምጥ! ዮሐንስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፣ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል።” (ራእይ 11:14) ሕዝበ ክርስትና እስከዚህ ጊዜ ድረስ በሆነው ነገር ይህን ያህል ከተናወጠች ሶስተኛው ወዮታ ሲነገር ምን ታደርግ ይሆን? ሰባተኛው መልአክ መለከቱን ይነፋል፣ የአምላክ ቅዱስ ምሥጢርም ይፈጸማል።—ራእይ 10:7
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት በሐምሌ 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም በታኅሣሥ 1, 1972 (እንግሊዝኛ) መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “አምልኮ የሚፈጸምበት እውነተኛ ቤተ መቅደስ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b “ጥልቁ” (በግሪክኛ አቢሶስ፣ በዕብራይስጥ ቴሆሂም) ምንም ዓይነት ሥራ የማይኖርበትን ሥፍራ ያመለክታል። (ራእይ 9:2ን ተመልከት።) ይሁን እንጂ ቃል በቃል ሲወሰድ ሰፊውን ባሕር ሊያመለክት ይችላል። የዕብራይስጡ ቃል አብዛኛውን ጊዜ “ጥልቅ ባሕር” ተብሎ ይተረጎማል። (መዝሙር 71:20 NW፤ መዝሙር 106:9፤ ዮናስ 2:5 [2:4 የ1954 እትም]) ስለዚህ “ከጥልቁ የወጣው አውሬ” “ከባሕር ውስጥ ከወጣው አውሬ” ጋር አንድ ነው ሊባል ይችላል።—ራእይ 11:7፤ 13:1
c በዚህ ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ያጋጠማቸውን ተሞክሮ በምንመረምርበት ጊዜ 42ቱ ወራት ቃል በቃል የሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ የሚያመለክቱ እንደሆኑ ብንገነዘብም ሦስት ቀን ተኩሉ ግን ቃል በቃል የ84 ሰዓት ጊዜ አያመለክትም። የሦስት ቀን ተኩል ጊዜ ሁለት ጊዜ የተጠቀሰው (ቁጥር 9 እና 11 ላይ) ከዚያ በፊት ከነበረው የሦስት ዓመት ጊዜ ጋር ሲወዳደር አጭር ጊዜ እንደሚሆን ለማመልከት ይመስላል።
d እንደ ሮሜ 6:2, 10, 11፤ 7:4, 6, 9፤ ገላትያ 2:19፤ ቆላስይስ 2:20፤ 3:3 ባሉት ጥቅሶች ላይ “ሙታን”፣ “መሞት” እና “መኖር” የሚሉት ቃላት እንዴት እንደተሰራባቸው አወዳድር።
[በገጽ 168 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የራእይ 11:10 ደስታ
ሬይ ኤች አብራምስ በ1933 በታተመ ሰባኪያን የጦር መሣሪያ ሲያቀርቡ በተባለው መጽሐፋቸው ቀሳውስት ያለቀለት ምሥጢር የተባለውን በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተዘጋጀ መጽሐፍ ምን ያህል አምርረው እንደተቃወሙ ገልጸዋል። ቀሳውስት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችንና የእነርሱን “ቸነፈራዊ ትምህርት” ለማስወገድ እንዴት እንደጣሩ አብራርተዋል። በዚህም ምክንያት ለጄ ኤፍ ራዘርፎርድና ለሰባት ባልንጀሮቹ የረዥም ዓመት የእስራት ፍርድ ምክንያት የሆነው ክስ ተመሠረተ። ዶክተር አብራምስ “ጉዳዩን ጠለቅ ብለን ስንመረምር ራስላውያንን ፈጽሞ ለመደምሰስ በተደረገው ጥረት የአብያተ ክርስቲያናትና የቀሳውስት እጅ እንዳለበት ለመረዳት እንችላለን። በካናዳ አገር በየካቲት ወር 1918 ቀሳውስት በእነዚህ ሰዎችና በጽሑፎቻቸው ላይ በተለይም ያለቀለት ምሥጢር በተባለው መጽሐፍ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ማካሄድ ጀመሩ። የዊኒፔግ ትሪቢዩን እንዳለው . . . መጽሐፋቸው ሊታገድ የቻለው በቀሳውስት ተጽእኖ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።”
ዶክተር አብራምስ እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ:- “የሃያው ዓመት የእስራት ፍርድ የመወሰኑ ዜና ለሃይማኖታዊ ጋዜጦች አዘጋጆች በደረሰ ጊዜ ሁሉም ከትልቅ እስከ ትንሽ ድረስ በጣም ተደሰቱ። በየትኛውም የሃይማኖት ጽሑፍ የሐዘኔታ ቃል ለማግኘት አልቻልኩም። አፕቶን ሲንክልየር እንዳለው ‘ለስደቱ መነሳት በከፊል ምክንያት የሆነው የታወቁት ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ጥላቻ እንደነበረ አያጠራጥርም።’ አብያተ ክርስቲያናት በቅንጅት ያደረጉት ጥረት መፈጸም ያልቻለውን አሁን መንግሥት ሊፈጽምላቸው የቻለ መሰለ።” ጸሐፊው የብዙ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን የነቀፌታ ቃላት ከጠቀሱ በኋላ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ቀድሞ የተሰጠውን ፍርድ መሻሩን ጠቀሱና “አብያተ ክርስቲያናት ውሳኔውን በዝምታ ተቀበሉት” ብለዋል።
[በገጽ 163 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሐንስ መንፈሳዊውን ቤተ መቅደስ ለካ፣ ቅቡዓኑ ካህናት የአቋም ደረጃዎችን መጠበቅ አለባቸው
[በገጽ 165 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዘሩባቤልና ኢያሱ ያከናወኑት የግንባታ ሥራ በጌታ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ከአነስተኛ ሁኔታ ተነስተው ትልቅ ጭማሪ እንደሚያገኙ ያመለክታል። እያደገ የሄደውን ፍላጎት ለማሟላት ሲባል በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኙትን ከላይ የሚታዩትን የመሳሰሉ ሕንጻዎች ማስፋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል
[በገጽ 166 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሙሴና ኤልያስ ያወጁት ትንቢታዊ መልእክት ሁለቱ ምሥክሮች ለሚያውጁት የእሳታማ የፍርድ መልእክት ጥላ ሆኖአል
[በገጽ 169 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሁለቱ ምሥክሮች በሕዝቅኤል ምዕራፍ 37 ላይ እንደተጠቀሱት የደረቁ አጥንቶች አዲስ ሕይወት አግኝተው ለዘመናዊው የስብከት ሥራ ተነሳሱ