ሰማያዊ ዜግነት ያላቸው ክርስቲያን ምሥክሮች
“እኛ ግን የመንግሥተ ሰማይ ዜጎች ነን።”—ፊልጵስዩስ 3:20 የ1980 ትርጉም
1. ይሖዋ አንዳንድ ሰዎችን በተመለከተ ምን አስደናቂ ዓላማ አለው?
ሰብዓዊ ፍጡራን ሆነው የተወለዱ ሰዎች በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው በመላእክት ላይ እንኳ ሳይቀር ይገዛሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:2, 3፤ ራእይ 20:6) ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ እውነት ነው! ሆኖም ይህ የይሖዋ ዓላማ ስለሆነ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይፈጽመዋል። ፈጣሪያችን እንዲህ ያለ ነገር የሚያደርገው ለምንድን ነው? ስለዚህ ጉዳይ ማወቅ በአሁኑ ጊዜ ያለ አንድ ክርስቲያንን ሊነካው የሚገባው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች እንዴት መልስ እንደሚሰጥ እንመልከት።
2. አጥማቂው ዮሐንስ ኢየሱስ ምን አዲስ ነገር እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር? ይህ አዲስ ነገር ከምን ነገር ጋር ግንኙነት ነበረው?
2 አጥማቂው ዮሐንስ ለኢየሱስ መንገዱን ሲጠርግ ኢየሱስ አንድ አዲስ ነገር እንደሚያደርግ አስታውቋል። ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “[ዮሐንስ] ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል። እኔ በውኃ አጠመቅኋችሁ እርሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ያጠምቃችኋል እያለ ይሰብክ ነበር።” (ማርቆስ 1:7, 8) ከዚያ ጊዜ በፊት ማንም ሰው በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቆ አያውቅም። ይህ መንፈስ ቅዱስን የሚመለከት አዲስ ዝግጅት ነበር፤ ይሖዋ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሰዎችን ለሰማያዊ አገዛዝ ለማዘጋጀት ካለው ዓላማ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ነበር።
‘ዳግም መወለድ’
3. ኢየሱስ መንግሥተ ሰማያትን በተመለከተ ለኒቆዲሞስ የገለጸለት አዳዲስ ነገሮች ምንድን ናቸው?
3 ኢየሱስ ከአንድ ታዋቂ ፈሪሳዊ ጋር በምሥጢር ባደረገው ውይይት ላይ ስለዚህ መለኮታዊ ዓላማ ተጨማሪ ነገር ገልጧል። ፊሪሳዊው ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሲመጣ ኢየሱስ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” አለው። (ዮሐንስ 3:3) ኒቆዲሞስ፣ ፈሪሳዊ እንደመሆኑ መጠን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ሳያጠና ስለማይቀር ስለ አምላክ መንግሥት ታላቅ እውነት አንድ የሚያውቀው ነገር ይኖራል። የዳንኤል መጽሐፍ ይህ መንግሥት ‘የሰው ልጅ ለሚመስል’ እና “ለልዑል ቅዱሳን ሕዝብ” እንደሚሰጥ ተንብዮአል። (ዳንኤል 7:13, 14, 27) ይህ መንግሥት ሌሎች መንግሥታትን በሙሉ ‘ካጠፋቸው’ በኋላ ለዘላለም ይቆማል። (ዳንኤል 2:44) ኒቆዲሞስ እነዚህ ትንቢቶች በአይሁድ ብሔር ላይ እንደሚፈጸሙ አስቦ ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ አንድ ሰው ይህን መንግሥት ለማየት ከፈለገ እንደገና መወለድ እንዳለበት ተናግሯል። ኒቆዲሞስ ነገሩ ስላልገባው ኢየሱስ በመቀጠል “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” አለው።—ዮሐንስ 3:5
4. ከመንፈስ ቅዱስ የተወለዱ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና የሚለወጠው እንዴት ነው?
4 አጥማቂው ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ስለሚደረግ ጥምቀት ተናግሯል። አሁን ደግሞ ኢየሱስ አንድ ግለሰብ ወደ አምላክ መንግሥት ለመግባት ከፈለገ ከመንፈስ ቅዱስ መወለድ እንዳለበት ተናገረ። በዚህ ልዩ ልደት አማካኝነት ፍጹማን ያልሆኑ ወንዶችና ሴቶች ከይሖዋ አምላክ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና ይፈጥራሉ። ልጆቹ ይሆናሉ። “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” የሚል እናነባለን።—ዮሐንስ 1:12, 13፤ ሮሜ 8:15
የአምላክ ልጆች
5. ታማኝ ደቀ መዛሙርት ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ የተጠመቁት መቼ ነበር? በዚሁ ወቅት ከዚህ ጋር ግንኙነት ያላቸው ምን የመንፈስ ቅዱስ አሠራሮች ተከሰቱ?
5 ኢየሱስ ከኒቆዲሞስ ጋር ከመነጋገሩ በፊት መንፈስ ቅዱስ ወርዶበት በአምላክ መንግሥት ውስጥ ወደፊት ለሚያገኘው ንግሥና ተቀብቶ ነበር፤ በተጨማሪም አምላክ በይፋ እንደ ልጁ አድርጎ እንደተቀበለው አሳውቆ ነበር። (ማቴዎስ 3:16, 17) በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ይሖዋ ተጨማሪ መንፈሳዊ ልጆችን ወልዷል። በኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኝ አንድ ሰገነት ላይ የተሰበሰቡ ታማኝ ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ተጠመቁ። በዚሁ ወቅት የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ ከመንፈስ ቅዱስ ተወለዱ። (ሥራ 2:2–4, 38፤ ሮሜ 8:15) ከዚህም በላይ ወደፊት የአምላክ መንግሥት ወራሾች እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ተቀቡ፤ ለሰማያዊ ተስፋቸው እርግጠኛነት ምልክት እንዲሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ታተሙ።—2 ቆሮንቶስ 1:21, 22
6. ይሖዋ ሰማያዊውን መንግሥት በተመለከተ ያለው ዓላማ ምንድን ነው? ሰዎች በዚህ መንግሥት ውስጥ መካፈላቸው ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?
6 እነዚህ ወደ መንግሥቱ ለመግባት በአምላክ የተመረጡ የመጀመሪያዎቹ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ነበሩ። ይህም ሞተው ከተነሡ በኋላ የሰማያዊው መንግሥት ድርጅት ክፍል ሆነው በሰዎችና በመላእክት ላይ ይገዛሉ ማለት ነው። ይሖዋ በዚህ መንግሥት አማካኝነት በፍጥረታት ሁሉ ፊት ታላቅ ስሙ እንዲቀደስና የሉዓላዊነቱ ትክክለኛነት እንዲረጋገጥ ዓላማ አለው። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ ዮሐንስ 12:28) ሰዎች በዚህ መንግሥት ውስጥ መካፈላቸው ምንኛ ተገቢ ነው! ሰይጣን ለመጀመሪያ ጊዜ በኤደን የአትክልት ስፍራ የይሖዋን ሉዓላዊነት ሲገዳደር በሰዎች ተጠቅሟል፤ አሁን ደግሞ ይሖዋ ይህን ጥያቄ በመመለሱ ተግባር ሰዎች እንዲሳተፉ ዓላማ አድርጓል። (ዘፍጥረት 3:1–6፤ ዮሐንስ 8:44) ሐዋርያው ጴጥሮስ በዚህ መንግሥት ውስጥ እንዲገዙ ለተመረጡት ሰዎች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፣ እድፈትም ለሌለበት፣ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህ ርስት በመጨረሻ ዘመን ይገለጥ ዘንድ . . . ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።”—1 ጴጥሮስ 1:3, 4
7. በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁ ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ምን ልዩ ዝምድና ይኖራቸዋል?
7 እነዚህ የተመረጡ ክርስቲያኖች የአምላክ ልጆች እንደመሆናቸው መጠን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች ሆነዋል። (ሮሜ 8:16, 17፤ 9:4, 26፤ ዕብራውያን 2:13) ኢየሱስ ለአብርሃም ቃል የተገባለት ዘር ስለሆነ እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች እምነት ላላቸው ሰዎች በረከት የሚያመጣው የዚያ ዘር ክፍል የሆኑ ተባባሪ ወይም ሁለተኛ ደረጃ ያላቸው ግለሰቦች ናቸው። (ዘፍጥረት 22:17, 18፤ ገላትያ 3:16, 26, 29) ይህ ዘር የሚያመጣው በረከት ምንድን ነው? ከኃጢአት የመቤዠት፣ ከአምላክ ጋር የመታረቅና ለአሁንና ለዘላለም እሱን የማገልገል አጋጣሚ ማግኘት ነው። (ማቴዎስ 4:23፤ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16, 36፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በምድር ላይ ያሉት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ወንድማቸው ለኢየሱስ ክርስቶስና ለአባታቸው ለይሖዋ አምላክ በመመሥከር ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደዚህ በረከት ይመሯቸዋል።—ሥራ 1:8፤ ዕብራውያን 13:15
8. በመንፈስ ቅዱስ የተወለዱት የአምላክ ልጆች “መገለጥ” ምንድን ነው?
8 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እነዚህ በመንፈስ የተወለዱ የአምላክ ልጆች “መገለጥ” ይናገራል። (ሮሜ 8:19) ከኢየሱስ ጋር በመንግሥቱ ተባባሪ ነገሥታት በመሆን የሰይጣንን ዓለም የነገሮች ሥርዓት በማጥፋቱ እርምጃ ይካፈላሉ። ከዚያ በኋላ ለአንድ ሺ ዓመት ለሰው ልጆች የቤዛዊ መሥዋዕቱን ጥቅሞች በማስተላለፍ የሰውን ዘር አዳም ወዳጣው ፍጽምና ለማድረስ እገዛ ያደርጋሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:8–10፤ ራእይ 2:26, 27፤ 20:6፤ 22:1, 2) የአምላክ ልጆች መገለጥ ይህን ሁሉ ያካትታል። ይህ አማኝ የሆነው ሰብዓዊ ፍጥረት በጉጉት የሚጠብቀው ነገር ነው።
9. መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም አቀፉን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን የሚጠቅሰው ምን ብሎ ነው?
9 በመላው ዓለም የሚገኘው የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድን ‘በሰማያት የተጻፈ የበኩራት ማኅበር’ ነው። (ዕብራውያን 12:23) ቅቡዓን ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በመጠቀም ረገድ የመጀመሪያዎቹ ናቸው። በተጨማሪም “የክርስቶስ አካል” ናቸው፤ ይህም ከኢየሱስ ጋርም ሆነ እርስ በርሳቸው ያላቸውን የተቀራረበ ዝምድና ያሳያል። (1 ቆሮንቶስ 12:27) ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፣ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል።”—1 ቆሮንቶስ 12:12, 13፤ ሮሜ 12:5፤ አፌሶን 1:22, 23፤ 3:6
‘የአምላክ እስራኤል’
10, 11. በመጀመሪያው መቶ ዘመን አዲስ እስራኤል ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይህ አዲስ እስራኤል እነማንን ያቅፋል?
10 የእስራኤል ሕዝብ፣ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ ሆኖ ከመምጣቱ በፊት ለ1,500 ዓመታት ያህል የአምላክ ልዩ ሕዝብ ነበር። ሕዝቡ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያዎች ቢሰጡትም በአጠቃላይ ሲታይ ታማኝ ሳይሆን ቀረ። ኢየሱስ ሲመጣ ሕዝቡ አልተቀበለውም። (ዮሐንስ 1:11) ስለዚህ ኢየሱስ ለአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች “የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 21:43) ይህንን ‘[የመንግሥቱን] ፍሬ የሚያፈራ ሕዝብ’ ለይቶ ማወቅ ለመዳን እጅግ አስፈላጊ ነው።
11 አዲሱ ሕዝብ በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት የተወለደው የቅቡዓን ክርስቲያን ጉባኤ ነው። የዚህ ሕዝብ የመጀመሪያ አባላት ኢየሱስን እንደ ሰማያዊ ንጉሣቸው አድርገው የተቀበሉት አይሁዳዊ ደቀ መዛሙርቱ ነበሩ። (ሥራ 2:5, 32–36) ሆኖም የአምላክ አዲስ ሕዝብ አባላት የሆኑት አይሁዳዊ ዝርያ ስለነበራቸው ሳይሆን በኢየሱስ ስላመኑ ነበር። ስለዚህ ይህ አዲስ እስራኤል ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ሕዝብ ነው። አብዛኞቹ አይሁዶች ኢየሱስን ለመቀበል እምቢተኛ ሲሆኑ የአዲሱ ሕዝብ አባል የመሆን ግብዣ ለሳምራውያን ከዚያም ለአሕዛብ ቀረበ። አዲሱ ሕዝብ ‘የአምላክ እስራኤል’ ተባለ።—ገላትያ 6:16
12, 13. አዲሱ እስራኤል ከአይሁድ እምነት የተገነጠለ ቡድን እንዳልሆነ ግልጽ የሆነው እንዴት ነው?
12 በጥንቷ እስራኤል አይሁዳውያን ያልሆኑ ሰዎች ወደ አይሁድ እምነት ሲለወጡ ለሙሴ ሕግ መገዛት ነበረባቸው፤ ወንዶች በመገረዝ ለሙሴ ሕግ እንደሚገዙ ማሳየት ነበረባቸው። (ዘጸአት 12:48, 49) አንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች ይህ ሕግ አይሁዳዊ ባልሆኑት የአምላክ እስራኤል ላይ ይሠራል ብለው አስበው ነበር። ሆኖም ይሖዋ አንድ የተለየ ነገር በአእምሮው ይዞ ነበር። መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስን ከአሕዛብ ወገን ወደ ሆነው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት እንዲሄድ መራው። ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ለሐዋርያው ጴጥሮስ ስብከት አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጡ ቀደም ሲል በውኃ ያልተጠመቁ ቢሆኑም እንኳ መንፈስ ቅዱስ ተቀበሉ። ይህም ይሖዋ እነዚህን አሕዛብ የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ሳይጠይቅ የአምላክ እስራኤል አባላት እንዲሆኑ እንደመረጣቸው በግልጽ ጠቆመ።—ሥራ 10:21–48
13 ጥቂት አማኞች ይህን ሁኔታ መቀበል አቃታቸው፤ ብዙም ሳይቆይ ጉዳዩ በኢየሩሳሌም ባሉ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ፊት ለውይይት መቅረብ ነበረበት። ይህ ሥልጣን ያለው አካል መንፈስ ቅዱስ አይሁድ ባልሆኑ ክርስቲያኖች ላይ እንዴት እንደሠራ የሚገልጸውን ዝርዝር መግለጫ አዳመጠ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተደረገው ምርምር ይህ የሆነው በመንፈስ አነሣሽነት የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም እንደሆነ ጠቆመ። (ኢሳይያስ 55:5፤ አሞጽ 9:11, 12) አይሁዳውያን ያልሆኑ ክርስቲያኖች ለሙሴ ሕግ የመገዛት ግዴታ የለባቸውም የሚል ትክክለኛ ውሳኔ ላይ ተደረሰ። (ሥራ 15:1, 6–29) ስለዚህ መንፈሳዊው እስራኤል ከአይሁድ እምነት የተገነጠለ ቡድን ሳይሆን በእርግጥም አዲስ ሕዝብ ነበር።
14. ያዕቆብ የክርስቲያን ጉባኤን “ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች” ብሎ መጥራቱ ምን ያመለክታል?
14 ከዚህ ጋር በሚስማማ መንገድ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች መልእክቱን ሲጽፍ “ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች” በሚሉት መክፈቻ ቃላት ተጠቅሞ ነበር። (ያዕቆብ 1:1፤ ራእይ 7:3–8) እርግጥ የአዲሱ እስራኤል ዜጎች በተወሰኑ ነገዶች አልተደለደሉም። በሥጋዊ እስራኤል እንደነበረው ዓይነት የተለያዩ የ12 ነገዶች ክፍፍል የለም። ሆኖም ያዕቆብ በመንፈስ አነሣሽነት የተናገረው ቃል በይሖዋ አመለካከት የአምላክ እስራኤል 12ቱን የእስራኤል ነገዶች ሙሉ በሙሉ እንደተካ ይጠቁማል። አንድ ሥጋዊ እስራኤላዊ የዚህ አዲስ ሕዝብ ክፍል ከሆነ የይሁዳና የሌዊ ነገድ ቢሆንም እንኳ ሥጋዊ ዝርያው አስፈላጊነት የለውም።—ገላትያ 3:28፤ ፊልጵስዩስ 3:5, 6
አዲስ ቃል ኪዳን
15, 16. (ሀ) ይሖዋ አይሁዳዊ ያልሆኑ የአምላክ እስራኤል አባላትን የሚመለከታቸው እንዴት ነው? (ለ) አዲሱ እስራኤል የተቋቋመው በምን ሕጋዊ መሠረት ነው?
15 በይሖዋ አመለካከት የዚህ አዲስ ሕዝብ እስራኤላውያን ያልሆኑ አባላት የተሟላ ቦታ ያላቸው መንፈሳዊ አይሁዳውያን ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ሁኔታው እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “በግልጥ አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ አይደለምና፣ በግልጥ በሥጋ የሚደረግ መገረዝም መገረዝ አይደለምና፤ ዳሩ ግን በስውር አይሁዳዊ የሆነ አይሁዳዊ ነው፤ መገረዝም በመንፈስ የሚደረግ የልብ መገረዝ ነው እንጂ በመጽሐፍ አይደለም፤ የእርሱ ምስጋና ከእግዚአብሔር ነው እንጂ ከሰው አይደለም።” (ሮሜ 2:28, 29) ብዙ አሕዛብ የአምላክ እስራኤል ክፍል እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለዋል፤ ይህም ሁኔታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ሆሴዕ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምሕረትም የሌላትን እምራለሁ፣ ሕዝቤም ያልሆነውን፦ አንተ ሕዝቤ ነህ እለዋለሁ፤ እርሱም፦ አንተ አምላኬ ነህ ይለኛል።”—ሆሴዕ 2:25፤ ሮሜ 11:25, 26
16 መንፈሳዊ እስራኤላውያን በሙሴ ሕግ ቃል ኪዳን ሥር ካልሆኑ የአዲሱ ሕዝብ ክፍል የሆኑት በምን መሠረት ነው? ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ከዚህ መንፈሳዊ ሕዝብ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን አድርጓል። (ዕብራውያን 9:15) ኢየሱስ በኒሳን 14፣ 33 እዘአ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ሲያስጀምር ቂጣና ወይን ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት ካዞረላቸው በኋላ ወይኑ ‘በደሙ የሚደረገውን ቃል ኪዳን’ እንደሚያመለክት ተናገረ። (ማቴዎስ 26:28 አዓት ፤ ኤርምያስ 31:31–34) በሉቃስ ዘገባ ላይ እንደተተረከው ኢየሱስ በጽዋው ውስጥ ያለው ወይን ‘አዲሱን ቃል ኪዳን’ ያመለክታል ብሏል። (ሉቃስ 22:20) ኢየሱስ በተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ መሠረት በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ሲወርድና የአምላክ እስራኤል ሲወለድ መንግሥቱ ከሥጋዊ እስራኤላውያን ተወሰደና ለአዲሱ መንፈሳዊ ሕዝብ ተሰጠ። በዚህ ወቅት በሥጋዊ እስራኤል ምትክ ምሥክሮቹን ያቀፈው ይህ አዲስ ሕዝብ የይሖዋ አገልጋይ ሆነ።—ኢሳይያስ 43:10, 11
“አዲሲቱ ኢየሩሳሌም”
17, 18. በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚጠብቃቸውን ክብር በተመለከተ ምን መግለጫዎች ተሰጥተዋል?
17 ለሰማያዊ ጥሪ የታደሉት እንዴት ያለ ክብር ይጠብቃቸዋል! በተጨማሪም እነሱ የሚጠብቋቸውን አስደናቂ ነገሮች ማወቅ ምንኛ ያስደስታል! የራእይ መጽሐፍ ስለሚያገኙት ሰማያዊ ውርሻ አስደናቂ ፍንጭ ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል፣ በራእይ 4:4 ላይ “በዙፋኑ [በይሖዋ ዙፋን] ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፣ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር” የሚል እናነባለን። እነዚህ 24 ሽማግሌዎች ከሞት የተነሡና በአሁኑ ወቅት ይሖዋ ቃል የገባላቸውን ሰማያዊ ስፍራ የያዙ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። አክሊላቸውና ዙፋኖቻቸው ያሳዩትን የታማኝነት አቋም ያስታውሰናል። በተጨማሪም በይሖዋ ዙፋን ዙሪያ ለማገልገል ያገኙትን በጣም ከፍተኛ የሆነ መብት አስብ!
18 በራእይ 14:1 ላይ እነሱን በተመለከተ ሌላ መግለጫ እንመለከታለን። ጥቅሱ “አየሁም፣ እነሆም፣ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፣ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ” ይላል። እዚህ ላይ የእነዚህን ቅቡዓን ቁጥር 144,000 እንደሆነ እንመለከታለን። በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ንጉሥ ከ“በጉ” ከኢየሱስ ጋር በመቆማቸው የንግሥና ቦታቸው ተለይቶ ተገልጿል። በተጨማሪም የቆሙት በሰማያዊቷ ጽዮን ነው። ምድራዊቷ የጽዮን ተራራ የምትገኘው የእስራኤል መንግሥታዊ ከተማ በነበረችው በኢየሩሳሌም ውስጥ ነበር። ሰማያዊቷ የጽዮን ተራራ ኢየሱስና ተባባሪ ወራሾቹ ያገኙትን ከፍተኛ ደረጃ ታመለክታለች፤ እነሱም በአንድነት ሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ይሆናሉ።—2 ዜና መዋዕል 5:2፤ መዝሙር 2:6
19, 20. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የየትኛው ሰማያዊ ድርጅት አካል ናቸው? (ለ) ይሖዋ ወደፊት ሰማያዊ ዜግነት የሚያገኙትን ሰዎች የመረጠው በየትኛው ጊዜ ውስጥ ነው?
19 በተጨማሪም ከዚህ ጋር በመስማማት ክብራማ ሰማያዊ ቦታቸውን የያዙት ቅቡዓን “አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ተብለው ተጠርተዋል። (ራእይ 21:2) ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም “የታላቁ ንጉሥ ከተማ” እና የእሱ ቤተ መቅደስ የሚገኝባት ቦታ ነበረች። (ማቴዎስ 5:35) ሰማያዊቷ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ታላቁ ሉዓላዊ ጌታ ይሖዋና እሱ የሾመው ንጉሥ ኢየሱስ አሁን የሚገዙባትና የሰው ልጆችን ለመፈወስ ከይሖዋ ዙፋን የተትረፈረፉ በረከቶች በሚፈስሱበት ጊዜ ክህነታዊ አገልግሎት የሚሰጥባት መንግሥታዊ ድርጅት ናት። (ራእይ 21:10, 11፤ 22:1–5) በሌላ ራእይ ላይ ዮሐንስ ከሞት የተነሡ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የበጉ ሚስት’ ተብለው ሲጠሩ ሰምቷል። እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር ያላቸውን ቅርርብና ለእሱ በፈቃደኝነት መገዛታቸውን የሚያሳይ እንዴት ያለ አስደሳች የሆነ ሥዕላዊ መግለጫ ነው! የመጨረሻ አባላቸው ሰማያዊ ሽልማቱን ሲቀበል በሰማይ የሚኖረውን ደስታ ገምት። በዚያ ወቅት “የበጉ ሰርግ” ሊደረግ ይችላል! በዚያን ጊዜ ይህ የሰማይ መንግሥታዊ ድርጅት የተሟላ ይሆናል።—ራእይ 19:6–8
20 አዎን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “እኛ ግን የመንግሥተ ሰማይ ዜጎች ነን” ያላቸው አስደናቂ በረከቶች ይጠብቋቸዋል። (ፊልጵስዩስ 3:20 የ1980 ትርጉም) ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ያህል ይሖዋ መንፈሳዊ ልጆቹን ሲመርጥና እነሱን ለሰማያዊ ውርሻ ሲያዘጋጅ ቆይቷል። ማስረጃው እንደሚያሳየው ይህ የመምረጥና የማዘጋጀት ተግባር ሊጠናቀቅ ተቃርቧል። ይሁን እንጂ በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ በተመዘገበው ለዮሐንስ በተገለጠለት ራእይ መሠረት ከዚያ በኋላ ሌላ ነገር ይፈጸማል። ስለዚህ አሁን ሌላ የክርስቲያን ቡድን ትኩረታችንን ይስባል፤ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለዚህ ጉዳይ እንመለከታለን።
ታስታውሳለህን?
◻ መንፈስ ቅዱስ ሰማያዊ ውርሻ ባላቸው ላይ በምን የተለያዩ መንገዶች ይሠራል?
◻ ቅቡዓን ከይሖዋ ጋር ምን የተቀራረበ ዝምድና አላቸው? ከኢየሱስ ጋርስ?
◻ የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የተገለጸው እንዴት ነው?
◻ የአምላክ እስራኤል የተቋቋመው በምን ሕጋዊ መሠረት ነው?
◻ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ሰማያዊ መብቶች ይጠብቋቸዋል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ይሖዋ ወደፊት በሰማያዊው መንግሥት የሚገዙትን ወደ ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት ያህል ሲመርጥ ቆይቷል