ይሖዋ ‘ሚስጥር ገላጭ ነው’
“በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክና የነገሥታት ጌታ፣ ምስጢርንም ገላጭ ነው።”—ዳን. 2:47
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ዝርዝር ጉዳዮችን ገልጦልናል?
ስድስቱ የአውሬው ራሶች ምን ያመለክታሉ?
በአውሬውና ናቡከደነፆር በተመለከተው ምስል መካከል ምን ተዛማጅነት አለ?
1, 2. ይሖዋ ምን ነገር ገልጦልናል? ለምንስ?
የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሚያጠፋበት ወቅት የዓለም ኃያል መንግሥት የሚሆኑት እነማን ናቸው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ቀላል ነው፤ ምክንያቱም ‘ሚስጥር ገላጭ’ የሆነው ይሖዋ አምላክ የእነዚህን መንግሥታት ማንነት ነግሮናል። ይህን ያደረገው ነቢዩ ዳንኤል እና ሐዋርያው ዮሐንስ በጻፏቸው መጻሕፍት አማካኝነት ነው።
2 ይሖዋ ለእነዚህ አገልጋዮቹ በተከታታይ የሚነሱ አራዊትን በራእይ አሳይቷቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ናቡከደነፆር በሕልም የተመለከተው ግዙፍ ምስል ምን ትርጉም እንዳለው ለዳንኤል ገልጦለታል። ይሖዋ እነዚህ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍሩና ተጠብቀው እንዲቆዩ ያደረገው ለእኛ ጥቅም ሲል ነው። (ሮም 15:4) በተጨማሪም ይህን ያደረገው የእሱ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በቅርቡ እንደሚያደቃቸው ያለንን ተስፋ ለማጠናከር ነው።—ዳን. 2:44
3. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች በትክክል ለመረዳት በቅድሚያ ስለ ምን ነገር መገንዘብ ይኖርብናል? ለምንስ?
3 የዳንኤልና የዮሐንስ ዘገባዎች በምድር ላይ የሚነሱትን ስምንት ነገሥታት ወይም ሰብዓዊ አገዛዞች ለይተን እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ነገሥታት የሚነሱበትን ቅደም ተከተል ማስተዋል እንድንችልም ይረዱናል። ይሁንና እነዚህን ትንቢቶች በትክክል መረዳት የምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የመጀመሪያው ትንቢት ምን ትርጉም እንዳለው መገንዘብ ከቻልን ብቻ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክትም ሆነ በውስጡ ያሉት ትንቢቶች በመጀመሪያው ትንቢት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። በሌላ አባባል ይህን ትንቢት እንደ ገመድ ብንቆጥረው ሌሎች ትንቢቶች በሙሉ የተንጠለጠሉት በዚህ ገመድ ላይ ነው ሊባል ይችላል።
የእባቡ ዘርና አውሬው
4. የሴቲቱ ዘር ክፍል እነማን ናቸው? ይህ ዘርስ ምን ነገር ያከናውናል?
4 በኤደን ዓመፅ ከተነሳ በኋላ ወዲያውኑ ይሖዋ ‘ሴቲቱ ዘር’ እንደምታስገኝ ቃል ገባ።a (ዘፍጥረት 3:15ን አንብብ።) የሴቲቱ ዘር ወደፊት የእባቡን ማለትም የሰይጣንን ራስ ይቀጠቅጣል። ይህ ዘር በአብርሃም በኩል እንደሚመጣ፣ ከእስራኤል ብሔር ወገን እንደሚሆን እንዲሁም በይሁዳ የዘር ሐረግና በንጉሥ ዳዊት የትውልድ መስመር በኩል እንደሚመጣ ይሖዋ ከጊዜ በኋላ አሳውቋል። (ዘፍ. 22:15-18፤ 49:10፤ መዝ. 89:3, 4፤ ሉቃስ 1:30-33) በኋላም የዚህ ዘር ዋነኛ ክፍል ክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ ተገኘ። (ገላ. 3:16) በመንፈስ የተቀቡ የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ደግሞ የዘሩ ሁለተኛ ክፍል ሆኑ። (ገላ. 3:26-29) ኢየሱስና ቅቡዓኑ በአንድነት የአምላክን መንግሥት ይመሠርታሉ፤ አምላክም ሰይጣንን ለመቀጥቀጥ ይህን መንግሥት መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል።—ሉቃስ 12:32፤ ሮም 16:20
5, 6. (ሀ) ዳንኤልና ዮሐንስ የጠቀሱት ስንት ኃያላን መንግሥታትን ነው? (ለ) በራእይ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው አውሬ ራሶች ምን ያመለክታሉ?
5 በኤደን የተነገረው የመጀመሪያው ትንቢት ሰይጣንም የራሱን “ዘር” እንደሚያስገኝ ይገልጻል። ይህ ዘር፣ ለሴቲቱ ዘር ጠላትነት እንደሚኖረውም ያሳያል። ለመሆኑ የእባቡ ዘር ክፍል እነማን ናቸው? የሰይጣንን መንገድ በመከተል አምላክን የሚጠሉና ሕዝቡን የሚቃወሙ ሁሉ ከእባቡ ዘር ክፍል ይመደባሉ። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰይጣን በተለያዩ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ወይም መንግሥታት አማካኝነት ዘሩን ሲያደራጅ ቆይቷል። (ሉቃስ 4:5, 6) ይሁን እንጂ በአምላክ ሕዝቦች ይኸውም በእስራኤል ብሔርም ሆነ በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩት ሰብዓዊ መንግሥታት በጣም ጥቂት ናቸው። ይህን ሐቅ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ዳንኤልና ዮሐንስ በተመለከቷቸው ራእዮች ላይ ስምንት ኃያላን መንግሥታት ብቻ የተጠቀሱት ለምን እንደሆነ ግልጽ ስለሚያደርግልን ነው።
6 ከሞት የተነሳው ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ አስደናቂ ራእዮችን ለሐዋርያው ዮሐንስ አሳይቶታል። (ራእይ 1:1) በአንደኛው ራእይ ላይ፣ በዘንዶ የተመሰለው ዲያብሎስ በባሕር አሸዋ ላይ እንደቆመ ዮሐንስ ተመልክቶ ነበር። (ራእይ 13:1, 2ን አንብብ።) በተጨማሪም ዮሐንስ ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣና ከዲያብሎስ ከፍተኛ ሥልጣን ሲቀበል ተመልክቷል። በኋላም ዮሐንስ መልኩ ቀይ የሆነና ልክ እንደ መጀመሪያው አውሬ ሰባት ራሶች ያሉት ሌላ አውሬ የተመለከተ ሲሆን ይህ ቀይ አውሬ በራእይ 13:1 ላይ ያለው አውሬ ምስል ነው። የቀዩ አውሬ ሰባት ራሶች ‘ሰባት ነገሥታትን’ ወይም መንግሥታትን እንደሚያመለክቱ አንድ መልአክ ለዮሐንስ ነግሮታል። (ራእይ 13:14, 15፤ 17:3, 9, 10) ዮሐንስ ራእዩን በጻፈበት ወቅት አምስቱ ወድቀው ነበር፤ አንዱ በሥልጣን ላይ የነበረ ሲሆን “ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም።” ለመሆኑ እነዚህ የዓለም ኃያላን መንግሥታት እነማን ናቸው? እስቲ በዚህ ራእይ ውስጥ የተጠቀሱትን ራሶች አንድ በአንድ እንመርምር። ከዚህም ሌላ ስለ አብዛኞቹ መንግሥታት ተጨማሪ ማብራሪያ ከዳንኤል መጽሐፍ እንመለከታለን። ዳንኤል ይህን ዝርዝር ሐሳብ የጻፈው እነዚህ መንግሥታት ከመነሳታቸው ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ነው።
ግብፅና አሦር—የመጀመሪያዎቹ ሁለት ራሶች
7. የመጀመሪያው ራስ የሚወክለው ማንን ነው? ለምንስ?
7 የአውሬው የመጀመሪያ ራስ ግብፅን ይወክላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለአምላክ ሕዝቦች ጠላትነት ያሳየችው የመጀመሪያዋ ኃያል መንግሥት ግብፅ ነበረች። የሴቲቱ ዘር መገኛ የሆኑት የአብርሃም ዘሮች በግብፅ ቁጥራቸው እጅግ እየበዛ ሄዶ ነበር። በዚህ ጊዜ የግብፅ መንግሥት እስራኤላውያንን መጨቆን ጀመረ። ሰይጣን የሴቲቱ ዘር ከመምጣቱ በፊት የአምላክን ሕዝብ ጨርሶ ለማጥፋት ሞክሮ ነበር። እንዴት? እስራኤላዊ የሆኑ ወንድ ሕፃናትን እንዲገድል ፈርዖንን በማነሳሳት ነው። ይሖዋ ግን ይህ የሰይጣን እቅድ እንዲከሽፍ ያደረገ ሲሆን ሕዝቡንም ከግብፅ ባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። (ዘፀ. 1:15-20፤ 14:13) ከጊዜ በኋላም እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር እንዲወርሱ አድርጓቸዋል።
8. ሁለተኛው ራስ የሚወክለው ማንን ነው? ምን ሙከራስ አድርጓል?
8 የአውሬው ሁለተኛ ራስ ደግሞ አሦርን ይወክላል። ይህ ኃያል መንግሥትም ቢሆን የአምላክን ሕዝቦች ጠራርጎ ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል። እርግጥ ነው፣ አሥሩን ነገድ ያቀፈው የእስራኤል መንግሥት ወደ ጣዖት አምልኮ ዘወር ባለበትና ባመፀበት ወቅት ይሖዋ የአሦርን መንግሥት ተጠቅሞ ቀጥቶት ነበር። ይሁንና አሦር በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ሰነዘረ። በዚህ ወቅት ሰይጣን፣ ኢየሱስ የሚመጣበትን ንጉሣዊ የዘር ሐረግ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አስቦ ሊሆን ይችላል። አሦር በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት እንዲሰነዝር ግን ይሖዋ አልፈለገም፤ በመሆኑም ይሖዋ ይህን ወራሪ ጠላት በማጥፋት ታማኝ ሕዝቦቹን ተአምራዊ በሆነ መንገድ አድኗቸዋል።—2 ነገ. 19:32-35፤ ኢሳ. 10:5, 6, 12-15
ባቢሎን—ሦስተኛው ራስ
9, 10. (ሀ) ይሖዋ ለባቢሎናውያን ምን እንዲያደርጉ ፈቅዶላቸዋል? (ለ) ይሖዋ የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ከተፈለገ ምን ነገር መከናወን ይኖርበታል?
9 ዮሐንስ በተመለከተው አውሬ ላይ የነበረው ሦስተኛው ራስ የሚወክለው የባቢሎንን መንግሥት ነው። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን እንዲያጠፉና ሕዝቧን በግዞት እንዲወስዱ ይሖዋ ፈቅዶላቸው ነበር። ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ከመከሰቱ በፊት ግን ይሖዋ ጥፋት እንደሚያመጣባቸው ዓመፀኞቹን እስራኤላውያንን አስጠንቅቋቸዋል። (2 ነገ. 20:16-18) በእሱ “ዙፋን” ላይ እንደተቀመጡ ተደርገው የሚቆጠሩት ሰብዓዊ ነገሥታት፣ በኢየሩሳሌም ሆነው መግዛታቸውን እንደሚያቆሙም አስቀድሞ ተናግሯል። (1 ዜና 29:23) በተጨማሪም ይሖዋ “ባለ መብት” የሆነው የንጉሥ ዳዊት ዘር እንደሚመጣና በእሱ ዙፋን ላይ እንደሚቀመጥ ቃል ገብቷል።—ሕዝ. 21:25-27
10 አንድ ሌላ ትንቢት እንደሚጠቁመው ደግሞ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ (የተቀባ የሚል ትርጉም አለው) በሚመጣበት ጊዜም ጭምር አይሁዳውያን ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ይሖዋን ማምለካቸውን ይቀጥላሉ። (ዳን. 9:24-27) ከዚህ ቀደም ሲል ማለትም እስራኤላውያን በምርኮ ወደ ባቢሎን ከመወሰዳቸው በፊት የተጻፈ አንድ ትንቢት ደግሞ መሲሑ በቤተልሔም እንደሚወለድ ተናግሮ ነበር። (ሚክ. 5:2) እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ከተፈለገ አይሁዳውያኑ ከግዞት ነፃ መውጣት፣ ወደ ትውልድ አገራቸው መመለስና ቤተ መቅደሱን በድጋሚ መገንባት ይኖርባቸዋል። ይሁንና የባቢሎን መንግሥት በግዞት የወሰዳቸውን ሰዎች ነፃ የመልቀቅ ልማድ አልነበረውም። ታዲያ ሕዝቡ ከግዞት ነፃ መውጣት የሚችሉት እንዴት ነው? ይሖዋ መልሱን ለነቢያቱ ገልጦላቸዋል።—አሞጽ 3:7
11. የባቢሎን መንግሥት በምን ነገሮች ተመስሏል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)
11 ነቢዩ ዳንኤል፣ በግዞት ወደ ባቢሎን ከተወሰዱት መካከል አንዱ ነው። (ዳን. 1:1-6) ይሖዋ ከባቢሎን በኋላ በተከታታይ ስለሚነሱት የዓለም ኃያላን መንግሥታት ለዳንኤል ገልጦለታል። ይሖዋ ይህን ሚስጥር ለዳንኤል የገለጠለት ተምሳሌት የሚሆኑ የተለያዩ ነገሮችን በመጠቀም ነው። ለአብነት ያህል፣ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከተለያዩ ማዕድናት የተሠራ አንድ ግዙፍ ምስል በሕልሙ እንዲመለከት አድርጎ ነበር። (ዳንኤል 2:1, 19, 31-38ን አንብብ።) ይሖዋ ዳንኤልን በመጠቀም የምስሉ የወርቅ ራስ የባቢሎንን መንግሥት እንደሚያመለክት ገለጠ።b ከባቢሎን በኋላ የተነሳው የዓለም ኃያል መንግሥት ደግሞ ከብር በተሠሩት የምስሉ ደረትና ክንዶች ተመስሏል። ይህ ኃያል መንግሥት ማን ነው? በአምላክ ሕዝቦች ላይስ ምን አድርጓል?
ሜዶ ፋርስ—አራተኛው ራስ
12, 13. (ሀ) ይሖዋ፣ ባቢሎን ድል ከምትደረግበት መንገድ ጋር በተያያዘ ምን ነገር ገልጧል? (ለ) ሜዶ ፋርስ በአውሬው አራተኛ ራስ መወከሉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ዳንኤል ከኖረበት ጊዜ አንድ መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ፣ ይሖዋ ባቢሎንን ድል ስለሚያደርገው የዓለም ኃያል መንግሥት ማንነት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ዝርዝር ጉዳዮችን ገልጦ ነበር። ይሖዋ የባቢሎን ከተማ እንዴት እንደምትያዝ ብቻ ሳይሆን ከተማዋን ድል የሚያደርገውን ሰው ስም ጭምር ጠቅሷል። ይህ ሰው ፋርሳዊው ቂሮስ ነው። (ኢሳ. 44:28 እስከ 45:2) ዳንኤል የሜዶ ፋርስን የዓለም ኃያል መንግሥት አስመልክቶ ሌሎች ሁለት ራእዮችን አይቷል። በአንደኛው ራእይ ላይ ይህ መንግሥት በአንድ ጐኑ ከፍ በሚል ድብ ተመስሏል። ይህ ድብ “እስክትጠግብ ድረስ ሥጋ ብላ!” ተብሎ ተነግሮታል። (ዳን. 7:5) በሌላ ራእይ ላይ ዳንኤል እንደተመለከተው ደግሞ ይህ ጥምር የዓለም ኃያል መንግሥት ሁለት ቀንድ ባለው አውራ በግ ተመስሏል።—ዳን. 8:3, 20
13 ይሖዋ በትንቢት ባስነገረው መሠረት ባቢሎናውያንን ለመገልበጥና እስራኤላውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ሜዶ ፋርስን ተጠቅሟል። (2 ዜና 36:22, 23) ይሁንና ይህ መንግሥት ከጊዜ በኋላ የአምላክን ሕዝብ ለማጥፋት ተቃርቦ ነበር። የፋርስ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ሐማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት ሴራ ጠንስሶ እንደነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የአስቴር መጽሐፍ ዘግቧል። ሐማ፣ ሰፊ በሆነው የፋርስ ግዛት ውስጥ የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ለማጥፋት ዝግጅት አድርጎ የነበረ ሲሆን ይህን የዘር ማጥፋት ዘመቻ የሚያደርግበትን ቀን ጭምር ወስኖ ነበር። በዚህ ወቅትም ቢሆን የአምላክ ሕዝቦች የሰይጣን ዘር ከሰነዘረባቸው ጥቃት ማምለጥ የቻሉት ይሖዋ ጣልቃ ስለገባ ነው። (አስ. 1:1-3፤ 3:8, 9፤ 8:3, 9-14) በመሆኑም የሜዶ ፋርስ መንግሥት በራእይ መጽሐፍ ላይ በተገለጸው አውሬ አራተኛ ራስ መወከሉ የተገባ ነው።
ግሪክ—አምስተኛው ራስ
14, 15. ይሖዋ ስለ ጥንቱ የግሪክ መንግሥት ምን ዝርዝር ነገሮችን ገልጦልናል?
14 በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው አውሬ አምስተኛ ራስ ግሪክን ይወክላል። ቀደም ሲል ዳንኤል ናቡከደነፆር ያየውን ሕልም አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ ላይ እንደተገለጸው ይህ አምስተኛ ራስ ከነሐስ በተሠሩት የምስሉ ሆድና ጭን ተመስሏል። በተጨማሪም ዳንኤል ስለዚህ ኃያል መንግሥትና ታዋቂ ስለሆነው የዚህ መንግሥት ገዥ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚገልጹ ሁለት አስደናቂ ራእዮችን ተቀብሏል።
15 ዳንኤል ባየው አንደኛው ራእይ ላይ ግሪክ አራት ክንፎች ባሉት ነብር የተመሰለ ሲሆን ይህ ደግሞ በፍጥነት ድል በማድረግ ግዛቱን እንደሚያስፋፋ የሚያመለክት ነው። (ዳን. 7:6) በሌላኛው ራእይ ላይ ደግሞ ዳንኤል አንድ ቀንድ ያለው ፍየል፣ ሁለት ቀንድ ያለውን አውራ በግ በፍጥነት ሲገድል ማለትም ሜዶ ፋርስን ሲደመስስ ተመልክቷል። ፍየሉ የግሪክን መንግሥት፣ የፍየሉ ትልቅ ቀንድ ደግሞ ከነገሥታቶቹ አንዱን እንደሚያመለክት ይሖዋ ለዳንኤል ነግሮታል። ዳንኤል ትልቁ ቀንድ እንደሚሰበርና በምትኩም አራት ትናንሽ ቀንዶች እንደሚበቅሉ ጽፏል። ይህ ትንቢት የተጻፈው የግሪክ መንግሥት ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ቢሆንም እያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ፍጻሜውን አግኝቷል። የጥንቱ ግሪክ ታዋቂ ንጉሥ የሆነው ታላቁ እስክንድር በሜዶ ፋርስ ላይ የዘመተውን ጦር መርቷል። ይሁንና ትልቁ ቀንድ ብዙም ሳይቆይ ተሰበረ፤ ይህ የሆነው ሰፊ ግዛቶችን የተቆጣጠረው ታላቁ እስክንድር በ32 ዓመቱ ሕይወቱ በአጭሩ በተቀጨ ጊዜ ነው። በኋላም ግዛቱ፣ ለአራት ጄኔራሎቹ ተከፋፈለ።—ዳንኤል 8:20-22ን አንብብ።
16. አንታይከስ አራተኛ ምን አድርጓል?
16 የግሪክ መንግሥት ፋርስን ድል ካደረገ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ይኖሩበት የነበረውን አካባቢ ተቆጣጠረ። በዚህ ወቅት አይሁዳውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር የተመለሱ ሲሆን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ እንደገና ገነቡ። በዚህ ጊዜም ቢሆን አይሁዳውያን የአምላክ የተመረጡ ሕዝቦች ነበሩ፤ እንዲሁም ቤተ መቅደሱ የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል መሆኑን ቀጥሎ ነበር። ሆኖም በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. የአውሬው አምስተኛ ራስ የሆነው ግሪክ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሰነዘረ። ከተከፋፈለው የእስክንድር ግዛት ውስጥ ከተነሱት ነገሥታት አንዱ የሆነው አንታይከስ አራተኛ ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ የጣዖት መሰዊያ ያቆመ ከመሆኑም በላይ የአይሁድን እምነት መከተል በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል እንደሆነ የሚናገር አዋጅ አወጣ። ይህም ቢሆን የሰይጣን ዘር ክፍል ጠላትነቱን የገለጸበት ድርጊት ነው። ብዙም ሳይቆይ ግሪክ በሌላ የዓለም ኃያል መንግሥት ተተካ። ታዲያ የአውሬው ስድስተኛ ራስ የሚሆነው ማን ነው?
ሮም—‘የሚያስፈራውና የሚያስደነግጠው’ ስድስተኛው ራስ
17. ስድስተኛው ራስ በዘፍጥረት 3:15 የሚገኘው ትንቢት እንዲፈጸም ምን ጉልህ ሚና ተጫውቷል?
17 ዮሐንስ ስለ አውሬው ራእይ በተመለከተበት ወቅት የዓለም ኃያል መንግሥት የነበረው ሮም ነው። (ራእይ 17:10) የአውሬው ስድስተኛ ራስ በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት እንዲፈጸም ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ሰይጣን የሮም ባለሥልጣናትን በመጠቀም የዘሩን ‘ተረከዝ’ ስለቀጠቀጠ በሴቲቱ ዘር ላይ ጊዜያዊ ጉዳት አድርሶ ነበር። ሮማውያን ይህን ያደረጉት በመንግሥት ላይ ዓመፅ ያነሳሳል በሚል ኢየሱስን በሐሰት ክስ በመወንጀልና በመግደል ነው። (ማቴ. 27:26) ይሁን እንጂ ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት ሲያስነሳው በዘሩ ተረከዝ ላይ የነበረው ቁስል ወዲያውኑ ዳነ።
18. (ሀ) ይሖዋ የመረጠው አዲስ ብሔር የትኛው ነው? ለምንስ? (ለ) የእባቡ ዘር ለሴቲቱ ዘር ጠላትነቱን ማሳየቱን የቀጠለው እንዴት ነው?
18 የእስራኤል ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን በመቃወም ከሮም መንግሥት ጋር የተመሳጠሩ ሲሆን አብዛኛው ሕዝብም መሲሑን አልተቀበለውም። በመሆኑም ሥጋዊ እስራኤላውያን የይሖዋ ሕዝብ የመሆን መብታቸውን አጡ። (ማቴ. 23:38፤ ሥራ 2:22, 23) ይሖዋም በእነሱ ምትክ አዲስ ብሔር ይኸውም ‘የአምላክ እስራኤልን’ መረጠ። (ገላ. 3:26-29፤ 6:16) ይህ ብሔር ከአይሁድና ከአሕዛብ የተውጣጡ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያቀፈ ጉባኤ ነው። (ኤፌ. 2:11-18) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም ቢሆን የእባቡ ዘር ለሴቲቱ ዘር ጠላትነት ማሳየቱን ቀጥሏል። የሮም መንግሥት በተለያየ ጊዜ የሴቲቱ ዘር ሁለተኛ ክፍል የሆነውን የክርስቲያን ጉባኤ ለማጥፋት ሙከራ አድርጓል።c
19. (ሀ) ዳንኤል ስድስተኛውን የዓለም ኃያል መንግሥት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ የትኞቹን ጉዳዮች እንመረምራለን?
19 ዳንኤል በፈታው የናቡከደነፆር ሕልም ላይ ሮም በብረት ቅልጥሞች ተመስሎ ነበር። (ዳን. 2:33) እንዲያውም ዳንኤል የተመለከተው ሌላ ራእይ የሮም መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ከሮም የሚወጣውን ቀጣዩን የዓለም ኃያል መንግሥትንም ጥሩ አድርጎ ገልጾታል። (ዳንኤል 7:7, 8ን አንብብ።) ለበርካታ መቶ ዓመታት ሮም ለጠላቶቹ “የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ በጣም ኀይለኛ” አውሬ ሆኖ ነበር። ይሁንና ትንቢቱ በመቀጠል ከሮም መንግሥት “ዐሥር ቀንዶች” እንደሚወጡ እንዲሁም ከእነዚህ ቀንዶች መካከል ሌላ ትንሽ ቀንድ እንደሚያድግ ብሎም ይህ ቀንድ ጎልቶ እንደሚወጣ ይገልጻል። እነዚህ አሥር ቀንዶች ምን ይወክላሉ? ትንሹስ ቀንድ ማን ነው? ይህ ትንሽ ቀንድ ናቡከደነፆር በሕልም ከተመለከተው ግዙፍ ምስል ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? በገጽ 14 ላይ የሚገኘው ርዕስ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ያብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ይህች ሴት በሰማይ ያሉ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችውንና በሚስት የተመሰለችውን የይሖዋን ድርጅት ትወክላለች።—ኢሳ. 54:1፤ ገላ. 4:26፤ ራእይ 12:1, 2
b የባቢሎን መንግሥት በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ በምስሉ ራስ፣ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ደግሞ በአውሬው ሦስተኛ ራስ ተመስሏል። ከገጽ 12-13 ላይ የሚገኘውን ሥዕላዊ መግለጫ ተመልከት።
c ሮማውያን በ70 ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን ያጠፉ ቢሆንም ይህ ጥፋት በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ አይደለም። በዚያን ጊዜ ሥጋዊ እስራኤላውያን የአምላክ የተመረጠ ሕዝብ መሆናቸው ቀርቶ ነበር።